ለለውጥ ያህል ከራሴ ችግር ብጀምር ምን አለበት? ግለሰብ ካልኖረ ማኅበረስብ አይኖርም፡፡ ደሞም የኔ ችግር የሁሉም ፣ የሁሉም ችግር የኔ መሆኑን የማያምን አንባቢ ቢኖር ችግር አለበት ማለት ነውና በጊዜ ራሱን ፈትሾ መድሓኒት ቢጤ ቢያፈላልግ ሳይሻለው አይቀርም፡፡
ትንሹዋ ወያኔ ጠምሳኛለች፡፡ እኔን ብቻም አይደለም የጠመሰችው፡፡ ብዙዎች ኢትዮጵያውያንንም እንጂ ነው፡፡ ከወያኔ ባልተናነሰ ሁኔታ ኑሯችንን እያቃወሰችው ትገኛለች – ትልቁ ወያኔ በደጅና በቤት ውስጥ እርሷ ደግሞ በቤት ውስጥ ብቻ በተናጠልና በቡድን እየተጋገዙ ወዲያ ወዲህ ውልፊት ልንል በማይቻለን ሁኔታ ወጥረውናል፡፡ ምን እንደምናደርግም ጨንቆናአለ፡፡ ይቺ የቤት ውስጥ ወያኔ ዐይጥ ናት፡፡
ዘመኑ ለይቶለት የዐይጦችና የወያኔዎች ሆኗል ወንድሞቼና እህቶቼ ማለትም ኢትዮጵያውያን፡፡ በኔ ቤት የተረፋት ነገር የለም፤ ለወትሮው ካልሲና ጨርቃ ጨርቅ እየለቃቀመች ነበር ወደጎሬዋ እምትወስድ፡፡ ዛሬ ግን ዘመን ተቀይሮ ባዶ ሞሰብ ሣይቀር መቆርጠም፣ አልሙኒየም የምጣድ አከንባሎ መጎርደም፣ ቁም ሣጥን መቀርጠፍ ይዛለች፤ ወያኔነት ከዚህ በላይ አለ? መጽሐፎችን አንብባ ላታነብ ነገር በጥርሶቿ መከታተፍ፣ ምግቦችን ከጉሮሮዋችን እየነጠቀች ማንከት፣ በሌሊትና አንዳንዴ ደግሞ በማንአለብኝነትና ወደር በሌለው ዕብሪት በቀንም ቤትን ተቆጣጥራ ሰላምን ማወክ የዘመናችን ትንሹዋ ወያኔ ገደቡን ያለፈ የድፍረት ተግባር ሊሆን በቅቷል – ወያኔን ተማምና መሆን አለበት መቼም፡፡ ድፍረቷ እኮ ድፍረት እንዳይመስላችሁ፡፡ ኧረረረረረ…. እንዳቃጠልሽኝ የሚያቃጥል ይዘዝብሽ፡፡ ብዙ ሰዎች በርሷ እንደተቸገሩና ዘመኑ ለርሷና ለወያኔ ዓይነቶቹ ምሥጥ መሠሪዎች የሰጠ መሆኑን ይህን ችግር የማወያያቸው ሰዎች ሁሉ ይነግሩኛል፡፡
ዛሬና አሁን በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ 6፡30 ገደማ ሲሆን ቀን የገዛሁትን እንትን በስምንት የጦር ግምባር አጥምጄ ወደብሶት አደባባይ መውጣቴ ነው – እንዳትሰማኝና እንዳታውቅብኝ ነው የገዛሁትን ነገር በእንትን የገለጸኩላችሁ ታዲያን – እንጂ “እዚያው በላች እዚያው ቀረች” የሚል አደገኛ መርዝ መግዛቴን ለመናገር አፍሬ እንዳይመስላችሁ፡፡ ለነገሩ ወያኔና ዐይጥ ከጠላታቸው የሚከላከሉበት ብዙ ተለዋዋጭ ዘዴ ስላላቸው በበሶ ዱዔት ያዘጋጀሁትን ግብዣ እንደሚቀበሉትና እንደማይቀበሉት አላውቅም – ውጤቱን ነገ አያለሁ፤ ዲዲቲና ወባ እንኳን ተለማምደው ጓደኛሞች መሆናቸውን ቀደም ሲል ሰምተን የለም? የሆነው ሆኖ ችግሩ ቀላል እንዳይመስላችሁ፤ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት የተለቀቁ ነው የሚመስሉት – እንደደፋርነታቸውና እንደሆዳምነታቸው፡፡ የሚምሩት ነገር እኮ የላቸውም፡፡ የሚሆንልኝ መስሎኝ “ዕቃ አትንኩብኝ፤ ቤቱ እንደሆነ ይበቃናል፡፡ ካለኝ አልፎ አልፎ ቀለብ እቆርጥላችኋለሁ – ከሌለኝ ግን ምን አደርጋለሁ? ብቻ አትተናኮሉኝ እንጂ እኔ መርዝ አላጠምድባችሁም፤ የዛሬን ኑሮ መቼም እናንተም ታውቁታላችሁ፡፡ ከመጠለቁ እግርን የሚፋጀው እሳተ መለኮቱ የቻይና ካልሲ እንኳን ባቅሙ ሠላሣና ዐርባ ብር በገባበት ወቅት እባካችሁን ተከባብረን እንኑር፡፡…” ብዬ ቃል ገብቼ በቤቴ ውስጥ የሚያደርሱትን ጉዳት ሰምቼ እንዳልሰማሁና ዐይቼም እንዳላየሁ ለብዙ ጊዜ ትቻቸው ነበር፡፡ እነሱ ግን የእንጀራ ሞሰብ አልጋችን ላይ አስቀምጠን ከባለቤቴ ጋር በየተራ እየጠበቅን እስክናድር ድረስ አሰቃዩን – የቤት ውስጥ ወያኔዎች! አሁን ባሰብኝና ቃሌን አፈረስኩ፡፡ እናም … የነሱስ አብነቱ ቀላል ነው፡፡ አለ እንጂ ወያኔ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረ! የወያኔስ ሰማያዊ መርዝ ካልተጨመረበት በምድራዊ መርዝ ብቻ አይጠራም፡፡ እናም ጎበዝ ግዴላችሁም ለላይኛውም በርትተን እንጩህ፡፡ የቃመ ብቻ ሣይሆን የጮኸም ተጠቀመ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡
ወያኔና ዐይጥ አንድ ናቸው፡፡ ይሉኝታ አያውቁ፤ ፍቅር አያውቁ፤ ሀፍረትና ኅሊና እሚባል የላቸው፤ የተረገሙ ፀረ-ሕዝቦች፡፡
የሰሞኑ የወያኔ ኢቲቪ ወሬ የአባይ የህዳሴ ግድብ ብቻ ሆኗል፡፡ ነገሩ “አንድ ያላት እንቅልፍ የላት” ዓይነት ነው፡፡ በሌሎች ሀገራት በየአሥር ኪሎ ሜትሩ የሚገኝ ግድብ ኢትዮጵያ ውስጥ ብርቅ ሆኖ ጆሯችን እስኪደነቁርና እጅ እጅ እስኪለን ድረስ አባይን እየተጋትን ነው፡፡ ይህ ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ይልቅ ፖለቲካዊ ፋይዳው እንደሚያመዝን ቀድሞውንም የታወቀ ነው፡፡ ፈረንጆቹ አንድን ነገር “politicized” ሆኗል ሲሉ ያ እንዲያ ሆነ የሚሉት ነገር በፊት ለፊት ከቆመለትና ከሚወራለት ዓላማ ውጪ ለሌላ ጉዳይ ውሏል ማለታቸው ነው፡፡ የወያኔ የህዳሴ ግድብም ወያኔ እንደሚለው ለሀገሪቱ የሚሰጠው የተለዬ ጥቅም ኖሮ ሣይሆን ሕዝብን ለማዘናጊያነትና ሊጠቀስም ሣይጠቀስ ሊዘለልም ለሚችል የተለዬ ፖለቲካዊ ፍጆታ መሆኑን እናውቃለን፡፡ አለበለዚያ የስድስት ሺህ ሜጋ ዋት ኮረንቲ ከቁም ነገር ተጥፎ እስከዚህን ድረስ 24 ሰዓት ከበሮ የሚያስደልቅና ይቀምሰውና ይልሰው ያጣን ድሃ ሕዝብ ያለ ርህራሄ የሚያዘርፍ ሆኖ አይደለም፡፡ “አንቺ ቁም ነገርሽ የጎመን ወጥሽ” እንደምንል ወያኔም በዚህች ድልድይ ማነው ግድብ ዕንቅልፍ አጥቶ እኛንም እንደሱ አትተኙብኝ እያለን ነው፡፡
በማለፊያ ክርስቶሳዊ አባባል አንድ የአደባባይ ምሥጢር እንድናገር መልካም ፈቃዳችሁ ይሁንልኝ፤ “እውነት እውነት እላችኋለሁ” አባይ ተገድቦ ቢያልቅ በኔም ሆነ በሌሎች ወገኖቼ ሕይወት ላይ አንዳችም ቁሣዊም ሆነ መንፈሣዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ በምንም ዓይነት መንገድ፡፡ እርግጥ ነው – የተሟላ የቴክኒክ ዕውቀት ያለው የሰው ኃይል ካለና እንዳሁኑ በተጭበረበረ የግዢ ሂደት አማካይነት ፎርጅድና የአገልግሎት ዘመኑን ጨርሶ የተጣለ የማቴሪያል አቅርቦት ከተወገደ እንዲሁም የሕዝብ ብዛት በቁጥጥር ሥር ከዋለ ምናልባት ልክ እንዳሁኑ በመብራት ዕጦት ዳፍንት ውስጥ ላንገባ እንችል ይሆናል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ልክ እንዳሁኑ ሁሉ ለማይጠረቃው የመንግሥት ባለሥልጣናት ኪስ ማደለቢያና ለአነስተኛ የሀገር ገቢ ሲባል ቤት ያለው ሰው ሳይጠግብ ለዬጎረቤት ሀገር ኮረንቲ መቸብቸቡ ከቀጠለ የዚያኔም ቢሆን – አባይም ተገድቦ ማለት ነው – የመብራት ፈረቃው ላይቀርልን ይችላል፡፡ እናም በአባይ ግድብ ሳቢያ ከወያኔ ጋ ድብን ያለ ፍቅር የገባችሁ ወገኖች እውነቱን ከወዲሁ እንድትረዱት ላሳስብ እወዳለሁ፡፡ ወጥመድ ውስጥ ዘው ብላችሁ አትግቡ፡፡ ሀገር ካላችሁ ሁሉም አለና፡፡
