Wednesday, August 23, 2017

ወያኔ በአምሳሉ የፈጠረው የአየር ሃይል ሲፈተሽ

አየር ሃይል ለአንዲት አገር መከላከያ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ የላቀ ነው። በዚህም አገራችን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ የራሷን የአቪየሽን ተቋም በመመስረት ግንባር ቀደምት ነች።ወይንም ነበረች ሳይሻል አይቀርም።ያኔ የአፍሪካ አገራት በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ወድቀው በሚማቅቁበት ዘመን ኢትዮጵያ የራሷ ጠንካራ የአየር ሃይል ተቋም ነበራት።በኢትዮጵያ የአቪየሽን ታሪክ የሚጀምረው በ1921 ዓ/ም እንደጀመረ ታሪክ ይነግረናል።የኢትዮጲያን አየር ሃይል በዘመናዊ መልኩ ማደራጀት የተጀመረው ደግሞ በ1936 ዓ/ም ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ በኋላ ነው። አየር ሃይሉ ከሌሎች የሃገሪቱ መከላከያ ተቋማት ጋር በመጣመር የሃገሪቱን ዳር ድንበርና ሉአላዊነትን ለማስከበር በተደረጉ ተጋድሎዎች  እስከደርግ ወድቀት ድረስ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በተለይም የኢትዮጵያን የአየር ክልል በማስከበር ረገድ የማይተካ ሚና ነበረው።

በ1969 ዓ/ም የሱማሊያው መሪ ጀነራል ዚያድ ባሬ የኦጋዴንን መሬት በመጠቅለል ታላቋን ሶማሊያ ለመመስረት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት የኢትዮጵያ የአየር ሃይል የዚያድባሬን ህልም ወደቅዠት በመቀየር አኩሪ ታራክ በመስራት ረገድ የፊታውራሪውን ድርሻ ወስዷል።እናም በታጠቀው ዘመናዊ መሳሪያ እጅግ የሚልቀውን የሱማሊያውን የአየር ሃይል ተቋም ለምን ጉድ ባሰኘ መልኩ ድባቅ መትቶቷል።በወቅቱ ኢትዮጵያ ለጦርነቱ በዋናነት ያሰለፈቻቸው F 5E የተባሉ የአየር ላየር ተዋጊ ጀቶች  በቁጥር ከ8 የማይበልጡ ሲሆኑ እንዲሁም ቁጥራቸው ከ—– የማይበልጡ F 5A ቦምብ ጣይ ጀቶች ብቻ ነበሯት።የዚያድ ባሬው የሱማሊያ አየር ሃይል በበኩሉ በመቶዎች በሚቆጠሩ በጊዜው እጅግ ዘመናዊ በሆኑ ሶቪያት ሰራሽ MIG 19 እና MG-21 በተባሉ ተዋጊና ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች እስከ አፍንጫው የታጠቀ ነበር።ኢትዮጲያ ለጦርነቱ ካሰለፈቻቸው የጦር ጀቶች አንጻር ሲመዘን የሶማሊያው አየር ሃይል በዘመናዊነቱም ሆነ በቴክኖሎጂ ጥራቱ የነበረው ብልጫ እጅግ የላቀና ለውድድርም የማይቀርብ ነበረ። ታዲያ በወቅቱ እንዴት የኢትዮጵያው የአየር ሃይል እጅግ የሚልቀውን የሱማሌውን የአየር ሃይል ተቋም  በልጦ ተገኘ? ጥያቄው ይሄ ነው።


