Thursday, February 27, 2014

አቶ አለማየሁ አቶምሳ ከክልሉ ፕሬዚዳንትነትና ከኦሀዴድ ሊቀመንበርነት ለመልቀቅ ደብዳቤ እንዳሰገቡ ተደርጎ በክልሉ መንግስት የተሰጠው መግለጫ ሃሰት ነው ተባለ

የካቲት ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኦህዴድ ከፍተኛ አመራር በክልሉ ፕሬዚዳንት በአቶ አለማየሁ አቶምሳ ቢሮ ውስጥ የተፈጠረውን ጉዳይ በዝርዝር ለኢሳት አስረድተዋል።
አቶ አለማየሁ ከኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ጋር የካቲት 10 ቀን፣ 2006 ዓም በክልሉ ውስጥ ስለሚታየው የመልካም አስተዳደር መበላሸትና የህዝብ ሮሮ፣ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ በመጣው ሙስና እንዲሁም በድርጅቱ ጎጠኛ አሰራር ዙሪያ እርሳቸውን ከሚቃወሙዋቸው ሌሎች የኦህዴድ ባለስልጣናት ጋር  ከጧት ጀምሮ  እስከ ምሽቱ 3 ሰአት ድረስ ግምገማ ሲያደርጉ ውለዋል፡፡
ብዙዎቹ የድርጅቱ አባላትና አባ ዱላ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ከፍተኛ ቦታዎችን ይዘው የነበሩት ባለስልጣናት በአቶ አለማየሁ ግምገማ ባለመደሰት ከአቶ አለማየሁ ጋር ውዝግብ ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ አቶ አለማየሁም ህመማቸው ከሚፈቅደው በላይ ድምጻቸውን እያወጡ ከአንዳንዶች ጋር ሲጨቃጨቁ ውለዋል።
በማእከላዊ ከሚቴ አባላት መካከል የተነሳው ውዝግብ እየከረረ ሄዶ አቶ አለማየሁ ስብሰባውን ምሽት ላይ ለመበተን የተገደዱ ሲሆን፣ ስብሰባው እንደተጠናቀቀም ሁሉም የምክር ቤት አባላት ቢሮውን በፍጥነት ለቀው ሲወጡ የኦህዴድ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊና የህወሃት የኦህዴድ ወኪል ተደርገው የሚቆጠሩት ወ/ሮ አስቴር ማሞ  ብቻ በጽህፈት ቤታቸው ቀርተዋል።
ወ/ሮ አስቴር አቶ አለማየሁን ” አትወጣም እንዴ?” ብለው ሲጠይቋቸው አቶ አለማየሁ ምንም ምላሽ ባለመስጠታቸው፣  ወ/ሮ አስቴር በድንጋጤ፣ አምቡላንስ በማስጠራት ገርጂ ወደሚገኝ አንድ ሆስፒታል እንዲላኩ አድርገዋል። ሆስፒታሉም በአስቸኳይ ወደ ውጭ መላክ እንዳለባቸው በመግለጹ፣ አቶ አለማየሁ ወዲያውኑ ወደ ውጭ ለህክምና ተልከዋል።
የአቶ አለማየሁ ህመም ለህይወታቸው አስጊ መሆኑ እንደታወቀ የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ  በማግስቱ ተሰብስቦ አቶ አለማየሁ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው እንደለቀቁ አድርጎ ደብዳቤ በመጻፍ፣ ለመንግስት የመገናኛ ብዙሀን በትኗል።
አቶ አለማየሁ በከፍተኛ ህመም መሰቃየታቸው እውነት ቢሆንም፣ ከስልጣን ለመልቀቅ ያስገቡት ደብዳቤ ግን የለም።
ቀድሞውንም  በግለሰቡ አመራር ያልተደሰቱት ሰዎች ቦታውን ለመያዝ ከፍተኛ ሩጫ ካደረጉ በሁዋላ፣ የአባዱላ ደጋፊ እንደሆኑ የሚታመኑት አቶ ሙክታር ከድር ስልጣኑን ተረክበዋል።
አቶ አለማየሁ ስልጣን በያዙ ማግስት በምግብ መመረዛቸውን አንዳንድ የኦህዴድ ባለስልጣናትን በመጥቀስ ኢሳት በወቅቱ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣  የእርሳቸው የግል ጠባቂ የሆነው ግለሰብም፣ እርሳቸው ከታመሙበት ቀን ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በተመሳሳይ ህመም እየተሰቃየ እንደሚገኝና ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ህመሙ ጸንቶበት ገርጂ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ እየታከመ ይገኛል።
አቶ አለማየሁ ስልጣን በያዙ ማግስት በክልሉ የሚታየውን ሙስና አጻዳለሁ በሚል አዲስ እንቅስቃሴ ቢጀምሩም ረጅም ርቀት ሳይጓዙ ለበሽታ ተዳርገዋል። እርሳቸው ከታመሙበት ጊዜ ጀምሮ ክልሉን ምክትሉ አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ ሲመሩት ቆይተዋል።
የአቶ ሙክታር ከድር የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆኖ መመረጥ ለህወሃት ትልቅ እፎይታ መሆኑን የውስጥ ሰዎች ይናገራሉ።
አቶ አለማየሁ ተሽሎአቸው ወደ አገር የሚመለሱ ከሆነ፣ በአዲሱ ሹም ሽር ግራ ሳይጋቡ እንደማይቀሩ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።

