Wednesday, February 12, 2014

የዩጋንዳ ጦር ደቡብ ሱዳንን ለቆ እንዲወጣ አቶ ሃይለማርያም አስጠነቀቁ

የካቲት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጠ/ሚ/ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የዩጋንዳ ጦር በሂደት ለቆ ካልወጣ አካባቢው የጦርነት ቀጠና ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ሁሉም ሃይሎች የራሳቸው የሆነ ፍላጎት አላቸው ያሉት አቶ ሃይለማርያም፣ በደቡብ ሱዳን ሰላም ይመጣ ዘንድ የዩጋንዳ ጦር ጁባን ለቆ መውጣት አለበት ሲሉ አሳስበዋል ።
አቶ ሃይለማርያም የገለጹት አቋም የደቡብ ሱዳንን መንግስት የሚያስከፋ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ግን ለተቀዋሚዎች መልካም ዜና ነውተብሏል። የሳልቫኪር መንግስት፣” ሰላማችንን ለማስጠበቅ  የፈለግነውን ሃይል የመጋበዝ መብት አለን” የሚል አቋም ይዟል።
ዩጋንዳ ለአቶ ሃይለማርያም ማስጠንቀቂያ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም። የዩጋንዳ መንግስት በአቋሙ ከጸና ኢትዮጵያን የመሳሰሉ የደቡብ ሱዳን ጎረቤት አገሮች የሚወስዱት አቋም ግልጽ አይደለም።
የዩጋንዳ ጦር ፕሬዚዳንት ሳለቫኪር በተቃዋሚዎች ላይ ድል እንዲያገኙ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ተጠልፈው የተወሰዱት ሁለቱ የኦጋዴን ነጻ አውጭ ባለስልጣናት በአንድ ወታደራዊ ሆስፒታል ውስጥ ሲታከሙ መታየታቸውን ግንባሩ ገለጸ

የካቲት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ግንባሩ ለኢሳት በላከው መረጃ ፣ ከኢህአዴግ መንግስት ጋር ድርድር ለማድረግ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ተገኝተው  በኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች ታፍነው የተወሰዱት የኦብነግ አመራሮች፣ የደረሰባቸውን ከፍተኛ ድብደባ ተከትሎ በአንድ ወታደራዊ ሆስፒታል ውስጥ ሲታከሙ ታይተዋል። የመንግስት የደህንነት ሰራተኞች ” ባለስልጣኖቹ በገዛ ፈቃዳቸው እጃቸውን እንደሰጡ ለማሳመን ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት ባለመሳካቱ  አሰቃቂ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው” ግንባሩ አክሎ ገልጿል።
ገዢው ፓርቲ ከዚህ ቀደም አንዳንድ ሰዎችን በሃይል ወይም ገንዘብ በመስጠትና በማማለል ሰላም ስምምነት እንዲፈርሙ ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሰው መግለጫው፣ በሁለቱ ባለስልጣኖች ላይ የደረሰውም ከዚህ የተለየ አለመሆኑን አትቷል።
ግንባሩ የኬንያ መንግስት፣የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት የኢህአዴግ መንግስት የሰዎቹን ደህንነት ጠብቆ እንዲለቃቸው ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቋል።

አንድ የአየር ሃይል ባልደረባ የአርበኞች ግንባርን ተቀላቀለ

የካቲት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የደብረዘይት አየር ኃይል አባል የነበረው ምክትል መቶ አለቃ ዳንኤል የሽዋስ የኢህአዴግን ስርአት በመቃወም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊትን መቀላለቀሉን ግንባሩ ለኢሳት በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ም/መ/አለቃ ዳንኤል የሽዋስ የ L-39  ስኳድሮን ተዋጊ ጀት አብራሪ እንደነበር መረጃው ያመለክታል።
ም/መ/አ ዳንኤል የሽዋስ “ተቃዋሚዎችን ትደግፋለህ ከእነሱም ጋር የጠበቀ ግኑኝነት አለህ በሚል ምክንያት ተጠርጥሮ ያለምንም ወንጀል ለአምስት ወር ያህል ታስሮ እንደነበርና ከእስር እንደተለቀቀም በደህንነት አባሎች አማካኝነት በአይነ ቁራኛ ክትትል ሲደረግበት ቆይቶ ፣ እንደገና ለ23 ቀናት በደብረዘይት እስር ቤት መታሰሩን፣ገልጿል፡፡ የአየር ሃይል ባልደረባው በዚህ መሃል ከእስር ቤት አምልጦ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊትን መቀላቀሉን” የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የአየር ሃይሉ ባልደረባ መኮብለሉን በተለመለከተ መንግስት የሰጠው መግለጫ የለም።
ግንባሩ በላከው ሌላ ዜና ደግሞ  በሁመራ አካባቢ  የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ደጋፊዎች ናችሁ በማለት ታስረው በነበሩ 10 ሰዎች ላይ ከ6 ዓመት እስከ 25 ዓመት እንደተፈረደባቸውና  ወደ መቀሌና ሽሬ እስር ቤት እንደተወሰዱ ገልጿል።
አርበኞች ግንባር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ወታደራዊ ጥቃቶችን በመፈጸም ላይ ይገኛል።

