Monday, August 31, 2015

የኤፍሬም ማዴቦ ጽሑፍ ከኤርትራ በርሃ: ከዊሃ እስከ ኦምሃጀር – አንድ ሰሞን ከአርበኞች ጋር

ቃል የዕምነት ዕዳ ነዉ። ከዊሃ እስከ ኦምሃጀር – አንድ ሰሞን ከአርበኞች ጋር ,-በኤፍሬም ማዴቦ ቃል የዕምነት ዕዳ ነዉ። አዎ! ማተቡን ላጠበቀና በአምላኩ ለሚታመን በእርግጥ ቃል የዕምነት ዕዳ ነዉ። ሰዉ ነኝና እንደ ፈጣሪ ቃሌ ሁሉ እዉነት ነዉ ብዬ አለተፈጥሮዬ አላብጥም። ግን ሰዉ ብሆንም ፈጣሪዬን የምፈራ ሰዉ ነኝና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ስል ልቦናዬ እያወቀዉ እንደነ ጋሼ እንደልቡ ዉሸት ደርድሬ ለአንባቢ የማቀርብበት ምንም ምክንያት የለም። ከዚህ ቀጥሎ የማስነብባችሁ እያንዳንዱ ቃል እንደ ዳያስፖራ ተረተኞች የምተርተዉ ‘ሰዉ ሰዉ’ የማይሸተት ተረት ሳይሆን ኢትዮጵያ ድንበር ላይ በየግንባሩ የተሰለፉትንና በስልጠና ላይ የሚገኙትን የኢትዮጵያ አርበኞች ስጎበኝ በአይኔ ያየሁትንና በጆሮዬ የሰማሁትን ቃል ነዉ። ቨርጂኒያ ወደሚገኘዉ “Dulles” አዉሮፕላን ማረፊያ የሄድኩት ከልጄ ጋር ነበር። ከቤቴ Dulles የግማሽ ሰዐት መንገድ ነዉ። ያቺን ግማሽ ሰዐትና አዉሮፕላን ማረፊያ ደርሼ ሻንጣዬን እስካስጭን ድረስ አይኔ እያንዳንዷን ደቂቃ ከልጄ ከቢኒያም አልተለየም። መለየቱን ስላልወደደዉ ልቤ ደንግጧል። ከወያኔ ጋር ለመፋለም በረሃ የሚጓዘዉ ኤፍሬም ከአንድ ልጁ መለየት አቃተዉ። ምነዉ ብዬ እራሴን ጠየኩት- እኔዉ መልሼ ምንም አልኩ። ልጄን አቀፍኩት፤ አሁንም ደግሜ ደጋግሜ አቀፍኩት። እምባ ፊቴን ሞላዉ። ቀና ብሎ ተመለከተኝና ሲከፋዉ ታየኝ። ሁለተኛ ዙር እምባ ፊቴን ሞላዉ። “Son I don’t want to do this, but I have to do it” አልኩ በሁለት እጄ አቅፌ እንደያዝኩት። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አባት ሆይ ፈቃድህ ከሆነች ይቺ ጽዋ ከኔ ትለፍ ብሎ የጸለየዉ ፀሎት ትዝ አለኝ። እኛ ሰዎች የዳንነዉ ይህ ፀሎት ባለመመለሱ መሆኑ ትዉስ ሲለኝ ልቤ በሀሳቡ ጸና። አባባ Come on . . . be strong. I promise I will be the son that you raised- you will be proud of me” አለኝ ቢኒያም በዚያ 17 አመት ሙሉ በማዉቀዉ ቆንጆ ድምጹ። የተናገራቸዉ ቃላት ዉስጤ ገብተዉ ኃይል ሲሆኑኝ ተሰማኝ። ጠነከርኩ። ተሰናብቼዉ ወደኋላ እያየሁት ወደ ዉስጥ ገባሁ። ወደ ፍተሻዉ ቦታ ስሄድ ልቤን ከፍተኛ የመለየት ኃዘን እንደ ግግር በረዶ ሲጫነዉ ተሰማኝ፤ መሸከም አቃተኝና እንደ ህፃን ልጅ እያነባሁ ፍተሻዉ መስመር ላይ ገብቼ ወረፋ ያዝኩ። እንደፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ረቡዕ ኦጎስት 5 ቀን ከሌሊቱ 9 ሰዐት የተሳፈርኩበት አዉሮፕላን አስመራ አለም አቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ አይኔ ላይ ዉል ዉል እያለ ልቤን የሰቀለዉ የሚጠብቀኝ የትግል ዉጣ ዉረድ ሳይሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቄ በ22 አመቴ ስራ የጀመርኩባት ዉቧ የአስመራ ከተማ ምን ትመስል ይሆን የሚል የሀሳብ ዉጣ ዉረድ ነበር። ሆኖም አካልም መንፈስም እየከዳ ምንም ነገር ማሰብ አይቻልምና ወደ ግዜያዊ ማረፊያ ቦታዬ እንደወሰዱኝ ለሁለት ቀን ከግማሽ የተጠራቀመ እንቅልፍ ይዞኝ ጭልጥ አለ። ረቡዕ ከቀኑ አንድ ሰዐት አካባቢ “እባክህ ተነሳና ምሳ እንብላ” የሚል የሁለት ሰዎች ድምጽ ተራ በተራ ጆሮዬ ዉስጥ ገባና እንቅልፌን ሰለበዉ. . . መነሳት ባልፈልግም በልቤ ትግሉ ተጀመረ አልኩና ከተጋደምኩበት ቀና አልኩ። ፊት ለፊቴ ቆመዉ ተነስ እያሉ የሚጨቀጭቁኝ የትግል ጓደኞቼ ነአምን ዘለቀና ብርሀኑ ነጋ ነበሩ። ምሳ ላይ ተቀምጠን እነሱ የሚያወሩት ወደ ኤርትራ በረሃዎች ሰለሚደረገዉ ጉዞ ሲሆን እኔ ደግሞ በወጣትነቴ ስለማዉቃት የአስመራ ከተማ ነበር። አስመራን ትቼ ከነሱ ጋር እንደነሱ ማሰብ ሞከርኩ . . . አሁንም አሁንም ሞከርኩና ሲያቅተኝ ተዉኩት። በተለይ ምሳ የበላንበት ካራቨል ሬስቶራንት ዉስጥ በወጣትነቴ ብዙ ትዝታዎች ነበሩኝና ጭራሽ ምግቡን ትቼ በምናብ ወደ ወጣትነቴ ሽምጥ ጋለብኩ። ባር ኡጎ፤ ባር ቱኔል፤ ባር ፀአዳ ፈርስ፤ ባር እምባባና የባቢሎን ጋጋታ እንዳለ ፊቴ ላይ እየመጡ ተደቀኑ። ቀና ስል ነአምንና ብርሀኑ . . . አትበላም እንዴ አሉኝ። ወደ ኋላ ሽምጥ ያስጋለበኝን ፈረሴን ልጓም ያዝ አደረኩና ካሁን በኋላ ወደፊት ብቻ ብዬ ከሁለቱ ጓደኞቼ ጋር በአካልም በመንፈስም ተቀላቀልኩ። የአስመራ ከረን መንገድ ከተነጠፈ አስፋልት ዉጭ ሌላ ምንም አይቶ ለማያዉቅ ለእንደኔ አይነቱ የዳያስፖራ ‘በለስ’ ቀርቶ ደጋግሞ የተጓዘበትንም ሰዉ ልብ ይሰልባል። አስመራን ይዞ፤ አዲአቤቶንና እምባደርሆን ይዞ በአዲተከለዛን፤ በኢላበርዕድ፤ በከረንና በሀጋዝ አድርጎ አቆርደት ድረስ የሚዘልቀዉ መንገድ የአለም ተራራዎች ስብሰባ ተጠራርተዉ ወደየመጡበት ላለመመለስ ተማምለዉ የመሸጉበት ቦታ ይመስላል። አንዱን ተራራ ሽቅብ ወጥተንና ቁልቁል ወርደን እፎይ ብለን ሳንጨርስ ሌላዉ ከተፍ ይላል። በስተቀኛችን ያለዉን ተራራ አይተን ወይ ጉድ ስንል በግራችን ያለዉ ድንቄም ጉድ እያለ ያሾፍብናል። እልፍ ስንል ተራራ፤ ከዚያም ተራራ፤ተራራ፤ ተራራ ብቻ ነዉ። ፊት ለፊቴ የማያቸዉ ተራራዎች ተፈጥሮ የቆለለዉ የዲንጋይ ክምር ሳይሆን አዋቂ በዉኃ ልክ እየጠረበ የደረደረዉ ሾጣጣ ኃዉልት ይመስላሉ። አንኳን ለሰዉ ልጅ ለገደሉ ንጉስ ለዝንጀሮም አይመቹም። ባጠቃላይ የአስመራ አቆርደትን መንገድ ሲመለከቱት እንደ አጥር ከተሰለፉት ተራራዎች ባሻገር አገር ያለ አይመስልም። አላማና ጽናት ላለዉ ሰዉ ግን ከተራራዉ ወዲያ አገር ከአገርም ወዲያ ሌላ. . . ሌላ ወያኔ የቀማን አገር አለ። አላማ የሌለዉ፤ ሆዱ ያልቆረጠ፤ ፈሪ፤ ወኔ የከዳዉና አይኑን ተራራዎቹ ላይ ብቻ ያሳረፈ ሰዉ ከአስመራ ተነስቶ በከረን በኩል አቆርደትን አቋርጦ የጀግኖቹ መንደር ሀሬና የሚደርስ አይመስለዉም። ለዚህ ነዉ ሁሉን የሚችል እግዚአብሄር አይዞህ ብሎ የላከዉ የብሉይ ኪዳኑ ነቢዩ ኤልያስ ኤልዛቤልን ፈርቶ እንደሸሸ ሁሉ የኛም ዘመን ጋዜጠኛ ነን ባዮች፤ ዘፋኞችና አርበኛ ነን ባይ የሀሰት ነቢያት ገና ከረን ሳይደርሱ ተራራዉን እየፈሩ በኤርትራ በኩል ምንም ነገር