  በወቅቱ የኢትዮጵያ የአየር ክልል ያልተደፈረው በሙያዊ ብቃታቸው የተካኑ፣ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚኮሩ፣ በሃገር ፍቅር ስሜት የነደዱ፣ በወታደራዊ ስነ-ምግባራቸው የተመሰገኑ፣ከራሳቸው ይልቅ ሃገራቸውን የሚያስቀድሙ እንደነ ጀነራል ለገሰ ተፈራ፣ ኮ/ል በዛብህ ጴጥሮስ፣ ጄ/ል ባጫ ሁንዴ፣ ጄ/ል አምሃ ደስታ፣ ጄ/ል ፋንታ በላይና የመሳሰሉ ብቃት ያላቸው አብራሪዎችና አመራሮች ስለነበሩ ነበር።እነኚህ ምርጥ አብራሪዎች 24 የሚሆኑ የሱማሊያን ሚግ 21 ጀቶች በF-5E አየር ባየር ውጊያ ዶግ አመድ አድርገዋቸው እንደነበር ታሪክ ዘግቦታል። ይህም ብቻ አልነበረም። በእብሪተኛው የዚያድ ባሬ ጦር የመደፈርና የመጠቃት ስሜት ውስጣቸውን ያንገበገባቸው አብራሪዎቻችን የሱማሊያን አየር ክልል ዘልቀው በመ-ግባት በተለያዩ ቦታዎች የተመረጡ ወታደራዊ ኢላማዎችን በማደባየት የጠላትን ጦር ዳግም እንዳያንሰራራ ማድረጋቸው መላው ኢትዮጲያዊ በኩራት የሚያስታውሰው ነው። በዚህም የተነሳ የሚግ 21 የጦር ጀቶች አምራች የነበረው  በጊዜው የልዕለ ሃያሏ ሀገር፣ የሶቪየት ህብረት፣ ኩባንያን ሳይቀር ጭንቅ ውስጥ በመክተት አሰራሩን ዳግም እንዲፈትሽ አስገድደውታል።ነገር ግን የምርመራው ውጤት እንዳረጋገጠው ዋናው ችግር የሚግ 21 የቴክኖሎጂ ጉድለት ሳይሆን፣ ይልቁንም በተነጻጻሪው ኋላ ቀር ሊባል የሚችል አውሮፕላኖችን ያበሩ የነበሩት ኢትዮጵያዊያን ፓይለቶች ሁለንተናዊ የብቃት ደረጃቸው እጅግ ልቆ በመገኘቱ ነበር።

በሌላ አነጋገር ሚግ 21 አውሮፕላን በወቅቱ ከነበረው የቴክኖሎጂ  ምጥቀት አኳያ ከነባሩ የአሜሪካን ኤፍ 5 ኢ የጦር ጀት ጋር ሲወዳደር የላቀ መሆኑ በመርማሪዎቹ ተረጋግጧል። በጦርነቱ ወቅት የሶቪየቱ ሚግ 21 ለደረሰበት ውድቀት ዋና ምክንያቱ በተቃራኒው ጎራ ተሰልፈው ሲፋለሙት የነበሩት የአይበገሬዎቹ ኢትዮጲያዊያን አብራሪዎች ወደር የሌለው የአየር ላየር ውጊያ ችሎታ፣ ወኔና ጀግንነት ነበር። ይህንን ደግሞ የሚግ 21 የጦር ጀት አምራቹ ካምፓኒ ሊሰራውም ሆነ ለደንበኞቹ ሊያስታጥቅ የሚቻለው ጉዳይ አልነበረም።