Wednesday, February 26, 2014

በኦሮምያ የክልል ፐሬዚዳንት ለመሾም የሚደረገው ሽኩቻ ቀጥሎአል

የካቲት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የክልሉ ምክር ቤት ሳያቀውቀው በስራ አስፈጻሚው እውቅና ከስልጣን የተነሱትን አቶ አለማየሁ አቶምሳን ማን ይተካቸው የሚለው አጀንዳ የአቶ አባ ዱላ ገመዳንና የአቶ አለማየሁ አቶምሳን ቡድኖች እያወዛገበ ነው። አቶ አለማየሁ አቶምሳ ወደ ስልጣን እንደመጡ የአቶ አባዱላን ቡድኖች በመምታት ከስልጣን ውጭ ያደረጉዋቸው ሲሆን፣ አባ ዱላ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ተመልሰው የእርሳቸውን ሰዎች ለማሾም እየሰሩ ነው።
እስካሁን ድረስ የክልሉ ምክር ቤት ስበሰባ አለመጠራቱም ታውቋል። አንዳንዶች እንደሚናገሩት ህወሃት ለዘብተኛ የሆነ መሪ እንዲመጣ ፍላጎት በሚያሳየው ፍላጎት የሁለቱም ሰዎች ደጋፊዎች ላይሾሙ ይችላሉ ፡፡ አቶ አለማየሁ የመሰረቱት አስተዳደር በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙትን መለስተኛ ከተሞችን ለመስተዳድሩ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የ10 በ90 ፕሮጀክት እንዲደናቀፍ ማድረጋቸውን በማንሳት  እርሳቸውን የሚተካው ሰው ለዘብተኛ ሆኖ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ተግባብቶ የሚሰራ እንዲሆን እንደሚፈለግ እኝሁ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ሰዎች ይናገራሉ።
በአባ ዱላ ዙሪያ የተሰባሰቡ ሰዎች ከሙስና ጋር በተያያዘ ድርጅቱን አደጋ ውስጥ በመጣላቸው በፌደራሉ መንግስት በዙም አይደገፉም። ከሁለቱም ቡድኖች ወጣ ያለ አዲስ ሰው ለማገኘት ኦህዴድ ፈተና እንደሆነበትና ምናልባትም ሽኩቻው በዚህ ከቀጠለ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ስልጣኑን ተረክበው ሊቀጥሉ ይችላሉ የሚለውን ግምት እያጠናከረው መምጣቱን ይገልጻሉ።

ብአዴን ባህርዳር ላይ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ እንዳይሳካ ለማድረግ የቀየሰው ስትራቴጂ ሳይሳካ መቅረቱን የውስጥ ምንጮች ገልጹ

የካቲት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አቶ አለምነው መኮንን የአማራን ህዝብ መዝለፋቸውን ተከትሎ አንድነት ፓርቲና መኢአድ የጠሩተን ሰልፍ ለማደናቀፍና ህዝብ በሰልፉ ላይ እንዳይገኝ የተቀየሰው ስትራቴጂ ሳይሳካ መቅረቱን የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ለኢሳት ገልጸዋል።
በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የሚገኘው ብአዴን ሰላማዊ ሰልፉን ለማጨናገፍ ከተጠቀመባቸው ዘዴዎች አንዱ በአንጻራዊነት የተሻለ ተሰሚነት ያላቸውን ወደ አዲስ አበባ ከመጡት የክልሉን ተወላጅ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮችን መካከል መርጦ በመላክ ወጣቶችን እንዲያረጋጉና እንዲያሳምኑ ማድረግ ነበር። የተሻለ የፖለቲካ አፈጻጸም አላቸው የተባሉ በሲቪል ሰርቪስና በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚገኙ አመራሮች ወደ ባህርዳር ተንቀሳቅሰው ወጣቱን ለማረጋጋት ቢሞክሩም ሳይሳካ ቀርቷል።
የተለያዩ የፖሊስ ኮማንደሮችን ከአዲስ አበባ ወደ ከተማዋ በማስገባት የስነ ልቦና ጫና መፍጠር ይህ ካልተሳካም የፌደራልና የክልሉ ፖሊሶችን በማንቀሳቀስ ፍርሃት በመፍጠር ወጣቱ ወደ አደባባይ እንዳይወጣ የተቀየሰው ስትራቴጂ ውጤት አልባ ሆኗል።
በተቃውሞው ማግስት ብአዴን ነባር አመራሮችን በአስቸኳይ ወደ ባህርዳር በመጥራት ዝግ ስብሰባ እያካሄደ ነው። ንቅናቄው እስካሁን ድረስ በሰልፉ ዙሪያ ወይም በአቶ አለምነው ንግግር ላይ የአቋም መግለጫ አላወጣም።
በባህርዳር የተካሄደው ሰልፍ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩንም ዘጋቢያችን ገልጻለች። አንዳንድ የብአዴን አባላት ሳይቀሩ ህዝቡ ባሳየው ተሳትፎ ከሁሉም በላይ ስለነጻነቱ፣ ስለ ኢኮኖሚውና ፍትህ አንግቦ የተነሳው ተቃውሞ እንዳስደሰታቸው ለዘጋቢያችን ገልጸውላታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ አለምነው መኮንን የአቶ መለስ ዜናዊ ጭፍን አምላኪ ተደርገው እንደሚቆጠሩ ጓዶቻቸው ለኢሳት ተናግረዋል። አቶ አለምነው በባህርዳሩ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ብቸኛ የርእዮት አለም ሰው መለስ ዜናዊ እንደነበርና ሌላው ሁሉ ተከታይ መሆኑን መናገራቸው የአቶ መለስ ፍልስፍና አራማጅ መሆናቸውን እንደሚያሳይ ገልጸዋል። ” ቢቀዳ ቢጨለጥ አንድ የርእዮት አለም ሰው የነበረው መለስ ዜናዊ ነው” የሚሉት አቶ አለምነው፣ ሌላው ሁሉ ተከታይ” ነው በማለት የኢህአዴግን አባላት ሳይቀር ከላይ እስከታች ተከታዮች አድርገው ፈርጀዋቸዋል። ” ሱፍ ለብሶ በመሄድ” አይደለም ሲሉም በአገሪቱ ባሉ ምሁራንና በኢህአዴግ መሪዎች ላይ ሳይቀር ተሳልቀውባቸዋል።
ኢህአዴግ ከአቶ መለስ ሞት በሁዋላ አዳዲስ ሃሳቦች የሚያመነጭ የርእዮት አለም ሰው ሰው የለውም ማለት ነው ሲሉ በስብሰባው ላይ የተሳተፉ አንዳንድ የብአዴን አባላት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከ 6 ሚሊዮን የኢህአዴግ አባላት መካከል እንዴት አንድ ሰው እንኳ አዲስ ሃሳብ የማመንጨት ብቃት የሌለው ይጥፋ በማለት አባላቱ ጠይቀዋል።
አቶ አለምነው አማራውን በተመለከተ የተናገሩት አቶ መለስ በተደጋገሚ ሲጽፉትና ሲናገሩት የነበረውን ያሉት አንዳንድ አመራሮች፣ ብአዴን በአማራው ስም የተደራጀ የህወሃት ጉዳይ አስፈጻሚ ድርጅት ነው እየተባለ የሚነገረው እውነት በመሆኑ፣ ድርጅቱን ከህወሃት ፈልቅቆ ለማውጣት የውስጥ ትግል እየተካሄደ መሆኑንም አክለዋል።

