Tuesday, February 24, 2015

በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች መፈክር የተፃፈባቸው ወረቀቶች ተበትነው አደሩ


በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች መፈክር የተፃፈባቸው ወረቀቶች ተበትነው አደሩ





አቡ ዳውድ ኡስማን
በአዲስ አበባ ትላንት ለሊቱን በተለያዩ አካባቢዎች ሙስሊሞችን የማሰር ዘመቻውን በመቃወም በራሪ ወረቀቶች ተበትነው እና ተለጥፈው ማደራቸውን ምንጮች አስታወቁ፡፡
ወረቀቶቹ በመንገድ ጋር ግድግዳዎች ላይ፣ በመንገድ ምልክቶች ላይ፣ በመብራት ፖሎች ላይ የተለጠፉ ሲሆን በየመንገዱም መበተናቸው ታውቋል፡፡
ትላንት ሌሊቱን ፒያሳ አምፒር አካባቢ፣ በሜክሲኮ ቄራ መንገድ ላይ፣ በጦር ሃይሎች፣በቦሌ ፒኮክ እና ወሎ ሰፈር፣ በመገናኛ፣ በመካኒሳ፣በቤተል እና በሌሎች ቦታዎች ላይ ወረቀት ተበትነው ማደራቸው ታውቋል፡፡
ከተበተኑት እና ከተለጠፉት መፈክሮች መካከል እስራት ትግላችንን አያስቆመውም፣መስዋትነት የኢስላም መንገድ ነው፣ሺ ሰው ቢታሰር ሺ ሰው ይተካል፣ ለኢስላም መታሰር ክብር ነው፣ ትግላችን ከምረጫው ቡሃላም ይቀጥላል፣ ድምፃችን ይሰማ፣ትግላችን ይቀጥላል የሚሉና ሌሎች በርካታ መልዕክቶችን የያዙ ወረቀቶች በመተናቸው ተገልፆል፡፡
መንግስት በአዲስ አበባ ሙስሊሞች የማሰር ዘመቻውን አጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት ህዝበ ሙስሊሙ እስራት መፍትሄ እንደማይሆን በተግባር ያረጋገጠ መልዕክት በትላንትናው ለሊት አስተላልፏል::

ጠበቃቸውን እንዳያገኙ የተከለከሉት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች በጨለማ ቤት መታሰራቸውን ገለጹ

(ነገረ ኢትዮጵያ) በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ የሚገኙት የሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀጠና/ዞን አመራሮች ለ16 ተከታታይ ቀናት በጨለማ ክፍል መታሰራቸውን ለፍርድ ቤት አስታወቁ፡፡ ዛሬ የካቲት 17 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀረቡት የሰማያዊ (የፓርቲው የጎንደር አደራጅ አቶ አግባው ሰጠኝ)፣ የአንድነት እና መኢአድ የዞን አመራሮች ‹‹መረጃ አውጡ፣ የደበቃችሁትን ሁሉ ተናገሩ›› እያሉ እንደሚደበድቧቸውና በጨለማ ክፍል እንዳሰሯቸው ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ አሁንም መረጃየን ሰብስቤ አልጨረስኩም በሚል ተጨማሪ 8 ቀናት ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ ተጠርጣዎቹ በማዕከላዊ እየደረሰባቸው የሚገኘውን ሰቆቃ አስመልክተው ለፍርድ ቤት አቤት ማለታቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የቀረበበትን አቤቱታ እንዲያስተካክል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በጎንደርና ጎጃም አካባቢዎች የዛሬ አራት ወር ገደማ በፖሊስ ታስረው ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ እንዲዛወሩ የተደረጉ ሲሆን፣ ጠበቃቸው በተደረገባቸው ክልከላ ምክንያት ተጠርጣሪዎቹን ካገኟቸው 2 ወር እንደሞላቸው ተናግረዋል፡፡ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አቶ አግባው ሰጠኝ እየተፈጸመበት ያለውን የመብት ጥሰት በመቃወም የርሃብ አድማ ላይ መሆኑ የታወቀ ሲሆን አድማውን ከጀመረ ሁለተኛ ቀኑ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው የጊዜ ቀጠሮ መሰረት አመራሮቹ የካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Monday, February 23, 2015

መልእክት ለወጣቶች፤ (በወጣቶች ጉዳይ መምርያ)

ወጣት ለአገር እድገትና ብልጽግና የሚያበረክተው አስትዋጾ ከፍተኛና በቀላሉ ለውጥ ማምጣት የሚችል ኃይል ያለው የህብረተሰብ ክፍል መሆኑ ይታወቃል። ይህን በቀላሉ ለውጥ ማምጣት የሚችል ትውልድ ጊዜው በሚጠይቀውና ለአገራችን በሚበጅ መልኩ ማደራጀት፣ መምራትና ንቅናቄው ለሚያደርገው የነጻነት፣ የፍትህና ዲሞክራሲ ትግል ግንባር ቀደም ሁኖ እንዲሰለፍ ማስቻል የንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት ሰባት ዋና ተግባር ነው። ስለሆነም ንቅናቄያችን ወጣቱ ትውልድ ለአገር እድገትና ዲሞክራሲያዊ ግንባታ የያበረክተው አስትዋጾ ከፍተኛና አስፈላጊ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የወጣቶች ጉዳይ መምሪያን አቋቁሞ ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል ትግሉን እንዲቀላቀል በማድረግ ላይ ይገኛል።

መምርያው የተቋቋመበት ዋና ዓላማ ወጣቱ ትውልድ የወያኔን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ፣ ኢ_ዲሞክራሲ፣ ኢ_ሰባዊ ድርጊት እና የሚያራምደውን የዘር ፖለቲካ በአጠቃላይ የወያኔን አምባገነናዊ ስርዓት በሚገባ እንዲገነዘብ በማድረግ እንዲሁም የንቅናቄያችንን ዓላማና ግብ በማስረዳት ለነጻነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ለሚደረገው የሁለገብ ትግል ወጣቱ ትውልድ ድርሻውን እንዲወጣ ማድረግ እና ኢትዮጵያ አገራችንን ጠብቆና አስከብሮ ለትውልድ የማስተላለፉን ኃላፊነት እንዲረከብ ማስቻል ነው።

እንደሚታወቀው የአንድ አገር ቀጣይነት ያለው እድገት የሚለካው በአላት መሠረተ ልማት፣ ቁሳዊ ሃብትና ንብረት ብቻ ሳይሆን በዋናነት ይህን ተረክቦ በአደራ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚችል ትውልዳዊ ትስስር ሲኖር ነው። ይህንንም የአገርና የህዝብ አደራ ድልድይ ሆኖ ከትውልድ ወደ ቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፍ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ስለሆነ ኢትዮጵያን ከወያኔ የጨለማ ቡድን መታደግ ለነገ የማይባይል አገራዊ ግዴታ መሆኑን ተገንዝቦ ወጣቱ ትውልድ ኃይሉንና አቅሙን ተጠቅሞ የእራሱን ነጻነት በእራሱ ማወጅ እንደሚችል መምርያው ያሳስባል።

በማንኛውም አገር፣ ጊዜና ዘመን እያንዳንዱ ትውልድ የአገሩ ወራሽ፣ ተተኪና ተረካቢ፣ ጠባቂና ለሚቀጥለውም ትውልድ የማውረስ፣ የማስተላልፍና የማስረከብ ኃላፊነትና ግደታ አለበት። ስለሆነም አገርን ከእነ ሙሉ ክብራ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ የእኛ የወጣቶች የዜግነት ግዴታ መሆኑን ተረድተን ጥልቅ በሆነ አገራዊ ስሜት በሦስቱም ዘርፍ ማለትም በማህበራዊ፣ በምጣኔ ሃብታዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ አገራዊ ተጽዕኖ ማድረግ እንደሚቻል በእርግጠኝነት የወጣቶች ጉዳይ መምርያ በድጋሚ በአጽንኦት ያሳስባል።

ውድ የአገራችን ወጣቶች ሆይ፤

የምንወዳትና የምንሳሳላት ብርቅዬ የጀግኖች አገር ኢትዮጵያ በባንዳዎች ወያኔ ለ24 ዓመታት የጥፋት ዘመቻ እየተካሄደና እየተፈጸመባት ሉዓላዊነቷ ተንቆ ትገኛለች። አምባገነኑ የወያኔ ቡድን በጠበንጃ ኃይል ስልጣን ከያዘበት ጀምሮ ሰብአዊ መብታችን ተጥሶ፣ ዲሞክራሲያዊ መብት ተነፍጎን፣ ተፈጥሮአዊ መብታችን ተነጥቆ፣ የዜግነት ማንነታችን ባንዲራችን ሳይቀር ተቀይሮ፣ ብሔራዊ ሃብትና ንብረት እየተዘረፈ፣ የአገራችን አርሶ አደር ለም መሬቱ እየተሸጠ፣ እተነጠቀና እየተባረረ፣ ለአገር የሚታገለው ንጹህ ዜጋ ፀረ ሰላም ፀረ ህግ ፀረ መንግሥት በመባል የሽብርተኛ ሕግ ወጥቶለት እየታሰረ፣እየተገደለና እየሞተ፣ እየተፈናቀለና እየተሰደደ፣ በግፍና በጭቆና ላይ መሆኑን ለአንተ ንቁ ህልሊና ላለህ ወጣት ትውልድ የተሰወረ አይደለምና በጽኑ በአስቸኳይ ታገለው። ነጻነትን አውጅ፤ ፍትህን ተቀዳጅ!ታሪክህን መልስ! ወያኔን ይብቃህ ከህዝብ ላይ ውረድ በለው።

ውድ የአገራችን ወጣቶች ሆይ፤

አገራችን ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዘመናት በነፃነት በቀደሙ አባቶቻችን ተጠብቃ የቆየችው በአካልና በደም ዋጋ ነው። በዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ ቆራጥነትና ፅናት አገርን በነፃነት መጠበቅ በዓለም ፊት ትልቅ ምሳሌነትን ያተረፈ፣ ዛሬ ለአለነውና ለመጭውም ትውልድ የሚኰራበት ሕያው የታሪክ አለኝታ፣ መመኪና ክብር ያለን ውድ ህዝቦች ነን። ይህ አኩሪ ታሪክ ፣ የዘላለም ሃብታችን በመሆኑ ጠብቀንና አስከብረን ለትውልድ ለማስረከብ ኃላፊነቱ በዋናነት የእኛ ወጣቱ ነው። ይህን እውነታ ተቀብሎ አገርን በነፃነት ለመጠበቅ ደፋ ቀና ከሚሉ ኢትዮጵያውያን ጋር አገራዊ ኃላፊነትንና ግዴታን ለመወጣት ዝግጁና ብቁ ሆኖ መታገል በእጅጉ ያስፈልጋል። ስለዚህ የአገራችን ወጣት ሁላችሁ ሰላም፣ ነጻነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባትና አገራዊ ድርሻንም ለመወጣት በህብረት ተነስ!፣ ታጠቅ!፣ ሰው ሁን! ታሪክህን መልስ!አረመኔው ወያኔን በቃህ በለው!