መስራት አይቻልም እያሉ እንደ ግመል ሽንት የኋሊት የሚጓዙት። ድንቄም ጋዜጠኛ! ጋዜጠኛ ታሪክ ሸራርፎ በሰጠዉ ግዜ እየኖረ ያየዉንና የሰማዉን ለትዉልድ እያስተላለፈ ለራሱ የማይኖር ልዩ ፍጡር ነዉ። የኛዎቹ “ጋዜጠኛ” ነን ባዮች ግን እራሳቸዉ ለራሳቸዉ በሰጡት ግዜ እየኖሩ የራሳቸዉን ግሳንግስ የፈጠራ ታሪክ የሚነግሩን ከህያዉ በታችና ከሙታን በላይ ባለዉ ባዶ ቦታ የሚኖሩ ባዶዎች ናቸዉ። አምላክ በምህረቱ ወደ ላይ ይሳባቸዉና ከህያዋን ጋር ይቀላቅላቸዉ። ምድረ የወሬ ቋቶች ይግባችሁ! የኢትዮጵያ ህዝብ ዉኃ ዉኃ የሚያሰኝ የእሳት ጉድጓድ ዉስጥ ነዉ ያለዉ፤እሱ ከጉድጓዱ ባስቸኳይ መዉጣት እንጂ እንደናንተ በኤርትራ በኩል ከሆነ ይቅርብኝ ብሎ የሚጃጃልበት ግዜዉም ትዕግስቱም የለዉም። ለነገሩ እነዚህ የወሬ አርበኞች ተራራ ወጥተዉ፤ በረሃ አቋርጠዉና ወንዝ ተሻግረዉ ከወያኔ ጋር ሳንጃ ሊማዘዙ ቀርቶ የገዛ ልጆቻቸውን የልደት ኬክ ደፍረዉ በቢላዋ የማይቆርጡ የ”ዳዉን ታዉን” ቅምጦልች ናቸዉና ከነወሬያቸዉ እዚያዉ “ዳዉን ታወን” ብንተዋቸዉ የሚበጅ ይመስለኛል። አይደል? ወሬና ስራ ለየቅል ናቸዉ፤ ለወሬ የሚያስፈልገዉ ሹል አፍ ብቻ ነዉ። ለስራ ግን አፍ፤ እጅ፤ አግር፤ አይን፤ ጆሮና የሚያስብ አዕምሮ ያስፈልጋል። ወረኛና ለስራ ያልተፈጠረ ሰዉ የተራራዉ ከፍታ እየታየዉ “በዚህ በኩል እንዴት ተደርጎ” እያለ የወሬ ቱማታዉን መደርደር ይጀምራል። የሚሰራ ሰዉ ግን ግቡ ከተራራዉ ባሻገር ከተከዜ ማዶ ነዉና ተራራዉን ሽቅብ ወጥቶና ከጠመዝማዛዉ መንገድ ጋር እኩል ተጠማዝዞ ወዳለመዉ ግብ ይጓዛል። አንባቢ ሆይ! ሠራተኛ በለኝ አትበለኝ እሱ ያንተ ጉዳይ ነዉ፤ መዳረሻዬ ከተከዜና ከመረብ ወንዞች ባሻገር መሆኑንና አላማዬም ፍትህና ነጻነት መሆኑን ግን እኔዉ እራሴ አብጠርጥሬ ልነግርህ እችላለሁ። የምወደዉን አንድ ልጄንና ጥሩ ስራዬን ደህና ሁኑ ብዬ በረሃ የገባሁት እናት አገሬ ዉስጥ ፍትህ፤ ነጻነት፤ እኩልነትና ዲሞክራሲ አብበዉ ለማየት ነዉ እንጂ የኤርትራ በረሃና ተራራ ናፍቆኝ አይደለም። የናፈቀኝ ተራራና በረሃ ቢሆን ኖሮ አሪዞናና ኮሎራዶ ይቀርቡኝ ነበር። ዉቧን የአቆርደት ከተማና ቀዳማዊ ኃ/ሥላሤ ያሰሩትን ግዙፍ መስጊድ በስተቀኝ እያየን ወደ ባሬንቱ ስናመራ ያ ከአስመራ ጀምሮ የተከተለን የተራራ መንጋ ፀሐይ እንደገላመጠዉ በረዶ እየሟሸሸ ሄዶ ገና ሀይኮታ ሳንደርስ ሜዳ ሆኖ አረፈዉ። የበረሃዉ ሙቀት እንዳለ ቢሆንም ባሬንቱ ስንደረስ የሚነፍሰዉ ቀዝቃዛ አየር ሙቀቱን አለዝቦታል። ባሬንቱን ለቅቀን ወደ ተሰነይ ስናመራ መሬቱ ሜዳ፤ ሰማዩ ደመናማ፤ አየሩ ነፋሻማ እየሆነ ይመጣል። ትናንሽ ልጆች እዚህም እዚያም ይዘልላሉ፤ ትራክተሩ ያርሳል፤ ግረደሩ ይዳምጣል፤ እንደኔ አይነቱ ጠመዝማዛዉ መንገድ ቀልቡን የሰለበዉና ፀሐዩ ያቀለጠዉ ምስኪን ደግሞ ወላዲት አምላክ ምን በደልኩሽ እያለ ያምጣል። ባሬንቱ ያኔ እኔ ሳዉቃት የጋሽና ሰቲት አዉራጃ ዋና ከተማ ነበረች፤ ዛሬ ከሃያ ስምንት አመት በኋላ ያየኋት ባሬንቱ ግን ከፍተኛ የንግድና የእርሻ እንቅስቃሴ ይታይባታል፤ ዉብትም ስፋቷም በእጥፍ ጨምሯል ፤ደግሞም የዛሬዋ ባሬንቱ የጋሽ ባርካ ዞን ዋና ከተማ ናት። ከባሬንቱ ወደ ተሰነይ ሲወጣ ግራና ቀኝ አዉራጎዳናዉን ይዞ ኢትዮጵያና ሱዳን ጠረፍ ድረስ የተንጣለለዉ መሬት የኤርትራ የእህል መቀነት ነዉ። አካባቢዉ ከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ ይታይበታል። የኤርትራን ልማትና የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ማየት የፈለገ ሰዉ ከአስመራና ከሌሎች ትላልቅ ከተማዎች ወጥቶ ገጠር መግባት አለበት። ግድቡ፤ እርሻዉ፤ የጤና ተቋሙና ሌላም ሌላ የመሠረተ ልማት ምልክቶች በጉልህ የሚታዩት ገጠሪቱ ኤርትራ ዉስጥ ነዉ። ከተሰነይ ወጥተን ጥቂት እንደተጓዝን መኪናችን አስፋልቱን ለቅቃ ኮረኮንቹ መንገድ ዉስጥ ገብታ ስትንገጫገጭ ከእንቅልፌ ነቃሁና እንደመንጠራራት ብዬ . . . ደረስን እንዴ አልኩ … የመኪናችንን ሾፌር። ገና ነዉ ትንሽ ይቀራል አሉ ወደኋላ ዞር ብለዉ። እንዳዉ ለነገሩ ነዉ እንጂ ሰዉዬዉ ዬት እንሄዳለን፤ መቼ አንሄዳለን ወይም መቼ እንመለሳለን ለሚሉ ጥያቄዎች በፍጹም መልስ አይሰጡም። ወያኔ የማይሰማን ሁሉንም ነገር ሆዳችን ዉስጥ ከያዝነዉ ብቻ ነዉ የሚል ፈሊጥ አላቸዉ። ዋናዉን መንገድ ለቅቀን ኮረኮንቹን ከተያያዝነዉ በግምት ከ20 ደቂቃ በኋላ አርበኞች መንደር ቁጥር አንድ ደርስን። ዘፈኑ፤ ጭፈራዉ፤ ሆታዉና ዕልልታዉ ቀለጠ። አርበኛዉ ጠመንጃዉን እንደታቀፈ እየዘለለና እየፎከረ እንኳን ደህና መጣህልን እያለ መሪዉ ላይ ተጠቀለለ። “የወያኔ ዘረኞችና አንዳንድ ተላላዎች አንተንና ጓዶችህን ትኩስ ሀምበርገር እየበላችሁ ወጣቱን በረሃ ዉስጥ ታስጨርሳላችሁ” እያሉ አርበኛዉንና መሪዉን ለመለያየት ብዙ ጥረዋል። እናንተ ግን የሞቀ ኑሯችሁን ትታችሁ ታግላችሁ ልታታግሉን በረሃዉ ድረስ መጥታችሁ ተቀላቅላችሁናል . . . እሴይ የኢትዮጵያ አምላክ! . . . ወያኔ የተሸነፈዉ ዛሬ ነዉ እየለ አርበኛዉ በሆታና በዕልልታ ከዉስጥ የመነጨ ደስታዉን ገልጸ። ብቻ ምን አለፋችሁ ጀግኖቹን ያሉበት ቦታ ድረስ ልናይ ሄደን የጀግና አቀባበል ተደረገልን። እንደ አንድ ታጋይ ድል አፋፍ ላይ ልድረስ አልድረስ አላዉቅም፤ ማሸነፋችንን ግን አረጋገጥኩ። የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዉን እንዳቀፈ ሰላም ሊለኝ ሲመጣ ትኩር ብዬ አየሁት። ወጣት ነዉ፤ ጽናቱና ቁርጠኝነቱ ፊቱ ላይ ይነበባል። በፈገግታ የታጀበዉ የዋህ ፊቱ ልጅነቱን በአዋጅ ይናገራል። ዕድሜዉ ከሃያ አይበልጥም። ተቃቅፈን ሰላም ስንባባል እጅብ እጅብ ብሎ የተጎነጎነ ፀጉሩን በእጄ እያሻሸሁ “እቺን ነገር ታበድረኛለህ” አልኩት ፀጉር እየከዳዉ ያስቸገረኝን እራሴን እያሳየሁት። ችግር የለም አለኝ። “ችግር የለም” በአርበኞቹ ሠፈር የተለመደ አባባል ነዉ። የበረሃዉ ንዳድ፤ የዉኃዉ ጥማት፤ የምግብ ችግር፤ ክብደት ተሸክሞ ተራራዉን ሽቅብ መዉጣትና ባጠቃላይ ወያኔንና ዘረኛ ስርዐቱን ማስወገድ ለአርበኛዉ ችግር አይደለም። አርበኛዉ ለእንደነዚሀ አይነት ችግሮች ተዘጋጅቶ ስለመጣ እንደችግር አይመለከታቸዉም። ድንኳን ዉስጥ ገብተን ቁጭ እንዳልን . . . . እዚህ አካባቢ ችግራቸሁ ምንድነዉ አልኩት። ይምጡ አለኝና ከድንኳኑ ይዞኝ ወጥቶ ገዢ መሬት ይዘዉ የመሸጉትን የተለያዩ ካምፖች አሳየኝና የእያንዳንዳቸዉን ስም ነገረኝ። ሁላችንም የመጣነዉ ከኢትዮጵያ ነዉ፤ ሁላችንም የምንታገለዉ ወያኔን ነዉ፤ ደግሞም የሁላችንም ጥያቄ ፍትህ፤ ነጻነትት፤ እኩልነትና ዲሞክራሲ ነዉ. . . .. ግን አንድ ላይ አንታገልም። እስከመቼ ነዉ የአንድ አገር አርበኞች ከአገራችን ወጥተን፤ የተለያየ ድንኳን ተክለን፤ በተናጠል የጋራ ጠላታችንን የምንዋጋዉ? እባካችሁ ገላግሉን ብሎኝ ቀና ሲል አይኑ ካይኔ ገጠመ። በአፉ ከነገረኝ በአይኑ የነገረኝ በለጠብኝ። እንዲህ አይነቱን ብስለት የተሞላዉ ንግግር የሰማሁት ከልጄ ብዙም ከማይበልጥ ኢትዮጵያዊ ወጣት መሆኑ ሲሰማኝ እራሴን ታዘብኩት፤ ኢትዮጵያዊነቴን ግን ከወደድኩት በላይ ወደድኩት። አዎ አሁንም አሁንም አትዮጵያዊነቴን ከነችግሩ ወደድኩት። ደግሞስ ዬኔ ስራ ችግር መፍታት ነዉ እንጂ የአገሬ ችግር ፊቴ ላይ በተደቀነ ቁጥር ኢትዮጵያዊነቴን ጥያቄ ዉስጥ ማስገባት አይደለም።