Thursday, May 21, 2015

የሕወሓት አስተዳደር በጦር መኮንኖች ላይ ከግንቦት 7 ጋር ልባችሁ ኮብልሏል በሚል ክስ መሠረተ


Zehabesha News
ከግንቦት ሰባት ድርጅት ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል፤ አባላትን መልምለዋል፤ ለቡድኑ መረጃ አቀብለዋል፤ እንዲሁም ወደኤርትራ በመኮብለል የድርጅቱን ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስልጠና ለመውሰድ ተሰናድተው ሲንቀሳቀሱ ደርሼባቸዋለሁ በሚል የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተባቸው ሰባት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ትናንት ግንቦት 11 ቀን 2007 ዓ.ም በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀረቡ።
በአዲስ አበባ የሚታተመው ሰንደቅ ጋዜጣ እንደዘገበው “በዐቃቤ ሕግ ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች 1ኛ መቶ አለቃ ማስረሻ ስጤ፣ 2ኛ መቶ አለቃ ብሩክ አጥናዬ፣ 3ኛ መቶ አለቃ ዳንኤል ግርማ፣ 4ኛ መቶ አለቃ ገዛኸኝ ደረሰ፣ 5ኛ ተስፋዬ እሸቴ፣ 6ኛ ሰይፉ ግርማ እና 7ኛ የሻምበል አድማው አዳሙ ናቸው። እንደክስ ዝርዝሩ ከሆነ ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በቀጥታ እንዲሁም በመላ ሃሳባቸውና አድራጎታቸው በወንጀል ድርጊቱና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን ሕገ-መንግስቱን እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል የማፈራረስ ዓላማን ይዘው ለማስፈፀም እና በመንግስት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር፤ ህብረተሰቡን ለማስፈራራት፤ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተቋማት ለማናጋትና ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሰውና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ከተባለው የግንቦት ሰባት ድርጅት አባል በመሆንና በሽብር ድርጅት ለመሳተፍ ሲንቀሳቀሱ ደርሼባቸዋለሁ” ይላል።
የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ ትናንት በችሎት ለተገኙት ተጠርጣሪዎች ክሱ እንደደረሳቸው ተደርጎ በዝርዝር ሲነበብ፤ በተጠርጣሪዎቹ ላይ 10 ክሶች እንደቀረቡባቸው ለማወቅ ተችሏል። በተለይም ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተከሳሾች ላይ በቀረበው ክስ መሠረት ቀኑና ወሩ በትክክል ተለይቶ ባልታወቀበት በ2006 ዓ.ም ከሽብር ድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ከሆነው ሻለቃ አክሊሉ መዘነ አማካኝነት በህቡዕ ተመልምለው አባላትን እንዲመለምሉም ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ይንቀሳቀስ ነበር ሲል ያትታል። በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ እያንዳንዳቸው ከአፌዲሪ መከላከያ የአየር ኃይል ንብረት የሆኑ አንድ-አንድ ማካሮቭ ሽጉጥና 16 ጥይቶችን ይዘው በመውጣትና በመሸጥ፤ እያንዳንዱ አንዱን ማካሮቭ በ2ሺህ 500 ብር እንዲሁም እያንዳንዳቸው የያዙትን 16 ጥይቶች በ240 ብር ዋጋ በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው በማዋል በፈፀሙት ወታደራዊ ትጥቅና መሣሪያዎችን ያለአግባብ መገልገል ወንጀል ተከሰዋል ባይነው፤ዐቃቤ ሕግ።
በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ በአጠቃላይ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ አባል በመሆን፣ ተልዕኮ በመቀበል፣ አባላትን በመመልመል፣ ለሽብር ድርጅቱ መረጃ በማቀበል እንዲሁም የሽብር ድርጅቱን ለመቀላቀል ወደኤርትራ ለመሄድ ሲሉ የተያዙ በመሆናቸው በፈፀሙት በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በማናቸውም መልኩ መሳተፍ ወንጀል ተከሰዋል ሲል የክስ መዝገቡ ያትታል።
በዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር ውስጥ በብቸኝነት 10ኛው ክስ የተመሰረተበት ሻንበል አድማው አዳሙ ፈፅሞታል የተባው ወንጀል ከኢፌዲሪ አየር ኃይል ድሬዳዋ ቅርንጫፍ የሆነ አንድ ማካሮቭ ሽጉጥ ከ8 ጥይቶች ጋር በ33 ሺህ 700 ብር መግዛቱ እንደሆነ የጠቀሰው የዐቃቤ ሕግ ክስ፤ በዚህም በፈፀመው በከባድ ሁኔታ የመሸሸግ ወንጀል ተከሷል ይላል።
ተከሳሾቹ ትናንት (ማክሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2007 ዓ.ም) ችሎት በቀረቡበት ወቅት የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው የጠየቁ ሲሆን፤ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የጠቀስኳቸው የወንጀል አንቀፆች የዋስትና መብትን የሚያስከለክሉ ናቸው በሚል ለችሎቱ በማስረዳቱ ተቀባይነት አግኝቷል። በመሆኑም ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ታዟል። ነገር ግን በ7ኛ ተከሳሽ ጉዳይ ላይ ያለውን የዋስትና ጥያቄ መርምሮ ብይን ለመስጠትና ሁሉም ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ ያላቸውን ሀሳብ ለማዳመጥ ለግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል ሲል ሰንደቅ ጋዜጣ ዘግቧል::

No comments:

Post a Comment