በ500 ብር ደሞዝ የሚተዳደረው የህወሃት ታጋይ ከ10 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ሃብት ማካበቱ ተገለጠ

የካቲት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የደህንነት ሃላፊ ከነበሩት ከአቶ ወልደስላሴ ወልደ ሚካኤል  ጋር በግብረ-አበርነት የተከሰሱት የህወሃት ታጋዮች ከደሞዛቸው ጋር ፈጽሞ የማይመጣጠን ሃብት አግበሰው መገኘታቸው ታውቋል።
በተለያዩ አለመግባባቶች የተነሳ እየተመሰረቱ ያሉ ክሶች የህወሃት ተጋዮች በህገወጥ መንገድ የሰበሰቡትን የሃብት መጠን ለማወቅ እየረዳ መሆኑን የገለጸው ዘጋቢያችን ከአቶ ወልደስላሴ ጋር በግብረ አበርነት የተከሰሱት የህወሃት ታጋዩ የአቶ ወልደስላሴ ወንድም አቶ ዘርአይ ወልደስላሴ የመከላከያ ሚኒስቴርን ሲለቁ በመጨረሻ ይከፈላቸው የነበረው ወርሃዊ ደሞዝ 532 ብር ብቻ እንደነበር አመልክቷል ፡፡  ይሁንና፣ ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ባደረገው ማጣራት ግለሰቡ በተለያዩ ባንኮች በስማቸው 5 ሚሊዮን ብር ከማስቀመጣቸውም በተጨማሪ፣ አዲስ አበባ ቤቴል ሆስፒታል አካባቢ በ74 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ግንባታ እያካሄዱ ፣ በአፋር ክልል ደግሞ ከ1 ሚሊዮን 400 መቶ ሽ ብር በላይ በሆነ ወጪ የእርሻ ኢንቨስትምንት እያከናወኑ መሆናቸው እንዲሁም  በስማቸው 2 ሚሊዮን 700 ሺ ብር ግምት ያላቸው 2 ሎደር መኪኖች መገኘታቸውን ገልጽዋል።
የአቶ ወልደስላሴ እህት የሆኑት ወ/ሮ ትርሃስ ደግሞ የ8ኛ ክፍል ተማሪና ምንም ስራ ያልበራቸው ሲሆን፣ በወንድሞቻቸው ድጋፍ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዛ አንድ ስካቫተር፣መኪና እንዲሁም   በአዲስ አበባ በየካና ቦሌ ክፍለ ከተሞች፣ በለገጣፎ፣ መቀሌና አክሱም 3 ሺ 266 ካሬ ሜትር ቦታዎች በስማቸው መገኘቱ ተመልክታል ፣እንዲሁም  በተለያዩ ባንኮችም 8 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ ማድረጋቸውን  አንድ ተጨማሪ ዘመናዊ መኪና በስማቸው ተመዝግቦ መገኘቱን ጸረ ሙስና ኮሚሽን በምርመራ አረጋግጧል።
ዋናው ባለስልጣን አቶ ወልደስላሴ ደግሞ ስራ ሲጀምሩ ደሞዛቸው 1600 ብር የነበረ እና በእድገት እስከ 6000 ሺ ብር ሲከፈላቸው የቆየ ቢሆንም ያካባቱት ሀብት ግን ፈጽሞ ከደሞዛቸው ጋር የማይመጣጠን ነው ተብሏል። ባለ 4 ፎቅ ህንጻ ባለቤት የሆኑት አቶ ወልደስላሴ በ1 አመት ከ2 ወራት ቤቱን አከራይተው 790 ሺ ብር ገቢ አግኝተዋል።
አቃቢ ህግ ያቀረበውን ክስ የእስረኞች ጠበቆች፣ አዲስ የተጨመረ ክስ ነው በማለት አቤቱታ አቅርበዋል።
አቶ ወልደስላሴ ከወ/ሮ አዜብ ጋር በነበራቸው መቀራረብ ከፍተኛ ሃብት ማፍራታቸውን ፤ አቶ መለስ ዜናዊ ከሞቱ በሁዋላ ግን የእርሳቸው ዋነኛ ተቀናቃኝ የሆኑት የደህንነቱ ዋና አዛዥ አቶ ጌታቸው አሰፋ ግለሰቡን በሙስና ከሰው እንዳሳሰሩዋቸው አንዳንድ የመገናኛ ብዙሀን ገልጸው ሲዘግቡ ቆይተዋል።
ህወሃቶች እርስ በርስ በሚያደርጉት ሽኩቻ እየተካሰሱ ፍርድ ቤት መቅረባቸው የካበቱትን ሃብት ለማወቅ እየረዳ ነው የሚለው ዘጋቢያችን፣ በጸረ ሙስና ኮሚሽን ያልተመረመረና በፍርድ ቤት ቀርቦ ያልታወቀ ከዚህም የባሰ የሙስና ታሪክ እንደሚኖር መገመት ይቻላል ሲል አስተያየቱን አስፍሯል።

