Tuesday, February 24, 2015
ጠበቃቸውን እንዳያገኙ የተከለከሉት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች በጨለማ ቤት መታሰራቸውን ገለጹ
(ነገረ ኢትዮጵያ) በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ የሚገኙት የሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀጠና/ዞን አመራሮች ለ16 ተከታታይ ቀናት በጨለማ ክፍል መታሰራቸውን ለፍርድ ቤት አስታወቁ፡፡ ዛሬ የካቲት 17 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀረቡት የሰማያዊ (የፓርቲው የጎንደር አደራጅ አቶ አግባው ሰጠኝ)፣ የአንድነት እና መኢአድ የዞን አመራሮች ‹‹መረጃ አውጡ፣ የደበቃችሁትን ሁሉ ተናገሩ›› እያሉ እንደሚደበድቧቸውና በጨለማ ክፍል እንዳሰሯቸው ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ አሁንም መረጃየን ሰብስቤ አልጨረስኩም በሚል ተጨማሪ 8 ቀናት ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ ተጠርጣዎቹ በማዕከላዊ እየደረሰባቸው የሚገኘውን ሰቆቃ አስመልክተው ለፍርድ ቤት አቤት ማለታቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የቀረበበትን አቤቱታ እንዲያስተካክል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በጎንደርና ጎጃም አካባቢዎች የዛሬ አራት ወር ገደማ በፖሊስ ታስረው ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ እንዲዛወሩ የተደረጉ ሲሆን፣ ጠበቃቸው በተደረገባቸው ክልከላ ምክንያት ተጠርጣሪዎቹን ካገኟቸው 2 ወር እንደሞላቸው ተናግረዋል፡፡ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አቶ አግባው ሰጠኝ እየተፈጸመበት ያለውን የመብት ጥሰት በመቃወም የርሃብ አድማ ላይ መሆኑ የታወቀ ሲሆን አድማውን ከጀመረ ሁለተኛ ቀኑ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው የጊዜ ቀጠሮ መሰረት አመራሮቹ የካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment