Sunday, June 29, 2014

የወያኔን የጥፋት ድግስ እናምክን!

ኢትዮጵያን የሚገዛው ጉጅሌ ሀገራችንን እየወሰደበት ያለው አደገኛ አቅጣጫ አሳሳቢ ከመሆን አልፎ የአደጋውን መራራ ፍሬ ማየት ከጀመርን ሰነበትን። የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ወሳኝ ከሆነው የወደፊቱ የጋራ ጥቅማቸውና ህልውናቸው በበለጠ ልዩነታቸውና ያለፈ ታሪካቸው እንደዋናው ነገር እየተቆጠረ ለሚሰበከው ስብከት የኢትዮጵያ ህዝብ አስተዋይ ባይሆን ኖሮ እስካሁን ብዙ ጥፋት በደረሰ ነበር።

ህወሃት በህዝቡ ውስጥ የኖረውን ልዩነት የጠብ፣ የግጭትና የመፈራራት መሰረት በማድረግ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ካለው ምኞት የተነሳ በመደዴ ካድሬዎቹ አማካኝነት ለዘመናት አብሮ የኖረውን ህዝብ በማቃቃር እኩይ ተግባር ላይ ተጠምዶ ይገኛል።

ህወሃት ይህን የማጋጨት ስራ በተለይ በስልጣን የመቆየት ፍርሃት ባባነነው ቁጥር የሚጠቀምበት መሳሪያ አድርጎታል። በባህርዳር ላይ የብሄረሰቦች ኳስ ጭዋታ ውድድር ምክንያት አድርጎ፣ መደዴ ካድሬዎቹን አሰማርቶ ስታዲዮም ውስጥ ኦሮሞዎች እንዲሰደቡ ካደረገ በኋላ ነገሩን ከማረጋጋት ይልቅ በኦሮሞኛ የቴሌቪዥንና ሬድዮ፣ ኦሮሞዎች በአማራዎች ተሰደቡ ብሎ ያስነገረው ለምንድን ነው? ከዚያ በኋላ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ቁጣና ጠብ ለመቀስቀስ ብሎም በዚህ ጠብ ውስጥ ገላጋይ በመምሰል የአንዱ ብሄር ጠባቂ መስሎ ለመታየት ጉዳዩን ባልተረዱ የዋሆች ውስጥ ለመግባት ይፈልጋል። በአማራ ተወላጆች አካባቢ እኛ ከሌለን ኦሮሞ ይፈጇቹኋል፤ በኦሮምያም በሶማሊያም እንዲሁ በተዘጋ በር ውስጥ በተቃራኒው ዘረኝነትንና መከፋፈልን በመስበክ ንጹሃኑ ህዝብ ከፍርሃት ተነስቶ ተገዥ ደጋፊዎቹ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ መሆኑንም ያልገባቸው የዋሆች ይኖራሉ። ህወሃትንና ባህርዩን በቅጡ ለምናውቀው ወገኖች ግን ይህ ተንኮሉ ትልቅ ሚስጥር አይደለም።

የጉጅሌው ቡድን የራሱን ስልጣንና የዝርፊያ ኢኮኖሚ ኮርቻ ለማደላደል እስከረዳው ወይም የሚረዳው መስሎ እስከታየው ድረስ ደሃ ገበሬዎችን ማፋጀትን፣ ህዝብን እርስበርስ ማናከስን፣ የቂም መርዝ መዝራትን የሚያየው እንደ ፖለቲካ ጥበብ ነው።

ጉጅሌው ብልጠት መስሎት የጎሰኝነትንና የማንነትን ደመነፍስ የሚነካ ፕሮፖጋንዳ በህዝቡ ውስጥ በመንዛት ሊያደርስ የፈለገው ጥፋት በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ስላልሰራለት የራሱን ሎሌዎችና ተካፋይ መደዴ ካድሬዎችን በማሰማራት የጭካኔ ስራዎችን በማካሄድ ላይ መሆኑን በብዙ መረጃዎች አረገጋግጠናል። በአሁኑ ወቅት በየቦታው የሚካሄደውን የህዝብ ማፈናቀልና ግጭት የሚመራው ራሱ ህወሃት ያሰማራቸው ካድሬዎች እንጂ በራሱ በህዝቡ ተነሳሽነት እንዳልሆነ ሁላችንም ልናውቅ ይገባል። በዚህ ሳይጣናዊ አካሄድ ለምትደርሰው ለያንዳንዷ ጉዳት ሀላፊነት የሚወስደውም ራሱ ህወሃት መሆኑን ግንቦት 7 አጥብቆ ያምናል።

ህወሃት መቃብር አፋፍ ላይ ሆኖ የሚደግስልንን የጥፋት ድግስ ለማምከን የየብሄረሰቡ ልሂቃን ሁሉ አንድ ላይ ሆነን ህዝባችንን እንድንታደግ ግንቦት 7 ለሁሉም የነጻነት ሃይሎች ጥሪውን ያቀርባል።

ግንቦት 7 በዚህ የህወሃት የጨለማ መንገድ ላይ የሚያበራውን የብርሃን ችቦ ይበልጥ በማብራት ላይ ይገኛል። ሁላችንም በምናገኘው የብርሃን ሃይል ጨለማው ላይ እያበራን ከማሳየት አልፈን ወደ መቃብሩ ልንገፋው ይገባል።

ግንቦት 7 በኢትዮጵያ የማንነትና የብሄር ብሄረሰብ ጉዳዮች በሰለጠነ መንገድ እና በመደማመጥ ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደረግ መንገድ መፍታት እንደሚቻል ያምናል። ይልቁንም የወደፊቱ የህዝባችንና የሀገራችን ጥቅም ይበልጥ የሚከበረው በስብጥርነታችን ላይ በምንገነባው አንድነት መሆኑን ያምናል።

የተከበራችሁ የአገራችን ዜጎች የነጻነታችን ጊዜ ቅርብ ነው። ህወሃት መቃብር አፋፍ ላይ ሆኖ ያዘጋጀልንን የጥፋት ድግስ፣ ሀገራችን የጋራ ጠላት በመጣባት ጊዜ ሁሉ እንደምታደርገው በአንድ ላይ ታግለን የጋራ ታሪክ እንሰራ ዘንድ የዘወትር ጥሪያችን እናቀርባለን።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!



Wednesday, June 25, 2014

ቀና ብለን የምንሄድበት ጊዜ አየመጣ ነው! ጎበዝ ተነሳ!

ጉጅሌዎቹ አይገባቸውም እንጂ የኢትዮጵያ ከተሞችና ገጠሮች የለውጥን ደመና ኣርግዘዋል። ወንዞችም ተራሮችም የለውጥ ማዕበል ማቆብቆቡን አያበሰሩ ናቸው። የቀደሙት ገዢዎች መረጃ የሚያገኙት እረኛ ምን ይላል ብለዉ እየጠየቁ ነበር። የአሁኖቹ አገር አጥፊ ገዢዎች ምሳሌ ያደረጉት ካድሬዎቻቸውን ብቻ ሆነ እንጂ ዛሬም የአገራችን እረኞች የለውጥን መምጣት በሚያምር ቅላጽያቸው አያንጎራጎሩ እንዲህ አያሉን ነው፣

የሀገሬ ጉብል የሰማውን እንጃ

የጎንደሬው ጉብል የሰማውን እንጃ

ከብቱን አየሸጠ ገዛ ኣሉ ጠብመንጃ።

የወለጋው ጉብል የሰማውን እንጃ

ቡናውን ሻሽጦ ገዛ ኣሉ ጠብመንጃ።

መልእክቱ ግልጽ ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶች አገራቸውን በክቡር ደማቸው ሊታደጓት ቆርጠው በመነሳት ወያኔን በማስወገድ የሀገራቸው ባለቤት ለመሆንና ያልተከፋፈለች ውብ ኢትዮጵያን ማየትን ለማረጋገጥ ጥርጊያውን መጀመራቸው ነው።

ላለፉት ፵ አመታት አምባገነኖች ባደረሱብን ጭቆና እና እንግልት የተነሳ የራሳችን የሆነ መንግሥት ሳይኖረን አንገታችንን ደፍተን ጀግኖቻችንን ስንገብር ኖረናል። በተለይም ባለፉት ፪፫ አመታት ጉጅሌዎቹ በአራት ኪሎ ከነገብን ጀምሮ በአንድ ላይ አንዳንቆም በማድረግና እና አርስ በራሳችን በማጋጨት ሲያባሉን ኖረዋል።

ዛሬ ሁኔታዎች ተለውጠዋል፤ በውጭም በአገር ውስጥም ለውጥ አየታየ ነው። የእንቅስቃሴው ማእበል አይሎ እየመጣ ነው። ዛሬ ሁሉም የዴሞክራሲ ሀይሎች ማለት በሚቻል ደረጃ በሁለት ነገሮች ላይ ስምምነት አለ፣

፩. ተቃዋሚዎች በግል ከሚያደርጉት ትግል ይልቅ በጋራ የመሰባሰብን አስፈላጊነት ተረድትው መሰባሰብ መጀመራቸው

፪. በአንድ ላይ መሰባሰብ ካልቻሉም እርስ በራስ ላለመጠላለፍ መስማማት መቻላቸውና አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ግዜ ሁሉ መረዳዳት መጀመራቸውና በግልም ከወያኔ ጋር የሚደረገውን ትግል ማፋፋም የቻሉበት ሁኔታ አየታየ መሆኑ የሕዝብ ወገኖችን እያስደሰተ ይገኛል።

በአገር ቤት የሚገኙ የዴሞክራሲ ኃይሎችም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሕዝቡ ከፍርሀት ተላቆ ለመብቱ አንዲነሳ የሚያደርጓቸው አንቅስቃሴዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ መጥተዋል። ለዚህም በቅርቡ በአዲስ ኣበባ መድረክ፣ ኣንድነትና ሰማያዊ ፓርቲዎች የጠሯቸው ሰልፎች ይበል የሚያስብሉ ናቸው።

ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ በዚሀ ኣጋጣሚ ለዴሞክራሲና ለነፃነት ታጋዮች ሁሉ ያለውን አክብሮትና ኣድናቆት ይገልጻል።

በሌላም በተለያዩ አቅጣጫዎች ወያኔን በኣመጽ ለመፋለም የወሰኑ ኃይሎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ወያኔን ለመፋለም ቆርጠው በጋራ ክንዳቸውን ኣቀናጅተው ለመፋለም አየተዘጋጁ ያሉበት ሁኔታ አበራታች ነው። እነዚህ ኃይሎች አዳዲስ የነጻነት ታጋይ አርበኞችን በተከታታይ በማስመረቅ ያሉ መሆናቸውና ከዚህም በተጨማሪ ከመላው የአገሪቱ አካባቢዎች ወጣቶች በገፍ ትግሉን እየተቀላቀሉ መሆኑን ስንሰማ ልባችን በደስታ ይሞላል።

በወያኔ ጉያ ውስጥ ያሉ የሕዝብ ወገኖች ደግሞ የቻሉትን በውስጥ ሆነው መቃብሩን እይቆፈሩለት ሲሆን፣ ያልቻሉትም የወያኔን ሚስጢር ይዘው በመውጣት የሕዝብ ወገንተኝነታቸውን አየገለጹ ይገኛሉ።

ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ለመላው ሕዝባችንና በተለይም ለወጣቱ ትውልድ በተደጋጋሚ አንደሚለው የሀገራችን ባለቤት ለመሆን የምናደርገውን ትግል ተቀላቀሉ!!! መቀላቀል ያልቻላችሁም በኣካባቢያችሁ ከምታምኗቸው ወገኖቻችሁ ጋር ተሰባሰቡ፣ በህዋስ ተደራጁ። ግንቦት 7 በዚህ ትግል የዳር ተመልካች ሳይሆን መሪ እንድትሆኑ ኣገራዊ ጥሪውን ያቀርባል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

Saturday, June 14, 2014

የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞችንና ጦማርያንን ማን ይፈራቸዋል?