Thursday, January 30, 2014

የኢትዮጵያ መንግስት የግንቦት7 መሪዎችን ኮምፒዩተሮች በዘመናዊ የስለላ መሳሪያዎች ሲሰልል እንደተደረሰበት አንድ አለማቀፍ ተቋም አጋለጠ

ጥር ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የህዝቦችን ደህንነት ከመንግስታት ጥቃት ለመከላከል የተቋቋመው ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል የተባለው  ተቋም ለእንግሊዝ መንግስት የገቢዎቸና ጉምሩክ መስሪያ ቤት በጻፈው ደብዳቤ “ጋማ ኢንተርናሽናል የተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ በአለም ላይ የሰብአዊ መብቶችን በመጣስ ለሚታወቁ አገሮች ኮምፒይተሮችን፣ የሞባይልና የስካይፕ የስልክ ግንኙነቶችን እንዲሁም የኢሜል ልውውጦችን በርቀት ሆኖ ለመከታተል የሚያስችለውን ፊን ፊሸር ወይም ፊን ስፓይ በሚል ስም የሚጠራውን የመሰለያ መሳሪያ ከአውሮፓ ህብረት ውጭ ላሉ አገሮች በመሸጥ ዜጎች እንዲሰለሉና ደህንነታቸው አደጋ ላይ እንዲወድቅ በማድረጉ  ምርመራ እንዲጀመር” ሲል ጠይቋል።
የግንቦት7 ከፍተኛ አመራር በሆኑት በ ዶ/ር ታደሰ ብሩ የግል ኮምፒዩተር ላይ የመሰለያ ቫይረሱ መገኘቱን በቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ የሙንክ ስኩል ግሎባል አፌርስ የምርምር ተቋም የሆነው ሲትዝን ላብ ማረጋገጡን ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል በደብዳቤው ገልጿል።
የመሰለያ መሳሪያው የሰብአዊ መብቶችን በሚጥሱ 36 አገራት ላይ መሸጡን የገለጸው ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል፣ በተለይም በቬትናም፣ ማሌዚያና ኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ለመሰለያነት እየዋለ ነው ብሎአል።
በኢትዮጵያ የግንቦት7 ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዶ/ር ታደሰ ብሩ ኮምፒተራቸው ሲሰለል መቆየቱን የገለጸው ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል፣ በአንድ የብሃሬን የሰብአዊ መብት ተማጓች ኮምፒዩተር ላይም ተመሳሳይ የስለላ ሶፍት ዌር መገኘቱን ገልጿል።
ዶ/ር ታደሰ ብሩ ለፕራይቪሴ ኢንተርናሽናል ጠበቃ የምስክርነት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተናግረዋል። ፕራይቪሲ ኢንተርናሽናል የስለላ ቫይረሱን የሸጠውን ጋማ ኢንተርናሽናልን የተባለውን ድርጅት ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ማቀዱን ዶ/ር ታደሰ ገልጸዋል፡
ከዶ/ር ታደሰ ጋር የተደረገው ቃለምልልስ ከዜናው በሁዋላ ይቀርባል።

Thursday, January 16, 2014

በሶማሊያ ክልል 47 ሰዎች መገደላቸውን የአገር ሽማግሌዎች ለአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በላኩት ደብዳቤ ገለጹ

