• ‹‹ቃል (በዛሬው ዕለት ለቀድሞው የአንድነት አመራሮችና አባላት የተዘጋጀው የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ላይ ከተናገሩት)
(ነገረ-ኢትዮጵያ) ፓርቲ ጣኦት አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ቅንጅትንም አፍርሶታል፡፡ አንድነትንም አልፈረሰም ብለው እንዳይከሱኝ እንጅ አፍርሰውታል ማለት እችላለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሰማያዊ ላይም አንድ ነገር ማምጣታቸው የማይቀር ነው፡፡ ያ ማለት ግን ሰላማዊ ትግሉ ምን ያህል እንዳስፈራቸው ነው የሚያሳየው፡፡ አገዛዙ በፓርቲዎች ላይ የሚወስደው እርምጃ የሚያሳየው ሰላማዊ ትግሉ መጠናከሩን እንጅ ወደኋላ መመለሱን አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ እንዲህ አይነት ችግር ሲከሰት ሰላማዊ ትግሉ አበቃለት ይላሉ፡፡ ሆኖም አገዛዙ ሰላማዊ ትግል አስፈርቶት አውሬ ሲሆን የሚያረጋግጥልን ሰላማዊ ትግሉ መጠናከሩን ነው፡፡
በመሳሪያ ትግል ውስጥ አንድ ጀኔራል ሲሞት አሊያም አንድ የጦሩ አካል ችግር ሲደርስበት ‹‹የትጥቅ ትግል አበቃለት›› እንደማይባለው ሁሉ ሰላማዊ ትግል ላይ አንድ ጫና ወይንም የስርዓቱ ደባ ሲከሰት ትግሉ አይሰራም ማለት አይደለም፡፡
ሰላማዊ ትግል መስዋዕትነት አያስከፍልም ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ሰላማዊ ትግል ውጤት ማምጣት ሲጀምር፣ ዙሩም ሲካረር፣ የሚከፈለው ዋጋም ይበልጥ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ የስርዓቱ አውሬነት በተገለጠ ቁጥር፣ እኛም በተሻለ አመራር ትግሉን ስንመራው መስዋዕትነቱ ይበልጡን እየበዛ እንደሚመጣ እንረዳለን፡፡
በአሁኑ ወቅት ስርዓቱ ሰላማዊ ትግሉ በመጠናከሩ ፍርሃት ውስጥ ይገኛል፡፡ ሰላማዊ ትግሉ ሲጠናከር ስርዓቱ ወደ አውሬነት ይቀየራል፡፡ እስካሁን በሰላማዊ ትግሉ፣ አሁንም በአንድነት ላይ የደረሰው ፈተና የሚያሳየው ሰላማዊ ትግሉ አሸናፊ እንደሆነ ነው፡፡
ዛሬ ያደረግነው ግንኙነት፣ አንድም ለመተዋወቅ፣ በሌላ መልዕክት ለማስተላለፍ፣ ከዚህም በተጨማሪ አንድነታችንን ለማጠናከርና ለትግሉም በቆራጥነት የተዘጋጀን መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ አሁን እዚህ ቦታ የተገናኘን ሰዎች ሰላማዊ ትግሉ ይበልጡን እየተጠናከረ ሲሄድ ምን አልባትም አንድ እስር ቤት የምንታጎር በመሆናችን ቃል ኪዳናችንን ማጥበቅ አለብን፡፡ አንድታችንም የቆየ የፓርቲ ድንበር ሳይገድበን ማጠናከር አለብን፡፡ ከአሁን በኋላ ለሚደርሱብን ችግሮችና እንቅፋቶች ፈጣን መልዕክት እየሰጠን እንቀጥላለን፡፡ ለዚህም የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ትግሉን በተገቢው መንገድ እንደሚመራው ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ አንድ የተለመደ ባህል አለ፡፡ በሰማያዊ ቤት ሁሉም ሰው ጓደኛ ነው፡፡ ሁሉም ሰው እኩል ነው፡፡ ማን የማን ጓደኛ መሆኑ አይታወቅም፡፡ የምክር ቤት አባል፣ ኦዲት፣ ስራ አስፈጻሚ፣ ተራ አባል የሚባል ነገር የለም፡፡ በሰማያዊ ቤት ስልጣን ለግንኙነት ምንም አይነት ችግር አይፈጥርም፡፡ አብዛኛዎቹን