ኢትዮጵያዊ መንግሥት ቢኖረን አንድ አይደለም አሥርና ከዚያም በላይ ትላልቅ ግድቦች ሊኖሩን የመቻላቸው ዕድል ሰፊ ነው፡፡ “ልማታዊ መንግሥታችን፤ ባለራዕዩና አባይን የደፈረ ጠቅላይ ሰይጣናችን ማነው ሚኒስትራችን” እያላችሁ ሟቹን ወያኔ የምታንቆለጳጵሱ ጥቅመኞች ሁሉ ዐይናችሁን ወደጭቁኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አዙሩና እውነቱን ለመረዳት ሞክሩ፡፡ ወያኔ ከኢትዮጵያ ታሪክ አንጻር ዕድሜው የጤዛ ያህል ነው፡፡ በማታለልና በማጭበርበር 23 ዓመታትን መኖሩም የሚገርም ነው፡፡ ለዚህ ቆይታው ግን ተጠያቂው ወያኔ ብቻ ሣይሆን በተንሸዋረረ ልማት ስም አንጀታቸው ለወያኔ የሚንቦጫቦጭ አድር ባዮችና እበላ ባይ ሆዳሞች የሚያደርጉለት ሁለገብ እገዛም ጭምር ነው፡፡ የኛም አንድ አለመሆንና በሃሳብ መለያየት ለወያኔ ዕድሜ መርዘም የድርሻውን አበርክቷል፡፡ ሌላ ሌላውን ምክንያት እናንተም ታውቃላችሁ፡፡
ወያኔ የአባይን ግድብ ብቻ ሣይሆን ሌሎች በሃያና ሠላሣ የሚቆጠሩ ታላላቅ ግድቦችን መሥራት ይችላል፡፡ እንዴት? በየተራ እንይ፡፡
ለአንድ ጡረተኛ ፕሬዚደንት መኖሪያ ቤት የተከራዩት በወር ስንት ብር ነው? (ልብ አድርግ – ከ400 ሺ ብር በላይ ነው!) በየወሩ የተመደበው ሌላ ሌላ ጥቅማ ጥቅምስ ስንት ነው ? ይህ በራሱ ቢደማመር በዓመትና በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ – የሙስና መርዝ ካልተጠናወተው በቀር- አንድ መለስተኛ ግድብ ይሠራል፡፡ ለአንዲት ድሃ ሀገር ተጧሪ “ፕሬዚደንት” – ለዚያውም ፈርም የሚባልን ወያኔያዊ ደብዳቤ ለሚፈርም ከዘበኛ ያነሰ ሥልጣን ለነበረው ሰው – ይህን ሁሉ ወጪ መመደብ በስተጀርባው ሌላ ቤተኛን በእግረ መንገድ ለመጥቀም የተሸረበ ሤራ አለ ማለት ነው እንጂ አሳማኝነቱና ምክንያታዊነቱ በፍጹም አይተየኝም – “ራቁቱን ለተወለደ … “ ምን አነሰው ነበር እንዴ የሚባል? ይህ ነገር ራስን ያለማወቅ ችግር ወይም ስለሀገር ያለማሰብና በእልህ የሀገርን ሀብት የማባከን አዝማሚያ ይመስለኛል፡፡ እንደኢቲቪ የቁጭ በሉ አገላለጽ ሣይሆን እንደተጨባጩ እውነታ ከአጠቃላዩ ሕዝብ ከ85 በመቶ በላይ በባዶ እግሩ በሚሄድባት የድሃ ገበሬዎች ሀገር ውስጥ አንድን ተጧሪ ባለሥልጣን እንዲህ አንቀባርሮ የሚይዝ መንግሥት ደግሞ አንድ ግድብ ለመገንባት በሚል ሰበብ ከኔ ቢጤው ተራ ዜጋ – የወር ደመወዙ ከልመና ካላወጣው፣ እየሠራ ከሚደኸይና የኗሪ አኗኗሪ ከሆነ ምንዱብ ሠራተኛ መዋጮ መጠየቅ አልነበረበትም – አሣፋሪ ነው፡፡ እኔ እንዴት እንደምኖር አውቃለሁ፡፡ እንኳንስ ከደመወዜ ተቆርጦ ይቅርና አሁን የሚከፈለኝ ደመወዝ ተብዬ ዕጥፍ ድርብ ቢከፈለኝ እንኳን የኑሮውን ክብደት ሊያቃልልኝ አይችልም፤ የኔ ቢጤዎች የምንኖረው አንዷን ኪሎ ቅቤ በ“አጠቃቀስኩሽ” ሥልት ለዓመት እንደተጠቀመችባት ብልህ ሴት ዓይነት የኑሮን ጨውና ቅመም በብልሃት ‹አጠቃቀስኩሽ› እያልን ነው፡፡ ይህን የአባይ መዋጮ በተመለከተ የወያኔ መንግሥት ደደብነትና አስተዋይነትን ማጣት በእጅጉ ይገርመኛል – ለነገሩ ደደብነትና ወያኔ ለካንስ ሞክሼዎች ናቸውና፡፡ ስንቶችን እያዘባነነ የሚያኖር መንግሥት ጦሙን ከሚያድር ዜጋ በግድ የወር ደመወዙን ሲቆርጥ በዚህ መንግሥት ባለሥልጣናት ጭንቅላት ውስጥ የሚገኘው ነጭ ጭቃ ምን እንደሆነ ወይም የምን እንደሆነ ለማወቅ በከንቱ የምንዳክር አንጠፋም – በበኩሌ በራስ ቅላቸው ውስጥ ምን ተሸክመው እንደሚዞሩ ለመረዳት ሞክሬ ሲሰለቸኝ ደክሞኝ ትቸዋለሁ – እንዲያው ግን አምባርጭቃ ይሆን እንዴ? ሲገርሙ!
