November 16, 2013
አስቸኳይ መግለጫ
በቅርቡ፤ በተከታታይና በሚዘገንን ደረጃ በሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚካሄደውን እልቂት ለማስቆም ብሄራዊ ግብረ ኃይል እአ በ November 12, 2013 በተደረገ አስቸኳይ ስብሰባ ተመሰርቷል።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሰብአዊ መብቶች፤ ለሰዎች ክብርና የህይወት ክቡርነት የቆሙ ሁሉ የሳውዺ የጦር፤ የፖሊስ፤ የጥበቃና ሌሎች በመንግሥት የተደራጁ ወጣት ቡድኖች በሰላማዊ ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚያደርጉት ግድያ፤ አስገድዶ መደፈር፤ ግለሰቦችን በገመድ አንቆ ዛፍ ላይ መስቀል፤ ገረፋ፤ በሓያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሰለጠነ መንግሥት በማይጠበቅ ደረጃ ግለሰቦችኝ እንደ እንሰሳ አስሮ በመንገድ መጎተት ወዘተ ለህሊና የሚቀፍ ድርጊት። እኛም በንፁሕ ኢትዮጵያዊያን ላይ መፈፀሙ አስቆጥቶናል፤ አሳዝኖላን፤ አበሳጭቶናል፤ ቀስቅሶናል፤ ለወገኖቻችን መብት እንድንነሳና ከሚመለከታቸው ጋር አብረን ድምጻችንን እንድናሰማ አስገድዶናል። በመጀመሪያ ደረጃ የምንጠይቀው፤ የሳውዲ መንግሥት ሃላፊነቱን በመወጣት ይህ አሰቃቂ እልቂት እንዲቆም ማድረግ ነው። ከዚህ ጋር አብረን የምናሳስበው ለሰብእነትና ለሰው ክብር የቆመው የዓለም ህብረተሰብ ሁሉ ይህን አሰቃቂ ድርጊት ተቀዳሚነት በመስጠት እንዲቆም ማድረግ የሞራል ሃላፊነት አለበት የሚል ነው። የኢትዮጵያዊያን ህይወት እንደ ማንኛውም ሰባዊ ፍጡር ትልቅ ዋጋ ያለው መሆኑን እናሳስባለን።
ይህን የተቀደሰ ዓላማ ስኬታማ ለማድረግ የሚከተሉትን ለሰብአዊ መብት፤ ለሰው ክብርና ነጻነት፤ ለእውነተኛ እኩልነት የቆሙ ሶስት ግለሰቦች በአሰባሳቢነት መርጠናል፤
1. አቶ አበበ ገላው
2. አቶ ብርሃኑ ዳምጤ (አባ መላ) እና
3. አቶ ታማኝ በየነ።
ኢትዮጱያዊያን፤ በተለይ ወጣት ወንዶችና ሴቶች በሳውዲ አረቢያና በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች በገፍ የሚሰደዱበትና በሰላም ሰርተው ለመኖር የሚፈልጉበት ምክንያት በአገራቸው የስራ፤ በሰላም የመኖር፤ የራሳቸውን ስራ የመፍጠር፤ መብታቸውን የማስከበር እድል ስለሌላቸው ነው። ስለሆነም፤ የሳውዲ አረብያ የጥበቃ፤ ፖሊስና ወጣት አፋኝ ቡድኖች በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደርጉት ግድያ፤ አፈናና ማሳደድ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ፤ ለህሊና የሚቀፍ፤ በተባበሩት መንግሥታት ውሎች የተከለከለ፤ የሰለጠነው ዓለም የማይቀበለው በሰብእነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነው። ይህን አሰቃቂ ድርጊት የአይን ምስክሮች፤ የቢቢሲ፤ የአልጀዚራና የግል ታዛቢዎች በቪዲዮ ቀርፀው ለዓለም ሕዝብ አሰራጭተውታል። ከዚህ የበለጠ ምስክር ሊኖር አይችልም። የሳውዲ አረቢያ መንግሥት ሆነ ብሎ የሚያደርገው ህገ ወጥ ድርጊት መሆኑን አንጠራጠርም፤ ስለሆነም፤ ይህን አሰቃቂ ተግባር ማቆም ያለበት የሳውዲ አረቢያ መንግሥት መሆኑን እናሳስባለን።
ከላይ እንዳሳየነው፤ ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ፤ ሲሰደዱ አሰቃቂና ለህሊና የሚዘገንን ግድያ፤ እስራትና ሌላ ኢ-ሰብአዊ ወንጀል የሚፈፀምባቸው ወደው አይደለም። አብዛኛው የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ በአገሩ ህይወቱንና ቤተሰቡን የሚደግፍበት ስራ የለውም፤ የኑሮ ዋስትና የለውም። የሕግ የበላይነት ስለሌለ፤ ከሕግ ውጭ የሆነ አፈና፤ ግድያ፤ እስራት፤ ኢ-ሰብአዊ ቅጣት፤ የውስጥና የውጭ ስደት፤ መባረር ወዘተ እጣው ሆኗል። ስለዚህ ነው ብዙ ሽህ ኢትዮጵያዊያን ብዙ ሽህ ብር ከፍለው ለህይወታቸው አደጋን የሚጋብዝ ጉዞ የሚያደርጉት። አሰቃቂ ሆኖ ያገኘነው፤ ኑሯችንን እናሻሽል ይሆናል ብለው ያደረጉት ተስፋ ወደ ጨለማ መርቶ ለህይወታቸው መጥፊያ፤ ለአካለ ስንኩልነት፤ ለክብራቸው መገፈፊያ ወዘተ ምክንያት መሆኑ ነው። ይህ በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጣ “የባርነት” ሁኔታ መፈጠሩን ያመለክተናል፤ መቆም አለበት የምንለው የእነዚህ ወገኖቻችን መዋረድ የሁላችንም ክብር መገፈፍ መሆኑን ስለምንረዳ ጭምር ነው።
