Friday, April 15, 2016

ትግሉ ሰፊ የምሁራን ተሳትፎ ይሻል!

ኢትዮጵያ በበብዛትም ይሁን በጥራት በውጭው አለምም ይሁን በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ምሁራን ያፈራች ሀገር ነች። በጅጉ የሚያሳዝነው ግን በሀገሪቱና በሕዝቧ ችግር ላይ ሀሳብ ሲሰጡ ፣ ባደባባይ ሲከራከሩና ሲታገሉ የሚታዩት በጅጉ ጥቂቶች ናቸው። ርግጥ ነው ተከታታይ መንግስታት በምሁራን ላይ ያደረሱት ጥቃትና ማግለል ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ብዙዎች መከራን ከህዝብ ጋር ከመጋፈጥ ይልቅ አጎንብሶ ማሳለፈን የመረጡበት ሁኔታ አለ። ቁጥራቸው ጥቂት ያልሆኑም ለግል ጥቅማቸው ቅድሚያ በመስጠት ከጨቋኝ ገዥዎች ጋር በመተባበር የሚሰሩ መኖራቸውም አይካደም። አብዛኛው ምሁራን በተለይም በብዙ የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸው ጭምር ሀገሪቱን ከገባችበት ማጥ ለማውጣት በሚደረገው ትግል ውስጥ እየተሳተፉ አይደለም። ይህ ዛሬ ባለው ችግርም ይሁን በታሪክ ፊት አሳዛኝ ነው።

ሀገራችን ዛሬ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች። የተማሩ ልጆቿ መላ እንዲመቱ በመጠየቅ ላይ ትገኛለች። ይልቁንም በሀገራችን ያለው ችግርና ሀገሪቱ እየሄደች ያለችበት መንገድና አቅጣጫ በተለይ ምሁራንን እንቅልፍ ሊነሰ ይገባል። ዕውነታው ከዚህም አልፎ የሀገሪቱን አሳዛኝና አደገኛ ሁኔታ ለመቀየር በሚደረገው ትግል ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ግድ ይላል። የመንግስት ግፍና ሰቆቃ በበዛበትና የሀገራችን ሕልውና አደጋ ላይ በወደቀበት በአሁኑ ሰዓት ምሁራን ላለመሳተፍ ምክንያት ማቅረብ የማይችሉበት ወቅት ላይ ደርሰናል። እንደማንኛውም ሀገር ምሁራን የኢትዮጵያ ምሁራን በሀገራችን ውስጥ ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲሰፍንና ፍትሕ የሰፈነበት ስርዓት እንዲመሰረት ሊሸሹት የማይገባ ትልቅ ሚና አላቸው።

ዛሬ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ዜጎች መንግስት በልማትና በልማት እያመካኘ የሚያካሂደውን ሰፊ ዝርፊያ እንዲሁም ወያኔ ሩብ ምዕተ አመት ሙሉ በብሄረሰብ እኩልነት ስም እየማለ የሚያደርሰውን ያንድ ብሄረሰብ ጉጅሌ የበላይነት ማስፋፋት እምርረው በመታገል ላይ ናቸው። መስዋዕትነቱን እየከፈሉ የሚታገሉትና የሚወድቁ የሚነሱት ወጣቶችና ምስኪን ገበሬዎች ናቸው። እነዚህ ወገኖቻችን ሕይወታቸውን ሳይቀር ሲገብሩ በየቀኑ እየሰማንና እያየን ነው። ይህንን የህዝብ ጥያቄና ትግል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ምሁር ተመልካች ሆኖ ሊቀመጥ አይገባም። ትግሉን ከመምራት ጀምሮ እስከ ተራ ታጋይነት ባሉት ረድፎች ሁሉ ምሁራን ቀጥተኛ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል። ሰለትግሉ እቅጣጫም ሆነ ስለሀገሪቱ መጻዔ ዕድል ሃሳብ ማመንጨትና ማሰራጨት ይኖርበታል። ሀገራችን የደለቡ ችግሮቿን ተቋቁማ ፍትሕ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ሀገር የሚያደርጋትን የምህንድስና ስራ አስቀድሞ ማሰብና ማመቻቸት ይኖርበታል። ርግጥ ነው ይህን መሰል ተሳትፎ የሚያደርጉ ምሁራን አሁንም አሉ። ቁጥራቸው ግን ሊሆን ከሚገባው ጋር ሲወዳደር በጅጉ አነስተኛ ነው።

