Thursday, January 18, 2018

ለዲሞክራሲ የሚናካሂደው ትግል በምንም አይነት ጥገናዊ ለውጥ አይደናቀፍም!

የአርበኞች ግንቦት 7 ርዕስ አንቀጽ

የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ከታህሳስ 3 ቀን 2010 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 21 ቀን ሲያካሂድ በሰነበተው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ በራሱ በድርጅቱ ውስጥ ተፈጥሮአል ባላቸው ችግሮች እና የአገራችንን ግዜያዊ ሁኔታና የወደፊት አቅጣጫ አስመልክቶ ግምገማ በማድረግ ባለ 8 ነጥብ ውሳኔዎችን አሳልፎ እንደተጠናቀቀ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል ።

ኢህአዴግ አወጣሁ ያለው ይህ መግለጫ በአጭሩ ሲዳሰስ በቅርጹም ሆነ በይዘቱ ብዙ ችግሮች የሚታዩበት ፤ አደናጋሪና ወጥነት የሌለዉ፥ እርስ በርሱ በሚጣረስ ሀሳቦች የታጨቀ ከመሆኑም በላይ አገራችን የገባችበትን መሰረታዊ ችግሮች ያላገናዘበ እና ህዝባችን በተለይ ላለፉት ሶስት አመታት እያነሳቸው ያሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች ከግምት ዉስጥ ያላስገባ ወይም እውቅና ያልሰጠ ፤ የህወሃት የበላይነት የነገሠበትን ሥርዓት ዕድሜ ለማስቀጠል ሲባል ገዢዉ ፓርቲ እስካሁን አከናወንኩ ያላቸውን በጎ እርምጃዎች በመዘርዘር “በአመራሮቹ ድክመት ካልሆነ በቀር ምንም አይነት የፖሊሲም ሆነ የፖለቲካ እምነት ችግር የለብኝም እና ተረጋጉ” የሚል መልዕክት ያስተላለፈበት ሆኖ ተገኝቶአል። እንዲህ አይነት መግለጫ ለማውጣት የህወሃትን የበላይነት ከውስጥ ሆነው አጥብቀው በመታገል ላይ ያሉ የሌሎች አባል ድርጅቶች አመራሮችስ እንዴት ብለው ተስማሙበት የሚል ጥያቄም በማስነሳቱ ምናልባትም ስብሰባው ከተበተነ ቦኋላ እራሱ ህወሃት “አለሁ” ለማለት በግሉ ጽፎና አጽድቆ ያሰራጨው ሊሆን ይችላል የሚልም ግምት አሳድሮአል። የግምቱን ምክንያታዊነት ደግሞ የሚያረጋግጠው መግለጫው ይፋ የሆነው ስብሰባው ተጠናቀቀ ከተባለበት ዓርብ ታህሳስ 21 ቀን ቦኋላ ለ36 ሰዓታት ዘግይቶ መሆኑ ነው። መግለጫው ላይ እንዲህ አይነት ጥርጣሬ በመፈጠሩ የተነሳ በኢህአዴግ 27 አመት የሥልጣን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የ4ቱም ድርጅቶች ሊቃነመናብርት በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ተገደዋል። በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅትም ህብረተሰቡ ውስጥ ጥርጣሬ በፈጠሩት እና መነጋገሪያ በሆኑት ነጥቦች ላይ በሁለት ጎራ የተከፈለ አስተያያት ሲሰጥ ተስተውሎአል።