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ እስክንድር ነጋን፣
 ርዕዮት ዓለሙን፣ ውብሸት ታዬን፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎችን…ማን ይፈራቸዋል?
bloggersየኢትዮጵያ የነጻው ፕሬስ እና ጦማርያን ቁንጮ የሆነው እስክንድር ነጋ ሀሳቡን በነጻ በመግለጹ ብቻ በአምባገነኑ የወሮበላ ቡድን ስብስብ የይስሙላው የዝንጀሮ ፍርድ ቤት የ18 ዓመታት እስር ተበይኖበት በገዥው አካል የማጎሪያ እስር ቤት በመማቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ሟቹ መለስ ዜናዊ ልዩ ትዕዛዝ እስክንድር ነጋ በቁጥጥር ስር እንዲውል እና የ18 ዓመቱ የሸፍጥ እስራት እንዲበየንበት ተደርጓል፡፡ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ማናቸውም ጋዜጠኞች የበለጠ እስክንድር ነጋን ይፈራዉና ይጠላው ነበር፡፡ ዝሆን አይጦችን “ይፈራል” ከሚለው ኢ-ስነ አመክንዮ አንጻር በተመሳሳለ መልኩ መለስም እስክንድር ነጋን እንደጦር ይፈራው ነበር፡፡
በቅርቡ እስክንድር ከማጎሪያው እስር ቤት ለ8 ዓመት ልጁ ለናፍቆት እንዲህ የሚል ግልጽ ደብዳቤ ጽፏል፣ “እንዲያው ሁኔታውን ሳየው እያለሁ የሌለሁ የዘፈቀደ አባት ሆኛለሁ፣ ምክንያቱም በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፈረንሳዮች ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍቅር እያሉ ደጋግመው ይጠሯቸው የነበሩትን ሶስት ቀላል ቃላትን በመውሰድ እኔም በሀገሬ ነጻነት፣ እኩልነት እና ፍቅር እንዲሰፍን በማሰብ እነዚህን ቃላት በማስተጋባቴ ነው በሸፍጠኞች ለእስር የተዳረግሁት“ ብሏል፡፡ እስክንድር ለነጻነት፣ ለእኩልነት እና ለአብሮነት ፍቅር ጦማሪ ነው፡፡ ለዚህም ነው ለእኔ የጀግናዬ ተምሳሌት የሚሆነው!
የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ቀንዲል ጀግናዋ የ34 ዓመቷ ወጣት ርዕዮት ዓለሙ በተመሳሳይ መልኩ በአቶ መለስ ዜናዊ የ14 ዓመታት እስር በይኖባታል፡፡ ይህች ጀግና ወጣት በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ዘንድ “እውነት ተናጋሪዋ ኢትዮጵያዊት እስረኛ” በመባል ትታወቃለች፡፡ ርዕዮት ለእስር የተዳረገችው የግድብ ፕሮጀክት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን በተመለከተ በገዥው የፖለቲካ ፓርቲ ላይ ጠንካራ ትችት በማቅረቧ እና በቅርቡ በህይወት የተለዩት የሊቢያ አምባገነን መሪ ሙአማር ጋዳፊ እና መለስ ዜናዊ ከአንድ ባህር የሚቀዳ ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸው መሆናቸውን በይፋ በመግለጿ ነው፡፡ ርዕዮት በእስር ቤት ተዘግቶባት እና አፏን ተሸብባ ለመቀመጥ ባለመፍቀድ በድፍረት አንገቷን ቀና አድርጋ ስልጣኖቻቸውን ከህግ አግባብ ውጭ በህገወጥነት ለሚጠቀሙት ህገወጦች እና ትዕቢተኞች እውነት እውነቱን እንዲህ በማለት እቅጬን ተናግራለች፣ ”የተሻለች ኢትዮጵያን ለማየት እኔ በግሌ የሚጠበቅብኝን ሁሉ ማበርከት አለብኝ የሚል እምነት አለኝ፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ኢፍትሀዊነቶች እና ጭቆናዎች ተንሰራፍተው ስለሚገኙ እነዚህን እኩይ ተግባራት በምጽፋቸው ትችቶቸ ማጋለጥ እና ከንቱ መሆናቸውን መቃወም አለብኝ… ለዚህ በጎ ዓላማ በድፍረት ትግል በማካሂድበት ወቅት ሊያስከፍለኝ የሚችለውን ዋጋ ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ“ በማለት ከእስር ቤት አፈትልከው በሚወጡ የእጅ ጽሁፎቿ ገልጻለች ጀግናዋ ርዕዮት ዓለሙ፡፡ በማይበገረው እና በማይንበረከከው ትክክለኛ የጽናት አቋሟ ምክንያት ገዥው አካል ሰብአዊነት የሚባለውን ክቡር ነገር በመደፍጠጥ የህክምና አገልግሎት እንዳታገኝ ቅጣት ጥሎባታል፡፡ መቀመጫውን ሎንዶን ያደረገ የህግ መከላከል የተነሳሽነት ሜዲያ/Media Legal Defense Initiative የተባለ ተቋም በአልጃዚራ ባቀረበው ዘገባ መሰረት ርዕዮት “በሰውነት አካሏ ላይ የተከሰተ እብጠት የተገኘ ቢሆንም ተገቢ የሆነ ህክምና እየተሰጣት እንዳልሆነ ግልጽ አድርጓል፡፡ ምንም ዓይነት የሰመመን መስጫ ማደንዘዣ ሳይሰጣት በጡቷ ላይ የቀዶ ህክምና ስራ በማከናወን የቀዶ ህክምና መስፊያ ክሩ ከጡቷ ሳይወጣ ከዓመት በላይ ከመቆየቱም በላይ ከደህረ ቀዶ ህክምናው በኋላም ቢሆን ተገቢ የሆነ ህክምና የተሰጣት አይደለም“ ብሏል፡፡ ለእኔ ርዕዮት የጀግና ተምሳሌታዬ ናት!
የማይበገረው ጋዜጠኛ እና አርታኢ ውብሸት ታዬ የመናገር አንደበቱን ተሸብቦ በመለስ ዜናዊ ዝዋይ በሚባል አስፈሪ እና ጭራቃዊ የማጎሪያ እስር ቤት በመማቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ በእርሱ ላይም የ14 ዓመታት እስራት ተበይኖበታል፡፡ ውብሸት የገዥውን አካል ሙስና እና ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀምን አስመልክቶ በጋዜጣ ላይ የሚያቀርባቸውን ትችቶች እና አስተያየቶች በፍጹም አያቋርጥም፡፡ ውብሸት ለሚጠዘጥዝ የኩላሊት ህመም ተጋልጦ የሚገኝ ቢሆንም እርሱም ህክምና እንዳያገኝ ተደርጎ በመሰቃየት ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ በማጎሪያው እስር ቤት ለሚገኙት የህሊና እስረኞች የህክምና አገልግሎት መንፈግ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል እለት በእለት የሚፈጽማቸው በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ የቅጣት ወንጀሎች ናቸው፡፡ ፍትህ እየተባለ የሚጠራው የውብሸት የአምስት ዓመት ልጅ እንዲህ በማለት ጥያቄ በማቅረብ ላይ ይገኛል፣ “ሳድግ እና ለአቅመ አዳም ስደርስ እኔም እንደ አባቴ ሁሉ ወደ እስር ቤት እጋዛለሁን?“ ሕፃኑ ፍትህ በአሁኑ ጊዜ አጥር የሌለው እስር ቤት ውስጥ እየኖረ መሆኑን ሊገነዘብ አይችልም፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት “የኢትዮጵያ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች” (የፖለቲካ እስረኞችን ከያዘው ከመሀል ከተማ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኘው የ “መለስ ዜናዊ ታዋቂው የቃሊቲ እስር ቤት” ህንጻዎች ቀጥሎ የተሰየመ) እና ሌሎች ጋዜጠኞች በስም አጥናፍ ብርሀኔ፣ ዘላለም ክብረት፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋቤላ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ተስፋለም ወልደየስ እና ኤዶም ካሳዬ የክሱ ጭብጥ ባልታወቀበት ሁኔታ ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር ውለው ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ፖሊስ በእነዚህ ጦማሪያን እና ጋዜጠኞች ላይ ምን ዓይነት ክስ መመስረት እንዳለበት ገና በመለግ ላይ ይገኛል፡፡
(የገዥው ቡድን ፖሊስ የሚጠረጥረውን ዜጋ በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር አውሎ እና እስርቤት በማጎር እያሰቃዬ ተሰራ ለተባለው ጥፋት ማስረጃ እና መረጃ በመፈለግ በዜጎቿላይ ሰብአዊ መብትን በመደፍጠጥ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ብቸኛዋ አገር ናት!!!የይስሙላዎች የዝንጀሮ ፍርድ ቤቶች በዘፈቀደ ከህግ አግባብ ውጭ በቁጥጥር ስርለዋሉት ዜጎች ዋስትና በመንፈግ ፖሊስ እና አቃቤህግ የሚባሉ የገዥው አካልየማጥቂያ መሳሪያ ሎሌዎች የሚፈበረኩ የፈጠራ ውንጀላዎችን አቀነባብረውእስኪያቀርቡ ድረስ የተንዛዙ እና አሰልቺ የሆኑ ማያልቅ ቀጠሮዎችን በመስጠት እናየይስሙላውን ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደት ከሚገባው በላይ በማዘግየት በንጹሀን ዜጎችላይ የቁማር ጨዋታ በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ነው አነዚህን ፍርድቤቶችን “የይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤቶች እያልኩ የምጠራቸው፡፡” እውነተኛው የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ወንጀል ሀሳብን በነጻ በመግለጽ የሚያምኑበትን ነገር በነጻ ማራመዳቸው እና እነርሱ የተሻለች ኢትዮጵያ በማለት ስለሚጠሯት ኢትዮጵያ ህልም ማለማቸው ነው፡፡ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንን ጉዳይ የሚመለከተው በቅርቡ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የዳኝነት ችሎት ለህዝቡ እና ጉዳዩን በቅርበት ለሚከታተሉት የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ዝግ ነበር፡፡
እስክንድር ነጋን፣ ርዕዮት ዓለሙን፣ ውብሸት ታዬን፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንን…የሚፈሯቸው ለምንድን ነው?
ናፖሊዮን ቦና ፓርት የተባሉት የፈረንሳይ አምባገነን መሪ በዚያች አገር የነጻው ፕሬስ ላይ ጦርነት ባወጁበት ወቅት “ከአንድ ባታሊዮን ጦር ይልቅ አራት ተቃዋሚ ጋዜጦች የበለጠ ይፈራሉ“ የሚለውን እውነታ የበለጠ ግልጽ አድርጎታል፡፡ ላለፉት 23 ዓመታት በኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ እንደ መዥገር በስልጣን ላይ ተጣብቆ ለሚገኘው ገዥ አካል ኤኬ – 47 ከታጠቀ አንድ ባታሊዮን ጦር ይልቅ ብዕር እና የኮምፒውተር ኪይ ቦርድ የያዙ ጥቂት ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን የበለጠ ያስፈሩታል፣ በፍርሀት ቆፈን ውስጥ እንዲወሸቅ ያደርጉታል፣ ያርዱታል፣ ያስደነብሩታል፣ የሚይዝ የሚጨብጠውን ያሳጡታል፣ የቀን ቅዠት ይፈጥሩበታል፣ በላብ እንዲጠመቅም ያደርጉታል፡፡ በታሪክ መነጽር ሲታይ እና ሲገመገም ሁሉም አምባገነኖች እና ጨቋኞች የነጻውን ፕሬስ የእውቀት እና የክህሎት ኃይል አጥብቀው ይፈሩታል፡፡ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ተንፈራጥጠው የሚገኙት አምባገነኖች ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው ከታቀው እና በልዩ ልዩ የጦር ክፍሎች ተዋቅሮ በጠላት ላይ ቅጽበታዊ ድልን የመቀዳጀት አቅም ካለው እና የጠላትን ኃይል በማያንሰራራ መልኩ ከሚያደባይ የጦር ኃይል ይልቅ የነጻውን ፕሬስ የዕውቀት እና የክህሎት ኃይል አጥብቀው ይፈራሉ፡፡
