Wednesday, March 26, 2014

ሃያ ሦስት የስቃይ፤ የሰቆቃና የእልቂትና ዓመታት

የኢትዮጵያ ህዝብ በፋሽስቱ ህወሓት ብልሹ አስተዳደርና አምባገነናዊ አገዛዝ ስር ወድቆ በኑሮ ውድነትና በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ፣ ሰብኣዊና ዲሞክራሲያዊ መብቱ ተነጥቆ ለአፈናና ለእስራት እየተዳረገ፣ ሉዓላዊ ክብሩ ተደፍሮ ለም መሬቱንና አንጡራ ሃብቱን እየተሸነሸነና እየተቦረቦረ ለባዕድ እየተሸጠ፣ በገዛ ሀገሩ ተፈናቃይና የውጭ እጅ ተመልካች ሆኖ ለስደትና ለእንግልት እየተዳረገ እነሆ ዛሬ ከ23 ዓመት በላይ የሰቆቃ፣ የእልቂትና የመከራ ዓመታት ተቆጠሩ።

ለአለፉት 23 ዓመታት የደፈረሰው ፖለቲካችን ወደ ጭቃነት እየተቀየረ ስለመሆኑም ምንም ምስክር አያሻውም።ፋሽስቱ ወያኔ ከሀገር ሉዓላዊነት እስከ ታሪካችን፣ ከባንዲራችን እስከ እንደ ሕዝብና እንደ ሀገር ያለን ደረጃ መቀመቅ አውርዶታል። አንዳንዶቻችን እንደዚህ ዘመን ትውልድ አባልነታችን ያለፈውን መለወጥ፣ ዛሬን የሰውነት ደረጀችን በጠበቀ ሁኔታ መኖርና ነገንም ላልተወለዱ ልጆቻችን መልክ አስይዞ ለማውረስ ከቁጥጥራችን እየወጣ መሆኑን በግልጽ እንመለከታለን። በሌላ ወገን ወያኔዎቹ የአለፉት 23 ዓመታት የአንድ ጀምበር ያህል አጥረውባቸው፤ ተጨማሪ 40 አመታትን ለመግዛት በማለም ሲንፈራገጡና በቀቢጸ ተስፋ ህዝብን ለማማለል ሲሞክሩ እያየንና እየሰማን ነው። ስንራብ መጥገባችንን ይነግሩናል። ስንታረዝ ደራርበን መጎናፀፋችን ይታያቸዋል። ሀገራችን ከአለም ሀገሮች ተርታ በሁሉም መስኮች ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ በማይታመን ፍጥነት እየወጣች ወደ ግርጌ ስትወረወር፤ ወንበዴዎቹ ወያኔወች ግን ሀገራችን ተሞሸረች አማራች ይሉናል። የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲረግጡት የሚደቅን ቅጠል ያህል በመቁጠር ከህግና ከአመክንዮ ውጭ በማን አለብኝነት ሕዝባችንን በንግድ ድርጅቶቻቸው እየገፈፉ እርቃኑን አስቀርተውታል።

ጉጅሌው ወያኔ ሥልጣን ሲይዝ፣ ከፎከረባቸው አንዱ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀን ሶስቴ የሚበላበትን ሁኔት ፈጥሮ ከረሀብ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚገላገልበትን ባዶ ቃል ኪዳን ገብቶ ነበር። ነገር ግን ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀን ሶስቴ አበሳውን እየበላ ይገኛል። ምግብማ ከየት ተገኝቶ! ረሀቡ፣ ጠኔው ከዛሬ ሀያ ዓመት ሁኔታ በሶስት ዕጥፍ ጨምሮ፣ ዛሬ እስከ 25 ሚሊዮን ሕዝብ ጦሙን የሚያድርባት አገር ስለሆነች በየጊዜው የተባበሩት መንግስታትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከሚያወጡት መግለጫ መረዳት ይቻላል። ዛሬማ፣ ነጻ ገበያ ብሎ የፎከረብን ነጻነት ተረስቶ የዘይትና የስኳር ዋጋ እስከመቆጣጠር ገብቷል። ከመብራት፣ ውሃና ኔትዎርክም ብሶ ህዝብ በእጦት ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ይገኛል። በቅርቡም በመላ ሃገሪቱ መብራት፣ ውሃና ኔትዎርክ እጦትን አስመልክቶ ሰልፍ ሊወጣ ቅድመ ዝግጅቶች እየተገባደዱ እንደሆነም እየተሰማ ነው። ከዚህ በላይ የጨለማ ጊዜ የለም።