በነገራችን ላይ በተናጠል የሚደረገዉ ትግል አያዋጣምና “እባካችሁ አንድ አድርጉን” የሚለዉ ጥያቄ የአንድ አርበኛ ጥያቄ ሳይሆን በየሄድኩበት ካምፕ፤ ግምባርና ምሽግ ዉስጥ ከአብዛኛዉ አርበኛ አፍ የሚወጣ ጥያቄ ነዉ። ቀኝ እጄን ወጣቱ አርበኛ ግራ ትከሻ ላይ አሳረፍኩና በሌባ ጣቴ በርቀት የሚታዩትን ካምፖች እያሳየሁት… አንዱጋ መሄድ እንችላለን አልኩት። አይ ጋሼ አሁን መሽቷል አለኝ። ሰዐቱ ገና ከቀኑ 9 ሰዐት ቢሆንም ሰፈሩ የአርበኞች ስለሆነ በነሱ ህግ መተዳደር አለብኝ ብዬ እሺ አልኩት። አይዞት እናንተ አስተባብራችሁ አንድ አድርጉን እንጂ ሌላ ሌላዉ ችግር የለዉም አለኝ። እኔም እንደ ወጣቱ አርበኛ በድፍረት “ችግር የለም” ለማለት ባልደፍርም . . . አይዞህ ትብብርን በተመለከተ በቅርብ ግዜ ሁላችንንም የሚያስደስት ዜና አብረን እንሰማለን አልኩት። ፈገግ አለና እሱን ከጨረሳችሁልን ሌላዉን ለኛ ተዉት አለኝና ይዞኝ ወደ ድንኳኑ ገባ። ሐሙስ ነኃሴ 13 ቀን ጎህ ሳይቀድ ከእንቅልፌ ተነሳሁና ትንሽ ዞር ዞር ብዬ አልጋዬ ላይ ተመልሼ መጽሐፌን ማንበብ ጀመርኩ። ሁለት ምዕራፍ ጨርሼ ሦስተኛዉን ልጀምር ስል ከሩቁ ቡና ቡና ሸተተኝ። ቀና ብዬ ስመለከት ፍረወይኒ የቆላችዉን ቡና እስከነማንከሽከሻዉ ተሸክማ ልታስሸትተኝ ስትመጣ አየኋት፤ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ቁርስ ደረሰ እንዴ ብዬ ማንከሽከሺያዉ ላይ የሚንቦገቦገዉን ጭስ በእጄ ደጋግሜ ወደ አፍንጫዬ ሳብኩት። ‘ኡወ ቁርሲ ደሪሱ’ ብላ ፍረወይኒ የተቆላዉን ቡና ይዛ ወደ መጣችበት ተመለሰች። ከጧቱ አንድ ሰዐት ከመሆኑ በፊት ቁርስ ተበልቶ አለቀና ሁላችንም ወደየተመደብንበት መኪና እንድንገባ ተነገረን። የሚጸዳዳዉ ተጸዳድቶ ሲጋራ የሚያጤሰዉም ሲጋራዉን ለምጦ ጉዞ ተጀመረ። ዬት እንደምንሄድ ወይም ለምን እንደምንሄድ የጠየቀም የተናገረም አልነበረም። . . . ዋ! ትንፍንሽ ብትሉ የተባለ ይመስል ሁሉም አፉን ዘግቶ ወደማያዉቀዉ ቦታ ጉዞዉን ቀጠለ። አንድ ሰዐት ያክል እንደተጓዝን . . . “እነዚያ ቤቶች ይታዩሃል” የሚል ድምጽ መኪናዉ ዉስጥ የሰፈነዉን የዝምታ ጽላሎት ሰበረዉ።አዎ ይታየኛል . . . ምን የምትባል ከተማ ናት ብዬ ቀና ስል ትልቅ ወንዝ አየሁ፤ ግን ወንዙንም ከተማዉንም ስለማላዉቃቸዉ ምንም አልተሰማኝም። እንድያዉም ፀሐይ ያጋለዉን ሰዉነቴን ለማቀዝቀዝ ወደ ወንዙ እንሂድ አልኳቸዉ። “ይቅርብህ እንደቀዘቀዝክ ትቀራለህ” አለኝ ከአጃቢያችን አንዱ። ከተማዉ ኦምሀጀር፤ ወንዙ ተከዜ፤ ከወንዙ ባሻገር የሚታየዉ ከተማ ደግሞ ሁመራ መሆኑ ሲነገረኝ . . . የምን ወንዝ መዉረድ እዚያዉ ቀዝቅዤ ቀረሁ። አደራ ቦቅቧቃ እንዳትሉኝ . . . አልፈራሁም አልደነገጥኩም። በእርግጥ እንኳን እንደዚያ ቀርቤዉ ከሩቅ ከባህር ማዶም ጠልፎ ሊወስደኝ የሚፈልግ ሰላቢ የነገሰበትን ምድር ሳላዉቀዉ እንደዚያ በድንገት መቅረቤ ትንሽም ቢሆን አሳስቦኛል። ይልቅ እንደዚያ ያፈዘዘኝና ገና ወንዙ ዉስጥ ሳልገባ ያቀዘቀዘኝ እናት አገሬን ኢትዮጵያን በ25 አመት ለመጀመሪያ ግዜ ማየት መቻሌ ወይም የእናት ኢትዮጵያ ናፍቆት ነዉ። ለነገሩ አገርም ሰዉም የሚናፍቀዉ ርቀዉ ሲሄዱ ነዉ። ዬኔ ናፍቆት ግን ልዩ ጭራሽ ልዩ ነዉ። አጠገቧ ቆሜ አገሬ ናፈቀችኝ። አዎ! መግቢያዬ ቀረበ መሰለኝ ኢትዮጵያ ስቀርባት ይበልጥ ናፈቀችኝ። በቃ አንሂድ አለ ይዞን የመጣዉ የበላይ መኮንን . . . አዎ እንሂድ እንጂ ከዚህ በላይ መቆየት ለወያኔ ካልሆነ ለሌላ ለማንም አይበጅም አሉ ሌላዉ በዕድሜ ጠና ያሉ የበላይ መኮንን። እኚህ ሰዉ የወያኔ ስም ሲነሳ ደማቸዉ ይፈላል ፤ እሳቸዉ እራሳቸዉ እንደ ዳዊት ሲደጋግሙት ግን ምንም አይሰማቸዉም። ከሰዐት በኋላ ረፋዱ ላይ ሁላችንም ወደየመኪናችን ገብተን ኦምሀጀርን ለቅቀን ወደ ጀግኖቹ አገር ወደ ሀሬና አቀናን። ሀሬና አርበኞች ግንቦት 7ን፤የጋምቤላ ህዝብ ነጻነት ንቅናቄን፤ የአማራ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄን፤ የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ድርጅትንና ደምህትን ወላድ ማህፀንዋ ዉስጥ አምቃ የያዘች እርጉዝ ምድር ናት። እርግጠኛ ነኝ በቅርቡ ትወልዳለች። የአስመራ ምፅዋ መንገድ እንደ ጥምጥም እየተጠመጠመ እየቀናና እየጠመመ ለረጂም ሰዐት የሚዘልቅ ያዋቂንም የልጅንም ቀልብ የሚሰልብ ሰላቢ መንገድ ነዉ። እግዚኦ . . . የከረን መንገድ በስንት መልኩ! ከአስመራ ምፅዋ መሄድ ማለት ከ2500 ሜትር ተራራ ላይ ቁልቁል ወርዶ ባህር ወለል መድረስ ማለት ነዉ። ትንፋሼን ቋጥሬ በቀኜ ገደሉን በግራዬ ተራራዉን እያየሁ ለሰዐታት ቁልቁለቱን ከተያያዝኩት በኋላ የቋጠርኩትን ትንፋሽ አዉጥቼ እፎይ ማለት የጀመርኩት ማይ አጣል ስደርስ ነዉ። ከማይ አጣል በኋላ ምፅዋ ድረስ መንገዱ ሜዳ ነዉ። ምፅዋ ልንደርስ ትንሽ ሲቀረን ሆዴን ባር ባር አለዉ። የደስታ ይሁን የሀዘን ወይም የሲቃ አላዉቅም ብቻ ልቤ ሌላ ሌላዉን ሰዉነቴን ትቶ ደረቴ ዉስጥ ብቻዉን ይዘላል። “ዉስጥ እጄን ይበላኛል” ምን ሊያሳየኝ ይሆን . . . ይል ነበር የልጅነት ጓደኛዬ። ምነዉ እኔም እንደሱ ሆኜ ዉስጥ እጄን በበላኝ . . . ልቤ ደረቴን ጥሶ የሚወጣ እሰኪመስል ድረስ ደረቴ ዉስጥ ከሚዘል። አይፎኔን አወጣሁና ግራና ቀኙን አይኔ ያረፈበትን ቦታ ሁሉ ፎቶ አነሳሁ። ቦታዉ ዶጋሌ ይባላል. . . አዎ! ዶጋሌ . . . ጀግናዉ ራስ አሉላ 500 የጣሊያን ወታደሮችን ዶጋ አመድ ያደረጉበት የድል ቦታ። ለካስ ልቤ አለምክንያት አልዘለለም! ጣሊያን ዋና ከተማ ሮም ዉስጥ የአምስት መቶዎቹ አደባባይ የሚባል ቦታ አለ (ፒያዛ ዴ ቺንኮ ቼንቶ)። እመኑኝ እኛም አገር አይቀርም! ባንዳ ባንዳዉንና ልክ ልኩ ሲነገረዉ ደንግጦ የሞተዉን ምናምንቴ ሁሉ ትተን ሞተዉ ህይወት የሆኑልንን የትናንትናና የዛሬ ጀግኖቻችንን እናስታዉሳለን። ምፅዋ ሁለት ቀን ብቻ ነዉ ያደርኩት – ቅዳሜና እሁድን። በጦርነቱ የፈራረሱ ህንጻዎች አሁንም አልፎ አልፎ ይታያሉ፤ ያም ሆኖ ምፅዋ ዉብ ከተማ ናት፤ ደግሞም አያሌ አዳዲስ ህንጻዎች ተሰርተዉባታል። የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ጠ/መምሪያ የነበረዉ ማዕከል ግን በጦርነቱ እንደፈረሰ ነዉ፤ ያየዉም የነካዉም ያለ አይመስልም። እሁድ ነኃሴ 16 ቀን ከምፅዋ ተነስተን 45 ደቂቃ ከነዳን በኋላ ዊሃ ደርስን። ዊሃ ሌላዉ የአርበኞች መንደር ነዉ። ዊሃ ያለዉ አርበኛ እንዴት እንደተቀበልን ለመግለጽ አማርኛ ቋንቋ እንደገና “ሀ” ብዬ መጀመር የሚኖርብኝ ይመስለኛል። በዚያ የወፍ ማረፊያ በሌለበትና በየሴኮንዱ ዉኃ ዉኃ በሚያሰኝበት ንዳድ ዉስጥ ወታደራዊ ሥልጠና መዉሰድ ቀርቶ አንድ ሜትር መራመድም እጅግ በጣም ይከብዳል። እንግዲህ ይታያችሁ የኛዎቹ ጀግኖች እንደዚህ የምድር ሲኦል በመሰለ ቦታ ነዉ ወገኖቻቸዉን ከወያኔ መንጋጋ ነፃ ለማዉጣት እልህ አስጨራሽ የሆነ ወታደራዊ ሥልጠና የሚወስዱት። እኔም የኢትዮጵያን ህዝብ ከወያኔ ዘረኞች ለማላቀቅ እንደወያኔ 17 አመት ጫካ ለጫካ መንፏቀቅ እንደሌለብን ቁልጭ ብሎ የታየኝ ዊሃ ሄጄ እነዚህን የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ስመለከት ነዉ። ሰኞ ነኃሴ 17 ቀን በጧት ተነስተን ጉርጉሱም ሄድን። ጉርጉሱም ቀይ ባህር ዳርቻ ላይ የሚገኝ ቆንጆ የመዋኛ ቦታ ነዉ። ቁርስ አዝዘን ሳንጨርስ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ መሪ አቶ ሞላ አስገዶም ከተፍ አለ። ታጋይ ሞላ በድንገት አልነበረም የመጣዉ፤ ልክ በቀጠሮዉ ሰዐት ነበር የደረሰዉ። አብሮን ቁርስ በላና እኛ ቀይ ባህር ዉስጥ ገብተን ስንምቦጫረቅ እሱ ማይ አጣል እንገናኝ ብሎ መኪናዉን አስነስቶ ከነፈ። ከጥዋቱ 11፡30 ሲሆን ዋናችንን ጨርሰን የምፅዋ አስመራን መንገድ ተያያዝነዉ። ከምፅዋ አስመራ ጉዞ ማለት ሽቅብ ወደሰማይ የሚደረግ ጉዞ ማለት ነዉ፤ እንደኔ አይነቱ የዋህ ሰዉ ሰማዩን ደርሶ በእጁ የሚነካ ይመስለዋል ፤ ግን ሰማዩም ሞኝ አይደለም ደረስኩብህ ሲሉት ይሸሻል። ከቀኑ 12፡30 ሲሆን ማይ አጣል ደረስንና አስፋልቱን ትተን ወደ ደምህቶች ካምፕ የሚወስደዉን የኮረኮንች መንገድ ተያያዝነዉ። ወደ ካምፑ ስንደርስ ዊሃን፤ ሄሬናን፤ አምሀጀርንና ሌሎቹንም የአርበኞች ግንቦት 7 ካምፖች ስንጎበኝ ያየነዉ ፍጹም ኢትዮጵያዊ የሆነ የእንግዳ አቀባበል ተደረገልን። በነገራችን ላይ የደምህቶችን ካምፕ ስንጎበኝ ይህ የመጀመሪያችን አይደለም። ለእግራችን ዉኋ ቀረበልንና ነጠላ ጫማ ያደረገዉ ሁሉ እግሩን በቀዝቃዛ ዉኃ አራሰዉ። ቀዝቃዛ ዉኋ ለእግር ማቅረብ በሁሉም አርበኞች ካምፕና በበረሃዉ የኤርትራ ክፍል የተለመደ ባህል ነዉ። ከቀኑ እንድ ሰዐት ሲሆን ምሳ ቀርቦ እየተበላ ቡና ይፈላ ጀመር። ረከቦቱ፤ጀበናዉ፤ ማቶቱ፤ የከሰል ምድጃዉ፤ ፈንዲሻዉና የተደረደረዉ ስኒ በቀጥታ ወደ አደኩበት ሠፈሬ ፒያሳ ወሰደኝ። አዎ! ፒያሳ… የአዲስ አበባዉ ሳይሆን የአዋሳዉ ፒያሳ። ቡናዉ እየተጠጣ ጨዋታዉ ሞቅ ሲል ቆየት ካሉት የጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃዎች አንዱ ከሩቅ በለሆሳስ ተሰማኝ። በዉኔ ነዉ በህልሜ ብዬ ቀና ስል ነአምን ዘለቀ ጥላሁንን ከቴፑ ጋር አብሮ ይጫወታል። በህልሜ አለመሆኔን አወቅኩት። በሞት የተለዩን ድምጻዉያን የኛዎቹም የዉጮቹም ከላይ ከሰማይ ቢጫወቱልን እርገጠኛ ነኝ ጋላክሲዉንና ናሳ “Black Hole” እያለ የሚነግረንን ዬትየለሌ ክስተት አቋርጦ ከፀሐይ ብርሐን ቀድሞ እኛጋ የሚደርሰዉ ዘመን አይሽሬዉ የጥላሁን ገሠሠ ድምፅ ብቻ ነዉ። ይህንን ስሜት የሚኮረኩር፤ ጅማት የሚወጥርና አዕምሮን ሰብስቦ በትዝታ የሚያስዋኝ ዉብ ቃና ነበር ደምህቶች ሲያሰሙን የዋሉት። ብቻ ምን ልበላችሁ. . . ወበቅ የተቀላቀለዉ የምፅዋ ንዳድ ሳይቀር ለጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃ ቦታዉን ለቀቀ። እኛም ወታደራዊ ትዕዛዝ የተሰጠን ይመስል የሁላችንም አፍ ተዘግቶ የሚንቀሳቀሰዉ እግራችን፤ ትከሻችንና ጭንቅላታችን ብቻ ሆነ። “አልማዝን አይቼ እልማዝን ሳያት”፤ “እንጉዳዬ ነሺ” “አመልካች ጣት” “መሳቁን ያስቃል” . . . ብቻ ምን አለፋችሁ የጥላሁን ሙዚቃ ተዥጎደጎደ። ጥላሁን ገሠሠ አስመራ ላይ የሚጠብቀንን ቀጠሮ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ እኛነታችንን አስረሳን። ቢበዛ አንድ ሰዐት ብለን የመጣን ሰዎች ከሦስት ሰዐት በላይ ከደምህት ጓዶቻችን ጋር ቆየን። በመጨረሻ የጉዟችን መሪ “አንድ ለመንገድ” ብሎ ከተቀመጠበት ተነሳ። እሱ ሲነሳ “እንክርዳድ እንክርዳድ የተንከረደደ፤ ስንዴ መስሎ ገብቶ ስንቱን አሳበደ” የሚለዉ ዘፈን እያለቀ ነበር። ነአምን. . . ነአምን ብዬ ስጣራ . . . “One for the road” ይቀረናልኮ አለ ነአምን . . . እንሂድ የምለዉ መስሎት። ይህንን ሙዚቃ እንደ እንክርዳድ ተቀላቅሎን ለሚያሳብደን የዳያስፖራ ቱልቱላ መርጫለሁ አልኩት። ሳቅ አለና ከቴፑ ጋር መጫወቱን ቀጠለ። እርግጠኛ ነኝ ተቦርነ በየነ ወይም መሳይ መኮንን አንድ ቀን “እንክርዳድ እንክርዳድን” በኢሳት ያሰሙናል። አይደል ተቦርነ? በመጨረሻ የኛም መሄጃ የሙዚቃዉም መገባደጃ ደረሰ። “One for the road” የተባለለት ሙዚቃ (ዘፈን) ገና ሲጀምር ሰማሁና ኢችንማ አምላክ ነዉ የመረጠልን አልኩ በልቤ። ያ በቁሙ “አጥንቴም ይከስከስ” ብሎ ያስተባበረን ጥላሁን ገሠሠ አሁንም ከላይ ከሰማይ ቤት “ቃልሽ አይለወጥ እባክሺ….ን” እያለ ቃል እንድንገባባ አደረገን። ተራ በተራ ከአርበኛ ሞላ አስገዶም ጋር እየተቃቀፍን “ቃልሽ- አይለወጥ- አባክሽን” ብለን ተለያየን። ቃል የዕምነት ዕዳ ነዉ ብዬ ነበር የጀመርኳችሁ፤ አሁንም ቃሌ ይሄዉ ነዉ። ቃላችን አይለወጥ! ቸር ይግጠመን። ኤፍሬም ነኝ ከአርበኞች መንደር

