Monday, February 20, 2017

የህወሓት ተላላኪ ሆኖ በርካታ በደሎችን በህዝብ ላይ ሲፈፅም የነበረው ደረጄ መከታው የተባለው ግለሰብ በአርበኞች ግንቦት 7 የውስጥ አርበኞች እርምጃ የተወሰደበት መሆኑ ታወቀ፡፡

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ)
የህወሓት ተላላኪ ሆኖ በርካታ በደሎችን በህዝብ ላይ ሲፈፅም የነበረው ደረጄ መከታው የተባለው ግለሰብ በአርበኞች ግንቦት 7 የውስጥ አርበኞች እርምጃ የተወሰደበት መሆኑ ታወቀ፡፡

ሰሞኑን በአርበኞች ግንቦት 7 የውስጥ አርበኞች የተገደለው ደረጄ መከታው የተባለው ግለሰብ ከዚህ በፊት የቀድሞው የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር አባል የነበረና በድርጅቱም ግዳጅ በመላክ ወደ ኢትዮጵያ ሲሄድ አብሮት ሲሄድ የነበረውን የትግል ጓዱንና ድርጅቱን በመካድ የጠላት ተባባሪ በመሆን በታጠቀው የድርጅቱ መሳሪያ ጓዱን በመግደል ለወያኔ ስርዓት እጁን በመስጠት ተቀላቅሏል፡፡ ከአገዛዙ ተቀላቅሎ በመኖር ላይ እያለም ከአንድ የስርዓቱ አገልጋይ ጓደኛው ጋር በመሆን የትጥቅ ትግሉን ይደግፋሉ እንዲሁም በገዢው ቡድን ላይ ህዝብን ያሳምፃሉ ብለው የሚፈርጇቸውን ሰዎች እንዲሰልሉ በአገዛዙ ተቀጥረው ሲሰሩ የነበረ ቢሆንም ከእለታ አንድ ቀን ሰው በመግደል ታስረው የቆዩ ሲሆን ባልታወቀ ምክንያትም ብዙም ሳይቆዩ ከእስራት ተፈተዋል፡፡ ይኸው ደረጄ መከታው የተባለው ግለሰብ ከእስራት ከተለቀቀ በኋላም ከወያኔ ደህንነት ጋር በመሆን በአሳቻ ሰዓትና በማታ ንፁሃን ዜጎችን በማደን ሲያሳስርና ሲያስደበድብ በተጨማሪም ሲያስገድል መቆየቱን የአካባቢው ህዝብ የአይን ምስክሮች ናቸው ፡፡

በመሆኑም ይህን የህዝብ ሰቆቃ ሰምቶ መታገስ ህሊናቸው ያልፈቀደላቸው በአርበኞች ግንት 7 ስር በሃገር ቤት የሚንቀሳቀሱ የውስጥ አርበኞች በዚሁ ደረጄ መከታው በተባለው ግለሰብ ህዝብ የሚደርስበትን በደልና ይኸው ግለሰብ ለወያኔ መላላክን ምርጫው ያደረገ በንፁሃን ዜጋ ሞት የሚደሰት መሆኑን በመመልከታቸው የአርበኞች ግንቦት 7 የውስጥ አርበኞች ተከታትለው ሊገድሉት ችለዋል ፡፡

አሁንም በዚህ ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ከህዝብ ጎን መቆም ሲገባቸው ለጥቅም ያደሩ ግለሰቦች መለስ ብለው መሳሳታቸውን አምነው ከህዝብ ጎን ካልተሰለፉና የህዝቡን ትግል ካልደገፉ ወይም ከቀደመው እኩይ ተግባራቸው ተቆጥበው ማሳሰራቸውንና ማስደብደባቸውን እስካላቆሙ ድረስ በሰላም መኖር እንደማይችሉና የእነርሱም እጣ ፈንታ እንደ ደረጄ መከታው እንደሚሆን የአርበኞች ግንቦት 7 የውስጥ አርበኞች ከሃገር ቤት ባደረሱን መረጃ አስታውቀዋል ፡፡

በህወሓት የበላይነት ስር የሚገኘው የኣገር መከላከያ ሠራዊት ከ25 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ሲፈተሽ

(በአርበኞች ግንቦት 7 ጥናትና ምርምር ቡድን የተዘጀ)

ታህሳስ 2009 ዓ.ም.