Tuesday, February 18, 2014

የረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ የአውሮፕላን ጠለፋ የአለም መነጋገሪያ በመሆን ቀጥሎአል

የካቲት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 702 የሆነውን አውሮፕላን በመጥለፍ ጄኔቫ ስዊዘርላንድ ያሳረፈው ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ እስካሁን ድረስ የጠለፋውን መንስኤና ምክንያት በግልጽ የመናገር እድል ባለማግኘቱ የአለም የመገናኛ ብዙሃን የተለያዩ አስተያየቶችን እየሰጡ ነው።
አንዳንዶች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አስከፊ ጭቆናና ፓይለቱ አውሮፕላኑን እንዲጠልፍ እንዳነሳሳው ሲገልጹ ሌሎች ወገኖች ደግሞ ጥገኝት ለመጠየቅ ተብሎ ከተደረገ ስህተት ፈጽሟል ብለው ይተቻሉ።
ባህርዳር አካባቢ ተወልዶ ያደገው ሃይለመድህን አበራ በአንጻራዊ መልኩ ሀብታም ከሚባል ቤተሰብ መምጣቱን የሚናገሩት ፓይለቱንም ሆነ ቤተሰቦቹንም እናውቃለን የሚሉ የባህርዳርና የአካባቢው ሰዎች፣ ፓይለቱ በትምህርቱ እጅግ ጎበዝ የሚባልና ታታሪ ሰራተኛ እንደሆነ ይገልጻሉ።
አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ ሰው ሃይለመድህን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ስላለው ቢሮክራሲና ዘረኝነት ደጋግሞ ይናገር እንደነበር ገልጿል።
ታናሽ እህቱ እንደሆነች የምትገልጽ ትንሳኤ አበራ በበኩሉዋ ሃይለመድህን ” የሰዎችን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል አይደለም እንስሳትን ለመጉዳት የሚፈልግ ሰው አለመሆኑን፣  ከአገር ውጭ ወጥቶ ለመኖር ፍላጎት እንዳልነበረውም ገልጻለች።
በብሄራዊ መልቀቂያ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ትምህረቱን ያጠናቀቀው ሀይለመድህን የጀመረውን የ አርክቴክቸር ትምህርት ትቶ ወደ ፓይለትነት የገባው ለሙያው ካለው ፍቅር የተነሳ መሆኑንም ገልጻለች።
“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህይወቱ ደስታ የራቀው መሰለ” የምትለው እህቱ፣ ስለሁኔታው ሲጠየቅ ” ጠላቶች እንዳሉ እንደሚያምን ፣ ስልኩን እንደጠለፉት እንደሚያስብ፤ በላፕቶፑ ካሜራ ሳይቀር ያዩኛል ብሎ ስለሚሰጋ ካሜራውን ሳይሸፍን እንደማይከፍት እንዲሁም፤ ወጥቶ እስኪገባ ቤቱን ሲበረብሩ የቆዩ ስለሚመስለው ካሜራ ጠምዶ መሄድ ሁሉ እንደጀመረ ገልጻለች።”
” ባጠቃላይ በታላቅ የመንፈስ ጭንቀት እየተሰቃየ ነው”፣ የምትለው እህቱ፣  የሚያሳዝነው ደግሞ ይህንን ጉዳቱን ለኛ ለቤተሰቡንኳ አብራርቶ አለመናገሩ ነው ” ብላለች።
ሌሎች ጓደኞቹ በበኩላቸው ሃይለመድህን የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ የገባው አጎቱ ባለፈው ጥር ወር ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ከተገደሉ በሁዋላ ነው ይላሉ። አጎቱ ዶ/ር እምሩ ስዩም ባለፈው ጥር ወር ከስራ ሲወጡ ታክሲ ውስጥ ሞተው የተገኙ ሲሆን፣ ዶ/ሩን ማን እንደገደላቸው በውል ባይታወቅም፣ አንዳንድ ወገኖች ግን ግድያው ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ  በድረገጹ ላይ ባሰፈረው ሪፖርት የፕሮፌሰር  እምሩ  ስዩም ሞት አስገራሚ መሆኑን ገልጿል።
ሃይለመድህን ከአጎቱ ሞት በሁዋላ እርሱም በተመሳሳይ አደጋ ውስጥ እገኛለሁ ብሎ ሲሰጋ እንደነበር፣ በተለይም በአየር መንግዱ ውስጥ የተሰባሰቡት ካድሬዎች፣ ያሳድዱኛል ብሎ እንደሚያስብ ፓይለቱን ባለፈው ጥር ወር ላይ እንዳገኘው የሚገልጽ ወጣት ለኢሳት ተናግሮአል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ስልጣን ለቀቁ