ኢትዮጵያዊያን በያሉበት በመገናኛ ብዙሃን፤ በድህረገጾች፤ በሰላማዊ ሰልፍና በሌሎች መንገዶች የሚያሳዩት ጥረት የሚያኮራ ጅምር ነው። በዚሁ መሰረት የሳውዲ አረቢያ መንግሥት የሚያደርገውን አሰቃቂ ግፍ ለዓለም ህብረተሰብ ለማጋለጥ፤ ወንጀሉን የፈፀሙ ሁሉ በሃላፊነት ለፍትህ ለማቅረብ የሚደረገው ተግባር በተከታታይና አስተማማኝነት ባለው ደረጃ እንዲካሄድ ቆርጠን ተነስተናል። የተቋቋመው ግብረ ኃይል ዋና ሚና በሳውዲ አረቢያ የሚካሄደውን ወንጀል ለሚመለከታቸው የዓለም ህብረተሰብ የሰብአዊ መብቶች፤ የፍትህ ተቋሞች፤ የለጋስ ድርጅቶችና ሃላፊዎች ማሳወቅ፤ ቅስቀሳ ማድረግ፤ የገንዘብና ሌላ ቁሳቁስ ድጋፍ ለወገኖቻችን ለማቅረብ ጥረት ማድራግን ይጨምራል። በዚህም መሰረት፤ ግብረ ኃይሉ፤ እውቅና፤ ተቀባይነትና አስተማማኝ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶችን፤ ሊቆችን፤ ጠበቃዎችን ወዘተ፤ በመቅረብና በመቀስቀስ፤ የሳውዲ መንግሥት በሰብአዊነት ላይ ያደረገውንና የሚያደርገውን ወንጀል (Crimes against humanity)
ለፍትህ ለማቅረብ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። በተጨማሪ፤ በሳውዲ አረቢያ ያለውን ሁኔታ በቀጥታ ለመመራመርና እውነተኛውን ዝርዝር ሁኔታና ስእል ለመገንዘብ አንድ ቡድን ለመላክ አቅዷል።
ይህ የተቀደሰና ሁሉም ኢትዮጵያዊያን፤ የሰው ክብርና መብቶች ደጋፊ የሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዲሁም መንግሥታት በያሉበት የሚጋሩት አስቸኳይ ጥሪ ፋታ አይሰጥም። ግድያው፤ ገረፋው፤ እስራቱ፤ የሴቶች ክብር ድፍረቱ ወዘተ የሁላችንም ስለሆነ ዓለም አቀፍ ጥረት ያስፈልገዋል። ሁላችን ሌሎችን በመቀስቀስ ይህ ግፍ በፍጥነት እንዲቆም በተግባር ማሳየት የሞራል ግዴታችን ነው። ወንጀሉን የፈፀሙት የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣናትና ሌሎች ተሳታፊዎች በሃላፊነት ተጠያቂ መሆን አለባቸው። የሳውዲ መንግሥት ባለስልጣናት የኢትዮጵያዊያንን መብቶች ገፈው፤ ገድለው፤ አዋርደው፤ አሳደው፤ ሰቅለው፤ ክብር ገፈው በኢትዮጵያ ያላቸውን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር እንደማይችሉ ማመን አለባቸው። ይህን ማሳመን መቻል አለብን።
የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ፤ ድፍረትና ሰቆቃ ኢትዮጵያውያንና የዓለም ሕብረተሰብ እንዲያወግዝልን ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርባል። በተጨማሪም፤ በኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ አስከፊና ኢሰብአዊ ድርጊት የፈጸሙት ሁሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ እናሳስባለን። እንዲሁም፤ በመረጃና ተሞክሮ መጋራት፤ ኢትዮጵያውያንን ከሳውዲዎች ሰቆቃና ግድያ ለማትረፍ ስለሚያስፈልገው እርዳታ ሁሉ ኢትዮጵያውያንና ለሰብአዊ መብት የሚታገሉ ድርጅቶች እንዲተባበሩልን ከአደራ ጋር እንጠይቃለን።
ይህን ለማድረግ የምንችለው ለዚህ ዓላማ በያለንበት ስንነሳ፤ አብረን ተባብረን ስንሰራ፤ ለወገኖቻችን መቆማችንን በተግባር ስናሳይ፤ ዜና፤ ሃሳብ፤ እውቀት፤ ልምድ፤ ስንለዋወጥ፤ የገንዘብ ሆነ ሌላ አስተዋፅኦ ስናደርግ ነው። ይህን በተቀነባበረና ስልት ባለው መንገድ ከሰራን በወገኖቻችን ላይ የደረሰውንና የሚደርሰውን እልቂት ለማቆም እንችላለን። የወገኖቻችንን ክብር በመታደግ፤ የራሳችንን ክብር ለማስከበር እንችላለን።
ሁሉም ህይወት እኩል ዋጋ አለው!!!
No comments:
Post a Comment