የጥላቻው እሳት ቆስቋሹን ያቃጥለው
March 30, 2014
ዳኛቸው ቢያድግልኝ
የትግል መሰረቱን ጎጥ ላይ ያደረገ፣ የእድገት ልኩን ዘረፋ ላይ ያዋለና የእውቀት ጥጉን ውሸት ላይ የመሰረተ እንዴትም ሆኖ የነጻነት ታጋይ አይሆንም። ይልቁንም በሕዝብ ጫንቃ ላይ ተንፈራጥጦ እንዲኖር የክፋት መርዙን ይረጫል እንጂ። ምንም በሁኔታዎች አስገዳጅነት ቢተጣጠፍ እንኳ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የማድረግ አቅም ስለሌለው ሕብረት ያስፈራዋል፣ ነጻነት ያጥወለውለዋል፣ አንድነትም ያስበረግገዋል። ኢትዮጵያ ለወያኔ ትርፍ እስካስገኘች ድረስ እንደምትታለብ ላም ነች። ከዚያ በላይ ወያኔዎች ሀገራዊ ራዕይ የሚባል ነገር የላቸውም።
እንደ ሀገርና እንደ ሕዝብ ያለብንን ፈተና በጎጥ መነጽር አይተን በጥላቻ ክርክር ተጯጩኸን በግል ስምና ዝና ጦዘን ልንወጣው ፈጽሞ አይቻለንም። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እለት በእለት የምንመለከተው ሁነት እያሳየን ያለው ተፋቅረንና ተደጋገፈን መኖር የሚገባን ወገኖች ተናንቀን ስንነካከስ ነው። ጃስ እያሉ የሚያናክሱን ደግሞ እንግሊዝ በቀበረው የእርስ በእርስ መተላለቂያ ፈንጂ፣ ጣልያን በቀመመው የጎሳ ክልል መርዝና በየሃገሩ እሳት ጭረው በሚወጡት ለጥቅማቸው ሲሉ ምንም ከማድረግ በማይመለሱ ሀያላን እገዛ እየተጠቀሙ ወደ ጥፋት የሚነዱን ደናቁርቶች ናቸው። ሰሞኑን በወያኔዎችና ለወያኔ የጥላቻና ፕሮፖጋንዳ ሰለባ በሆኑ ቡድኖች ወገኖቻችንን በዘር ለማናከስ እንደ አበደ ውሻ የሚክለፈለፉ በዝተዋል። የሰከነ የአንድነት ድምጽ እንዳይደመጥ ወያኔ ከፍተኛ አፈና በሚያደርግባት ኢትዮጵያ ጎልቶ የሚደመጠው የደንቆሮ ጩኸት ነውና አማራጭ ድምጽ እንዲደመጥ ካላደርግን ህዝባችን ሊወናበድ ይችላል።
በከሃዲና ስግብግብ የአፍሪካ መሪ ተብዬዎች ውክልና የሀገርና አህጉር ሀብትና ቅርስ በንግድ ሽፋን ዘረፋ ላይ ለተሰማሩ ሀገር በቀልና የወጪ ከበርቴዎች እየተቸረ ነው። በዘመናዊ ትምህርት ስም የሀገር ፍቅርንና ለህዝብ የመቆም አስፈላጊነት ችላ እንድንል የተበረታታን ተልፈሰፈስንና የማንነት መሰረታችን ተናግቶብን ብዙ ዘመነኞች እኛንና ህዝባችንን ለብልቦ የሚፈጀንን የጥፋት እሳት እንደ ደመራ እያጨበጨብን ከበን እያየነው እንገኛለን። ኢትዮጵያ በታሪክዋ አይታ የማታውቀው በሌላውም አለም ያልተለመደ አይነት አሳፋሪ የሀገር ጠላት የሆነ የዱርዬ ስብስብ መንግስት ነኝ እያለ አገሪቱን ለእቁብ ወይንም ለቤት ኪራይ ገንዘብ እንዳጠረው ነጋዴ ሃገራችንን በርካሽ ዋጋ እየቸበቸበ ይገኛል።