ወያኔዎች ኢንሳ በሚሉት የስለላ ድርጅታቸው ኢሳትን በዋናነት ጨምሮ የተቃዋሚ ሚዲያዎችን ሲቻላቸው ከዓለም ለማጥፋት ያ ባይቻል ደግሞ ወደ ሀገር ገብተው ሕዝብን በማንቃት የወያኔ ቅሌትና ውርደት እንዲሁም ከብረት የጠነከረ ፈርዖናዊና ናቡከደነፆራዊ የግፍ አገዛዛቸው ሕዝብ ላይ በዬጊዜው የሚፈጥረው ጭቆናና ግፍና በደል እንዳይገለጥባቸው በማሰብ በየወሩ የሚከሰክሱት የሀገር ሀብት አንድ አባይን ብቻ ሳይሆን አሥር ባሮና አሥር አዋሽን ያስገድባል፡፡ በዚያ ረገድ እኛን ብቻ ሣይሆን ሌላውን ዓለምም በሚያስደምም ሁኔታ እንደጉድ ነው ገንዘባችንን ለኛው መጨቆኛ የሚመዠርጡት፡፡ ይህን የማናውቅ እየመሰላቸው ከሆነ ተሞኝተዋል፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለትርኪ ምርኪ የሚዲያ ማፈኛ ቁሣቁስና የውጪ ኤክስፐርቶች እንዲሁም የስለላ ቫይረስ ለመግዛት ሜዳ ላይ ከሚበትኑት ለሀገር ዕድገት ቢያውሉት ከጉራማይሌያዊ የልመና ባህላቸው በወጡ ነበር፡፡ እንደነሱ የገንዘብ አወጣጥ እኮ ኢትዮጵያ እጅግ ሀብታም ናት፡፡ እነሱ ገንዘብን በሚሊዮንና በቢሊዮን መዝረጥ የሚያደርጉት የነሱን ሥልጣን ለማስጠበቅ መሆኑ ከፋ እንጂ እንዳመነዛዘራቸው ለጭቁኑ ሕዝብ ቢሆን ኖሮ ረሀብና እርዛት ከሀገራችን ጠቅልለው ከወጡ በትንሹ 23 ዓመታትን ባስቆጠሩ ነበር፡፡ ለደኅንነት የተቃዋሚ ክትትልና የፀረ-ስለላ ስለላ አባላት በገፍ የሚወጣው መዝገብ የማያውቀው ወጪ፣ በወያኔ አገዛዝ የፊጥኝ ከታሰረው ምሥኪን ሕዝብ ተቀምቶ የወያኔን ወንበር ለመጠበቅ ለተሠማራው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተብዬ የሚገፈገፈው ገንዘብ፤ ለመሣሪያ ግዢና በግዢው ሰበብ በሙስና ወደግል ካዝና የሚዶለው ቁጥር የማይገልጸው እጅግ ብዙ ገንዘብ፣ በመከላከያና በደኅንነት እንዲሁም በመሰል የፀጥታ ተቋማት ለሚርመሰመሰው ጆሮ ጠቢና አፋዳሽ ሁላ ካለበቂ ሥራ እንደ ቅጠል የሚረግፈው የሀገር ገንዘብ፣ ካበቂ ጥናትና ካለተጨባጭ ሀገራዊ ፋይዳ በዬጊዜው ለሚቋቋሙ አዳዲስ መሥሪያ ቤቶችና አደረጃጀቶች የሚወጣው ገንዘብ፣ ውጤቱ አስቀድሞ ለሚታወቅ የማይረባ ምርጫ የሚከሰከሰው ብዙ ሚሊዮን ገንዘብ፣ ለአብዮታቸው ጥበቃ ሲባል ለዬግልገል ካድሬው የሚዘራው ብር፣ሕወሓትን በዋናነት ይዞ ለዬአጋር ድርጅት ተብዎች ዓመታዊ የምሥረታ በዓላት ለፈንጠዝያና ለቸበርቻቻ የሚወጣው ገንዘብ፣ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም በባለሥልጣናት የሚመዘበረው የሀገር ሀብትና ንብረት … ሁሉ ቢደማመር ሀገራዊ ልመና ሱስ ላልሆነበት የመንግሥት መዋቅር ያለ አንዳች ምፅዋትና ቡገታ አንድ አይደለም ከመቶ በላይ ግድብና ሌላም የልማት ዕቅድ ያሠራል፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አንድ ብሔራዊ እስቴዲየም ለማሠራት ወገቤን የሚል መንግሥት ያላት ኢትዮጵያ 200 ታንኮችንና በአሥራዎች የሚቆጠሩ የጦር አውሮፕላኖችን በአንዴ ሲገዛ በሰበቡም ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው በመቶ ሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ በየማይማን የጦር “ጄኔራሎች” የግል