ይህ አኩሪ ታሪክ ዛሬ የለም።

 ዛሬ ሕወሃት የሚመራውና የሚቆጣጠረው አየር ሃይል በቀደሞዎቹ የኢትዮጵያ ስርአቶች የነበረውን ግርማ ሞገስ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ተግፍፎ ዕርቃኑን ቆሞ ይገኛል። በዘረኞች ትናጋው ተዘግቶ፣ስጋውን ጨርሶ በስም ብቻ አጥንቱ ገጦ ይገኛል። ለዘመናት በጀግኖቻችን ፓይለቶች ታፍሮና ተከብሮ የቆየው የኢትዮጵያ የአየር ክልል ዛሬ በዘመነ-ወያኔ ከማንኛውም አቅጣጫ ለሚሰነዘር ጥቃት ተጋላጭ ሆኗል።ጋምቤላ ላይ ያለምንም ፈቃድ ስፖርተኞችን የጫኑ የውጭ አውሮፕላኖች የኢትዮጵያን የአየር ክልል ጥሰው ሲገቡና ባህርዳር ላይ ደግሞ 5 የሩሲያ ሄሊኮፕተሮች በተመሳሳይ መልኩ የአየር ሃይሉ መቀመጫ ወደሆነው ዋናው ኤይር ፖርት ላይ ሰተት ብለው ሲያርፍ ሕወሃት የሚመራው አየር ሃይል ምንም አይነት መረጃም ሆነ ዝግጁነት አልነበረውም። በወቅቱ ለነኚህ ጥሰቶችና ድፍረቶች ከአየር ሃይሉ ተቋም ማንም በሃላፊነት የተጠየቀ አልነበረም። በአለም አቀፍ የአቪየሽን ህግ መሰረት ያለ ሃገሩ ፈቃድ ማንም ቢሆን የአንድን ሃገር የአየር ክልል መድፈር አይችልም።ሆኖ ከተገኘም ያለፈቃድ የገባውን አውሮፕላን የአየር ክልሏ የተደፈረባት አገር ለደህንነቷ ስትል  የመጨረሻ ዕርምጃ የሆነውን፣ ማለትም በሚሳኤል እስከመምታት የሚያደርስ ውሳኔ ብትወስድ ተጠያቂ አትሆንም።ምክንያቱም ደህንነቷ አደጋ ላይ ወድቋል፣ ሉአላዊነቷም   ተደፍሯልና።ለመሆኑ እነኝህ አውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮች የኢትዮጵያን የአየር ክልል ጥሰው ሲገቡ ብዙ የተደሰኮረለት የሕወሃት አየር ሃይል ምን ይሰራ ነበር? የራዳር ምድብተኞቹ የት ነበሩ? ክፉ ተልዕኮ የነበራቸው የጠላት ሃይሎች ቢሆኑ ኑሮስ አገር አውድመው ህዝብ ጨርሰው በሰላም ተመልሰው መሄድ ይችሉ ነበር ማለት ነው? ግን ለባዶ ፕሮፓጋንዳና ከአቅም በላይ በመንጠራራት ጉራ የተለከፉት የሕወሃት መኮንኖች Su-27 ኢንተር ሴፕተር ሁሌም በተጠንቀቅ ነው ይሉናል።የሚገርመው ነገር እስካሁን ድረስ Su-27ን የሚያበር ብቁ የሆነ አብራሪም ሆነ ቴክኒሺያን  አንድም አለማፍራታቸው ነው። አውሮፕላኑን የሚያበሩት ፓይለቶችም ሆኑ ቴክኒሻኖች ዩክሪኒያኖችና ሩሲያዊያን ናቸው። በቅጥረኛ  የሚተዳደርና የሚተማመን ተቋም ሆኗል አየር ሃይሉ ባጭሩ። ይህንንም ዕውነት የሚያረጋግጥልን በአንድ ወቅት ስርዓቱን እየከዱ የሚሄዱ ፓይለቶች ቁጥራቸው እየበረከተ መምጣቱን አስመልክቶ በተካሄደ ስብሰባ ላይ የወቅቱ የአየር ሃይል አዛዥ ሌ/ጄ/ል አደም መሃመድና ሌሎችም የሕወሃት መኮንኖች “ይህንን አየር ሃይል በትነን ከውጭ በመቅጠር እናዋጋለን” ያሉት አነጋገር ይህንን ሙግታችንን የሚያጠናክር አንድ ተጨማሪ ምሳሌ ነው።

    ሃቁ ይህ ሁኖ ሳለ የወያኔ ጀነራል ተብየዎች አየር ሃይሉ ከመቸውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ዛሬ ዘምኗል ሲሉ ይደመጣሉ።አየር ሃይሉ በርግጥም ከዘመነ ለምን በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ የአየር ክልል ተደፈረ?እንደገናስ  ሚያዚያ 11/2007 ዓ/ም ሊቢያ ውስጥ የሚኖሩ ስደተኛ  ኢትዮጵያዊያን እራሱን እስላማዊ መንግስት ወይም በሃጽሮተ ቃል አይ ሲ ስ እያለ በሚጠራው ጽፈኛ ቡድን እንደበግ ሲታረዱ እውነት ወያኔዎች እንደሚሉት አየር ሃይሉ የዘመነ እና የሃገር ዋልታና መከታ ከሆነ ለምን የኢትዮጵያዊያንን ደም አልመለሰም?