Friday, August 28, 2015

መልዕክት በድሆች ድህነት ለመክበር መሯሯጥ ላይ ላሉ የዲያስፓራ ማኅበረሰብ አባላት !

የግል ኑሮን ለማደላደል ሲባል የወያኔ አባል መሆን “ወይን ለመኖር” የሚል ስያሜ ከተሰጠው ዓመታት ተቆጥሯል። “ወይን ለመኖር” ዜጎች ነፃነታቸውን ለጥቅም አሳልፈው የሚሸጡበት፤ የሰው ልጅ ክብር የሚዋረድበት ገበያ ነው። በወይን ለመኖር “የገበያ ህግ” መሠረት እያንዳንዱ ዜጋ ሊያገኘው መብቱ የሆነውን አገልግሎት እንዲያገኝ የህወሓት፣ የብአዴን፣ የኦህዴግ፣ የደህዴግ፣ የአብዴፓ፣ የቤጉህዴፓ፣ የጋህአዴን፣ የሀብሊ ወይም የኢሶዴፓ አባል መሆን፤ አልያም መደገፍ ግዴታ ነው። እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች የህወሓት ተቀጽላ ወያኔዎች ናቸው። የእነዚህ ድርጅቶች አባል ወይም ደጋፊ ያልሆነ እንኳስ የመንግሥት አገልግሎት ሊያገኝ ጥሮ ግሮ ያፈራውንም ይነጠቃል።

በዚህም ምክንያት፣ በገጠር ያለው አርሶ አደር ቁራጭ የእርሻ መሬት፣ የግብርና ባለሙያዎች የምክር እገዛ፣ የማዳበሪያና ዘር ግዢ፣ ብድር ወይም እርዳታ ለማግኘት በአካባቢው ባለ የወያኔ ድርጅት አባልነት መመዝገብ፤ አንድ ለአምስት መደራጀት እና የወያኔን የስልጣን እድሜ የሚያራዝሙ ነገሮችን መሥራት ይጠበቅበታል። በከተሞች ውስጥም ሥራ ለመቀጠር፣ ለደረጃ እድገት፣ የመኖሪያ ቤት (ኮንዶሚንየም) ለመግዛት ሲባል መወየን አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ሆኗል:: በንግዱም ዘርፍ የንግድ ፈቃድ፣ የሥራ ቦታ እና የባንክ ብድር ለማግኝት፣ የመንግሥት ጨረታዎችን ለማሸነፍ፣ ከጉምሩክ እቃ ለማስለቀቅ፣ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት መወየን ግዴታ ነው።

“ወይን ለመኖር” የኢትዮጵያን ሕዝብ ያዋረደ፤ ለትውልድ የሚተርፍ የማኅበራዊ ስነልቦና ኪሳራ ያደረሰ እና ደካማውን ወያኔን ጠንካራ በማስመሰል በሕዝብ የትግል መንፈስ ውስጥ ፍርሃትን የረጨ መሆኑ ግንዛቤ እየዳበረ በመጣ መጠን እየቀነሰ የመጣ ክስተት ነው። በአሁኑ ሰዓት ከቀድሞው እጅግ በተሻለ ኢትዮጵያ ውስጥ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን ራሳችንን ከህወሓት ባርነት እያላቀቅን ምሬታችንን በግልጽ መናገር የጀመርንበት ወቅት ነው፤ ከዚያም አልፎ የህቡዕ ተግባራዊ የትግል እንቅስቃዎችን ማድረግ ደረጃ ላይ ደርሰናል።

አገር ውስጥ እየተዋረደ የመጣው “ወይን ለመኖር” በአገዛዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት በውጭ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን (ዲያስፓራ) መካከል ነፃነታቸውን በጥቅም የሚለውጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ፍለጋ ተሠማርቷል። አገዛዙ ተስፋ ያደረገው ያህል ባይሆንም ጥረቱ የተወሰነ ውጤት እያስገኘለት ነው። በጥቅማ ጥቅም እየደለለ ካመጣቸው ውስጥ በስርዓቱ ብልሹነት ያዘኑና የተሰማቸውን በግልጽ የተናገሩ መኖራቸው የሚያስደስትና የሚያበረታታ ቢሆንም ከመንደር ካድሬዎች ባነሰ ተለማማጮችና አጎብዳጆች በማየታችን ተሸማቀናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ካለነው አብዛኛው ሕዝብ አንፃር ሲታይ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ዲያስፓራዎች መካከልም ነፃነታቸውን በጥቅም ለመለወጥ የሚፈቅዱ መገኘታቸው አሳዛኝ ነው። እነዚህ ክብራቸውን በጥቅም የለወጡ ዲያስፓራዎች ዓለም ባንክንና የዓለም የገንዘብ ድርጅትን (IMF) ተክተው ህወሓት ስላስገኘው ፈጣን እድገት በአገዛዙ ራድዮ እና ቴሌቪዥን ሲነግሩን መስማት ያሳፍራል። የህወሓት አገዛዝ “ፍትህን፣ መልካም አስተዳርንና ዲሞክራሲን አስፍኗል፤ ይህንንም መጥተን በዓይኖቻችን ተመልክተናል” እያሉ የግፉን ገፈት እየቀመስን ላለነው ሲነግሩን መስማት ያማል።

እነዚህ ወገኖቻችን ህወሓትን በማሞካሸት የሚያገኙት መሬት ብዙ ድሆች የተፈናቀለቡት፤ ለእነሱ በብላሽ የተሰጠው ብድር በረሃብ ለሚጠቃ ወገን የተላከ እርዳታ መሆኑ ማሳሰብ ይገባል። ከህወሓትና አጫፋሪዎቹ ጋር ተስማምተው ባገኙት ገንዘብ የሚቆርሱት እያንዳንዱ እንጀራ የብዙ ወገኖቻችን ደምና እንባ የፈሰሰበት መሆኑ ማስገንዘብ ያሻል። ከህወሓት ጋር በማበር በወገኖቻችን ድህነትና ችጋር እየከበሩ ያሉ የዲያስፓራ ማኅበረሰብ አባላት ከዚህ እኩይ ሥራቸው እንዲታቀቡ ማስጠንቀቅ ይገባል። እኚህ ወገኖች የራሳቸው ክብር ማጉዳፋቸውን ብቻ ሳይሆን የልጅ ልጆቻቸውም የሚያፍሩባቸው መሆኑን ማስታወስ ይገባል። ከዚህም አልፎ የዛሬ ተግባራቸው ነገ በህግ የሚያስጠይቃቸው መሆኑን ሊያውቁ ይገባል።

አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የአገዛዙን እድሜ በማራዘም ላይ የተሰማሩ፤ በድሆች ድህነት ለመክበር በመሯሯጥ ላይ ያሉ፤ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ለአገዛዙ ጥብቅና የቆሙ የዲያስፓራ አባላት ከዚህ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ያሳስባል።

አርበኞች ግንቦት 7 “ከህወሓት ውድቀት በኋላ ያለው ጊዜ ለእናንተም ከዛሬው የተሻለ ይሆናል። ዛሬ ከህወሓት ጋር ያላችሁን ሽርክና አቋርጡ። ለነፃነት የሚደረገውን ትግል እርዱ፤ መርዳት ባትችሉ እንቅፋት አትሁኑ፤ አለበለዚያ ግን ከተጠያቂነት የማታመልጡ መሆኑን እወቁ” ይላል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!! !

Wednesday, August 19, 2015

አርበኞች ግንቦት 7 በዋሽንግተን ዲሲ፣ በዳላስ እና በሲያትል የተሳካ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን አካሄደ

August 18, 2015
አርበኞች ግንቦት 7 ባለፈው ነሐሴ 10 2007 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ በሸራተን ሆተል ባካሄደው የተሳካ የገንዝብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ቁጥሩ በርካታ ኢትዮጵያዊ መገኘቱን ለማወቅ ተችሏ።

ንቅናቄው በመላው አለም በማካሄድ ላይ ባለው ተመሳሳይ ፕሮግራም በአውስትራሊያ፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ከተሞች በስደት ነዋሪ የሆነው ነጻነት ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በነቂስ በመሳተፍ ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግል በደጀንነት ለማገዝ ቁርጠኝነቱን እያሳየ ይገኛል።

በየክፍለ አህጉሩ በመደረግ ላይ ባለው ዝግጅት ወያኔ በብዙ ሚልዮን ዶላር ወጭ ከየመን አውሮጵላን ጣቢያ ጠልፎ የወሰዳቸው የቀድሞ ግንቦት 7 ንቅናቄ ዋና ጸሃፊ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌና በቅርቡ የውህድ ድርጅቱን ለመምራት ወደ ትግሉ ሜዳ ያመሩት የንቅናቄው ሊቀመንበር የፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ምስሎች ለጨረታ እየቀረበ በውድ ዋጋ መሸጣቸው ታውቋል።

የወያኔ አገዛዝ በህዝባችን ላይ የጫነውን ግፍና መከራ በማስወገድ አገራችን ውስጥ ፍትህ እኩልነትና ነጻነት የሰፈነበት ዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የተጀመረውን ትግል የሚያግዝ የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ ዝግጅቶች በቀጣዩ ሳምንታት በሰሜን አሜካ፡በካናዳና በአውሮጳ ከተሞች እንደሚደረጉ እየተነገረ ነው።

አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን የሃይማኖት አባቶች፣ አርቲስቶች፣ የፖለቲካ አክቲቪስቶችና የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች ኢትዮጵያውያን በየዝግጅቶቹ ላይ በመገኘት ህዝቡን በማበረታታትና በማወያየት ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ።










Tuesday, August 18, 2015

እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ ግንቦት 7ን ለመቀላቀል መንቀሳቀሳቸውን አመኑ

እነ ብርሃኑ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ

‹‹ድርጊቱን ፈጽመናል፣ ጥፋተኞች ግን አይደለንም››

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር


ከግራ ወደ ቀኝ – ፍቅረማርያም አስማማው፣ ብርሃኑ ተክለያሬድ እና እየሩሳሌም ተስፋው
የኢትዮ-ኤርትራ ድንበርን በማቋረጥ ኤርትራ ከሚገኘው ግንቦት ሰባት የተባለ በተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ ከተፈረጀ የሽብር ቡድን ጋር ለመቀላቀል ሲጓዙ ድንበር አካባቢ ማይካድራ ላይ እንደተያዙ በመግለጽ በመንግስት የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ፡፡