የካቲት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኦህዴድ ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳ የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ ምከር ቤቱ እንዳሰናበታቸው የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል። አቶ አለማየሁ መታመማቸው ከተዘገበ የቆየ ቢሆንም እስካሁን ከስልጣን ሳይወርዱ ቆይተው አሁን ለምን ለማንሳት እንደተፈለገ ግልጽ አይደለም።
በአፋር በቅርቡ በሚካሄደው የምክር ቤት ስበሰባ ላይ ፕ/ት አሊ ሴሮ ከስልጣን ሊነሱ እንደሚችል ለኢሳት የደረሱ መረጃዎች አመልክተዋል። ምንም እንኳ ኢሳት ከመንግስት በኩል መረጃውን በማግኘት ለማረጋገጥ ባይችልም፣ ህወሀት በአሊ ሴሮ ምትክ ሌሎች ሰዎችን ለመሾም ማቀዱን የሚያሳዩ ፍንጮች ደርሰውታል።

የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ዘጋቢ አደጋ እንደደረሰበት ተዘገበ

የካቲት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጋዜጠኛ ዮሃንስ ገ/እግዚያብሄር ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች በመኪና እንደገጩትና “ገና እንገድልሃለን” የሚል ዛቻ እንደሰነዘሩበት ለፍኖተ ነፃነት መናገሩን ጋዜጣው ዘግቧል።
“ጋዜጠኛው ከአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌው ጋር በፓርቲው ጽ/ቤት ቃለምልልስ አድርጎ ወደ መገናኛ አካባቢ ሲደርስ ኮድ 1 የታርጋ ቁጥር18345 የሆነ ሚኒባስ ታክሲ ሆነ ብሎ አደጋ አድርሶበታል፡፡” ሲል ጋዜጣው ዘግቧል።
“ገጭታቸሁኝ ወዴት ትሄዳለትሁ” በማለት ሲጠይቃቸውም “ገና እንገድልሃለን” ብለውት እንደሄዱ  የገለጸው ጋዜጣው፣ በታክሲው ውስጥ ሹፌሩና አንድ ግለሰብ ብቻ እንደነበሩም ታውቋል፡፡
ስቱዲዮ እስከገባንበት ሰአት ድረስ የጀርመን ሬዲዮ በጉዳዩ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም።

Sunday, February 16, 2014

ወያኔን ካላጠፋነዉ ዘረኝነቱና ዉርደቱ ይቀጥላል

ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች በራሳቸዉ እጅ የጻፉት ማኒፌስቶ በግልጽ እንደሚያሳየን እነዚህ ዘረኞች ጫካ ገብተዉ የትጥቅ ትግል እንዲጀምሩ ያነሳሳቸዉ በአማራ ህዝብ ላይ ያላቸዉ ጥላቻና መሰረተ ቢስ ቂም በቀል ነዉ። ይህ ጥላቻቸዉ ደግሞ አማራዉን በመግደልና ግዛቱን ሲያሻቸዉ ከራሳቸዉ ክልል ጋር በመቀላቀል አለዚያም ለጎረቤት አገሮች በመሸለም ብቻ ሊቆም ወይም ሊገታ አልቻለም። እነሆ የአማራው ህዝብ የወያኔ ዘረኞች ዋነኛ ዒላማ ሆኖ የአገዛዙን የግፍ ፅዋ ያለማቋረጥ መጋት ከጀመረ ድፍን 23 አመታት ተቆጠሩ። ፋሽስቱ ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ብሔራዊ ስሜት በማምከን ፣ የዘመናት ተገዥነቱን ለማረጋገጥ በቅድሚያ የአማራን ሕዝብ ማንነት ማጥፋት ፣ የአማራን ሕዝብ ስነ ልቦናዊ ጥንካሬ መስለብ እና አንገቱን ማስደፋት አስፈላጊ መሆኑን በጽናት ያምናል። ይህ በመሆኑም ፣ በአማራ ህዝብ ላይ በወያኔ የሚፈፀመው ግፍ እና በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ስር እየሰደደና እየከፋ በግልፅም በስውርም በተቀነባበረ መንገድ ቀጥሏል።

ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ብሔራዊ ስሜት በማዳከም፣ ለዘመናት ሥልጣን ላይ ለመቆየት ያገለግለኛል ብሎ ዘመቻ ከከፈተባቸው ብሄረሰቦች አንዱና ዋንኛው የሆነው የአማራ ህዝብ በራሱ ማንነት እንዲያፍርና ብሄራዊ ኩራቱ እንዲሟሽሽ ላለፉት 23 አመታት በግብር ከፋዩ ህዝባችን ገንዘብ በሚተዳደሩ የመንግሥት መገናኛዎች ሳይቀር ከፍተኛ የስነ ልቦና ዘመቻ ተካሂዶበታል። በአማራ ሥም አማራውን የወያኔ አገር የማፍረስ አጀንዳ አስፈጻሚ ለማድረግ የተሾሙበት ተላላኪዎች በህወሃት አለቆቻቸው የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም በተለያዩ አጋጣሚዎች አማራውን የሚያዋርድና የሚዘልፍ አስተያየት በአደባባይ ሲሰጡ ሰምተናል አይተናል። ይህ ተግባራቸው ለአማራ ህዝብ ቅንጣት ታህል ክብርና ፍቅር ያልነበረው ዘረኛው አለቃቸው መለስ ዜናዊ ከዚህች አለም በሞት ከተሰናበተ ቦኋላም ተጠናክሮ ቀጥሎአል።

