ሚያዚያ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከኢህአዴግ የውስጥ ምንጮች ለኢሳት የተላከው የ2007 ዓም ምርጫ ማስፈጸሚያ እቅድ እንደሚያሳየው ለአርሶ አደሩ የማዳበሪያ እዳ እፎይታ በ2006/2007 የመኸር ምርት ዘመን የሚሰጥ ሲሆን፣ ለከተማ ነዋሪዎች ደግሞ በ20 ሺ ብር ቅድመ ክፍያ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውሉ ቦታዎችን ይሰጣል።
20 ሺ ብር የቅድመ ክፍያ ገንዘብ ለማቅረብ ለማይችሉት የከተማ ነዋሪዎች የምርጫ ቅስቀሳ በሚካሄድባቸው ወራት ከባንክ በብድር ገንዘቡን ለመልቀቅ እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጿል፡፡ የቦታ መስጠት ሂደቱን በመላ ሃገሪቱ ተግባራዊ ለማድረግ የቦታ መረጣ አዘጋጅቶ መጨረሱንም ገልጿል፡፡
ኢህአዴግ የማሸነፊያ ስትራቴጂዎች በሚል ርእስ ከዘረዘራቸው ተግባራት መካከል “ አርሶ አደሩንና አመራሩን የመዳበሪያ እዳ እፎይታ በ2006/2007 የመኽር ምርት ዘመን እንዳለ መንገር፤ ተቃዋሚችን ማንኳሰስ፣ በኢህአዴግ ላይ ሊነሱ የሚያስቡትን እስከ ማግለል እንዲደርስ ማሰረዳት፣ ምርጫውን በ1 ለ 5 እንዴት ድምፅ እንደሚሰጡ ማስረዳት /በሙከራ ማሳየት፣ ያለውን የፍትህ እና የልማት ችግር ወደ ፊት እንደሚፈታ በተስፋ መሙላት” የሚሉት ተጠቅሰዋል።
ኢህአዴግ ባዘጋጀው የስትራቴጂ ወረቀት ላይ ” የኢህአዴግ ትምህርት እና ስልጠና ከአመቱ መጀመሪያ ጀምሮ ህዝቡን ለመቀየር ቅርብ ናቸው ለተባሉ አርሶ አደሮች እና የቀበሌ አመራሮችን ‹‹ የኢህአዴግ ታሪክ››፤ የኢህአዴግ የልማት ስልቶች ፤ የብሄርተኝነት ግንባታ፤ የሃገራችን የምርጫ ተሞክሮ፤” በሚሉት ርእሰ ጉዳዮች ላይ የሰጠው ስልጠና መሳካቱን ይዳስሳል።
የአማራ እና የኦሮምያ ክልሎችን ማመን እንደማይቻል የሚገልጸው ሰነዱ፣ ”አመራሩ ኢህአዴግ ከወደቀ እስር ቤት እንደሚገባ ፤ የሚመጣው መንግስት አሁን በስልጣን ላይ ያሉትን የአመራር አካላት ቤተሰብም ጭምር ህይወት የሚያመሳቅል መሆኑን በማስረዳት፣’ ኢህአዴግ ወይም ሞት’ ብሎ በመነሳት ሊያሰፈፅም እንደሚገባው ያትታል።
የስራ መመሪያው ለከፍተኛ ጀማሪ አመራሮች በአስኳይ መውረዱን ለማወቅ ተችሎአል። የምርጫ ማስፈጸሚያ እቅድ ስልጠና የወረዳ እቅድ ከቀረበ በኋላ ተገምግሞ ሲያልቅ በዚህ መሰረት ቀበሌዎች ምርጫዎችን እንዴት ማሸነፍ እንደሚችሉ የቀበሌ እቅድ እንደሚያዘጋጁም ተገልጿል።
ለታችኛው አመራር ስልጠና የሚያገለግሉ መልእክቶች ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል ” ምርጫ 2007 የኢህአዴግ አሸናፊነት ይረጋገጣል ፣“ታላቁ መሪያችን ያስቀመጠልንን አደራ እናስቀጥላለን “፣ “በገጠር ቀበሌዎች የልማት ፣ የዴሞክሲና የመልካም አስተዳደር ግቦቻችን በዘላቂነት ለማሳካት እንረባረባለን ፣ ፈጣን ልማት መልካም አስተዳደርና የህዝብ ተጠቃሚነት ተልእኮን የተገነዘበ ንቁ የቀበሌ አመራር የመፍጠር ተልእኳችን ይሳካል ፣ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመራችን አስተማማኝ ደረጃ መድረስ ብቁ የቀበሌ አመራር የመፍጠር ትግላችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ፣ መጭው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ ነው“ የሚሉት ይገኙበታል።
ከኢህአዴግ የውስጥ ምንጮች ለመረዳት እንደተቻለው ደግሞ ኢህአዴግ የራሱን አባሎች በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ አስርጎ በማስገባት በተቃዋሚ ስም አሸንፈው እንዲወጡ ለማድረግ እየሰራ ነው።
No comments:
Post a Comment