ካዝና ሲገባ ስናይ “የነዚህ ሰዎች ዜግነት ምን ይሆን? በውነቱ ኢትዮጵያዊነቱ ይቅርና ጤናማነታቸው የማያጠራጥር ሰዎችስ ናቸው ወይ?” ብለን መጨነቃችን አይቀርም፡፡ ሰው እኮ አንድ ዓመት ይዘርፋል፤ አንድ ዓመት ይዋሻል፤ አንድ ዓመት ይሰርቃል፤ አንድ ዓመት ይሞስናል፤ አንድ ዓመት ይዘሙታል፣ አንድ ዓመት ያጭበረብራል፣ አንድ ዓመት … አዎ፣ በወረት ለተወሰነ ጊዜ ከመስመር መሠወር/መጥፋት ያለ ነው፡ አንድ ሰው የሀብት ፍቅር ካራዠው መቼስ ምን ይደረጋል በሚፈልገው ነገር እስኪጠረቃ ድረስ ወይም በቃኝን እስያውቅ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ መጥፎ ነገርን እያደረገ ይቆያል፤ ሰው ከሆነ ግና በሕይወት ውጣ ውረድ መማር አለበት፡፡ የተሸከመው አንጎል ጭቃ ሣይሆን ዛሬን ከነገና ትናንትን ከትናንት በስቲያ እያመዛዘነ ገምቢ ግንዛቤን ሊያስጨብጠው የሚችል ትልቅ መለኮታዊ ስጦታ ስለሆነ በሕይወት ፈተና ተሸንፎ ከተዘፈቀበት ሰውነትን ከሚያሳንስና ኅሊናን ከሚያጎድፍ ወደእንስሳነት ደረጃም ከሚያወርድ አዘቅት ለመውጣት መሞከር አለበት – ከወያኔ እንዲያውም ብዙ እንስሳት የተሻሉ “ሞራላዊ” ፍጡራን ናቸው፡፡ ዕድሜ ልኩን በክፋትና በመጥፎ ድርጊቶች ተበክሎና በዚያው ቆርቦ መኖር ለታዛቢም ይሰቀጥጣል፡፡ ወያኔዎች ከጧት እስከማታ ቢያጋፍሩ በቃኝን የማያውቁና በቂምና በበቀል የታጀሉ ትንግርተኛ ፍጡራን ናቸው – “የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባዬ” እንዳትሉኝ እንጂ ለምሳሌ በዐሥራዎቹ ዕድሜ ሳሉ የጀመራቸው ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-አማራ ጥላቻ አሁን ድረስ በስተርጅናም አብሮ ዘልቆ እነስብሃትንና ሣሞራን ምን ያህል እያሰቃያቸው እንደሆነ የምናውቀው ነው፡፡ ይሄ ታዲያ መረገም አይደለም ትላላችሁ? ብቻ ይህንን የምለውን ሁሉ የማናውቅና ሁኔታዎች ሲያመቹና ጊዜው ሲደርስ የማንጠይቅ ከመሰላቸው አሁንም ተሞኝተዋል፡፡
ካሉት ጥቂት መጻሕፍት ውጪ ምንም ምድራዊ ሀብትና ንብረት እንዳልነበረው ካላንዳች ሀፍረት በራሱ አንደበት ሲናገር የነበረውና የባሕርይ አምሳያው ወላጅ አባቱም “ [በድህነቱ ምክንያት] የአምስት ብርና የአሥር ብር ኖቶችን እንኳን መለየት አይችልም” በማለት የወፍ ምሥክሯ ድምቢጥ ዓይነት የዋቢነት ቃሉን የሰጠለት መለስ ዜናዊ 3.7 ቢሊዮን ዶላር በስሙ ተመዝግቦ መገኘቱን አንድ ዓለም አቀፍ ተቋም በቅርቡ አጋልጧል፡፡ ከዚያም ቀደም ብሎ በዚሁ ብዔል ዘቡል የበኩር ልጅ በሰምሃል መለስ ስም ከአምስት ቢሊዮን ዶላር (ሚሊዮን አይደለም!) – ልድገመው ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ እንደተገኘ ተዘግቧል፡፡ በአባትና ልጅ ስም የተገኘው ገንዘብ ብቻውን ከሁለት በላይ የአባይን መሰል ግድቦችን ያስገነባል፡፡ ታዲያ የምን ቧጋችነትና ማራሪነት ነው? የምንስ ማስመሰል ነው? የቆሎ ተማሪ የሀብታምም ልጅ ቢሆን ቧግቶ መብላቱ፣ ለምኖ ካልበላ ትምህርቱ ስለማይገባው ነው የሚል አፈ ታሪክ ስላለ ነው፡፡ ኢትዮጵያስ ካልቧገተችና ድሃ ልጆቿን ራቁታቸውን ካላስቀረች ልትለማ አትችልም ማለት ነው? ምን ዓይነት ዕንቆቅልሽ ነው? ኢትዮጵያየን ከ30 ዓመታት