ምሁርነት ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ መቀዳጀት ብቻ እንዳልሆነ የታወቀ ነገር ነው። ምሁርነት ምሉዕ የሚሆነው መላውን የተፈጥሮ ከባቢ ከህዝብ ማህበራዊ ሕይወት ጋር አጣምሮ የሚያስብ አዕምሮን በዕውነት ላይ ለተመሰረተ ሀሳብና ዕውቀት ክብር መስጠትን ለተግባራዊነቱ መሟገትን የጨመረ ሲሆን ነው ። በመሆኑም ሁሌ እንደሚባለው ምሁርነት የጋን መብራትነት አይደለም። ምሁርነት በጨለማ ውስጥ ችቦ ሆኖ ብርሃን መፈንጠቅን ይመለከታል። ምስዋዕትነትንም ይጠይቃል።

ያለንበት ወቅት ለኢትዮጵያ ምሁራን ከፍተኛ ፈተናም ዕድልም ይዞ ቀርቧል። ይህ ልሽሽህ ቢሉት የማይሸሽ ፈተና ከመሆኑ ባልተናነሰ በታሪካችን እንድ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የጎላ አሻራን ለማኖርም ትልቅ የታሪክ ዕድል ነው። ይህ ፈተና ከፍተኛ ያርበኝነት ስሜትንና ሀላፊነት መውሰድን ይጠይቃል። አገር በተወሳሰበ ችግር ምክንያት ወደ አረንቋ እየገባች ምንም ሳይሰሩ መቀመጥ ወይም ዝም ብሎ ከመመልከት የበለጠ ለምሁር ሂሊና የሚከብድ ነገር ሊኖር አይችልም:: በጣም ላስተዋለ ሰው እንዲህ አይነት ዝምታ ሐጢያትም ነው። በእንዲህ አይነት ፈታኝ ወቅት የኢትዮጵያ ምሁራን ሀገሪቱን ወደተሻለ አቅጣጫ እንድትሔድ ላለመታጋል ምንም ምክንያት ማቅረብ አይችሉም። ሀሳብ የሚሰራጭባቸው የሀሳብ ክርክር የሚካሔድባቸው መድረኮች ፣ አደባባዮች ፣ የመገናኛ መሳሪያ አይነቶች የፖለቲካና የሲቪክ ማህበሮች ባገር ውስጥም በውጭም ያሉት መሳተፊያ ናቸው።

ድርጅታችን አርበኞች ግንቦት 7 ምሁራን በሰፊውና እንደየፍላጎቶቻቸውና ችሎታቸው ሊሳተፉ የሚችሉባቸው በርካታ የትግል መስኮች አሉት። የሀገሪቱን ውስብስብ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ የጥናት ውጤቶች ፣ ሀሳቦች ፣ ምክሮችም ሆነ ቀጥተኛ የምሁራን ተሳትፎ ለማስተናገድ አመቺ ሁኔታ ያለበት ድርጅት ነን። ወደፊትም የምሁራን ተሳትፎ እንዲጎለብት ሁኔታዎችን ይበልጥ ለማመቻቸት እንሰራለን። ዽርጅታችን የሀገራችን ችግር የሚወገደውና ዲሞክራሲና የዜጎች እኩልነት የሚረጋገጠው በበሰለና ከተራ ዜጋ እስከ ብስል ምሁራን በሚያከሂዱት ክርክርና የበሰለ ሃሳብ ላይ ተመስርቶ መሆኑን ያምናል። አሁን ያለው የሀገራችን ምሁራን ተሳትፎ ደረጃ ሁላችንም ከምንጠብቀው በታች በጅጉ ያነሰ መሆኑ ሁላችንንም ከማሳዘን አልፎ የሚያስቆጭና የሚያንገበግብ ሆኖአል:: አገርና ህዝብ ድረሱልኝ እያለ በሚጣራበት በዚህ የታሪክ አጋጣሚ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ የተለያዩ ምክንያቶችን እየደረደሩ ማለፍ ይቻል ይሆናል። ይዋል ይደር እንጂ ለነጻነቱ ቀናዕ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የደረሰበትን አፈናና ጭቆና እምቢኝ ብሎ ነጻነቱን ሲቀዳጅ ግን ከታሪክ ፍርድና ከህዝብ ትዝብት ማምለጥ አይቻለም።

አርበኞች ግንቦት 7 በአገር ውስጥም ሆነ በተለያየ ምክንያት በአለም ተበትኖ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ምሁር ለወገን ደራሽነቱንና አለኝታነቱን አሁኑኑ ይወጣ ዘንድ ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል::

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!