Wednesday, February 18, 2015

ፍርድ ቤቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አቤቱታ ላይ ቀጠሮ ሰጠ

የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በዘላለም ወርቃገኘው ክስ መዝገብ የተከሰሱት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በማረሚያ ቤት አስተዳደር ላይ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 25/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጠ፡፡ በዛሬው ችሎት የተከሳሾቹ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ‹‹ህዳር 12 ለ 13/2007 ዓ.ም አጥቢያ ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎ የተጠርጣሪዎቹ ንብረት ተወስዶባቸዋል፣ የሰብአዊ ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል፣ ድንገተኛ ፍተሻው ህገ ወጥ ነው›› በሚል በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ላይ ላቀረቡት አቤቱታዎች ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን መልስ ሰምቷል፡፡
የማረሚያ ቤቱ መልስ በጽሁፍ ከቀረበ በኋላ በቃልም እንዲቀርብ በታዘዘው መሰረት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የቀጠሮ ማረፊያ አስተዳደር አስተዳዳሪ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አምባዬ ክቡር ፍተሻው መካሄዱን አምነው ነገር ግን፤ ‹‹ፍተሻው የተከናወነው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከጠዋቱ 12 ሰዓት በኋላ ነው፡፡ ፍተሸውም በአቤቱታው ላይ እንደቀረበው ባልታወቁ ሰዎች ሳይሆን በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጥበቃዎች ነው የተከናወነው›› ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡ የፍተሻውን አላማም ‹‹የታራሚዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የተከለከሉ ነገሮችን ፈትሾ ለማስወገድ ነው፡፡ በፍተሸውም ሚስማር፣ ስለት ነገሮች፣ እንዲሁም ብጥብጥ የሚቀሰቅሱ ጽሁፎች ተገኝተዋል፡፡›› ብለዋል፡፡
ባለፈው የአብዛኛዎቹ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ውድቅ ሲደረግ የ7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን፣ እንዲሁም 8ኛ ተከሳሽ ሰለሞን ግርማ የተወሰኑ የክስ ማሻሻያዎች እንዲያደርግ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረት በዛሬው ዕለት በሁለቱ ተከሳሾች ላይ አሻሽየዋለሁ ያለውን ክስ አቃቤ ህግ ይዞ ቀርቦ በንባብ አሰምቷል፡፡
በመጨረሻም በፍተሻው ወቅት ተፈጽሟል በሚል በተከሳሾቹ ጠበቃ የቀረበውን አቤቱታና ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን መልስ አገናዝቦ ውሳኔ ለመስጠት እንዲሁም፤ በሁለቱ ተከሳሾች ላይ የቀረበው ማሻሻያ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ‹‹ተሸሽለዋል ወይንም አልተሸሻሉም›› የሚለውን ለመወሰን ለየካቲት 25/2007 ዓ.ም ጠዋት 3 ሰዓት ላይ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Tuesday, February 17, 2015

‹‹ሰላማዊ ትግሉ ሲጠናከር ስርዓቱ ወደ አውሬነት ይቀየራል›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት

• ‹‹ቃል (በዛሬው ዕለት ለቀድሞው የአንድነት አመራሮችና አባላት የተዘጋጀው የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ላይ ከተናገሩት)


(ነገረ-ኢትዮጵያ) ፓርቲ ጣኦት አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ቅንጅትንም አፍርሶታል፡፡ አንድነትንም አልፈረሰም ብለው እንዳይከሱኝ እንጅ አፍርሰውታል ማለት እችላለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሰማያዊ ላይም አንድ ነገር ማምጣታቸው የማይቀር ነው፡፡ ያ ማለት ግን ሰላማዊ ትግሉ ምን ያህል እንዳስፈራቸው ነው የሚያሳየው፡፡ አገዛዙ በፓርቲዎች ላይ የሚወስደው እርምጃ የሚያሳየው ሰላማዊ ትግሉ መጠናከሩን እንጅ ወደኋላ መመለሱን አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ እንዲህ አይነት ችግር ሲከሰት ሰላማዊ ትግሉ አበቃለት ይላሉ፡፡ ሆኖም አገዛዙ ሰላማዊ ትግል አስፈርቶት አውሬ ሲሆን የሚያረጋግጥልን ሰላማዊ ትግሉ መጠናከሩን ነው፡፡

በመሳሪያ ትግል ውስጥ አንድ ጀኔራል ሲሞት አሊያም አንድ የጦሩ አካል ችግር ሲደርስበት ‹‹የትጥቅ ትግል አበቃለት›› እንደማይባለው ሁሉ ሰላማዊ ትግል ላይ አንድ ጫና ወይንም የስርዓቱ ደባ ሲከሰት ትግሉ አይሰራም ማለት አይደለም፡፡