የመከላለያ አዛዞች የብሄር ስብጥር ጥናት ውጤት ታህሳስ 2009 (PDF)

መግቢያ

የዛሬ ሰባት አመት (እ.ኤአ. 2009) ያኔ “ግንቦት 7- የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ” ይባል የነበረውና አሁን አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ውስጥ የተጠቃለለው ድርጅት በዘር የተደራጀዉን የወያኔ መከላከያ ተቋም አደረጃጀት ምን እንደሚመስል በመረጃ አስደግፎ ለኢትዮጵያ ብሎም ለዓለም ማኅበረሰብ ማቅረቡ የሚታወስ ነዉ። ያ ጥናታዊ ሪፓርት ለዓለም ዓቀፍ ማኅበረሰብም ቀርቶ አገዛዙን ትዝብት ላይ በመጣሉ “የመካከያ ሠራዊታችንን ብሄራዊ ተዋጽዖ እናመጣጠንን ነው” የሚል ፕሮፖጋንዳ የወያኔ ኣገዛዝ መንዛት ተጀመረ።

በዝቅተኛና በተራ ውትድርና ደረጃ መመጣጠን መኖሩ ድሮም ጥያቄ ተነስቶበት አያውቅም። ድሮም አሁንም ጥያቄው ያለው በሠራዊቱ አመራር ላይ ያሉት እነማን ናቸው የሚለው ላይ ነው። በዚህ ረገድ በእርግጥ እንደሚባለው ለውጥ አለን? ይህ ጽሁፍ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የተደረገ ጥናት ውጤት ነው።

የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው የአገዛዙ ሠራዊት አመራሮች የብሄር ተዋጽዖ በተመለከተ ዛሬ ሰባት ዓመት ከነበረው እጅግም የተሻለ ነገር የለም። በህወሓት ስር የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ ከተደረገ ከሃያ አምስት ዓመታት በኋላም 6% ብቻ የሆነውን የትግራይን ሕዝብን አንወክለዋለን በማለት በሚነግዱ የትግራይ ብሄር ተወላጆች የበላይ ኃላፊነት፣ እዝና ቁጥጥር ስር ወድቆ እናገኛለን። ይህ ጥናት እንደሚያሳየው የኣሮሞና የኣማራ ብሄሮችም ሆኑ ሌሎችሁ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በመከላከያ ሠራዊቱ የኃላፊነትና የእዝ ቦታዎች ላይ እጅግ ዝቅተኛ ወይንም ከነኣካቴው ምንም እይነት የኃላፊነት ድርሻ የላቸውም። ይህ ያገጠጠ ኢ-ፍትሃዊነት ኣንድምታው ህሊና ላለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ምን ማለት መሆኑ ግልጽ ነው ብለን እንገምታለን። ዛሬም እንደትናቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ ወያኔ ለፈጠረዉ ዘረኛ ስርዐት ብቸኛ ምሳሌ ሆኖ መቅረብ የሚችለዉ በቀድሞዋ ደቡብ አፍሪካ ዉስጥ ነጮች ፈጥረውት የነበረው ዘረኛ (Apartheid) ስርዐት ብቻ ነዉ።

በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዉስጥ በተለይ በቁጥሩ ከፍተኛ ብልጫ ያለዉና ትግርኛ ተናጋሪ ያልሆነዉ ሠራዊት እጅግ ያኮረፈ፤ የተቆጣና ያመረረ ሠራዊት ከመሆኑ የተነሳ እራሱን የሚመለከተዉ እንደ አገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሳይሆን አንደ ህወሓት የቤት ዉስጥ አገልጋይ ባሪያ ነዉ። ይህ የህወሓት ዘረኞች በሠራዊቱ ላይ የፈጠሩት የመገዛትና የበታችነት ስሜት በየቀኑ ከፍተኛ ቁጣና የውስጥ ለውስጥ ተቃውሞ የሚገጥመዉ ቢሆንም ህወሓት በዘረጋዉ ከፍተኛ የአፈና መረብ የተነሳ የሕዝብ መነጋገሪያ አርዕስት መሆን አልቻለም። የህወሓት መሪዎችም ቢሆኑ ይህንን ቁጣና ተቃዉሞ በሚገባ ስለሚያዉቁ “ግምገማ” እያሉ በሚያዘጋጇቸዉ መድረኮች ላይ እንደነዚህ አይነቶቹን የህወሓትን የበላይነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ማስተናገድ ቀርቶ ጥያቄዎቹ እንዲነሱም አይፈቅዱም። አንዳንዴ ደፍረዉ እነዚህን ጥያቄዎች የሚያነሱ ግለሰቦች ሽብርተኛ፤ የደርግ ስርዐት ናፋቂዎች፤ ጠባብ ብሄረተኞች ወይም የጥላቻ ፖለቲካ አራማጆች የሚል ተቀጥላ ስም ይሰጣቸዋል። ዛሬ ዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዉ በተለያዩ የወያኔ እስር ቤቶች ዉስጥ የሚሰቃዩት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ለዚህ አሳዛኝ ሁኔታ የበቁት በመከላከያ ተቋሞች ዉስጥ ሠራዊቱን በዬትኛዉም እርከን የሚመሩ መኮንኖች አመዳደብ ወታደራዊ አመራር ችሎታን፤ ልምድንና የብሄር ስብጥርን ያካተተ መሆን አለበት ብለዉ ደፍረዉ በመናገራቸዉ ነዉ።

የአፈናውና ሰቆቃው መጠናከር ለነጻነታችን ከምናደርገው ትግል አይገታንም።

የመንግሥትን በትረ ሥልጣን በጠመንጃ ሃይል ተቆጣጥረው ያሉት የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች ላለፉት 25 አመታት በህዝባችን ላይ ተንሰራፍተው  የዘረፉት የአገር ሃብት ፤ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ  በየባንኩ ያከማቹት ጥሬ ገንዘብና በዘመድ አዝማዶቻቸው ሥም እዚህና እዚያ የዘረጉዋቸው የንግድ ድርጅቶች ብዛት እንዲሁም ያለዕውቀታቸውና ልምዳቸው ለሩብ አመታት ሲሿሿሙበት የኖሩት ሹመትና ማዕረግ  አሁንም ቢሆን በቃኝ ከሚሉበት ደረጃ እንዳላደረሳቸው ሥልጣንን በሰላማዊ መንገድ እንዲያስረክቡ የተቃውሞ ድምጻቸውን በሚያሰሙ ወገኖቻችን ላይ እየወሰዱት ካለው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ መረዳት ይቻላል።

በአንድ ወቅት አገሪቱ ውስጥ ሰፍኖ የኖረው አስተዳደራዊ በደል የፈጠረው ህዝባዊ ብሶት ብረት እንዲያነሱ እንዳደረጋቸው በኩራት በመደስኮር ገድላቸውን በታሪክ መዝገብ ላይ ለማስፈር ደፋ ቀና እያሉ ያሉ እነዚህ ሃይሎች፡ አስመርሮናል ብለው መሳሪያ ካነሱበት ሥርዓት የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ ፤ በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የአገር ሃብት ዘረፋ ተግባር ላይ በጅምላ ተሰማርተው ሃብት ሲያካብቱ ፤ በአገሪቱ ባህልና ወግ የገዘፈ ልዕልናና ክብር የነበረውን የህግ የበላይነት ባህል አጥፍተውና በራሳቸው ተጽፎ የጸደቀውን ህገ መንግሥት ተላልፈው በጠራራ ጸሃይ ብዙዎችን ጎዳና ላይ ሲጨፈጭፉ፤ ሲያስሩና ሲያንገላቱ ፤ ከአያት ቅድመ አያቱ ጀምሮ እትብቱ ከተቀበረበት ቀዬ ሺዎችን አፈናቅለው መሬቱን ሲቀራመቱና  ከአቅማቸው በላይ የሆነውን ለባዕዳን በርካሽ ዋጋ በመቸብቸብ ለጎዳና ተዳዳሪነት ሲዳርጉት ከማየት የበለጠ ወንጀልና ህሊናን የሚያቆስል ኢፍትሃዊነት በዚህች ምድር አይኖርም።