በሀገር ልማት ስም ከየአቅጣጫው የሚሰበሰበው የብድር መአት በኛ ዘመን ቀርቶ በልጅ ልጆቻችን ጊዜም ተከፍሎ አያልቅም። የተበደሩት ገንዘብ ግን ግማሹ ወደ መጣበት ሀገር ተመልሶ በሌቦቹ ባለስልጣናት ስም በተከፈቱ የባንክ ሂሳቦች ገቢ ተደርጎ የጨረቃ ሚሊየነሮችን መፍጠሪያ ሆኗል። ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መሰረትዋና አብዛኛው ህዝቡዋ የሚተዳደርበት ሁኖ ሳለ የእርሻ መሬቶች ለውጪ መንግስታትና ግለሰቦች እየተቸበቸቡ ነው። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያውያንን ዛሬ መሬት አልባ ነገ ደግሞ አገር አልባ ያደርጋቸዋል።
የዛሬዎቹ መሪ ተብዬዎች መሬትን መያዝ ሀገርን መቆጣጠር ነው ብለውም ነው መሬት የመንግስት ነው የሚሉት። አዎን ዛሬ መሬት የትግራይ ማፊያዎች ሀብት ነው። ያሻቸውን ለማድረግ የያዙት ታንክና ላውንቸር መብት አጎናጽፎአቸዋል። የተቀረው ኢትዮጵያዊ መሬትም መብትም የለውም! ሌላ ቀርቶ ነገና ከነገወዲያ ጤፍ፣ ስንዴና ገብስም የትላልቅ ‘ምርጥ ዘር’ አምራቾች ሸቀጥ እንጂ ለዘመናት መሬቱንና የሰብሉን ዘር ሲንከባከብ የኖረው ገበሬው ሀብት አይሆኑም። ገበሬው የዘርና ማዳበርያ ዋጋ መክፈል እያቃተው መሬቱን ጥሎ ለማኝና ስደተኛ እንዲሆን እያደረጉት ነው። ይህን አደገኛ አኪያሄድ አሁን ካልገደብነው ኢትዮጵያ የምትባል አገር መኖሩዋ አጠራጣሪ ይሆናል። ይህም ባይሆን እንኩዋን ህዝባችን በገዛ ሀገሩ ለጥቂት የውጭና የውስጥ ዘራፊ ባለሃብቶች ጪሰኛ ይሆናል። ወያኔዎች ያለመታከት ለዚህ መከራ እያሰናዱን ነው እኛም ዛሬ ለነሱ ደባ ተመቻችተንላቸው ለዘመናት በጎሳ በቁዋንቁዋም ይሁን በሀይማኖት ሳንለያይ አብረን መኖራችንን ችላ በማለት በጎጥ አንሰን በመንደርም እየተከፋፈልን አገርም ማንነትም ለሚያሳጡን አረመኔዎች በራችንን በርግደን እንዲያምሱን ልንፈቅድ አይገባም።
ዛሬ በራሱና በወገኖቹ ላይ በሚደርሰው ሰቆቃ በማዘን “ራሴን ጠላሁ” “በኢትዮጵያዊነቴ አፈርኩ” የሚለው የተቆጣ ሕዝብ ብዙ ነው። ይህን ቁጣውንና ዱላውን ለሰቆቃው ምንጭ በሆነው ወያኔ ላይ እንዳያሳርፍ እነ ስብሃትና በረከት ስምኦን ጸቡን በአማራና ኦሮሞ፣ በክርስትያንና ሙስሊም ወ.ዘ.ተ. መካከል ለማስቀረትና ለኛው የእልቂት ድግስ መደገስ ከጀመሩ ብዙ ቆዩ። ያለመንግስትና ያለፖሊስ ተከባብሮ የመኖር ድንቅ ባህልን ያዳበረውን ሕዝብ ዛሬ አናቁረውት ሌብነት ቅጥፈትና ዘረፋ የብልጥ መንገድ እንደሆነ እየሰበኩ ወደ ንቅዘት የሚመሩት እነዚሁ የወያኔ ወሮበሎች ናቸው። የማይሞላ ከርስና ባዶ ጭንቅላት ያላቸው የየብሄረሰቡ ተወካይ ተብዬዎች ደግሞ አንደ ተወጠረ ከበሮ አለቆቻቸው ትንሽ ኮርኮም ወይም ኮርኮር ሲያደርጉዋቸው ይጮሀሉ። በጎሳና ሀይማኖት ህዝባችን አይነጣጠልም ያልነው እውነት እንዲሆን እርስ በራሳችን እንዳንፋጅ ሁላችንም የወያኔን የጥላቻ ቅስቀሳ ልማክሰም የድርሻችንን የምናደርግበት ጊዜ ዛሬ ነው። ይሄ አያገባኝም ወይም አይደርስብኝም ማለት ከሌሎች ተሞክሮ አለመማር ይሆናል።