ሰላማዊ ትግል መስዋዕትነት አያስከፍልም ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ሰላማዊ ትግል ውጤት ማምጣት ሲጀምር፣ ዙሩም ሲካረር፣ የሚከፈለው ዋጋም ይበልጥ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ የስርዓቱ አውሬነት በተገለጠ ቁጥር፣ እኛም በተሻለ አመራር ትግሉን ስንመራው መስዋዕትነቱ ይበልጡን እየበዛ እንደሚመጣ እንረዳለን፡፡

ተመስገን ደሳለኝ ምልክታችን ነው! – ከበድሉ ዋቅጅራ

ተመስገን ደሳለኝ ምልክታችን ነው፤ ልንሸፍነው ያልቻልነው ምልክት፡፡ ተመስገን የተከሰሰውና የተፈረደበት ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት አለው ወይም ደግሞ አሸባሪ ነው ተብሎ አይደለም፤ የተከሰሰውም የሶስት አመት እስር የተፈረደበትም በጻፈው ጽሁፍ ነው፡፡ በመሆኑም ተመስገን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ህገመንግስታዊ መብታችን ያለመከበር ምልክት ነው፡፡ ተመስገን ጠንካራ ግለሰባዊ ሰብእናውንና ህገመንግስታዊ መብቱን በመጠቀም፣ ለዚህች ሀገርና ለህዝቦቿ ይበጃል ያለውን ሀሳብ ለመግለገልጽና በሰላማዊ መንገድ ለመሟገት አፍላ የወጣትነት እድሜው ያላጓጓው ዜጋ ነው፡፡ በመሆኑም ተመስገን የ‹መሬት ላራሹንና የብሄረሰቦችን መብት ጥያቄ አንግበው በነሳት ላመኑበት እንደታገሉት አይነት ወጣቶች ዛሬም ለመኖራቸው ምልክት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ተመስገን የዘመን ተሻጋሪው ኢትዮጵዊ አስተሳሰባችንና ስብእናችን አጋላጭ ምልክት ነው፡፡ በዘመነ ፊውዳሊዝም ለተገኘው ለውጥ (ትሩፋቱ በጎም ይሁን ክፉ) መስዋእትነት የከፈሉት ጥቂቶች ናቸው፡፡ በደርግ አብዮታዊ አገዛዝ ዘመንም የታሰሩት፣ ተገድለው የተጣሉት፣ ለትግል የወየኑት፣ የተሰደዱት ጥቂቶች ናቸው፡፡ አሁንም ከዚሁ የተለየ አይደለም፤ ስለህዝባችንና ሀገራችን፣ ስለፖለቲካዊው አስተዳደራችን ያገባናል ብለው በድፍረት መንግስትን የሚሞግቱት ጥቂቶች ናቸው፡፡ በሶስቱም ዘመን በአጋጣሚው ተጠቅመው ሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅምን፣ በአንድ እንጀራ አፉን ለሚዘጋ ወስፋታቸው ጩኸትና በቃኝ ለማያውቅ ፍትወተ-ንዋይ ማርኪያ የተጠቀሙበት በርካቶች ናቸው፡፡ አብዛኛው ህዝብ ግን በገዢዎቹ የጭካኔ ድንኳን ውስጥ በፍርሀት ተደቅድቆ ‹‹በአያገባኝም›› እንዳላዘነ አለ፡፡ ይህ ህዝብ ስለልጁ መረሸን አልጠየቀም፤ አላለቀሰም፡፡ በገዢዎቹ የሚጣሉበትን አዋጆች ይቆጥራል እንጂ፣ በአዋጆቹ ስለሚያጣው መብቱ ወይም ስለሚያጎናጽፉት ትሩፋት አይጠይቅም፡፡ ይህ ህዝብ እያጨበጨበ የሚፈጥራቸውን ተሟጋቾቹን (ጀግኖቹን) እራሱን እየነቀነቀ ወደ እስር ቤት፣እያለቀሰ ወደ ቀብር ከመሸኘት በቀር ‹‹ለምን?›› ብሎ አይጠይቅም፡፡ በመሆኑም ተመስገንና ሌሎች ሀሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ ሲገልጹ፣ ለእስርና ለስደት የተዳረጉ ዜጎች፣ የዚህ ከዘመን ጋር እየሰለጠነና እየዳበረ የመጣ ጸያፍ ኢትዮጵያዊ ስብእና አሉታዊ ምልክቶች ናቸው፡፡