ሁላችንም እንደምናውቀው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የሆኑት 3ቱም ድርጅቶች ህወሃት የራሱን የፖለቲካ አጀንዳ ለማሳካትና ጥቅሙን ለማስጠበቅ በህወሃት የተፈጠሩ ናቸው። በዚህም የተነሳ ድርጅቶቹ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ከአገርና ከወገን ጥቅም በላይ በአካል ለፈጠራቸው ህወሃት ታማኝ ሆነው ሲያገለግሉ ኖረዋል። ይህ ሃቅ መሆኑ እየታወቀ አንዳንዶች ከዚህ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ በጎ ውጤት በመጠበቅ አገዛዙ እስካሁን በተከተላቸው የተሳሳቱ ፖሊሲዎች እና በፈጸማቸው ህገወጥ ተግባሮች ምክንያት አገራችን ከገባችበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች የምትወጣበትንና ከተጋረጠባት የህልውና አደጋ የምትታደግበትን ሥርነቀል እርምጃዎች ለመውሰድ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ብለው ጓጉተው ነበር። ህወሃት/ ኢህአዴግ በእስከዛሬ ተሞክሮው ምንም አይነት ለአገርና ለወገን የሚጠቅም እርምጃዎችን ከራሱ ጠባብ አላማ አስበልጦ እንደማያውቅ እየታወቀ እንዲህ አይነት ጉጉት ያደረባቸው ወገኖች ተስፋ ያደረጉት እንዲያው በድፍኑ አልነበረም። ምክንያቱም መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት ከተለየ ወዲህ ህወሃት ውስጥ የተፈጠረው የሥልጣን ክፍፍል የህወሃትን የበላይነት ተቀብለው በኖሩ አባል ድርጅቶች በተለይም በኦህዴድና በብአዴን ዘንድ“እንደከዚህ በፊቱ ታዛዥ ሆነን አንኖርም” የሚል አመጽ እና የእኩልነት ጥያቄ ቀስቅሶአል። በሌላ በኩል ደግሞ በአብዛኛው የአገራችን ክፍል የሚኖረው ህዝባችን አገዛዙ አሠልጥኖ ካዘመተበት የአጋዚ ጦር ጋር እየተፋጠጠ ለመብቱና ለክብሩ በማካሄድ ላይ የሚገኘው ሁለገብ ትግል ከግዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረና አድማሱን እያሰፋ እንጂ ወደ ኋላ እየተመለሰ ስላልሆነ በራሱ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ በተለያየ የሥልጣን እርከኖች ላይ ባሉ አመራሮች ዘንድ ግንዛቤና ድጋፍ እያገኘ የመጣበት ሁኔታም አለ። ከዚህ በተጨማሪ ህወሃት በገጠመው ንቅዘትና በህዝብ ዘንድ ባጣው ተቀባይነት ምክንያት ከከፍተኛ አመራሩ ጋር ተሻርከው በሃብት ዘረፋ የተሰለፉ ነባር የኦህዴድና የብአዴን አመራሮችን በሙስናና በመልካም አስተዳደር ጉድለት ስም እያባረረ በወታደራዊና የስቪል ደህንነት ተቋሞቹ ውስጥ ተኮትኩተው ያደጉ ወጣት አመራሮችን ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ሁኔታዎችን አመቻችታል። በተለይም በኦህዴድ ውስጥ። እነዚህ አዳዲሶቹ አመራሮች ደግሞ እንደቀደሞዎቹ ነባር አመራሮች ህሊናቸውን ሽጠው ለሚከፈላቸው ደመወዝ የሚገዙ አልሆኑም። እንዲያውም እንወክለዋለን የሚሉት ማህበረሰብ የሚያሰማውን የዘመናት ብሶትና የመብት ጥያቄ ከመደገፍ አልፈው ወገናዊነታቸውን በተለያየ መንገድ መግለጽ ጀምረዋል። ከነዚህ ሁሉ ምክንያቶች በመነሳት ህወሃት እንደ እስከዛሬው የኦህዴድንና የብአዴንን ሙሉ ድጋፍና ትብብር ሳያገኝ ብቻውን እየገደለ፤ እያሰረ ፤ እየገረፈና እያፈናቀለ ለመዝለቅ እንደማይችል ሥለሚረዳ አጋጣሚውን በመጠቀም እራሱን ለህዝብ ጥያቄ ለማስገዛት ሥርነቀል ውሳኔ ለማስተላለፍ ይችል የሆናል የሚል ተስፋ ይዘው ነበር።

ብዙዎችን ተስፋ ያስቆረጠው ይህ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች አንዳንዶች ጠብቀውት እንደነበረው ሥርነቀል ለውጥ ለማምጣት አስተዋጽዖ የሚያደርግ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ከማናችንም በላይ ተጠቃሚው እራሱ ህወሃት ይሆን እንደነበር ግልጽ ነው። ምክንያቱም ላለፉት 27 አመታት ሥልጣንን ከለላ በማድረግ በአገር ሃብት ዘረፋ እጅግ የከበሩ፤ የሥልጣን ዕድሜያቸውን ለማራዘም በፈጸሙት አፈና በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በግፍ ያስጨፈጨፉ ፤ ያሠሩ ፤ ያስገረፉ ፤ ያፈናቀሉና ለስደት የዳረጉ እነርሱ ስለሆኑ አገራችን ውስጥ የሚደረገው ማንኛውም አይነት ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ይዞት የሚመጣው ብሄራዊ እርቅ በአብዛኛው ተጠቃሚ የሚያደርገው በወንጀል የተጨማለቀውን የህወሃት አመራርን ነበር። ዛሬ የአጋዚ ጦር የሚፈጽምበትን አፈናና ግድያ ተቋቁሞ ነጻነቱን ለማስመለስ በመፋለም ላይ ያለው ህዝባችን በምንም ተዓምር መብቱንና ክብሩን ሳያስመልስ ወደ ቤት እንደማይገባ ከምንግዜውም በላይ ግልጽ ሆኖአል። በህወሃት ገታራነትና ትዕቢት ህዝባችን ለዚህ ትግል የሚከፍለው መስዋዕትነት እየከበደና እየገዘፈ ከሄደ ለህወሃት የእስካሁኑ ወንጀሎች የሚኖረው የይቅርታ ልብ እየተመናመነና እየደነደነ በስተመጨረሻው የሚያስከፍለውም ዕዳ እየከፋ ይሄዳል። ይህ በሞራልም በህግም የተረጋገጠ ነው።