በአጠቃላይ እኛ ወጣቶች ለአገር ነጻነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ለሚደረገው ትግል የወጣትነትን አቅምና ኃይል ተጠቅመን የታሪክ ባለቤት እንሆን ዘንድ በሁለገብ ትግል የኢትዮጵያን ጠላት ወያኔን ለማስወገድ ከሚታገለው አርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ ጋር በመቆም ሰላም፣ ነጻነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት እና በጽናት አረመኔው ወያኔን ከህዝባችን ጫንቃ ላይ ለማስወገድ የበኩላችንን ኃላፊነትና ግዴታ መወጣት አለብን።

እንዲሁም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አገራችን የጣለችብንንና የሚጠበቅብንን አገራዊ ኃላፊነት በትጋትና በንቃት መወጣት የሁላችንም ግዴታ መሆኑን ተገንዝበን ለአገር እድገት የጀርባ አጥንት የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ወጣቱን ከወያኔ ትውልድ ገዳይና አገር ሻጭ አገዛዝ መታደግ ተቀዳሚ ተግባር በማድረግ ትግላችንን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለብን በጥብቅ ለማሳሰብ እንወዳለን።

ወጣቱ ትውልድ ጊዜውን፣ ኃይሉን፣አቅሙንና ጉልበቱን ተጠቅሞ ለአገርና ለእራሱ ነጻነት እንዲታገል ምቹ ሁኔታወችን መፍጠር፣ ወኔና አገራዊ ስሜት እንዲኖረው መቀስቀስ፣ ወጣቱ ትውልድ በንቃትና በቁርጠኝነት ትግሉን በባለቤትነት ተረክቦ የድልና የነጻነት ዓርማ እንዲያውለበልብ ማድረግና ጥቅሙንም ማስገንዘብ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አገራዊ ተግባርና ኃላፊነት መሆኑን ተገንዝበን ሁላችንም ወጣቱን ትውልድ ከወያኔ ለመታደግ የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል።

በመጨረሻም ዘመኑ በአፈራቸው የብዙኃን መገናኛ መንገዶች በመጠቀም ለወጣቶች ወጣት ተኮር መልክቶችን በቀጣይነት ማስተላለፈ ስለተፈለገ በማነኛውም መንገድ ወጣቱን ለትግል ሊያነቃቃና አገራዊ እውቀት ሊያስጨብጥ የሚችል ግብዓት በመስጠት ትውልድ የማዳንና የማፍራት ተልእኮን እንድትጋሩ የወጣቶች ጉዳይ መምሪያ መልእክቱን በአክብሮት ያስተላልፋል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
የአርበኞች ግንቦት 7 ወጣቶች ጉዳይ መምርያ

ድል የአላማ ጽናት እንጂ የመሳሪያ ጋጋታ ዉጤት አይደለም

ጣሊያን ዋና ከተማ ሮም ዉስጥ ዋና ከተማዋን ከተለያዩ የጣሊያን ከተሞችና ጣሊያንን ከፓሪስ፤ከሙኒክ፤ከጄኔቫና ከቪዬና ጋር የሚያገናዉና በአመት ከ 150 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን የሚያስተናግድ አንድ ትልቅ የባቡር መስመር አለ። ይህ የባቡር መስመር የሚጠራዉ ሮማ ተርሚኒ እየተባለ ሲሆን የባቡር መስመሩ አድራሻ ደግሞ የአምስት መቶዎቹ አደባባይ በመባል ይታወቃል። ወደዘህ ትልቅ ባቡር መስመር ሲገባ አንድ እጅግ በጣም ትልቅ ሀዉልት ወለል ብሎ ይታያል፤ ይህም ሀዉልት የአምስት መቶዎቹ አደባባይ ወይም ፒያዛ ዴ ቺንኮቼንቶ በመባል የታወቃል። የፒያሳ ዴ ቺንኮቼንቶ መታሰቢያ ሀዉልት የተሰራዉ ወራሪዉ የጣሊያን ጦር አገራችንን ለመወረር ሲመጣ ዶጋሌ ላይ በራስ አሉላ ጦር የተገደሉትን አምስት መቶ የጣሊያን ወታደሮች ለማስታወስ ነዉ። በ1877 ዓም ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ ጦርና ጎራዴ በታጠቀዉ የራስ አሉላ ጦር ዉርደት የተከናነበዉ የጣሊያን ወራሪ ሠራዊት ብድሩን ለመመለስ በ1888 ዓ.ም ብዛት ያለዉ ካባድ መሳሪያ፤ መድፍና መትረየስ ታጥቆ አድዋ ድረስ ቢመጣም በዳግማዊ ሚኒሊክ የተመራዉ ጀግናዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት እንደገና ዉርደት አከናንቦት በጥቁር ህዝብ ታሪክ ዉስጥ ትዝታዉ ምንግዜም የማይደበዝዝ ድል አስመዝግቧል። የኢትዮጵያ ሠራዊት ዶጋሌና አድዋ ላይ እስካፍንጫዉ የታጠቀዉን የጣሊያን ወራሪ ጦር ደጋግሞ ያሸነፈዉ በመሳሪያ በልጦ ወይም የተሻለ የዉትድርና ችሎታ ስለነበረዉ ሳይሆን ከወራሪዉ ጦር የበለጠ ቆራጥነትና የአለማ ጽናት ሰለነበረዉ ነዉ።

በሃያኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን የተደረጉ ሌሎች የነጻነት ትግሎችን ስንመለከት በወቅቱ የአየር ኃይል ያልነበራት ትንሿ አገር ቬትናም በባህር፤ በአየርና በየብስ ጦርነት የገጠማትን ትልቁን የአለማችን ሀይል አሜሪካንን አሸንፋ ነፃነቷን ያስከበረችዉ በመሳሪያ ጋጋታ ሳይሆን የዛፍ ላይ ቅጠልና የተቦጫጨቀ ጨርቅ በለበሱ ነገር ግን ከፍተኛ የአላማ ጽናት በነበራቸዉ ጀግኖች ልጆቿ አማካይነት ነዉ።

አለማችን ትልቅ የጦርነት አዉድማ ናት ቢባል አባባሉ እምብዛም ከእዉነት የራቀ አባባል አይደለም። በእርግጥም አለም የጦርነት መድረክ ናት። ወደድንም ጠላን ወይም ብናምንም ባናምንም ጦርነቶች ሁሉ የተካሄዱት የህዝብን ነፃነት በሚደፍሩ ኃይሎችና መብቴንና ነጻነቴን አትንኩ በሚሉ ኃይሎች መካከል ነዉ። የአለማችን ታሪክ ወለል አድርጎ እንደሚያሳየን ደግሞ ይዋል ይደር እንጂ ሁሉም ዘለቄታዊ ድሎች የተመዘገቡት የአላማ ጽናት ባላቸዉ መብቴንና ነጻነቴን አትንኩ በሚሉ ኃይሎች ነዉ እንጂ የመሳሪያ ጋጋታ በተሸከሙ ኃይሎች አይደለም። የመሳሪያ ጋጋታ የተሸከመና ብዛት ያለዉ ወታደር ያሰለፈ ነገር ግን ለምን እንደሚዋጋ የማያዉቅና የአላማ ጽናት የሌለዉ ሠራዊት ግዜያዊ የጦር የጦር ሜዳ ድል ለያገኝ ይችላል፤ ሆኖም ጦርነቱን አሸንፎና የህዝብን ነጻነት ቀምቶ መዝለቅ በፍጹም አይችልም።

የአለም ታሪክ በነጭ ወረቀት ላይ በጥቁር ቀለም ቁልጭ አድርጎ የጻፈዉ አንድ ግዙፍ ሀቅ ቢኖር እልፍ ታንክና እልፍ አዕላፋት መድፎች ቢታጠቁም አምባገነኖች ለግዜዉ እንደተቆጣ ነብር ያስፈራሉ እንጂ ህዝባዊ አለማና ጽናት ያለዉ ጦር ፊት ሲቆሙ ፀሐይ እንደገላመጠዉ በረዶ ሟሽሸዉ የሚጠፉ ደንባራ ፈረሶች ናቸዉ። ለዚህም ነዉ ህዝብ አምባገነኖችን የወረቀት ላይ ነብር እያለ የሚጠራቸዉ።

ዛሬ ዕድሜዉ 35 እና ከዚያም በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚኒልክን ቤ/መንግስት ተቆጣጥረዉ የረገጡትን፤ የገደሉትንና መብቱንና ነጻነቱን ገፍፈዉ ያዋረዱትን ሁለት የወረቀት ላይ ነብሮች ያስታዉሳል የሚል ሙሉ እምነት አለን። ደርግ በ1967 ዓም “ያለ ምንም ደም እንከኗ ይዉደም” እያለ ወደ ሥልጣን ሲመጣ በፊዉዳሉ ስርዐት ጀርባዉ የጎበጠዉን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ደስ አሸኝቶ ነበር። እየቆየ ሲሄድና የተደበቀ ትክክለኛ መልኩ አደባባይ ሲወጣ ግን ያንን “ያለ ምንም ደም” የሚለዉን መፈክሩን ረስቶ ኢትዮጵያን የደም ገንዳ ሲያደርጋት በኢትዮጵያ ህዝብ ተጠልቶ አይንህን ለአፈር ተባለ። በሩሲያ ሰራሽ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች አስካፍንጫዉ የታጠቀዉና በቁጥሩና በወታደራዊ ብቃቱ አፍሪካ ዉስጥ ትልቁን ሠራዊት የገነባዉ ደርግ “እንደ ዉኃ የሚያጥለቀልቅ ኃይል አለኝ” እያለ ቢፎክርም እሱ እራሱ ተጥለቅልቆና በያለበት ተሸንፎ አገራችን ኢትዮጵያን ለዘረኛ አምባገነኖች ያስረከበዉ ለእግሩ ጫማ ለወገቡ መታጠቂያ በሌለዉ የገበሬ ጦር ተሸንፎ ነዉ። ደርግ እንደታጠቀዉ መሳሪያ ብዛት፤ እንዳደራጀዉ ወታደራዊ ብቃትና እንደ ወታደራዊ መሪዎቹ ችሎታ ቢሆን ኖሮ ደርግን እንኳን ተዋግቶ ለማሸነፍ በዉግያ ለመግጠምም የሚያስብ ኃይል በፍጹም አይነሳም ነበር፤ ነገር ግን ድል ምን ግዜም ቢሆን የመሳሪያ ጋጋታ ዉጤት ሳይሆን የራዕይ ጥራትና የአላማ ጽናት ዉጤት በመሆኑ በወቅቱ ይህንን የተገነዘቡ ኃይሎች ህብረትና አገር ዉስጥ የተቀሰቀሰዉ ህዝባዊ ቁጣ አንድ ላይ ሆነዉ ደርግን ጠራርገዉ የታሪክ ቆሻሻ ዉስጥ ሊጨምሩት ችለዋል።
ዛሬ ደርግን አሸንፈዉ ደርግ የተቀመጠበት ወንበር ላይ የተቀመጡት ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች የአገርን ኃብት ከመዝረፍ፤ የተቃወማቸዉን ከመግደልና የኢትዮጵያን አንድነት ከማፍረስ ዉጭ እንዴትና ለምን ደርግን የመሰለ ሠራዊት እንዳሸፉ የተገነዘቡ አይመስልም። ወያኔዎች ደርግ ከወደቀ ከ24 አመት በኋላ ዛሬም በየቀኑ ደርግን ቢኮንኑም ተቀምጠዉ አገር የሚገዙት ልበቢሱ ደርግ የተቀመጠበት ወንበር ላይ ነዉና የደርግ በሽታ ተጋብቶባቸዉ እነሱም እንደደርግ ልበቢሶች ሆነዋል።

