Wednesday, August 23, 2017

ትልቁ ሰውዬና የጅጅጋ ሕዝብ ሰቆቃ

ከሙክታር ኦማር የእንግሊዝኛ መጣጥፍ በግርድፉ የተተረጎመ

በድህረ ቅኝ ግዛት ዘመኗ አፍሪካ የገባችበትን የአስተዳደር ብልሹነትና የፖለቲካ ቀውስ አስመልክቶ  እንደ ካሜሩናዊው የማህበረሰብ ጥናት ተመራማሪ አቺሌ ሜምቤ  በትክክል የተረዳና የጻፈ ምሁር  ጥቂት ነው። ” የብልግና ውበት” በተባለው ድንቅ ጥናታዊ ጽሁፉ የነጮቹን ጌቶቻቸውን ቦታ ተረክበው አፍሪካን እየተጫወቱባት ያሉት “ጌቶቹ አምባገነን መሪዎቻችንና ባለስልጣናቱ” የፈጠሩት ስርዓት ጥቂቶቹን ጨቋኞችና ብዙሃኑን ተጨቋኝ ህዝብ በአንድ ላይ ጠፍንጎና አቆላልፎ አስከፊ ወደሆነ የስብዓና ዝቅጠትና ሕይወት አልባ ወደሆነ የደመ ነፍስ ጉዞ እንደሚጎትታቸው በሚያስደንቅ ብዕሩ ገልጾታል።

ገደብ አልባ በሆነ የስልጣን ኮርቻ ላይ ለዕድሜ ልክ የተፈናጠጡት ትላልቆቹ አምባገነኖች በመንፈሳቸው የበሰበሱና ፍቅርና ሰላም አልባ ውስጣዊ ማንነታቸው ከውጭ በሚታየው አካላዊ ቅርጻቸው ላይ ይነበባል ይላል አቺሌ ሜምቤ። እነኚህ የቁም ሙታኖች፣ ቦርጫቸው አለቅጥ ተንዘርጥጦ፣ ፊታቸው ጤናማ ባልሆነ ውፍረት ተነፍቶና ላባቸው አለማቋረጥ ሲወርድ፣ ቅርጽ የለሽ ደረታቸውና ሆዳቸው በጸጉር ተወርሮ ለሚያያቸው ለዓይን የሚቀፉ ሰው መሰል አውሬዎች ያስመስላቸዋል። ይህ ጸያፍ የሆነውን አካላዊ ቅርጻቸውን እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሰው ደግሞ ስርዓትና ገደብ የሌለው የአመጋገብ ባህላቸው ነው። ከሆዳቸው ፍቅር በተጨማሪም ለዚህ እንስሳዊ ማንነት የዳረጋቸው ስልጣናቸውን ተገን አድርገው የሚፈጽሙት የዜጎች ላይ ጥቃትና ግድያ፣ ለከት የሌለው የወሲብ ፍላጎትና ነውረኛ እርካታ፣ የእርስ በርስ የመጠላለፍ ሴራ፣ አጠቃላይ የምግባረ ብልሹነትና ነፍስን ለስጋ ፍጹም አሳልፎ የመሸጥ ክፉ ውጤት ነው ይላል አቺሌ ሜምቤ።


ላቦው ታንሲ የተባለው የኮንጎው ጸሃፊ በበኩሉ ” ጸረ-ሕዝብ” በሚለው ትረካው ውስጥ በአንድ ትንሽ የአፍሪካ መንደር ውስጥ የተከሰተን የማሕበረሰብ ቀውስ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል። ” ጸረ ሰላምና አሸባሪ የሆኑ ተቃዋሚ ሃይሎችን በመዋጋት ስም የስርዓቱ ወታደሮች በዚች መንደር ውስጥ ዘልቀው ገብተው በተለይም በሴቶች ላይ የሚፈጽሙት አካላዊና ወሲባዊ ጥቃት እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ነው። ባሎቻቸውንና ወንድሞቻቸውን በድብቅ ትረዳላችሁ ተብለው ስቃያቸውን የሚያዩት የአካባቢው ሴቶች ለደህንነታቸው ሲሉ ለነኚህ የዘመኑ ጌቶቻቸው ስጋቸውን አሳልፈው ከመስጠት በስተቀር ሌላ ምንም ምርጫ የላቸውም” ይላል ጸሃፊው።

