Friday, February 20, 2015

ምርጫ ቦርድ ከ200 በላይ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎችን ሰረዘ

‹‹ምርጫ ቦርድ ሰማያዊ በምርጫ ሂደቱ እንዲቆይ አይፈልግም›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
ሰማያዊ ፓርቲ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከ200 በላይ ዕጩዎቹ በምርጫ ቦርድ ትዕዛዝ እንደተሰረዙበት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በመላ አገሪቱ በተለይም በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በወላይታ፣ በቤንች ማጅ፣ በምዕ/ጎጃም፣ በሲዳማ፣ በከምባታ፣ በጋሞጎፋ፣ አዲስ አበባ፣ በደቡብ ጎንደርና ጉጅን ጨምሮ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ከ200 በላይ ዕጩዎቹ አንድን ዕጩ ለመሰረዝ የሚያበቃ ምንም አይነት ህጋዊ ምክንያት ሳይኖር ‹‹ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ታዘናል›› በማለት ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤትና ለክልል ምክር ቤቶች ያስመዘገብናቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎቹን በመሰረዝ ከምርጫው ውድድር ውጪ እንዲሆኑ እየተደረገ እንደሆነ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ገልጸዋል፡፡
በየክፍለ ሀገሩ የተሰረዙት ዕጩዎች ‹‹ፓርቲው ትብብር የሚባል ህገ ወጥ አደረጃጀት መስርቷል፣ የሌሎች ፓርቲዎች አባላት ናችሁ›› የመሳሰሉ ምክንያቶችና ደብዳቤ የተሰጣቸው ሲሆን በአንጻሩ በአዲስ አበባ የተሰረዙት ዕጩዎች ከምርጫ አስፈጻሚዎች ምንም አይነት ምክንያትና ደብዳቤ እንዳልተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዕጩዎቹ ‹‹የተሰረዝንበትን ምክንያት ንገሩን፣ ደብዳቤ ልትሰጡን ይገባል›› ቢሉም የምርጫ አስፈጻሚዎቹ ‹‹እኛ እናንተን ለመመዝገብ ችግር የለብንም፡፡ ግን ከበላይ አካል እንዳንመዘግብ ተነግሮናል፡፡ ደብዳቤም ልንሰጣችሁ አንችልም፡፡›› የሚል መልስ እንደሰጧው ተግልጾአል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች መሰረዛቸውን ተከትሎ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የቦርዱን ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃናን ለማግኘት ቢጥሩም ‹‹ከከተማ ውጭ ናቸው፡፡ አሁን አታገኟቸውም›› የተባሉ ሲሆን ፕ/ር መርጋ የህወሓትን 40ኛ አመት ለማክበር መቀሌ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በትናንትናው ዕለት በጉዳዩ ላይ ከቦርዱ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ዱፌሳ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን አቶ ነጋ ‹‹ማመልከቻ አስገቡ›› ከማለት ውጭ ዕጩዎቹ ለመሰረዛቸው ተጨባጭ ምክንያት መስጠት እንዳልቻሉ ኢ/ር ይልቃል ገልጸውልናል፡፡
‹‹የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎችን ያለ አግባብ የሚሰርዙት ሰማያዊ በምርጫ ሂደቱ ጫና መፍጠር ስለሚችል በሂደቱ እንዲቆ ስለማይፈልጉ ነው›› ያሉት ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት፤ ሆኖም ይህ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ለነጻነት የሚያደርጉትን ትግል ትክክለኛ እንደሆነ እንዳስረገጠላቸው፣ ይህን የነጻነት ትግልም አጠናክረው እንደሚቀጥሉና የካቲት 22 ፓርቲያቸው ከትብብሩ ፓርቲዎች ጋር በ15 ከተሞች በተመሳሳይ ጊዜ በ15 ከተሞች የሚያደርገው ሰልፍ የዚሁ የነጻነት ትግል አካል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/39143#sthash.A3O53duo.dpuf

No comments:

Post a Comment