Monday, December 30, 2013

በአዲስ አበባ የቅርብ ጊዜ የጅምላ መቃብር ተገኘ

December 30, 2013
ሁኔ አቢሲኒያዊ

ነገሩ የተከሰተው አርብ እና ቅዳሜ እለት ነው ከስድት ኪሎ ወደ ፈረንሳይ በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው የጃንሜዳ ጦር ካምፕ(በቀድሞ ስሙ ሦስተኛ ሻለቃ) ግቢ ውስጥ በትንሹ ወደ 6 የሚጠጉ አስከሬኖች በብርድልብስ እንደተጠቀለሉ ተገኝተዋል! አስከሬኖቹ ሊገኙ የቻሉት ለመንገድ ስራ የጦር ካምፑ ግቢ አጥር ወደ ውስጥ ፈርሶ መቆፈር ነበረበት፡፡ በዚህ ሂደት ላይ ነው እንግዲህ በስካቫተር ሲቆፈር በመጀመሪያ ሁለት አስከሬኖች በብርድልብስ እንደተጠቀለሉ ተንከባለሉ፡፡ በዚህ የተደናገጡት ሰራተኞች ለጊዜው ስራቸን ያቋረጡ ሲሆን በበነጋው ቅዳሜ እለት ረፋዱ ላይ በሌላ አቅጣጫ ቁፋሮ ሲያደርጉ በዛም በኩል እዲሁ በብርድ ልብስ የተጠቀለሉ አራት አስከሬኖች በተመሳሳይ ሁኔታ ከአፈሩ ዉስጥ ተገኙ፡፡

በዚህ መሃል ከጦር ካምፑ አካባቢ የተወሰኑ መኮንኖችና ከፍተኛ ማዕረግ(ጄነራሎች)በትከሻቸው ላይ ያለባቸው ሰዎች ወደ ቦታው በመምጣት ስራው እንዲቆም ትእዛዝ ያስተላለፉ ሲሆን በአካባቢው የነበረውንም ሰው ከቦታው አባረው በትነዋል፡፡ በስፋራው ተገኝተው ሁኔታውን ሲከታተሉ እና በስራው ላይም ተሳታፊ የነበሩ ለሰማያዊ ፓርቲ ቅርብ የነበሩ ሰዎች ፎቶ ለማንሳት ጥረት ቢያደርጉም በወታደሮቹ ተመናጭቀዉ ክልከላ ደርሶባቸዋል፡፡ እንደምንጮቻችን እና የምስል ማስረጃዎች ከሆነ አስከሬኖቹ የተጠቀለሉበት ብርድልብስ አንዳችም ሳይቀደድና ሳይበሰብስ ከነአዲስነቱ መገኘቱ ጅምላ ግድያው በቅርቡ የተፈፀመ ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ጥርጣሬን አሳድሯል! በጉዳዩ ላይ ማጣራት ለማድረግ ሙከራ ያደረጉት የሰማያዊ ፓርቲ አባሎችንም ፊት እንደተነሳቸውና ለማናገርም ፈቃደኛ የሆነ ሰው አለማግኘታቸዉንም እንዳዉም ቦታውን ባስቸኳይ እንዲለቁ ከሀይለ ቃል ጋር መታዘዛቸውንም ጨምረውተናግረዋል፡፡

ከወታደሮቹ መሀከል የሆነ አንድ ስምና ሀላፊነቱ ለጊዜው ያልታወቀ ምናልባትም የግቢው አዛዥ ሊሆን የሚችል ሰው ይህ ግቢ ሶስት ስርዓቶችን ያገለገለ በመሆኑ የማናቸው እንደሆነ ለማወቅ ባይቻልም ሰዎች በመሆናቸው ክቡር ናቸውና አፈር አልብሷቸው ብሎ ትእዛዝ ሲሰጥ የሰሙ የአይን ምስክሮች ለምንጫችን ስለሁኔታው አስረድተዋል! በሁኔታው በአካባቢው የነበሩ ሰዎች በእጅጉ ያዘኑና የተደናገጡ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላትና መንግስት ይህን ጉዳይ አጣርተው ለህዝብ ይፋ እንዲሆን አስተያየት ሲሰጡም ተደምጠዋል! በአሁኑ ሰዓት በስፍራው ምንም አይነት የስራ እንቅስቃሴ አይታይም፡፡ አካባቢውም በቆርቆሮ ተከልሏል፡፡

ተጨማሪ ብርድልብሱ ደብረ ብርሃን ሲሆን ዲዛይኑ በኢህአዲግ ዘመን በቅርብ የተጀመረው ነው!

ሁኔ አቢሲኒያዊ
ከፒተርቦሮው ዩ.ኬ

Wednesday, December 25, 2013

በደቡብ ሱዳን ተገደው የተደፈሩ 4 ኢትዮጵያውያን ሴቶች ጁባ ገቡ

ታህሳስ ፲፬( አስራ አራት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም  ኢሳት ዜና :- በደቡብ ሱዳን የተነሳውን የእርስ በርስ ግጭት ተከትሎ የተደፈሩ 4 ሴቶች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሆስፒታል በሚገኝበት ጁባ ደርሰው ምርመራ እየተደረገላቸው ነው። ሴቶቹ መደፈራቸውንና ሆስፒታል መግባታቸውን ኢሳት ለማረጋገጥ የቻለ ሲሆን፣ ሴቶቹ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ያደረገው ጥረት በመስመር ግንኙነት የተነሳ ሊሳካለት አልቻለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ከውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ ጋር በመሆን ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ታውቋል። አምባሳደሩ በዚህ አስቸጋሪ ሰአት ወደ አገራቸው መመለሳቸውን በአገሪቱ ያሉ ኢትዮጵያውያን ተችተዋል።

በሌላ በኩል ግን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሀኖም  የኢትዮጵያን ስደተኞች በተመለከተ ኢምባሲው በቅርበት ጉዳዩን እየተከታተለ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ ለሱዳን ችግር የኢጋድ አገሮች የሽምግልና ጥረት መጀመራቸውንም ገልጸዋል። በሽምግልና ጥረቱ ስለተገኘው ውጤት ግን ያሉት ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ ሱዳን የተፈጠረውን የ እርስበርስ ግጭት ተከትሎ  ጎሳ ላይ ያነጣጠረ የጅምላ ግድያ እንደተፈፀሙ የሚያሳዩ አዳዲስ መረጃዎች በመውጣት ላይ ናቸው።
ጋዜጠኞች ከጁባ የዓይን ምስክሮችን ዋቢ አድርገው እንደዘገቡት ግጭቱን ተከትሎ ከ200 በላይ የሚሆኑ የንዌር ጎሳ ተወላጆች በደህንነት ሀይሎች በጅምላ ተገድለዋል።
ሌላ የጁባ ነዋሪም ሲናገር ብዙዎቹ የጸጥታ ሀይሎች ከዲንካ ጎሳ አባላት ስለሆኑ ኑዌሮችን  እየለዩ ይገድሉ ነበር ብሏል።
ከሳምንት በፊት በጁባ የተቀሰቀሰው ግጭት ወደተለያዩ ቦታዎች ተሸጋግሮ በሪክ ማቻር የሚመሩት አማጽያን  “ቦር” እና “ቤንትዩ” የተሰኙ ቁልፍ ከተሞችን ተቆጣጥረዋል።
ፕሬዜዳንት ሳልቫኪር  የቀድሞ ምክትላቸው መፈንቅለ መንግስት ሊፈፅሞባቸው እንዳሰቡ ክስ ቢያሰሙም፤ ሪክ ማቻር ግን  በተቃውሞ የተነሱት በስርዓቱ እየተፈፀመ ባለው ጎሳ ላይ ያነጣጠረ የመብት ረገጣ እና ጥሰት ተከፍተው እንደሆነ በመግለጽ ነው  ክሱን ያስተባበሉት።
በቀድሞ  ሁለት  የትግል ጓደኛሞች መካከል በስልጣን ማግስት የተከሰተው ይህ ግጭት በኑዌር እና ዲንካ ጎሳዎች መካከል ሙሉ ጦርነት በማስነሳት ደቡብ ሱዳንን ዳግም መውጫ ወደሌለው የጦርነት አዙሪት ውስጥ እንዳይከታት ከፍተኛ ስጋት ማሳደሩን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
በተመሳሳይ ዜና ደግሞ ሰሞኑን በአማጺዎች ቁጥጥር ስር ውላ ነበረችው ቦር በመንግስት ሀይሎች እጅ መውደቋን ቢቢሲ ዘግቧል። የመንግስት ቃል አቀባይ እንደሉት ጦራቸው ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ከአማጽያን እጅ አስለቅቀዋል። አማጽያኑንም እግር በግር እየተከተሉ እየወጉዋቸው ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካይ ማምሻውን እንዳስታወቁት ደግሞ በአገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሳይገደሉ አልቀረም። በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች በጅምላ የተቀበሩባቸውን ቦታዎች ማግኘታቸውን ባለስልጣኑ ገልጸዋል።