አሁን ይህንን በሌላ አለም የተከናወነ የድህረ ቅኝ ግዛት ታሪክ እንተውና እስቲ ለኣፍታም ቢሆን ወደራሳችን የሱማሌ ክልል በተለይም ጅጅጋ ወደተባለው አካባቢ እየተፈጸመ ስላለው አሰቃቂ ወንጀልና ስቃይ እንመለስ። በርግጥ የኮንጎውና የካሜሩኑ ጸሃፊዎች የገለጹት ታሪክ ምናልባት በጊዜና በቦታ ይለያይ እንደሆን እንጂ በይዘቱ ፍጹም ተመሳሳይ የሆነ ወንጀል በዚሁ በኛው የክልል መንግስት ተብዬው የሶማሌ ግዛት ውስጥ አልተፈጸመም ትላላችሁ? ይህ   ክልልም ሆነ የክልል መንግስት ተብሎ ሊጠራ በማይችል የማፊያዎች ዓለም ውስጥ እየተፈጸመ ያለው ፍጹም የሆነ ኢሰብዓዊ ወንጀልና ሊታሰብ የማይችል ነውረኛ ድርጊት ታሪክ ያልዘገበው፣ አደባባይ ያልወጣ፣ ግን በይፋ የሚፈጸም የቀን በቀን የሕይወት ክስተት ከሆነ ዓመታትን አስቆጥሯል።የአካባቢው ሕዝብ በተለይም ድጋፍና መከታ የሌላቸው ሴቶች ለዚህ ክፉ ሕይወት ተጋላጭና ሰለባ ሆነዋል።

አቺሌ ሜምቤ የፍጹም ፈላጭ ቆራጮች አገዛዝ ህብረተሰቡን ምን ያህል በዘፈቀደ ለሚመራ ስርዓተ አልበኛ ሕይወት፣ አድር ባይነት፣ ስነ ልቦናዊ ስቃይ፣ ክብረ ቢስነት፣ ፍጹም የወረደ ስጋዊ ብልግናና ርካሽነት እንደሚለውጠውና ይህም ሁኔታ ቀስ በቀስ ተቀባይነትን ያገኘ የቀን በቀን የኑሮ ዘይቤ ብሎም ባህል እየሆነ መምጣቱን  በጽሁፉ ገልጾታል። ታዲያ ይህንን ስታነቡ ከዚህ በፊት ካየነውና ከሰማነው ውጪ ምን አዲስ ነገር አለው ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም። እርግጥ ነው ይህ ሁኔታ በዚችው በኛዋ ጅጅጋ ውስጥ “አባ ” ወይንም አባታችን በመባል የሚታወቀውን በማይጠረቃ የሆድና የወሲብ ፍላጎት የታወረውን፣ ከሱ ባልተሻሉ ትናንሽ መሃይም ጉጅሌዎች ተከቦ ህዝቡን የቁም ስቅሉን የሚያሳየውን፣ በማስመሰል ልማትና የሰላም ዋስትና ፕሮፓጋንዳው ዳያስፖራውን የሚጫወትበትን፣ የአካባቢውን ዜጎች ህይወት የሲኦል ሕይወት ያደረገውን የክልሉን “ትልቁን ሰውዬ” ወይንም መሪ አያስታውሳችሁም? በርግጥም ነውር፣ የዘፈቀደ ጥቃትና ግድያ የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች የቀን በቀን የሕይወት ልምዳቸው አልሆነም ትላላችሁ? እስቲ ቀጥሎ የምነግራችሁን ጥቂት በአካባቢው ደረሱ የተባሉ ክስተቶችን ላውጋችሁና በውነትም በዚህ ክልል ውስጥ መሰረታዊ የሆኑ የባህልና የሃይማኖት እሴቶች አልጠፉም? አጠቃላይ የማህበረሰብ መፈራረስስ አልደረሰም ትላላችሁ?