 እንደምናስታውሰው በዚያው አመት አይ ሲ ስ የኢትዮጵያን ዜጎች ብቻ አልነበረም በግፍ ያረደው።ቀደም ብሎ የግብጽ ዜጎችንም ቢሆን እስላማዊው መንግስት አርዷል።ግን ግብጽ እንደወያኔው ቡድን በዜጎቿላይ የተፈጸመውን ዘግናኝ ግፍ በዝምታ አላለፈችም።ቦምብ ጣይ ጀቶቿን አንደረደረች!! ከዚያም አበረረች!! ወደ አይ ሲ ስ ሰፈር።እናም አሸባሪውን ቡድኑን ድባቅ መታችው።በዚህም የዜጎቿን ደም ግብጽ መለሰች!! የሟች እናቶችም ቤተሰቦችም ምንም እንኳን ልጆቻቸው መቃብር ፈንቅለው ባይነሱም እባቸውን ጠረጉ።በመንግስታቸው ኮሩ።

የኢትዮጵያ እናቶች ግን አፈሩ።አንድንድ ወገኖች <<ግብጽና ሊብያ ኩታገጠም አገሮች ናቸው። ስለዚህ ግብጽ አሸባሪውን ቡድን ለመደብደብ ይመቻታል።ለእኛ ግን ሁኔታው ዳገትነው!! አይመችም። ምክኒያቱ በመካከላችን ሱዳን የምትባል አገር አለች>> ሲሉ ይደመጣሉ። ልብ ሊባል ወይም ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ግን ሱዳን እና ኢትዮጵያ ከመቼውም በላይ የቀረበና የጠበቀ የጋራ ወታደራዊ ቃል ኪዳን ወይም military alliance ፈጥረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሕወሃት በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ አለኝ የሚለው ወታደራዊ ተጽዕኖና በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረክም ያለውን ተደማጭነት ተጠቅሞ ልክ እንደ ግብጾቹ ቀልጣፋ፣ ወሳኝና ታሪካዊ ግዳጁን አልተወጣም? ለነገሩ ዕውነት እንነጋገር ከተባለ ሊቢያና ኢትዮጲያ ኩታ ገጠም ሀገሮች ቢሆኑ ኖሮ ሕወሃት መራሹ አየር ሃይል የወገኖቻችንን ደም የመመለስና ክብራችንን የማደስ ብቃት ይኖረው ነበርን? ወይንስ ጋምቤላና ባህር ዳር ገብተው እንዳረፉት አውሮፕላኖች አላየሁም አልሰማሁም ብሎ ዝም ሊል ይሆን? ለነገሩ ይህን ዝምታውን ቢያሳይም የሚገርም ክስተት አይሆንም። ምክንያቱም  የሙሩሌ ጎሳ አባላት በተደጋጋሚ ድንበራችንን ጥሰው እየገቡ ከ200 በላይ ኢትዮጲያዊያን ሕጻናትን አፍነው ሲወስዱ፣ ሲገድሉና ከብትና ንብረቶችን ሲዘርፉ የወያኔው አየር ሃይል አብራሪዎች በአለም አቀፉ ማሕበረሰብ አማላጅነት የተመለሱ ሕጻናትን አቅፈው ፎቶ ከመነሳት የዘለለ ሚና አልነበራቸውም። ለምን? ምክኒያቱም ለህዝብ የሚቆረቆር የሃገር ክብር ይሉት ነገር የሚገባው መንግስት ስሌለለን።ስምምነቱ ፣ወታደራዊ አደረጃጀቱም ሆነ ሃገራዊ አወቃቀሩ ለህዝብና ለሃገር የሚጠቅም ሳይሆን ስልጣን የሙጥኝ ብሎ ዘላለማዊ ለመሆን በከንቱ የሚንደፋደፍ የመንፈስ ድንክዪዎች ራዕይ አልባ መንደረኞች ስብስብ በመሆኑ ነው ሕዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ።

No comments:

Post a Comment