ጠቅላላ የብዙሀን መገናኛዎችን እና ነጻውን ፕሬስ መቆጣጠር የገዥዎች እኩይ ምግባር ነው፡፡ የመረጃ ፍሰቶችን በመቆጣጠር በኃይል የሚገዙትን ህዝብ ልብ እና አእምሮ የተቆጣጠሩ እንደሚመስላቸው እምነት አላቸው፡፡ የብዙሀን መገናኛ ዘዴዎችን በመቆጣጠር እንደ በቀቀን እየደጋገሙ ከሚቀፈቅፉት ነጭ ውሸታቸው እውነትን የሚፈበርኩ ይመስላቸዋል፡፡ ነጻውን ፕሬስ አፈር ድሜ በማብላት ሁሉንም ህዝብ ሁልጊዜ ማሞኘት የሚችሉ ይመስላቸዋል፡፡ ሆኖም ግን “እውነት ለዘላለም ተቀብራ እንደማትቀር እና ግፈኞችም በጉልበት ነጥቀው በያዙት የስልጣን ዙፋን ወንበር ላይ ለዘላለም ተጣብቀው እንደማይቆዩበት ድንጋይ በሆነው ልባቸው ያውቁታል፡፡“ ሁልጊዜም ስልጣናቸውን የሚያጡ እየመሰላቸው እለት በእለት የውሸት ድሪቷቸውን እየደረቱ ኑሮ አድርገው ይዘውታል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ወንበር ላይ ተጣብቆ የሚገኘው አረመኔ አምባገነን ገዥ ከብዙ ዓመታት በፊት ናፖሊዮን ተጋፍጦት የነበረውን ዓይነት ሁኔታ ተጋፍጦ ይገኛል፡፡ “ጋዜጠኛ የህዝቡን እሮሮ የሚያሰማ፣ ስህተትን አራሚ፣ ምክርን የሚለግስ፣ የሉዓላዊነት ወኪል እና የአገሮች መምህር ነው፡፡“ ጋዜጠኛ “አገርን የሚያስተምር” ነው፣ መረጃን ለህዝብ የሚሰጥ ነው፣ ህዝቡን በእውቀት የማነጽ እና የማስተማር ኃላፊነት አለው፡፡ እንግዲህ እነዚህ እውነታዎች ነበሩ ናፖሊዮን ነጻውን ፕሬስ እንዲፈሩት ያስገደዳቸው፡፡ የነጻው ፕሬስ ኃይል የናፖሊዮንን አምባገነናዊ አገዛዝ ትርጉም ባለው መልኩ እንደሚያጋልጠው እና በህዝቡ ዘንድ ተጠያቂ እንደሚያደርገው ናፖሊዮን ይገነዘቡ ነበር፡፡ ናፖሊዮን የፈረንሳይን ህዝብ ለማስፈራራት በማሰብ መጠነ ሰፊ የሆነውን የስለላ መረባቸውን በመዘርጋት ሲያካሂዱት የነበረውን ስለላ ሲያጋልጡ የነበሩትን ጋዜጠኞች ለማስፈራራት፣ በእስር ቤት ለማጎር፣ በስራዎቻቸው ላይ ቁጥጥር ለማድረግ እና አንደበታቸውን ለመሸበብ ጊዜ አላባከኑም፡፡ ነጻው ፕሬስ የናፖሊዮን ወታደራዊ እቅድ መክሸፉን አጋልጧል፡፡ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ባልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ማንንም ሳይለይ በጅምላ በዋና ዋና መንገዶች ላይ የተካሄዱትን ጭፍጨፋዎች እና የእርሳቸው የፖለቲካ ተቀናቃኝ በሆኑት ቡድኖች እና ግለሰቦች ላይ የተካሄደውን እስራት፣ ማሰቃየት እና ግድያ አውግዟል፡፡ በኢትዮጵያ እንደ መዥገር በስልጣን ወንበር ላይ ተጣብቀው የሚገኙት አምባገነኖች በናፖሊዮን ቅዠት በመውደቅ በተመሳሳይ መልኩ ወጣት ጦማሪያንን እና የነጻው ፕሬስ አባላትን ያስራሉ፣ ያሰቃያሉ፡፡ እውነታውን በመፍራት እንቅልፋቸውን አጥተው በነጭ ላብ ተዘፍቀው ያድራሉ!
የኢትዮጵያ ጦማሪያን እና ጋዜጠኞች ልዩ የኢትዮጵያ ጀግናዎች እና ጀግኒቶች ናቸው፡፡ የእውነት ተናጋሪ ተዋጊዎች ናቸው፡፡ አረመኔ አምባገነኖችን በብዕሮቻቸው እና በኮምፒውተር ኪቦርዶቻቸው ይዋጋሉ፡፡ የእነዚህ ወጣቶች ጥይቶች እውነት፣ ቃላት፣ ሀሳቦች፣ እውነታዎች እና እምነቶች ብቻ ናቸው፡፡ የተንሰራፉትን ውሸቶች በእውነት ጎራዴ ይከትፏቸዋል፡፡ መጥፎ እና መሰሪ ሀሳቦችን በጥሩ ሀሳቦች ያሳድዷቸዋል፣ እናም ያረጁ እና ያፈጁ፣ እንዲሁም የጃጁ፣ እና የበከቱ አሮጌ አስተሳሰቦችን በአዲስ እና ተራማጅ በሆኑ አስተሳሰቦች ለመተካት የማስተማር ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የህዝቦችን ተስፋቢስነት በመዋጋት በተስፋ ቃላት ያለመልማሉ፡፡ ፍርሀት በጀግንነት እና በደፋርነት ድል እንደሚመታ ለህዝቡ ያስተምራሉ፡፡ ድንቁርናን እና ኃይለኛ ደንቆሮዎችን በእውቀት እና በምክንያታዊነት ይዋጋሉ፡፡ በእብሪት እና ትእቢት ለተወጠሩት የገዥው አካል አባላት በሰለጠነ መልኩ ለማስተማር እና ለማግባባት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ትዕግስትየለሽነትን በታጋሽነት፣ ጭቆናን ከመሸከም በጽናት ታግሎ በማስወገድ እና በጥርጣሬ ከመሸነፍ በሙሉ እምነት አሳድሮ ድል በመምታት ለመቀየር ይፈልጋሉ፡፡ የህዝቡን ልብ እና አእምሮ ለመያዝ በሚደረገው የትግል አውድ እንደ ወሮበላው የገዥ አካል ስብስብ በተራ የውሸት ፕሮፓጋንዳ እና በኃይል በጉልበት ጨፍልቆ ለመያዝ ሳይሆን እውነታውን እና እውነቱን ብቻ ለወገኖቻቸው በማሳየት በብዕሮቻቸው እና በኮምፒውተር ኪቦርዶቻቸው ይታገላሉ፡፡
ክህደት፣ ውሸት እና ፍርሀት በተንሰራፋባት ምድር ላይ መኖር፣
በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል እውነት ውሸት በሆነባት፣ እውነት በእየለቱ በምትደመሰስባት እና ሸፍጠኛ አታላዮች በፍርሀት ተዘፍቀው የሚኖሩባት የእራሳቸውን ምድር ፈጥረዋል፡፡ ገዥው አካል እንዲህ የሚለውን የካርቴሲያንን መርህ አዛብቷል፣ “በኛ አስተሳሰብ ብቻ ነገሮች ሁሉ ህልውና ይኖራቸዋል ወይም ደግሞ ህልውና አልባ ይሆናሉ“፡፡ መለስ ዜናዊ የክህደት አለቃ ነበር፡፡ ሁልጊዜ በሱ የማጎሪያ አስር ቤቶች ውስጥ ምንም ዓይነት የፖለቲካ እስረኛ የለም በማለት ሽምጥጥ በማድረግ ይክድ ነበር፣ እንዲህ በማለት፣ “በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የፖለቲካ እስረኛ የለም፡፡ በእስር ቤት ያሉት አመጸኞች እና አሸባሪዎች ናቸው፡፡ እናም በእስር ቤቶቻችን የፖለቲከ እስረኞች አሉ ብሎ ለመግለጽ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው ምክንያቱም የፖለቲካ እስረኞች አይደሉምና፡፡ በሱ የንጉስነት ወቅት ምንም ዓይነት ረሀብ እና ቸነፈር እንዳልነበረ ሙልጭ አድርገው በመካድ እንዲህ ብሎ ነበር፣ በጣም ጥቂት የሆኑ በጣት የሚቆጠሩ በምግብ እጥረት ጉዳት የደረሰባቸው በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ የወረዳ ኪስ ቦታዎች እና በሶማሊ ክልል አካባቢ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ብቻ ነው የነበሩት በማለት ዓይኔን ላፈር ብለዋል፡፡ በአገሪቱ ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ያፈጠጠ እና ያገጠጠ እውነታ ሙልጭ አድርገው በመካድ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት የሰብአዊ መብት ጥሰት የለም“ ብለዋል፡፡ ይህንን ለማስረገጥ በማሰብ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ኦጋዴን አካባቢ መንደሮችን አቃጥለዋል እየተባለ ውንጀላ ቀርቦብናል፡፡ ሆኖም ግን በእርግጠኝነት ልነግራችሁ እፈልጋለሁ፤ ኑስ አንድ መንደር እንኳ አልተቃጠለም፡፡ እናም እኔ እስከማውቀው ድረስ አንዲት ጎጆ አልተቃጠለችም፡፡ እኛ እየተከሰስን ያለነው በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ቀድሞ ከነበሩባቸው መንደሮች በማንቀሳቀስ ወደ መጠለያ ካምፖች በማስገባታችን ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ቅንጣት መረጃ ሊቀርብ አይችልም“ ብሎ ነበር፡፡ የአሜሪካ የሳይንስ እድገት ማህበር/American Association for the Advancement of Science በኦጋዴን መንደሮች ላይ የተካሄደውን የጅምላ የመንደሮች ማቃጠል ወንጀል በሳቴላይት ምስሎች የተረጋገጠው እውነታ ለመለስ ምድር ምናባዊ ህይወት ምንም አይደለም፡፡ አደናጋሪ የፕሬስ ህግ አዋጅ በማውጣት በደርዘን የሚቆጠሩ ምርጥ የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ለእስር እና ግዞት ሲዳረጉ የሌባ አይነ ደረቅ እንዲሉ በሀሰት በነተበው አንደበታቸው መልሰው “ከዓለም የተሻለ ምርጥ የፕሬስ ህግ” በማለት ያደናግራሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 የተካሄደውን አገር አቀፋዊ “ምርጫ” ተከትሎ መለስ ፓርቲው ምርጫውን በ99.6 በመቶ ያሸነፈ መሆኑን በኩራት ተናግሮ ነበር፣ ምክንያቱም ህዝቡ ፓርቲያቸውን የሚወደው ስለሆነ ነው በማለት አፋቸውን ሞልተው ተናግረው ነበር፡፡ አቶ መለስ የኦርዌላን/Orwellian የእንስሳት ትረካ ዓይነት እውነታን የሚያራምድ ሰው ነበር፡፡ ውሸቱን ለመንዛት ሲፈልግ “የፖለቲካ ቋንቋን በመጠቀም የለየለትን ነጭ ውሸት እውነት እንዲመስል አድርገው በማቅረብ፣ ግድያ መፈጸም ወንጀል እና የስነምግባር ዝቅጠት መሆኑ ቀርቶ የሚያስከብር እንደሆነ አድርገው በማቅረብ ነጩን ውሸት የእውነት ቅርጽን እንዲላበስ አድርገው በማስመሰል የማቅረብ የባዶ ብልጣብለጥነት አካሄድ መንገድን ይጠቀሙ ነበር፡፡”
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ወንበር ላይ ተቀምጠው አገሪቱን እያተራመሱ በመግዛት ላይ ስለሚገኙት ስብስቦች አንድ የማይካድ ሀቅ አለ፡፡ ሁሉም በፍርሀት ቆፈን ውስጥ ተወሽቀው ነው እየኖሩ ያሉት፡፡ ያገጠጠውን እና ያፈጠጠውን እውነታ አየፈሩ ነው በመኖር ላይ ያሉት፡፡ የነጻው ፕሬስ ኃይል እውነታውን የሚያጋልጥ ስለሆነ የነጻውን ፕሬስ ኃይል በመፍራት ነው እየኖሩ ያሉት፡፡ በአንድ ወቅት የእነርሱ የአመለካከት ፍልስፍና አለቃ ቁንጮ የነበሩት ቪላድሚር ሌኒን አንዳለው “የመናገር ነጻነት እና የፕሬስ ነጻነት ለምንድን ነው የሚፈቀደው? ለምንድን ነው መንግስት ትክክል ነው ብሎ ያመነበትን ነገር ሲሰራ ትችት እንዲቀርብበት የሚፈቅደው? ተቃዋሚዎችን የጠላት መሳሪያ እንዲሆኑ መንግስት መፍቀድ የለበትም፣ ሀሳቦች ከጠብመንጃ የበለጠ የገዳይነት ባህሪ አላቸው፡፡ ለምንድን ነው ማንም ሰው የማተሚያ ቤት እንዲገዛ እና የሚቀርቡ ሀሳቦችን አትሞ በማሰራጨት በስልጣን ላያ ያለውን መንግስት በተቀነባበረ ስሌት ለመተቸት እና ለማሳፈር እንዲችል የሚፈቀደው?“ ፡፡
እውነታውን በሚገባ ያውቁታል ምክንያቱም እውነታው ህዝቡን ነጻ እንዲሆንያ ደርገዋል፡፡ ነጻነትን ይፈራሉ ምክንያቱም አዲስ ሀሳቦችን ይፈራሉ፡፡ አዲስ ሀሳቦችን ይፈራሉ ምክንያቱም ለውጥን ይፈራሉ፡፡ ነጻ የሆነ ህዝብ የእውነትን ጥሩር ታጥቆ የሀሳብ ነጻነትን ተጎናጽፎ በእራሱ ፈቃድ የእራሱን የመንግስት ዓይነት ለመመስረት ሙሉ ነጻነት አለው፡፡