ነገሩ የሆነው ከአንድ ወር በፊት ነው። የክልሉ መሪ በተለመደው ስድ አንደበቱ አንዷን የካቢኔ አባል የሆነች ሴት በሚያሸማቅቁና የሴትን ክብር በሚያዋርዱ ቃላት ” አንቺ ሰካራም፣ የወሲብ ሴሰኛ፣ ሀሺሻም” ሲል በሰው ፊት ይሰድባታል። ሴቲቱስ መች የዋዛ ነበረች! “ አንተ አለህ አይደል ከሕጻናት ሴቶች ጋር የምትባልግ ነውረኛ! አንት ንገሩኝ ባይ!” ስትል ልክ ልኩን ትነግረዋለች። ይህንን ወሬ የሰማው ህዝብ ይበልጥ ያስገረመውና ያስደነገጠውና የ8 ሚሊዮን ነፍሶች አስተዳዳሪ የሆነው ትልቅ ሰውዬ ከአንድ መሪ በማይጠበቅ ደረጃ የካቢኔ አባል የሆነችውን ሴት በሚያዋርድ ቋንቋ መስደቡ ሳይሆን ይልቁንም ሴቲቱ ምንና ማንን ብትተማመን ነው አጸፋዊ ምላሿን በሰላ አንደበት የሰጠችው የሚለው ጥያቄ ነበር። ስድቡንና ውርደቱን ጠጥቶ በዝምታ ከሚኖር ማህበረሰብ የማይጠበቅ ምላሽ ነበርና። ይህ ታሪክ ነገሮችን በፊት ለፊትና በድፍረት በመናገር ባህሉ የሚታወቀው የሶማሌ ክልል ሕዝብ ዛሬ ፈሪና ጭምት መሆኑን ማሳያ አንድ ምሳሌ ነው።



አንድ ሌላም ክስተት ላውጋችሁ። ከሶስት ወራት በፊት አንድ በውጭ አለም የምትኖር ዳያስፖራ ሴት አባቷ ጅጅጋ ውስጥ እንደታሰሩና ቤት ንብረታቸውም እንደተወረሰ በተለያዩ ድረ ገጾች ላይ ጽፋ የድረሱልኝ ጥሪ ታሰማለች። ትንሽ ቆይቶም የክልሉ መሪ የተለመደውንና ከጌቶቹ የተማረውን የስም ማጠልሸት ዘመቻ ባሰለጠናቸው ርካሽ የፖለቲካ ተዋኒያን በኩል አስተላለፈ። የዚችን ሴት ስምና ገጽታ የሚያበላሽ ፊልም በዩ ቲዩብና በክልሉ ቲቪ አሰራጨ። ሴትዬዋ ቀደም ሲል

በስርዓቱ ውስጥ የነበራትን ሚናና የፈጸመቻችውን ሕገ ወጥና ግብረ ገብነት የጎደላቸው ድርጊቶች በስፋት የሚያትቱ ማጋለጦች የነበሩበት ፊልም ነበር። አሁንም የሕዝቡ ትኩረት የነበረው በእንደዚህ አይነት የረከሰና መሰረተ ቢስ መንገድ የሰውን ስምና ስብዕና በሚያጎድፈው ቂም በቀለኛው የክልሉ መሪ ላይ ሳይሆን በዚች ምስኪን ዳያስፖራ ሴት ላይ ነበር። እጅግ የሚያስገርመው ግን በአንድ ወቅት የማህበረሰቡ መንፈሳዊ ህይወት ጠባቂዎችና የሃይማኖት መሪዎች የነበሩት ሼኮች፣ ኢማሞችና ሽማግሌ አባቶች ይህንን ድርጊት መኮንንና መቃወም ትተው ዝምታን መምረጣቸው ነበር። ይህ ታሪክ የሚያሳየን የሃይማኖትና የባህል እሴቶቻችን ፈርሰው የፍርሃትና የአድር ባይነት ባህል መንገሱን ነው።

