Friday, October 25, 2013

ተስፋዬ ገብረአብ–ኢሰብዓዊ እና የሞራል ድሃ! ገላነው ክራር

ጥቂት ቀደም ሲል “አጼ ሚኒሊክ እና እቴጌ ጣይቱ በደራሲ ተስፋዬ ገ/አብ አይን” በሚል ርእስ በለቀቅሁት ጽሁፍ ሳቢያ በርካታ አንባቢያን የተለያዬ አስተያየት ልከውልኛል። አንዳንዱ “ይህን እየወጣ ያለ ደራሲ ወደታች ባትጎትተው ምናለ?” ሲል ሌሎችም “አበጀህ” ብለውኛል።

መጽሃፍትን አነባለሁ ብዬ አስባለሁ–በተለይ የአማርኛ ስራዎችን። አሁን አሁን የሚወጡትን ካልሆነ በቀር ብዙም ያመለጠኝ ስራ አልነበረም። አንድ መጽሃፍ አጀማመሩ ካላስደሰተኝ ለመጨረስ ራሴን አላስገድደውም። ጀምሬ ወዲያ ከወረወርኳቸው መጽሃፎች ውስጥ “የቡርቃ ዝምታ” አንዱ ነው። ይህ ስራው ተስፋዬን ከሞራሊቲ አኳያ እንዳወረደው ይኖራል። ባብዛኛው ሰው ተቀባይነት ያለው የሞራል ድርጊትና ሃሳብን፣ ሰብአዊነትን እና በስነ-ጽሁፍ ውበት ውስጥ ፍቅርን እና ሰላምን መስራትን ደግሞ “አደንቃቸዋለሁ” ከሚላቸው ደራሲያን–ስብሃት ገ/እግዚአብሄር እና በአሉ ግርማ አለመማሩ አሳዛኝ ነው። በተለይ በዓሉ ግርማ ለተስፋየ ሞዴል ሊሆን አይችልም። እኔ ተስፋዬን ብሆን፣ የበአሉን ስራዎች እንደገና አነባለሁ። ፍቅርና ሰላምን፣ እውነትን፣ ስለሰው ልጆች ሁሉ አንድነት ለመጻፍ እሞክራለሁ። የ“ቡርቃ ዝምታ” በወቅቱ የመለስ አገዛዝ ለተስፋዬ የሰጠው የቤት ስራ ነው ለማለት ባልደፍርም፣ በራስ ጊዜ ተነሳስቶ የሰራው ቢሆንም እንኳን፤ እኔ ተስፋዬን ብሆን ኖሮ የመጀምሪያ ስራዬ በ“የቡርቃ ዝምታ” ያደማሁትን ያብዛኛውን ልብ አጠግጋለሁ። ባጭሩ “አጥፍቻለሁ… ይቅርታ ይደረግልኝ” እላለሁ። በዚህ ብቻ አይደለም። ተስፋዬ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን አልበደለም አይባልም። “እፎይታ”ን ሲያዘጋጅ ያኔ በፕ/ር አስራት ወ/የስ ስም የወጣውን ጽሁፍ የሚያስታውስ አለ? ባለፈው ጽሁፌ “ … በ1980ዎቹ አጋማሽ አካባቢ በእፎይታ መጽሄት በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ስም አንድ ጽሁፍ ይወጣል። [ይህን አሁን ከዚህ በላይ እኔ የጻፍኳቸው ሁለት አንቀጾች፣ አንባቢ የየራሱን Nth term (ለምሳሌ እያንዳንዱን አምስተኛ/ስድስተኛ ቃል) እያወጣ በመጣል፣ ቀሪውን ጽሁፍ በምናብ ለማንበብ ይሞክር። ምንም እጅና እግሩ የማያስታውቅ ጽሁፍ ነው የሚሆነው] የሚል ጠቅሼ ነበር። ጽሁፉ በፕሮፌሰሩ ስም ሲወጣ የመጽሄቱ ዋና አዘጋጅ ተስፋዬ ገ/አብ ነበር። ጋዜጠኝነት እና ደራሲነት እንዲህ ዘቅጦ የሚወርድበትን የመለስ አገዛዝ፣ ያኔ እውስጡ እያለ አያውቅም አይባልም። “ያኔ የት ሄዶ ነበር?” ብዬም አልሞገተውም ተስፋዬን። የመለስን አገዛዝ (ኢህአዴግን) ያኔ የተቀላቀለው ወዶ ሳይሆን ተማርኮ ቢሆንም፣ እያደር በአመራራቸው ተመስጦ፣ በርዕዮተ አለማቸው ተማርኮ… ሊሆን ይችላል–እነሱው ጋር የከረመው። ይሁን። ግን እንደዚያ የፕ/ር አስራትን ጽሁፍ በወሮበላ አስቀምቶ ጽሁፋቸውን እንደ ማሳተም ያለ ስራ ሲሰራ፣ ከሞራል አንጻር ተስፋዬን ምን ተሰማው? ያን በፕ/ሩ ስም የወጣውን ጽሁፍ ቆይቼ ደጋግሜ አንብቤያለሁ። እውነት ለመናገር በረቂቅ ደረጃ እንኳን እንደዚያ አይነት ጽሁፍ የሚጽፍ የ5ኛ ክፍል ተማሪ የሚኖር አይመስለኝም። (ያ ጽሁፍ በአጋጣሚ በእጁ ያለው ሰው እታች ባሰፈርኩት አድራሻየ ቢልክልኝ ወይም አንባቢ እንዲያየው በአንዱ ሳይት ቢያወጣው አገራችን በእነማን እጅ እንደወደቀች እና የተስፋየንም ማንነት ማወቅ ይችላል)።