ይህ ሁሉ ግፍና መከራ እየተፈራረቀበት ያለውን ህዝብ በትግላችን ውጤት ፍትህና ርትዕ አቀዳጅተንሃል፤ በብሄር ማንነትህና በምትናገረው ቋንቋ እንድትኮራ አድርገንሃል፤ ተገፍተህባት የኖርክባት አገር ባለቤት እንድትሆን አስችለንሃል ፤ዲሞክራሲን በአገራችን እውን በማድረግ በየ5 አመቱ በምትመርጠው መንግሥት የምትተዳደርበት ሥርዓት ዘርግተንልሃል ፤ ደሃውን ህዝብ ተጠቃሚ ያደረገ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማውጣት በምድራችን ፈጣን የሆነ ልማትና ዕድገት አስገኝተንልሃል፤ በዚህም የተነሳ ከኖርክበት ረሃብና እርዛት መላቀቅ ብቻ ሳይሆን በአጭር ግዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ልናሰልፍህ ነው ፤ ወዘተ እያሉ ሲያላግጡበትና ሲዘባበቱበት ማየት እጅግ የሚያሳምም ነው።

ላለፈው አንድ አመት አገሪቷ ውስጥ እጅግ ተጠናክሮ የቀጠለውና ወያኔ በፈረጠመ ክንዱ ለመጨፍለቅ ያለ የሌለ ሃይሉን ለመጠቀም ደፋ ቀና እያለ ያለው ህዝባዊ እምቢተኝነት መሠረቱ ይህ ለሩብ አመታት በአገራችንና በህዝባችን ላይ ተንሰራፍቶ የቆየውን ኢፍትሃዊነት፤ አፈናና ጭቆና ከህዝባችን ጫንቃ አሽቀንጥሮ ለመጣል የሚደረግ የነጻነት ትግል ነው።  ይህንን ትግል ለማፈን ህወሃት ከአለም አቀፍ ለጋሽ አገሮች በተሰበሰበ ገንዘብ ከምዕራባዊያን ወዳጆቹ፤ ከራሺያና ከቻይና የፈለገውን ዘመናዊ የጦር መሣሪያ በግዢ ቢያግበሰብስ፤ የአገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም የተቀጠረ እልፍ አእላፍ  የአጋዚ ወታደርና ልዩ ጦር በየመንደሩ ተሰማርቶ የታዘዘውን ያህል አፈና፤ ግዲያና እስራቱን ቢያጧጡፍ የሚቻል አይሆንም። በገዛ አገራችን እንደሁለተኛ ዜጋ እየተቆጠርን ከሥራ ፤ ከመኖሪያ ቀያችንና ከትውልድ መንደራችን መፈናቀል ሰልችቶናል። ልጆቻችን በገዛ አገራቸው ተስፋ ቆርጠው እንጀራ ፍለጋ  በረሃ ሲያቋርጡ በጨካኞች እጅ እየወደቁ በአክራሪዎች ሰይፍ እንደከብት መታረዳቸውን ማስቆም ከኛ ውጪ ለሌላ ለማንም የተሰጠ ሃላፊነት አይደለም። ከአሁን ቦኋላ የአገራችን የኢትዮጵያ ምድር የሚቆረቆሩላትን ልጆቿን እየቀበረች የጠላትን ህልም ለማሳካት ሊያጠፏት ሌት ተቀን የሚማስኑ ባንዳ ልጆቿን እሽሩሩ የምትልበት ዘመን ማብቃት ይኖርበታል።