ዛሬ ነሐሴ 11/2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ 14ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ እየሩሳሌም ተስፋው፣ ፍቅረማርያም አስማማውና ደሴ ካህሳይ ‹‹በክሱ ላይ የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም›› የሚል ጥያቄ ከፍርድ ቤቱ እየተነሳላቸው፣ በየተራ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚህም አራቱም ተከሳሾች ድርጊቱን እንደፈጸሙ በመግለጽ፣ ነገር ግን ጥፋተኛ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አንደኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ‹‹ሀገሬ በፋሽስት አምባገነኖች ተይዛ ዜጎች በጨቋኝ ስርዓት ውስጥ ስላሉ ሀገሬንና ህዝቤን ነጻ ለማውጣት ወጣትነቴን ሰውቼ ለመታገል ግንቦት ሰባት ከሚባል ነጻ አውጭ ድርጅት ጋር ለመቀላቀል ወስኜ ወደዚያው አቅንቻለሁ፡፡ ስለዚህ ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ፣ የግንቦት ሰባት አባል ነኝ፡፡ ወንጀለኛ ግን አይደለሁም›› ሲል ቃሉን ለፍርድ ቤቱ ሰጥቷል፡፡ ሁለተኛ ተከሳሽ እየሩሳሌም ተስፋው በበኩሏ፣ ‹‹ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ፤ ነገር ግን ጥፋተኛ አይደለሁም›› ብላለች፡፡

ሦስተኛ ተከሳሽ ፍቅረማርያም አስማማው ደግሞ፣ ‹‹ህገ-መንግስቱን አምኜ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ስሳተፍ የደረሰብኝን አውቃለሁ፡፡ ሰላማዊ ትግል እንደማያዋጣም ተረድቻለሁ፡፡ በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን ለመገንባት የሚያስፈልገው የነጻነት ትግል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ግንቦት ሰባት ነጻ አውጭን ለመቀላቀል ስጓዝ ማይካድራ ላይ ተይዣለሁ፡፡ ስለዚህ ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ፤ ጥፋተኛ ግን አይደለሁም›› ብሏል ለችሎቱ፡፡

አራተኛ ተከሳሽ ደሴ ካህሳይ በበኩሉ፣ ‹‹አርሶ አደር ነኝ፣ ሰሊጥ አመርታለሁ፡፡ ነገር ግን ያመረትሁትን ሰሊጥ የኢህአዴግ ወታደሮች ይዘርፉኛል፤ መስራት አልቻልኩም፡፡ በዚህ ምክንያት ሌላ ስራ መስራት ስላልቻልኩ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባርን ተቀላቅያለሁ፡፡ ለዚህ ግን ጥፋተኛ አይደለሁም›› ሲል የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን ቃል ካዳመጠ በኋላ የአቃቤ ህግን አስተያየት የጠየቀ ሲሆን፣ አቃቤ ህግ ተከሳሾች ጥፋተኝነታቸውን ስላላመኑ ማስረጃ እንዲያቀርብና እንዲያሰማ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ ማስረጃን ለመስማት ለነሐሴ 22/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Wednesday, August 12, 2015

አለቃዎ ሳይሆን ቅን ህሊናዎ የሚያዝዎትን በመፈፀም መልካም ዜጋ ይሁኑ!

መልካም ዜጋ ማለት ምን ማለት ነው?

ይህን ጥያቄ ለመመለስ በርካታ መጻሕፍት መፃፍ ይቻላል፤ መሠረተ ሀሳቡን ግን በጥቂት ዓረፍተ ነገሮች ማቅረብ ይቻላል።

መልካም ዜጋ ኢፍትሃዊ ተግባር ሲፈፀም “እኔ ምናገባኝ?” አይልም። መልካም ዜጋ “ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ”፤ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶም አይብቀል”፤ “እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም” እና በርካታ መሰል ምሳሌዎችን አይሰማም። መልካም ዜጋ በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ከነፃና ቅን ህሊናው ጋር ታርቆ ይኖራል።

የህወሓት አገዛዝ፣ መልካም ዜጋ ማለት የመንግሥት ሥልጣን የያዘን ማንኛውም አካል ማክበርና በታማኝነት ማገልገል ተደርጎ እንዲተረጎምለት ይሻል። ፍትህ የሚያዛባ መንግሥትን መቃወም የመልካም ዜጋ አቢይ ተግባር መሆኑ የዘመናችን ወጣት እንዳይገነዘብ ያደርጋል። በተለይ ባለሙያዎች የሚያገለግሉትን አገዛዝ ባህርይ እግምት ውስጥ ሳያስገቡ የተቀጠሩበትን ሥርዓት በታማኝነት ማገልገል የዜግነት ግዴታቸው አድርገው እንዲወስዱት ይወተውታል።

ኦስካር ግሮኒንግ ( Oskar Groening)የዘጠና አራት ዓመት ሽማግሌ ጀርመናዊ ነው። በጀርመን የሂትለር አገዛዝ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንፁሃን የተፈጁበት አሽዊትስ ካምፕ ውስጥ የሂሳብና ጽህፈት ሠራተኛ ነበር። ኦስካር ግሮኒንግ አንድም ሰው አልገደለም፤ አንድም ሰው አልገረፈም። እሱ ሂሳብ ነው የሠራው። ሆኖም በደል ሲፈፀም አይቶ “ምናገባኝ” ብሎ አልፏልና ከብዙ ዓመታት በኋላ ተከሶ በቅርቡ የ4 ዓመታት እስር ተፈርዶበት በሁለት እግሮቹ መቆም በማይችልበት በ 94 ዓመቱ በእርጅናውና በመጦሪያው ዘመን ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ፊት ተዋርዶ እስር ቤት ወርዷል።

በአንፃሩ ኦስካር ሽንድለር (Oskar Schindler) በጀርመን ናዚ ወቅት ሂትለር ይመራው የነበረው የናዚ ፓርቲ አባልና ሰላይ ነበር። ሆኖም ግን የሥርዓቱን ኢሰብዓዊነት ሲረዳ እዚያው የናዚ ፓርቲ ውስጥ ሆኖ አለቆቹ ያዘዙትን ሳይሆን ቅን ህሊናው ያዘዘውን በምስጢር መሥራት ጀመረ፤ በዚህም የ 1200 ሰዎችን ሕይወት ታደገ። ከጦርነቱ በኋላ ኦስካር ተከብሮ የኖረ በርካታ የክብር ስሞችና ሽልማቶች የተሰጠው በመልካም አርዓያነቱ የሚጠቀስ ሰው ሆነ።

በአገራችንም በአምስት ዓመታቱ የፋሽስት ወረራ ወቅት ስመ ጥር የውስጥ አርበኞች ነበሩ። ከነፃነት በኋላ ባንዶች እንኳን በውስጥ አርበኝነት ለመጠራት ያደርጉት የነበረውን እሽቅድድም ልብ በሉ።

በህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴግ፣ ደህዴግ እንዲሁም አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊና ኢሶዴፓ ያላችሁ ወገኞች ኦስካር ግሮኒንግን ወይንስ ኦስካር ሽንድለርን መምሰል ትፈልጋላችሁ? በህወሓት ፋሽስታዊ አገዛዝ የጦርና የፓሊስ ሠራዊት ውስጥ ያላችሁ ወገኖቻችን ነገ የምትዋረዱበትን ሥራ መሥራት ነው የሚበጃችሁ ወይስ ዛሬ ከህሊናችሁ ጋር ታርቃችሁ እየኖራችሁ ነገ ደግሞ ልጆቻችሁና የልጅ ልጆቻችሁ የሚኮሩበትን ተግባር መፈፀም ትፈልጋላችሁ? በአገዛዙ የስለላ ድርጅቶች ውስጥ ያላችሁ ወገኖች ስማችሁን በመልካም ማስጠራት አትሹምን?

ልቦና ያላችሁ ወገኖቻችን ሆይ! መልካም ዜግነት ሎሌነት አይደለም። መልካም ዜግነት ለቅን ህሊና ታማኝ መሆን ነው። መልካም ዜግነት ሲመች በገሀድ፤ ሳይመች በምስጢር ኢፍትሃዊነትን መዋጋት ነው።

አርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ በማናቸውም መንገድ በአገዛዙ የፓለቲካ፣ የጦርና የፓሊስ ተቋማት፤ በስለላም ይሁን በሌላ የሲቪል ሙያ የተሰማራችሁ ወገኖቻችን የታዘዛችሁትን ሳይሆን ቅን ህሊናችሁ የሚጠይቃችሁን በመሥራት ኢፍትሃዊ፣ ፋሽስታዊና ዘረኛ የሆነውን የህወሓት አገዛዝን እንድታዳክሙ ጥሪ ያቀርብላችኋል። በአገዛዙ ውስጥ ሆናችሁ እያለም የምትሠሩት ለሀገርና ለትውልድ የሚጠቅም በርካታ ሥራ አለ። የአገዛዙን ምስጢራዊ ሰነዶች ለአርበኞች ግንቦት 7 እንዲደርስ ማድረግ፤ አሊያም በማኅበራዊ ሚዲያዎች (ለምሳሌ ፌስ ቡክና ቱተር) ማሰራጨት ትልቅ ዋጋ ያለ ሥራ ነው። የህወሓት ፀረ-አገር እና ፀረ-ሕዝብ ፕሮጀክቶችን ማሰናከል ሌላ ትልቅ ሥራ ነው። በነፃነት ታጋዮች ላይ የሚደረጉ ዱለታዎችን ማክሸፍ ሕይወት አድን ሥራ ነው። ድርጅቶቹ ውስጥ ሆኖ ድርጅቶቹን ማዳከም የመልካም ዜግነት ግዴታ መወጣት ነው።

በሥርዓቱ ውስጥ ሆነው ኢፍትሃዊነትን ለማጋለጥ እና ሥርዓቱን ለማዳከም ለሚጥሩ ወገኞች አርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ ክብር አለው፤ ደህንነታቸው እንዲጠበቅም የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ፀረ ኢትዮጵያ እና ፀረ ሰው የሆነውን የህወሓትን ሥርዓት ለመጣል እና በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲ፣ እኩልነትና የሀገር አንድነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን ለማጽናት ከሥርዓቱ ውስጥም ውጭም የሚደረገውን ትግል እናፋፍም።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