Friday, December 20, 2013

አቶ አያሌው ጎበዜም የድል አጥቢያ አርበኛ እንደ ውሃ ላይ ኩበት እመሀል ላይ እንደዋለሉ የማይቀረውን ስንብታቸውን ተሰናበተዋል

አቶ አያሌው ጎበዜም እንደምንም  የመምህርነት ስራቸውን ትተው የድል አጥቢያ አርበኛ በመሆን ገብተው ወይ ራሳቸውን ነፃ ሳያወጡ ወይ ህዝቡን በትክክል ሳያገለገሉ እንዲሁ እንደ ውሃ ላይ ኩበት  እመሀል ላይ እንደዋለሉ የማይቀረውን ስንብታቸውን ተሰናበተዋል፡፡ወያኔ እንደ ሸንኮራ ምጥጥ አድርጎ ተፋቸው፡፡እኔ እስከማውቃቸው አቶ አያሌው ከሌሎች የወያኔ ባለስልጣናት የሚለዮት በሙስና አለመጠርጠራቸው፤ብዙ ማውራት የማይወዱ ሲናገሩም ከባህል እና ከሞራል የማያፈነግጡ፤ለሚኖሩበት ማሀበረሰብ ክብር በመስጠት ሚስታቸው ሳይቀር አብረዋቸው ከሚኖሩት እድርተኞች እኩል መሳተፋቸው ነው፡፡ አቶ አያሌው እንደአባዱላ ገመዳ ብዙ ቤት ገንብተው ለትግሉ ስላስቸገረኝ ውሰዱልኝ ሲሉ አልተደመጡም፡፡እስካሁን ባለኝ መረጃ መሰረት አቶ አያሌው ባህርዳር ከተማ ውስጥ ቀበሌ 14 አካባቢ በማህበር ተደራጅተው በወሰዱት አንድ ቦታ ቤት እንደገነቡ ነው ፡፡ ዘመድ አዝማዳቸውን ስራ በማስገባት አይታሙም ፡፡የአቶ አያሌው ልጆች እንደ ሌሎች የባለስልጣን ልጆች አሜሪካ እና አውሮፓ ወይም አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ ውድ የግል ትምህርት ቤቶች አይደለም  የሚማሩት፡፡እንደማንኛውም ደሃ ቤተሰብ ባህርዳር ውስጥ ባሉ የመንግስት ትምህርቤቶች ያስተምሩ ነበር፡፡
አቶ አያሌው እንግዲህ እነዚህ መልካም ነገር ቢኖራቸውም የተሰጣቸውን መክሊት አባክነው የክልሉ ህዝብ በየቦታው ሲፈናቀል የክልሉ መሬት እንደዳቦ እየተሸነሸነ ሲታደል የተቀመጡባትን ወንበር ላለማጣት በዝምታ ማለፍን መርጠዋል፡፡ይህ ደግሞ በምንም መልኩ ከተጠያቂነት አያድንም፡፡ከሌባ ጋር አብሮ ስርቆት ሂዶ  በቅርብ ርቀት ሲሰርቁ እያዩ ዝም ማለት እና የሰረቀው አብሮኝ ያለው ሰው ነው አንጂ እኔ ነፃ ነኝ ቢሉ ከቅጣት አያመልጡም፡፡እንግዲህ እርሳቸው በስልጣን ላይ በቀዮበት ጊዜ ለጠፋው ሀይወት፤ለወደመው ንብረት፤ለተፈጠረው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድቀት የድርሻቸውን ይወስዳሉ፡፡
መቼም በዘመኔ ወያኔ ስራና ሰራተኛ ተገናኝተው ባይውቁም እንደአማራ ክልል  ባለስልጣናት በእውቀት ድርቅ የተጠቃ የለም፡፡”ሰው ሢታጣ ይመለመላል ጎባጣ” ነው ነገሩ፡፡ሰው ሲታጣ ማለቴ ለወያኔ በታማኝነት የሚያገለግል ማለቴ ነው፡፡አቶ አያሌውን የተኩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በርቀት ትምህርት በማኔጅመት የመጀመሪያ ዲግሪ ሲኖራቸው በ1998 ዓ.ም የብአዴን ቢሮ ውስጥ ይሰሩ ነበር፡፡የተኛው የተምህርት ዝግጅት ተዛምዶ የክልሉየግብርና ቢሮ ኃላፊ ሁነው እንዲሰሩ እንዳበቃቸው የሚያውቀው ወያኔ ብቻ ነው፡፡ይባስ ብሎ ክልሉን የመምራት ሀላፊነት ለሳቸው መስጠት ከምጡ ወደ ዳጡ ነው፡፡ አቶ ገዱን የአማራ ወጣቶች ከከፍተኛ ትምህርቶች ተመርቀው የፓሪቲ አባል ካልሆኑ ስራ እንዳይሰጣቸው በክልሉ ላሉ ሁሉም ዞኖች ትእዛዝ ሲያስተላልፉ በተቃራኒው አባል ለሆኑት ስልክ ብቻ በመደወል እንዲቀበሉዋቸው ያል ምንም ውድድር እና ማስታወቂ  በደብዳቤ ብቻ ሲመድቡ እንደነበር ይታወቃል፡፡በተለይ በ1998ዓ.ም የንግድ እና ኢንዱስትሪ ጽ/ቤት በወረዳዎች መከፈትን ተከትሎ በሁሉም ወረዳዎች የተመደቡ ፈላፊዎች በዚህ አይነት የተመደቡ ነበሩ፡፡አቶ ገዱ የክልል ፕሬዚዳንት ቀርቶ ለቀበሌ አመራርነት ሚያበቃ ስብእና እንደሌላቸው ሚያወቁዋቸው ሁሉ የሚስማሙበት ሀቅ ነው፡፡ግን ምን ይደረግ ወያኔ በሚመራው ሀገር ውስጥ ለሀገር የሚጠቅም ነገር በነፃነት መስራት ስለማይቻል አንዴ አዲሱ ለገሰ፤አንዴ ደመቀ መኮነን፤አንዴ ገዱ አንዳርጋቸው እተፈራረቁ በህዝቡ ትክሻ ላይ ያለከልካይ ይጫናሉ፡፡
በመጽሀፍ ቅዱስ ታሪክ የምናውቀው ደጉ አብረሀም የተወለደው ያደገው ከጣኦት አምላኪ ቤተሰብ ነበር፡፡  እግዚያብሔርም አብርሀምን “አብርሀም አብርሀም ውጣ !እኔ ወደማሳህም ወደዚያ ተራራ ሂድ አለው”፡፡አብርሀምም ቤተሰቡ የሚያመልከው ጣኦት አይን እያለው የማያይ ጆሮ እያለው የማይሰማ “ልክ እንደ ኢህአዴግ”  ነበርና ከፈጣሪው የመጣለትን ትእዛዝ ሳያመነታ ተቀበለው ፡፡በሀጢያት ከረከሰው አካባቢውም ተለይቶ ወጣ፡፡አብርሀም ያደረገው ከሚወደው ቤተሰቡ  በባእድ አምልኮ አብሮ ላለመኖር የግድ መለየት ነበረበት ተለያም፡፡ዛሬ በተለያዮ የስልጣን እርከን በወታደራዊም ሆነ በሲቪል ተቋማት ከወያኔ ጋር እየሰራችሁ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ አብረሀም በደም ከተበከለው ፤ህዝብን አፍኖ በችግር እየገደለ ካለው ስርኣት ራሳችሁ ለይታችሁ ውጡ፡፡አብርሀም ቅድስናን የተቀዳጀው ከባእድ አምልኮው ተለይቶ ነው፡ለጊዜያዊ ሥልጣን ጥቅም ወዘተ ራሳችህን እስካሁን አስገዛችሁ፡፡መጀመሪያ እውነት አለ መስሎአችሁ ገብታችሁ ይሆናል፡፡ግን ወያኔ ጋ ቀርቦ ያላየ የለም ደረጃው ይለያ እንጂ ፡፡ አንድም እውነት የለም ሁሉም ነገር የውሸት የማስመሰል ነው፡፡ወያኔ ጣኦት ነው፡፡ህገ-መንግስቱ፤የመለስ ራዕይ፤የብሄር መብት፤እድገት እና ትርናስፎርሜሽኑ፤የሚወራው ዲሞክራሲ ሁሉም ባእድ አምልኮዎች ጣኦቶች ናቸው፡፡እውነታውን ታውቁታላችሁ፡፡ስለገባችሁበት ነው እንጂ ሁሉም የህወአትን እድሜ ማራዘሚያ ነው፡፡ማንም ከወያኔ ጋር ሁኖ ህሌናው ያመነበትን እንደማይሰራ እናንተም ታውቁታላችሁ፡፡ፍርድቤቶች የሚፈርዱት በህሌናቸው ነው?ጋዜጠኞች እየሰራችሁ ያላችሁት እውነታውን ነው? ወታደሩ  የገንዛ ወንድሙን፣እህቱን  በቆመጥ የሚቀጠቅጠው አምኖበት ነው?፤የሚስኪኑዋ እናትክን ቤት እላይዋ ላይ የምታፈርሰው ህሌናህ ፈቅዶ በችግር ለተቆራመደው ወገናችን መርዳት ስንችል ለምን ተጨማሪ እዳ እንሆንባቸዋለን፡፡ከወያኔ ፍርፋሪ መጠበቅ ለጣኦት የተሰዋ መብላት ነው፡፡ ነው?ከወያኔ አገልጋይነት ተለዩ!ከወያኔ መንደር ውጡ!