የህወሃት መሪዎች አማራው ላይ ያላቸው ጥላቻ ወደሥልጣን ከመጡ ቦኋላ የተፈጠረ ሳይሆን ገና በጫካ ትግል ላይ በነበሩበት ወቅት በጻፉት የድርጅታቸው የፖለቲካ መረሃግብር በግልጽ እንደተቀመጠው ለትግል ያነሳሳቸውም አማራ ብለው የሚጠሩት ብሄረሰብ እንወክለዋለን በሚሉት ብሄረሰብ ላይ አድርሰዋል በሚሉት የፈጠራ በደልና ቂም እንደሆነ አረጋግጠዋል። ላለፉት 23 አመታት አማራው ከሚኖርበት የራሱ ክልሉ ሳይቀር እንዲፈናቀል ተደርጎ እየደረሰበት ያለው በደል የዚህ የቆየ የወያኔ ቂም በቀል ውጤት መሆኑ ግልጽ ነው።

ሰሞኑን አለምነው መኮነን የተባለ ሆድ አደር የባንዳነት ተግባሩን በመፈጸም በአለቆቹ ፊት ግርማ ሞገስ ለማግኘት እመራዋለሁ የሚለውን የአማራ ህዝብ እጅግ በወረደና ጸያፍ በሆነ ቃላት ያን ያህል ሲዘባበትበት መደመጡ አማራውን ብቻ ሳይሆን መላውን የአገራችንን ህዝብ አስቆጥቶአል።

በእርግጥ አለምነው መኮንን አማራን በማዋረድ የመጀማሪያው የወያኔ ተላላኪ አይደለም። የህወሃቶቹን ቁንጮዎች ስድብና ዘለፋ ወደ ጎን ትተን በወያኔ የዘር ፖለቲካ አማራውን እወክለዋለው የሚለው ብአዴን ከፍተኛ አመራር እነ እነታምራት ላይኔ ተፈራ ዋልዋና በረከት ስሞን በተለያየ ወቅት ንቀትና ስድባቸውን አሰምተውናል። አለምነህ መኮንን እንደዚያ በወረደ ቃላት አማራውን ሲያዋርድ በስብሰባው አዳራሽ የነበሩ ህወሃት የፈጠራቸው የብአዴን ልጆች በሳቅ ካካታ ሲያጅቡት እንደነበረ እድሜ ለኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥን ከአዳራሹ ሾልኮ ለህዝብ ጀሮ የደረሰው የኦዲዮ ድምጽ አጋልጦአል።

ሁላችንም፤ እንደምንገነዘበው ወያኔ የገዛ ብሄረሰባቸውን ረግጠው በመግዛት የጥፋት አላማውን እንዲያስፈጽሙለት በራሱ አምሳል ከፈጠራቸው ድርጅቶች አንዱ የሆነው ብአዴን በታሪኩ አንድም ለህዝቡ የቆመ መሪ አፍርቶ አያውቅም። ለራሳቸውና ከአብራኩ ለተገኙት ህዝብ ምንም አይነት ክብር የሌላቸው የብአዴን መሪዎች ጣሊያን አገራችንን በወረረችበት ወቅት ለሆዳቸው ሲሉ ከባዕድ ጋር ተሻርከው ህዝባቸውን ካስጨፈጨፉት ባንዳዎች የከፋ ተግባር በህዝባቸው ላይ እየፈጸሙ ነው።

ወያኔ ለም የሆነውን የአማራ ግዛት እንዳለ የኔ ነው ወደሚለው የትግራይ ከልል ሲወስድ፤ በአማር ክልል ወስጥ በቀሩት ለም ቦታዎች የህወሃት ታማኝ ካድሬዎችን ከያሉበት እያጓጉዘ ሲያሰፍር፤ የአገሬውን አርሶ አደር እያፈናቀለ ለራሱ ታማኞች ለም መሬት እየሸነሸነ ለሰፋፊ እርሻ አገልግሎት ሲያድል አማራውን እወክለዋለው የሚለው ብአዴን አንድም የተቃውሞ ድምጽ አሰምቶ አያውቅም። የብአዴን መሪዎች የወያኔን ተልዕኮ ከማስፈጸም አልፈው በሟቹ አለቃቸው በመለስ ዜናዊ ሥም እየማሉ በአገራችን ኢትዮጵያና በሚያስተዳድሩት የአማራ ህዝብና ክልል የሚፈጽሙት በደል ብዙ ነው። ልክ እንደ ብአዴን የዘረኛውን ወያኔ የጥፋት ፖሊሲ ለማስፈጸም ከሚተጉት አንዳንዶቹ አማራውን ከክልላቸው ለማጽዳት በቤኒሻንጉል፤ በቤንች ማጅና ጉራፈርዳ ወረዳ እርምጃ ሲወስዱና ንብረታቸውን ቀምተው ባዶ እጃቸውን ሲያባርሩዋቸው ብአዴን ቁጭ ብሎ ተመልካች ነበር። ከአማራ ክልል ጋር የሚዋሰነው ዳር ድንበራችን ላይ በተነሳው የባለቤትነት ጥያቄም ላይ የወሰደው አቋም በህዝብና በታሪክ ፊት ውሎ አድሮ የሚያስጠይቀው ነው።

