ዘ-ሐበሻ) የሕወሓት መንግስት በኤርትራ በማይ እዳጋ የሚገኘው የሚሻዕ ወርቅ ማዕድን ካምፓኒ ላይ የአየር ጥቃት አደረስኩ ብሎ ከገለጸ በኋላ የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ምንም አይነት ጥቃት እንደደረሰበት የገለጸው ነገር አልነበረም:: አስመራ የሚገኙ የዘ-ሐበሻ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ በማይ እደጋ እንኳን የአየር ድብደባ ይቅርና ሞቅ ያለ ጭብጨባም አልተሰማም::
በኤርትራ ይህን የወርቅ ማዕድን የሚያወጣው የካናዳው የማዕድን አውጪ ድርጅት ማምሻውን በድረገጹ ባወጣው መግለጫ የአየር ጥቃት እንደደረሰበት አልገለጸም:: ድርጅቱ ማርች 13 ቀን 2015 ልክ በማንኛውም መስሪያ ቤት እንደሚደርስ አደጋ መጠነኛ መሰባበር የደረሰበት ቢሆንም ጥገና አድርጎ ወደ ስራ እንደሚመለስ ገልጿል:: ይህ ጉዳት የደረሰበት የሕወሓት መንግስት እንደሚለው በአየር ጥቃት እንደሆነ ካምፓኒው ያስቀመጠው ነገር የለም::
የሕወሃት መንግስት ለምን ይህ ዜናን ማሰማት ፈለገ? የሚለውን ዘ-ሐበሻ ወደ አስመራ ምንጮቿ ጋር ደውላ የነበረ ሲሆን ምንጮቹም “የሕወሓት መንግስት ይህን ዜና ማሰራጨት የፈለገው ከፍራቻ የተነሳ ነው:: በዚህ በሚሻዕ የወርቅ ማዕድን ማውጫ በማንኛውም ድርጅት ውስጥ እንደሚፈጠር መጠነኛ የማሽኖች መሰባበር አደጋ መፈጠሩን የወያኔ ደህነንቶች መረጃ አላቸው:: የዚህ ድርጅት አካባቢ ደግሞ የኢትዮጵያ ነፃነት ታጋዮች የሚገኙበት ወታደራዊ ካምፖች አሉ:: አደጋው ከደረሰ ከአንድ ሳምንት በኋላ የሕወሓት መንግስት በኤርትራ ላይ የአየር ጥቃት እንደፈጸመ ማውራቱ ከገባበት ውጥረት የሕዝቡን አመለካከት ለመቀየር ነው” ብለዋል::
በተለይም በጎንደር አካባቢ በሕወሓት ወታደሮች እና በጎንደር ሕዝብ መካከል በተፈጠረው ውጥረት በዛሬው ዕለት 4 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎና ሰሞኑንም ሕዝቡ ጠመንጃ እየያዘ ጫካ እየገባ በመሆኑ ይህን ለማስቀየስ የሕወሓት መንግስት የቀየሰው የፕሮፓጋንዳ ስልት ነው ሲሉ እነዚሁ ወታደራዊ ምንጮች ለዘ-ሐበሻ ገልጸዋል::
No comments:
Post a Comment