ጥር ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቀላፎ አካባቢ የሚኖሩ የየረር ባሬ ጎሳ  የአገር ሽማግሌዎች ለጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ያስገቡትና መረጃው ለኢሳት እንዲደርስ በሚል በላኩት መረጃ ፣ የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሀመድ ኡመር እና ጄኔራል አብርሀም በቅጽል ስማቸው ኳታር የሚመራው ልዩ ሚሊሺያ እየተባለ የሚጠራው ሀይል ታህሳስ 1 እና 2 በከፈተው ተኩስ በትምህርት ላይ የነበሩ ህጻናትንና ወጣቶችን ጨምሮ 47 ሰዎችን መግደሉን የሟቾቹን ስም ዝርዝር በመጥቀስ ገልጸዋል።
ልዩ ሚሊሺያው ተማሪዎች በትምህርት ላይ እንዳሉ ተኩስ መክፈቱን የአገር ሽማግሌዎቹ በደብዳቤያቸው ላይ የገለጹ ሲሆን፣ የፌደራሉ መንግስት በአስቸኳይ ደርሶ እንዲታደጋቸውም ጠይቀዋል።
የየረር ባሬ ጎሳ አባላት የክልሉ መንግስት ጭቆና ያደርስብናል በማለት ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር ሲጠይቁና በተደጋጋሚ እርምጃ ሲወሰድባቸው እንደነበር አውስተው ፣ በቅርቡ የተወሰደው አስከፊ እርምጃ ግን በደቡብ አፍሪካ እንሰማው የነበረ እንጅ በአገራችን ላይ የሚፈጸም ነው ብሎ ለማመን ይቸግራል ብለዋል።
ባከፍ ድር እየተባለ በሚጠራው ትምህርት ቤት ላይ እና በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ በተከፈተው ተኩስ  ኡመር ሀጂ ሙሀመድ፣ ሙኒየር አዳቢ ሙሀመድ፣ ካሊድ ሙሀመድ አብዲ፣ ሀሰን አሊ ቤላህ፣ ወ/ሮ ሀሺ ሃጅ መሀመድ፣ ማዴቦ ሞሀመድ አብዲ፣ ሀጂ ኑሩ  ሙሀመድ፣ ማዴባ ሞሀመድ አብዲ፣ መሀለም ካልየ ደውሀሊ፣ አብረሳ አደም ሞሀመድ፣ ሀጂ ኑሩ ሙሀመድ፣ ሞርየ ሞሀመድ ካር፣ ጋለው አብዲ የኑስ፣ የሱፍ ረምሳ አደም፣ ካሊባን ሳራህ ኡመርነህ፣ ኡስማን  አብደሌ፣ ጠኒ ሙሀመድ ጣር፣ መንሲን ሙሀመድ ጣር፣ ደልግ አሊ ኡመር፣ ካሊድ ሙሀመድ አብደሌ፣ ሀሰን ማሌ አብዱላሂ፣ የሱፍ የሄ፣ ጀማል ኡመር ጠባህ፣ ሙሀመድ ኡስማን ጦለቤ፣ አህመድ መሀመድ፣ አሊ ቀሲም ቀለኔ፣ ባቡል ዳሩር፣ ከሬ ባዴ፣ ማን ኦረየ ባዴ፣ ጦርየ አዊ ባዴ፣ አብዲ ሸክለሌ፣ አሊ ኡስማን ቀለሌ፣ ሊሞ አሌባዴ፣ ማዲህ አብዱልኑር፣ ዙቅ ኡር እና የሌሎች የ12 ተጨማሪ ሟቾች ስም ዝርዝር ቀርቧል።
በአካባቢው የተነሳው ውጥረቱን ተከትሎ በትናንትናው አለት ደግሞ ተጨማሪ ሀይል ወደ አካባቢው መጓዙን ሽማግሌዎች ገልጸዋል።
ክልሉን ከጀርባ ሆነው የሚያንቀሳቅሱት ጄኔራል አብርሀ በክልሉ ለሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ መሆናቸውን የአካባቢው ሰዎች ይገልጻሉ።
መረጃው እንደተላከልን የክልሉን ፕሬዚዳንት ለማነጋገር በተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም። ጠ/ሚንስትሩ ለተጻፈላቸው ደብዳቤ እስካሁን መልስ አለመስጠታቸውን ሽማግሌዎቹ ገልጸዋል።
የሶማሊ ክልል በቅርቡ የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን ማክበሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያን ታሪክ ጥላሸት የመቀባት አባዜ (ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም)

