በዳዊት ዮሃንስ

የዳቦ ቅርጫት እየተባለች ስትሞካሽ የኖረችው ኢትዮጵያ የሚላስ የሚቀመስ ጠፋቶ ሕዝቦቿ አንጀታቸው እየተጣበቀ አደባባይ ወጥተው ብሶታቸውን እንዳያስተጋቡ አንደበታቸው እየታፈነ፣ የሕወሓት ሹመኞች እንደልባቸው በሚቦርቁበት አሻንጉሊት ፓርላማ ሕዝብን የሚያሸማቅቁና ዜጎችን እግር ተወርች የሚጠፍሩ ሕጎች እየተፈበረኩ ሲተገበሩ፣ ሕዝቡ ከድህነት ጋር ታግሎ ያፈራውን አንጡራ ሃብቱን በጠረራ ፀሐይ ሲቀማና ሲዘረፍ የአገዛዙ ሹማምንትና ሆድ አደር ባለሃብቶች ለቀጣይ ሦስትና አራት ትውልድ የሚተርፍን የአገር ሀብት በየአቅጣጫው እየዘረፉና እየተቀራመቱ አገሪቱን በድቅድቁ አጨልመዋታል።
ታሪክ እንደሚዘክረው ቀደምት አባቶቻችን ጣሊያን አገራችንን ሊነጥቅና በባርነት ሊገዛን በዘመናዊ ጦር ሲወረን አገር የለንም ብለው አልተሰደዱም፡፡ የሕይወት መስዋዕትነትን ከፍለውና የጠላትን ጦር ድባቅ በመምታት አንበርክከው ኢትዮጵያን የራሳቸው አደርገው ለኛ አስረክበውን አልፈዋል፡፡ ዛሬ ግን በመካከላችን የወጡ ዘረቢስ ፋሽስቶች አገር እንደሌላው ባይተዋር ወይም አንደ ፀጉረ ልውጥ ቆጠረውን ሲሳለቁብንና ሲያጎሳቁሉን ዝም ብለን የመመልከታችን ነገር ሁሌም ለእኔ እንቅልሽ ነው። ወገን ምንድን ነው ዝምታው! ከአባቶቻችን የወረስነው እኮ ባርነትን አይደለም ይልቁኑ ጀግንነትን አልገዛም ባይነትን እንጂ። ስለዚህ ዛሬ ዘረ ቢስ የሕወሓት ፋሽስቶቹን እምቢኝ አሻፈረኝ ብለን በፅናት ልንታገላቸው መነሳት በሁላችንም ጫንቃ ላይ የወደቀ ግዴታ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡

በነገራችን ላይ የሕወሓት ነፍሰ ገዳይ ሹማምንት ፈጣሪን እየተገዳደሩ ኢትዮጵያን በእጃቸው በመጠፍጠፍ ሰርተው በገፀ በረከትነት የሰጡን ይመስል ነጋ ጠባ ለጆሮ የሚገለማ ዲስኩራቸውንና ውሸታቸውን እያንቧረቁ አደንቁረው ለመግዛት ሌት ተቀን የሚዶሉቱትን ሴራ በቃ በማለት ነቅተን ማክሸፍም የሁላችንም ግዴት መሆን ይገባዋል እላለሁ። ጆሮ ሰጥተን ልንሰማቸው ፈጽሞ አይገባም። ሕወሓቶች የሥልጣን ኮርቻው ላይ ጉብ ባሉ ማግስት በዘር በመገነጣጠል የከፋፈሉን፤ ከጐንደርና ከጋምቤላ ለም መሬቶችን ቆርሰው ለሱዳን በገፀ በረከትነት የሰጡ፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ድሃ ገበሬዎችን እያፈናቀሉ መሬቶቻቸውን በመንጠቅ ለውጭ አገር ቱጃሮች በማይረባ ገንዘብ የሸጡ፤ የአገር ሃብትን ጨምሮ በእርዳታና በብድር የተገኘ ገንዘብ ዘርፈውና አዘርፈው ከአገር ያስወጡ የጥፋት መልእክተኞች ናቸው።
ስለዚህ በመጨረሻ በድጋሚ አትኩሮት ሰጥቸ ማስተላልፈው የምፈልገው መልዕክት ቢኖር ሕወሓት ያፈረሳትን አገር፤ ሕወሓት የዘረፈውን የአገርና የሕዝብ ሐብት፤ ሕወሓት የበተነውን ሕዘብ ፤ ሕወሓት ያረከሳቸውን ቤተ እምነቶች፤ ሕወሓት ያነገሰውን ሕግ አልባነት ግድያ አፈና ሺብር ስደትና የግዞት ስርዓት ለማስወገድ መተኪያ የሌላትን ውድ ሕይወታቸውን በመገበር በዚህ ወቅት በየትኛውም የፍልሚያ ጎራ ተሰልፈው የሕወሓትን እብሪት ለማስተንፈስና ለኢትዮጵያዊያን ነፃነት፤ አንድነት፤ ለጋራ እድገት፤ ፍቅርና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ነፃነት ያለመስዋእትነት አይገኝምና የታሪክና የትውልድ አደራቸውን አንግበው ከሕዝባቸው ጎን ሆነው ግዳጃቸውን በመወጣት ላይ ከሚገኙት ከአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ እንዲሁም ከሌሎች የአንድነት ሃይሎች ጎን በመሰለፍ የተጀመረውን እልህ አስጨራሽ የአገር አድን ትግል ከዳር ለማድረስ መረባረብ ያለብን ሰአት አሁን ስል አጥብቂየ ወገናዊ ጥሪየን አቀርባለሁ። ይንን የተቀደሰ አገርና ሕዝብን የማዳን ተግባር ለዲሰፖራው ወገን እግዚአብሔር ቅን ልቦና ስጥቶት በአንድነት የነፃነት ሃይሎችን እንዲቀላቀል ጥሪየን እያቀረብኩ ፈፃሚው እሱ ነውና ለሐያሉ ጌታም የነፃነታችንንና የትንሳኤያችንን ቀን እንዲያቀርብልን ልመናየን በማቅረብ ፅሁፌን እቋጫለሁ።
ድል ለጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ!
No comments:
Post a Comment