Monday, August 10, 2015

የፕሬዚዳንት ኦባማ የአፍሪካ ኅብረት ንግግርና እንደምታው

የዩ ኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሐምሌ 21 ቀን 2007 ዓም አዲስ አበባ ውስጥ በአፍሪካ ኅብረት ጽ/ቤት ያደረጉት ንግግር በርካታ ቁምነገሮችን የያዘ በመሆኑ አንጽዖት ሊሰጠው እንደሚገባ አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ያምናል።
ፕሬዚዳንቱ በዚህ ንግግራቸው የአፍሪቃን በተለይም ደግሞ የአገራችንን ችግሮች ነቅሰው አሳይተዋል። ሰብዓዊ መብቶች ሰው በመሆናችን ያገኘናቸው በመሆኑ በቆዳችን ቀለም፣ በተወለድንበት አካባቢ፣ በምንናገረው ቋንቋ ወይም በሌላ ማናቸውም ምክንያቶች ሊሸራረፉ የማይገቡ መሆኑን በመግለጽ “ሁላችንም እኩል ተወልደናል” በማለት ዘረኞችን አፍ የሚያዘጋ ኃይለቃል ተናግረዋል። “ሁላችንም ከአንድ ግንድ የበቀልን ነን፤ ሁላችንም አንድ ቤተሰብ ነን፤ ሁላችንም አንድ ጎሳ ነን” ካሉ በኋላ በዓለም ያለው አብዛኛው ችግር ይህንን መረዳት አለመቻላችን፤ ራሳችንን በእያንዳንዳችን ውስጥ ማየት አለመቻላችን ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ በብዙ የአፍሪቃ አገሮች፣ ዜጎች ነፃነታቸው የተገፈፈ መሆኑን፤ ምርጫ መኖሩ ብቻ ዲሞክራሲ ሰፈነ ማለት አለመሆኑ አብራርተዋል። ጋዜጠኞች፣ የተቃውሞ ፓለቲካ መሪዎችና ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች፣ የሲቪክ እንቅስቃሴዎች መሪዎችን በእስር ቤት እያጎሩ ወይም በነፃነት እንዳይቀሳቀሱ እያደረጉ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አደረግን የሚሉ አገሮች መኖራቸው ለመግለጽ ኢትዮጵያን በዋቢነት ጠርተዋል።

ፕሬዚዳንት ኦባማ የሰላምና የደህንነት ጉዳይ ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑን በሰፊው ከገለጹ በኋላ ለሰላም ሲባል ነፃነትን መንፈግ ሁለቱንም ሊያሳጣ የሚችል መሆኑም አስገንዝበዋል።
እድገትን በማፋጠን ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት አዲስ አስተሳብ ያሻል፤ ለአዲስ አስተሳሰብ ደግሞ በነፃነት ማሰብ፤ ድምፃቸው የሚሰማ ዜጎች መኖር እና የሰብዓዊ መብቶች መከበር ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸው አጽንኦት ሰጥተውበታል። የአፍሪቃ መሪዎች ሥልጣን ላለመልቀቅ የሚሄዱትን ርቀት በማንሳት ተሳልቀውበታል፤ ሙስናም የልማትና የመልካም አስተዳደር ፀር መሆኑን አስምረውበታል።

አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ ይኸ ቀራቸው በማይባል ሁኔታ በአህጉራችን በአፍሪቃ በተለይ በኢትዮጵያ የሰፈነው ክፉ አገዛዝ መተቸታቸው፤ ይህንን እዚያው የአፍሪቃ መዲና በሆነችሁ አዲስ አበባ ተገኝተው መናገራቸው በበጎ ይመለከተዋል። እሳቸው ያነሷቸውን ቁም ነገሮችን አድምጠው ማስተካከያዎችን የሚያደርጉ ገዢዎች ኑረውን ቢሆን ኖሮ የኛ ትግል ባላስፈለገ ነበር። ችግሩ መስማት እንጂ ማዳመጥና መተግበር የማያውቁ ገዢዎች የሰፈኑብን መሆኑን ነው።
ስለሆነም፣ አርበኞች ግንቦት 7: ፕሬዚዳንት ኦባማ በአፍሪቃ ኅብረት ንግግራቸው ሀቁን አብጠርጥረው በመናገራቸው የተሰማውን አድናቆት ይገልፃል፤ በዚሁ አጋጣሚ ደግሞ በንግግራቸው ያነሷቸው ቁምነገሮችን መደመጣቸውና በተግባር መተረጎማቸውን እንዲከታተሉ አበክሮ ይጠይቃል።

የፕሬዚዳንት ኦባማ ንግግር በሀቅ ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ የህወሓት ሽማምንት የተከፉ ቢሆንም የኢትዮጵያን ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እውነታ የመቀየር ኃላፊነት የእኛው የኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት መሆኑን በመረዳት፤ ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲና ለአገር አንድነት ግድ ያለን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ተባብረን አገራችን ከዘረኛውና ፋሽስታዊ ህወሓት አገዛዝ ነፃ የማውጣት ተጋድሎዓችን አጠናክረን እንድንቀጥል አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

Wednesday, August 5, 2015

በአርበኞች ግንቦት 7 ሕዝባዊ ትግል ላይ ከየአቅጣጫው እየተሰነዘሩ ያሉ ፈተናዎችና ማርከሻ መድኃኒታቸው!


በአርበኞች ግንቦት 7 ሕዝባዊ ትግል ላይ ከየአቅጣጫው እየተሰነዘሩ ያሉ ፈተናዎችና ማርከሻ መድኃኒታቸው!





እግዚአብሔር ይመስገንና አሁን የነገዋን ነጻይቱን ኢትዮጵያ ለማየት መንገዱ ላይ ቆመን መራመድ የቻልንበት ሰዓት ላይ ደርሰናል፡፡ ይሄ ትልቅ ትልቅ እመርታ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ራሱ ወያኔ ተሸንፎ እንደወደቀ መቁጠር ይቻላል፡፡ የቀረው የባለሥልጣኑ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ነገ የሚሆነው ነገ እንጅ ዛሬ ስለማይሆን ብቻ ነው፡፡ ነገ ግን ዛሬ መሆኑ አይቀርምና ነገ የምንጨብጠውን ዛሬ እንደጨበጥነው መቁጠር ይቻላል፡፡
ይህ ታላቅ እመርታ እንዳይመዘገብ ወያኔ የሀገር ክህደት በመፈጸም ለጎረቤት ሀገራት ሉዓላዊ የሀገሪቱን መሬት እየቆራረሰ ከመስጠት ጀምሮ በተለያየ ጥቅም በመያዝ መሸሻ መሸፈቻ መደራጃ መንቀሳቀሻ መንደርደሪያ እሱ ሱዳንን ይጠቀምባት እንደነበረውና ከሱዳን ያገኝ የነበረውን ድጋፍና ምቹ ሁኔታዎች የሚሰጠን ጎረቤት ሀገር እንዳይኖርና እንዳናገኝ ለማድረግ ያላደረገው ነገር ያላስቀመጠው መሰናክል ያልቆፈረው ጉድጓድ አልነበረም፡፡ ይሄንን ዕድል ልናገኝ የምንችልበት አንድ ቦታ ከተገኘ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሶተኛ ከመሆኑና ይሄንን አጋጣሚ የሚጠባበቅ ከመሆኑ የተነሣ አርፎ ተቀምጦ የነበረውም አማራጭ ስላጣ ብቻ እንደሆነ ይሄንን ዕድሉን ባገኘ ጊዜ ግን ወያኔ ዕድሜ እንደማይኖረው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያልቅለት ጠንቅቆ ያውቀዋልና፡፡ መሸሻ መሸፈቻ ለማሳጣት ይሄንን ያህል ርቀት የተጓዘው ወያኔ ይህ አሁን ከባሕረ ምድር (ኤርትራ) ላይ ያገኘነውንም ለማሳጣት ለማበላሸት ይሄም አልሆን ሲለው ሐሰተኛ የፈጠራ ወሬና ሴራ በመጠንሰስ እንድንሸሽና እንዳንጠቀምበት ለማድረግ በከፍተኛ ደረጃ ሲጥር ነበር እየጣረም ይገኛል፡፡ እውነቱን መለየት ማወቅ መረዳት እስኪያቅተን ድረስ ባሕረ ምድር የመሸጉትን የነጻነት ታጋዮችን ትግል ሊያደናቅፍ ሊያሰናክል ሊያጨናግፍ የሚችሉ የሆኑና ያልሆኑ ነገሮችን መሠረት ያደረጉ ስሞታዎችን ስም ማጥፋቶችን ድምዳሜዎችን የያዙ መጣጥፎች አሁን ማንነታቸው ይበልጥ ግልጽ እየሆኑ እየታወቁ በመጡ ግለሰቦች ቀደም ሲል ግን በጣም ተአማኒነት በነበራቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ድረ ገጾች ላይ እየተለቀቁ እየቀረቡ ትግሉን እንድንጠራጠር እንዳናምን እንድንሸሽ ከዚያም አልፎ በጠላትነት እንድንፈርጅ ለማድረግ ከባድ ከባድ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡
ከዚህ በኋላም ወያኔ እስካለ ድረስና የዕጣ ፈንታው የመጨረሻ መጨረሻ ሰዓት የደረሰ መስሎ እስከታየው ድረስ አያደርገውም የሚባል ነገር ሳይኖረው ሊያደርገው የማይችለው ምንም ዓይነት ነገር ሳይኖር እስከ የመጨረሻ ህቅታው ድረስ የጣረሞቱን በመንፈራገጥ አቅሙን አሟጦ በመጠቀም የተቻለውን ሁሉንም ዓይነት ጥረቶች በማድረግ ይቀጥላል እንጅ ይቆማል ብላቹህ አታስቡ፡፡ አሁን አሁን ከእነዚያ ስም ማጥፋቶች የተጋነኑ ስሞታዎችና የፈጠራ ውንጀላዎች ትክክለኛ የተፈጸሙ ከሆኑትም ጀርባ የወያኔ እጅ እንዳለ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡ እኔ በእርግጥ ጥርጣሬው የነበረኝ ቢሆንም አብዛኞቻችን ይሄንን አለመገመታችን አለመጠርጠራችን ምን ያህል የዋሆች ብንሆን ነው እያሰኘኝም ነው፡፡
እነኝህን ጽሑፎች ይጽፉና በድረ ገጻቸው ይለጥፉ የነበሩ ግለሰቦችና ድረ ገጾች አንዳንዶቹ አስቀድሞ በነበረው ማንነታቸው በወያኔነት የምንጠረጥራቸው አልነበሩም፡፡ አንዳንዶቹ ግን ወያኔ በስውር ለዚሁ ዓላማው አስቀድመው ተአማኒነትን አግኝተው እንዲቆዩ አድርጎ ያዘጋጃቸው ናቸው፡፡ ቀደም ሲል በወያኔነት የማንጠረጥራቸው ወይም ወያኔ ያልነበሩትም ቢሆኑ ትናንት አልነበሩም ማለት ዛሬ አይሆኑም ማለት አይደለም፡፡ ወያኔ የመጨረሻው መጨረሻ የደረሰ መስሎ ከታየው እራሱን ለማዳን የሚቆጥበውና የሚሰስተው ምንም ነገር የለም፡፡ እንዳልኳቹህ የሀገርን ካዝና አራቁቶም ቢሆን ገንዘብ ይረጫል፣ ፍላጎታቸው ገንዘብ ሳይሆን ጉዳዮች እንዲፈጸምላቸው ለፈለጉት ጉዳዮቻቸውን ይፈጽምላቸዋል፣ ፍላጎታቸው እነዚህ ሁቱም ያልሆነና ሥልጣን ለሚፈልጉትም ከሚንስትርነት እስከ ዲፕሎማትነት (አቅናኤ ግንኙነት) ድረስ ሥልጣን እየሰጠ ይደልላል፡፡ ሌላው ቀርቶ አያገኝም እንጅ እንዲህ አድርገሀል እንዲህ ብሎ ለፍርድ ላቅርብህ ሳይለው ከሀገር ክህደት እስከ የዘር ማጥፋት ለፈጸመው ወንጀል ላይጠይቀው አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጠው አካል ቢያገኝ የመንግሥት ሥልጣንን ሁሉ አሳልፎ በመስጠት እራሱን ለማዳን ዝግጁ ነው፡፡