ኢትዮጵያ በየዘመኑ እያደገና እየዘመነ የመጣ፤ ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተዉጣጣና ሞያን፤ ችሎታንና ወታደራዊ ሳይንስን አዳብሎ የታጠቀ ዘመናዊ የአገር መከላከያ ተቋም የነበራት አገር ነበረች። ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ ይህንን ዘመናዊ የአገርና የወገን መመኪያ የሆነ ሠራዊት አፍርሰዉና በየበረሃዉ ለእናት አገሩ የተዋደቀዉን ሰራዊት ለማኝ አድርገዉት ነዉ እነሱ ወርቃማዉ ዘር ብለዉ በሚጠሩት ዘር የበላይነት ላይ የተመሰረተ የመከላከያ ተቋም የገነቡት። ወያኔ የገነባዉ የመከላከያ ተቋም ባለፉት ሃያ አራት አመታት ዉስጥ አዲስ አበባ፤ ኦጋዴን፤ ጋምቤላ፤ ደቡብ ኦሞና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የወሰዳቸዉን ፀረ ህዝብና ፀረ አገር እርምጃዎች ስንመለከት ተቋሙ እዉነትም ለአገር ጥበቃ ሳይሆን የወያኔን የበላይነት ለማረጋገጥ የተቋቋመ ኃይል መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይችላል።

ይህ ሙሉ በሙሉ በትግርኛ ተናጋሪዎች የሚታዘዘዉ መከላከያ ሠራዊት ጋምቤላና ኦሞ ሸለቆ ዉስጥ ገበሬዉ ከቀዬዉ ተፈናቅሎ መሬቱ ባዕዳን ሲቸበቸብ አፉን ዘግቶ እንዲመለከት አድርጓል። ይሄዉ ሠራዊት በ1997 ዓም በአግአዚ ነብሰ ገዳዮች እየተመራ የህዘብ ድምጽ ይከበር ያሉ ከ200 በላይ ሠላማዊ ዜጎችን በግፍ ጨፍጭፏል፤ ከዚህ በተጨማሪ የወያኔ መከላከያ ሠራዊት አጋዴንና ጋምቤላ ዉስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል አሁንም እየፈጸመ ነዉ። እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ትኩረት ሰጥቶ ሊመለከተዉ የሚገባዉ ነገር አለ፤ እሱም ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች ልማታዊ ሠራዊት ብለዉ እያሞካሹና “የመከላከያ ኃይሎች ቀን” የሚል ስያሜ ሰጥተዉ በየአመቱ ማክበር የጀመሩት በዐል የሚያወድሰዉ ይህንኑ አንድነቱንና ነፃነቱን እጠብቃለሁ ብሎ ቃል ኪዳን የገባለትን ህዝብ ያለ ርህራሄ የሚጨፈጭፈዉን የወያኔ ሠራዊት ነዉ። በተለይ ወያኔ ባለፈዉ ሳምንት ባህር ዳር ዉስጥ ያለ የለሌ የመሳሪያ ጋጋታዉን አደባባይ አዉጥቶ ለህዝብ እያሳየ ባከበረዉ የመከላከያ ቀን በዐል ለህዝብ ማስተላለፍ የፈለገዉ መልዕክት ቢኖር “ይህንን እያያችሁ ከወያኔ ጋር በእሳት አትጫወቱ “ የሚል የሞኝ መልዕክት ነዉ።

ይህ ባህር ዳር ላይ የተላለፈዉ መልዕክት ለማን እንደሆነና በተለይ ባህር ዳር የመልዕክቱ ማስተላለፊያ ቦታ ሆና የተመረጠችበት ምክንያት ለማንም ኢትዮጵያዊ ግልፅ ይመስለናል። የዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች መሰባሰቢያ የሆነዉ ህወሓት የተወለደዉም ሞቶ የሚቀበረዉም ሰሜን ኢትዮጵያ ዉስጥ መሆኑን እሱም ደጋፊዎቹም ካወቁ ቆይቷል። ዉቧና የጀግኖች መፍለቂያ የሆነችዉ ባህር ዳር ደግሞ ይህንን የወያኔን የቀብር ጉዞ ከጀመረች አመታት አስቆጥራለች። እንገዲህ ወያኔ በየቀኑ ከባድ መሳሪያና ስፍር ቁጥር የሌለዉ ወታደር ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሚያጓጉዘዉ ከዚሁ ከማይቀርለት ዉድቀቱ የሚያድኑት እየመሰለዉ ነዉ። እዚህ ላይ አንድ ወያኔ በፍጹም ያልተረዳዉ ነገር ቢኖር ህወሓትን ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርጎ የሚያጠፋዉና ግብዐተ መሬቱን የሚፈጽመዉ ይሄዉ ወያኔ በነጋ በጠባ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሚያጓጉዘዉ ሠራዊት መሆኑን አለመረዳቱ ነዉ። የወያኔ አይን ያወጣ ዘረኝነት በከፍተኛ ደረጃ ከተንጸባረቀባቸዉና በየቀኑ በዘረኝነት እሳት ከሚለበለቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ የመከላከያ ሠራዊት ነዉ። ይህ ሰራዊት እንደ መሬት የሚረግጡትን የወያኔን አለቆቹን ትዕዛዝ ተቀብሎ ከታሰረበት የዘረኝነት እስር ቤት ነፃ ሊያወጡት በሚታገሉ የኢትዮጵያ ህዝብ የነጻነት ኃይሎች ላይ መሳሪያዉን ያዞራል ብሎ የሚያምን ኢትዮጵያዊ ያለ አይስለንም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የወያኔን የመሳሪያ ጋጋታ አይቶ ለእናት አገሩ አንድነትና ለኢትዮጵያዉያን ወገኖቹ ነጻነት ህይወቱን ከመስጠት ወደ ኋላ የሚል ኢትዮጵያዊ ቢኖር እሱ ከወያኔ ጋር በጥቅም የተጋባ ከሃዲ መሆን አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብ ምንግዜም ቢሆን በወሬ ቱማታና በመሳሪያ ጋጋታ ትጥቁን ፈትቶ አያዉቅም። በ1930ዎቹ ፋሺስት ጣሊያኖችንና በ1970ዎቹ ወታደራዊዉን ደርግ ተዋግቶ ያሸነፈዉ እነዚህ ኃይሎች የታጠቁትን መሳሪያ እየቀማ በተዋጋቸዉ ነጻነት የጠማዉ ኃይል ነዉ። የዛሬዎቹ የወያኔ ፋሺስቶች እጣም ጣሊያንና ደርግ ከገጠማቸዉ ሽንፈት የተለየ አይሆንም።

የአገራቸዉን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ከጠላት ለመከላከል የመከላከያ ሠራዊትን የተቀላቀሉ የኢትዮጵያ ልጆች “ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት” የሚለዉን የአባቶቻቸዉ ምሳሌያዊ አባባል ምንነት በሚገባ የሚረዱ ይመስለናል። ስለሆነም ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ በዘር ለይቶ እየረገጣቸዉ፤ እያዋረዳቸዉና ከሰዉ በታች አድርጎ እየተመለከታቸዉ ይህንን ቅጥ ያጣ በደል ለማረሳሳት የመከላከያ ቀን እያለ በሚያከብረዉን የይስሙላ በዐል እንድም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ሊታለል አይገባም። ከአግአዚ ነብሰ ገዳዮች ዉጭ ያለዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንደማንኛዉም የወያኔ እስረኛ እንደሆነ የህብረተሰብ ክፍል ነፃ መዉጣት የሚገባዉ ክፍል ነዉ። ይህ የህዝብ ወገን የሆነዉ የመከላከያ ሠራዊት እራሱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዉያን ወንድሞቹንና እህቶቹን ጭምር ከወያኔ ዘረኝነት ነጻ ሚያወጣት አለበት። እስከቅርብ ግዜ ድረስ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ብዙም አማራጭ ስላልነበራቸዉ አንገታቸዉን ደፍተዉ የጠላታቸዉን የወያኔን ትዕዛዝ እየተቀበሉ ሲፈጽሙ ቆይተዋል፤ አሁን ግን አንገታቸዉን ቀና አድርገዉ የወያኔን አንገት የሚያሰደፉበት አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል። ዛሬ ለእናት አገራቸዉ ነጻነት በህይወታቸዉ ቆርጠዉ ብረት ያነሱ የነጻነት አርበኞች የመከላከያ ሠራዊት የወያኔ አለቆቼን ትዕዛዝ ላለመቀበልም ሆነ ወይም የታጠቀዉን መሳሪያ ወደ ጠላቱ ወደ ወያኔ ማዞር የሚችልበትን አመቺ ሁኔታ ፈጥረዉለታል።

ዉድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ሆይ ጨለማዉ ሊጠራ ሲል ይበልጥ ይጨልማልና ወያኔ ወደ ሰሜናዊዉ የአገራችን ክፍል የሚያጓጉዘዉ የመሳሪያ ጋጋታና የሠራዊት ብዛት በፍጹም ልትደናገጥ አይገባም። ወያኔን ካንተ በላይ በቅርብ የሚያዉቀዉ የለም፤ የወያኔ ኃይለኝነትና ትልቅ መስሎ መታየት አንተ በዉስጡ ስላለህበት ብቻ ነዉ። ስለዚህ ይህንን ፀረ ኢትዮጵያ ኃይል ለቅቀህ በያለህበት ላንተ፤ ለወገኖችህና ለእናት አገርህ ነፃነት መከበር ከቆረጡ ወገኖችህ ጋር በፍጥነት ተቀላቀል። ይህንን ማድረግ የማትችለዉ ደግሞ ወያኔ ከገዛ ወገኖችህ ጋር እንድትዋጋ ትዕዛዝ ሲሰጥህ የታጠከዉን መሳሪያ ወደ ወገኖችህ ሳይሆን ወደ ራሱ ወደ ወያኔ አዙር። ወያኔ ለትንሽ ግዜ የማይበገር መስሎ ሊታይ ይችል ይሆናል የማይቀረዉ የዘለቄታ ድል ግን ምን ግዜም የህዝብ ነዉ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ደግሞ ትናንት አንደነበረ ሁሉ ዛሬም የኢትዮጵያ ህዝብ አለኝታ ነዉ።

ድል የህዝብ ነዉ!

አዋራጅ ሰልፎችና ድግሶች እንዲያበቁ ህወሓት ይወገድ!