ሩዋንዳውያን አንድ ሚሊየን ያህል ወገኖቻቸው በግፍ ከተፈጁ በሁዋላ በህልማችንም በእውናችንም ጉዋደኛ ለጉዋደኛ ጎረቤት ለጎረቤት እየተራረድን እንዲህ ያለ ክፋት እኛው በኛው ላይ እንፈጸማለን ብለን አናስብም ነበር ሲሉ መስማት የተለመደ ነው። ከበርካታ አመታት በሁዋላ በሕዝብዋ ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ አሁንም ድረስ ድባቡ አልጠፋም። አሁንም ድረስ እያስታወሱ የሚያለቅሱ አሉ። በዚሁ ግፍ ምክንያት በርካቶች አይምሮአቸውንም ስተዋል። በቁንጅናዋ ተማርኮ በጸባይዋ ተመስጦ አፍቅሮ ያገባትን ሚስቱንና የልጆቹን እናት የጥላቻ ቅስቀሳ ሰለባ በመሆን በቆንጨራ ጨፍጭፎ እንዲገድል የተደረገ ሰው በህይወት ቢኖርም ሰው መሆን አይችልም። ሺህ ይቅርታ ሺህ ሱባዔ ሺህ ቅጣት ያንን ጤና መልሶ ሊሰጠው አይችልም። የጥላቻውን መርዝ መጀመሪያ የረጩትና እሳቱን ያራገቡት ግን ለመግዛት እንዲመቻቸው አንዱን ከሌላው አሳንሰው እርስበርስ እንዲጠላላ በማድረግ የኖሩት ቅኝ ገዢዎቹ ናቸው። ከነጻነት በሁዋላም ጎረቤት በጎረቤቱ ላይ በጥላቻ እንዲነሳሳና ያ ሁሉ እልቂት እንዲፈጸም እጃቸው አለበት የሚባሉት መስቀል ይዘው ክርስትና ሰባኪ ነን የሚሉ ነጮች መሆናቸው ይነገራል።
ኤርትራ “በነጻ አውጪዎቹ” ስትያዝ ለብዙ አመታት እዚያው ኑሮ መስርተው ሃብት አፍርተው የነበሩ ኢትዮጵያውያን “አያት ቅድም አያቶቻችሁ ከዚህ አይደሉም” እየተባሉ በጎሳ ጥላቻ ቤተሰባቸው እንዲፈርስ ተደርጎ ባዶ እጃቸውን በባዶ እግር እንዲባረሩ ወደባህርም እንዲገፉ የተደርጉትን ልናስብ ይገባል። ከመሀል አገርም ከሌላ ብሄረሰብ ተወላጆች ጋር ተጋብተው ይኖሩ የነበሩ ኤርትራውያን እራሱ ኤርትራው በሆነው በመለሰ ዜናዊ “የአይናቸው ቀለም ካላማረን እናባርራልን” የሚል የ እብሪት ፖለቲካ ቤተሰባቸውንና ንብረታቸውን በትነው ከሀገር እንዲወጡ እንደተደርጉ ልናስታውስ ይገባል። ዛሬም ከየቦታው የሚፈናቀሉት ወገኖቻችንን ቁጣ ልናስብና ይህ ቁጣም ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ማሰቡ ከሚጠብቀን አደጋ እንድንጠነቀቅ ያመቻቻል።
አማራው ከኦሮሞው ቢጣላ ገላጋይ ሆነን እንቆማለን የሚሉት የትግራይ ተገንጣይ ቡድን አባላትና ደላሎቻቸው ሕዝብን ከሕዝብ ለማናከስ ደፋ ቀና የሚሉት እሳቱ ቢነሳ እነርሱ የሚተርፉ መስሏቸው ነው። የተገፋው የተጨቆነውና በደል በቃኝ የሚለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቱን ለይቶ አውቆ የጥላቻ እሳት እየቆሰቆሱ ያሉትን በተባበረ ክንድ ሊደቁሳቸው እንደሚችል የተገነዘቡ አይመስልም። ለዚህም ነው ሕዝቡ ቁጣውን ወደነዚህ አረመኔዎች ሊያዞርና ሴራቸውን ሊያከሽፍ የሚገባው ዛሬ ነው ጊዜው እየረፈደም ነው የሚል ጥሪ ከየአቅጣጫው የሚስተጋባው። በርካቶች ወደ ጥላቻ ወጥመዳቸው እንዳይገቡ እነዚህን ክፉዎች መንጥሮ ማውጣት ለነገ የማይባል አስቸኩዋይ የህልውና ጥያቄ ነው። መሰረታዊው ልዩነት ሀገር በሚዘርፉ፣ በሚያፈርሱና እልቂት በሚደግሱት ወያኔዎችና በተቀሩት ኢትዮጵያውያን መካከል እንጂ በተለያዩ ብሄረሰቦችና ሃይማኖት ተከታዮች መሀከል አይደለም።