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የትግል ጥሪ አስተላለፈ

የ9ኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል መርህ የሁለተኛ ዙር የሠላማዊ ትግል ጥሪውን ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስተላለፈ፡፡ ትብብሩ የካቲት 15 ቀን 2007 ዓ.ም በተመሳሳይ ሰዓት በ15 ከተሞች ሊያደርገው አቅዶት የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ በሳምንት አራዝሞ ለየካቲት 22 ቀን 2007 ዓ.ም ማስተላለፉንም አስታውቋል፡፡
ትብብሩ ዛሬ የካቲት 10 ቀን 2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በሰጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ገዢው ፓርቲ የቱንም ያህል አሰቃቂና አረመኔያዊ የአፈና እርምጃዎች ቢወስድም የህዝብ ጥያቄዎች እስካልተመለሱ ድረስ ህዝባዊ ትግሉን ማዳፈን እንጂ ማስቆም እንደማይችል ይልቁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከተለያዩ የህዝብ እንቅስቃሴዎች መገንዘቡን ገልጹዋል፡፡ ትብብሩ ምርጫን በተመለከተ እንዳስታወቀው ኢህአዴግ ስለመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከቃላት ያለፈ እምነትም ሆነ ቁርጠኝነት የሌለው መሆኑን በዚህ የምርጫ ወቅት በተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ እየወሰደ ያለው ህገ-ወጥ እርምጃ ማሳያ ነው ብሏል፡፡
‹‹ለውጡ የሚመጣባቸው አምባገነኖች ድንገተኛ ከፍተኛ ፍርኃትና ሥጋት በማሳደሩ ህገ-መንግሥቱን በመጨፍለቅ በግልጽና በአደባባይ ህገ-ወጥ ውሳኔዎችንና እርምጃዎችን ለመውሰድ መገደዳቸው፣ ይህም የህዝቡን የለውጥ ፍላጎትና የትግል ተነሳሽነት በማሳደግ ህዝባዊውን ትግል ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገሩ የበለጠ ግልጽ ሆኗል›› ብሏል ትብብሩ፡፡
ትብብሩ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ የአገራችንና ዜጓቿ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በሁለት አማራጮች ላይ የተንጠለጠለ ነው ያለው መግለጫው፣ አንድም ያለውን አምባገነናዊ ሥርዓት ተቀብሎ የጭቆና ቀንበር ተሸክሞ በከፋ ውርደት ሥር ሰጥ- ለጥ ብሎ መገዛት፣ አሊያም አምባገነንነትና ጭቆናን ‹‹በቃ›› በማለት በሕዝባዊ የተቀናጀ ሰላማዊ ትግል ለአገራችን ሉዓላዊነትና የዜግነት ክብራችንን ለማስመለስ በህገ መንግስታዊ መብታችን ተጠቅመን ትግላችንን እስከማይቀረው ለውጥ ድል ደጃፍ ድረስ በቆራጥነት መቀጠል ናቸው ብሏል፡፡
በዚህም ትብብሩ ህገ-መንግስታዊ መብትን በመጠቀም በህግና በሥርዓት ትግሉን ለመምራት መዘጋጀቱን በመግለጽ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የትግል ጥሪውን እንዲቀላቀሉት አሳስቧል፡፡ ስለሆነም ትብብሩ ‹‹ኢህአዴግነት ከዜግነት በላይ›› ለሆነባቸው የሥራ ዋስትናቸው፣ ዕድገትም ሆነ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች በሙያቸው፣ በልምዳቸው፣ ክህሎታቸው፣ በመሳሰሉት ባልተመሰረተ መልኩ በደል እየደረሰባቸው ላሉ ሁሉ የትግል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
‹‹የህወኃት/ኢህአዴግ ተራ አባላትና ካድሬዎች፤ የፖለቲካ ልዩነት የተለያየ አመለካከትና ሀሳብ ማራመድ ጤናማ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ መገለጫ እንጂ እንደሚነገራችሁ ‹‹ጠላትነት›› ባለመሆኑ፣ ትግላችንም ለሠላማዊና ህጋዊ የሥልጣን ሽግግር እንጂ በናንተ ‹‹መቃብር›› ላይ አዲሱን ሥርዓት የማቆም፣ የነበረውን አጥፍቶ ከዜሮ የመጀመርና እናንተን የማጥፋት ዓላማ እንደሌለው ተረድታችሁ፣ ተቃዋሚዎች እንደናንተው ኢትዮጵያዊያንና ለኢትዮጵያና ህዝቧ የሚጨነቁ መሆናቸውን በመረዳት ተቃዋሚዎችን እንደ‹‹ ጠላት›› ከመመልከት አስተሳሰብ ራሳችሁን ነጻ እንድታወጡ›› ሲልም ትብብሩ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ወጣቶችና ሴቶች በተለይም የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች፣ መምህራንና ተማሪዎች በተለይም የዩኒቨርስቲና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ የእምነት ነጻነት መብት ጠያቂ የማኅበረሰብ አባላት፣ የመገናኛ ብዙሃን አባላት፣ የፍትህ አካላት፣ የዴሞክራቲክ ፓርቲዎች አባላት፣ የነጻነትና የዴሞክራሲ ሰላማዊ ታጋዮች፣ በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵዊያን/ዲያስፖራዎች እና ሌሎችም ጥሪው የተላለፈላቸው አካላት መሆናቸውን መግለጫው አትቷል፡፡
በመሆኑም፣ ‹‹በምናርገው አገራዊ፣ ሰላማዊና ሕዝባዊ ትግል በማይቀረው የሥርዓት ለውጥ ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በአንድነትና በቆራጥነት እንድትሰለፉ፤ የካቲት 22/07 በየከተሞቹ በቦታውና በሰዓቱ እንድትገኙ ጥሪያችንን አበክረን እናቀርባለን›› ብሏል የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር፡፡

