Tuesday, May 19, 2015

በትጥቅ ትግል ለዉጥ ለማምጣት የሚታገሉ ድርጅቶች የጥምረት ስምምነት ተፈራረሙ

በገዢው የኢህአዴግ መንግስት ላይ የትጥቅ ትግልን እያካሄዱ የሚገኙ የተቃዋሚ ድርጅቶች ወደ ጥምረት እና ውህደት የሚወስዳቸውን ውይይት መጀመራቸውን ባለፈዉ አርብ ይፋ አደረጉ ።
የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፥ የጋምቤላ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፥ የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ፥ የአማራ ዴሞክራሲ ሀይል ነቅናቄ፥ እና የአርበኞች ግንቦት ፯ ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ የጥምረት ብሎም የውህደት ዉይይቶችን መጀመራቸውን አስታወቁ ።
“ሀገርን እና ህዝብን ለማዳን የጋራ ግብ አድርጎ ለመስራት” በሚል መርህ የተዘጋጀውን ውይይት በማካሄድ ላይ መሆኑን ንቅናቄዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል ።
በቅርቡ በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኘው አርበኞች ግንባር፥ ከግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ ጋር ውህደት ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን አምስቱ ንቅናቄዎች በማካሄድ ላይ ያሉትን ውይይት አስመልክቶ ውጤቱን በቀጣይ መረጃዎችን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከድርጅቶቹ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ንቅናቄዎቹ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ከመቼውም ግዜ በላይ በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይና መከራ ተባብሶ መቀጠሉን የገለጹት ድርጅቶቹ፥ አንድነትን በማጠናከር ሀገርንና ህዝብን ነጻ ማውጣት የሚገባበት ወቅት አሁን ነው ሲሉ በጋራ ባወጡት መግለጫ አክለው አስታቀዋል።

No comments:

Post a Comment