የጎንደር ከተማ (ፎቶ ፋይል)
(ዘ-ሐበሻ) በአማራ ክልል ስር ያሉትና በሰሜን ጎንደር ስር የሚገኙት 2 ወረዳዎችን ወደ ትግራይ ክልል ለማጠቃለል የፊርማ ማሰባሰብ መጀመሩን ለዘ-ሐበሻ ከስፍራው የደረሰው መረጃ አመለከተ። ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል በጎንደር ስር የነበሩት አብረሃ ጅራ እና አብደራጊ የተባሉ ሁለት ወረዳዎች ውስጥ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ገበሬዎች በሰፊው የሰፈሩ ሲሆን እነዚሁ የትግራይ ተወላጆች ወረዳዎቹ ወደ ትግራይ ክልል እንዲጠቃለሉ ፊርማ ማሰባሰብ ጀምረዋል። በአሁኑ ወቅት እነዚህ 2 ወረዳዎን የትግራይ አመራሮች እንደሚቆጣጠሩት የገለጹት የዘ-ሐበሻ ምንጮች ገበሬዎቹም አስተዳደራዊ የበላይነትን በመጠቀም ወረዳዎቹን ወደ ትግራይ ለማካለል ሰፊ እንቅስቃሴ ላይ ናቸው። ገበሬዎች ከጥቅምት 5 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ወረዳዎቹ ወደ ትግራይ ክልል እንዲጠቃለሉ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ የጀመሩ ሲሆን ይህን ለማሳካት ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ መዋጮ እንዳዋጡም ተጠቁሟል።
የአማራ ክልል በነዚህ የትግራይ ገበሬዎች በተጀመረው እንስቃሴ ዙሪያ እስካሁን የሰጠው ምላሽ ባይኖርም ክልሉ ፈቀደም አልፈቀደም ገበሬዎቹ እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ ጉዳዩን ወስደው እነዚህን ሁለት የጎንደር ወረዳዎች ወደ ትግራይ ክልል ለማጠቃለል የሚመልሳቸው እንደሌለ በመናገር ላይ ናቸው ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሳንጃ፣ ጠገዴ፣ ዳባትና አፎኛ ደምቢ ወደራ የሚገኙ ነዋሪዎች የትግራይ ገበሬዎችን ጥያቄ እንደሚቃወሙ ገልጸው የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ በ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው ተሰምቷል።
No comments:
Post a Comment