አሁን በዚህ ዘመን በእነዚህ ወያኔ ያንዣበበበትን አደጋ ለማስቀረት ሳይሰስት በሚያቀርባቸው መደለያወች የማይለወጥ የማይደለል ሰው ማግኘት በጣም ከባድ እየሆነ ከመምጣቱ የተነሣ ብዙዎች ያውም በቀላል በቀላል ነገር እየተደለሉ ሕዝብን እንደካዱ ስናይ ቆይተናል፡፡ አብሶ ደግሞ ሀገርና ሕዝብ ነጻ ሆነው ማየት ቁርጠኛ ዓላማ ይዞ ሳይሆን ከግል ጥቅሙ ከዝናና እውቅና ፍለጋ አኳያ እንዲሁም ወያኔ ተወግዶ እሱም ሥልጣን ይዞ በተራው ባለ ሥልጣን ለመባል፣ ለመኮፈስ፣ ሕዝብን ከጫማው ስር ለመርገጥ፣ በግል ጉዳዩ ለገጠመው ችግር የተጣላውን ለመበቀል፣ ለማዘዝ ለመናዘዝ ወይም ደግሞ ለመብላት ምኞትና ፍላጎት ይዞ በተለያዩ የሕዝባዊ ትግል ዘርፎች ተሰማርቶ ወያኔን እየተገዳደረ እየተሯሯጠ ያለ ሰው ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን ሰው የያዘውን ሕዝባዊ ትግል በማስካድ ወያኔ የሚፈልገውን ነገር አቅርቦለት አድርጎለት ደልሎ መጠቀሚያው አገልጋዩ እንዲሆን ለማድረግ አይቸግረውም፡፡ አሁን እያስቸገሩ ያሉ ግለሰቦች የተደለሉበት ገንዘብ ወይም ሌላ የመደለያ ነገር መጠንና ዓይነት ይለያይ እንደሆነ ነው እንጅ ከላይ የጠቀስኩትን ዓይነት ፍላጎቶች ይዘው በተለያየ መስክ ሕዝባዊ ትግል ያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች እንደነበሩ አሁን ላይ እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡

በሙስሊም እንቅስቃሴ መሪዎች ላይ የተሰጠውን ፍርደገምድል ፍርድን እናወግዛለን!

የህወሓት አገዛዝ የሚዘውረው የይስሙላ ፍርድ ቤት ዛሬ ሀምሌ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በሙስሊም ወገኖቻችን መሪዎች ላይ ፍርደገምድል ውሳኔ ሰጥቷል። በዚህ ውሳኔ መሠረትም የእምነት መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው በሰላማዊ በሆነ መንገድ የጠየቁ ወገኖቻችን መሪዎች እስከ 22 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

ሙስሊም ወገኖቻችን ጥያቄዎቻቸው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ሥርዓቱ ያደረገውን ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችን ተቋቁመው “ድምፃችን ይሰማ!” የሚል አቤቱታ ከማቅረብ የዘለለ አንዳችም የኃይል እርምጃ ወስደው አያውቁም። ሆኖም “በደል ደርሶብኛልና ልሰማ” ብሎ አቤቱታ ያቀረበ ሕዝብ መሪዎችን እስከ ሃያ ሁለት ዓመታት በእስር መቅጣት የአገዛዙ እብሪትና ማናለብኝነት አጉልቶ የሚያሳይ ተግባር ነው።

አርበኞች ግንቦት 7:የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህን ፍርደገምድል ውሳኔ አጥብቆ ያወግዛል።ይህ ፍርደገምድል ውሳኔ የተሰጠው ፕሬዚዳንት ኦባማ በአገራችን መዲና ተገኝተው “ለሰላም ሲባል ነፃነትን ማፈን ሁለቱንም ያሳጣል” ባሉ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሆኑ አገዛዙ የሚሰማ ጆሮ የሌለው መሆኑ የሚያረጋግጥ ሆኗል።

የሙስሊም መሪዎች በእስር ላይ በነበሩት ጊዜ በምርመራ ስም ተደብድበዋል፤ ክብራቸው ተደፍሯል፤ የተለያዩ ዘግናኝ ሰቆቃዎች ተፈጽሞባቸዋል፤ የሀሰት ዶክመንታሪ ፊልሞች እንዲሰራጩ ተደርገው ስማቸውን ለማጥፋት ሙከራ ተደርጓል።

በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ የደረሰው በደል ሃይማኖት ሳይለይ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰ በደል ነው፤ መፍትሄ የምናገኘውም በጋራ በምናደርገው ትግል ህወሓትን አስወግደን በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና የአገር አንድነት የሚጠብቅ የመንግሥት ሥርዓት ስናቆም ነው። ከዚህ በመለስ የሚገኝ መፍትሄ የለም። የእምነት መብቶች የሚከበሩት ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ ሲከበሩ እንደሆኑ “በድምፃችን ይሰማ” ሥር የተሰባሰቡ ወገኖቻችን ይረዳሉ ብለን እናምናለን።

አርበኞች ግንቦት 7 ሙስሊም ወገኖቻችን ለዓመታት ያለመታከት ያካሄዱትን ትግል ያደንቃል። ከእንግዲህ ደግሞ እጅ ለእጅ ተያይዘን፤ ተደጋግፈን በመታገል ህወሓትን አስወግደን በምትኩ ለሁላችንም የምትመች አገር እንድንገነባ ጥሪ ያደርጋል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ

Saturday, August 1, 2015

ሁሉም በያለበት የነፃነት ትግሉን ይቀላቀል!!!

እኛ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ የሰውነት መብታችን ተገፎ የዜግነት ነፃነታችን ተረግጦና ተዋርደን የምንገኝበት ጊዜ ቢኖር ዛሬ ነው፡፡ የጅምላ ግድያ፤ የጅምላ እስርና የጅምላ ስደት እንደ ዘመነ ወያኔ የታየበት ዘመን የለም፡፡ ህፃናት በረሀብ ከሚማሩበት ክፍል ውስጥ የሚወድቁበት ፤ ወንድ ልጅ በደህንነት ሀይሎች ታፍኖ የሚደፈርበት፤ ሴት ልጅ በገመድ የታሰረ የባልዋነወ ብልት መንገድ ለመንገድ እንድትጎትት የተደረገበት ዘመን ቢኖር ያሳለፍነው የወያኔ ዘመናት ብቻ ነው፡፡ ባጠቃላይ የሰው ልጅ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ መከራና ሰቆቃ እንድንሸከም የተገደድንበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡

በአንፃሩም ስለ ለፃነት ስለ ፍትህና እኩልነት ሲሉ የተሰዉ ዋጋም የከፈሉ፤ አሁንም እየከፈሉ የሚገኙ ጥቂት አይደ ሉ ም፡፡ ከነዚህም አንዱ አርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይህ ለነፃነት ለፍትህና ለ ዲሞክራሲ የሚደረገው ተጋድሎ ውሎ አድሮ ዛሬ ከዋናውና ወሳኝ ከሆነው ምእራፍ ላይ መድረሱ ደግሞ የሁላችንንም ተስ ፋ ያለመለመና የተደፋው አንገታችን ቀና ያደረገ መሆኑና በተቃራኒው የወያኔን ካንፕ ያሸበረ መሆኑ በገሀድ እየታየ የሚገኝ እውነት ነው፡፡

እንግዲህ ይህን ወራዳ ስርአት አስወግዶ በምትኩ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመተካት የሚደረገው ትግል ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ የተደረገው ርብርብ ቀላል ባይሆንም ቀሪውን አጠናቆ ከዳር ለመድረስ ከመቼውም ጊዜ በላይ የእያንዳዱን ኢትዮጵያዊ የተግባር ተሳትፎ የሚጠይቅ፤ ሁሉም ከያለበት ስለ ነፃነት የሚደረገውን የአርነኝነት ትግል በመቀላቀል የድርሻ ውን ሀላፊነት መወጣት ከሚጠይቅበት ወሳኝ ምእራፍ ላይ መድረሳችንን መረዳት ግድ ይላል፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ያለ ማንም እርዳታና ድጋፍ ዋጋ ከፍሎ ለፃነትን የማሰከበር እንግዳ ሳንሆን በታሪክ የምንታወቅበት መለያችን መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ እንኳን ዛሬ አለም አለም በጠበበችበት ዘመን ቀርቶ ትናንት በጨለማው ዘመን እንኳ እነ ዶ/ር መላኩ በያን ከአኛ አልፎ ለአፍሪካ ነፃነት ፈር ቀዳጅ ሆነው የተገኙበትን ታሪክ ማስታወስ ይገባል፡፡

እናም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኟውም ስፍራ የሚገኝ ሁሉ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግል እውቀት ያለው በእውቀቱ፤ ጉልበት  ያለው በጉልበቱ፤ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ለመደገፍ ዛሬ ነገ ሳይል አሁኑኑ ከአርበኝነቱ ትግል መቀላቀል ይጠበቅበታል፡፡ ኢትዮጵያዊነታችንን ብቻ ሳይሆን ሰው መሆናችን የሚረጋገጠው ነፃነታችንን አስጠብቀን በነፃነት መኖር ስንችል ብቻ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

ስለዚህ ዛሬ አርበኞች ግንቦት ሰባት የለኮሰው የነፃነት ቀንዲል ከነጻነት አደባባይ ለመትከል የጀመረውን ጉዞ በሰው ሀይል፤ በገንዘብና በቁሳቁስ በማገዝ ሁላችንም የድርሻችንን እንድንወጣ ጥሪ ስናደርግ ለእኛ ኢትዮጵያውያን ከእኛ ኢትዮጵ ያውያን ውጭ ማንም እንደሌለ በማስገንዘብ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!