የአንድነት አባላት አውቃቸዋለሁ፡፡ ይህ የሰማያዊ ፓርቲ ባህል ጋርም ተላምዳችሁ፣ ጥያቄና ሀሳብ ሲኖራችሁም በግልጽ ማቅረብ የምትችሉበት ቤት ነው፡፡ በዚህ መልክም ጠንክረንና ቃል ኪዳናችን አድሰን ትግላችን ማስቀጠል አለብን፡፡ ለምንጓዝበት የተራራ ጉዞም ወገባችን ጠበቅ፣ ልባችን ሞቅ አድርገን በቃል ኪዳናችን ፀንተን ለምንወዳት አገራችን ትግላችን አጠናክረን እንድንቀጥል ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡
‹‹አንድነትን ያሳጣኝ ኃይል ለእኔ ጠላቴ ነው››
ወጣት ስንታየሁ ቸኮል (የቀድሞው አንድነት ወጣቶች ጉዳይ)
አንድነት የኢትዮጵያን ፖለቲካ መቀየር የሚችሉ ምሁራንና ታጋዮች የያዘ ፓርቲ ነበር፡፡ አንድነት የኢትዮጵያን ያለባትን ችግር የሚገባ የሚረዱ ወጣትና ሴቶችም ስብሰብ ያለው ፓርቲ ነበር፡፡ አንድነት በነበረው ቁመና ምን አልባትም የመንግስትን ስልጣን መቀበል የሚያስችል አቅም የነበረው ፓረቲ ነው፡፡ አንድነትን ማፍረስ የተፈለገው አንድነት በነበረው አቅም ቢቀጥል ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣኑን እንደሚለቅ ስለሚያውቀው ነው፡፡ አንድነት ያፈረሱት ፓርቲው ውስጥ ምንም አይነት ችግር ኖሮ ሳይሆን ስርዓቱ ስለፈራው ነው፡፡ አንድነት ፕሬዝደንቱን የሰየመው በጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡ አሁን ግን ፕሬዝደንቱ ከኢህአዴግ ጽ/ቤት ነው የተመደበው፡፡ ይህን ከኢህአዴግ ጽ/ቤት የተመደበውን ፕሬዝደንት ነው በቀጥታ ተቀበሉት የተባልነው፡፡ እኛ ደግሞ አንቀበልም፡፡ ያልተቀበልነውና ወደሰማያዊ የመጣነው ሰላማዊ ትግሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማሳየት ነው፡፡
የአንድነት አባላት ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ሲመጡ ለፕሮግራምና ለመሳሰሉት ጥቃቅን ነገሮች እየተጨነቁ አይደሉም፡፡ እኛ ወደዚህ የመጣነው በቁጭት ነው፡፡ አንድነትን ያሳጣኝ ኃይል ለእኔ ጠላቴ ነው፡፡ ይህን ጠላት ለመታገል ነው የመጣሁት፡፡ ጥቃቅን የፕሮግራም ልዩነቶች ይህን ትግሌን አያደናቅፈውም፡፡ ስርዓቱ ሰላማዊ ትግል አይቻልም፣ ሲለን እኛ ደግሞ እንዴት እንደሚቻል እናሳየዋለን፡፡ ወደሰማያዊ የመጣንበት ዋነኛው አላማ ይህ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ከሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች ጋር መተዋወቅ አይጠበቅብኝም፡፡ አውቃቸዋለሁ፡፡ እንዲያውም ወደ ቤታችን እንደመጣን ነው የሚሰማኝ፡፡ የጊዜ ጉዳይ መልሶ አገናኝቶናል፡፡ የዚህ አገር ችግር ምን እንደሆነ እናውቀዋለን፡፡ ከዚህ በኋላ የምናደርገው ትግል የነጻነት ትግል ነው፡፡ ወደ ሰማያዊ በመጣንበት ወቅት ከሊቀመንበሩ ጀምሮ በጣም ደስ በሚል ሁኔታ ተቀብለውናል፡፡ ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ በጣም ደስ የሚል አቀባበል አድርገውልናል፡፡ ወደፊትም ለምናደርገው ትግል በተመሳሳይ መንፈስ እንደምንቀጥል ተስፋ አለኝ፡፡ኪዳናችንን ማጥበቅ አለብን!›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
No comments:
Post a Comment