በላይ በሙያዬ ያገለገልኳት ሰውዬ የእኔ ልጅ በወያኔ ወለድ የኑሮ ውድነት ሳቢያ በቀን አንዴም መመገብ እያቃተው ከኔ ከአባቱ መናኛ የወር ደሞዝ ለአባይ አዋጣ ስባል ሰምሃል መለስ ደግሞ የኢትዮጵያን አንጡራ ሀብት በሎንዶን ታላላቅ ሆቴሎች እየተዘዋወረች ከሎንዶናውያንና ወያኔያውያን ወሮበሎች ጋር በዬምሽት ክበባቱ ጢምቢራዋ እስኪዞር እየጠጣች ስታስታውክበትና አለመላው ስትዘባነንበት ሲታይ ምን ዓይነት ሀገራዊ ስዕል ነው የምናስተውለው? የዚህን አስገራሚ እውነት ተፈጥሯዊ ፍትህስ መቼ ነው የምናየው? የሆነ የሚያበሳጭ ሀገራዊ ምስል በአእምሯችሁ ብልጭ አላለባችሁም? ስንቱ ባለሥልጣንና የጦር አበጋዝ ነው ከነየልጁ በዚህ መልክ በሀገር ሀብት እየተጫወተ የሚገኘው? ታዲያ ይሄ ሁሉ አላግባብ በሙስናና በዝርፊያ የሚባክን ሀብት ስንት ግድብ፣ ስንት የባቡር መንገድ፣ ስንት አውራ ጎዳና፣ ስንት ሆስፒታል፣ ስንት ትምህርት ቤት፣ ስንት ኮሌጅና ዩኒቨርስቲ (ያልተማሩ መምህራን የታጨቁበት ባዶና ከርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ቀድሞ የሚሰነጣጠቅ – ጥቂት ቆይቶም የሚፈራርስ ሕንፃ ሣይሆን በሁሉም ረገድ ደረጃውን የጠበቀ ማለቴ እንደሆነ ተረዱልኝ)፣ ስንት የበጎ አድራት ተቋም፣ ስንት ክሊኒክና የጤና ኬላ፣ ስንትና ስንት የመኖሪያ ቤቶችና ሕንፃዎች አይሠራም ነበርን? ይህ ሁሉ ገንዘብ ቅን ተገዢ ያደረገንን ማይምነት ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርጎ አያወጣውም ነበርን? ይህንንም ሕዝቡ አያውቅብንም ዘመኑ ሲደርስም አይጠይቀንም ብለው ከሆነ በርግጥም ተጃጅለዋል፡፡ ለነገሩ ሆድ አለልክ ሲጠግብ እኮ ጭንቅላት ፉዞ ይሆናል አሉ፡፡
በቀዳማዊ ኃ/ሥ ጊዜ ስንት ብድርና ዕርዳታ ወደ ሀገር ገባ? በደርጉስ? በአሁኑ የወያኔ ጉጅሌስ? በዕርዳታና በብድር መልክ ከሚገባው ገንዘብ ምን ያህሉ ነው በትክክል በታለመበት ሥራ ላይ የሚውለው? አሁን የሚባለውን እንስማ ካልን ወደ ሀገር ከሚገባው የብድርም ሆነ የዕርዳታ ገንዘብ ውስጥ ሩብ ያህሉ እንኳን የሀገር ጥቅም ላይ አይውልም፡፡ ይመዘበራል፤ የግለሰቦችን ኪስ ያሞቃል፡፡ ለሀገር የሚቆረቆር ባለሥልጣንም ሆነ ተቆጣጣሪ ለጋሽና አበዳሪ ሀገር ባለመኖሩ በኢትዮጵያ ስም የተቃፈፈው የዕርዳታም ይሁን የብድር ገንዘብ እሳት ውስጥ የገባ ቅቤ ሆኖ ይቀራል፡፡ በመሠረቱ ሙሰኝነት ዱሮም ነበር – ግን እንደዛሬው ዐይኑን ያፈጠጠና ግዘፍ ነስቶ በአደባባይ ሲራመድ የሚታይ አልነበረም፤ ይሉኝታ የሚባል የኅሊና ዳኛ በመጠኑም ቢሆን ነበር፡፡ ዛሬ ግን ደመወዙን የምናውቀው አነስተኛ ባለሥልጣንና የሥራ ኃላፊ ሁሉ የወር ገቢው ለሦስት ቀንም እንደማይበቃው እየተረዳን ወር ከወር ጮማ ሲቆርጥና ዊስኪ ሲጨልጥ ነው የሚገኘው – የሚመነዝረው ረብጣ ብርማ አይነሣ፡፡ ከየት አመጣው? ባለፈው ከአንድ መጽሔት እንዳነበብኩት እርሱና ሚስቱ ተኝተው ባደረጉት ነገር ምክንያት ፈጣሪ የሰጣቸውን ሦስተኛ ልጅ ሚስቱ ብቻ እንደሰጠችው በመቁጠር ትልቅ የፌሽታ ድግስ በቤቱ ውስጥ አድርጎ የ2.5 ሚሊዮን ብር መኪና ቁልፍ ለምሽቱ የሸለመው ወያኔ ሀብታም ያን የሚጫወትበትን ገንዘብ ከየት አባቱ እንዳመጣው ብንጠይቅ መልስ የሚሰጠን የለም፡፡ እነዚህን መሰል