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደሚገነዘበው ፋሽስቱ ወያኔ በአገራችንና በህዝባችን ላይ እየፈጸመው ያለው አንዱን ዘር ከሌላው ጋር የማጋጨትና በተናጠል ደግሞ እያንዳንዱን ለይቶ የማዋረድና የማጥፋት ተግባር አሁን የተጀመረ ክስተት አይደለም። የቆየና ወያኔ ህዝባችንን ከፋፍሎ ለመግዛት ከመነሻው ሲጠቀምበት የነበረ ስልት ነው። ስለዚህ ወያኔ በራሱና በተላላኪዎቹ አማካይነት ላለፉት 23 አመታት በህዝባችን ላይ እየፈጸመ ያለውና የፈጸመው ግፍ፤ ውርደትና መከራ እንዲያበቃ ሁላችንም እጅ ለ እጅ ተያይዘን መነሳት ይኖርብናል። በወያኔ ከፋፋይ አጀንዳ እርስ በርስ እየተናቆርን የጥቃት ሰለባ የመሆናችንን እንቆቅልሽ ለማስቀረት ከኛ በላይ ሃይል ያለው አይኖርም።

በተለይ ግንባር ቀደም የወያኔ ሰለባ የሆነው የአማራ ህዝብ ወጣት በጫንቃው ላይ ተፈናጠጠው የወያኔን የጥላቻና የበቀል እርምጃ የሚያስፈጽሙትን ከአብራኩ የተገኙ ባንዳዎች ላይ የጥቃት ክንዱን መሰንዘርና ለክብሩ መቆሙን ማሳየት ያለበት ጊዜው አሁን ነው።

በብአዴን ሥር የተሰባሰቡ የአማራ ተወላጆች፤ በመከላኪያ ሠራዊቱ፤ በፖሊስና በደህንነት፤ በወጣት ማህበር፤ በሠራተኛ ማህበርና በተለያየ ሙያ ማህበር ብአዴን ራሱ ያደራጃቸው ሁሉ ለክብራቸውና ለኢትዮጵያዊ ማንነታቸው ሲሉ ከትግሉ ጎን በመሰለፍ የወያኔን ዕድሜ ለማሳጠር ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የሚያካሂደውን ትግል እንዲቀላቀሉ ንቅናቄው ጥሪውን ያቀርባል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

Thursday, February 13, 2014

በርካታ ወጣቶች ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት እየተጋዙ ነው

የካቲት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ አሸባሪ ካላቸው ግንቦት ሰባት እና ሌሎች ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ በርካታ የአዲስ አበባና አማራ ክልል ወጣቶች ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት እየተጋዙ መሆኑን የአይን እማኞች ተናገሩ፡፡
ኢህአዴግ በጀመረው አዲስ አሰሳ በሀገሪቱ አንድንድ ቦታዎች ኢንተርኔትን ጨምሮ ስልክ እንዳይሰራ የተደረገ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎችም የመከላከያ ሀይል ተበትኗል፡፡ የዚህን ዜና ዝርዝር  በሌላ ጊዜ ይዘን እንቀርባለን። በሌላ ዜና ደግሞ ብአዴን ከፍተኛ የሞራል ውድቀት የደረሰበት መሆኑን ምንጮች ገለጹ።
የብአዴን የጽፈት ቤት ሃላፊ እና የአማራ ክልል ም/ል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ አለመነው መኮንን የሚመሩት ህዝብ  ጸያፍ ስድብ መሳደባቸውን ተከትሎ ብአዴን የሞራል ውድቀት እንደደረሰበት ከክልሉ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የክልሉ ህዝብ ያሳየው ቁጣና በብአዴን የንግድ ድርጅቶች ላይ የጣለው ማእቀብ ያሰጋቸው አቶ በረከት ስምኦን ወደ ባህርዳር በማቅናት ፣ የደረሰውን ኪሳራ ለመቋቋም ያስችላሉ የሚሉዋቸውን አማራጮች ሁሉ ለመጠቀም ከሌሎች አመራሮች ጋር እየመከሩ ናቸው።
የብአዴን አመራሮች ባደረጉት የመጀመሪያ ግምገማ “የአማራ ህዝብ ፊት ለፊት የምንናገረውና ከጀርባ የምንናገረው ነገር የተለያየ ነው” ብሎ እንዲያስብና እምነቱን እንዳይጥልብን አድርጓል” ብለዋል። ብአዴን በመጪው ምርጫ ላይ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ኪሳራ ሊደርስበት እንደሚችልም በግምገማው ወቅት ተነስቷል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ በኢሳት የቀረበው የአቶ አለምነው ድምጽ አይደለም ብለው ማስተባበል ሳይችሉ ቀርተዋል። ፕሬዚዳንቱ በባህርዳር ስብሰባ መካሄዱንና ድምጹም በጊዜው የተቀረጸ መሆኑን በተዘዋዋሪ መንገድ ያመኑ ሲሆን፣ መክትላቸው የተናገሩትን በቀጥታ ከማስተባበል ይልቅ አቶ አላምነው ለአማራው ህዝብ ስላላቸው ፍቅር መግለጽን መርጠዋል።
አቶ አለምነው እራሳቸው ቀርበው ለምን መግለጫ እንዲሰጡ እንዳልተፈለገ ግልጽ አይደለም። የክልሉ ህዝብ የብአዴን ንብረት የሆነውን ዳሸን ቢራን እንዳይጠጣ የሚደረገው ቅስቀሳ አግባብ አይደለም ሲሉ አቶ ገዱ ተናግረዋል።
ድርጊቱን ያወገዙት አንድነትና መኢአድ  የካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ደብዳቤ ማስገባታቸው ታውቋል። ፓርቲዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ ”  ህዝብ ያዋረዱ አመራሮች በተገቢው ፍጥነት ለፍርድ እስኪቀርቡ ድረስ የተቃውሞ ሰልፉ በሌሎች የሀገራችን ክፍሎችም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል” ብለዋል፡፡
የተቃውሞ ሰልፉ ከጣቱ በሶስት ሰአት ከቀበሌ 12 ( ግሽ አባይ ተነስቶ)፣ በክልሉ መስተዳድር ጽ/ቤት ከቀኑ ስምንት ሰአት ላይ ያበቃል። የባህርዳር እና አካባቢዋ ህዝብ በስፍራው ተገኝቶ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት በህዝቡ ላይ ያወረዱትን ዘለፋ እንዲያወግዝ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል።