ዳዊት 

ዓረና መድረክ ከተምቤን ኗሪዎች ጋር ለመወያየት እሁድ ህዝባዊ ስብሰባ ጠርቷል (አብርሃ ደስታ ከመቐለ/ትግራይ

ዓረና መድረክ ከተምቤን ኗሪዎች ጋር ለመወያየት እሁድ ታህሳስ 13, 2006 ዓም በዓብይ ዓዲ ከተማ (ማዘጋጃቤት አዳራሽ) ህዝባዊ ስብሰባ ጠርቷል። የዓረና አባላት ከትናንት ሐሙስ ጀምሮ በተለያዩ የተምቤን ከተሞች ቅስቀሳ እያካሄዱ ነው። እስካሁን የተምቤን ህዝብ በጥሩ መንፈስ እየተቀበላቸው ሲሆን የአከባቢው አስተዳዳሪዎች ግን እያንገራገሩ ነው። አስተዳዳሪዎች ቅስቀሳ የሚያካሂዱ የዓረና አባላትን ይሰድባሉ፣ ዕንቅፋት ይፈጥራሉ። የዓረና አባላት ቅስቀሳ በማድረጋቸው በፖሊስ ተይዘው ታስረዋል። ቅስቀሳው ግን በሌሎች አባላትም ቢሆን ይቀጥላል። የማይጨው ከተማ አስተዳዳሪዎች በጥሩ መንፈስ ተቀብለውን ነበር። የተምቤኖቹ ግን ለምን አንገራገሩ? ህወሓት ምክንያት አለው።

ኢህአዴግን ሙሉ በሙሉ ለማሸነፍ በትግራይ ክልል መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ትግራይ ክልል የህወሓት መሰረት ነው። ኢህአዴግ ያለ ህወሓት ዋጋ የለውም። ምክንያቱም ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በህወሓት ጠመንጃ ድጋፍ የሚኖሩ እንጂ የህዝብ ድጋፍ የላቸውም። ስለዚህ የህወሓት የትግራይ መሰረት ከተናጋ ኢህአዴግ ይናጋል።

ከትግራይ ክልል ደግሞ ሁለት ቦታዎች በደምብ መያዝ በቂ ነው፤ ተምቤንና ዓጋመ። በፖለቲካ ዘርፉ የተምቤን ህዝብ ከጎንህ ማሰለፍ ከቻልክ መለው ትግራይ መቆጣጠር ቀላል ይሆናል። (ምክንያት ሌላ ግዜ)። ሁለተኛው ቁልፍ የትግል መሰረት የዓጋመ ህዝብ ነው (በኢኮኖሚ ዘርፍ)። (ምክንያት ሌላ ግዜ)። የዓጋመ ህዝብ ከጎንህ ለማሰለፍ ግዜ ሊወስድ ይችላል። የተምቤን ግን ትንሽ ጥረት ማድረግ በቂ ነው። እናም ጉዟችን ወደ ተምቤን ነው።

ህወሓትም ይሄ የተምቤን ጉዳይ በደምብ የተረዳው ይመስላል። በተምቤን ዓብይ ዓዲ ከተማ በምናደርገው ህዝባዊ ስብሰባ ለመረበሽ የተዘጋጀ ይመስላል።

እሁድ በዓብይ ዓዲ ከተማ ማዘጋጃቤት አዳራሽ ስለሚደረገው ስብሰባ ተጨማሪ ዘገባ በወቅቱ ይቀርባል።

ተጨማሪ ማብራሪያ፡ ከህወሓት የትጥቅ ትግል ወቅት ጀምሮ በትግራይ ክልል ከሚገኙ ህዝቦች ዓቅሙ እያላቸው በህወሓት የተንኮል አገዛዝ ምክንያት ተጨቁነው (ታፍነው) የሚኖሩ ህዝቦች የተምቤንና የዓጋመ ናቸው። የተምቤን ህዝብ የፖለቲካ ዓቅም አለው። የዓጋመ ህዝብም የኢኮኖሚ ዓቅም አለው። ሁለቱም ህዝቦች (የተምቤንና ዓጋመ) መቀስቀስ ከተቻለና አብረው ከሰሩ መላው ትግራይ አንቀሳቅሰው ህወሓትን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ ይችላሉ። ህወሓት አሁንም የሁለቱም ህዝቦች መነሳት ያስፈራዋል። ተምቤኖች በፖለቲካ እንዳይሳተፉ ይደረጋል፤ ዓጋሜዎቹም በኢኮኖሚ እንዲዳከሙ ይደረጋል። ተምቤኖች እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ለዚህም ነው የህወሓት አስተዳዳሪዎች በተምቤን ለሚደረግ የስብሰባ ቅስቀሳ ለመረበሽ የተነሱት (የተምቤን አስተዳዳሪዎች የተምቤን ተወላጆች አይደሉም)። ህወሓት በተምቤንና ዓጋመ ምንም ድጋፍ የለውም። በጠመንጃ ሃይል ነው የሚገዛው።

Thursday, December 19, 2013

የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን በማሰጠትና ለዜጎች ሞት የሚጠየቁት አቶ አያሌው ጎበዜ ስልጣናቸውን ለቀቁ

(ዘ-ሐበሻ) የአማራ ክልል መሬቶች ለሱዳን እንዲሰጡ ከገዢው ሕወሓት ጋር በመተባበር ወንጀል፣ እንዲሁም ከጉራፈርዳ ተባረው
ወደ አማራ ክልል የመጡ ዜጎች የሚቀበላቸው የክልል መስተዳድር ጠፍቶ ለርሃብና ለሞት በመዳረጋቸው በዚህም ወንጀል እንደሚጠየቁ የሚነገርላቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አያሌው ጎበዜ ስልጣናቸውን አስረከቡ።

መንግስታዊ ሚድያዎች አቶ አያሌው ጎበዜ “በመተካካት” ሂሳብ ስልጣኔን ተረክበውኛል ሲሉ ይዘግቡ እንጂ የአማራ ክልል ምክር ቤት በአስቸኳይ ተሰብስቦ ይሄን ውሳኔ ማጽደቁ ከበስተጀርባው የተደበቀ ምስጢር ሳይኖር እንዳልቀረ ብዙዎች ይገምታሉ። በተለይም አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ሰሞኑን አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከሱዳን ጋር የኢትዮጵያን መሬቶች አሳልፈው ለመስጠት ከተፈራረሙ በኋላ የአቶ አያሌው ስልጣኔን ልልቀቅ ጥያቄ ምንልባትም ለሱዳን ከሚሰጠው የኢትዮጵያ መሬት ጋር በተያያዘ ሊሆን እንደሚችል አስተያየታቸውን ለዘ-ሐበሻ ሰጥተዋል።

የአማራ ክልል አስቸኳይ ስብሰባውን ከትናንት ምሽት ጀምሮ በባህር ዳር ያካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት ክልሉን ላለፉት 8 ዓመት ተኩል የመሩትን የአቶ አያሌው ጎበዜን ጥያቄ ወዲያውኑ በመቀበል ከስልጣን ያወረዳቸው ሲሆን በምትካቸውም በሕወሓት ተላላኪነታቸው ከአቶ ደመቀ መኮንን አይተናነሱም የሚባሉት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተተክተው ተሾመዋል። አቶ ገዱ የአማራ ክልል ም/ል ፕሬዚዳንትና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን አቶ አያሌው አልፈጽምም ሲሉ የነበሩ ሥራዎችን ለሕወሓት በማደር ይሰሩ እንደነበር እርሳቸውን የሚያውቁ ወገኖች ለዘ-ሐበሻ ጠቁመዋል። በተለይም አምባገነንና እኔ ያልኩት ይድመጥ የሚል ባህሪይ እንዳላቸው የሚነገርላቸው አቶ ገዱ የአማራ ክልል ስር ያሉ የኢትዮጵያ መሬቶችን ለሱዳን በመስጠት ከሕወሓት ጋር አብረው እንደሚሰሩ ይጠበቃል።

አቤል የተባሉ በክልሉ የሚኖሩ በፌስቡክ ዘ-ሐበሻን የሚከታተሉ አንድ አስተያየት ሰጪ በሰጡት አስተያየት “ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ክቡር አቶ አያሌው ጎበዜ ዛሬ በአቶ ደጉ አንዳርጋቸው የተተኩበት አስቸኳይ ጉባኤ አንደምታው ምን ይሆን? ምን አልባት ከሠሞኑ የሚሠሙ ወሬዎችን እልባት ለመስጠት ይሆን? ያ ማለt ዐድርቃይን ለትግራይ፣ መተማን ለሱዳን፣ ጃዊ አካባቢ ያለ የአማራ ክልል ግዛቶችን ለመስጠት መሠናክሉን ከወዲሁ ለማቅለል ይሆን እንዴ? ያ ምርጫ፣  ዘመን ሣይጠናቀቅ ከስልጣን አቶ አያሌውን ማንሣት ምን ማለት ነው? እርሣቸው ለክልሉ ልዑላዊነት መከበር ጥብቅና የሚቆሙ ታማኝ መሪ ስለነበሩ ገለል ለማድረግ የታለመ ሹም ሽር ነው የሚል ግምት አለኝ” ብለዋል።

ሌላው የዘሐበሻ የፌስቡክ ተከታይም እንዲሁ “የአማራን ክልል መሬት ለሌላ አሳልፌ አልሰጥም በማለታቸው ስልጣናቸውን እንደለቀቁ ነው” የማምነው ሲሉ አስተያታቸውን ሰጥተውናል።

አንድ ቀን በኢትዮጵያ ነፃነት ሲመጣ ምንም እንኳ እርሳቸው አልፈረሙም፤ የፈረሙት አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው የሚባል ወሬ ቢኖርም አቶ አያሌው ጎበዜ ለሱዳን በተሰጠው መሬት፣ በአማራ ክልል ለደረሱ ጭፍጨፋዎች፣ በዜጎች መፈናቀል ዙሪያ ላሳዩት ቸልተኝነት ለፍርድ ይቀርባሉ የሚሉ ወገኖች ብዙ ናቸው።

Wednesday, December 18, 2013

ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ በኖርዎይ በርገን ከተማ በደመቀ ሁኔታ ተካሔደ

በበርገን ከተማ ለመጀመርያ ግዜ በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዎይ  በርገን ቅርንጫፍ አስተናጋጅነት በዲሴምበር 14፥2013 የተዘጋጀው ህዝባዊ ስብሰባ በደመቀ ሁኔታ የተጠናቀቀ ሲሆን ከ100 በላይ የሚገመት ህዝብ የተገኘ ሲሆን ከተለያዩ የኖርዎይ ከተሞች የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን በዝግጅቱም ላይ ተገኝተዋል፥፥

በዝግጅቱ ላይ ተጋባዥ እንግዶች የነበሩት

1ኛ. ዶ/ር ታደሰ ብሩ የግንቦት7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ስራ አስፈጻሚ አባል
2ኛ. አቶ ዮሃንስ አለሙ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዎይ  ዋና ሊቀመንበር
3ኛ. ዶ/ር ሙሉአለም አዳም የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ በኖርዎይ የድርጅት አባል ናቸው፥፥

