ባለፉት 26 ዓመታት በወያኔ ዘረኛ፣ ከፋፋይ፣ አፋኝና ገዳይ ፖሊሲ ስቃይ ያልደረሰበት ዜጋ አለ ከተባለ ያ ግለሰብ የአገዛዙ አባል መሆን አለበት። በወያኔ ፖሊሲ ህዝባችን ተገድሏል፤ አካለ ጎደሎ ሆኗል፣ ታስሯል፤ ተገርፏል፤ ተሰዷል። ህዝባችን በምድር ላይ ያለውን ስቃይና መከራ ሁሉ ተቀብሏል። ከዛሬ ነገ ይሻሻል ብሎ ተስፋ ሲያደርግ፣ ስቃዩ እየጨመረ፣ የህዝቡ የመኖር ህልውና አደጋ ውስጥ እየወደቀ፣ እንደ ህዝብ በጅምላ የሚጠፋበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ጥቂቶች የህወሃት ሽፍቶችና ግብረአበሮቹ፣ የማይጠረቃውን ቋታቸውን ለመሙላት ሲሉ ህዝቡን በአጥንቱ አስቀርተው አገሩን ሁሉ ለመውረስ ላይ እና ታች እያሉ ነው።
የመንግስት ሰራተኛው በአንድ ለአምስት ተጠርንፎ በኑሮ ውድነት ሲጠበስ ቆይቶ አሁን ግን የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ትግል ማድረግ ጀምሯል። አርሶአደሩ ሞፈሩንና ቀንበሩን እየሰቀለ፣ ጎተራውን አራቁቶ፣ ጥሪቱን አሟጦ ረሱን ለመከላከል እየተጋደለ ነው። “በብልጽግና ላይ ብልጽግናን አጎናጸፍነው” እየተባለ በእየለቱ የሚዘመርለት አብዛኛው ነጋዴ ደግሞ፣ ጥቂቶች ለበሉት እሱ እዳ እንዲከፍል በመታዘዙ ፣ “ በቃኝ” ብሎ ትግሉን ለኩሷል። ወያኔ አስፈራርቶ ለመግዛት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወደ ጎን በመተው፣ ህዝባችን ከአቅጣጫው ትግሉን ማቀጣጠሉ ለወያኔ ያለውን ንቀት ብቻ ሳይሆን፣ ከእንግዲህ ወያኔንና ሰንኮፉን በአገራችን ምድር ለማየት እንደማይፈልግ ማሳያ ሆኖአል። ኩሩውና ጀግናው ህዝባችን ለወያኔ ያለውን ንቀት፣ የወያኔን የተጣመመ ህግ አልቀበልም ብሎ በማደም ብቻ ሳይሆን፣ የወያኔን የጥይት ጥቃት በመመከት ጭምር እያሳየ ነው። ጥይትና አፈና የማያንበረክከው ህዝባችን፣ ወያኔን ስልታዊ በሆነ ትግሉ ወደ ማይመለስበት መቃብር እየከተተው ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝባችን እየተገበራቸው ያለው የትግል ስልቶች፣ ነጻነት ወዳዱን ህዝብ ሁሉ የሚያኮራ፣ ገዳዮችን የወያኔ ጀሌዎች ደግሞ የሚያስበረግግ ነው።
ወያኔ “የኢትዮጵያ ህዝብ ካልተጎሳቆለ፣ ካልተራበና ካልታረዘ አይገዛም” የሚል ኋዋላ ቀር ፍልስፍና የሚከተል አገዛዝ ነው። ባለፉት 26 ዓመታት ወያኔ ጥቂት ገዢዎችን እያበለጸገ፣ በሃብት ላይ ሃብት እየቆለለ፣ በስልጣን ላይ ስልጣን እየደረበ፣ በጉልበት ላይ ጉልበት እየጨመረ፣ አብዛኛውን ህዝብ በድህነት ማጥ ውስጥ ከትቶ በመግዛት ይህን ከዘመኑ ጋር የማይሄድ የስግብግቦችና የሁዋላ ቀሮች ፍልስፍና ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሯል። በታሪክ ተርበው የማያውቁት በርካታ ቦታዎች ፣ በወያኔ “ አስርቦ፣ አደህይቶና አዋርዶ” የመግዛት ፖሊሲ ምጽዋት ፈላጊዎች ሆነዋል። በአገራችን በቀን ሶስት ጊዜ ቀርቶ አንድ ጊዜ እንኳን በወጉ በልቶ የሚውለው ህዝባችን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቶአል። ባዶ አንጀታቸውን ወደ የትምህርት ቤቶቻቸው በመሄድ በረሃብ ምክንያት ክፍል ውስጥ የሚወድቁ ተማሪዎች ቁጥር አስደንጋጭ ነው። በየእርዳታ ጣቢያዎች የተኮለኮሉ ፣ በየመንገዱ የሚለምኑ ወገኖችቻን ፣ በእየለቱ በኑሮ ውድነት የተነሳ ቀስ በቀስ እየጠፉ ያሉ ዜጎቻችን ሁሉ የወያኔ “ አደህይቶ” የመግዛት ፖሊሲ ውጤቶች ናቸው።