ድግሶችን፣ ወታደራዊ ሰልፎችንና ሀውልቶችን ማብዛት የአባገነኖች ሁሉ የጋራ ባህርይ ነው። ዘረኛውና ፋሽስቱ የህወሓት አገዛዝም በሕዝብ እየተጠላ፣ እያረጀና እየወላለቀ በሄደ መጠን በየተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ደግሶ መብላት፤ ወታደራዊ ሰልፍና የመሣሪያ ጋጋታ ማሳየት እና በየመንደሩ ሀውልት መመረቅ ሙያው አድርጎት ቆይቷል።

የህወሓት ድግሶችና ፌሽታዎች የአገራችን ሀብት ከማሟጠጣቸውም በላይ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ የአርሶ አደሮችንና የአነስተኛ ነጋዴዎችን ኪስ እያራቆቱ ናቸው። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች በእስር ቤቶች እየማቀቁ በሚገኙበት ሁኔታ፤ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ የአማራ አርሶአደሮች ተፈናቅለው እያለ፤ በጋምቤላና በኦጋዴን ወገኖቻችን ላይ ዘግናኝ የጅምላ ጭፍጨፋዎች እየተደረጉ፤ በአፋር፣ በሲዳማ፣ በቦረና፣ በወልቃይት እና በመላው ኢትዮጵያ ግጭቶች በበዙበት፤ ሕዝብ እያለቀሰ ባለበት በአሁኑ ሰዓት “የብሔር፣ ብሔረሰቦች መብት ተከበረ” እያሉ እነዚህኑ በደል እየደረሰባቸው ያሉ ዜጎችን ማስጨፈር እና ለእነዚህ ጭፈራዎች በርካታ ሚሊዮኖች ብር ማውጣት በእጅጉ ያስቆጫል። እነዚህ ጭፈራዎች ለህወሓት ሰዎች የገቢ ምንጮች መሆናቸው ጥርጥር የለውም፤ ለድሀው ኢትዮጵያዊ ግን መራቆቻዎች ናቸው። ከዚህም አልፎ በዘረኝነት እየተበደለ ያለ ሕዝብ ስለእኩልነት ዝፈን ማለት ክብረ ነክ ተግባር ነው። ዘንድሮ በአሶሳ የተደረገው አገር አቀፍ ድግስ ካለቀ ጥቂት ወራት በኋላ አገራችን በሌላ ዙር የህወሓቶች ድግስ ተወጥራለች።

ሰሞኑን በባህር ዳር በተደረገው የጦር ሠራዊት ሰልፍ እና ሰልፉን ተከትሎ በነበረው የድግሶች ግርግር ከሁሉም በላይ የተሰደበውና የተዋረደው የሠራዊቱ አባል ነው። አዛዦቹ መቶ በመቶ የህወሓት አባላት የሆኑበትን ሠራዊት “የኢትዮጵያ መከላከያ” ተብሎ መጠራቱ ራሱ የሚያሳፍረው ኢትዮጵያዊ ወኔ በልባቸው ውስጥ እየተንቀለቀለና እልህ እየተናነቃቸው ያሉ የሠራዊቱን አባላት ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዴት የኢትዮጵያ ጠላቶች በሆኑ የህወሓት ካድሬዎች ይመራል? እንዴት የአስር አለቃ እንኳን ሊሆን የማይገባው የህወሓት ካድሬ “ጄኔራል” ተብሎ ኢትዮጵያዊያን ወታደሮችን እንደ ሎሌው ያዛል? እንዴት አንድ የህወሓት ሎሌ ሹመት ተሰጥቶት እየፏለለ በልምድ፣ በትምህርትና በእውቀት የሚበልጠውን ኢትዮጵያዊ ተንቆ ይዋረዳል? ይህ ቁጭትና እልህ ሠራዊቱ የዘረኛውን ህወሓት ሰልፍ አድማቂ መሆኑ የሚያከትምበት ጊዜ ይበልጥ እንዲናፍቅ የሚደረገው ነው። አልያማ ሰልፍ ያሳመረ ሠራዊት ሁሉ አሸናፊ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። በሰልፍ ብዛትና በመሣሪያ ትዕይንት ማሸነፍ ቢቻል ኖሮ የትም አገር አምባገነኖች ባልወደቁም፤ ህወሓት ራሱን ስልጣን ላይ ባልወጣም ነበር።

የህወሓት ምሥረታ 40ኛ ዓመት ድግስም ሌላው የታሪክና የሀብት ውድመት የሚያስከትል ክስተት ነው። የካቲት 11 ቀን 1967፣ ጥቂት ኢትዮጵያዊያን እናታቸውን ኢትዮጵያን ለመግደል ያሴሩበት እና ልጆች በእናታቸው ላይ ቢላዋ የሳሉበት ዕለት በመሆኑ በሀዘንና በሱባኤ እንጂ በድግስና በጭፈራ የሚታሰብ ዕለት አይደለም። ሲነሳ ምንም ይሁን ምን ዛሬ በደረስንበት ሁኔታ ሲገመገም፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ ህወሓትን የመሰለ መሠሪና አድርባይ ድርጅት ገጥሟት አያውቅም። እነሆ ዘንድሮም ይኸው አድርባይ ድርጅት የመሪዎቹን የሀብትና ዝና ረሀብ ለማስታገስ ሲል ያልነበረ ታሪክ እየፈጠረ በድግስ ስም ከድሀው ገንዘብ እየሰበሰበ ለሀብታም የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ያሸጋግራል። የድግሶቹ ሁሉ አዘጋጆች፣ እቃ አቅራቢዎችና ተጠቃሚዎች ራሳቸው የህወሓት መሪዎችና አሽቃባጮቻቸው ሲሆኑ ከፋዩ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። በህወሓት ድግስ የሚባክነው የሕዝብ ሀብት ስንት ሆስፒታል ይገነባ እንደነበር ስናስብ እና ይህ ሀብት በተገቢው ቦታ ውሎ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ስም ብቻ የያዙ ዩንቨርስቲዎቻችንን ትምህርት መቅሰሚያ ማድረግ እንችል እንደነበር ስናሰላ ሀዘናችን ጥልቅ ነው። ህወሓት ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ ዕዳ እየቆለለ ዳንኪራ ሲረግጥና ሲያስረግጥ ማየትና መስማት ህሊና ሊሸከመው ከሚችል በላይ ነው።

አርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በህወሓት ወታደራዊ ሰልፍ እና የመሣሪያዎች ትዕይንት የሚረበሽ ድርጅት አይደለም። ይልቁንም በሰልፉ ጨኸት የታፈነው የኢትዮጵያዊ ወታደር ጩኸት ይሰማዋል። ኢትዮጵያዊ ወታደር በአዛዦቹ ላይ ጥርሱን ነክሶ፣ ቂም አርግዞ ሰልፋቸውን እንደሚሰለፍ አርበኞች ግንቦት 7 ያውቃል። አርበኞች ግንቦት 7፣ የሠራዊቱ አባላት ውስጥ ውስጡን እየተሰቃዩ የታዘዙትን መፈፀማቸው መብቃት አለበት ይላል፤ ወይ ተቀላቀሉን፣ አሊያም እውስጡ ሆናችሁ ሥርዓቱን የማዳከም ሥራዎችን ሥሩ። በእናንተ ውርደት የዘራፊዎች፣ ሙሰኖች፣ ጎጠኞችና ዘረኞች ደረት አብጦ መታየት የለበትም።

አርበኞች ግንቦት 7፣ የዘንድሮው የህወሓት 40ኛ ዓመት በዓል የጨረሻው በዓል እንዲሆን፤ ከርሞም ተመሳሳይ አዋራጅ በዓል እንዳናከብር፤ ሠራዊቱ በዘራፊዎች ታዞ የሚሰለፍበት ውርደት እንዲያበቃ ተባብረን ህወሓትን እንቅበር ይላል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

Saturday, February 21, 2015

ተወዳድሮ ማሸነፍ የሚችለው ሰማያዊ ብቻ መሆኑ ተረጋገጠ

ነገረ ኢትዮጵያ
መድረክ 218 ኢዴፓ 127 መቀመጫዎች ብቻ ነው ያሰመዘገቡት
የምዝገባ ጊዜ ሳይጀምር፣ የአንድነት ፓርቲ ከሶማሌ ክልል በስተቀር በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ለፓርላማና ለክልል ምክር ቤቶች ተወዳዳሪዎች አዘጋጅቶ እንደነበረ ይታወቃል። የአንድነት ጥንካሬ ከወዲሁ የተረዳሁ የሕወሃት ፖሊት ቢሮ ለምርጫ ቢርድ መመሪያ በመስጠት፣ ተለጣፊ ቡድን በማደራጀት አንድነት ላይ የኃይል እርምጃ ወስዷል።
የአንድነት አባላታ ለድርጅት ሳይሆን ለነጻነት የሚታገሉ እንደመሆናቸው ማሊያ ቀይረው በሰማያዊ ፓርቲ ሥር ለመንቀሳቀስ ተነሱ። የሰማያዊውች እና የአንድነቶች መያያዝ ትግሉን የበለጠ አጠናከረው። ሳምንታ ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ አንድነቶ ተነቃነቁ። ወደ ሰማያዎ ጎረፉ። በፊትም ጠንካራ የሆነው የሰማያዊ ፓርቲ አንድነቶች ሲመጡ የበለጠ ተጠናክሮ ከአራት በላይ ለፓርላማ፣ ከሰባት መቶ በላይ ለክልልተወዳዳሪዎች አስመዘገበ። ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች በምርጫ ቦርድ የሌላ ፓርቲ አባል ናችሁ በሚል ተሰረዙ።
እንደዚያም ሆኖ ከኢሕአዴግ ቀጥሎ ብዙ ተወዳዳሪዎችን ሰማያዊ ፓርቲ እንዳሰለፈ ለማወቅ ተችሏል። ኢሕአዴግ ከ547 የፓርላማ መቀመጫዎች 457 ላይ ተወዳዳሪዎች ያስመዘገበ ሲሆን፣ ሰማያዊ የተሰረዙትን ሳይጨመር ለፓርላማ 345 (63%) ተወዳዳሪዎችን አስመዝግቧል። ኢሕአዴግ የሚወዳደረው በትግራይ፣ ደቡብ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልልም በአዲስ አበባ ብቻ ነው። በአፋር፣ ሶማሌ፣ ቤኔሻንጉልና ጋምቤላ የሚወዳደሩ ኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶች የሚላቸው ናቸው።፡
የብዙ ድርጅቶች ስብስብ የሆነ መድረክ 218 ( 39%) መቀመጫ ብቻ ሲሆን ለፓርላማ ያሰለፈው በትግራይ ከ38 መቀመጫዎች ከሰላሳ በላይ፣ በኦሮሚያ ከ175 መቀመጫዎች በ160ው ተወዳዳሪዎችን አሰልፏል። በደቡም ክልል ወደ ሃያ ብቻ የሚሆኑ ተወዳዳሪዎችን ያሰለፈ ሲሆን በአማራዉ ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በቤኔሻንጉልና በሶማሌ ክልል ምንም ተወዳዳሪዎችን አላስመዘገበም።
ከመድረክ ቀጥሎ ብዙ ቁጥር ያስመዘገበው ኢዴፓ ሲሆንም ፣ ለ127 መቀመጫዎች (23%) ተወዳዳሪዎችን አስመዝግቧል።
በዚህ መሰረት ገዢው ፓርቲ ድምጽ መስረቁ አይቀርም እንጂ፣ ካሰመዘገባቸው 345 የፓርላማ አባላት 274 ቱን ( 80% ) ማሸነፍ ከቻለ ስልጠና የመያዝ እድል ይኖረዋል። እንድ እመድረክ፣ ኢዴፓና ሌሎች ያሰለፏቸውን በሙሉ መቶ በመቶ ቢያሸንፉም ስልጣን መያዝ አይችሉም