January 16, 2014
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ጥር 7 ቀን 2006 ዓ.ም

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው ገዥው አካል በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ንጉስ የነበሩት የዳግማዊ አጼ ምኒልክ መቶኛ የሙት ዓመት በዚህ በያዝነው ዓመት (በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር) እየተከበረ ባለበት ወቅት ሙሉ ጊዜውን በመስጠት ንጉሱ የሰሩትን ታላቅ ስራ ሁሉ በማጣጣል እና ጥላሸት በመቀባት ዘመቻ ላይ በመጠመድ ታሪክ የማጠልሸት ድራማውን በመተወን ላይ ይገኛል፡፡ የታሪክ ማጠልሸት ዘመቻው በዋናነት እየተከናወነ ያለው ለገዥው አካል ቅርበት ባላቸው ታማኝ ሎሌዎች፣ የጥቅም ተጋሪዎች እና የእራሳቸው ስብዕና በሌላቸው አሻንጉሊቶች አማካይነት ነው፡፡ ገዥው አካል ሲያስነጥሰው መሃረብ ይዘው በሚቀርቡ አጎብዳጆቹ አማካይነት የጥላቻ መርዛማ ቃላትን፣ የሚቆጠቁጡ ባዶ ዲስኮሮችን እና እርባናየለሽ ምዕናባዊ ስዕል በአዕምሮው ላይ እየፈጠረ አጼ ምኒልክ የግዛት ማስፋፋት ጥማታቸውን ለማርካት ሲሉ በዜጎች ላይ የጭካኔ ተግባራትን እንደፈጸሙ በማስመሰል ለምንም የማይጠቅሙ እርባናየለሽ እና ተራ አሉባልታዎችን በማሰራጨት ላይ ይገኛል፡፡

የገዥው አካል ድንጉላ አገልጋዮች በማናቸውም የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በመሰማራት ታሪካዊ ቅጥፈቶችን፣ አሳሳች ዘገባዎችን፣ የሀሰት ታሪክ ፈጠራዎችን፣ ሆን ተብሎ በሀሰት ላይ የተመሰረቱ መረጃዎችን እና ነጭ ውሸቶችን እንደ በቀቀን እየደጋገሙ በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡ የዕኩይ ዓላማው አራማጆች በታላቁ የኢትዮጵያ መሪ ላይ ግነታዊ ኩምክና በመስራት፣ በማዋረድ እና እውነተኛውን ስብዕናቸውን ጥላሸት በመቀባት የስሜት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ውስጥ በመዘፈቅ ጌቶቻቸውን ለማስደሰት በታለመ ዕኩይ ምግባር ላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ የታላቁ መሪ ነብስ ከስጋቸው ከተለየች ከአንድ መቶ ዓመታት የጊዜ ቆይታ በኋላ የተቀበረን ጉዳይ በማንሳት ታላቁን መሪ ሰይጣናዊ ስብዕና እንደነበራቸው ለማስመሰል በማሰብ የዕኩይ ምግባር ጎተራዎቹ የቻሉትን ያህል ጥረት ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት ከተለዩ ሁለት ዓመታት እንኳን ሳይሞላቸው የዕኩይ ምግባራት ቋቶቹ የኢትዮጵያ አዳኝ መልዓክ ሊያደርጓቸው ይፈልጋሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ላይ በተከፈተው የገፍ ወይም የኃይል የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ወይም ደግሞ የአጼ ምኒልክን የሙት መንፈስ ደጋግመው በማንሳት ፍጹም ጥላቻ እና የጥላቻ አመለካከት እንዲንሰራፋ በገዥው አካል ስልታዊ እና የተቀነባበረ ዘመቻ የማካሄድ አመክንዮ ለማንም ቢሆን ሊደንቅ አይገባም፡፡ ሀቁ አንድ እና አንድ ብቻ ነው፡፡ የኸውም የምኒልክን ስም ጥላሸት በመቀባት (ሰይጣናዊ ስብዕና በመስጠት) በሚሽከረከር ጉዳይ ላይ ብቻ የሚቆም ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን በቅርቡ በህይወት የተለዩትን የገዥውን አካል የአለቆች ሁሉ አለቃ (Capo di tutti capi) አቶ መለስ ዜናዊን በመላዕክነት ቀብቶ ለማቅረብ የታቀደ ዕኩይ ምግባር ነው፡፡