Wednesday, December 16, 2015

በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ላይ የሚነሳው ጥያቄ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥያቄ መሆን አለበት

ወያኔ አዘጋጀሁት የሚለውን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን አስመልክቶ የተነሳው ተቃውሞ በበርካታ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በተለይም በተማሪዎች ዘንድ እንደገና ተቀስቅሷል። ባለፈው አመት ከዚህ ጋር ተያይዞ የፈሰሰው የበርካታ ንጹሀን ደም ገና ሳይደርቅ ካንዳንድ አካባቢዎች የሚደርሱን መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አሁንም አዲስ ደም መፍሰስ ጀምሯል።

ሕዝብ በስፋት ሳይመክርበትና ፕላኑ በሚሸፍነው አካባቢ ሊያመጣ የሚችለውን ጥቅምም ሆነ ጉዳት ሳይወያይበት ስራ ላይ የሚውል ማስተር ፕላን መዘዙ ብዙ ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ የታወቀ ነው። በሰለጠኑ ሀገሮች የብዙ ሕዝብ ኑሮ ሊያቃውስ የሚችል ፕላን ቀርቶ አንዲት የመንደር ውስጥ መንገድ ለማስፋፋት እንኳን ህዝብ እንዲወያይበት ይደረጋል። ሕዝቡ መወያየት ብቻ ሳይሆን አይጠቅመኝም ካለ ምክንያቱን አቅርቦ እንዲሰረዝ ማድረግም ይችላል።

ሕዝቡ በጉዳዩ ላይ እንዲወያይ አለመደረጉ አንድ ነገር ሆኖ በማስተር ፕላኑ ግንባር ቀደም ተቃውሞ የተሰለፉት የኦሮሞ ተወላጆች በተለይ የኦሮሞ ወጣቶች ብቻ መሆናቸውና የሌላ ብሔረሰብ ተወላጆችን የጨመረ ሰፊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ አለመሆኑ ሌላው አሳሳቢ ነገር ነው። በሌላ አነጋገር  ከማስተር ፕላኑ ጋር የተያያዙ  ብሄረሰብ ዘለል የሆኑና ሁሉም የዴሞክራሲ ሀይል በጋራ ሊቆምላቸው የሚገባቸው ብዙ ጥያቄዎች ጎልተው መውጣት አልቻሉም።   በዚህ ጉዳይ ላይ አስፈላጊ የሆነ ሁሉን አቀፍ ውይይት በተገቢው መጠን አላደረግንም። በዚህም የተነሳ በጥያቄው ዙሪያ ግር የተሰኙና ዝርዝሩ ያልገባቸው ቅን ዜጎች በጣም ብዙ ናቸው። ብዙ ሰዎች አዲስ አበባ ትልቅ ከተማ እንደመሆኗ መጠን ማስተር ፕላኑ አስፈላጊ እንደሆነና ተቃውሞውም ተገቢ እንዳልሆነ ያስባሉ።  እንደውም የኦሮሞ ብሔርተኞች ያነሱት ጥያቄ ጭፍን የግዛት ባለቤትነት ጥያቄ እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም። ይህን ተቃውሞ በማስተባበር ላይ ያሉት የኦሮሞ አክቲቪስቶችም ሌላው የብሔረሰብ ክፍል ጥያቄያቸውን በመደገፍ እንዲቀላቀላቸው ተገቢ ጥረት ሲያደርጉም አይታይም። ሰፊና ብሔረሰብ ዘለል ተሳትፎ እንዲኖር ማድረግ በመጨረሻው ውጤት ላይ ያለውን እንድምታ በቅጡ ያጤኑት አይመስልም።

የወያኔው ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ሹማምንት ይህን ማስተር ፕላን ስራ ላይ ካልዋለ ብለው የሚጣደፉበት አልፎም ጥያቄ ያነሳውን ሁሉ ካለርሕራሄ የሚጨፈጭፉበት ዋነኛ ምክንያት ለሁላችንም ግልጽ ሊሆን ይገባል። የወያኔ ባለስልጣናትና ሎሌዎቻቸው ቅጽበታዊ ሚሊዮነርና ሀብታም ቱጃር ያደረጋቸው የአዲስ አበባ ውስጥና ዙሪያ መሬት መሆኑ ይታወቃል። የወያኔው ሹማምንት በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በብዙ አሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የገበሬ ቤተሰቦችን በማፈናቀል በተቀራመቱት መሬት ከብረው በእንደኛው አለም ሀገራት ላይ የማይታይ የቅንጦት ኑሮ ላይ ናቸው። ይህ የዘረፋ ልምዳቸው ደግሞ ብዙ መሬት ቢዘርፉና ቢሸጡ የራሳቸውና የዘመዶቻቸው ሀብት የት ሊደርስ እንደሚችል አሳይቷቸዋል።  ስለዚህ ብዙ መሬት መዝረፍ ይፈልጋሉ። የሚዘረፈው መሬት የትና የት ድረስ ሊሆን እንደሚችልም ያውቃሉ። የጥድፊያቸውና በተቃዋሚዎቻቸው ላይ የሚያሳዩት ጭካኔ ሚስጥርም ይኸው ነው።