ሰበር ዜና – የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በዕጩነት እንዳይቀርቡ ተደረገ

‹‹ምርጫ በህዝብ ፍላጎት ሳይሆን በሎተሪ ሆኗል›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት

አዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 5 ለመጭው ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ሊቀርቡ የነበሩት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ‹‹ከቀረቡት 17 ዕጩዎች መካከል በተጣለ ዕጣ ወድቀዋል›› በመባላቸው ለመጭው ምርጫ በዕጩነት እንዳይቀርቡ መደረጋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል በዕጩነት በቀረቡበት ወረዳ 5 የምርጫ ጣቢያ ኢህአዴግ፣ የትግስቱ አንድነት፣ ቅንጅትን ጨምሮ ሌሎች ስድስት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ያለ ምንም ዕጣ አልፈዋል የተባለ ሲሆን ‹‹የሚያልፉት በዕጣ ነው›› የተባሉት ሰማያዊን ጨምሮ 11 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች መካከል ሰማያዊና ሌሎች አራት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ‹‹ዕጣ አልወጣላቸውም፡፡›› ተብሏል፡

ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ‹‹ሰማያዊ ህዝብ ውስጥ በሰፊው እየገባና እያንቀሳቀሰ ያለ ግንባር ቀደም ፓርቲ ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ ያሉን ጨምሮ ዕጣ ውስጥ አይገቡም፡፡ ሰማያዊ ደግሞ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ከማያደርጉት ፓርቲዎች ጋር ዕጣ ውስጥ ገብቶ ወደቀ መባሉ ዴሞክራሲ ከጅምሩ ጀምሮ የህዝብ ድምጽ ሆኖ እያለ በእኛ አገር ሎተሪ ሆኗል ማለት ነው፡፡›› ብለዋል

ሊቀመንበሩ አክለውም ‹‹ሂደቱ ምንም ይሁን ምን አንድን ፓርቲ ወይንም ተወካይን ህዝብ ነው መምረጥ ያለበት፡፡ ህዝብ የሚፈልገውና የሚመረጥ ፓርቲ ነው ለምርጫ መቅረብ ያለበት፡፡ አሁን ግን እየተባለ ያለው በአንድ በኩል ህዝብ የማይፈልገው ያለ ዕጣ ሲገባ፣ በሌላ በኩል ህዝብ የሚፈልገው ሰማያዊን የመሰለ ፓርቲ ዕጣ ውስጥ ገብቶ አላለፈም እየተባለ ነው፡፡ በአንድ በኩል ህዝብ የተማረረባቸው ያለ ቅድመ ሁኔታ ህዝብን እንደሚያንቀሳቅስ የሚታወቀው ሰማያዊ ደግሞ ህዝብ ስፈለገው አሊያም በጥንካሬው ሳይሆን በሎተሪ ወድቀሃል ተብሏል›› ሂደቱ የተሳሳተ ነው ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

Friday, February 20, 2015

ምርጫ ቦርድ ከ200 በላይ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎችን ሰረዘ

‹‹ምርጫ ቦርድ ሰማያዊ በምርጫ ሂደቱ እንዲቆይ አይፈልግም›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
ሰማያዊ ፓርቲ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከ200 በላይ ዕጩዎቹ በምርጫ ቦርድ ትዕዛዝ እንደተሰረዙበት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በመላ አገሪቱ በተለይም በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በወላይታ፣ በቤንች ማጅ፣ በምዕ/ጎጃም፣ በሲዳማ፣ በከምባታ፣ በጋሞጎፋ፣ አዲስ አበባ፣ በደቡብ ጎንደርና ጉጅን ጨምሮ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ከ200 በላይ ዕጩዎቹ አንድን ዕጩ ለመሰረዝ የሚያበቃ ምንም አይነት ህጋዊ ምክንያት ሳይኖር ‹‹ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ታዘናል›› በማለት ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤትና ለክልል ምክር ቤቶች ያስመዘገብናቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎቹን በመሰረዝ ከምርጫው ውድድር ውጪ እንዲሆኑ እየተደረገ እንደሆነ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ገልጸዋል፡፡
በየክፍለ ሀገሩ የተሰረዙት ዕጩዎች ‹‹ፓርቲው ትብብር የሚባል ህገ ወጥ አደረጃጀት መስርቷል፣ የሌሎች ፓርቲዎች አባላት ናችሁ›› የመሳሰሉ ምክንያቶችና ደብዳቤ የተሰጣቸው ሲሆን በአንጻሩ በአዲስ አበባ የተሰረዙት ዕጩዎች ከምርጫ አስፈጻሚዎች ምንም አይነት ምክንያትና ደብዳቤ እንዳልተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዕጩዎቹ ‹‹የተሰረዝንበትን ምክንያት ንገሩን፣ ደብዳቤ ልትሰጡን ይገባል›› ቢሉም የምርጫ አስፈጻሚዎቹ ‹‹እኛ እናንተን ለመመዝገብ ችግር የለብንም፡፡ ግን ከበላይ አካል እንዳንመዘግብ ተነግሮናል፡፡ ደብዳቤም ልንሰጣችሁ አንችልም፡፡›› የሚል መልስ እንደሰጧው ተግልጾአል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች መሰረዛቸውን ተከትሎ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የቦርዱን ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃናን ለማግኘት ቢጥሩም ‹‹ከከተማ ውጭ ናቸው፡፡ አሁን አታገኟቸውም›› የተባሉ ሲሆን ፕ/ር መርጋ የህወሓትን 40ኛ አመት ለማክበር መቀሌ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በትናንትናው ዕለት በጉዳዩ ላይ ከቦርዱ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ዱፌሳ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን አቶ ነጋ ‹‹ማመልከቻ አስገቡ›› ከማለት ውጭ ዕጩዎቹ ለመሰረዛቸው ተጨባጭ ምክንያት መስጠት እንዳልቻሉ ኢ/ር ይልቃል ገልጸውልናል፡፡
‹‹የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎችን ያለ አግባብ የሚሰርዙት ሰማያዊ በምርጫ ሂደቱ ጫና መፍጠር ስለሚችል በሂደቱ እንዲቆ ስለማይፈልጉ ነው›› ያሉት ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት፤ ሆኖም ይህ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ለነጻነት የሚያደርጉትን ትግል ትክክለኛ እንደሆነ እንዳስረገጠላቸው፣ ይህን የነጻነት ትግልም አጠናክረው እንደሚቀጥሉና የካቲት 22 ፓርቲያቸው ከትብብሩ ፓርቲዎች ጋር በ15 ከተሞች በተመሳሳይ ጊዜ በ15 ከተሞች የሚያደርገው ሰልፍ የዚሁ የነጻነት ትግል አካል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/39143#sthash.A3O53duo.dpuf

Wednesday, February 18, 2015

ፍርድ ቤቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አቤቱታ ላይ ቀጠሮ ሰጠ

የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በዘላለም ወርቃገኘው ክስ መዝገብ የተከሰሱት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በማረሚያ ቤት አስተዳደር ላይ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 25/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጠ፡፡ በዛሬው ችሎት የተከሳሾቹ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ‹‹ህዳር 12 ለ 13/2007 ዓ.ም አጥቢያ ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎ የተጠርጣሪዎቹ ንብረት ተወስዶባቸዋል፣ የሰብአዊ ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል፣ ድንገተኛ ፍተሻው ህገ ወጥ ነው›› በሚል በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ላይ ላቀረቡት አቤቱታዎች ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን መልስ ሰምቷል፡፡
የማረሚያ ቤቱ መልስ በጽሁፍ ከቀረበ በኋላ በቃልም እንዲቀርብ በታዘዘው መሰረት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የቀጠሮ ማረፊያ አስተዳደር አስተዳዳሪ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አምባዬ ክቡር ፍተሻው መካሄዱን አምነው ነገር ግን፤ ‹‹ፍተሻው የተከናወነው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከጠዋቱ 12 ሰዓት በኋላ ነው፡፡ ፍተሸውም በአቤቱታው ላይ እንደቀረበው ባልታወቁ ሰዎች ሳይሆን በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጥበቃዎች ነው የተከናወነው›› ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡ የፍተሻውን አላማም ‹‹የታራሚዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የተከለከሉ ነገሮችን ፈትሾ ለማስወገድ ነው፡፡ በፍተሸውም ሚስማር፣ ስለት ነገሮች፣ እንዲሁም ብጥብጥ የሚቀሰቅሱ ጽሁፎች ተገኝተዋል፡፡›› ብለዋል፡፡
ባለፈው የአብዛኛዎቹ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ውድቅ ሲደረግ የ7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን፣ እንዲሁም 8ኛ ተከሳሽ ሰለሞን ግርማ የተወሰኑ የክስ ማሻሻያዎች እንዲያደርግ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረት በዛሬው ዕለት በሁለቱ ተከሳሾች ላይ አሻሽየዋለሁ ያለውን ክስ አቃቤ ህግ ይዞ ቀርቦ በንባብ አሰምቷል፡፡
በመጨረሻም በፍተሻው ወቅት ተፈጽሟል በሚል በተከሳሾቹ ጠበቃ የቀረበውን አቤቱታና ማረሚያ ቤቱ የሰጠውን መልስ አገናዝቦ ውሳኔ ለመስጠት እንዲሁም፤ በሁለቱ ተከሳሾች ላይ የቀረበው ማሻሻያ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ‹‹ተሸሽለዋል ወይንም አልተሸሻሉም›› የሚለውን ለመወሰን ለየካቲት 25/2007 ዓ.ም ጠዋት 3 ሰዓት ላይ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Tuesday, February 17, 2015

‹‹ሰላማዊ ትግሉ ሲጠናከር ስርዓቱ ወደ አውሬነት ይቀየራል›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት

• ‹‹ቃል (በዛሬው ዕለት ለቀድሞው የአንድነት አመራሮችና አባላት የተዘጋጀው የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ላይ ከተናገሩት)