በየቀኑ፣ በየሳምንቱና በየወሩ በእስር ላይ ያሉ ወጣት ሴቶችና እናቶች በወህኒው ባለስልጣናት ይደፈራሉ። ከዚህ የእስር ቤት ሲኦል ያመለጡትም ሴቶች ቢሆኑ በየጫትና በየሺሻ ቤቱ ለወሲብ ጥቃትና ድፍረት የተጋለጡ ናቸው። ከዚህ አልፎ  “የመጣውን መቀበል ነው” በሚል የሽንፈት  መርህ ራሳቸውን ካለው የሱስ ህይወትና የዘቀጠ ወሲባዊ ባህል ጋር በሚገባ አዛምደው ስጋቸውንና የሴትነት ክብራቸውን ለትላልቆቹ የክልሉ ሹማምንቶች የሸጡት ቆነጃጅቶች አለምንም ችግር በየመንግስት መስሪያ ቤቶች ቁልፍ ስልጣን እየተሰጣቸው ወይነው ይኖራሉ። ለዚህም ነው በክልሉ መንግስት ውስጥ ባሉ የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ብዛት ያላቸው ወጣት፣ ቆንጆና አማላይ የሆኑ አንስቶች የተሰገሰጉት! በሴቶች የእኩልነትና የጥንካሬ መንፈስ የተገኘ ስልጣን ሳይሆን በወሲብ ንግድ የተገዛ ሹመት!  እነሆ የነገዋ የሶማሊያ ህጻናት ተስፋ በዛሬው የእናቶቻቸው የዝሙትና የአስረስ ምቺው ጉድጉድ ውስጥ አየተቀበረች ትገኝለች!



ዋናው ጥያቄ ” ከዚህ ከገባንበት ማጥ ውስጥ እንዴት ብለን እንወጣለን?” ነው። ይህ ጥያቄ ደግሞ ስለተጨቆነው ህዝብ ብቻ ሳይሆን ስለጨቋኞቹም ሲባል መነሳት ያለበት ጥያቄ ነው። ጨቋኞቹም ሆኑ ተጨቋኞቹ በአንድ ሰንሰለት፣ በአንድ ዕጣ ፈንታ ተቆራኝተው ታስረዋልና! ስለምንስ አንዋጋም? የተቃዋሚ ሃይሎችስ ከወዴት አሉ? ምሁሮቻችንም ሆኑ የሃይማኖት አባቶቻችንስ ስለምን ዝምታን መረጡ?



በርግጥም እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ሰፊ ጥናትና ውይይት ይጠበቅብናል። አንድ ነገር ላይ ግን እርግጠኛ ሆነን መናገር እችላለን። በይፋና ባደባባይ ግልጽ በሆነ መንገድ ባይታይና ባይዘገብም ሕዝቡ በመሰለው መንገድና በመረጠው ሰዓት ሁሉ ስርዓቱን መቃወሙን አላቋረጠም። ለዚህም ትልቁ ማስረጃ በተቃዋሚነት ተፈርጀው በየእስር ቤቱ የሚማቅቁትን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የክልሉን ዜጎች ስናስብና ስናስታውሳቸው ነው።