ይህን የግፍና የማናለብኝነት ዝርፊያ ዘርና ብሔረሰብ ሳንለይ ልንቃወመው፤ብሎም በጽኑ ልንታገለው ይገባል። የኦሮሞ ተወላጆች የተለየ ጥያቄ ብቻ ሊሆን አይገባም። ይህ ጥያቄ የኦሮሞ ጥያቄ ብቻ መስሎ የሚታያቸው ኦሮሞዎችም ይህ አስተሳሰብ የተሳሳተ እና ሊታረም የሚገባው እንደሆነ ሊገነዘቡት ይገባል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ጥያቄው ውጤት ወደሚያመጣ ትግል የሚያድገው የሁላችንም ሀገራዊ ጥያቄ ሲሆን ብቻ ነው። ጥያቄውን የብሔር ወገንተኝነት ጥያቄ እንዲሆን ማድረግ የሚጠቅመው ዘራፊውንና አንዱን ብሔረሰብ በሌላው ላይ በመቀስቀስ ፤ በማናቆርና በማስፈራራት ለመቀጠል የወሰነውን ወያኔን ብቻ ነው።

አርበኞች ግንቦት 7 ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በኦሮሞ ወጣቶች እየተደረገ ያለው ተቃውሞ ሐገራዊ ፤ የጸረ ህዝብና የወያኔ ዝርፊያ ፕሮጀክትን እንደመቃወም ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ተቃውሞ እንደሆነ ይገነዘባል። በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ድምጻቸውን በሚያሰሙ ወጣት ኢትዮጵያዊያን ኦሮሞዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጭፍጨፋም በጥብቅ ያወግዛል። በጋራ ትግል በምንመሰርታት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያም እነዚህ ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸውም በጽኑ ያምናል። መላው የዴሞክራሲና የፍትሕ ወዳጅ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህን ህዝብ ያላሳተፈ ፕላንና የዝርፊያ ፕሮጀክት እንዲቃወምና በትግሉ እንዲሳተፍ በዚያውም አንድነታችንን እንዲያጠናክር ጥሪውን ያቀርባል።

የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ዴሞክራሲና የሕዝብ ወሳኝነት ባልተረጋገጠበት ስርዓት ውስጥ በሕዝብና በሐገር ልማት ስም የሚካሔድ ፕሮጀክት ሁሉ ሕግ የማይገዛቸው ዘራፊዎችን ከለላ ለመስጠት የሚደረግ ዝግጅት ነው ብሎ ያምናል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ
አንድነት ኃይል ነው

የወገኖቻችን ስቃይ፣ ችግርና ብሶት በያለንበት ይሰማን፤ ለመፍትሔውም በጋራ እንነሳ!- የአርበኞች ግንቦት 7 መግለጫ

በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ሰበብ በከተማዋ ዙርያ ያሉ ወገኖቻችንን ማፈናቀል በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው። በማስተር ፕላኑ ሰበብ የሚፈናቀሉ ገበሬዎች የሁላችን ወላጆች፣ ወንድሞችና እህቶች ናቸው። በማስተር ፕላኑ ሰበብ የምንፈናቀለው ሁላችንም ነን። ይህን መሰሪ ፕላን በመቃወም ላይ ያሉት የኦሮሞ ተወላጅ ወገኖቻችን ትግል ፍትሀዊ በመሆኑ አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ከጎናቸው ይቆማል።

በዚሁ ወቅት በጎንደር ሌላ አሳዛኝ ጉዳይ ተከስቷል። ህወሓት ከሶስት ሺህ በላይ ዜጎቻችንን ያጎረበት እስር ቤት በእሳት ሲጋይ ዜጎች ተቆልፎባቸው እንዲነዱ ተደርጓል። ከእሳቱ በእድል ያመለጡት በጥይት ታድነዋል። ኢትዮጵያዊያን እንዲህ ዓይነቱን ጭካኔ የሚያውቁት በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ ነው። ይህን ጥቃት በመቃወም ላይ ያሉ የአማራ ተወላጅ ወገኖቻችን ትግል ፍትሀዊ በመሆኑ አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ከጎናቸው ይቆማል።

ግፍ ያልተፈፀመበት የኢትዮጵያ ክፍል ባይኖርም ሰሞኑን በአማራና በኦሮሚያ ላይ በርክቷል። በሁለቱም የአገራችን ክፍሎች የንፁሀን ደም እየፈሰሰ ነው፤ በሁለቱም ቦታዎች የእናቶች ዋይታና እሪታ ጎልቶ እየተሰማ ነው። የህወሓት አገዛዝ የትውልድ ቦታ፣ ቋንቋና ዘር ሳይለይ በኢትዮጵያዊያን ሁሉ ላይ የተደቀነ አደጋ መሆኑ ከምንጊዜውም በላይ ዛሬ ግልጽ ሆኗል።