Sunday, February 15, 2015

የ2007ቱን ሀገራዊ ምርጫ ሂደት እና ከምርጫዉ ዉጭ ያሉ አዋጭ አማራጮችን በተመለከተ የአርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የአቋም መግለጫ

አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላማዊ፣ ተዓማኒና ፍትሀዊ በሆነ ምርጫ የማይፈልጋቸውን መሪዎች መሻር፤ የሚፈልጋቸውን ደግሞ መሾም የሚያስችሉትን መሠረቶች ለመጣል የሚታገል ንቅናቄ ነው። እንደሚታወቀው የሕዝብ እውነተኛ ፍላጎት የሚገለጽበት እውነተኛ ምርጫ እንዲኖር ገለልተኛና ቀልጣፋ የፍትህ ሥርዓት፣ የጦርና የፓሊስ ሠራዊት ሊኖሩ ይገባል። ነፃ የሚዲያ ተቋማትና በነፃነት የሚንቀሳቀሱ የሲቪክ ማኅበራት መኖርም መታለፍ የሌለባቸው አቢይ ጉዳዮች ናቸው። አማራጭ ፓሊሲዎችን ማቅረብ የሚችሉ በነፃነት የሚንቀሳቀሱ የፓለቲካ ፓርቲዎች ከሌሉም አማራጮች የሉምና ምርጫ ትርጉም የለውም። ይህ ሁሉ ቢሟላ እንኳን ምርጫውን የሚያስፈጽመው አካል ገለልተኛ፣ ሀቀኛና ተዓማኒ ካልሆነ የሚደረገው ምርጫ የመራጩን ሕዝብ ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ሊሆን አይችልም።

ከላይ የተዘረዘሩትን የምርጫ እሴቶች ሙሉ በሙሉ ባይሆንም እንኳን የተወሰኑትን በመጠኑም ቢሆን ያካተተ ምርጫ እንዲኖር መጣርና በሂደት የምርጫውን አፈፃፀም ማሻሻል ይቻል ይሆናል በሚል እምነት የዲሞክራሲ ኃይሎች በህወሓት የሴራ ምርጫዎች ሲሳተፉ ቆይተዋል። ሆኖም በህወሓትና በእውነተኛ ምርጫ መካከል ያለው ተቃርኖ እያደር እየሰፋ ሲሄድ እንጂ ሲጠብ አልታየም። በህወሓት ሙሉ ቁጥጥር ስር በሚካሄድ ምርጫ ኢትዮጵያን የሚጠቅም ለውጥ ሊመጣ ይችላል የሚለው እምነት ለአርበኞች ግንቦት 7 ፈጽሞ የተሟጠጠው ከምርጫ 97 ማግስት ጀምሮ ነው። በግንቦት 7 ቀን 1997 ዓም የኢትዮጵያ ሕዝብ በታላቅ የለውጥ ተስፋ የሰጠው ድምጽ በህወሓት የተዘረፈው ከላይ የተዘረዘሩት ተቋማት ያልነበሩ በመሆናቸው፤ ስለዚህም ከምርጫ በፊት ተቋማቱን መገንባት፤ ተቋማቱን ለመገንባት ደግሞ ህወሓትን ከስልጣን ማስወገድ ይገባል ብሎ በማመኑ ነው አርበኞች ግንቦት 7 በሁለገብ የትግል ስልት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው።

Wednesday, February 11, 2015

ለወያኔ ዉንብድና መልሱ ህዝባዊ እምቢተኝነትና ህዝባዊ አመጽ ነዉ!

ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎ የኢትዮጵያን በትረ ስልጣን ጨብጠዉ በኖሩባቸዉ ባለፉት ሃያ አራት አመታት የአገራችን የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እጅግ በጣም ከዘቀጠና ከረከሰ የወያኔ ድራማ ዉጭ ሌላ ምንም ነገር የማይታይበት አለባሌ መድረክ አድረገዉት ቆይተዋል አሁንም እያደረጉት ነዉ። አንድ ቋንቋ የሚናገሩትና ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸዉ የወያኔ መሪዎች ኢህአዴግ የሚባል አጋሰስ የሽፋን ድርጅት ፈጥረዉ በኢትዮጵያ ህዝብ ሰብዓዊ መብትና ነጻነትና ላይ ተነግሮም ተጽፎም የማያልቅ ግዙፍ ግፍና በደል ፈጽመዋል። ህጻን፤አዛዉንት፤ ወንድና ሴት ሳይለዩ መብቴን አትንኩ ያለቸዉን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያለምንም ርህራሄ በጥይት ጨፍጭፈዋል። ሴቶች እሀቶቻችንን እጅና እግራቸዉን አስረዉ ጡታቸዉን በመቆንጠጫ እየቆነጠጡ በሴትነታቸዉ ላይ የዉርደት ተግባር ፈጽመዋል። ወንዶች ወንድሞቻችንን ደግሞ ዉስጥ እግራቸዉን ገልብጠዉ እየገረፉ ጥፍራቸዉን አይናቸዉ እያየ በጉጠት እየሳቡ ነቅለዋል። ባጠቃላይ የወያኔ ዘረኞች በዛሬዉ ዘመን አንኳን ወገን በወገኑ ላይ የዉጭ ጠላትም በህዝብ ላይ የማይፈጽመዉ በደል በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ፍጽመዋል።

ወያኔ ስልጣን እንደያዘ “አባይ ትግራይ” ወይም “ታላቋ ትግራይ” የሚለዉን ህልሙን ለማሳካት ወልቃይት ጠገዴን ከጎንደር ቆርሶ ከትግራይ ጋር ቀላቅሏል። ስልጣን ይዞ ከተደላደለ ከአመታት በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያን ገበሬ ከመሬቱ አፈናቅሎ ለምለም መሬቱን በርካሽ ዋጋ ለባዕዳን ሽጧል፤ ከዚህ አልፎ ተርፎም የአባቶቻችን አጽም ያረፈበትን የአገራችን ዳር ድንበር ቆርሶ ለጎረቤት አገር ገጸ በረከት አቅርቧል። ይህ አገራቸዉንና የሚመሩትን ህዝብ በሚጠሉ ጠባቦች የተሞላ ድርጀት ባለፈዉ ሳምንት የኢትዮጵያን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ደጋፊዎቹንና በአንቀልባ ታዝለዉ አስከዛሬ ያቆዩትን ምዕራባዉያን ጭምር ግራ ያጋባ ፀረ አገርና ፀረ ህዝብ እርምጃ ወስዷል። ድርጅት እያፈረሰና በፓርቲ ላይ የራሱን ተለጣፊ ፓርቲ እያቋቋመ ዛሬ ላይ የደረሰዉ ወያኔ ምርጫ የሚባል ድራማ በደረሰ ቁጥር የሚይዘዉ በሽታ ዘንድሮም ይዞት አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲንና መላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትን አፍርሶ በምትካቸዉ የራሱን መኢአድና የራሱን አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ፈጥሯል። ይህ ወያኔ ከሰሞኑ የወሰደዉ የፖለቲካ እርምጃ በየትኛዉም አለም በተለይ የመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዐትን እንከተላለን በሚሉ አገሮች ዉስጥ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ እጅግ በጣም ትልቅ የፖለቲካ ሸፍጥ ነዉ።

የወያኔን ታሪክ ተወልዶ ካደገበት ከደደቢት በረሃ እስከ ሚኒልክ ቤ/መንግስት ድረስ ያደረገዉን ጉዞ ስንመለከት ወለል ብሎ የሚታየን አንድ ሐቅ አለ፤ እሱም ወያኔ ሁሉንም ነገር በዘር መነጽር ብቻ የሚመለከትና ህዝብን በወዳጅና በጠላት ጎራ ለይቶ ወዳጅ አይደለም ያለዉን ሁሉ እንደ ሩሲያዊዉ ዮሴፍ ስታሊን እየገደለ የመጣ ድርጅት ነዉ። በእርግጥም ወያኔ ጫካ ዉስጥ እያለም ሆነ ዛሬ ከተማ ገብቶ የሚቃወመዉንና በሀሳብ የማይግባባዉን ድርጅትም ሆነ ግለሰብ እያፈረሰና እገደለ ባፈረሳቸዉ ድርጅቶች ምትክ ደግሞ የራሱን ተለጣፊ ድርጅት እየፈጠረ የመጣና ከዲሞክራሲያዊ አሠራርና ከስልጣኔ ጋር የማይተዋቅ ድርጅት ነዉ።