ምንም እንኳ ወያኔ እንዲህ አይነት ፣ “ህዝብን ገድሎ ጥቂቶችን የሚያኖር ፍልስፍና” ለተወሰኑ አመታት በስልጣን ላይ እንዲቆይ ቢያስችለውም፣ እድሜ ልኩን በስልጣን ላይ ሊያኖረው እንደማይችል ግን ታሪክ ምስክር ነው። ጥቂቶች ጉልበተኞች ብዙሃኑን ረግጠው ለረጅም ጊዜ ሊገዙ አይችሉም። ካለፈው ሁለት አመት ወዲህ በመላ አገራችን ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ በመቀጣጠል ላይ ያለው ትግል ይህንን እውነታ የሚያሳይ ነው። የጥቂት ጉልበተኞች አገዛዝ እድሜ እያጠረ ብዙሃኑ የስልጣን ባለቤት ሆኖ ራሱን በራሱ የሚመራበት ጊዜ እየቀረበ መምጣቱን የሚያመለክቱ ምልክቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መጥቶአል።
ወያኔ ሰሞኑን የጣለው የዘፈቀደ ግብር አገዛዙ በከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ መግባቱን፣ በነጋዴው ላይ ከፍተኛ ግብር ካልጣለ በስተቀር በዙሪያው ያሰለፋቸውና በገንዘብ ሃይል ድጋፍ የሚሰጡትን አካሎች ይዞ ለማቆየት እንደማይችል አረጋግጧል። ወያኔ ላለፉት 26 አመታት በታክስ ማጭበርበር፣ እቃዎችን ከቀረጥ ነጻ በማስገባት እንዲሁም በጨራታ ስም የአገሪቱን ኩባንያዎች በራሱ ስም ወደ አቋቋማቸው የንግድ ድርጅቶች በማዞር በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ሃብት አጋብሷል። ወያኔ በግሉ ባቋቋማቸው በእነዚህ ኩባንያዎች ምክንያት አገዛዙን የማይደግፉ እጅግ በርካታ ነጋዴዎች በኪሳራ ከጨዋታ ውጭ ሆነዋል። ዛሬ የአገሪቱን ገበያዎች ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረው ያሉት እነዚህ የህወሃትና ከህወሃት ጋር የተጣቡት ድርጅቶችና ግለሰቦች መሆናቸው ግልጽ ነው። አብዛኛው የአገራችን ህዝብ እንደሚያውቀው እነዚህ የወያኔ ንብረት የሆኑ ንግድ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች ምንም አይነት ግብር አይከፍሉም። ሌላው ነጋዴ ግን “ ግብር መክፍልን እንደ ዜግነት ግዴታው አድርጎ በመውሰድ ቤተሰቡን እያስራበም ቢሆን የሚጣልበትን ግብር በጸጋ ሲከፍል ቆይቶአል። ሆኖም ግን እሱ ከሚከፍለው ግብር አብዛኛው እጅ የሚተላለፈው ወደ ህወሃት ኩባንያዎች እንደነበር ይታወቃል።
