በእለቱ የነበረውን ፕሮግራም የኢሳት በርገን ቅርጫፍ ድጋፍ ሰጭ ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን አሸናፊ እና ጋዜጠኛ ገሊላ መኮንን በአማረ መልኩ መርተውታል ፡፡ ዝግጅቱን በንግግር የከፈተው የኢሳት በርገን ፀሐፊ የሆነው ወጣት ሺበሺ ጌታቸው ሲሆን ንግግሩም ያተኮረው “ኢሳት ይቀጥላል” ስንል ምን ማለታችን ነው በማለት ሰፋ ያለ ማብራሪያ አቅርቧል በተጨማሪም በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም አይነት ነፃ ሚዲያ ባለመኖሩ ይህንን ክፍተት ለመሸፈን ኢሳት የኢትዮጵያን ህዝብ በመረጃ ሙሉ ከማድረግ አንፃር እየሰራ ያለውን ስራ አድንቀዋል ፡፡ ኢሳት የህዝባችን አንደበት፣አይን እና ጆሮ ስለሆነ ኢሳትን ለመርዳትና ቋሚ አባል በመሆን የዜግነት ግዴታችንን በመወጣት በመረጃ እጦት ውስጥ ላለው ወገናችን አለኝታ እንድንሆንና የኢሳትን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የኛ ድጋፍ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው አስገንዝበዋል ፡፡
በቀጣይነትም የኢሳትን ስራ የሚዘክር የኢሳት መዝሙር በአቶ ማርቆስ አብይ ተደርሶ በቶማስ አለባቸው ዜማው ተሰርቶ በአቶ ኢሳያስ አዘጋጅነት ተዘጋጅቶ ቀርቧል ፡ የመዝሙሩ መጠሪያ “ኢሳት ይቀጥላል በፍጹም አይቆምም ” የሚል ሲሆን በህብረት ዘማሪያን ለታዳሚው ቀርቦ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፏል ፡፡ መዝሙሩም በሲዲ ተቀርፆ ለኢሳት ኖርዌይ በስጦታ ተበርክቷል ፡፡
በመቀጠል ተጋባዥ የኢሳት እንግዶች ጋዜጠኛ አበበ ቶላ እና ጋዜጠኛ ፍሰሐ ተገኝ በወቅታዊ የሃገራችን ጉዳዮች እና በኢሳት ዙሪያ አዝናኝና አስተማሪ የሆኑ ገጠመኞቻቸውን ለታዳሚው እያዋዙ አቅርበዋል ፡ በተጨማሪ ጋዜጠኛ ገሊላ መኮንን በነፃነት ታጋዩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ዙሪያ የሚያተኩር ስሜትን የሚነካ ግጥም ያቀረበች ሲሆን ታዳሚውም በአፀፋው ለሶስቱ ጋዜጠኞች ያለውን ፍቅርና አክብሮት በጭብጨባ ገልፀውላቸዋል ፡፡
ሌላው በእለቱ ለየት ያለ ዝግጅት የቀረበው የኢሳት የሶስቱም ስቱዲዮ ጋዜጠኞች የሚያቀርቧቸውን ዝግጅቶች የሚዘክር የፎቶ ኤግዚብሽን ለእይታ የቀረበ ሲሆን በእያንዳንዱ ስቱዲዮ የሚቀርቡትን ዝግጅቶች ማለትም አቶ ሚካኤል አቦዬ የአመስተርዳም ስቱዲዮን ፣ አቶ አሰግድ ታመነ የዋሽንግተን ስቱዲዮን እና አቶ ዳዊት ዮሐንስ የለንደን ስቱዲዮን ዝግጅቶች ለጎብኚዎቹ በስፋት አብራርተዋል ፡፡
ሌላው በዝግጅቱ ላይ የቀረበው “የሳኦል ፍሬዎች” የሚል በአቶ አይንሸት ገበያው ተደርሶ በገሊላ መኮንን አዘጋጅነት በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ ለእይታ የሚቀርበው ፊልም የተመረቀው በዚሁ እለት ነበር ፡፡ ይህ ፊልም በሃገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ሲሆን በአጭሩ ለተመልካች ቀርቧል ፡፡ በተጨማሪም በኢሳት ላይ የሚያተኩር እና መሳጭ ግጥም በወጣት ዳዊት እዮብ ቀርቦ ከተመልካች አድናቆትን አትርፏል ፡፡
በመጨረሻም የቀረበው የአትሌት ሙሉጌታ ዘውዴ በኖርዌይ “በርገን ሲቲ” በሚል የሚዘጋጀውን የግማሽ ማራቶን ውድድር የኢሳትን ቲሸርት በመልበስ ሮጦ ያሸነፈበትን ዋንጫ ለጫረታ አቅረቦ በተለይም በኦስሎ እና በበርገን ከተሞች የመጡ የኢሳት ቤተሰቦች ከፍተኛ የሆነ ፉክክር ያደረጉበት ሲሆን በመጨረሻም ከኦስሎ የመጣው አቶ ፋንታሁን ተሰማ በከፍተኛ ገንዘብ ጨረታውን አሽንፎ ዋንጫውን የግሉ አድርጓል በተጨማሪም አትሌት ሙሉጌታ ዘውዴ “በበርገን ፋና ግማሽ ማራቶን” ያሸነፈበትን ዋንጫ ለኢሳት በስጦታ መልክ አበርክቷል ፡፡ በዕለቱ ከጫረታ፣ ከትኬት እና ከመስተንግዶ ከ 100000.00 / ከመቶ ሺህ ክሮነር/ በላይ መስብሰቡን በበርገን የኢሳት የገቢ ማሰባሰብ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ባጫ ደበሌ ለተሰብሳቢው ይፋ አድርገዋል ፡፡
የዝግጅቱም ፍፃሜ ለተጋባዥ ጋዜጠኞች እና ለኢሳት ቤተሰቦች እንኳን ለ4ኛ አመት አደረሳችሁ በሚል የተዘጋጀውን ኬክ የመቁረስ ስነ ስርዓት ተካሂዶ “ኢሳት ይቀጥላል በፍጹም አይቆምም “ በሚለው መዝሙር ታጅቦ በተሳካ እና አስደሳች በሆነ ሁኔታ ተጠናቋል ፡፡
ኢሳት ይቀጥላል
ዳዊት እያዩ
በኖርዌይ የኢሳት በርገን ቅርጫፍ ድጋፍ ሰጪ