በመርፌ የተጠቃቀመ ቁምጣና ጥብቆ ለብሶ አስራ ሰባት አመት ጫካ ለጫካ የተጓዘዉ ወያኔ ጎንደር፤ ጎጃምና አምቦ እያለ ወደ አዲስ አበባ ሲጠጋ ከተገነዘባቸዉ ነገሮች አንዱ የለበሰዉ የተጠቃቀመ ቁምጣ የትም እንደማያደርሰዉና ለከተማ ኑሮ የሚስማማ አዲስ ልብስ እንደሚያሰፈልገዉ ማዉቁ ነዉ። በጥላቻ ተረግዞ በክፋት ላደገዉ ወያኔ ቢበቃዉም ባይበቃዉም ወይም ቢያምርበትም ባያምርበትም ይህንን ለከተማ ዉስጥ ኑሮ የሚያስፈልገዉን አዲስ ልብስ ለማዘጋጀት ብዙ ግዜ እልወሰደበትም። የሚሰርቅና የሚስቅ ምን ግዜም ተባባሪ አያጣም እንዲሉ ወያኔ የአዲስ አበባን መሬት የረገጠዉ ጦር ሜዳ ላይ የማረካቸዉን ወታደሮችና አገር ዉስጥ ያገኛቸዉን ደካማ ሰዎች ሰብስቦ በፈጠረዉ ኢህአዴግ በሚባል ፈረስ ጀርባ ላይ ተፈናጥጦ ነበር። ትግራይን ነጻ አወጣለሁ ብሎ ትግል የጀመረዉ ወያኔ ኢህአዴግን የፈጠረዉ ወያኔነቱን ለመተዉ ሳይሆን እራሱን በዚህ በኢትዮጵያ ስም በፈጠረዉ ድርጅት ዉስጥ ሸሽጎ እዉነተኛ ባህሪዩን ለመደበቅ ነበር።

Sunday, February 1, 2015

የሰላም በሮች ሲዘጉ የሁለገብ ትግል ስልት በሮች ይከፈታሉ!!!

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በምርጫ ቦርድ አማካይነት እየደረሰበት ያለውን በደል ለሕዝብ ለማሰማት ጥር 17 ቀን 2007 ዓም በአዲስ አበባ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጂንካና ሸዋ ሮቢት የተቃውሞ ሰልፎችን ጠርቶ ነበር። በተለይ በአዲስ አበባው ሰልፍ ላይ የተገኙ ወገኖቻችን ለህወሓት ፍጹም ታማኝ በሆነው የፓሊስ ክፍል ያለርህራሄ መደብደባቸው እና የተቃውሞ ሰልፉም በጉልበት መበተኑ ነፃነትና ፍትህ ናፋቂውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳዘነ ብቻ ሳይሆነ ያስቆጨ ጉዳይ ነው። በመላው ዓለም በሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የተለመደውን ድንጋይ ውርወራ እንኳን ሳይከጅሉ፤ የፓሊሶችን ሰብዓዊ ርህራሄ ለማግኘት “ፓሊስ የኛ ነው” እያሉ እየዘመሩ በፓሊስ ተደበደቡ። ሴቶችና አዛውንት ብቻ ሳይሆን ተላላፊ መንገደኞች እንኳን ከፓሊስ ዱላ አላመለጡም። ከሁሉም በላይ የሚዘገንነው ደግሞ የ 7 ወራት ነብሰ ጡር ሴትም በፓሊስ መመታትዋና ሆዷ መረገጡ ነው። ይህ እኩይ ተግባር የሚፈጥረው ቁጭት በህወሓት ላይ ብቻ አያበቃም። ትዝብቱ ለፓሊስም ተርፏል። ይህ የጭካኔ ተግባር ለፍትህና ለነፃነት በሚደረገው ትግል የሕዝብ አጋር ይሆናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የፓሊስ ሠራዊትን የሚያዋርድ ነው። ደካማ እናቶችን፣ አረጋዊያንን፣ ባዶ እጃቸውን ተቃውሞ እያሰሙ ያሉትን ወጣቶችንና ነፍሰጡሮችን በጭካኔ መደብደብ ለራሱና ለሥራው ክብር ለሚሰማው ፓሊስ ውርደት ነው፤ የሞት ሞት ነው። የኢትዮጵያ የፓሊስ ሠራዊት አባላት ተግባራቸው ያሳፍራቸዋል፣ ይቆጫቸዋል፤ ቁጭታቸውንም ይህን ትዕዛዝ በሰጡ አለቆቻቸው ላይ በግልም ሆነ በተደራጀ መንገድ በሚወስዱት እርምጃ እናያለን ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ ያደርጋል።