የውይይት መድረኩ ከመጀመሩ በፊት በሳውዲ አረቢያ እየተሰቃዩ፥ እየተገደሉ እንዲሁም በግፍ ኢሰብአዊ ድርጊት ለተፈፀመባቸው ወገኖቻችን የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረ ሲሆን የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዎይ  የበርገን  ቅርንጫፍ ጽ/ት ሰብሳቢ አቶ ሹሜ ወርቁ አጭር የመክፈቻ ንግግር ካረጉ በኋዋላ ተጋባዥ እንግዶቹ በየተራ ስለሚመሩአቸው ድርጅቶችና የወቅቱን የሃገራችንን አስከፊ የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተና ሁሉም የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አብረው በስምምነት የሚሰሩበትን ሁኔታ ማምጣት እንዳለብን እንዲሁም ስለ  መደራጀት አስፈላጊነት ሰፋ ያለ ማብራርያ  ሰጥተዋል፥፥

ዶ/ር ታደሰ ብሩ ስለ ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዓላማ ራእይና ግብ እንዲሁም ስለውጭ እምቢተኝነት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከሰጡ  በኋላ ሁሉም ኢትዮያዊ ግንቦት7ትን እንዲቀላቀልና ሃገራችን ኢትዮጵያ ከገባችበት አዘቅት ውስጥ ተባብረን እንታደጋት በማለት  ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተለያዩ ድርጅቶች ስር ተደራጅቶና ታቅፎ መንቀሳቀሱ ያለውን ጠቀሜታና የሐይማኖትና የሲቪክ ማህበራትን ማደራጀትና ማጠናከር ጠቃሚ መሆኑን አሳስበዋል፥፥ ፥፥

 አቶ ዮሃንስ አለሙ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዎይ  ዋና ሊቀመንበር ስለ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ አመሰራረትና የደረሰበትን ደረጃ እንዲሁም ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ በሰፊው ገለጻ  ያደረጉ ሲሆን  ከህዝቡም  ለቀረበላቸው ጥያቄም  ምላሽ ሰጥተዋል፥፥

በተጨማሪም ዶ/ር ሙሉዓለም አዳም በኖርዎይ የስደተኞች አኗኗር ዙሪያ ያለውን ችግር እንዲሁም ሁሉም የተቃቃሚ ድርጅቶች አንድ ላይ ሆነው እንዲሰሩ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በመጨረሻም የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዎይ የበርገን ቅርንጫፍ በተቋቋመ በአጭር ግዜ ውስጥ የደረሰበት ደረጃም በእጅጉ አስደሳች እንደሆነ በመግለፅ ያላቸውን አድናቆት ገልጸው ህዝቡ ለነጻነት ለሚደረገው  ትግል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፥፥

እንዲሁም በዝግጅቱ ላይ በሐና ሰመረ ሐቅ ተሰደደ በሚል ርእስ አጭር ግጥም የቀረበ ሲሆን በመቀጠልም በሎሚታ ገብረሚካኤል በምስል በተደገፈ በቀረበው የኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ከነገስታት ስርአት እስከ ሐገራችን በወያኔ አገዛዝ ስር ወድቃ አሁን የደረሰችበትን ሁኔታ የሚያሳይ ዘገባ ለታዳሚው ቀርቧል፥፥

በመጨረሻም ለእንግዶቹ የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርቦ ውይይት ከተደረገ በኋላ ዝግጅቱ የግንቦት 7 ህዝባዊ ሐይል መዝሙርን በመዘበር በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል፥፥

የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዎይ  የበርገን  ቅርንጫፍ ጽ/ት

ዲሴምበር 14፥2013

Thursday, December 12, 2013

በኢትዬጲያ ሙስሊሞች ታሳሪዎች ላይ መንግስት የጥፋተኛነት ውሳኔ አስተላለፈ

መንግስት በኢትዬጲያ ሙስሊሞች ላይ የጥፋተኘነት ውሳኔ ማስተላለፉን ምንጮች አስታወቁ፡፡ ለታህሳስ 3 በተቀጠረው የብይን ቀነ ቀጠሮ መሰረት 10 ተከሳሾችን ነፃ ናቸው ሲል ፍርድ ቤቱ ያሰናበተ ሲሆን የተቀሩት ላይ ግን በሽብር ድርጊት ፈፃሚነት ወንጀል ጥፋተኛ ናችሁ ሲል ብይን አስተላልፏል፡፡ በዚህም መሰረት ሁሉም በዕድሜ የገፉት አባቶች ዶ/ር ከማል ገለቱ፣ሼህ አብዱረህማን፣ሼህ ሃጂ ኢብራሂም፣ ሼህ ጣሂር፣.ሼህ ሱልጣን አማን፣ ኡስታዝ ጀማል ያሲን ፣ኡስታዝ ሃሰን አሊ ፣ወንድም አሊ መኪ ፣ ወንድም ሀሰን አቢ እና ወ/ሮ ሃቢባ መሃመድ በነፃ ፍርድ ቤቱ እንዲሰናበቱ መወሰኑ ተዘግቧል፡፤ በተቀሩት ላይ ደግሞ የጥፋተኘነት ክስ በማስተላለፍ ለጥር 22 የመከላከያ ምስክራቸውን እንዲያቀርቡ ውሳኔ በማስተላለፍ ችሎቱ ተጠናቋል፡፡

Tuesday, December 10, 2013

ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በአባይ ግድብ ዙሪያ እንደገና ጥናት እንዲካሄድ ተስማሙ

ታህሳስ ፩(አንድ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም  ኢሳት ዜና :-ብሉምበርግ እንደዘገበው  ከአራቱም አገራት የተውጣጣ ኮሚቴ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከተቋቋመ በሁዋላ፣ በግድቡ ላይ ጥናት የሚካሂዱ ምሁራንንና ይመርጣል። ይህ ቡድን ጥናቱን ሲያጠቃልል ለሶስቱም መንግስታት የጥናት ውጤቱን ያቀርባል።
ከዚህ ቀደም የተቋቋመው አንድ አለማቀፍ ቡድን በግድቡ ፕሮጀክት ላይ ተጨማሪ ጥናት እንዲካሄድ ጠይቆ ነበር። ባለፈው ወር በሚቋቋመው ኮሚቴ ላይ አለማቀፍ ተወካዮች እንዲገኙ ግብጽ ያቀረበችውን ጥያቄ ኢትዮጵአ አልተቀበለችውም ነበር። አሁን ግብጽ አቋሟን መቀየሩዋንና ኮሚቴውን በሶስቱ አገሮች ወኪሎች ለማካሄድ መስማማቷን ዘገባው አመልክቷል። የሶስቱም አገራት ወኪሎች በጥር ወር መግቢያ ላይ እንደገና ሱዳን ላይ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዋል።

Monday, December 9, 2013

ማንዴላና የማንዴላ የማይመስሉ እዉነቶች

ባለፈዉ ዓመት ደግሞ ሳይንቲስቶች አንድ ግንደ ቆርቁር መሰል የጥንት ወፍ ዝርያ አገኙ። «ኔልሰንማንዴላ» ብለዉ ሰየሙት።ማንዴላ ጀርመናዊዉ ፖለቲከኛ እንዳሉት ታሪክን የዘወሩ ታላቅ ሰዉ ነበሩ።በዚያ ዘመን ግን ሰዉ መሆናቸዉን እንኳ ያወቁት ካንዲት የጥቁሮች ነፃ ሐገር ሲደርሱ ነበር።1962።



ማንዴላ እና ማንዴላን የማይመስሉ ማንዴላዎች።ሰዉዬዉ ሞቱ።ሐሙስ።ዕሁድ ይቀበራሉ።ሥራ ምግባራቸዉን እየጠቃቀስን፥ የማንዴላ የማይመስሉ ድርጊቶችን ባጭሩ እንቃኛለን።አብራችሁኝ ቆዩ።

ማንዴላ፥ አንዴ እንዲሕ ብለዉ ነበር አሉ።«እንዲያዉ ሁሌም የሚሞክርን ሐጢያተኛ እንደ ቅዱስ ካለሰብክ በስተቀር እኔ ቅዱስ አይደለሑም።» ይበሉ እንጂ በተለይ ከእስር ቤት ከተፈቱ በኋላ አብዛኛዉ ዓለም እንደ ከከሰዉ በላይ ሰዉ ይመለከታቸዉ ነበር።ሚሊዮኖች ሊያዩ፥ የተሳካላቸዉ ሊያነግሩ፥ ሊጨብጡ፥ ሊያቅፏቸዉ በሚመኙበት ወቅት ግን በቴሌቪዥን መስኮትም አልታይም አሉ።ግን በተቃራኒዉ እኔ እደዉልላችኋለሁ።

«የአደባባይ እንቅስቃሴዬ ከዛሬ ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል።እንዳትደዉሉሉኝ። እኔ እደዉልላችኋለሁ።»

የመጨረሻቸዉ መጀመሪያ ነበር።ባንድ ወቅት ግን «ትምሕርት» አሉ «ዓለምን የምትለዉጥበት መሳሪያ ነዉ።» የሌላዉን አናዉቅም ወይም አያገባንም።እሳቸዉ ግን ያሉትን ከማለታቸዉ ከብዙ ዘመን በፊት ተማሩ።በሕዋላም ዓለምን በርግጥ ለወጡ።ዓለምን የለወጡበትን ትምሕርት በ1925 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ኤ ከማለታቸዉ በፊት ግን ወላጆቻቸዉ እንደ አፍሪቃዊ ባሕል-ወግ ያወጡላቸዉ ሥም ለአዉሮጳዉያን ቅኝ ገዢዎች እንዲመች፥ በአዉሮጳዉያን ቅኝ ገዢዎች ሲለወጥ መቀበል ግድ ነበረ ባቸዉ።

Sunday, December 8, 2013

የመለስ ጎጂ ሃሳቦችና ድርጊቶች

December 5, 2013
የኢትዮጵያ ሲቪክ ንቅናቄ
Ethiopian Civic Movement
Email: ethiocivic@gmail.com
ሕዳር 2006

