ህወሃት የትግሬ ተወካይ ብቻ ሳልሆን ለትግራይ ህዝብ የሚያመልከውን አምላክም ጭምር የምመርጥለት እኔ ነኝ በሚል እብሪት ውስጥ ይገኛል። በዚህ እብሪቱም እየተመራ የምታመልኩትን ልመርጥላችሁ ብሎ አጠቃላይ ሙስሊሙንም ክርስትያኑንም እያመሰው እንደሆነ እያየን ነው። እኔን የማይቀበል እጣ ፈንታው ከመታመስ በላይ የሆነ ወዮታ ነው የሚል ያልተፃፈ አዋጅም አለው። ህወሃት በትግራይ ትከሻ ላይ ተፈናጦ፤ ትግራይን ምርጫ አሳጥቶ እኔን እምኑ መንገዳችሁም ህይወታችሁም እኔ ብቻ ነኝ ብሎ ራሱን የትግራይ ጣዖት አድርጎ ሹሟል። ይሄን ጣዖት አንቀበልም፤ እኛ የራሳችን ሂሊና ያለን እንደ ሰው ማሰብ የምንችል ነን ያሉ ብዙ የኢትዮጵያ ልጆች ባልታወጀው አዋጅ መሠረት አብዮታዊ ፀሎት እየተፀለየላቸው አፈር ለብሰው ቀርተዋል።የህወሃት የእብሪቱ መጀመሪያ “እኔ ያልኩት ካልሆነ ሁሉም ገደል ይግባ” ማለቱ ነው። የትግራይ ተወካይ እኔ ብቻ ነኝ ሌላው ሁሉ የትግራይ ህዝብ ጠላት ነው የሚል እምነቱ የድርጅቱን ሥር የሰደደ መሠሪነትና እብሪት የሚያሳይ ነው።
ብዙ ኢትዮጵያዊያን ህወሃት የቆመው ለትግራይ ህዝብ ነው የሚል ዕምነት አሳድረዋል። ይሄን አስተሳሰብ መቀበል የሚጠቅመው ለህወሃት ብቻ ነው።ህወሃት ለትግራይ ህዝብ ክብርም ፍቅርም ያለው ቡድን አይደለም። ለትግራይ ህዝብ በጎ ምኞት እና ክብር ያለው ቢሆን ኑሮ የትግራይ ህዝብ የወደደውን እንዲመርጥ፤ ያልወደደውን እንዲተው ያልተሸራረፈ ነፃነት እንዲኖረው ያደርግ ነበር። እኛ እንደምናየው ግን የትግራይ ህዝብ የወደደውን ለመምረጥ፤የጠላውን ለመተው እንዲችል ነፃነትያለው ህዝብ አይደለም። የትግራይ ህዝብ ነፃነቱን በነፃነት ሥም ያጣ ህዝብ ሁኗል። ህወሃቶች የትግራይን ህዝብ ነፃነት ሸራርፈው ሸራርፈው ህዝቡን በሙሉ መያዣ አድርገውና ከወገኑ ለይተውት እየገዙት ይገኛሉ። የትግራይም ህዝብ ሳይወድ በግዱ ህወሃቶችን ተሸክሞ መከራው በዝቶ እየተገዛ ይገኛል።