በኢትዮጵያ ላይ ስላለው ገዥ አካል ያለው እውነታ ምንድን ነው? እውነታው በሰው ልጆች ላይ ግፍን የፈጸሙ ወንጀለኞች ናቸው፡፡ ምንም ዓይነት ህጋዊነት የላቸውም፡፡ በጠብመንጃ ኃይል በጉልበት በስልጣን ወንበር ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው የሚገኙ አምባገነኖች ናቸው፣ ምርጫዎችን በመስረቅ እና በመዝረፍ ተመርጠናል እያሉ በማታለል ተክነዋል፣ በጥልቅ የሙስና ማእበል ውስጥ ተዘፍቀው የአገሪቱን ሀብት በማውደም ላይ ይገኛሉ፣ ስልጣናቸውን በህገወጥ መንገድ በመጠቀም ላይ ይገኛሉ፣ የህግ የበላይነትን በመደፍጠጥ በጫካው ህግ የሚገዙ ህገወጦች ሆነዋል፣ እውነታው ሲታይ በአጠቃላይ በሸፍጥ የታወሩ የጫካውን አስተዳደር ወደ መንግስታዊ አስተዳደርነት አዙረው ህዝብን በማተራመስ ላይ የሚገኙ የስግብግብ ወሮበላ ቡድን ስብሰቦች ናቸው፡፡ እውነታው በአጠቃላይ ሲታይ የአፍሪካን የጨካኝ ዘራፊነት ስርዓት በሀገራችን ላይ የሚተገብሩ ወሮበላ ዘራፊዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ወሮበላ ዘራፊዎች ነጻ ጋዜጠኞችን እና ጦማሪያንን ይፈራሉ ምክንያቱም እነዚህ ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪዎች አምባገነኖቹ የሚሰሯቸውን ወንጀሎች እና ሙስናዎች፣ የመከኑ እና የወደቁ ፖሊሲዎቻቸውን፣ የአቅም ድሁርነታቸውን እና ድንቁርናቸውን በማጋለጥ እውነታውን ያወጡባቸዋል፡፡ እነዚህ ጭራቃዊ ፍጡሮች በጫማቸው ስር እረግጠው የያዟቸው የግፍ ሰለባዎች ነጻ ቅዱስነት እና የያዙት ጸበል ስለሚያቃዣቸው ነጻ ጋዜጠኞችን እና ጦማሪያንን አጥብቀው ይፈራሉ፡፡ በያዙት ሁሉ ኃይል በመጠቀም እውነቱ ወጥቶ ለህዝብ እንዳይደርስ እና እንዳይታወቅባቸው ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም፡ የሳቴላይት ስርጭቶችን ሳይቀር አፍነዋል፣ የኢንተርኔት ግንኙነቶችን አቋርጠዋል፣ ጋዜጦችን በመዝጋት ጋዜጠኞችን በእየእስር ቤቶች አጉረዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት የአረብሳት ለዓለም አቀፉ የግንኙነት ህብረት/International Communication Union እና ለአረብ ሊግ/Arab League ኢትዮጵያ ስርጭቱን ያፈነች መሆኗን እና “ወንጀለኛውን ለመቅጣት አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ” እና በዚህ ህገወጥ ድርጊት ምክንያት ለደረሰው ጉዳት ወይም በዚህ ህገወጥ የአፈና ተግባር ምክንያት ወደፊት ለሚደርስ ማንኛውም አደጋ ተገቢውን ካሳ እንድትከፍል እንዲደረግ ተማጽዕኖውን አቅርቧል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ገዥው አካል በገበያ ላይ የቀሩትን እና በገዥው አካል ላይ ጠንካራ ጥችት የሚያቀርቡትን ጥቂት ጋዜጦች በየመንገዶች እያዞሩ የሚሸጡትን ጋዜጣ አዟሪዎችን እያሳደደ፣ እያስፈራራ እና በቁጥጥር ስር እያዋለ ይገኛል፡፡
እውነታው በኢትዮጵያ ሀሳብን በነጻ ከመግለጽ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ እየተካሄደ ላለው ጭቆና እና አፈና የቻይናዎች ስውር እጆች ያሉበት መሆኑ ነው፡፡ ቻይናዎች ለገዥው አካል የማፈኛ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ማቅረብ ብቻ አይደለም የሚያከናውኑት፡፡ ሆኖም ግን ለተንቀሳቃሽ ስልኮች እና ለኢንተርኔት አገልግሎት የመሰረተ ልማት ስራዎችም ግንባር ቀደም ተዋንያን ናቸው፡፡ የመረጃ ፍሰት ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ እና ወደ ኢትዮጵያም እንዳይገባ ለመገደብ እና ለማቋረጥ የአንድ መስኮት ፈጣን የአግልግሎት መስጫ ኪቶችን ይዘዋል፡፡ ከዛሬ ሁለት ዓመታት ገደማ በፊት የቀድሞዋ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሄላሪ ክሊንተን ዛምቢያን በመጎብኘት ላይ ሳሉ የቻይናውያን በአፍሪካ አህጉር ላይ ያላቸውን ሚና በማስመልከት እንዲህ ብለው ነበር፣ “በቅኝ ግዛት ዘመን ጊዜ መምጣት እና ለመሪዎቹ ገንዘብ በመስጠት የተፈጥሮ ሀብቶችን ከአፍሪካ መውሰድ ቀላል ነበር፣ በምትለቅቅበት ጊዜ እዚህ ላለው ህዝብ ምንም ነገር ትተህ አትወጣም፣ በአሁኑ ጊዜ አዲስ ቅኝ ተገዥነት በአፍሪካ ማየት አንፈልግም“ ብለው ነበር፡፡ እውነታው ግን ቻይናውያን በኢትዮጵያ መቆየታቸው እና የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት መያዛቸው ብቻ ሳይሆን ለገዥው አካል የቴክኒክ እገዛ በመስጠት፣ የኦዲዮ እና ቪዲዮ መሳሪያዎችን በማቅረብ የመረጃ ምርመራ በማድረግ እና በኤሌክትሮኒክ መገናኛ ብዙሀን ላይ አፈናዎችን በማካሄድ ነጻ አሰተሳሰብን በመጨቆን በዋናነት ተጠያቂዎች ናቸው፡፡
ነጻነትን ይፈራሉ፡፡ ነጻነት ምንድን ነው? የሁሉም የሰው ልጆች ነጻነቶች ባህሪያት ከፍርህት የሚገኙ ነጻነቶች ናቸው፡፡ በተግባራዊ ሁኔታ ሲታይ አንድ ሰው ያሰበውን ለመናገር መፍራት ወይም ደግሞ አንድ ሰው ደስ ያለውን መጻፍ መፍራት ወይም በአንድ ሀሳብ ማለትም ሀይማኖት ወይም ፍልስፍና ላይ ማመን እና አለማመንን መፍራት ወይም ደግሞ አንድ ሰው ከመረጠው ሰው ጋር አብሮ መገናኘት መፍራት ማለት አይደለም፡፡ ዋናው እና የመጨረሻው የሰው ልጅ ሁሉ ሊያደርገው የሚገባው ህዝቡ እራሱ ስልጣን የሰጣቸው በስልጣን ወንበር ላይ ያሉት ሰዎች ናቸው በህብረተሰቡ የኑሮ ሂደት ላይ መፍራት እና ህዝቡን ማክበር ያለባቸው፡፡
ሀሳብን ይፈራሉ፡፡ “ሀሳቦች ከጠብመንጃ የበለጠ ገዳዮች ናቸው“ በማለት ሌኒን አስጠንቅቀዋል፡፡ ሀሳቦች ሳይንስን፣ ፖለቲካን እና ማናቸውንም የሰው ልጅ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ሁሉ የመለወጥ ኃይል አላቸው፡፡ ከምንም በላይ ዓለም ጠፍጣፋ አይደለችም፡፡ ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ያሉ ገዥዎች የአዲስ ጠፍጣፋ መሬት ባለቤቶች ናቸው፡፡ እንደ ጥንቱ ንጉሶች፣ ዛሮች፣ እና ማሃራጃሆዎች ሆነው ከህዝቡ ፈቃድ ውጭ ( በተሰረቀ ስምምነት) መሰረት መግዛት ይፈልጋሉ፡፡ ጥቂት ሞራላዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሀሳቦች ሲኖሯቸው ነገሮችን በቀላሉ ለመገንዘብ እና አዳዲስ ሀሳቦችንም ለማድነቅ እና ተቀብሎ ወደ ተግባር ለማዋል የምሁርነት አቅሙ የሌላቸው የመንፈስ የአስተሳሰብ ድሁሮች ናቸው፡፡ ሆኖም ግን የጎሳ ክፍፍልን ለማራመድ፣ ስግብግብነት እና ጥላቻን ለማምጣት፣ የጥላቻ ከባቢን የመፍጠር፣ ግጭትን የመጫር፣ ሙስናን ለማስፋፋት እና ለማጠናከር፣ ህብረትን በመናድና የጥላቻ መንፈስን በመዝራት እንዲሁም በሰዎች መካከል ጥርጣሬ እና አለመተማመን እንዲነግስ በማድረግ ጭንቅላቶቻቸው ዋና የዲያብሎሳዊነት ቤተሙከራዎች ናቸው፡፡ ህዝብን ሊያስተባብሩ እና ሊያፋቅሩ የሚችሉ ሀሳቦችን ለማመንጨት፣ በጎሳዎች መካከል ፍቅርን የማስፈን፣ ብሄራዊ አንድነትን የማምጣት፣ የጋራ መግባባትን የመፍጠር፣ የጓዳዊነት መንፈስ የማጠናከር እና እምነትን የማራመድ አቅመቢሶች ናቸው፡፡
አዳዲስ ሀሳቦችን የሚፈሩ በኢትዮጵያ በስልጣን ወንበር ላይ ተቆናጥጠው የሚገኙ አምባገነኖች የአዲስ ሀሳብ አመንጭ እና ባለራዕይ መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፡፡ ህዝቡ እና ዓለም ወደፊት ጥሩ ነገር የሚያስቡ መልካም ነገር አላሚዎችና ፈጣሪዎች እንደሆኑ አድርጎ እንዲመለከታቸው እና እምነት እንዲኖረው ይፈልጋሉ፡፡ ሆኖም ግን በህልም የቅዠት ፍርሀት ተዘፍቆ ያለ ማንም ሰው መልካም አላሚ ሊሆን አይችልም፡፡ ባለራዕይ መሪዎች ለሚያደርጓቸው ማለትም ታማኝነት፣ ኃላፊነትነትን የመሸከም ብቃት፣ ሌሎችን አነቃቅቶ እና አሳምኖ በስራ የማሳተፍ ችሎታ፣ ያለፉትን ስህተቶች በግዴለሽነት እንዳሉ ከመድገም ይልቅ ከስህተት እና ከውድቀት መማርን፣ ስህተት በሚሰሩበት ጊዜ ይቅርታ አድርጉልኝ ብሎ መጠየቅን፣ ግልጽነት፣ ትክክለኛውን ነገር ለመስራት ፍትሀዊነት እና በፍቅር ላይ የተመሰረተ ሆኖ ከመገኘት ተግባራት ጋር ሁሉ አይተዋወቁም፡፡ መጥፎ እና ዕኩይ ተግባራትን ለማድረግ ፍቅር ያላቸው መሰሪ መሪዎች ናቸው፡፡ ኪሶቻቸውን የሚወጥሩትን የተዘረፉ በርካታ ገንዘቦችን ዓይኖቻቸው በቀላሉ ማየት ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን አሁን እየፈጸሟቸው ያሏቸው በርካታ ወንጀሎች በዘለቂነት ለወደፊት ሊያስከትሉት የሚችሏቸውን እንደምታዎች ለማየት የታወሩ ናቸው፡፡ ጠንካራን ሀሳብ ጊዜው እየመጣ ያለውን ሀሳብ የሚያቆመው ምድራዊ ኃይል የለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለነጻነት የሚያደርገውን ተጋድሎ የሚያቆመው ኃይል የለም፡፡ አንዴ ከተጀመረ በመንገዱ ላይ ያለውን ጋሬጣ ሁሉ እየጠራረገ ወደፊት ይገሰግሳል፡፡
ለውጥን ይፈራሉ፡፡ ለውጥ ምንድን ነው? ለውጥ በሁሉም ነገር የሚከሰተውን የዕድገት እና የመበስበስ ዓለም አቀፋዊ ዘላለማዊ የለውጥ ህግ የሚገዛ ሂደት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው ገዥ አካል ለውጥን አጥብቆ ይፈራል ምክንያቱም በህበረተሰቡ ላይ ያላቸውን የኢኮኖሚ እና የፖሎቲካ የበላይነት ቦታ ስለሚያሳጣቸው ነው፡፡ ለውጥን ሊያመጡ የሚችሉ ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ለማምጣት የሚንቀሳቀሱትን ማናቸውንም ሙከራ ሁሉ ይደመስሳሉ፡፡ ከዚህ አንጻር “በሰላማዊ መንገድ የለውጥ አብዮት እንዳይመጣ የሚከለክሉ ሁሉ የአመጽ ለውጥ በኃይል እንዲመጣ ይገደዳሉ“ የሚለውን ሀቅ ለመገንዘብ የተሳናቸው ይመስላል፡፡
በፖለቲካ ህጋዊነት ማጣት እና በመንግስት አቅም ማጣት ምክንያት ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በፖለቲካ መበስበስ የመጨረሻ ጠርዝ ላይ ያለችበት ሁኔታ ነው የሚታየው፡፡ የጨነገፈ መንግስት ሆናለች፡፡ ባለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት የጎሳ ክፍፍል ፖሊሲ (የጎሳ ፌዴራሊዝም) “ልማታዊ መንግስት” ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዘገብን በማለት የሚራገበው እርባናየለሽ ፕሮፓጋንዳ ቢኖርም እንኳ ኢትዮጵያን በሁለት አማራጮች ላይ ጥሏታል፡፡ የእነርሱ ነጭ ውሸት ብቻ ነው በባሁለት እና በባለሶስት አሀዝ እድገት ያስመዘገበው፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማለች፡፡ እንደተባበረች ሀገር አንድ ሆና ወደፊት ትገሰግሳለች ወይም ደግሞ ወደተለያዩ ትናንሽ የተበጣጠሱ ክልሎች ትገነጣጠላለች፡፡ የአፓርታይድ ዓይነት ባንቱስታንስ በኢትዮጵያ ክልል እየተባለ በዘር እና በቋንቋ የተቀየደ የአገዛዝ ስርዓት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተበጣጠሱ ግዛቶች ስብስብ የምትሆን ከሆነ የመጀመሪያው ቸግር ቀማሽ የሚሆኑት አሁን በስልጣን ላይ ተጣብቆ የሚገኘው ገዥው አካል፣ የእነርሱ ጋሻጃግሬዎች እና ደጋፊዎች ናቸው፡፡ በፖቲካ ስልጣን ማጣት ብቻ የሚቆም ሳይሆን ቢያንስ እስከ አሁን ድረስ በአገር ውስጥ የሚደረግ ለውጥ ዘግይቶ እንደደረሰ ባቡር ይቆጠራል፡፡ በምስራቅ አውሮፓ በመካከለኛው ምስራቅ ሲነፍስ የነበረው የለውጥ ነፋስ ያለምንም ጥርጥር በኢትዮጵያም መንፈሱ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ ሊነሳ የሚችለው ብቸኛ ጥያቄ ግን እነዚህ ነፋሶች ተስማሚ እና በሰላም የሚያልፉ ወይስ ደግሞ ሁሉንም ነገር እየገነደሱ እና እየቦደሱ የሚጥሉ ኃይለኛ የሁሪኬን/hurricane-force ሞገዶች ይሆናሉ የሚለው ነው፡፡
