
የመንግስት ሰራተኛው በአንድ ለአምስት ተጠርንፎ በኑሮ ውድነት ሲጠበስ ቆይቶ አሁን ግን የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ትግል ማድረግ ጀምሯል። አርሶአደሩ ሞፈሩንና ቀንበሩን እየሰቀለ፣ ጎተራውን አራቁቶ፣ ጥሪቱን አሟጦ ረሱን ለመከላከል እየተጋደለ ነው። “በብልጽግና ላይ ብልጽግናን አጎናጸፍነው” እየተባለ በእየለቱ የሚዘመርለት አብዛኛው ነጋዴ ደግሞ፣ ጥቂቶች ለበሉት እሱ እዳ እንዲከፍል በመታዘዙ ፣ “ በቃኝ” ብሎ ትግሉን ለኩሷል። ወያኔ አስፈራርቶ ለመግዛት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወደ ጎን በመተው፣ ህዝባችን ከአቅጣጫው ትግሉን ማቀጣጠሉ ለወያኔ ያለውን ንቀት ብቻ ሳይሆን፣ ከእንግዲህ ወያኔንና ሰንኮፉን በአገራችን ምድር ለማየት እንደማይፈልግ ማሳያ ሆኖአል። ኩሩውና ጀግናው ህዝባችን ለወያኔ ያለውን ንቀት፣ የወያኔን የተጣመመ ህግ አልቀበልም ብሎ በማደም ብቻ ሳይሆን፣ የወያኔን የጥይት ጥቃት በመመከት ጭምር እያሳየ ነው። ጥይትና አፈና የማያንበረክከው ህዝባችን፣ ወያኔን ስልታዊ በሆነ ትግሉ ወደ ማይመለስበት መቃብር እየከተተው ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝባችን እየተገበራቸው ያለው የትግል ስልቶች፣ ነጻነት ወዳዱን ህዝብ ሁሉ የሚያኮራ፣ ገዳዮችን የወያኔ ጀሌዎች ደግሞ የሚያስበረግግ ነው።