የምሁራኖቻችን ከሀገሪቱ መሸሽና በተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ ተደብቀው የግል ኑሮአቸውን መኖራቸው ብዙም ሊያስገርመንና ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም። ስር የሰደደ የአፍሪካ ምናልባትም የዘመኑ የአለማችን ክስተት ነው ማለት ይቻላል። መልካሙ ዜና ግን በነኚህ ምሁራን መሰደድ የተፈጠውን ክፍተት እየሞሉትና አገራዊ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉት የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ አክቲቪስቶች፣ ነፍሳቸውን በፍቅረ ነዋይ ያልለወጡ የሃይማኖት መሪዎች፣  ነጋዴዎችና ሀገር በቀል ምሁራን ሆነዋል። እነኚህ አዲስ ሃይሎች በሕወሃት መሃንዲስነትና ለሆዳቸው ባደሩ የክልሉ ባለስልጣናት አስፈጻሚነት እየተሰራ ያለውን ባህልን፣ ሃይማኖትን፣ ሰብአዊነትን፣ መተሳሰብንና ሰውን ሰው ያደረጉትን መሰረታዊ እሴቶችን የማፈራረስ ሴራዎች በተለያዩ መንገዶች ለማክሸፍ የድርሻቸውን እየተወጡ ነው።



በዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ በሆነ የሞራል ዝቅጠት ውስጥ በምንገኝበት ሰዓት ላይ ማንኛውም አይነት የጨዋ ስነ ምግባር ማሳየትና ክብርን መጠበቅ ስርዓቱን እንደ መቃወም ሊቆጠር ይገባል። ልጆቿን ሞራልና ግብረ ገብ እያስተማረች የምታሳድግ እናት እሷ ከተቃዋሚ ጎራ የምትመድ ናት! እያንዳንዱ ትምህርቱን በስነ ስርዓት እየተከታተለ፣ ራሱን ከጫትና ከሺሻ ሱስ ገድቦ እስከመጨረሻውው የሚዘልቅ ወጣት ተማሪ እሱ ስርዓቱን እየተቃወመ ነው! በሌብነትና በሙስና ሳይጨማለቅ ስራውንም ሆነ ንግዱን በላብና በወዙ ለማግኘት የሚጥር ሰራተኛና ነጋዴ እሱ ተቃዋሚ ነው! የሰላምንና የመቻቻልን ሃይማኖታዊ አስተምህሮት በየአካባቢው እየሄደች የምትሰብክና ፍቅርን የምታስተምር ዜጋ እሷ የስርዓቱ ጠላት ናት። በቋንቋ፣ በብሄርና በሃይማኖት ልዩነት ጥላቻና ጸብ እንዳይፈጠር ብሎም የወደፊቱን የማህበረሰቡን ሕይወት እንዳያበላሽ ባለመሰልቸት መቻቻልናና ትዕግስትን የሚያበረታታ ዜጋ እሱ የሕወሃትና የክልሉ መንግስት ተቃዋሚ ነው። በሙዚቃቸው፣ በቅኔዎቻቸው፣ በመድረክ ቀልዶቻቸውና በስዕሎቻቸው የስርዓቱን ብልሹነት፣ መበስበስና የማይቀር ውድቀት መልዕክት የሚያስተላልፉ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ሁሉ የዚህ መንግስት ቀንደኛ ጠላቶችና የጭቁኑ ህዝብ ጠበቃዎች፣ የነጻነቱም ተፋላሚዎች ናቸው!



እነኚህን ወጣትና ብዙ ያልተዘመራቸውን ጀግኖች ሳይ ነው እንዳንድ ጊዜ በሃገሬ ላይ ተስፋ እንዳልቆርጥ እንዳውም በተቃራኒው ተስፋዬ እንዲለመልምና እንዲጠነክር የሚያደርጉኝ። ሕብረተሰቡ እንደ ህብረተሰብ በርግጥም አልፈረሰም፣ ወደፊትም ይበልጥ ይጠነክራል በሚል ተስፋ መንፈሴን የሚሞሉት። እስከዚያች የነጻነት ቀን ድረስ ግን ስቃያቸውና መከራቸው ያልተነገረላቸው የሶማሌ ኢትዮጲያዊያን በአቺሌ ሜምቤ ቋንቋ ” ይገረፋሉ፣ ይደፈራሉ፣ ይሰደዳሉ፣ ይዋረዳሉ፣ ይገደላሉ” ።

No comments:

Post a Comment