Tuesday, October 22, 2013

ወያኔና አሸባሪነት ምንና ምን ናቸው

የወያኔ ጉጅሌ ሰሞኑን የሚያሳዝን ባይሆን ኖሮ በእጅጉ ሊያስቅ የሚችል ቧልት ላይ ተጠምዷል። የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ሳይቀር ህብረተሰቡን በየተቋሙና በየመኖሪያው እየሰበሰበ ስለሽብርተኝነት ማብራሪያና ገለፃ በመስጠት ዜማ ላይ ተጠምዷል።

የወያኔ የሽብረተኝነት ገለፃ ዘመቻ ሚስጥር ደግሞ ብዙ ምርምር የሚሻ አይደለም። የሀገራችን ሰዎች ዶሮ ጭራ ልታወጣው የምትችል የሚሉት አይነት ሚስጥር ነው። አላማው ነጻነት አማረኝ፣ እምቢ ዘረኝነት እና ቢያንስ መሰረታዊ ሰበአዊ መብቴ ይገባኛል በማለት መብቱን እየጠየቀ የመጣው ህዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ታይቶታል።

የማእበሉ የመጀመሪያ ንቅናቄዎች ከወዲያ ወዲህ መታየት ጀምረዋል። የገለፀው ሽርጉድ ዋና አላማ ይህ መብቱን የሚጠይቅና አጎንብሶ መኖር የሰለቸው ህዝብ ለመብቴ የማደርገውን ትግል ሽብርተኛ ያስብለኛል ብሎ እንዲፈራና ይበልጥ እንዲያጎነብስ መሆኑ ነው። ይህን ደግሞ ህዝቡ አውቆታል። ሰሞኑን በአለምያ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ለገለፃው ለመጡ ካድሬዎች የሰጧቸው አጸፋዊ ገለጻ ይህንኑ ያሳያል፡፡


ሽብርተኝነት አንድና በነጻነትና በዴሞክራሲ ለመኖር የሚመኝና የወሰነን ህዝብ ሰላም በመንሳት የፖለቲካ አላማዪን አሳካለሁ ብለው የሚያምኑ ቡድኖችና ድርጅቶች የፖለቲካ መሳሪያ ነው። የወያኔ መሪዎች የሽብርተኝነት ትርጉም አልገባቸው ከሆነ ሰብስብ ብለው መሰዋእት ፊት ቢቆሙ ሽብረተኝነትን አፍጥጦ ሊያዩት ይችላሉ፡፡ ሽብርተኛው ወያኔና ወያኔ ብቻ ነው።

ህዝቡ ፊት በቆሙ ቁጥር ግን ህዝቡ ሽብርተኞችን ያያል። ሰለባውን ለማስተማር መሞከር ለእናት ምጥ የማስተማር ያህል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ሁሉንም የዲሞክራሲና የሰላም ጥያቄ ሁሉ በጉልበትና ባፈና የደፈጠጠ አሸባሪ ቁጥር አንድ ወያኔ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከሽብር ጋር የመረረ ችግር ላለባቸው ሀገሮች ሎሌነት ገብቶ ሌሎች ሽብርተኞችን ወደሀገራችን የሚጎትተው ራሱ ወያኔ ነው።

ዛሬ በማንም የባእድ አሸባሪ በህዝባችን ላይ ለሚደርስ ጉዳት ዋናው ተጠያቂ ወያኔ የሚሆነውም ለዚህ ነው። ለምእራብያውያን ጸረ ሽብር አጋራችሁ ነኝ እያልኩ ራሴ በምገዛው ህዝብ ላይ የምፈጽመውን ሽብር እንዳለ ያዩልኛል፣ ፍርፋሬም አገኝበታለሁ በሚል ስሌት የተገባበት መሆኑንም የማያውቅ ኢትዮጵያዊ ቁጥሩ ትንሽ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፡- ነጻነት የናፈቀህ፣ አጎንብሶና በገዛ ሀገርህ ተዋርዶ መኖር የሰለቸህ፣ በወያኔ ተሰደህ በባእድ ሀገር የምትሰቃይ፣ የምትሞት የኢትዮጵያ ልጅ ሁሉ ወያኔዎች ከግፍ አልፈው ሊቀልዱብህ፣ በቁምህ ሊገሉህ፣ ሊከፋፍሉህ አይገባም። ወያኔ የፈሪ አብራሪ ነው። አሻፈረኝ ሲሉት እንጂ ቢሸሹለት በቃኝ ብሎ አይመለስም፡፡

ግንቦት 7 ንቅናቄ እንደሁልግዜው ዛሬም ወገን ሆይ፡- የሀገርህን ህልውና ለመታደግ ተነሳ፣ ተቀላቀለን፤ የመከራችንን ቀን አጭር እንደርገው ዘንድ ጸሃይ ሳትገባብን፣ ሳይመሽብን ኑ ተቀላቀሉን የሚለውን ጥሪ ዛሬም አጠናክሮ ያቀርብልሃል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

No comments:

Post a Comment