Click here for PDF

የኢትዮጵያ አንድነትንና የመንግስት ስርዓቱን የሚመለከቱት የመለስ ሃሳቦችና ድርጊቶች ለኢትዮጵያ ህዝብ ከባድና አሳሳቢ ትርጉም አላቸው፡፡ የአንድነቱ ጥያቄ የኢትዮጵያ እንደ አገር የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ሲሆን፣ ስርአቱ ደግሞ በኢትዮጵያ ህዝብ መብቶች ላይ ማን መወሰን እንደሚችል ያመለክታል፡፡ የአገር ህልውና እና የህዝብ መብትን ያህል ትልቅ ጉዳይ ሊኖር ስለማይችል ክብደቱና አሳሳቢነቱ አያጠያይቅም፡፡

መለስ አንድነትን በሚመለከተው ሃሳቡ ትግራይን ከመገንጠል ኣላማ ጀምሮ ሳይተገብረው ቢቀርም፤ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ አድርጓል፤ ህዝብን በቋንቋ ክልሎች ከፋፍሎ በጉራ ፈርዳና ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ለተከሰቱት አማሮችን የማፈናቀል ግፍ መሰረት ጥሏል፤ የመገንጠል “ህገ መንግስታዊ” አንቀፅ አዘጋጅቷል፤ ለሱዳን መሬት አድሏል፤ ዜጎችን አፈናቅሎ ለም መሬት ለውጭ ድርጅቶች በርካሽ ለረዥም ጊዜ አከራይቷል፡፡

የመንግስት ስርዓቱ በቃላት መድብለ ፓርቲ በተግባር ያንድ ፓርቲ አፋኝ ስርዓት ነው፡ስለዚህም ስርዓቱ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ወሳኙ መለስ እንደነበረ ለ21 ዓመታት ደጋግሞ አረጋግጧል፡፡ ሰውየው በኢትዮጵያ በነበሩ መንግስታት በተለመደ መሳሪያ ማለትም የፈላጭ ቆራጭነት ስልጣንን በመጠቀም፣ በኢትዮጵያ ግን ያልተለመደና በውጭ ሃይሎችም ያልተሳካ፣ ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማ ለመተግበር ሞክሯል፤ በከፊልም ተሳክቶለታል፡፡

Friday, December 6, 2013

ኔልሰን ማንዴላ እና ኢትዮጵያ!!

ecember 6, 2013
የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ በ95 አመታቸው ከዚህ አለም ሲለዩ፤ የተለያዩ አገሮች እንደየራሳቸው ግንኙነት የራሳቸውን ታሪክ ሲያወሩ ነበር። የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ሃዘናቸውን ሲገልጹ ከማንዴላ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በመግለጽ ነበር። እኔ በምኖርበት አትላንታ ከተማ ዜናው ሲቀርብ፤ ኔልሰን ማንዴላ አትላንታ በመጡበት ወቅት፣ ከነአንድርው ያንግ ጋር ሆነው የማርቲን ሉተር ኪንግ ማዕከልን ስለመጎብኘታቸው ነበር – ዋናው ዜና። ሁሉም አገር ስለማንዴላ የየራሱ ትዝታ አለው። ኢትዮጵያውያንም ስለኔልሰን ማንዴላ የራሳችን ታሪክ እና ትዝታ አለን። እናም ማንዴላ የዛሬ 51 አመት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ስለነበረው ጉዳይ በማውጋት ታሪካችንን እንጀምራለን

በዳዊት ከበደ ወየሳ

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት አቶ ከተማ ይፍሩ በ1962 ዓ.ም አራተኛው የፓን አፍሪካ ስብሰባ በኢትዮጵያ እንዲደረግ ጃንሆይን ፍቃድ ጠየቁ። ጃንሆይ በጉዳዩ ተስማሙና በፌብሩዋሪ 1962 ዓ.ም የአፍሪካ ታዋቂ የነፃነት ታጋዮች ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ከእነዚህም መሃከል ሚስተር ኦሊቨር ታምቦ፣ ሚስተር ሮበርት ሙጋቤ፣ ሚስተር ኬኔት ካውንዳ እና ሚስተር ኔልሰን ማንዴላ ይገኙበታል። (በኋላ ላይ እነዚህ ወጣት ታጋዮች የየአገራቸው ፕሬዘዳንት ሆነዋል) ይህ ጉዞ በተለይ ለኔልሰን ማንዴላ በህይወታቸው ውስጥ ልዩ ስፍራ የሚሰጡት ነው።

Thursday, December 5, 2013

ወያኔ የአፄ ምኒልክ 100ኛ አመት መታሰብያ በዓል እንዳይከበር ፍቃድ ከለከለ

የሰማያዊ ፓርቲ የአፄ ምኒልክ 100ኛ አመትን በተለያዩ ዝግጅቶች አስቦ ለመዋል በጃንሜዳ የመሰብሰብ ፍቃድ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ ነበር፣ ይሁንና መንግስት ጥያቄውን ተልካሻ ምክንያቶችን በመደርደር ውድቅ ማድረጉን የሚገልጽ ደብዳቤ ለሰማያዊ ፓርቲ ልኳል።



brhanutekleyared

የፊታችን ታህሳስ 3 የእምዬ ምኒልክን 100ኛ እረፍት በሰማያዊ ፓርቲ አዘጋጅነት እንደሚዘክር የታወቀ ነዉ፡፡ በፕሮግራሙ ላይም በርካታከሀገር ዉስጥና ከዉጪ ሀገር ምሁራን ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ይገኛሉ ተብሉ ይጠበቃል፡፡ የፕሮግራሙ አዘጋጅ ሰማያዊ ፓርቲ ለዝግጅቱ በሚያስፈልጉ ጉዳዩች ላይ ስራ እየሰራ ይገኛል! በስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ አዋጅ መሰረትም ስብሰባ እንደሚያደርግ ለስብሰባና ሰልፍ ማሳወቂያ ክፍል ደብዳቤ በትናንትናዉ እለት ያስገባ ሲሆን ዘሬ በደብዳቤ የተመለሰዉ መልስ እጅጉን አስቂኝና አጠያያቂ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡

በደብዳቤዉ ላይ ለምታደርጉት ስብሰባ እዉቅና ልነሳጥችሁ አንችልም ምክንያቱም የፖሊስ ጥባቃ መመደብ አንችልም የሚል ነዉ፡፡ የሚገርመዉ ደግሞ የፅፈት ቤቱ ሀላፊ ተብዬዉ አቶ አሰግድ በንቀት ደግሞ ማናችሁና ምኒልክ ምናምን የምትሉት ደግሞ ምኒልክ ማነዉ በሚል በእብሪት የመለሰዉ መልስ ነበር፡፡

እንኳን ድንኳን ጥሎ ለመሰብሰብ ይቅርና ጎዳና ሙሉ ህዝብ በመላበት የሩጫ የሰልፍ መሰል የገዢዉ ፓርቲ መልካም ፈቃድ ያገኙ ፕሮግራሞች ከህዝቡ እኩል ፌደራል ፖሊስ ለጥበቃ እንደሚታዘዝላቸዉ እየታወቀ ፤ በሌላ መልኩም በድፍረት እንወጣለን ብለን በተለያየ ምክንያት በተጠሩ ሰልፎች ላይ ለድብደባ የሚላከው ቁጥር ስፍር የሌለዉ የፀጥታ ሀይል አሁን ምን ቢውጠው ነዉ የጥበቃ የሚሆን የሰዉ ሀይል ልናስተባብር አንችልም ስለዚህ ዝግጅታችሁን እዉቅና አንሰጠዉም መባሉ??? ይህ ከእብሪት በላይ ምን ሊሆን ይችላል!!!?

ያም ሆነ ይህ ዝግጅቱ በታቀደለት ምልኩ እንደሚፈፀም በተለመደ ቁርጠኝነት ላይ ነን! ሲፈልጉ ለጥበቃ የከለከሉትን ሀይል ለድብደባ ይላኩት!!! እኛ የምንዘክራቸዉ ፍርሃት ካልፈጠረባቸዉ ሞተዉም መንፈሳቸዉ ካልተለየን እምቢ ባይ አባቶቻችን ተወልደናል፡፡
ድል ለኢትየጵያ ህዝብ!!!

Wednesday, December 4, 2013

ኢህአዴግ ለግንቦት7 ያቀረበው የእንደራደር ጥያቄ የተለያዩ አስተያየቶችን እያስተናገደ ነው

ህዳር (ሃያ አራ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚኖሩ ዜጎች በስልክ እየሰጡ ባለው አስተያየት  ግንቦት7 ከኢህአዴግ ጋር መነጋገሩን አይደግፉም። አብዛኞቹ የሚሰጡት ምክንያት ደግሞ “ኢህአዴግ ተዳክሟል፣ ኢህአዴግ የሚታመን ድርጅት አይደለም” የሚሉ ናቸው። በዚህ ዙሪያ ኢትዮጵያውያን የሰጡት አስተያየት የሚከተለውን ይመስላል
በሌላ በኩል ደግሞ የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን የድርድሩ ዜና መልካም ወሬ መሆኑን ለኢሳት በላኩት የኢሜል መልክት አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ፓርቲዎች በሰላም ተነጋግረው ለአገራቸው ቢሰሩ መልካም መሆኑን የጠቀሱት እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች ድርድሩ ከልብ የመጣና ኢህአዴግ እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት ዝግጁ ከሆነ፣ ለአገሪቱ መልካም ዜና ነው ብለዋል።
ኢህአዴግ ለግንቦት7 የድርድር ጥያቄ ማቅረቡን መዘገባችን  ይታወቃል። ግንቦት 7 በተለያዩ ምክንያቶች የቀረበለትን  ድርድር ሳይቀበለው ቀርቷል።

