ሁለት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ውስጥ ብቻ ከ150 በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በአማራ፣ በጋምቤላና በሶማሌ ቁጥራቸው የማይታወቅ በርካታ ወገኖቻችን ተገድለዋል፤ በሌሎችም ክልሎች ወገኖቻችን እየተገደሉ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተደብድበዋል፤ ታስረዋል። የህወሓት አገዛዝ ዜጎች መግደል፣ መደብደብና ማሰር መደበኛ ሥራው አድርጎታል።
በተለይ በኦሮሚያ ክልል እየቀጠለ ያለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት እና ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የሁላችንም ተሳትፎ የሚሻ ነው። ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ትናንሽ የገጠር ከተሞችን ሳይቀር ያዳረሰ መሆኑ የበርካታ ሕዝብ ስሜትንና ጥቅምን የሚነካ አጀንዳ በፍጥነት እንደሚሰራጭና ሕዝብን እንደሚያደራጅ አመላካች ነው። ከዚህ ሕዝባዊ ትግል በርካታ ድሎች የተገኙ ቢሆኑም ሁለቱ መሠረታዊ በመሆናቸው አጽንዖት ሊሰጣቸው ይገባል።
አንደኛ
በአለፉት ሁለት ወራት በኦሮሚያ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት የኢትዮጵያን ማኅበረሰብ አቀራርቧል። ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ሕዝብ ያልመከረበት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መቃወም ፍትሃዊ መሆኑ በሰላማዊም ሆነ በአመፅ መንገድ የህወሓትን አገዛዝ መታገል የመረጡ የዲሞክራሲ ኃይሎችን በሙሉ ያስማማ፤ በኦሮሞና በአማራ ማኅበረሰብ መካከል መልካም የሆነ መግባባትን የፈጠረ መሆኑ ትልቅ ድል ነው። ይህ ማለት ግን አፍራሽ ጽንፈኛ አስተያየቶች ከወዲህም ከወዲያም መወርወራቸው ቀረ ማለት አይደለም፤ ያም ሆኖ ግን በሕዝቡና በፓለቲካ ልሂቃኑ መካከል ያለው መናበብ ከቀድሞው በጣም በተሻለ ሁኔታ መገኘቱ ተስፋ ሰጪ ነው። ይህንን ድል ማስከንና አድማሱን ማስፋት ያስፈልጋል። በተለይም የነፃነት ትግሉ አካል የሆኑትን የትግራይ ወገኖቻችንን ማቀፍ እና ህወሓትን ከትግራይ ሕዝብ መነጠል ያስፈልጋል። ወደ ህወሓት የሚወረወሩ ፍላፃዎች ወደ ትግራይ ሕዝብ የተወረወሩ መስለው እንዳይታዩ በንግግሮቻችንና ጽሁፎቻችን ሁሉ ግልጽ ማድረግ ይኖርብናል። ሶማሌን፣ አፋርን፣ ሲዳማን እና ሌሎችን ማኅበረሰቦችን በተመለከተ ተመሳሳይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ወሳኝ ወቅት በማኅበረሰቦች መካከል እየተፈጠረ ያለው መግባባትን የሚቀለብስ ወይም ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገባ አንዳችም ተግባር እንዳይፈፀም ነቅቶ መጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት ነው። ይህ ትግል፣ እስካዛሬ አጥተነው የነበረው የኢትዮጵያውያንን ማኅበረሰብ መቀራረብን አምጥቶልናል፤ በሚገባ ከተጠቀምንበት ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን የመገንባት አቅማችንን በከፍተኛ ሁኔታ ያጠነክርልናል። ስለሆነም፣ ከግራ እና ቀኝ በሚወረወሩ ዘረኛ አስተያየቶች እና ተግባራት ይህንን ስሜት ለማደፍረስ የሚጥሩትን በጋራ ልንታገላቸው ይገባል።
ሁለተኛ
ከእንግዲህ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተፈፃሚ ማድረግ አይቻልም፤ አስፈፃሚም የለውም። ይህ አንድ ትልቅ ድል ነው፤ ሆኖም ህወሓት የአገዛዙ ወንበር ላይ እስካለ ድረስ ይህ ድል መሠረታዊ የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ አያመጣም። እስከ አሁን ከአንድ መቶ አምሳ በላይ ዜጎች ተገለውብናል፤ የሟቾች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረም ነው። ገዳዮች በመግደላቸው ሲሸለሙ እንጂ ሲጠየቁ አላየንም። በግልባጩ የሟች ቤተሰቦች የጥይት ወጪ ካልከፈላችሁ አስከሬን አንሰጥም እየተባሉ ነው።
ገዳይን እየሸለመ፤ ሟችን የሚቀጣ ኋላ-ቀር ፍርደ-ገምድል ሥርዓት ማብቃት ይኖርበታል። ስለሆነም የወቅቱ ጥያቄ መላዋን ኢትዮጵያ ከህወሓት አገዛዝ ነፃ ማውጣትን ዓላማው ያደረገ መሆን ይኖርበታል። “ኦሮሚያ አምባገነንነትን እንቢኝ ብላለች!” ከሚለው መሪ መፈክር “ኢትዮጵያ አምባገነንነትን እንቢኝ ብላለች!” ወደሚለው መሪ መፈክር መሸጋገር ድላችንን ያቀርባል።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የወገኖቻችን ደም በከንቱ ፈሶ መቅረት የለበትም፤ ገዳዮች በህግ ሊጠየቁና ሊቀጡ፣ ተበዳዮች ደግሞ ሊካሱ ይገባል ብሎ ያምናል። ሆኖም ህወሓት ስልጣን ላይ ሆኖ እያለ እነዚህ ነገሮች ሊፈፀሙ ይችላሉ ብሎ አያምንም። በአርበኞች ግንቦት 7 እምነት ኢትዮጵያ አምባገነንነትን አሻፈረኝ ብላለች፤ ይህም በሕዝባዊ እምቢተኝነት እና በሕዝባዊ አመፅ እየታየ ነው። ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ሕዝባዊ አመፅ ሲደጋገፉ ባነሰ ኪሳራ አምባገነኑን አገዛዝ ከጫንቃችን ለማውረድ ያስችለናል ብሎ ያምናል። ስለሆነም ኢትዮጵያ አምባገነንነትን እምቢ ትበል!
አንድነት ኃይል ነው!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
No comments:
Post a Comment