Wednesday, February 12, 2014

የዩጋንዳ ጦር ደቡብ ሱዳንን ለቆ እንዲወጣ አቶ ሃይለማርያም አስጠነቀቁ

የካቲት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጠ/ሚ/ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የዩጋንዳ ጦር በሂደት ለቆ ካልወጣ አካባቢው የጦርነት ቀጠና ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ሁሉም ሃይሎች የራሳቸው የሆነ ፍላጎት አላቸው ያሉት አቶ ሃይለማርያም፣ በደቡብ ሱዳን ሰላም ይመጣ ዘንድ የዩጋንዳ ጦር ጁባን ለቆ መውጣት አለበት ሲሉ አሳስበዋል ።
አቶ ሃይለማርያም የገለጹት አቋም የደቡብ ሱዳንን መንግስት የሚያስከፋ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ግን ለተቀዋሚዎች መልካም ዜና ነውተብሏል። የሳልቫኪር መንግስት፣” ሰላማችንን ለማስጠበቅ  የፈለግነውን ሃይል የመጋበዝ መብት አለን” የሚል አቋም ይዟል።
ዩጋንዳ ለአቶ ሃይለማርያም ማስጠንቀቂያ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም። የዩጋንዳ መንግስት በአቋሙ ከጸና ኢትዮጵያን የመሳሰሉ የደቡብ ሱዳን ጎረቤት አገሮች የሚወስዱት አቋም ግልጽ አይደለም።
የዩጋንዳ ጦር ፕሬዚዳንት ሳለቫኪር በተቃዋሚዎች ላይ ድል እንዲያገኙ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ተጠልፈው የተወሰዱት ሁለቱ የኦጋዴን ነጻ አውጭ ባለስልጣናት በአንድ ወታደራዊ ሆስፒታል ውስጥ ሲታከሙ መታየታቸውን ግንባሩ ገለጸ

የካቲት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ግንባሩ ለኢሳት በላከው መረጃ ፣ ከኢህአዴግ መንግስት ጋር ድርድር ለማድረግ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ተገኝተው  በኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች ታፍነው የተወሰዱት የኦብነግ አመራሮች፣ የደረሰባቸውን ከፍተኛ ድብደባ ተከትሎ በአንድ ወታደራዊ ሆስፒታል ውስጥ ሲታከሙ ታይተዋል። የመንግስት የደህንነት ሰራተኞች ” ባለስልጣኖቹ በገዛ ፈቃዳቸው እጃቸውን እንደሰጡ ለማሳመን ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት ባለመሳካቱ  አሰቃቂ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው” ግንባሩ አክሎ ገልጿል።
ገዢው ፓርቲ ከዚህ ቀደም አንዳንድ ሰዎችን በሃይል ወይም ገንዘብ በመስጠትና በማማለል ሰላም ስምምነት እንዲፈርሙ ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሰው መግለጫው፣ በሁለቱ ባለስልጣኖች ላይ የደረሰውም ከዚህ የተለየ አለመሆኑን አትቷል።
ግንባሩ የኬንያ መንግስት፣የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት የኢህአዴግ መንግስት የሰዎቹን ደህንነት ጠብቆ እንዲለቃቸው ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቋል።

አንድ የአየር ሃይል ባልደረባ የአርበኞች ግንባርን ተቀላቀለ

የካቲት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የደብረዘይት አየር ኃይል አባል የነበረው ምክትል መቶ አለቃ ዳንኤል የሽዋስ የኢህአዴግን ስርአት በመቃወም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊትን መቀላለቀሉን ግንባሩ ለኢሳት በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ም/መ/አለቃ ዳንኤል የሽዋስ የ L-39  ስኳድሮን ተዋጊ ጀት አብራሪ እንደነበር መረጃው ያመለክታል።
ም/መ/አ ዳንኤል የሽዋስ “ተቃዋሚዎችን ትደግፋለህ ከእነሱም ጋር የጠበቀ ግኑኝነት አለህ በሚል ምክንያት ተጠርጥሮ ያለምንም ወንጀል ለአምስት ወር ያህል ታስሮ እንደነበርና ከእስር እንደተለቀቀም በደህንነት አባሎች አማካኝነት በአይነ ቁራኛ ክትትል ሲደረግበት ቆይቶ ፣ እንደገና ለ23 ቀናት በደብረዘይት እስር ቤት መታሰሩን፣ገልጿል፡፡ የአየር ሃይል ባልደረባው በዚህ መሃል ከእስር ቤት አምልጦ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊትን መቀላቀሉን” የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የአየር ሃይሉ ባልደረባ መኮብለሉን በተለመለከተ መንግስት የሰጠው መግለጫ የለም።
ግንባሩ በላከው ሌላ ዜና ደግሞ  በሁመራ አካባቢ  የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ደጋፊዎች ናችሁ በማለት ታስረው በነበሩ 10 ሰዎች ላይ ከ6 ዓመት እስከ 25 ዓመት እንደተፈረደባቸውና  ወደ መቀሌና ሽሬ እስር ቤት እንደተወሰዱ ገልጿል።
አርበኞች ግንባር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ወታደራዊ ጥቃቶችን በመፈጸም ላይ ይገኛል።