Tuesday, December 3, 2013

የወያኔ አገዛዝ በመልዕክተኞቹ በኩል ላቀረበው የ“እንደራደር” ጥያቄ ከግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የተሰጠ ምላሽ

ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ የገነባዉ ሥርዓት በከፍተኛ ችግሮች የተወጠረ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የመሪው ሞት በወያኔ መሀል ያስከተለው ቀውስ፤ የሕዝብ ሁለገብ ትግል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበት መሄድ የፈጠረበት ስጋት እና ምርጫ በደረሰ ቁጥር የሚደርስበት ጭንቀት መጨመር ተደማምረው ውጥረቱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ እያደረሱት መሆኑን የሚያሳዩ በቂ ምልክቶች አሉ። የእስካሁኑ ተሞክሮዓችን እንደሚያሳየው ወያኔ ውጥረት ሲበዛበትና መዉጪያና መግቢያዉ ሲጠፋዉ ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶችን “እንወያይ፣ እንደራደር” በማለት ለውጥረት ማስተንፈሻ ጊዜ የሚገዛ መሆኑን ነው። ሰሞኑን በወያኔ አገዛዝ መልዕክተኞች በኩል የደረሰንን “የእንደራደር” ጥያቄ ንቅናቄያችን በዋናነት ያየው ወያኔ እንደለመደው ድርድርን ለውጥረት ማስተንፈሻነት ለመጠቀም እየሞከረ መሆኑን ነው።

Monday, December 2, 2013

አይ አበሻ! አበሻና ሆድ፤ ክፍል ሁለት (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም )

December 2, 2013
አበሻ ድግስ ይወዳል፤ ድግስ የሚወደው መብላትና ማብላት ስለሚወድ ነው፤ ለመብላት የአበሻ ምክንያቱ ብዙ ነው፤ ልጅ ተወለደ ብሎ መብላት ነው፤ ልጅ ክርስትና ተነሣ ብሎ መብላት ነው፤ ልጅ አገባ ብሎ መብላት ነው፤ ልጅ ሞተ ብሎ መብላት ነው፤ አበሻ ሰው ቀብሮ ሲመለስ በንፍሮ ይጀምርና ቀስ በቀስ ወደሌላው ይተላለፋል።



ሃይማኖትም ቢሆን ለመብላት ካልሆነ የነፍሱ ጉዳይማ በጣም ሩቅ ነው፤ ሕያዋን ለነገሥታት፣ ሙታን ለካህናት ይገብራሉ፤ በሚለው መመሪያ መሠረት
ግብር መቀበል ያለ ነው፤ ክርስቶስ ተወለደ መብላት ነው፤ ክርስቶስ ተጠመቀ መብላት ነው፤ ክርስቶስ ሞተና ተቀበረ መብላት ነው፤ ክርስቶስ ተነሣ መብላት ነው፤ ማርያም አረገች መብላት ነው።

ማኅበርም የሚጠጣው (የሚበላው ለማለት ነው፤) ለመብላት ነው፤ አምላክ በተለያዩ ስሞቹ፣ ቅድስት ማርያም በተለያዩ ስሞችዋ፣ መላእክት፣ ቅዱሳን፣ ሰማዕታት ሁሉ ለመብላትና ለማብላት ያገለግላሉ፤ ወደመንግሥተ ሰማያት ለመግባት አማላጅ ሊሆኑ የሚችሉ ሁሉ ማኅበር ለመብላት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፤ የሌሎች አገሮች ክርስቲያኖች በመብል አይመለሱም፤ ገበያቸው በጠገራ ብር ነው፤ ስለዚህም አብሮ መብላት ብሎ ነገር የለም።

አበሻ የሚበላው የመጣውን ሲቀበል ብቻ አይደለም፤ የሚሄደውን ሲሰናበትም መብላት ይወዳል፤ ሞትም ቢሆን ለመብላት ምክንያት ነው፤ ቀብር ብሎ እዝን እያቀረቡ መብላት ነው፤ ሠልስት ብሎ መብላት ነው፤ ለሰባት መብላት ነው፤ ለዓርባው መብላት ነው፤ የሙት-ዓመት ደግሶ መብላት ነው፤ በቀብር ላይም ቢሆን ለቅሶውም ‹‹ሆዴ! ሆዴ!›› ነው።

ለአበሻ ጾምም ቢሆን ለመብላት ነው፤ የጾም ትልቁ ምሥጢሩ ምግብ እንዲናፍቅ ለማድረግ ነው፤ የፍስኩ የተትረፈረፈ ምግብና ጥጋብ ባይኖር ማን ይጾማል? የለየላቸው ጠጪዎች በሁዳዴ መለኪያውንና ብርጭቆውን አርግፍ አድርገው የሚተውት ሲፈሰክ በናፍቆት ዊስኪውንና ቢራውን ለመጋት ነውኮ! ይህ ባይሆን አንድ ጊዜ ሞጣ ያየሁትየበግ ሌባ ለምን ይጦም ነበር? ታሪኩ እንዲህ ነው፤ በሞጣ አውሮጵላን ማረፊያ አንድ የበግ ቆዳ የያዘ ሰውዬ በፖሊሶች ይጠበቃል፤ እንደሰማሁት በግ ሰርቆ ጫካ ይወስድና ቆዳውን ገፎ ለመሸጥ ወደገበያ ሲሄድ ተይዞ ነው፤ የሁዳዴ ጾም ስለነበረ ሥጋውን ለማይጾሙ አውሬዎች ጫካ ውስጥ ጥሎ ነው! አሁን ይህ ሰውዬ የሚጾመው ሲፈሰክ ደህና አድርጎ በናፍቆት ለመብላት ካልሆነ ለሌላ ለምንድን ነው ሊባል ነው?

ሥራም ቢሆን ለመብል ነው፤ ከመኝታው ሲነሣ ጀምሮ እስኪተኛ ቢበላ ደስታውን አይችለውም፤ለገና፣ ለፋሲካ፣ ለእንቁጣጣሽና ለመስቀል ለገናና ለፋሲካ፣ ለእንቁጣጣሽና ለመስቀልም ከሌሊት ጀምሮ ከአንዱ ቤት አንዱ ቤት እየተዘዋወሩ በመብላት ቀኑ ያልፍ የለም እንዴ! በእውነት አበሻ መብላት የሚወደውን ያህል ማብላትም ይወዳል፤ ስሞት! ስቀበር! አፈር ስገባ! … ወዘተ. እየተባባለ የጠገበውን ሰው በቁንጣን እንዲሰቃይ ማድረግ የአበሻ ልዩ የፍቅር መግለጫ ነው! መጎራረስም አለ፤ ፍቅርና ጉርሻ ሲያስጨንቅ ነው እየተባለ ፍቅርና ሆድን ያያይዛል፤ አነጋገሩ አበሻ ለመብላት ያለውን እንጂ ፍቅርን አይገልጽም፤ ማሰጨነቅንና ፍቅርን ምን አገናኛቸው! አበሻ ሌላም ተረት አለው፤ የወለዱትን ካልሳሙለትና የሠሩትን ካልበሉለት ደስ አይለውም ይባላል፤ የልጅ ፍቅር ከምግብ ፍቅር ጋር ተስተካክሎ የቀረበ ይመስላል፤ ደሞም ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል፤ ይላል፤ ጉድ ነው! ሲሞትም ተከተሉኝ የሚል ይመስላል!! ለነገሩማ ፍቅርምኮ አበሻ ዘንድ ምግብ ነው፤ ሆዴ! አንጀቴ! ጎንደሬዎች ሲያሳምሩት ደግሞ ራቴዋ! ይሉታል።

ዛሬ ዛሬ አበሻ ከማብላት ይልቅ ማጠጣት ይወዳል፤ እስቲ ሰዎች ሰብሰብ ብለው በሚጠጡበት ቦታ ብቅ በሉ፤ ያቺን የፈረደባትን ጉበት ለማቃጠል በአቦ፣ በሥላሴ የማይል የለም፤ ቸገረኝ ብሎ ገንዘብ የሚጠይቅ አይምጣ እንጂ ለማብላትና ለማጠጣት፣ ለአንድ ጥሪኝ ፈሳሽ አበሻ ቸር ነው፤ በላኤ ሰብስ በማርያም ስም አንድ ጥሪኝ ውሀ ሰጥቶ አይደለም እንዴ የበላው ሰው ሁሉ የተሰረዘለት? አበሻ በሆድ አይጨክንም።

ለአበሻ ምግብ ክቡር ነው፤ ስለዚህም ምንም ነገር ሲበላ ተቀምጦ ነው፤ ፈረንጅ ቂሉ በየመንገዱ እንደመጋዣ ያመነዥካል፤ በየመንገዱ ማመንዠክ ምግቡን ማዋረድ ነው፤ ከዚያም በላይ ቆመው ሲበሉ ወደጉልበት ይወርዳል ይላል፤ ለአበሻ ጨጉዋራና ጉልበት በቀጥታ የተገናኙ ናቸው፤ ሳይንሱ የሚለው ሌላ ቢሆንም አበሻ አበሻ ምን ቸገረው?

ለመሆኑ ከሆድ ጋር ያልተያያዘ ነገር አበሻ ምን አለው? ነገርን በሆድህ ያዘው ምን ማለት ነው? ነገርን ማብላላት የማሰብ ምትክ መሆኑ ነው፤ ልጆች ሆነን አይጥ አበላሁት እንል ነበር፤ አሸነፍሁት ለማለት ነው፤ ዛሬም ቢሆን ቁማርተኞች በላሁ-ተበላሁ ይባላሉ፤ አይጥ ከማብላት ገንዘብ ወደማብላት ተለወጠ እንጂ ከሆድ አልወጣም፤

አበሻ በሆዱ የማይዘው ምን ነገር አለ? ፍቅርም፣ ጥላቻም በሆድ ነው፤ ቂምም በሆድ ነው፤ ምኞትም ፍላጎትም በሆድ ነው፤ ተስፋም በሆድ ነው፤ መጥኔ ይስጠው የአበሻ ሆድ! ሁሉን ከተናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል፤ አይ የአበሻ ሆድ! የነገር ስልቻ ከመሆኑ በላይ ነገር አልቆበት ‹‹ነገር እንዳይርበው(!)›› ጥንቃቄ ማድረግ አለበት! የአበሻ ሆድ እህል ቢያጣና ከእህል ባዶ ቢሆንም ከነገር ባዶ መሆን የለበትም፤ እህል ቢጠፋም ነገር አይጥፋ!