ለዚህ የምንሰጠው ምላሽ ምንድነው? ዛሬም ኦሮሚያ ውስጥ የሚፈፀመው በደል የኦሮሞ፤ አማራ ውስጥ የሚፈፀመው በደል የአማራ ጉዳይ አድርገን እንወስዳለን? መቸ ነው ኦሮሚያ ላይ ለደረሰው ጥቃት አማራዉ፤ አማራ ላይ ለደረሰው ጥቃት ኦሮሞው የሚቆረቆረው?
የሁላችን የጋራ ጠላት የሆነው ህወሓት መኖሩ በዘውግ የተከፋፈለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ አንድነት የሚያመጣ ታላቅ ኃይል ሊሆን ይገባል። ይህ የመከራና የመጠቃት ወቅት የምንቀራረብበት ወቅት ሊሆን ይገባል። ይህ የመከራ ወቅት በህወሓት ላይ በጋራ የምንነሳበት ወቅት ሊሆን ይገባል። ዛሬ በኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ ማኅበረሰቦች በሙሉ በፀረ-ህወሓት ትግል መቀናጀት ይኖርባቸዋል። ይህ ማድረግ ግዴታችን ነው።

ለችግሮቻችን መፍትሄ የምናገኘው ችግሮቹ ከተፈጠሩበት እርከን በላይ ሆነን ስናስብ እንጂ ችግሮቹ በፈጠሩበት ደረጃ ላይ ቆመን መሆን አይችልም። ችግሮቹ ከተፈጠሩበት እርከን በላይ ለመሆን አገር አቀፍ እይታ መኖሩ እጅግ ተፈላጊ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያን ሁሉ በተለይም የአማራና የኦሮሞ ልሂቃን ይህንን ጉዳይ አበክረው እንዲያስቡበት አርበኞች ግንቦት 7 በጽኑ ያሳስባል።

ግፍ ሞልቶ የፈሰሰበት ወቅት ላይ እንገኛለን። የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሆኑት ሕፃናት በፌዴራል ፓሊስ ጥይት የሚገደሉበት አሳዛኝ ወቅት ላይ ነን፤ ዜጎች በር ተዘግቶባቸው በእሳት እየጋዩ ነው። ሰፊ እና ለም የእርሻ መሬት ለሱዳን በስጦታነት ለመስጠት ዝግጁቱ የተጠናቀቀበት ወቅት ላይ ነን። ከአስር ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተርቧል። በፍትህ እጦት እስር ቤቶች በንፁሃን ዜጎች ተሞልተዋል። ውሀ፣ መብራትና የቴሌፎን አገልግሎት ብርቅ ሊሆኑ ነው። ይህ ሁሉ እየሆነ ግን የሥርዓቱ አገልጋዮችና ደጋፊዎች በህንፃ ላይ ህንፃ እየገነቡ በድሀው ላይ ይሳለቃሉ። የህወሓት አገዛዝ ድህነትን፣ ችጋርን፣ ስደትን፣ የእርስበርስ ግጭቶችን እያባባሰ ኢትዮጵያን እየጋጠ የሚኖር አገዛዝ ነው። አገዛዙ በቀደደልን ቦይ ከተጓዝን ችግሮችን ማባባስ እንጂ ማርገብ እንኳን አንችልም። ይህንን ሥርዓት በቃህ ማለት የአማራ ወይም የኦሮሞ አጀንዳ አይደለም፤ ይህ የሁላችንም – የኢትዮጵያዊያን – ጉዳይ ነው።

ለቀምት፣ ሀረር፣ ሱልልታ እና ሌሎች በርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ውስጥ ለደረሱ ጥቃቶች ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ሀዋሳ፣ መቀሌ፣ አሶሳ፣ ሁመራ፣ ጋምቤላ ውስጥ ተቃውሞ መሰማት አለበት። በጎንደርና ባህርዳር ለደረሰውም ጥቃት አዳማ፣ ጅማ፣ ሆሳዕና፣ ጅግጅጋ፣ አክሱም ላይ ተቃውሞ መሰማት አለበት። በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ለሚደርሰው በደል መላዋን ኢትዮጵያ ሊያሳምም ይገባል። መከፋፈላችን መከራችን አብዝቶታል፤ የህወሓት እድሜን አርዝሟል፤ ይብቃ!

አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የመከራ ጊዜዓችን እንዲያጥር በዘውግ ሀረግ፣ በብሔርና እና በሀይማኖትና ሳንታጠር የወገናችን ህመም ይሰማን፤ ተሰምቶንም ለጋራ ትግል እንነሳ ይላል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!