በ500 ብር ደሞዝ የሚተዳደረው የህወሃት ታጋይ ከ10 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ሃብት ማካበቱ ተገለጠ

የካቲት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የደህንነት ሃላፊ ከነበሩት ከአቶ ወልደስላሴ ወልደ ሚካኤል  ጋር በግብረ-አበርነት የተከሰሱት የህወሃት ታጋዮች ከደሞዛቸው ጋር ፈጽሞ የማይመጣጠን ሃብት አግበሰው መገኘታቸው ታውቋል።
በተለያዩ አለመግባባቶች የተነሳ እየተመሰረቱ ያሉ ክሶች የህወሃት ተጋዮች በህገወጥ መንገድ የሰበሰቡትን የሃብት መጠን ለማወቅ እየረዳ መሆኑን የገለጸው ዘጋቢያችን ከአቶ ወልደስላሴ ጋር በግብረ አበርነት የተከሰሱት የህወሃት ታጋዩ የአቶ ወልደስላሴ ወንድም አቶ ዘርአይ ወልደስላሴ የመከላከያ ሚኒስቴርን ሲለቁ በመጨረሻ ይከፈላቸው የነበረው ወርሃዊ ደሞዝ 532 ብር ብቻ እንደነበር አመልክቷል ፡፡  ይሁንና፣ ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ባደረገው ማጣራት ግለሰቡ በተለያዩ ባንኮች በስማቸው 5 ሚሊዮን ብር ከማስቀመጣቸውም በተጨማሪ፣ አዲስ አበባ ቤቴል ሆስፒታል አካባቢ በ74 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ግንባታ እያካሄዱ ፣ በአፋር ክልል ደግሞ ከ1 ሚሊዮን 400 መቶ ሽ ብር በላይ በሆነ ወጪ የእርሻ ኢንቨስትምንት እያከናወኑ መሆናቸው እንዲሁም  በስማቸው 2 ሚሊዮን 700 ሺ ብር ግምት ያላቸው 2 ሎደር መኪኖች መገኘታቸውን ገልጽዋል።
የአቶ ወልደስላሴ እህት የሆኑት ወ/ሮ ትርሃስ ደግሞ የ8ኛ ክፍል ተማሪና ምንም ስራ ያልበራቸው ሲሆን፣ በወንድሞቻቸው ድጋፍ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዛ አንድ ስካቫተር፣መኪና እንዲሁም   በአዲስ አበባ በየካና ቦሌ ክፍለ ከተሞች፣ በለገጣፎ፣ መቀሌና አክሱም 3 ሺ 266 ካሬ ሜትር ቦታዎች በስማቸው መገኘቱ ተመልክታል ፣እንዲሁም  በተለያዩ ባንኮችም 8 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ ማድረጋቸውን  አንድ ተጨማሪ ዘመናዊ መኪና በስማቸው ተመዝግቦ መገኘቱን ጸረ ሙስና ኮሚሽን በምርመራ አረጋግጧል።
ዋናው ባለስልጣን አቶ ወልደስላሴ ደግሞ ስራ ሲጀምሩ ደሞዛቸው 1600 ብር የነበረ እና በእድገት እስከ 6000 ሺ ብር ሲከፈላቸው የቆየ ቢሆንም ያካባቱት ሀብት ግን ፈጽሞ ከደሞዛቸው ጋር የማይመጣጠን ነው ተብሏል። ባለ 4 ፎቅ ህንጻ ባለቤት የሆኑት አቶ ወልደስላሴ በ1 አመት ከ2 ወራት ቤቱን አከራይተው 790 ሺ ብር ገቢ አግኝተዋል።
አቃቢ ህግ ያቀረበውን ክስ የእስረኞች ጠበቆች፣ አዲስ የተጨመረ ክስ ነው በማለት አቤቱታ አቅርበዋል።
አቶ ወልደስላሴ ከወ/ሮ አዜብ ጋር በነበራቸው መቀራረብ ከፍተኛ ሃብት ማፍራታቸውን ፤ አቶ መለስ ዜናዊ ከሞቱ በሁዋላ ግን የእርሳቸው ዋነኛ ተቀናቃኝ የሆኑት የደህንነቱ ዋና አዛዥ አቶ ጌታቸው አሰፋ ግለሰቡን በሙስና ከሰው እንዳሳሰሩዋቸው አንዳንድ የመገናኛ ብዙሀን ገልጸው ሲዘግቡ ቆይተዋል።
ህወሃቶች እርስ በርስ በሚያደርጉት ሽኩቻ እየተካሰሱ ፍርድ ቤት መቅረባቸው የካበቱትን ሃብት ለማወቅ እየረዳ ነው የሚለው ዘጋቢያችን፣ በጸረ ሙስና ኮሚሽን ያልተመረመረና በፍርድ ቤት ቀርቦ ያልታወቀ ከዚህም የባሰ የሙስና ታሪክ እንደሚኖር መገመት ይቻላል ሲል አስተያየቱን አስፍሯል።