የወያኔ አገዛዝ ለአለፉት 23 ዓመታት የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም አሳልፎ በመስጠትም በተደጋጋሚ ብሄራዊ ክህደት ሲፈጽም የቆየ ቡድን ነው። ይህንን ብሄራዊ ክህደት ሲፈጽም ካለማወቅ፤ ከችኮላ ወይም በደመነፍስ ከመጓዝ የተሠራ ስህተት አይደለም። ከአጠቃላይ የፓለቲካ ስትራተጂውና ግብ ጋር የተያያዘ አካሄድ ስለመሆኑ መስካሪ አያሻም። ፋሽስቱ ህወሓት በህዝብ የተተፋ ቡድን በመሆኑ የሀገሪቱን ፓለቲካና ኤኮኖሚ ለመቆጣጠር የውጭ ኃይሎችን የገንዘብ፤ የወታደራዊና የዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ስለሚሻ ነው የሀገሪቷን ብሄራዊ ጥቅሞች መረን በለቀቀና ድፍረት በተሞላበት መልክ ለውጭ ኃይሎች በየጊዜው አሳልፎ የሚሰጠው።ለዚህም ነው የምግብ እጥረት ያለባት የሀገራችንን ሰፋፊ ድንግል መሬቶቿን ለሀገሪቷ ዜጎች ከልክሎና አፈናቅሎ ለመካከለኛው ምሥራቅና ለእስያ ሀገሮች ልማታዊ ድርጅቶች በነፃ በሚባል ደረጃ እስከ 99 ዓመት በሚደርስ ውል ፈርሞ እየሸጠ የሚገኘው። ሰፊ ለም የድንበር መሬታችንንም ቆርሶ ለባዕዳን በመሸጥ ላይም ለመሆኑ ከሰሞኑ ለሱዳን ተላልፎ የተሰጠው መሬት ማስረጃ ነው።

በርግጥ የተደራረበ ጭቆናና መከራ ያንገሸገሸውና በልቡ የሸፈተው ህዝብ የጥቂት አምባገነኖችና ሰው በላ መሪዎች የባርነት ቀንበር ተሸክሞ ዘላለም መኖር እንደማይችል ግልፅ እየሆነ መጥቷል። በመሆኑም እንደ እሳተ ጎመራ ውስጡ ውስጡን እየተብላላ ቆይቶ ዛሬ ሊፈነዳ የተቀራበውን የህዝብ ዓመፅ መለብለብ የማይቀርላቸው መሆኑን በውል የተረዳው የጉጅሌው ወያኔ ቡድን ከመቼውም በላይ በፍርሃትና በጭንቀት ተውጠው እንዳበደ ውሻ መቅበዝበዝ፣ መወራጨት፣ መናከስና መተራመስ እንደ ጀመሩ በጋሃድ እየታየ ነው። ባለፈው ሳምንት በሰማያዊ ፖርቲ ሴት አመራርና አባላት መሪነት የታየውን አመጽ ተከትሎ ፋሽስቱ ወያኔ የወሰደው እርምጃ ለዚህ በቂ ማሳያ ነው። ሌላው የአዋጅ ጋጋታ፣ የዉሸት እምብልታ፣ ዜጎችን ያላንዳች ምክንያት ማስፈራራት፣ እስር ቤት ማጎር፣ ማሳደድ፣ መግረፍና ማፍን የመሳሰሉ የቀቢፀ ተስፋ እርምጃዎች በግልፅ የሚያሳዩን የስርዓቱን መፈረካከስና የውድቀቱን ዋዜማ መቃረቡን ነው።

ስለዚህ ግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህንን በሞት ጣር ላይ ሆኖ እያቃሰተ የሚገኘውን አገዛዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር መፍትሄው በእጃችን ነው ይላል። ግንቦት 7 መፍትሔው ስለጨቀየው ፖለቲካ እያወሩ ፈጣሪ ባመጣው ይመልሰው ማለት አይደለም ብሎ በፅኑ ያምናል። መፍትሔው እርስ በእርሳችን ስንወጋገዝ መኖርም ሳይሆን ልዩነቶቻችን በማጥበብ፤ ጠብታዎች ባህር እዲሆኑ ማድረግ ነው። መፍትሔው እጅን አጣምሮ ጥቂቶች ታምር እንዲሰሩ መጠበቅም አይደለም። መፍትሔው ከያንዳንዳችን የሚጠበቀውን ሌላውን ሳንጠበቅ መወጣት እንጂ። ስለዚህ አምባገነኖችን መካብ ዙፋናቸውን አግዝፎ በመመልከት ከትግል መሸሽ የችግሩ መፍትሔ በጭራሽ ስለማይሆን ኑ! ግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አገዛዙን ከህዝብ ጫንቃ ለማውረድና ሃገርን ለማዳን እያደረገ ያለውን ትግል ይቀላቀሉ በማለት ሃገራዊ ጥሪውን በድጋሚ ያቀርባል።



No comments:

Post a Comment