(ነገረ-ኢትዮጵያ) ፓርቲ ጣኦት አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ቅንጅትንም አፍርሶታል፡፡ አንድነትንም አልፈረሰም ብለው እንዳይከሱኝ እንጅ አፍርሰውታል ማለት እችላለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሰማያዊ ላይም አንድ ነገር ማምጣታቸው የማይቀር ነው፡፡ ያ ማለት ግን ሰላማዊ ትግሉ ምን ያህል እንዳስፈራቸው ነው የሚያሳየው፡፡ አገዛዙ በፓርቲዎች ላይ የሚወስደው እርምጃ የሚያሳየው ሰላማዊ ትግሉ መጠናከሩን እንጅ ወደኋላ መመለሱን አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ እንዲህ አይነት ችግር ሲከሰት ሰላማዊ ትግሉ አበቃለት ይላሉ፡፡ ሆኖም አገዛዙ ሰላማዊ ትግል አስፈርቶት አውሬ ሲሆን የሚያረጋግጥልን ሰላማዊ ትግሉ መጠናከሩን ነው፡፡

በመሳሪያ ትግል ውስጥ አንድ ጀኔራል ሲሞት አሊያም አንድ የጦሩ አካል ችግር ሲደርስበት ‹‹የትጥቅ ትግል አበቃለት›› እንደማይባለው ሁሉ ሰላማዊ ትግል ላይ አንድ ጫና ወይንም የስርዓቱ ደባ ሲከሰት ትግሉ አይሰራም ማለት አይደለም፡፡

ሰላማዊ ትግል መስዋዕትነት አያስከፍልም ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ሰላማዊ ትግል ውጤት ማምጣት ሲጀምር፣ ዙሩም ሲካረር፣ የሚከፈለው ዋጋም ይበልጥ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ የስርዓቱ አውሬነት በተገለጠ ቁጥር፣ እኛም በተሻለ አመራር ትግሉን ስንመራው መስዋዕትነቱ ይበልጡን እየበዛ እንደሚመጣ እንረዳለን፡፡

ተመስገን ደሳለኝ ምልክታችን ነው! – ከበድሉ ዋቅጅራ

ተመስገን ደሳለኝ ምልክታችን ነው፤ ልንሸፍነው ያልቻልነው ምልክት፡፡ ተመስገን የተከሰሰውና የተፈረደበት ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት አለው ወይም ደግሞ አሸባሪ ነው ተብሎ አይደለም፤ የተከሰሰውም የሶስት አመት እስር የተፈረደበትም በጻፈው ጽሁፍ ነው፡፡ በመሆኑም ተመስገን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ህገመንግስታዊ መብታችን ያለመከበር ምልክት ነው፡፡ ተመስገን ጠንካራ ግለሰባዊ ሰብእናውንና ህገመንግስታዊ መብቱን በመጠቀም፣ ለዚህች ሀገርና ለህዝቦቿ ይበጃል ያለውን ሀሳብ ለመግለገልጽና በሰላማዊ መንገድ ለመሟገት አፍላ የወጣትነት እድሜው ያላጓጓው ዜጋ ነው፡፡ በመሆኑም ተመስገን የ‹መሬት ላራሹንና የብሄረሰቦችን መብት ጥያቄ አንግበው በነሳት ላመኑበት እንደታገሉት አይነት ወጣቶች ዛሬም ለመኖራቸው ምልክት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ተመስገን የዘመን ተሻጋሪው ኢትዮጵዊ አስተሳሰባችንና ስብእናችን አጋላጭ ምልክት ነው፡፡ በዘመነ ፊውዳሊዝም ለተገኘው ለውጥ (ትሩፋቱ በጎም ይሁን ክፉ) መስዋእትነት የከፈሉት ጥቂቶች ናቸው፡፡ በደርግ አብዮታዊ አገዛዝ ዘመንም የታሰሩት፣ ተገድለው የተጣሉት፣ ለትግል የወየኑት፣ የተሰደዱት ጥቂቶች ናቸው፡፡ አሁንም ከዚሁ የተለየ አይደለም፤ ስለህዝባችንና ሀገራችን፣ ስለፖለቲካዊው አስተዳደራችን ያገባናል ብለው በድፍረት መንግስትን የሚሞግቱት ጥቂቶች ናቸው፡፡ በሶስቱም ዘመን በአጋጣሚው ተጠቅመው ሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅምን፣ በአንድ እንጀራ አፉን ለሚዘጋ ወስፋታቸው ጩኸትና በቃኝ ለማያውቅ ፍትወተ-ንዋይ ማርኪያ የተጠቀሙበት በርካቶች ናቸው፡፡ አብዛኛው ህዝብ ግን በገዢዎቹ የጭካኔ ድንኳን ውስጥ በፍርሀት ተደቅድቆ ‹‹በአያገባኝም›› እንዳላዘነ አለ፡፡ ይህ ህዝብ ስለልጁ መረሸን አልጠየቀም፤ አላለቀሰም፡፡ በገዢዎቹ የሚጣሉበትን አዋጆች ይቆጥራል እንጂ፣ በአዋጆቹ ስለሚያጣው መብቱ ወይም ስለሚያጎናጽፉት ትሩፋት አይጠይቅም፡፡ ይህ ህዝብ እያጨበጨበ የሚፈጥራቸውን ተሟጋቾቹን (ጀግኖቹን) እራሱን እየነቀነቀ ወደ እስር ቤት፣እያለቀሰ ወደ ቀብር ከመሸኘት በቀር ‹‹ለምን?›› ብሎ አይጠይቅም፡፡ በመሆኑም ተመስገንና ሌሎች ሀሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ ሲገልጹ፣ ለእስርና ለስደት የተዳረጉ ዜጎች፣ የዚህ ከዘመን ጋር እየሰለጠነና እየዳበረ የመጣ ጸያፍ ኢትዮጵያዊ ስብእና አሉታዊ ምልክቶች ናቸው፡፡

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የትግል ጥሪ አስተላለፈ

የ9ኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል መርህ የሁለተኛ ዙር የሠላማዊ ትግል ጥሪውን ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስተላለፈ፡፡ ትብብሩ የካቲት 15 ቀን 2007 ዓ.ም በተመሳሳይ ሰዓት በ15 ከተሞች ሊያደርገው አቅዶት የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ በሳምንት አራዝሞ ለየካቲት 22 ቀን 2007 ዓ.ም ማስተላለፉንም አስታውቋል፡፡
ትብብሩ ዛሬ የካቲት 10 ቀን 2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በሰጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ገዢው ፓርቲ የቱንም ያህል አሰቃቂና አረመኔያዊ የአፈና እርምጃዎች ቢወስድም የህዝብ ጥያቄዎች እስካልተመለሱ ድረስ ህዝባዊ ትግሉን ማዳፈን እንጂ ማስቆም እንደማይችል ይልቁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከተለያዩ የህዝብ እንቅስቃሴዎች መገንዘቡን ገልጹዋል፡፡ ትብብሩ ምርጫን በተመለከተ እንዳስታወቀው ኢህአዴግ ስለመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከቃላት ያለፈ እምነትም ሆነ ቁርጠኝነት የሌለው መሆኑን በዚህ የምርጫ ወቅት በተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ እየወሰደ ያለው ህገ-ወጥ እርምጃ ማሳያ ነው ብሏል፡፡
‹‹ለውጡ የሚመጣባቸው አምባገነኖች ድንገተኛ ከፍተኛ ፍርኃትና ሥጋት በማሳደሩ ህገ-መንግሥቱን በመጨፍለቅ በግልጽና በአደባባይ ህገ-ወጥ ውሳኔዎችንና እርምጃዎችን ለመውሰድ መገደዳቸው፣ ይህም የህዝቡን የለውጥ ፍላጎትና የትግል ተነሳሽነት በማሳደግ ህዝባዊውን ትግል ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገሩ የበለጠ ግልጽ ሆኗል›› ብሏል ትብብሩ፡፡
ትብብሩ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ የአገራችንና ዜጓቿ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በሁለት አማራጮች ላይ የተንጠለጠለ ነው ያለው መግለጫው፣ አንድም ያለውን አምባገነናዊ ሥርዓት ተቀብሎ የጭቆና ቀንበር ተሸክሞ በከፋ ውርደት ሥር ሰጥ- ለጥ ብሎ መገዛት፣ አሊያም አምባገነንነትና ጭቆናን ‹‹በቃ›› በማለት በሕዝባዊ የተቀናጀ ሰላማዊ ትግል ለአገራችን ሉዓላዊነትና የዜግነት ክብራችንን ለማስመለስ በህገ መንግስታዊ መብታችን ተጠቅመን ትግላችንን እስከማይቀረው ለውጥ ድል ደጃፍ ድረስ በቆራጥነት መቀጠል ናቸው ብሏል፡፡
በዚህም ትብብሩ ህገ-መንግስታዊ መብትን በመጠቀም በህግና በሥርዓት ትግሉን ለመምራት መዘጋጀቱን በመግለጽ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የትግል ጥሪውን እንዲቀላቀሉት አሳስቧል፡፡ ስለሆነም ትብብሩ ‹‹ኢህአዴግነት ከዜግነት በላይ›› ለሆነባቸው የሥራ ዋስትናቸው፣ ዕድገትም ሆነ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች በሙያቸው፣ በልምዳቸው፣ ክህሎታቸው፣ በመሳሰሉት ባልተመሰረተ መልኩ በደል እየደረሰባቸው ላሉ ሁሉ የትግል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
‹‹የህወኃት/ኢህአዴግ ተራ አባላትና ካድሬዎች፤ የፖለቲካ ልዩነት የተለያየ አመለካከትና ሀሳብ ማራመድ ጤናማ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ መገለጫ እንጂ እንደሚነገራችሁ ‹‹ጠላትነት›› ባለመሆኑ፣ ትግላችንም ለሠላማዊና ህጋዊ የሥልጣን ሽግግር እንጂ በናንተ ‹‹መቃብር›› ላይ አዲሱን ሥርዓት የማቆም፣ የነበረውን አጥፍቶ ከዜሮ የመጀመርና እናንተን የማጥፋት ዓላማ እንደሌለው ተረድታችሁ፣ ተቃዋሚዎች እንደናንተው ኢትዮጵያዊያንና ለኢትዮጵያና ህዝቧ የሚጨነቁ መሆናቸውን በመረዳት ተቃዋሚዎችን እንደ‹‹ ጠላት›› ከመመልከት አስተሳሰብ ራሳችሁን ነጻ እንድታወጡ›› ሲልም ትብብሩ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ወጣቶችና ሴቶች በተለይም የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች፣ መምህራንና ተማሪዎች በተለይም የዩኒቨርስቲና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ የእምነት ነጻነት መብት ጠያቂ የማኅበረሰብ አባላት፣ የመገናኛ ብዙሃን አባላት፣ የፍትህ አካላት፣ የዴሞክራቲክ ፓርቲዎች አባላት፣ የነጻነትና የዴሞክራሲ ሰላማዊ ታጋዮች፣ በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵዊያን/ዲያስፖራዎች እና ሌሎችም ጥሪው የተላለፈላቸው አካላት መሆናቸውን መግለጫው አትቷል፡፡
በመሆኑም፣ ‹‹በምናርገው አገራዊ፣ ሰላማዊና ሕዝባዊ ትግል በማይቀረው የሥርዓት ለውጥ ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በአንድነትና በቆራጥነት እንድትሰለፉ፤ የካቲት 22/07 በየከተሞቹ በቦታውና በሰዓቱ እንድትገኙ ጥሪያችንን አበክረን እናቀርባለን›› ብሏል የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር፡፡

