ሚያዝያ ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን አሰቃቂ አደጋ ተከትሎ ለተቃውሞ የወጡ ኢትዮጵያውያን በፌደራል ፖሊሶች ተደብድበው እንዲታሰሩ በተደረገ ማግስት፣ የኢህአዴግ የጸጥታ ሃይሎች በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለከተሞች የሚገኙ ወጣቶችን በምሽት በማፈን ወደ እስር ቤት እያጋዙ ነው።
የከተማዋ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ባለፉት ሶስት ቀናት ብቻ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጭ ተወስደው ታስረዋል መጪውን ምርጫ ተከትሎ ገዢው ፓርቲ ረብሻ ይነሳል በሚል ፍርሃት ወጣቶችን እያፈነ በማጋዝ ላይ መሆኑን ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ሰዎች ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በወንጅ ወረዳ የገዢው ፓርቲ ኳድሬዎች እናቶችን ብቻ በመሰብሰብ ልጆቻችሁን ምከሩ በማለት እያስፈራሩ መሆናቸው ተመልክቷል።
ባለፈው ረቡዕ በነበረው ተቃውሞ ላይ ተይዘው የተፈቱት ወጣቶች ለኢሳት እንደተናገሩት፣ በተያዙበት እለት ምግብና ውሃ ከመከልከላቸውም በላይ ይደበደቡ ነበር ። ወጣቶቹ ሲለቀቊ አሻራቸውን መስጠታቸውንና ከአሁን በሁዋላ በየትኛውም መንገድ ተቃውሞ ቢያደርጉ
የከፋ ጉዳት እንደሚደርስባቸው ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአንድነት ፓርቲ አባል እና የሚሊየኖች ድምፅ አምደኛ የነበረው እስማኤል ዳውድ መታሰሩ ተዘግቧል።
ወላጅ እናቱ እንደተናገሩት ትላንት ከጠዋቱ ሁለት ሰአት ላይ ሲቪል የለበሱ ሰዎች ወደመኖሪያ ቤት መጥተው እስማኤልን ወስደው አስረውታል።
ሰዎቹ ሲወስዱት፦ ‹‹ፖሊስ ጣቢያ ቃል ሰጥተህ ትመለሰላህ›› ቢሉትም፤ አራዳ ፖሊስ ጣቢያ ቃሉን ከሰጠ በሁዋላ ግን እንደማይለቀቅ አስታውቀውት ወደ ወረዳ 9 ፖሊስ ጣቢያ መወሰዱን ወላጅ እናቱ ገልፀዋል።
በትላንትናው እለትም ከአራዳ ፖሊስ ጣቢያ ስልክ ተደውሎላቸው፤ ልጃቸው እስማኤል ችሎት መድሃኒያለም አካባቢ ወደሚገኘው ወረዳ 9 ፖሊስ ጣቢያ መዛወሩ እንደተገለፀላቸውም ተናግረዋል።
እስማኤል፣ ዛሬ ሚያዚያ 21 ቀን 2007 ዓመተ ምህረት ከረፋዱ 5፡30 ላይ ፒያሳ በሚገኘው አራዳ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን፤ በችሎቱ የተሰየሙት ሴት ዳኛ ‹‹በአራት ቀን ውስጥ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ ለክስ የሚያበቃ በቂ ማስረጃ ካለው ፍርድቤት እንዲያቀርበው፤ አለበለዚያ ግን በነጻ እንዲያሰናብተው›› ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
ልጃቸው በምን ምክንያት እንደታሰረ ያውቁ እንደሆነ የተጠየቁት ወላጅ እናቱ ፦በረቡዕ ሰልፍ ላይ በመገኘቱ ምክንያት እንደሆነ በመጥቀስ፤ ከእሱም ሌላ ሁለት ጓደኞቹ ለእስር መዳረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
ከስልፉ ጋር በተያያዘ ሰማያዊ ፓርቲ ስድስት አባሎቹ እንደታሰሩ ያስታወቀ ሲሆን፤ በ አቶ በላይ ፍቃዱ ይመራ ከነበረው ከቀድሞው አንድነት ፓርቲ ውስጥ ደግሞ ለእስር የተዳረጉት ቁጥራቸው ሶስት ደርሷል፡፡
እነሱም፦እስማኤል ዳውድ፣ ስንታየሁ ቸኮልና የፓርቲው የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ዳዊት አስራደ ናቸው። በአገር ውስጥ ያለው ውጥረት እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት፣ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በሊቢያ፣ ሳውድ አረቢያና የመን ዜጎች ላይ የደረሰውን ግፍ ማውገዛቸውን ቀጥለዋል።
በቤልጂየም ብራሰልስ ኢትዮጵያውያን ዛሬ በአውሮፓ ህብረት ጽ/ቤት ፊት ለፊት ተገኝተው ሀዘናቸውንና ቁጣቸውን ገልጸዋል። በቶሮንቶ አካባቢ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም የሻማ ማብራትና የጸሎት ምሽትት በማድረግ ብዙ ሕዝብ በተገኘበት ከፍተኛ ሃዘናቸውን
ገልሰዋል፡፡ በስነስርአቱ ላይ የተለያዩ እምነት ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በተገኙበት በዚህ የሃዘን ቀን ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘው በጋራ እንዲነሱ ጥያቄ ቀርቧል።
በኒዮርክም እንዲሁ የሻማ ማብራትና የጸሎት ስነስርአት ተካሂዷል።
No comments:
Post a Comment