የወያኔ ንፋስ ወለድ ሀብታሞች በከንቱ የሚቀዳድዱትን ብር ለቁም ነገር ቢያውሉት አንድ ቀርቶ አምስት ስድስት ግድብ አይሠሩም ነበር ወይ? የኔ ቢጤን የሥጋን ምግብ ተውትና በቅጡ የተሠራች ኩርጥ ያለች የአተር ወጥ እንኳን ካዬ ወራት ያስቆጠረ መንዳካ ድሃ ያለችውን መናኛ ሣንቲም በግድ ከሚቀሙ እነዚህንና አላሙዲንን የመሳሰሉ ደደብ ሀብታሞችንና ቱጃር የባለሥልጣን ነቀዞችን ቢያስተባብሩ አባይን የሚያስንቅ ስንትና ስንት ግንባታ ሊሠሩ አይችሉም ነበር ወይ? እነሱ እንደልባቸው ለሚምነሸነሹባት ሀገር እኔ ምን ቤት ነኝና የሌለኝን ልስጥ? ይህኛው ግፍ ከሁሉም ግፎች አይበልጥምን? አሁን ኢትዮጵያ በርግጥ የማን ናት? ከትንሽ ጣት ምን ተቆርጦ ይወሰዳል? እነዚህ የመንግሥት ሰዎች ግፍ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም ማለት ነው? ጤፍ በኩንታል ከብር 1600 በላይ በሆነበትና የአንድ ወዛደር ወርሃዊ ደሞዝ ከ400 ባልበለጠበት ሁኔታ ምኑን ነው ከምኑ የሚቆርጡት? ምነው እስከዚህን አቅል አሳጣቸው? …
አባይን ተገድቦ ማየት ማንም አይጠላም፡፡ “አሻራውን አባይ ላይ የማያስቀምጥ ኢትዮጵያዊ አይደለም” የሚሉት ፈሊጥ ደግሞ የእውነት መሠረት የሌለውና ጠርዝ የለቀቀ የግድብ ‹ፖሊቲሳይዜሽን› ነው፡፡ ከእውነቱ ፍጹም የራቀ የማጨናበሪያ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ መቼም ቢሆን አባይ ቢገድብ የሚጠላ ኢትዮጵያዊ ሊኖር አይችልም – መንግሥት ቀርቶ የመንግሥት ጳጳስ ቢያወግዘንም የአባይን መገደብ ሣይሆን የምንቃወመው ጠንጋራ አካሄዱንና የወያኔን ገደብ የለሽ ቱልቱላ ነው፡፡ ለምሳሌ ከፍ ሲል እንደተገለጸው ግድቡ ለሆነ ችግር ማስተንፈሻ ድንገት ጣልቃ ገባ እንጂ ሕዝብ አልመከረበትም፤ የሥራው ኮንትራት አሰጣጥም ብዙ ችግር እንዳለበት፣ ዕቃ አቀራረብና ሌላ ሌላ ሂደት ላይም ወያኔያውያን ባለጠጎችና ሞሰቦን የመሳሰሉ የወያኔው መርዝአቀባይ ደንገጡር ድርጅቶች ይበልጥ እንዲከብሩበት ተደርጎ እየተካሄደ መሆኑ ከታማኝ የዜና ምንጮች ሰምተናል፤ ታዲያስ? ለምን እንታለላለን? እንጂ በመሠረቱማ ወያኔን መጥላትና የአባይ መገደብ የግድ የሆነ ግንኙነት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ችግሩ ተደጋግሞ እንደተነገረው ዘረኝነትን በዋነኛነት ጨምሮ ከአባይ በፊት መገደብ ያለባቸው ብዙ ወያኔያዊ የመጥፎ አገዛዝ ጎርፎች መኖራቸው ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ ለአባይ ድምቡሎ አላዋጣም፤ ፍላጎቴ ራሱ ዜሮ ነው፡፡ የኔ ሰዎች የያዙት ስለማይመስለኝና ስላልሆኑም እንዲያውም ስለአባይ ወሬው ራሱ ባይነሳብኝ እመርጣለሁ – ወያኔን ብሎ ለኢትዮጵያ አሳቢ ይታያችሁ! አንድስ አንድስ እሚያህል መሬት እየገነደሰ ለባዕድ የሚሸጥ ወያኔ እንዴት ለሀገር ተቆርቁሮ ይህን ታላቅ ፕሮጀክት ሊጀምር ይችላል? እደግመዋለሁ – ግድቡን ግን ጠልቼ አይደለም፡፡ በሌላም በኩል ካየነው እኔን እየራበኝ፣ ኑሮየ የጎሪጥ እያየኝ ነጋ ጠባ እያላገጠብኝ ከኔ ተርፎ ለአባይ ማለት ከጅብ ተርፎ ለውሻ እንደማለት ስለሆነ ላዋጣ ብዬ ልግደርደር ብል እንኳን እንደስድብ ተቆጥሮ “ተው አንተ፣ አቅምህን ዕወቅ፣ ዕረፍ እንጂ፣ አንተን አይመለከትም፤ ምን አለህና! “ ነው ልባል እሚገባ፡፡ ዐይን አይቶ ልብ ይፈርዳል ይባላል፡፡ በቀን አንዴ መቅመስ ያቃተው ሰው፣ የነተበ ሸሚዝና አቧራ የቃመ የሸራ ይሁን የላስቲክ ጫማ ማድረጉ የማይታወቅ ሰው፣ ወር በገባ በአምስተኛውና ስድሰተኛው ቀን ሁሉም የቤት አስቤዛው ተመካክሮ በአንዴ የሚያልቅበትና ኑሮውን በብድርና እልፍ ሲልም በውጭ ሀገራት በሚኖሩ ዘመዶቹ መጠነኛ የበጀት ድጋፍ ተሰናባቹን ወር ከአዲሱ ወር ለማገጣጠም የሚፍጨረጨር ሰው፣ ልብሱ እላዩ ላይ አልቆ – ከአንሶላ ጋር ተቆራርጦ – ከሶፋና አዳዲስ የቤት ዕቃዎች ግዢና ጥገና ጋር እስከወዲያኛው ተፋትቶ፣ … በደመ ነፍስ ብቻ (ጌታ) ናስቲለው የሚኖር ሰው የግድብ ወሬ አይገባውም – እንዲገባው መጠበቅ ራሱ ቂልነትና ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡን የሚያስተርት ፌዝና ቀልድ ነገር ይመስለኛል፡፡ ይህ ግድብና የግድብ ቱሪናፋ የቅንጦት ወሬና እውነትም ለቡትለካ እንዲያመች ለወያኔ ዕድሜ ማራዘሚያነት ተለክቶ የተሰፋ መለስ ዜናዊያዊ የማጭበርበሪያ ካባ ነው – ካባ አሰፋፍ እንደሱ እንደመለስ የሚሆን ደግሞ በዓለም የለም፤ ማገብት፣ ተሓት፣ ተሓህት፣ ሕወሓት፣ማሌሊት፣ ኢማሌኃ፣ ኢዴመአን፣ ኢሕዲን፣ ብኣዴን፣ ደኢሕዴግ፣ ኦሕዴድ፣ ብዙ ንቅናቄዎች፣ ብዙ ዴዶች … ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ …ይህ ሁሉ ካባ ወያኔ ላይ የሚጠለቅና በአብዛኛው በኢንጂኔር መለስ ዜናዊ የተሰፋ ነውና ነበርም – አማርኛውም ጠፋኝ ልጄ፡፡ በዚህ በአባይ ግድብ የውሸት ካባ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት አይለካም – መለካት ካለበት እንግዲያውስ ይህን ወያኔያዊ ቅራቅንቦና የነፃነት ትግልን የማደናቀፊያ ሥልት ተከትሎ ራሱ በመወናበድ ሌሎችን የሚያወናብድ ቀፎ ዜጋ ነው – በቃ ቀፎ፡፡ አናቱን በመዶሻ እየወቀጡት እግሩን ሲያኩት መታለሉ የማይገባው ዝንጉ ካለ ቀፎ ብቻ ሣይሆን ድንጋይ ራስም ሆዳምም ደንቆሮም ነው፡፡ ለእኔ ሀገርና መሪ ሲኖረኝ ሁሉም ይደርሳል፡፡ ዝንጀሮ “ቀድሞ የመቀመጫየን” እንዳለችው ሀገራዊ ነፃነት ሣይኖረኝ አንድ ሺህ ግድብና አንድ ሌላ ሺህ ባቡር ከነሃዲዱ ቢኖረኝ ምንም አይፈይድልኝም፡፡ ጣሊያን በአምስት ዓመት የሠራቸው የልማት አውታሮች ጥቅማቸው እንዳለ ሆኖ ቅኝ ገዢውን ግን ወደ መልአክነት አልለወጡትም፤ በአፓርታይድ ዘመን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የታዩና ሀገሪቷን ከበለጸጉ የዓለም ሀገሮች ተርታ ያስሰለፉ የዕድገትና ልማት እመርታዎች የአፓርታይድን ሥርዓት ከመገርሰስ ካለማዳናቸውም በላይ ሥርዓቱን ከዓለም አቀፍ ውግዘትና መነጠል አውጥተው ለጽድቅና ለበረከት አላበቁትም፡፡ ኦ!ኦ! አሁንስ በቃኝ እባክህን፡፡ ዕንቅልፌ እያዳፋኝ ነው፡፡ እነዚያ እርጉም ትናንሽ ወያኔዎችም ግብዣየን መቀበል አለመቀበላቸውን ላረጋግጥና ጋደም ልበል፡፡ ከቅብዥር ነፃ የሆነ እውነተኛ ዕንቅልፍ ባይኖርም ዐረፍ ማለቱ አይከፋም፡፡ እነዚህ ነቀዝ ወያኔዎች እያሉ በቅጡ መተኛትም እኮ ቀረ፡፡ 11፡30 ሌሊት (ንጋት?)፡፡ 24/7/2006ዓ.ም
No comments:
Post a Comment