Sunday, February 15, 2015

የ2007ቱን ሀገራዊ ምርጫ ሂደት እና ከምርጫዉ ዉጭ ያሉ አዋጭ አማራጮችን በተመለከተ የአርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የአቋም መግለጫ

አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላማዊ፣ ተዓማኒና ፍትሀዊ በሆነ ምርጫ የማይፈልጋቸውን መሪዎች መሻር፤ የሚፈልጋቸውን ደግሞ መሾም የሚያስችሉትን መሠረቶች ለመጣል የሚታገል ንቅናቄ ነው። እንደሚታወቀው የሕዝብ እውነተኛ ፍላጎት የሚገለጽበት እውነተኛ ምርጫ እንዲኖር ገለልተኛና ቀልጣፋ የፍትህ ሥርዓት፣ የጦርና የፓሊስ ሠራዊት ሊኖሩ ይገባል። ነፃ የሚዲያ ተቋማትና በነፃነት የሚንቀሳቀሱ የሲቪክ ማኅበራት መኖርም መታለፍ የሌለባቸው አቢይ ጉዳዮች ናቸው። አማራጭ ፓሊሲዎችን ማቅረብ የሚችሉ በነፃነት የሚንቀሳቀሱ የፓለቲካ ፓርቲዎች ከሌሉም አማራጮች የሉምና ምርጫ ትርጉም የለውም። ይህ ሁሉ ቢሟላ እንኳን ምርጫውን የሚያስፈጽመው አካል ገለልተኛ፣ ሀቀኛና ተዓማኒ ካልሆነ የሚደረገው ምርጫ የመራጩን ሕዝብ ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ሊሆን አይችልም።

ከላይ የተዘረዘሩትን የምርጫ እሴቶች ሙሉ በሙሉ ባይሆንም እንኳን የተወሰኑትን በመጠኑም ቢሆን ያካተተ ምርጫ እንዲኖር መጣርና በሂደት የምርጫውን አፈፃፀም ማሻሻል ይቻል ይሆናል በሚል እምነት የዲሞክራሲ ኃይሎች በህወሓት የሴራ ምርጫዎች ሲሳተፉ ቆይተዋል። ሆኖም በህወሓትና በእውነተኛ ምርጫ መካከል ያለው ተቃርኖ እያደር እየሰፋ ሲሄድ እንጂ ሲጠብ አልታየም። በህወሓት ሙሉ ቁጥጥር ስር በሚካሄድ ምርጫ ኢትዮጵያን የሚጠቅም ለውጥ ሊመጣ ይችላል የሚለው እምነት ለአርበኞች ግንቦት 7 ፈጽሞ የተሟጠጠው ከምርጫ 97 ማግስት ጀምሮ ነው። በግንቦት 7 ቀን 1997 ዓም የኢትዮጵያ ሕዝብ በታላቅ የለውጥ ተስፋ የሰጠው ድምጽ በህወሓት የተዘረፈው ከላይ የተዘረዘሩት ተቋማት ያልነበሩ በመሆናቸው፤ ስለዚህም ከምርጫ በፊት ተቋማቱን መገንባት፤ ተቋማቱን ለመገንባት ደግሞ ህወሓትን ከስልጣን ማስወገድ ይገባል ብሎ በማመኑ ነው አርበኞች ግንቦት 7 በሁለገብ የትግል ስልት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው።

Wednesday, February 11, 2015

ለወያኔ ዉንብድና መልሱ ህዝባዊ እምቢተኝነትና ህዝባዊ አመጽ ነዉ!

ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎ የኢትዮጵያን በትረ ስልጣን ጨብጠዉ በኖሩባቸዉ ባለፉት ሃያ አራት አመታት የአገራችን የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እጅግ በጣም ከዘቀጠና ከረከሰ የወያኔ ድራማ ዉጭ ሌላ ምንም ነገር የማይታይበት አለባሌ መድረክ አድረገዉት ቆይተዋል አሁንም እያደረጉት ነዉ። አንድ ቋንቋ የሚናገሩትና ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸዉ የወያኔ መሪዎች ኢህአዴግ የሚባል አጋሰስ የሽፋን ድርጅት ፈጥረዉ በኢትዮጵያ ህዝብ ሰብዓዊ መብትና ነጻነትና ላይ ተነግሮም ተጽፎም የማያልቅ ግዙፍ ግፍና በደል ፈጽመዋል። ህጻን፤አዛዉንት፤ ወንድና ሴት ሳይለዩ መብቴን አትንኩ ያለቸዉን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያለምንም ርህራሄ በጥይት ጨፍጭፈዋል። ሴቶች እሀቶቻችንን እጅና እግራቸዉን አስረዉ ጡታቸዉን በመቆንጠጫ እየቆነጠጡ በሴትነታቸዉ ላይ የዉርደት ተግባር ፈጽመዋል። ወንዶች ወንድሞቻችንን ደግሞ ዉስጥ እግራቸዉን ገልብጠዉ እየገረፉ ጥፍራቸዉን አይናቸዉ እያየ በጉጠት እየሳቡ ነቅለዋል። ባጠቃላይ የወያኔ ዘረኞች በዛሬዉ ዘመን አንኳን ወገን በወገኑ ላይ የዉጭ ጠላትም በህዝብ ላይ የማይፈጽመዉ በደል በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ፍጽመዋል።

ወያኔ ስልጣን እንደያዘ “አባይ ትግራይ” ወይም “ታላቋ ትግራይ” የሚለዉን ህልሙን ለማሳካት ወልቃይት ጠገዴን ከጎንደር ቆርሶ ከትግራይ ጋር ቀላቅሏል። ስልጣን ይዞ ከተደላደለ ከአመታት በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያን ገበሬ ከመሬቱ አፈናቅሎ ለምለም መሬቱን በርካሽ ዋጋ ለባዕዳን ሽጧል፤ ከዚህ አልፎ ተርፎም የአባቶቻችን አጽም ያረፈበትን የአገራችን ዳር ድንበር ቆርሶ ለጎረቤት አገር ገጸ በረከት አቅርቧል። ይህ አገራቸዉንና የሚመሩትን ህዝብ በሚጠሉ ጠባቦች የተሞላ ድርጀት ባለፈዉ ሳምንት የኢትዮጵያን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ደጋፊዎቹንና በአንቀልባ ታዝለዉ አስከዛሬ ያቆዩትን ምዕራባዉያን ጭምር ግራ ያጋባ ፀረ አገርና ፀረ ህዝብ እርምጃ ወስዷል። ድርጅት እያፈረሰና በፓርቲ ላይ የራሱን ተለጣፊ ፓርቲ እያቋቋመ ዛሬ ላይ የደረሰዉ ወያኔ ምርጫ የሚባል ድራማ በደረሰ ቁጥር የሚይዘዉ በሽታ ዘንድሮም ይዞት አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲንና መላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትን አፍርሶ በምትካቸዉ የራሱን መኢአድና የራሱን አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ፈጥሯል። ይህ ወያኔ ከሰሞኑ የወሰደዉ የፖለቲካ እርምጃ በየትኛዉም አለም በተለይ የመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዐትን እንከተላለን በሚሉ አገሮች ዉስጥ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ እጅግ በጣም ትልቅ የፖለቲካ ሸፍጥ ነዉ።

የወያኔን ታሪክ ተወልዶ ካደገበት ከደደቢት በረሃ እስከ ሚኒልክ ቤ/መንግስት ድረስ ያደረገዉን ጉዞ ስንመለከት ወለል ብሎ የሚታየን አንድ ሐቅ አለ፤ እሱም ወያኔ ሁሉንም ነገር በዘር መነጽር ብቻ የሚመለከትና ህዝብን በወዳጅና በጠላት ጎራ ለይቶ ወዳጅ አይደለም ያለዉን ሁሉ እንደ ሩሲያዊዉ ዮሴፍ ስታሊን እየገደለ የመጣ ድርጅት ነዉ። በእርግጥም ወያኔ ጫካ ዉስጥ እያለም ሆነ ዛሬ ከተማ ገብቶ የሚቃወመዉንና በሀሳብ የማይግባባዉን ድርጅትም ሆነ ግለሰብ እያፈረሰና እገደለ ባፈረሳቸዉ ድርጅቶች ምትክ ደግሞ የራሱን ተለጣፊ ድርጅት እየፈጠረ የመጣና ከዲሞክራሲያዊ አሠራርና ከስልጣኔ ጋር የማይተዋቅ ድርጅት ነዉ።

በመርፌ የተጠቃቀመ ቁምጣና ጥብቆ ለብሶ አስራ ሰባት አመት ጫካ ለጫካ የተጓዘዉ ወያኔ ጎንደር፤ ጎጃምና አምቦ እያለ ወደ አዲስ አበባ ሲጠጋ ከተገነዘባቸዉ ነገሮች አንዱ የለበሰዉ የተጠቃቀመ ቁምጣ የትም እንደማያደርሰዉና ለከተማ ኑሮ የሚስማማ አዲስ ልብስ እንደሚያሰፈልገዉ ማዉቁ ነዉ። በጥላቻ ተረግዞ በክፋት ላደገዉ ወያኔ ቢበቃዉም ባይበቃዉም ወይም ቢያምርበትም ባያምርበትም ይህንን ለከተማ ዉስጥ ኑሮ የሚያስፈልገዉን አዲስ ልብስ ለማዘጋጀት ብዙ ግዜ እልወሰደበትም። የሚሰርቅና የሚስቅ ምን ግዜም ተባባሪ አያጣም እንዲሉ ወያኔ የአዲስ አበባን መሬት የረገጠዉ ጦር ሜዳ ላይ የማረካቸዉን ወታደሮችና አገር ዉስጥ ያገኛቸዉን ደካማ ሰዎች ሰብስቦ በፈጠረዉ ኢህአዴግ በሚባል ፈረስ ጀርባ ላይ ተፈናጥጦ ነበር። ትግራይን ነጻ አወጣለሁ ብሎ ትግል የጀመረዉ ወያኔ ኢህአዴግን የፈጠረዉ ወያኔነቱን ለመተዉ ሳይሆን እራሱን በዚህ በኢትዮጵያ ስም በፈጠረዉ ድርጅት ዉስጥ ሸሽጎ እዉነተኛ ባህሪዩን ለመደበቅ ነበር።

Sunday, February 1, 2015

የሰላም በሮች ሲዘጉ የሁለገብ ትግል ስልት በሮች ይከፈታሉ!!!