የጥር 17 ቀን 2007ቱ ሽብር በአንድ ወቅት የተፈጠረ፤ በአንድነት ፓርቲ ላይ ብቻ ያነጣጠረ፣ የተናጠል ክስተት ሳይሆን ህወሓት ደግሞ ደጋግሞ ሲፈጽመው የነበረ ነው። ከዚህ በፊት በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ ፈጽሞታል። የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላንን በተቃወሙ የተለያዩ ዩንቨርስቲዎች ተማሪዎች በተለይም በአምቦ ላይ የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሽብር ነዝቷል። በቅርቡ ደግሞ በሰማያዊ ፓርቲ አባላት ላይ ተመሳሳይ አረመናዊ ድርጊት ፈጽሟል።

አርበኞች ግንቦት 7: ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የህወሓት ታጣቂዎች በወገኖቻችን ላይ ያደረሱትን ድብደባ፣ ህገወጥ እስር፣ እና የተቃውሞ ሰልፍ ክልከላን አጥብቆ ይቃወማል። አርበኞች ግንቦት 7፣ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው ህመም ህመሙ፣ ቁስላቸው ቁስሉ ነው።

ባለፉት ሃያ ሶስት ተከታታይ ዓመታት፣ በአምቦ፣ በጅማና በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞችና ገጠሮች፣ በባህዳር፣በጎንደርና በበርካታ የአማራ ከተሞችና ገጠሮች፣ በጋምቤላ፣ በሶማሊ፣ በአፋር፤ በአጠቃላይ በመላው ኢትዮጵያ በየአስፋልቱ፣ በየሜዳውና በየጥሻው በህወሓትና ተላላኪዎቻቸው የፈሰሰው የኢትዮጵያውያን ደም በከንቱ ፈሶ መቅረት የለበትም ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 በጽኑ ያምናል። አርበኞች ግንቦት 7 ከሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር በመተባበር የህወሓትን እድሜ በማሳጠር የእናቶቻችን እምባ ሊያብስ ዝግጁ ነው። አርበኞች ግንቦት 7 ኢትዮጵዊያን እንደከብት እየተደበደቡ ወደ ማጎሪያ የሚያጋዙበት እና በጠገቡ ሰላዮችና ፓሊሶች እየታነቁ የሚታረዱበት ጊዜ ማብቃት አለበት ይላል።

የቱን ያህል ቢለመንም ሆነ ቢወገዝ ህወሓት ለነፃ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒን ምርጫ ዝግጁ ሊሆን ቀርቶ በምርጫ የሚወዳደሩት ፓርቲዎች እነማን እንደሆኑና እነማን በእጩ ተወዳደሪነት መቅረብ እንዳለባቸው ሳይቀር የሚወስን ዓይን አውጣ አጭበርባሪ ድርጅት ነው። ይህንን ከዚህ በፊት አይተነዋል፤ አሁንም በአንድነትና በመኢአድ ላይ እየተደገመ ነው። ህወሓት፣ በየአምስቱ ዓመታቱ በሚያደርጋቸው የሴራ ምርጫዎች በሚቀጥሉት አርባና ከዚያም በላይ ለሆኑ ዓመታት በሥልጣን ላይ የሚቆይበትን ስልት ቀይሶ የሚንቀሳቀስ፤ ኢትዮጵያን ለብዙ ዓመታት ለመግዛት ማድረግ የሚችለውን ክፋት ሁሉ ከማድረግ የማይመለስ አገር በቀል ቅኝ ገዥ ነው። ህወሓት የዘረጋው ሥርዓት ህገ-አልባነት፣ ፀረ-ሕዝብነት እና አምባገንነት ለማጋለጥ በሚል ርህራሄን በማያውቁ የሥርዓቱ አገልጋዮች ፊት ባዶ እጅ መጋፈጥ የሚፈጥረው የሞራል የበላይነትና የመንፈስ ጀግንነት ባያጠራጥርም የሚያስከፍለው ዋጋ ከሚገኘው ውጤት ጋር ማመዛዘን ግን እጅግ ተገቢ የሆነ የማይታለፍ ሥራ ነው ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከህወሓት የሴራ ምርጫ ፋይዳ ያለው ውጤት ይገኛል ብሎ አይጠብቅም። ከምርጫው የሚፈልገው ውጤት አንድ ነገር ብቻ ነው፤ እሱም የመንግሥት ለውጥ ነው። ምርጫው በምርጫነቱ ወደ መንግሥት ለውጥ አያደርስም፤ ወደ መንግሥት ለውጥ ወደሚያመራ ሕዝባዊ አብዮት ሊያሸጋግር ግን ይችላል። ይህም ቢሆን የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በተለይም የሠራዊቱን ዓይነትና አደራጀጀት እግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ መታቀድ ይኖርበታል።