አርበኞች ግንቦት 7 የህወሃት አገዛዝ ህዝባችንን በቋንቋና በዘር ከፋፍሎ እርስ በርሱ በማናከስ ለዘመናት የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ሲሰራው የነበረው የተንኮል ሴራ ሁሉ ከሽፎአል ብሎ ያምናል። የጎንደርና የባህርዳር ህዝብ ባሰማው ተቃውሞ በህወሃት አልሞ ተኳሾች ጥይት የሚሞተው ኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው ሲል በአርሲ፤ በቢሾፍቱ፤ በደምቢዶሎና በተለያየ የኦሮሚያ ክልል የሚኖረው ህዝብ አማራ ወገናችን ነው ከአሁን ቦኋላ እትለያዩንም፤ አንድ ነን ሲል ድምጹን ከፍ አድርጎ አሰምቷል። ይህ የወንድማማችነትና የአንድነት መንፈስ ህወሃትን ያሸብረዋል ብቻ ሳይሆን እንዳበደች ውሻ ያቁነጠንጠዋል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ የህወሃት ወታደራዊ መኮንኖች ሥልጣን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ሥር ያደረጉበት የኮማንድ ፖስት የተቋቋመው ይህ የወንድማማችነትና የአንድነት መንፈስ ሊፈጥረው የሚችለውን ህብረት በጠመንጃ ሃይል ከወዲሁ ለመቅጨት ነው። በመላው አገሪቱ በተለይም በአማራ፤ በኦሮሚያና በኮንሶ በርካታ ሺዎችን ሰብስቦ በማጎር ፤ የታሠሩትን በጉልበት ወይም በጊዜያዊ ጥቅም በመደለል ቅስም መሥበር በስፋት የተያያዘውም የህብረትና የአንድነት ድምጽ ጎልቶ መሰማት ከጀመረ ወዲህ መሆኑ ግልጽ ነው። ከአንድ ወር የጅምላ  እስር ቦኋላ ሰሞኑን የተለቀቁ 9 ሺህ ለውጥ ፈላጊዎችን “አይደገምም” የሚል ጽሁፍ የተጻፈበት ነጭ ካናቴራ ማልበስ በህወሃት ቤት ማሸማቀቅ ነው። ካለፈው ስህተቱ መማር ያልፈጠረበት  ወያኔ በምርጫ 97 የንብ አርማ አልብሶ ለድጋፍ ሰልፍ መስቀል አደባባይ ያወጣው በሚሊዮን የሚቆጠር የአዲስ አበባ ህዝብ በማግሥቱ ካናቴራውን እንደለበሰ ለቅንጅት ሰልፍ ወጥቶ ጉድ እንዳደረገው ዘንግቶታል። ጮማና ውስኪ አዕምሮአቸውን ለሸፈናቸው ኋላ ቀር የህወሃት አመራሮች “አይደገምም” የሚል ካናቴራ በማልበስ ወደየቤታቸው ለሸኟቸው ታሳሪዎች ህዝባችን በነቂስ ወጥቶ ያሳየው ድጋፍና ደማቅ አቀባበል ሚያዚያ 30,1997 ቀንን የደገመ ትዕይንት መሆኑን እንዲረዱ አያስችላቸውም።

ህወሃት ህዝባችን ለነጸነቱ የሚያካሂደውን ትግል ለመቀልበስ የፈለገውን ያህል ጉልበት ለመጠቀም ቢፍጨረጨር ፤ እስር ግድያና የማሳደድ ተግባሩን አጠናክሮ ቢቀጥል ከህዝባችን ልብ የበለጠ እየራቀ፤ የጥላቻና የበቀል እርምጃ የሚቀሰቅስ ወኔ ለምናካሄደው ትግል ይፈጥር እንደሆነ እንጂ ከጀመርነው የነጻነት ትግል ወደ ኋላ እንደማይገታን አርበኞች ግንቦት 7 በጽናት ያምናል። ፍትህ እኩልነትና ነጻነት የሰፈነበት አገር ባለቤት ለመሆን የጀመርነው ትግል የፈለገውን ዋጋ ቢያስከፍለንም በድል ይጠናቀቃል። ለዕለት ጉርሳቸው ሲሉ በውትድርና ተቀጥረው ለህወሃት የሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ ውድ ህይወታቸውን እየገበሩ ያሉ ምስኪን ወገኖቻችን እየተካሄደ ያለው ትግል ለነርሱም ነጻነት መሆኑን ተረድተው የያዙትን መሣሪያ የደሃውን ልጅ እየገደሉና እያስገደሉ የማይጠረቃ የሃብት ዘረፋ ጥማታቸውን ለመወጣት በሚያዘምቷቸው አለቆቻቸው ላይ እንዲያዞሩና ትግሉንም እንዲቀላቀሉ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪውን ያቀርባል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!