የአበሻና የሆድ ነገር በዚህ አያበቃም፤ አበሻ ሲያመው ቡዳ በልቶት ነው፤ ቆንጆውን ሁሉ ቡዳ ይበላዋል፤ ልብ በሉ ለአበሻ በዓይንም ይበላል ማለት ነው! አንዳንዴም ሲያመው መድኃኒቱ ምግብ ነው፤ ለሆድ ቁርጠት ብላበት፤ አበሻ ሲሞትም ለቅሶው ሁሉ ስለሆድ ነው፤ ‹‹የኔ ሆድ፣ ሆዴ እንዴት ይቻለው! ፋሲካን የት ልፈስክ?››

እስከናካቴው ‹‹ሆድ›› የሚባል ቃል ከአበሻ ቋንቋ ፈጽሞ ቢሰረዝ ቋንቋው ብቻ ሳይሆን አበሻም ጉድ ይፈላበታል፤ አእምሮ፣ ኅሊና የሚባሉትን ቃላት አበሻ አያውቃቸውም፤ ተግባራቸውንም ሁሉ ለሆድ ሰጥቶታል።

Saturday, November 30, 2013

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በውጭ ስርአቱ ጥሩ ነው ይበሉ እንጅ በግል ሳናግራቸው ለውጥ እንደሚፈልጉ ገልጸውልኛል ሲሉ ወ/ሮ አና ጎሜዝ ተናገሩ

ህዳር ፳(ሃያ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባል እና የኢትዮጵያን የ1997 ምርጫ የታዘቡት ወ/ሮ አና ጎሜዝ ይህን የተናገሩት አዲስ ስታንዳርድ ለተባለ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ነው።
በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለው የአውሮፓ፣ አፍሪካና ካረቢያን አገሮች የፓርላማ ጉባኤ ላይ የተገኙት ወ/ሮ አና የአምባገነን ምንጭ የሆነው መለስ ዜናዊ ቢሞትም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካዊ ለውጥ አለመምጣቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ተለውጣለች በማለት በአደባባይ የሚናገሩት ባለስልጣናት በግል ሳነጋግራቸው በኢትዮጵያ ፈጣን ለውጥ መደረግ አለበት ብለው ይላሉ ያሉት ወ/ሮ አና፣ አቶ ሀይለማርያም  ከሙስና ጋር በተያያዘ አንዳንድ መጠነኛ እርምጃዎችን ቢወስዱም፣ የትግራይ ተወላጅ ባለመሆናቸው ስልጣናቸውን ለማቆየት እየተቸገሩ መሆኑን ገልጸዋል። ቀደም ብለው እስክንድር ነጋንና ርእዮት አለሙን ለመጎብኘት በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ትእዛዝ ወደ ቃሊቲ የተጓዙት የአውሮፓ ህብረት ልኡካን፣ በእስር ቤቱ ሀላፊዎች መከልከላቸው በአገሪቱ ውስጥ ያለውን እውነታ የሚያሳይ ነው ያሉት ወ/ሮ አና በኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ የስልጣን ሽኩቻ እንዳለ እንደሚያውቁም ተናግረዋል።
የመለስ ዜናዊ መንግስት ስልጣኑን ለማቆየት ሲል ሙስሊምና ክርስቲያኑን ለማጋጨት ጥረት ሲያደርግ እንደነበርም የፓርላማ አባሉዋ ተናግረዋል። የኢትዮጵያን ወጣቶች አፍኖ መያዝ አይቻልም ያሉት ወ/ሮ አና የፖለቲካ ሜዳውን ለዲሞክራሲ መክፈት ኢትዮጵያን ከውድቀት እንደሚታደጋት ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ዜጎች ጋር በተያያዘ በሳውድ አረቢያ ከፍተኛ የሆነ አደጋ ማንዣበቡን ኢትዮጵያውያን ተናገሩ

ህዳር ፳(ሃያ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሳውድ አረቢያ የሚታየው ሁኔታ እጅግ አስፈሪ ነው ይላሉ ያነጋገርናቸው ዜጎች። ከ40 ሺ በላይ ኢትዮጵያን በእስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ። ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚፈልጉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቀናቸውን ይጠባባቃሉ። የኢትዮጵያ መንግስት በመቶ ሺ የሚቆጠረውን ስደተኛ ለማስተናገድ የመደበው የሰው ሀይል 40 ብቻ ነው። የሳውድ አረቢያ መንግስት ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢትዮጵያውያን ከአገሪቱ ምድር ተጠራርገው እንዲወጡ እየቀሰቀሰ ነው። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አደጋ ሊፈጠር ይችላል ብሏል  አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ ጋዜጠኛ።
በዛሬው እለት በተለያዩ የሳውዲ ከተሞች የተበተነው የኤስ ኤም ኤስ መልዕክት  ህጋዊ ለተባሉትም ሆነ ህገወጥ ለሚባሉት ኢትዮጵያውያን የማስጠንቀቂያ ደወል ነው ይላሉ እኝህ ጋዜጠኛ።

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ኢ/ር ይልቃል በጀርመን- በስዊዘርላንድ – በሆላንድ – በዋሽንግተን ዲሲ ውይይት ያደርጋሉ

(ኢ.ኤም.ኤፍ) የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ ጉብኝታቸውን ጀምረዋል። ትላንት ኖቨምበር 29 ጀርመን ፍራንክፈርት የገቡት ኢ/ር ይልቃል በመጪዎቹ ቀናት በአውሮፓ ከተሞች ተከታታይ የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ አስተባባሪ ኮሚቴው በተለይ ለኢ.ኤም.ኤፍ አስታውቋል።

ለጊዜው በደረሰን የስራ ሰሌዳ መሰረት :-

- ቅዳሜ ኖቬምበር 30 በጀርመን ኑረንበርግ ከኢትዮጵያኖች ጋር ውይይት ያደርጋሉ።
- ሰኞ ዲሴምበር 2 በፍራንክፈርት የሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ይገኛሉ።
- ዲሴምበር 5 ጄኔቭ ስዊዘርላንድ የሚደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ይሳተፋሉ።
- ቅዳሜ ዲሴምበር 7 በሆላንድ ህዝባዊ ውይይት ያደርጋሉ።

ከአውሮፓ ቆይታቸው በኋላ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ በመጓዝ በዲሴምበር 30 አርሊንግተን በተዘጋጀው ስብሰባ ከፕ/ር አል ማርያም ጋር ንግግር ያደርጋሉ።

Nov 30: Nuremberg : Public meeting and fundraising
Dec 02: Frankfurt: Appearance at a rally; Meet with invited guests for dinner
Dec 05: Geneva: appearance at a rally
Dec 07: Amsterdam: Public meeting

Washington DC Public Meeting with Semayawi Party Chairman Eng. Yilkal Getnet – Sunday Dec 15, 2013 – Sheraton Arlington Hotel.


የህዝባችን መከራ የወያኔ የፖለቲካ መጠቀሚያ አይሆንም!

በሳውዲ አረቢያ ውስጥ እጅግ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሁንምመከራና ስቃይ ላይ ናቸው። የደረጃ ጉዳይ ነው እንጂ ችግሩ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ የተንሰራፋ ነው። በመላው አለም ተበትኖ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ካለማቋረጥ ያደረገው ወገንና ሀገር አኩሪ ጩኸትና አቤቱታ ችግሩ በአለም ዙሪያ ትኩረት እንዲያገኝ ባያደረግ ኖሮ የወገኖቻችን መከራ ከዚህም በከፋ መልክ ይቀጥል እንደነበር ጥርጥር የለውም። አንድ ቀን እንኳን ለሚገዛው ህዝብ ሀላፊነትና ተጠያቂነት ተሰምቶት የማያውቀው የወያኔ ጉጅሌ መንግስት እግሩን እየጎተተ ቢሆንም ወደ ችግሩ አቅጣጫ እንዲመለከት የተገደደው በዚሁ የወገን ጩኸት መሆኑ ግልጽ ነው።

ወያኔ ስላልቻለ ነው እንጂ ይህንን ከአለም አጽናፍ እስከ አለም አጽናፍ ያስተጋባ የወገን ደራሽ ድምጻችንን አዲስ አበባ ላይ እንደ አደረገው በሃይል ለማፈን ወደኋላ አይልም ነበር።

ሀፍረት የለሾቹ የወያኔ መንግስት ባለስልጣኖች ይህን የተጋለጠ ሀገርና ህዝብ አዋራጅ ተግባራቸውን እና በውሸት የተበከለ ገመናቸውን ለመሸፈን ከዚያም አልፈው የዋሆችን በማታለል የፖለቲካ ትርፍ ለማትረፍ የተለመደ ቲያትር መስራቱን ተያይዘውታል። ቴዎድሮስ አድሃኖም ችግሩ ባለበት በሳውዲ መሬት ላይ ሳይሆን የሳውዲ አረቢያ መንግስት በራሱ ወጪ አሳፍሮ ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ባፈሰሳቸው ኢትዮጵያውያን መሃል እየተጎማለለ ያዛኝ ቅቤ አንጓች ቲያትሩን ሲሰራ ትንሽ እንኳን ሀፍረት አይታይበትም።

እነዚሁኑ ወደ ሀገር የተመለሱ አእምሯቸው በችግር የተመሰቃቀለ ዜጎች ወደ ካሜራ እየገፉ ስለ ሳውዲ ኤምባሲያቸውና ስለመንግስታቸው ‘ድንቅ” አገልግሎት እንዲናገሩ ያስጠኗቸውን ተመሳሳይ አረፍተ ነገር መስማት የሚያሳዝን ባይሆን ኖሮ ተወዳዳሪ የሌለው ኮሜዲ ይወጣው ነበር።