አርበኞች ግንቦት 7 የራሱን ጥናት አድርጎ ለኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ እና ህወሓትን ለመሰለ ጠላት የሚመጥን የትግል ስልት ሁሉንም የትግል ስልቶች እንደሁኔታው ያዳቀለ – ሁለገብ – መሆን ይኖርበታል ብሎ ወስኖ ለተግባራዊነቱ እየተንቀሳቀሰ ነው። ሁለገብ የትግል ስልት ሕዝባዊ ተቃውሞን፣ ሕዝባዊ እምቢተኝነትንና ሕዝባዊ አመጽን እንደወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ ማፈራረቅና ማደባለቅን ይፈልጋል። ሰላማዊ ትግል በተለይም ሕዝባዊ እምቢተኝነት ሲባል ደግሞ ህወሓት ያወጣቸው አፋኝ ህጎች እያከበሩ የሚደረግ አለመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ይረዳል። ሁለገብ ትግል በተቻለ መጠን የወገን ኃይል ራሱን ፈጽሞ መከላከል በማይችልበት ሁኔታ እንዳይገኝ ለማድረግ ይጥራል። በአርበኞች ግንቦት 7 እምነት ሁለገብ የትግል ስልት ሰፊ ተቀባይነት የሚያገኝበት ወቅት ደርሷል። ከዚህ በፊት “የሰላም በሮች ሲዘጉ የአመጽ በሮች ይከፈታሉ” ተብሎ በአንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ታጋይ የተነገረው “የሰላም በሮች ሲዘጉ የሁለገብ ትግል ስልት በሮች ይከፈታሉ” በሚል እንዲሻሻልና በዚህ ወለል ብሎ በተከፈተው በር ሁላችንም እንድንገባ አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል። በሁለገብ የትግል ስልት በሰላማዊ መንገድ የሚደረጉ የትግል ዓይነቶች አሉ፤ በሌላም መንገድ የሚደረጉ አሉ። ስለሆነም በሁለገብ ትግል እያንዳንዳችን እንደየዝንባሌዓችንና እንደየችሎታዎቻችን አስተዋጽኦ ልናበረክት የምንችልበት ሰፊ እድል ይከፍትልናል።

ስለሆነም፣ በዚህ አጋጣሚ አርበኞች ግንቦት 7፣ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለጦር ሠራዊትና ፓሊስ አባላት ወገናዊ ጥሪ ያደርጋል።

በህወሓት ዘረኛ አገዛዝ በሚደርስብን ውርደት፣ እንግልት፣ ስደት፣ ሥራ አጥነትና ድህነት የተማረራችሁ እና እኩልነቷ የተረጋገጠ፣ የበለፀገች ኢትዮጵያን ማየት የምትመኙ ሁሉ የሁለገብ የትግል ስልትን አዋጪነት እንድታጤኑ የዚሁ ስልት አካል ሆናችሁ እንድትታገሉ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።

የኢትዮጵያ የጦርና የፓሊስ ሠራዊት አባላት በግል ከሚደርስባችሁ ግፍ በተጨማሪ የገዛ ራሳችሁን ወገኖች መግደላችሁ፣ ማቁሰላችሁ፣ ማድማታችሁና መደብደባችሁ የህሊና እረፍት ሊነሳችሁ ይገባል። ህሊናችሁ እረፍት የሚያገኘው የሥርዓቱ እድሜ ሲያጥር መሆኑን በመገንዘብ ለገዛ ራሳችሁ ክብር፣ ለወገናችሁና ለአገራችሁ ስትሉ ፋሽስቱን ወያኔ ከድታችሁ ከአርበኞች ግንቦት 7 ኃይል ጋር ተቀላቀሉ።

እነዚህን ጥሪዎች ተግባራዊ ካደረግን ወገኖቻችን መሠረታዊ መብቶቻቸውን በመጠየቃቸው በመወደስ ፋንታ በፓሊስ ዱላ ሲደበደቡ የማናይበት ዘመን ይመጣል። ይህ ካልሆነ ግን “ውሀና መብራት አጣን” ብሎ አቤቱታ ማሰማት እንኳን በጥይት የሚያስገድልበት ቀን ይመጣል። ያ ከመሆኑ በፊት እንወስን፤ ራሳችንና አገራችን ከህወሓት ዘረኛ አገዛዝ ነፃ እናውጣ።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!