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በምርጫ ቦርድ አማካይነት እየደረሰበት ያለውን በደል ለሕዝብ ለማሰማት ጥር 17 ቀን 2007 ዓም በአዲስ አበባ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጂንካና ሸዋ ሮቢት የተቃውሞ ሰልፎችን ጠርቶ ነበር። በተለይ በአዲስ አበባው ሰልፍ ላይ የተገኙ ወገኖቻችን ለህወሓት ፍጹም ታማኝ በሆነው የፓሊስ ክፍል ያለርህራሄ መደብደባቸው እና የተቃውሞ ሰልፉም በጉልበት መበተኑ ነፃነትና ፍትህ ናፋቂውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳዘነ ብቻ ሳይሆነ ያስቆጨ ጉዳይ ነው። በመላው ዓለም በሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የተለመደውን ድንጋይ ውርወራ እንኳን ሳይከጅሉ፤ የፓሊሶችን ሰብዓዊ ርህራሄ ለማግኘት “ፓሊስ የኛ ነው” እያሉ እየዘመሩ በፓሊስ ተደበደቡ። ሴቶችና አዛውንት ብቻ ሳይሆን ተላላፊ መንገደኞች እንኳን ከፓሊስ ዱላ አላመለጡም። ከሁሉም በላይ የሚዘገንነው ደግሞ የ 7 ወራት ነብሰ ጡር ሴትም በፓሊስ መመታትዋና ሆዷ መረገጡ ነው። ይህ እኩይ ተግባር የሚፈጥረው ቁጭት በህወሓት ላይ ብቻ አያበቃም። ትዝብቱ ለፓሊስም ተርፏል። ይህ የጭካኔ ተግባር ለፍትህና ለነፃነት በሚደረገው ትግል የሕዝብ አጋር ይሆናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የፓሊስ ሠራዊትን የሚያዋርድ ነው። ደካማ እናቶችን፣ አረጋዊያንን፣ ባዶ እጃቸውን ተቃውሞ እያሰሙ ያሉትን ወጣቶችንና ነፍሰጡሮችን በጭካኔ መደብደብ ለራሱና ለሥራው ክብር ለሚሰማው ፓሊስ ውርደት ነው፤ የሞት ሞት ነው። የኢትዮጵያ የፓሊስ ሠራዊት አባላት ተግባራቸው ያሳፍራቸዋል፣ ይቆጫቸዋል፤ ቁጭታቸውንም ይህን ትዕዛዝ በሰጡ አለቆቻቸው ላይ በግልም ሆነ በተደራጀ መንገድ በሚወስዱት እርምጃ እናያለን ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ ያደርጋል።

የጥር 17 ቀን 2007ቱ ሽብር በአንድ ወቅት የተፈጠረ፤ በአንድነት ፓርቲ ላይ ብቻ ያነጣጠረ፣ የተናጠል ክስተት ሳይሆን ህወሓት ደግሞ ደጋግሞ ሲፈጽመው የነበረ ነው። ከዚህ በፊት በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ ፈጽሞታል። የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላንን በተቃወሙ የተለያዩ ዩንቨርስቲዎች ተማሪዎች በተለይም በአምቦ ላይ የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሽብር ነዝቷል። በቅርቡ ደግሞ በሰማያዊ ፓርቲ አባላት ላይ ተመሳሳይ አረመናዊ ድርጊት ፈጽሟል።

አርበኞች ግንቦት 7: ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የህወሓት ታጣቂዎች በወገኖቻችን ላይ ያደረሱትን ድብደባ፣ ህገወጥ እስር፣ እና የተቃውሞ ሰልፍ ክልከላን አጥብቆ ይቃወማል። አርበኞች ግንቦት 7፣ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው ህመም ህመሙ፣ ቁስላቸው ቁስሉ ነው።

ባለፉት ሃያ ሶስት ተከታታይ ዓመታት፣ በአምቦ፣ በጅማና በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞችና ገጠሮች፣ በባህዳር፣በጎንደርና በበርካታ የአማራ ከተሞችና ገጠሮች፣ በጋምቤላ፣ በሶማሊ፣ በአፋር፤ በአጠቃላይ በመላው ኢትዮጵያ በየአስፋልቱ፣ በየሜዳውና በየጥሻው በህወሓትና ተላላኪዎቻቸው የፈሰሰው የኢትዮጵያውያን ደም በከንቱ ፈሶ መቅረት የለበትም ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 በጽኑ ያምናል። አርበኞች ግንቦት 7 ከሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር በመተባበር የህወሓትን እድሜ በማሳጠር የእናቶቻችን እምባ ሊያብስ ዝግጁ ነው። አርበኞች ግንቦት 7 ኢትዮጵዊያን እንደከብት እየተደበደቡ ወደ ማጎሪያ የሚያጋዙበት እና በጠገቡ ሰላዮችና ፓሊሶች እየታነቁ የሚታረዱበት ጊዜ ማብቃት አለበት ይላል።

የቱን ያህል ቢለመንም ሆነ ቢወገዝ ህወሓት ለነፃ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒን ምርጫ ዝግጁ ሊሆን ቀርቶ በምርጫ የሚወዳደሩት ፓርቲዎች እነማን እንደሆኑና እነማን በእጩ ተወዳደሪነት መቅረብ እንዳለባቸው ሳይቀር የሚወስን ዓይን አውጣ አጭበርባሪ ድርጅት ነው። ይህንን ከዚህ በፊት አይተነዋል፤ አሁንም በአንድነትና በመኢአድ ላይ እየተደገመ ነው። ህወሓት፣ በየአምስቱ ዓመታቱ በሚያደርጋቸው የሴራ ምርጫዎች በሚቀጥሉት አርባና ከዚያም በላይ ለሆኑ ዓመታት በሥልጣን ላይ የሚቆይበትን ስልት ቀይሶ የሚንቀሳቀስ፤ ኢትዮጵያን ለብዙ ዓመታት ለመግዛት ማድረግ የሚችለውን ክፋት ሁሉ ከማድረግ የማይመለስ አገር በቀል ቅኝ ገዥ ነው። ህወሓት የዘረጋው ሥርዓት ህገ-አልባነት፣ ፀረ-ሕዝብነት እና አምባገንነት ለማጋለጥ በሚል ርህራሄን በማያውቁ የሥርዓቱ አገልጋዮች ፊት ባዶ እጅ መጋፈጥ የሚፈጥረው የሞራል የበላይነትና የመንፈስ ጀግንነት ባያጠራጥርም የሚያስከፍለው ዋጋ ከሚገኘው ውጤት ጋር ማመዛዘን ግን እጅግ ተገቢ የሆነ የማይታለፍ ሥራ ነው ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከህወሓት የሴራ ምርጫ ፋይዳ ያለው ውጤት ይገኛል ብሎ አይጠብቅም። ከምርጫው የሚፈልገው ውጤት አንድ ነገር ብቻ ነው፤ እሱም የመንግሥት ለውጥ ነው። ምርጫው በምርጫነቱ ወደ መንግሥት ለውጥ አያደርስም፤ ወደ መንግሥት ለውጥ ወደሚያመራ ሕዝባዊ አብዮት ሊያሸጋግር ግን ይችላል። ይህም ቢሆን የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በተለይም የሠራዊቱን ዓይነትና አደራጀጀት እግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ መታቀድ ይኖርበታል።

አርበኞች ግንቦት 7 የራሱን ጥናት አድርጎ ለኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ እና ህወሓትን ለመሰለ ጠላት የሚመጥን የትግል ስልት ሁሉንም የትግል ስልቶች እንደሁኔታው ያዳቀለ – ሁለገብ – መሆን ይኖርበታል ብሎ ወስኖ ለተግባራዊነቱ እየተንቀሳቀሰ ነው። ሁለገብ የትግል ስልት ሕዝባዊ ተቃውሞን፣ ሕዝባዊ እምቢተኝነትንና ሕዝባዊ አመጽን እንደወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ ማፈራረቅና ማደባለቅን ይፈልጋል። ሰላማዊ ትግል በተለይም ሕዝባዊ እምቢተኝነት ሲባል ደግሞ ህወሓት ያወጣቸው አፋኝ ህጎች እያከበሩ የሚደረግ አለመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ይረዳል። ሁለገብ ትግል በተቻለ መጠን የወገን ኃይል ራሱን ፈጽሞ መከላከል በማይችልበት ሁኔታ እንዳይገኝ ለማድረግ ይጥራል። በአርበኞች ግንቦት 7 እምነት ሁለገብ የትግል ስልት ሰፊ ተቀባይነት የሚያገኝበት ወቅት ደርሷል። ከዚህ በፊት “የሰላም በሮች ሲዘጉ የአመጽ በሮች ይከፈታሉ” ተብሎ በአንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ታጋይ የተነገረው “የሰላም በሮች ሲዘጉ የሁለገብ ትግል ስልት በሮች ይከፈታሉ” በሚል እንዲሻሻልና በዚህ ወለል ብሎ በተከፈተው በር ሁላችንም እንድንገባ አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል። በሁለገብ የትግል ስልት በሰላማዊ መንገድ የሚደረጉ የትግል ዓይነቶች አሉ፤ በሌላም መንገድ የሚደረጉ አሉ። ስለሆነም በሁለገብ ትግል እያንዳንዳችን እንደየዝንባሌዓችንና እንደየችሎታዎቻችን አስተዋጽኦ ልናበረክት የምንችልበት ሰፊ እድል ይከፍትልናል።

ስለሆነም፣ በዚህ አጋጣሚ አርበኞች ግንቦት 7፣ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለጦር ሠራዊትና ፓሊስ አባላት ወገናዊ ጥሪ ያደርጋል።

በህወሓት ዘረኛ አገዛዝ በሚደርስብን ውርደት፣ እንግልት፣ ስደት፣ ሥራ አጥነትና ድህነት የተማረራችሁ እና እኩልነቷ የተረጋገጠ፣ የበለፀገች ኢትዮጵያን ማየት የምትመኙ ሁሉ የሁለገብ የትግል ስልትን አዋጪነት እንድታጤኑ የዚሁ ስልት አካል ሆናችሁ እንድትታገሉ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።

የኢትዮጵያ የጦርና የፓሊስ ሠራዊት አባላት በግል ከሚደርስባችሁ ግፍ በተጨማሪ የገዛ ራሳችሁን ወገኖች መግደላችሁ፣ ማቁሰላችሁ፣ ማድማታችሁና መደብደባችሁ የህሊና እረፍት ሊነሳችሁ ይገባል። ህሊናችሁ እረፍት የሚያገኘው የሥርዓቱ እድሜ ሲያጥር መሆኑን በመገንዘብ ለገዛ ራሳችሁ ክብር፣ ለወገናችሁና ለአገራችሁ ስትሉ ፋሽስቱን ወያኔ ከድታችሁ ከአርበኞች ግንቦት 7 ኃይል ጋር ተቀላቀሉ።

እነዚህን ጥሪዎች ተግባራዊ ካደረግን ወገኖቻችን መሠረታዊ መብቶቻቸውን በመጠየቃቸው በመወደስ ፋንታ በፓሊስ ዱላ ሲደበደቡ የማናይበት ዘመን ይመጣል። ይህ ካልሆነ ግን “ውሀና መብራት አጣን” ብሎ አቤቱታ ማሰማት እንኳን በጥይት የሚያስገድልበት ቀን ይመጣል። ያ ከመሆኑ በፊት እንወስን፤ ራሳችንና አገራችን ከህወሓት ዘረኛ አገዛዝ ነፃ እናውጣ።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!