እውነት ነጻ ያወጣሀል ነጻ አስከሆንክ ድረስ ሆኖም ግን ነጻ ያልሆኑት ይሰቃያሉ፣
“እውነት ነፃ ታወጣሀለች” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ነጻነት እና ፍርሀት ለእየራሳቸው ተነጥለው የሚኖሩ ናቸው፡፡ የነጻው ፕሬስ እና ጦማሪያን ብቸኛው ተግባራቸው እንዳዩት እውነታውን ወዲያውኑ መናገር ነው፡፡ ስለ እውነታው ያላቸውን ሀሳብ የለምንም ፍርሀት የመግለጽ ነጻነት አላቸው፡፡ ሆኖም ግን ህዝቡ እውነታውን ቀድሞም ቢሆን ያውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ በባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች የሚለው ነጭ ውሸት ቢሆንም ህዝቦች እውነታውን ያውቁታል፡፡ የሚበላ በቂ ምግብ እንደሌለ ያውቃሉ፣ እናም ሚሊዮኖች በየቀኑ እየተራቡ እንዳሉ ያውቃሉ፡፡ እንዲሁም በቂ የውኃ አገልግሎት ወይም የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሌለ ያውቃሉ፡፡ አናሳ የህክምና አገልግሎት ነው እየተሰጠ ያለው፣ ወጣቶች ጥራት ያለው ትምህርት አያገኙም እናም ስራ አጦች ናቸው፡፡ ገዥው አካል በሙስና ማጥ ውስጥ የተዘፈቀ እና የበከተ ነው፣ እንዲሁም በሰው ልጆች ላይ ወንጀልን ይፈጽማል፡፡ ህዝቦች በግልጽ የአየር ድባብ ውስጥ እስረኛ ሆነው እንደሚኖሩ ያውቃሉ፡፡
የነጻ ጋዜጠኞች እና የጦማሪዎች ወንጀል የሚያውቁትን ነገር ለማያውቁት ወገኖቻቸው መግለጻቸው ብቻ ነው፡፡ የእነርሱ ወንጀል የማዕድን ሙስና እና ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀምን፣ እንዲሁም በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙትን ወንጀሎች እየቆፈሩ በማውጣት ማስረጃ በማቅረባቸው ነው፡፡ ለዚህም በስልጣን ላያ ያለው ገዥ አካል እየፈራቸው ያለው፡፡ ገዥው አካል እውነታው ሳይታወቅ ተቀብሮ እንዲቀር እና እንዲረሳ ይፈልጋል፡፡ ገዥው አካል እውነታው እንዳይታወቅ በመደበቅ፣ እውነት ተናጋሪዎችንም ጸጥ በማስደረግ እና በየእስር ቤቶች በማጎር ለዘላለም ጸጥ በማድረግ ትንፍሽ እንዳይሉ በማድረግ እውነትን የመግደል እምነት አለው፡፡ ጆርጅ ኦርዌል እንደጠቆሙት፣ ”የማጨበርበር እና የሀሰት ሸፍጥ በተንሰራፋበት ጊዜ እውነትን መናገር አብዮተኛነት ድርጊት ነው“ ብለው ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ጦማሪያን የኢትዮጵያ የማይበገሩ አብዮተኞች ናቸው፡፡
ፍርሀትን በብዙሀን መገናኛ እንደ መሳሪያ መጠቀም፣
በስልጣን ላይ ያለው ገዥ አካል ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ዋና ድክመትን እንደ ትልቅ መጠቀሚያ መሳሪያ አድርጎ ይጠቀምበታል፡፡ ህዝብን ግራ ለማጋባት፣ እርስ በእርስ ለመከፋፈል፣ ለማታለል፣ ጥላሸት ለመቀባት እና ሀሳብን ከዋናው ጉዳይ አቅጣጫውን ለማስቀየስ ፍርሀትን በዋና መሳሪያነት ይጠቀምበታል፡፡ ማቋረጫ የሌለው የፍርሀት ዘመቻ በህብረተሰቡ ላይ ለመንዛት ሲፈልግ፣ ጥላሸት ለመቀባት እና ለማጠልሸት ሲፈልግ በህዝብ የግብር መዋጮ የሚተዳደረውን መገናኛ ብዙሀን ለእኩይ ምግባር ሌት ቀን ይጠቀማል፡፡ ገዥውን አካል የሚቃወሙትን ቡድኖች እና ግለሰቦች ጸጥ ለማድረግ ሲፈልግ እርባናየለሽ በውሸት ላይ ተመስርተው የተቀነባበሩ ዘጋቢ ፊልሞችን በመፈብረክ “አሸባሪ” የሚል ታፔላ በመለጠፍ በአሰልችው የመገናኛ ብዙሀን እንደበቀቀን ይደጋግማቸዋል፡፡ የውሸት ሸፍጥ በታጨቀበት እና ለመስማት እና ለማየትም አስቀያሚ በሆነው “አኬልዳማ” ብሎ በሰየመው ለምንም የማይውል እርባናየለሽ ዘጋቢ ፊልም ኢትዮጵያ በዲያስፖራው ተቃዋሚ ኃይል እና በአገር ውስጥ ባሉ የእነርሱ የግብር ተመሳሳዮች አማካይነት እንዲሁም ሌሎች አሸባሪ ቡድኖች ትብብር እና ርብርብ አደገኛ የሽብር አደጋ ተደቅኖባት እንደሚገኝ አደንቋሪ ጩኸታቸውን አሰምተዋል፡፡ “አኬልዳማ” በዓለም ላይ የተደረጉትን በጣም አስፈሪ እና አስቀያሚ ምስሎችን ሁሉ ለቃቅሞ በቪዲዮ በማሳየት በቅርቡ በህይወት የተለዩት አቶ መለስ ዜናዊ ተቃዋሚዎቻቸውን ጥላሸት በመቀባትና በሶማሌ የሚንቀሳቀሰው የአልቃይዳ እና አልሻባብ ቅጥረኞች ናቸው ብለው በአሸባሪነት በመፈረጅ የጥቃት ብቀላቸውን በንጹሁነ ዜጎች ላይ በሰፊው ተግብረውታል፡፡
በሌላ “ጅሃዳዊ ሀራካት” በተባለ እርባናየለሽ ዘጋቢ ፊልም በክርስቲያን እና በሙስሊሙ ህብረተሰብ መካከል ፍርሀት እና ጥላቻን ለማስፋፋት በማሰብ ጸረ እስልምና እሳትን የመጫር ሙከራ አድርገው በህዝቡ አርቆ አስተዋይነት እና የንቃት ደረጃ ምክንያት እኩይ ምግባራቸው ሳይሳካ መክኖ ቀርቷል፡፡ ለዘመናት አብሮ እና ተከባብሮ እየኖረ ያለውን የክርስቲያን እና የሙሰሊም ማህበረሰቡን በማጋጨት የእስልምና አሸባሪዎች በድብቅ ጅሀዳዊ መንግስት ለመመስረት ዕቅድ አውጥተው ተንቀሳቅሰዋል በማለት በሁለቱ ታላላቅ ኃይማኖቶች እምነት ተከታዮች መካከል የማያባራ እልቂት እና የደም ጎርፍን ለማዝነብ የታቀደ ዲያብሎሳዊ የድርጊት ዕቅድ ነድፈው ነበር፡፡ አሁንም ህዝቡ የነቃባቸው እና ከእነርሱ እኩይ አስተሳሰብ ውጭ የመጠቀ ሀሳብ ስላለው እና ስላወቀባቸው ዕቅዳቸው አሁንም መክኖ ቀርቷል፡፡
ፍርሀት እና ጥላቻን በህዝቡ ውስጥ ለማስፋፋት እና ምናባዊ የሆነ የዘር እና የጎሳ እልቂት እንዲሁም የኃይማኖት ጽንፈኝነት እልቂት እንደሚከሰት በመስበክ ይህንንም እልቂት ለማስወገድ ብቸኛ ቅዱሶች እነርሱ እንደሆኑ አድርገው በማቅረብ እና በማደናገር ጸረ ኢትዮጵያ እና ዘረኛ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ጎጠኞች መሆናቸውን በአደባባይ አስመስክረዋል፡፡ አሁንም ተስፋ ባለመቁረጥ አንዱን ጎሳ በሌላው ላይ በማስነሳት ለማጋጨት ሌት ቀን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ “የጎሳ ፌዴራሊዝም/ethnic federalism” በሚል እኩይ ስልት የዘር ማጽዳት ዘመቻቸውን ቀጥለውበታል፡፡ የጎሳ ጥላቻን ለመቀስቀስ ታሪካዊ ብሶቶችን እየፈበረኩ እና ጥቃቅን ነገሮችን እያጋነኑ በህዝቡ ዘንድ አለመተማመን እና ግጭቶች እንዲነሱ አበርትተው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ህዝቡ ግን ስለነቃባቸው በባዶነታቸው ቀልበቢስ በመሆን እንደ አበደ ውሻ ከወዲያ ወዲህ በመቅበዝበዝ ላይ ይገኛሉ፡፡ የእራሳቸውን ፍርሀት እንደ መሳሪያ በመጠቀም ህዝቡን ለማደናገር ይሞክራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ትንታግ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ላይ የተከፈተው ጦርነት በእራሷ በእውነት ላይ የተከፈተ ጦርነት ነው፣
በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ የሚገኘው ገዥ አካል በነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች እና በጦማሪያን ላይ ያወጀው ጦርነት በእውነት በእራሷ ላይ ያወጀው ጦርነት ነው፡፡ ገዥው አካል ላለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት በተደረጉት ጦርነነቶች እና ግጭቶች ሁሉ በድል አድራጊነት ተወጥቷል፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ ጎራዴ እና ኤኬ 47 አውቶማቲክ ጠብመንጃዎችን በታጠቁ አምባገነኖች እና ብዕሮች እና የኮምፒውተር ኪቦርዶችን በሚጠቀሙ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን መካከል የሚደረገው ወሳኙ ፍልሚያ ተቃርቧል፡፡ ያ ጦርነት እና ፍልሚያ በኢትዮጵያውያን/ት ልብ እና አእምሮ ውስጥ ሰርጾ ሁሉንም ዜጎች ለወሳኙ ፍልሚያ እና ለድል ጉዞ ጥርጊያ መንገዱን የሚያመቻች ይሆናል፡፡ የዚያ ጦርነት እና ፍልሚያ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በእርግጠኝነት የምናገረው ነገር ቢኖር ፍልሚያው የሀገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን ይሆናል፡፡ በእርግጥ ያ ጦርነት በእውነት አራማጅ ወገኖች አሸናፊነት እንደተደመደመ እምነት አለኝ፡፡ ኤድዋርድ ቡልዌር ሊቶን የተባሉት ገጣሚ በትክክል እንዳስቀመጡት ጎራዴ በታጠቁት እና ብዕርን በጨበጡት ተዋጊዎች መካከል በሚደረግ የጦርነት ፍልሚያ በመጨረሻ ሁልጊዜ የወሳኙ ድል ባለቤት የሚሆኑት ብዕርን የጨበጡት ናቸው፡፡
እውነትን ጨብጠዋልና!
እውነት፣ ይህ!
ከሰዎች አገዛዝ ስር ሌላ ታላቅ ነገር አለ፣
ብዕር ከጎራዴ የበለጠ ኃይል አለው፡፡ አስተውል/ይ
ቀስት ተሸካሚዎች ይፈነድቃሉ፣ ግን ምንም የሚመጣ ነገር የለም!-
ልዩ ታምር ከጌታቸው እጀ ይቀበላሉ፣
እናም ቄሳሮችን በድን ለማድረግ ያምጻሉ
ታላቋ መሬት ትንፋሽ ያጥራታል!- ጎራዴውን ከዚህ ወዲያ ውሰዱ-
መንግስታት ከእርሱ ውጭ ሊጠበቁ ይችላሉና!
ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ያለውን ገዥ አካል ማዳን ወይስ ደግሞ የኢትዮጵያን ነጻ ፕሬስ እና ጦማሪያንን ማዳን የሚል ወሳኝ ጥያቄ ቢቀርብልኝ ቶማስ ጃፈርሰን እንደመረጡት ሁሉ እኔም የኋለኛውን ማዳን የሚለው እንዲጠበቅልኝ እመርጣለሁ፡፡ ቶማስ ጃፈርሰን እንዲህ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው የሚከተለውን መልስ ሰጥተው ነበር፣ ”የእኛ መንግስት መሰረቱ የህዝብ ሀሳብ እንደመሆኑ መጠን የመጀመሪያው ዓላማ መሆን ያለበት ያንን መብት ማስከበር ነው፡፡ እናም ጋዜጦች የሌሉበት መንግስት ከሚኖር ወይም ደግሞ መንግስት በሌለበት ጋዜጦች ብቻ ከሚኖሩ የትኛው የተሻለ ነው የሚል ምርጫ ቢቀርብልኝ የኋለኛውን ለመምረጥ ለሰከንድ እንኳ ጥርጣሬ አይኖረኝም፡፡ ሆኖም ግን ይህን ስል ማንኛውም ሰው እነዚህን ጋዜጦች መቀበል እና ማንበብ መቻል አለበት፡፡“
በተመሳሳይ መልኩ ለእኔም ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን የሌሉበት ገዥ አካል ከሚኖር ወይም ደግሞ ገዥ አካል በሌለበት ነጻ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ብቻ ከሚኖሩ የትኛው የተሻለ ነው የሚል ምርጫ ቢቀርብልኝ የኋለኛውን ለመምረጥ ለሰከንድ እንኳ ጥርጣሬ አይኖረኝም፡፡ ከሁሉም በላይ ለዓላማ በጽናት የቆምኩ፣ ለምሰራው ትክክለኛ ስራ ሁሉ ኩራት የሚሰማኝ፣ ላመንኩበት ዓላማ ከልብ እና በወኔ የቆምኩ፣ ዓላማየን ለማስፈጸም በከባድ እርምጃ ወደፊት የምገሰግስ፣ ላልሰራሁት ወንጀል ይቅርታን የማልጠይቅ፣ በምሰራው ስራ ሁሉ የማላፍር፣ ቆራጥ እና የማያወላውል ባህሪን የተላበስኩ የኢትዮጵያ ጦማሪ ነኝ!!!
ኃይል ለነጻ ጋዜጠኞች እና የኢትዮጵያ ጦማሪያን!
ውድቀት እና ዉርደት ህዘብን በጠብመንጃ ኃይል አስገድደው ለመግዛት ለተነሱ የዕኩይ ምግባር አራማጆች!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ወጣቶቹና – ቅዳሜ (ጽዮን ግርማ)

ለአብዛኛው ወጣት አዲስ አበባ ላይ ”ቅዳሜ” ትርጉም አላት። የሣምንቱን የሥራ ቀናት በየፈርጁ ያሳለፈው ኹሉም ወጣት
”ቅዳሜ”ን ደግሞ እንደየምድቡ ይውልባታል። እንደሰማኹት ከኾነ ለዞን ዘጠኝ አባላትና ጓደኞቻቸውም ቅዳሜ ልዩ ቀን ናት። ለወጣቶቹ አብሮነት የጡመራ መድረኩ ቢያግዛቸውም ከዛ በላይ ግን ጓደኝነታቸው ቤተሰባዊነትን ፈጥሮላቸው አብዛኛውን ቅዳሜ እንደየቅርበታቸው አብረው ያሳልፋሉ።
አብረው እስረኛ ይጠይቃሉ፣ የታመመን ያጽናናሉ፣ በጋራ ምሳ ይቋደሳሉ፣ የተለየ ዝግጅት ካለም አብረው ይሳተፋሉ። ከዚህ የተረፈ ጊዜ ካላቸው ደግሞ ፈጣንንና ነጻ የገመድ አልባ ኢንተርኔት አገልግሎት በሚገኝበት ሆቴል ገብተው ዓለም በምን ኹኔታ ላይ እንዳለች ለመከታተል ይሞክራሉ። አገሪቷ ውስጥ ባለው ከፍተኛ የኢንተርኔት ኮኔክሽን ችግር ምክንያት አብዛኛው ጋዜጠኛና ጥቂት ወጣቶች የእነዚህ ትልልቅ ሆቴሎች ገመድ አልባ ኢንተርኔት ተጠቃሚ ነው። በቅዳሜ ወደእነዚህ ሆቴሎች ጎራ ያለ ከጦማሪያኑ ወይም ከጋዜጠኛ አንድ ሰው ሊያገኝ ይችላል። በቃ ሲገናኙ ሰላም ተባብለው መቀላቀል ነው። እናም በአንድ ጉዳይ ጨዋታ ጀመራል። አብዛኛው ጨዋታ በአገር ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሊኾን ይችላል። ኮምፒዩተሮቻቸውን እየነካኩ ስለ አገራቸው ግድ ያላቸውን ይነጋገራሉ፣ ይከራከራሉ አሊያም ይጨቃጨቃሉ። መሄጃው ሰዓት የደረሰበት ደግሞ ተሰናብቶ ይሄዳል። በእነዚህ ሆቴሎች በቀጠሮ የሚገናኝ ሰው የለም። ”የት ነህ? የት ነሽ?” የሚለው የስልክ ጥያቄም ለመገናኘት በቂ ነው።
የተስፋዓለም ቅዳሜ ደግሞ ሌላ ነበረች። ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አብዛኛውን አርቦች ከእነ ለሊታቸው በሥራ ያጠፋቸዋል። ቅዳሜንም ረፈድ አድርጎ ይነሳል። እናም የመጀመሪያ ሥራው ለሕትመት የበቁ ጋዜጣና መጽሔቶችን አበጥሮ ማንበብ ነው። በማንበብ ብቻም አያቆምም፤ ከዘገባዎቹ አብዛኖቹ የተሠሩት በጓደኞቹ አሊያም በሚያውቃቸው ጋዜጠኞች ስለሚኾን ስልክ ይደውላል። ከዘገባዎች ውስጥ ተስፋዓለምን የሚያስደስቱት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ሊኾኑ ስለሚችሉ የስልክ ልውውጦቹ ”እንዲህ ብታደርግ/ብታደርጊ ኖሮ፣ እንትናን ብታናግረው በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ ይሰጥህ ነበር፣ እዚህ ቦታ እኮ እንዲህ ዓይነት መረጃ ነበር፣ ይሄ እኮ ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ሕትመት ላይ ወጥቷል፣ እውነቱን ለመናገር ይሄ ለሕትመት የሚበቃ ዘገባ ነው ብዬ አላምንም” በሚሉ አስተያየቶች የተሞሉ ነበሩ። በዚያው ልክ ደግሞ የሚያስደስተውን ዘገባ ሲያነብ ወይም ፕሮግራም ሲሰማ አዘጋጁን አወቀው አላወቀው ስልክ አፈላልጎ በመደወል ያበረታታል። የተስፋዓለም ግማሽ ቅዳሜ የምታልቀው ይህን ሲያደርግ ነው።
አኹን እነዚህ ወጣቶች ቅዳሜያቸውን በፌደራል ወንጀል ምርመራ መምሪያ (ማዕከላዊ) ፖሊስ ተነጥቀዋል። ሃምሳ ቀናት ታስረው ዘጠኝ ቅዳሜን አጥተዋል። እንዳሻቸው የሚያደርጓትን ቅዳሜ አኹን እነርሱ አያዙባትም። ከጠዋቱ ዐስራ ሁለት ሰዓት ሲል ከእንቅልፋቸው ይቀሰቀሳሉ። ለቁርስ ዳቦ በሻይ ይሰጣቸዋል። (ቤተሰብ የሚያወስድላቸው ምግብ ቁርስ ከበሉ በኋላ ነው የሚደርሳቸው) እናም ተመልሰው ገብተው ይዘጋባቸዋል። አብዛኞቹ ለየብቻ ከሌሎች እስረኛ ጋር የታሰሩ ሲኾን ሁለት፣ ሁለት ተደርገው የታሰሩም አሉ። እናም ከምርመራ የተረፈ ቀናቸውን በዝጉና በጨለምተኛው ክፍል ያሳልፋሉ። በአንዷ ቅዳሜ ደግሞ እንደዛሬው ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።
አንዷን ቅዳሜ – በፍርድ ቤት
ዛሬ ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2006 ዓ.ም.፤ ሦስቱ ወጣቶቹ እነርሱ በማያዙባት ቅዳሜ እጆቻቸውን በካቴና ታስረው ፒያሳ በሚገኘው የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ግቢ ውስጥ ሲደርሱ ከሌላው ጊዜ የበለጠ ቁጥር ያለው በዐይን ግምት ሦስት መቶ የሚደርስ ችሎት ተከታታይ በግቢ ውስጥ ተገኝቶ ነበር። የዛሬዎቹ ጠባቂ የፌደራል ፖሊሶች ባለፈው ጊዜ ከነበሩት ሻል ያሉ ስለነበሩ ቤተሰቦች ችሎት ውስጥ ገብተው እንዲታደሙ ባይፈቀድላቸውም ግቢ ውስጥ ከመቆም የከለከላቸው ወይም ያመናጨቃቸው አልነበረም።
ከጠዋቱ አራት ሰዓት ከሃያ ደቂቃ አካባቢ ሲኾን ችሎቱ በሴት ዳኛ በመሰየሙ፤ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎቹ ናትናኤል ፈለቀ እና አጥናፉ ብርሃነ እጃቸውን በሰንሰለት እንደታሰሩ ወደ ግቢው ገቡ። ዛሬ ወጣቶቹ በስስ ፈገግታ ”አይዞአችሁ ደህና ነን” የሚል የተስፋ ምልክት ለቤሰተቦቻቸውና ለጓደኞቻቸው አሳይተዋል። ከእነርሱ ቀጥለው በፖሊስ ታጅበው የገቡት ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስና የሕግ መምሕርና የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ዘለዓለም ክብረት እጆቻቸው በካቴና እንደታሰረ ለቤተሰቦቻቸው ሰላምታን ሰጥተዋል። የእነርሱ ፈገግተኛ መኾን ለቤተሰቦቻቸው፣ ለጓደኞቻቸውና ለወዳጆቻቸው ጥቂትም ቢኾን እፎይታን ሰጥቷል።
ተጠርጣሪዎቹ ችሎት የቀረቡት እንደወትሮው ኹሉ በሁለት መዝገብ ተከፍለው ቢኾንም ፖሊስ ያቀረበው ምክንያትና መከራከሪያ አንድ ዓይነት ነበር። ችሎቱ ከተሰየመ በኋላ ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ ቀጠሮ በርካታ ጉዳዮችን ሲመረምር መቆየቱንና አሁንም ያልተጠናቀቀ ምርመራ ስለሚቀረው ተጨማሪ ሃያ ስምንት ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል።
ጠበቃው አቶ አመሐ፤ ”ፖሊስ ከዚህ ቀደም በወሰደው ጊዜ ቀጠሮ ሰነድ ለማስተርጎም፣ የምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ ኢሜሎቻቸውን ለመፈተሽ እንዲሁም ያልተያዙ ግብረአበሮቻቸውን ለመያዝ ብሎ እንደነበርና አሁን ዝም ብሎ በጥቅሉ በርካታ ሥራዎችን ሠርቼያለሁ እንደገና ይጨመርልኝ ማለቱ አግባብ አይደለም” ሲሉ አመልክተው ነበር። ዳኛዋ ፖሊስ የሠራውን ሥራና የሚቀረውን ምርምራ እንዲያስረዳ በማዘዛቸው፣ ”ከሠራናቸው በርካታ የምርመራ ሥራዎች መካከል የተባባሪዎቻቸውን ቤት ፈትሸናል፣ ለተለያዩ ባንኮች የተጠርጣሪዎቹን ዝርዝር መረጃ እንዲሰጡን ጠይቀን ከተወሰኑት ምላሽ አግኝተናል፣ የተወሱ ምስክሮችን ቃል ተቀብለናል፣ ከትርጉም ሥራውም የተወሰነውን ሠርተናል። ግብረአበሮቻቸው ወደ ክፍለ ሃገርና ወደ ተለያዩ አገራት እየሸሹ መያዝ ስለተቸገርን የፖሊስ ኃይል አሰማርተን እያፈለግናቸው ነው እነርሱንም መያዝ ይቀረናል።” በማለት ተናግሯል።
አቶ አመሐ በበኩላቸው፤ ”ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ካዋለ ሃምሳ ቀናት ሞልቶታል። እነዚህ የሚላቸውን ነገሮች አጠናቆ ለመጨረስ የነበረው ጊዜ ከበቂ በላይ ነው። አሁንም ቢኾን እነዚህን ምርመራዎች ለማድረግ ደንበኞቼን አስሮ ማስቀመጥ አስፈላጊ አይደለም፤ ስለዚህም ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቻውን ሊያከብርላቸው ይገባል። ይህን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ባይቀበለው እንኳን ከዚህ በኋላ ፖሊስ በሚሰጠው ሃያ ስምንት ቀናት ጊዜ ውስጥ ምርመራውን አጠናቆ እንዲመጣ፤ አጠናቆ ባይመጣ ደግሞ ጥያቄው ተቀባይነት እንደማይኖረው ተደርጎ ይመዝገብልን” በማለት ጠይቀዋል።
ዳኛዋ አቤቱታውን ካደመጡ በኋላ፤ ፖሊስ ከዚህ በኋላ ሲቀርብ ለተጨማሪ የምርመራ ቀነ ቀጠሮ መጠየቂያ አሁን የጠቀሳቸውን ምክንያቶች በምክንያትነት ይዞ እንዳይቀርብ በማሳሰብ የጠየቀውን የሃያ ስምንት ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ፈቅደዋል።
በዛሬው ዕለት ችሎት ከቀረቡት መካከል ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፤ ከፍተኛ የኾነ የጀርባ ሕመም ስላለበት ወንበር እንዲገባለት መጠየቁንና እስካኹን ሊገባለት እንዳልቻለ ጠቅሶ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት አመልክቷል። ዳኛዋ ከምንም ነገር በላይ የጤና ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ በማሳሰብ የጠየቀው ወንበር እንዲገባለት ሲሉ ተናግረዋል። በችሎት የተገኘው መርማሪ ፖሊስ፤ ”በአጋጣሚ የእርሱ መርማሪ እኔ ነኝ የጀርባ ሕመም እንዳለበት ነግሮኛል። ወንበር እንዲገባለት ግን አልጠየቀኝም። አሁንም ቢኾን ይህ በጣም ቀላልና እዛው እኛው ጋር ሊያልቅ የሚችል ነገር ነው። ችግር የለም እናስገባለታለን” ሲል ቃሉን ሰጥቷል።
እስረኞቹ ከችሎት ሲወጡ እንደ አገባባቸው በፈገግታ ሰላምታ እየሰጡ ሲኾን፤ ችሎቱን ለመከታተል መጥቶ ፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ የቆመው ሰውም እጁን በማውለብለብ ተሰናብቷቸዋል።