አርበኞች ግንቦት 7 አገራችን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ትግል የዲሞክራሲ ሥርዓት ለማምጣት የሚካሄድ የሞት ሽረት ትግል ስለሆነ ህወሃት በሚያስበው ማንኛውም አይነት የጥገና ለውጥ እንደማይሰናከል አጥብቆ ያምናል።በዚህም ምክንያት ህዝባችን የጀመረው ትግል ግቡን እንዲመታ ያለውን ሃይል በሙሉ አስተባብሮ እስከመጨረሻው በጽናት ይታገላል።

ህወሃት በድል አድራጊነትና በአይነኬነት እስከዛሬ የአገራችንን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ምህዳር በበላይነት ተቆጣጠሮ ለመዝለቅ የቻለው ህዝባችንን በቋንቋና በሃይማኖት የመከፋፈል ሴራው ስለተሳካለት ነበር። ያስኬት ዳግም ላያንሰራራ እየሞተ ነው። የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ “መርህ አልባ ግንኙነት “ በማለት የኮነነው የሁለቱ ትላልቅ ማህበረሰቦች ግንኙነት የህይወት እስትንፋስ ሆኖ ህወሃትን ላለፉት 26 አመታት ሥልጣን ላይ ያቆየውን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ አፈር ከድሜ አብልቶታል። ህወሃት ምን ያስከትል ይሆን ብሎ ሳያስብ “መርህ አልባ ግንኙነት” ብሎ የኮነነው የአማራና የኦሮሞ ህዝብ ግንኙነት የበለጠ የህዝብ ቁጣ ቀስቅሶበት ከተለመደው አሰራር ውጪ በቡድን ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሰጥ አስገድዶታል። “ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ” እንዲሉ መልዕክቱ ዒላማውን ከመታ ቦኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ አልተሰጠ ልዩነት የለውም።“እሳትና ጭድ የሆኑት ሁለቱ ማህበረሰቦች መቀራረብ የጀመሩት በኛ ሥራ አለመሥራት ነው” ተብለንስ የለ? በቃል አቀባዩ ጌታቸው ረዳ? ሌላው ማዘናጊያና ጊዜ መግዣ ደግሞ በስብሰባው ውሳኔ ላይ ያልተጻፈና ከጋዜጣዊ መግለጫው የሰማነው የፖለቲካ እስረኞች የመፈታት ዜና ነው።


አርበኞች ግንቦት 7 ኢህአዴግ የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለሁ ብሎ የሰጠው ዜናም ቢሆን እርስ በርሱ የተምታታና ተዓማኒነት የሌለው የተለመደ ቅጥፈት ነው ብሎ ያምናል። የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት ለዲሞክራሲ ለምናደርገው ትግል እንደ አንድ አስተዋጾ የሚቆጠር እንጂ ብቻውን የትግላችን ግብ አይደለም። ስለዚህ ህወሃት በማይተገብረው የተሥፋ ቃል ትግላችንን ለአፍታም ቢሆን ሊያቆመው እንደማይችል ሊያውቅ ይገባል።

የምናካሂደው ትግል ዓላማና ግብ ግልጽ ነው። አገራችን ውስጥ የህወሃት/ ኢህአዴግ አገዛዝ ሥርዓት የመጨረሻው አምባገነን እንዲሆንና ከአሁን ቦኋላ ህዝብ በራሱ ነጻ ፍላጎት ያስተዳድረኛል ብሎ ግልጽና ዲሞክራሲያዊ በሆነ የምርጫ ህግ የሚመሠረት የመንግሥት ሥርዓት ማስፈን ነው። ከውስብስብ ችግሮቻችን ለመላቀቅ መፍትሄው ይህ ብቻ እንደሆነ ህዝባችን ያምናል።

ህወሃት ጊዜ ለመግዛት የሚጫወተውን የሞኝ ፖለቲካ ቁማር አቁሞ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር የንቅናቄያችን ዋና ጸሃፊ የነበረውን አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ በእጁ የሚገኙትን ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ ይፍታ! ጸረ ሽብር አዋጁንና ሌሎች አፋኝ ህጎችን በሙሉ አሁኑኑ ይሰርዝ! የጸጥታ ተቋማትንና የአገር መከላኪያ ሠራዊትን ለጠባብ የድርጅት ፍላጎት ማራመጃነት መጠቀም ያቁም! የምርጫ ቦርድ ይፍረስ! መገናኛ ብዙሃን ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሆነው ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ የሚችሉ ተቋማት ይሁኑ! ሁሉንም ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችንና ባለድርሻ አካላትን ያቀፈ ብሄራዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል አገራዊ ውይይት በአስቸኳይ ይጠራ! እነዚህ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ አርበኞች ግንቦት 7 መላው ህዝባችን የጀመረውን ሁለገብ ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ በድጋሚ ያረጋግጣል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

No comments:

Post a Comment