በምዕራቡ ሀገራት በሚሰበክው የመድብለ ፓርቲዎች አስፈላጊነት ምክንያት ኬንያ በርካታ ፓርቲዎች ማቋቋም ባሰበችበት ወቅት ፖለቲከኞቹ መራጮቻቸውን ፍለጋ በየጎጡ መሄዳቸው ያስከተለው ከባድ ቀውስ ዛሬ የሚታወስ ነው። አሜሪካ መድብለ ፓርቲ ብላ አስጨንቃ ከያዘችን ብለው እነዚያው የቀድሞ ፖለቲከኞች ወደየዘመዶቻቸው ሲሄዱ ይህ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ያገናዘበ አገናዝቦም መፍትሄ የሰጠ አልነበረም። ብዙ ፓርቲዎችም ተፈጠሩ ግን የጎጥ ፓርቲዎች ሆኑ። ይህን በመከተልም አሰቃቂ የሆነ አደጋ ሰላማዊ ተብላ በምትታወቀው አገር ተከሰተ። የአንድ ሀገር ልጆች መሆናቸውን ከመቅጽበት ዘንገተው ኩኩዩ ሉዎ እየተባባሉ በገጀራና በቀስት እርስበርስ ይገዳደሉ ጀመር። ኬንያውያንም እኛ ሰላም ወዳዶችና የጎሳ ፖለቲካ ወደ ጽንፍ የማይወስደን ነን የሚል ጽኑ እምነት የነበራችው ቢሆኑም የጥላቻው ቅስቀሳ ለጊዜያው የፖለቲካ ጥቅም ከተለኮሰ በሁዋላ በሀገራችን እናያለን ብለው ያልገመቱት የጥላቻ ግድያ ሲፈጸም ለመመልከትና ተሳታፊም ለመሆን ተገደዱ። ። የረገፉት ረገፉ የተፈናቀሉትና ከሞት የተረፉት ግን ዳግም የሰላም እንቅልፍ አይኖራቸውም። ኬንያ የበርካታ የውጭ መንገስታትና ድርጅቶች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም የሚያገኙባት ሀገር በምሆኑዋ ዓለም ትኩረት ሰጥቶት እንደ ኮፊ አናን ያሉ መፍትሄ አፈላላጊዎች ሁሉ ተረባርበው እሳቱን ለጊዜውም ቢሆን አበረዱት።
የኛዋ ኢትዮጵያ ግን እኛው ካላዳንናት በእሳቱ ላይ ነዳጅ የሚጨምር እንጂ እሳት የሚያበርድላት ብዙ እንደማይኖር ልብ ልንል ይገባል። ወራሪን በማሸነፍ የሚገኝ ነፃነት የሚያስከፍለውን መስዋትነት በኩራት ልንሸከም የሚገባን እኛው ኢትዮጵያውያን ነን። አዋሳኝ አገሮችም በአብዛኛው ለኛ መዳከምና መበታተን ተግተው የሚሰሩ ናቸው። የጎጠኞችና የባንዳዎች ብቸኛ ሕልም ደግሞ ምንም ያክል ትሁን ስልጣንና ሀብት ማጋበስ ብቻ ነው። በጎጥ የጀመረ ፀብ በእንጭጩ ካለተቀጨ መንደርና ቤተሰብ ድረስ ይዘልቃል። የትግራይ ተገንጣይ ቡድን ሚሊየኖችን አስፈጅቶ ስልጣኑና ሀብቱ ግን የተገደበው በጥቂት ቤተሰብና መንደር ላይ መሆኑ ሩቅ የማይወስድ ምሳሌ ነው። የትግራይ ሕዝብ በጥቅሉ ከሌላው በተለየ ደስተኛ እንዳልሆነ ማየት ትምህርት ነው። በመከባበርና በመተሳሰብ ለልጆቻችን ለልጅ ልጆቻችን ህልውናና ነፃነት ስንል የአቅማችንን እንስራ ኢትዮጵያንም እናድናት።
በጎጠኞች መርዘኛ ሴራ ኢትዮጵያዊነት አይረታም!
ኢትዮጵያ በነፃነትዋ ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!
No comments:
Post a Comment