በቅርቡ “ተስፋዬ ገብረአብ ከሚበጀው የሚፈጀው” በሚል የጻፈልንን– (አለማየሁ ገላጋይን) ከልብ ልናመሰግነው ይገባል። የተስፋዬ ስራ፣ በህይወት የሌሉትን ቀርቶ ያሉትን እና ውብ ሰብእና ያላቸውን ሰዎች (ቡልቻ ደመቅሳ እና ዶ/ር ነጋሶ…) ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ታች ለማውረድ ሆን ብሎ የሚሰራ የጭቃ ውስጥ እሾህ ነው። ሲፈልግ የራያን ኦሮሞነት በተዘዋዋሪ ይነግረናል። ተስፋዬ አራት እና አምስት ዘር ማንዘሩን ወደ ኋላ ተመልሶ ቢመረምር፣ ወይም የደሙን DNA ቢያስመረምር፣ ወይ የኮንሶ ታልሆነም የሻኪሶ ዘር ደም አይታጣበትም። በመሰረቱ አይደለም የኢትዮጵያ፣ የጠቅላላው ምስራቅ አፍሪካ ህዝብ በአብዛኛው የተደበላለቅን ነን።

ተስፋዬ፣ የኤርትራውን ኢሳያስ የጤና ደህንነት፣ የመለስን ክፉኛ መያዝ እና የመሞታቸውን አይቀሬነት በተዘዋዋሪ ይነግረናል። በነገራችን ላይ የሁለቱም፡ ኢሳያስም ሆነ መለስ ሞት ቅርብ ነው። ሁለቱም ለአመታት ሲሰሩት በኖሩት ወንጀል የገዛ ህሊናቸው ሲያስጨንቃቸው የሚኖሩ፣ ደስታ የሚባል ነገር ያልዞረባቸው፣ በዲፕረሽን ሲሰቃዩ የኖሩ፣ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው። እንዲህ አይነት ሰው ደግሞ የበሽታዎች ሁሉ ጎተራ ቢሆን አይገርምም። እናም “they both will die young”። በዚህ አጭር እድሜያቸው የቀበሩት ቦንብ ግን አገራችንን ሁለት መቶ አመት ወደኋላ የመለሱ ሰዎች ናቸው። እና አበሳው ገና ይጠብቀናል። የነሱ መሞት ግን ብቻውን ለሃገር ምሉዕ መፍትሄ አይደለም። በየምናምንበት የተቃዋሚ ድርጅቶች መደራጀት እና አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን። እንደተስፋዬ ካሉ የጭቃ ውስጥ እሾሆች ራሳችንን መጠበቅ አለብን። ተስፋዬ በቅርቡ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ያወጡትን “አንገት ሲደፋ ምን ፈሰሰ..” ጽሁፋቸውን ለይቶ በብሎጉ ያወጣውም ፕ/ሩ የጻፉት እውነትነት ቢኖረውም፣ ስለ ኤርትራ እሱ በሚፈልገው መልኩ የተጻፈ ስላለ ነው። “የቤተመንግስት ሹክሹክታ…” በሚል የጻፈውንም፣ ጠንቃቃ አንባቢ ደግሞ ቢያየው፣ መሰሪነቱን በሚገባ ያውቃል። “…የመለስ ስጋት ኦሮሞ ብቻ አይደለም። ከኦሮሞ ባላነሰ አማራንም ይፈራል። ከኦሮሞና ከአማራም ባልተናነሰ የትግራይንም ህዝብ ይፈራዋል….” ሲል በዚሁ ጽሁፉ ያሰፈረልን ተስፋዬ ነው። እንዲህ ኦሮሞ፣ ትግሬ አማራ እያለ ለምን እየሸነሸነ እንደሚሰፍረን አይገባኝም። የመለስ አገዛዝ የሚከፋፍለን እና እርስ በርስ ሲያናክሰን የሚውለው መቼ አነሰንና። እስኪ አሁን ስለ “… ራያ ኦሮሞነት…” መንገር ምን ይባላል? ተስፋዬ ለምን “የኢትዮጵያ ህዝብ…” አይለውም? ሰብዓዊነት የሌላቸው መሪዎች፣ ወታደሮች፣ ገዢዎች… ቢኖሩ ብዙም አይገርምም። ደራሲ እና ጋዜጠኛ ነኝ የሚለው ተስፋዬ ከሰብዓዊነት እንዲህ ውርዶ መገኘቱ አሳዛኝ ነው። ተስፋዬ ሰብዓዊነትን ‘አደንቃቸዋለሁ’ ከሚላቸው ከነበዓሉ ግርማ እና ስብሃት ገ/እግዚአብሄር ያልተማረ እጅግ የሚታዘንለት እና የወረደ ሰብዕና ያለው እና የሞራል ድሃ የሆነ ሰው ነው። ይህን በተመለከተ በቅርቡ በሌላ ጽሁፍ ብቅ እላለሁ። ተስፋዬ ገ/አብን ‘የሞራል እና የፖለቲካ ድሃ ነው’ ብለን ብቻ የምናልፈው ሰው አይደለም። የጭቃ ውስጥ እሾህ ነው።

No comments:

Post a Comment