አርበኞች ግንቦት 7 በተለያዩ ወቅቶች ሲገልጽ እንደቆየው ወያኔ ህዝባችንን አፍኖ ለመግዛት የሚጠቀምበትን የአፈናና የግዲያ መሣሪያዎች ከውጪ አገር በውድ ዋጋ እየገዛ የሚያስገባው ከግብር ከፋይ ህዝባችን በሚሰበስበው ገንዘብ ነው ። ከዚያም በተጨማሪ እንደ አሸን ለፈሉት የመከላከያ፣ የደህንነትና የፖሊስ አባሎቹ በየወሩ ደመወዝ የሚከፍለው ህዝባችን በግብር ስም ከሚከፍለው እና የህወሃት ኩባንያዎች ተከፋፍለው በሚተርፈው ገንዘብ ነው። እጅግ የሚያሳዝነው ከህዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ ደመወዝ የሚከፈለው የአገሪቱ መከላኪያ፤ ደህንነትና ፖሊስ የወር ደመወዙን የሚከፍለው ህዝብ ምሬት ሲያሰማ የህወሃት አለቆቻቸውን ተእዛዝ ተቀብለው “ ልምን አባትክ ታማርራለህ?” በማለት ቃታ ይስቡበታል። ወያኔ ከህዝብ በሚሰበስበው የግብር ገንዘብ ቀለብ የሚሠፈርላቸው እነዚህ የሠራዊቱ አባላት ወገናቸው በሆነው ህዝብ ላይ ተኩሱ ሲባሉ ካልተኮሱ የምትወረወርላቸውን የነፍስ ማቆያ አያገኙም እና “የአብራኩ ክፋይ የሆኑኩትን ወገኔን ለምን እገድለዋለሁ?’ ብለው አይጠይቁም። የህዝባቸው ምሬት ገብቶአቸው ይህንን ጥያቄ ለመጠየቅ የሞከሩ ጥቂቶች ቢኖሩም እጣ ፈንታቸው የጭካኔ እርምጃ ከሚወስዱባቸው ግብር ከፋይ ወገናቸው የተለየ አለመሆኑ ይታወቃል።
ህወሃት የአገራችንን በትረ ሥልጣን በጠመንጃ ሃይል ከተቆጣጠረ ወዲህ ህዝባችን በተለያዩ ወቅቶች “በምከፍለው የግብር ገንዘብ ቀለብ የሚሠፈርለት ሠራዊት ለምን እንዲገለኝ ይሰማራብኛል ሲል ለመጠየቅ ሞክሮአል። ግብር ሳላቋርጥ እየከፈልኩ “ ለምንስ የመብራት፣ የንጽህ ውሃ፣ የጤናና ሌሎችንም
ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን በበቂ አላገኘሁም?” በማለትም በሰላም ሲጠይቅ ቆይቶአል። እንኳን ስቃይና መከራ “ማርም ሲበዛ ይመራል …” እንዲሉ አሁን ምሬቱ በዝቶበት በአንድነት መነሳሳቱ ትክክለኛ እርምጃ እንደሆነ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል።
በዚህም ምክንያት በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራው የንግድ ማህበረሰብ ሰሞኑን እየወሰደ ባለው እርምጃ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ይኮራል። የንግዱ ማህበረሰብ የጀመረውን ይህንን የተቃውሞ ትግል በመንግሥትና በግል ሥራ ላይ የተሠማሩ ሠራተኞች ፤ መምህራንና ተማሪዎች ፤ አርሶ አደሮች ፤ አርብቶአደሮች ፤ እንዲሁም የፋብሪካ ሠራተኞችና የአገራችንን ሉአላዊነት ለማስከበር ተግባር በመከላኪያ ሠራዊት፤ በፖሊስ እና ደህንነት ተቋሞች ውስጥ ተቀጥረው የሚያገለግሉ ዜጎች ሁሉ እንዲቀላቀሉት አርበኞች ግንቦት 7 የትግል ጥሪውን ያስተላልፋል። ዘረኛው የህወሃት አገዛዝ ሥልጣን ላይ ለመቆየት የአንድ ቀን እድሜ ባገኘ ቁጥር በህዝባችን ላይ የሚደርሰው መከራና ስቃይ በዚያው ልክ እንደሚጨምር ሁላችንም መረዳት ይኖርብናል። ስለዚህ ህወሃት እስከዛሬ በመብታችንና በነጻነታችን ላይ የደቀነውን ፈተና በድል ለመወጣት የምንችለው ሁላችንም በጋራ የአገዛዙን ዕድሜ ማሳጠር ስንችል እንደሆነ ታውቆ
ዛሬውኑ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንነሳ !!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
No comments:
Post a Comment