የወያኔ ግፍ ለከቱን አልፏል!

የወያኔ ጉጅሌ ራሱ ከሳሽ፣ ፖሊስና ዳኛ ሆኖ በሚገዛት ሀገራችን ውስጥ የሚያካሂደው ግፍ አንድ ህዝብ ሊሸከመው ለሚችለው በላይ ሆኗል።

የወያኔ ሹማምንትና በዘር ለዝርፊያ የተሰማራው ድርጅታቸው በቅርቡ ደግሞ ስዘርፍ አያችሁኝ በሚል ቁጣ ከአንደበታቸው በላይ ምንም ባልታጠቁ የኦሮሞ ተማሪዎች ላይ ከአካሄደው ጅምላ ጭፍጨፋ አልፎ ግለሰብ ተማሪዎችን በማሳደድ ሰቆቃ መፈጸሙን ቀጥሎበታል። በዚህ ሰአት በርካታ ተማሪዎች በታወቁና ባልታወቁ እስር ቤቶች ታጉረዋል። ብዙዎቹ ከትምህርት ገበታ ካላንዳች ጥያቄ ተባረዋል እየተባረሩም ይገኛሉ።

ከወያኔ ግፎች ሁሉ በእጅጉ የሚዘገንነው ሌሎችን በመወንጀል ማሰቃየትና መግደል በፈለገ ቁጥር ራሱ ወንጀል ከፈጸመ በኋላ ወንጀሉን በሌሎች ላይ ለማመኻኘትና ለመቅጣት የሚጠቀሙበት የሃሳብ ዘዴ ነው።

በአለምያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በተሰበሰቡበት አዳራሽ ውስጥ የደህንነት አባሎች ቦንብ አፈንድተው ጉዳት ካደረሱ በኋላ የሚፈልጓቸውን ወጣቶች ቦንብ ሲያፈነዱና ሲጠምዱ ያዝናቸው በማለት ከዚህ በፊት በዊክሊክ መረጃ እንደተለቀቀው የተለመደ በሰው ልጆች ላይ ሰቆቃ ይፈጽማሉ። ሌላው ቀርቶ ቦምብ አፈነዱ ተብለው የተከሰሱት ተማሪዎች በገዛ ጓደኞቻቸው ላይ ቦምብን የሚወረውሩበት ምክንያት የላቸውም።

ወያኔ ተማሪዎቹን አረመኔና እብድ ለማስመሰል የሰራው የራሱ ትንሽዪ ድራማ ወይም ሌላኛው አኬልዳማ መሆኑ ግልጽ ነው።

ወያኔ ደግሞ እንዲህ አይነት የወሮበላ ስራ እንደሚሰራ እንዳላዪ የሚያዩት ለጋሽ ሀገሮች ሁሉ ያጋለጡት፣ የሚያውቁት የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ሰንብቷል።

በዚህ መሰሪ ወንጀል ያዝናቸው ብለው ከአሰሯቸው ተማሪዎች ውስጥ የቦኮ ትቤ ተወላጅ የሆነ ኑረዲን ሃሰን የተባለ የአለመያ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በድብደባ አሰቃይተው ከገደሉት በኋላ ራሱን ገደለ ብለው አስክሬኑን ለቤተሰቦቹ ሸጠውታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ብዙ ተማሪዎች የደረሱበት እና የገቡበት ተፍጧል።

ይህ ሰቆቃ መጠኑን አልፏል! ግፍ በዚሁ እንዲቀጥል ከሆነ ደግሞ መቆም የሚችልበት ተግባር ባለመፈጸማችን ሁላችንም የዚያች ሀገር ልጆች ከታሪክ ወቀሳ እና ከህሊና ጸጸት አናመልጥም። ወያኔዎች በዘር ከፋፍለው በየተራ ስለሚያጠቁን ነው ይህ የሽብር አገዛዛቸው እድሜ ያገኘው። ይህን አደገኛ ክፍተት ካልዘጋነው መከራው ቀጥሎ ያሰቃየናል።

ግንቦት 7 የፍትህና የዴሞክራሲ ንቅናቄ አገራችን ይህን ሁሉ ግፍና መከራ ማስተናገድ እንዲበቃት ልጆቿ ተባብረን እንድንነሳ ደጋግሞ ጥሪውን ያቀርባል።

ለወያኔ የተመቸነው በየተራ ለመጠቃት አንዱን ብሄረሰብ በሌላው በማስፈራራትና ጥርጣሬ በመንዛት ለመግዛት የቀየሰው ዘዴ ሰለባ መሆናችን ነው።

ግንቦት 7 ንቅናቄ፤ የወያኔ የግፍ ቀንበር እንዲሰበር ሰፊ ህብረት ፈጥረን ከመታገል ውጪ አማራጪ የለንም ይላል።

የወያኔ ግፍ ይብቃ!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!