እውነቱ ዛሬ በሀገራችን የሰፈነው ስደትና አብሮት የሚመጣው መከራ ሁሉ ዋናው አምራች ፋብሪካ ወያኔ መሆኑ ነው። ወያኔ የገነባው ጥቂት ጀሌዎቹንና ሎሌዎችን ተጠቃሚ ያደረገና አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በተለይ ወጣቱ በሀገሩ ተስፋ እንዲቆርጥ ያደረገው ስርአት ነው። የስደታችንና የመከራችን ምንጭ ስደት የሚመጣው በሀገር ተስፋ መቁረጥ ነው። እንጀራ ፍለጋና ጭቆናና አፈና ሽሽት አምልጠን በየባዕድ ሀገሩ እንድንከራተት የሚያደርገን የወያኔ ስርአት ነው። በታሪካችን ውስጥ ተሰደን በባዕድ የተዋረድነው በወያኔ ምክንያት ነው።

በሀገር ውስጥ በአፈና ስር ሆናችሁ፣ በውጪው አለምም በየኢምባሲው የምታሰሙት ጩኸትና የምታፈሱት እምባ እብሪትና ትእቢት ያደነደነውን፣ ዝርፊያ ያደነዘዘውን የወያኔን ልብ እንደማያሸብረው ማወቅ አለብን።

የወያኔ ሹማምንቶች ይግረማችሁ ብለው ከአላንዳች ሀፍረት ያውም በሳውዲ አረቢያ ወጪ ተጓጉዘው ሀገር የገቡትን ግራ የተጋቡ ስደተኞች ለፖለቲካቸው ማሳመሪያ በቴሌቪዥን ስእልና ፎቶግራፍ መነሻ ሲያደርጉትና ለፖለቲካ ስራ መሳሪያ ሲያውሉት እያየን ነው። በነሱ ቤት ብልጥ ፖለቲከኞች መሆናቸው ይሆናል። በኛ ቁስል ላይ እንጨት እየሰደዱ መሆናቸውን ግን ፈጽሞ አይሰማቸውም።

ወያኔ በመካከለኛው ምስራቅ ተሰደው ለፍተው የሚኖሩት ወገኖቻችን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ያውቃል። ቢያንስ በየኢምባሲው ያስቀመጣቸው ነጋዴዎች ይነግሩታል። ችግሩን እንዳላየና እንዳልሰማ የሚያየው ከዜጎች ይልቅ እነሱ አፈር ግጠው ለፍተው ለሚያመጧት የውጪ ምንዛሬ የበለጠ ፍቅር ስላለው ነው። በዚህ ተግባሩ ወያኔ ወገኑን የሸጠ ባሪያ ፈንጋይ ነጋዴ እንጂ የመንግስት መሪ መሆኑ ያጠራጥራል።

ግንቦት 7 የፍትህና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ዘወትር እንደሚለው ሁሉ ይህ የዜግነትና የሀገር ውርደት፣ ይህ ሁሉ የወገን መከራ የሚቆመው የዚህ ሁሉ መሰረት የሆነው ወያኔና ስርአቱ ከመሰረቱ ሲነቀልና ሲወገድ መሆኑን ላፍታም አይዘነጋውም።

እንባችን የሚደርቀው ደማችን በየቦታው መፍሰሱ የሚቆመው መብታችን እንደዜጋ ተከብሮ ቀና ብለን የምንሄድበት ሀገር በትግላችን የተቀዳጀን ጊዜ ብቻ ነው።

ግንቦት 7ን ተቀላቀሉ በያላችሁበት ግንቦት 7 ሁኑ!! እኛ ከዚህ ውርደት ሞቶ የሚገኘው ነጻነት ይሻላል ብለን የተነሳን ልጆቻችሁ ነን። እርሰዎስ?

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

Thursday, November 28, 2013

የአና ጐሜዝ ውይይቶች ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር

አና ጐሜዝ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ገንቢና ግልጽ ውይይቶችን አደረግኩ አሉ


ከዘጠኝ ዓመት በፊት በተካሄደው የግንቦት 1997ቱ ምርጫ የአውሮፓ ኅብረትን በመወከል የምርጫ ታዛቢ የነበሩት ፖርቱጋላዊቷ አና ጐሜዝ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸውን ገለጹ፡፡

ዛሬ በሚጠናቀቀው የአፍሪካ፣ የካሪቢያን፣ የፓስፊክና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ የፓርላማ 26ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ለመካፈል አዲስ አበባ የመጡት አና ጐሜዝ፣ በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ገንቢና ግልጽ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የጋራ ስብሰባው ላይ ለመካፈል ወደ አዲስ አበባ የመጡት የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አባልና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ትችት በመሰንዘር የሚታወቁት አና ጐሜዝ፣ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ምንም ዓይነት የቪዛ ችግር እንዳልገጠማቸው ገልጸው ይህም አዲስ ዓይነት የፖለቲካ አተያይ እየተፈጠረ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ በኢትዮጵያ የተለየ የፖለቲካ አተያይ አለ ያሉት አና ጐሜዝ፣ አጠቃላይ የፖለቲካው ምህዳር ግን ከ1997ቱ ምርጫ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የባሰ ነው የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ «ከ1997 ምርጫ ቀደም ብሎ ተስፋ ይታይበት የነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ምህዳር በምርጫው ምክንያት በተፈጠረው ቀውስ ከምርጫው በፊት ወደነበረበት አስከፊ ሁኔታ ተመልሷል፤» በማለት መንግሥትን ተችተዋል፡፡

ለዚህም እንደ መከራከሪያ የሚያነሱት ከምርጫው በኋላ የወጡትን ሕጐች በምሳሌነት በማቅረብ ነው፡፡ «ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ሁሉም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት መታሰራቸው፣ የሲቪክ ማኅበራት መፈናፈኛ ማጣታቸው፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና የመሳሰሉት ነገሮች በአሉታዊነት የሚነሱ ናቸው፤» በማለት ተናግረዋል፡፡

«ከሁሉም በተለየ ሁኔታ ግን መንግሥት የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን ያለአግባብ በመጠቀም ተቃዋሚዎችን ፀጥ ለማድረግ እያዋለው ነው፤» በማለት አና ጐሜዝ ከፍተኛ ትችት የሰነዘሩ ሲሆን፣ በዚህም ጉዳይ ላይ ከአፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር እንደተወያዩ አብራርተዋል፡፡

ምንም እንኳን የውይይቱን ዐበይት ነጥቦች በዝርዝር ከመግለጽ ቢቆጠቡም ውይይቱ ግን ገንቢ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ውይይቱ በዋነኛነት የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት፣ የፖለቲካ እስረኞችን ማስፈታት፣ ለሲቪክ ማኅበረሰቡ የምርጫ ሜዳውን ማስፋት፣ እንዲሁም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማጠናከር የሚሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ በዝርዝር የተወያዩ መሆኑን ከመግለጽ ውጪ፣ አና ጐሜዝ ከመንግሥት ወገን ያገኙትን ምላሽ ምን እንደሆነ ከማብራራት ተቆጥበዋል፡፡

የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አስተዳደር የተሻለ ሊሆን እንደሚችል የገለጹት አና ጐሜዝ፣ በተለይ ሙስናን በተመለከተ የተጀመረው እንቅስቃሴ ሊበረታታ እንደሚገባው አስታውቀዋል፡፡

የፖለቲካ እስረኞችን ለመጠየቅ በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን በጋራ ስብሰባው ጥያቄ መቅረቡን ያመለከቱት አና ጐሜዝ፣ የመንግሥትን ምላሽ እየተጠባበቁ እንደሆነም አክለው አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን በተመለከተ ምንም ዓይነት ግለሰባዊ ችግር እንደሌለባቸው የገለጹት አና ጐሜዝ፣ ሥራዬን ግን በአግባቡ የመወጣት ግዴታ አለብኝ ብለዋል፡፡

የጋራ ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሲሆኑ፣ በአባል አገሮች ሕገ መንግሥታት ላይ የሥልጣን ክፍፍል እንዲሰፍንና የፖለቲካ ምህዳሩ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሰፋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የሲቪል ማኅበረሰቡን ለመደገፍ፣ ፍትሕና የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል፣ ሙስናን ለመዋጋት እንዲሁም የሥነ ዜጋ ትምህርትን ለማስፋፋትና ለማጐልበት ተቋማዊ ተግዳሮቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በእነዚህ ዙሪያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በጥምረት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ግንኙነቱ ግን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡

የአፍሪካ፣ የካሪቢያን፣ የፓስፊክና የአውሮፓ ኅብረት የጋራ የፓርላማ ስብሰባ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

ሁከት ፈጠሩ” የተባሉት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ጉዳይ ፍ/ቤት ቀረበ

(አራያ ጌታቸው) ዛሬ ህዳር 18 ቀን 2006 ዓ.ም ከላይ ባለው የክስ መጥሪያ የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ የሽዋስ አሰፋ እና የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት አባል አቶ ስሜነህ ጸሀይ አዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርበው፤ አቃቤ ህግ ወንጀሉን ከዘረዘሩ በኋላ ፍርድ ቤቱም ጥፋተኝነታቸውን ያምኑ ወይም ይቃወሙ እንደሆነ ጠይቆ ተከሳሾቹም ምንም አይነት ጥፋት እንዳለጠፉ ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የምስክሮችን ቃል ለመስማት ለህዳር 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ አሰናብቷቸዋል፡፡
የክሱን ዝርዝር እንዲያነቡት ከዚህ ዜና ጋር አቅርበነዋል።


የክሱ አቤቱታ

Wednesday, November 27, 2013

የአንዷለም አራጌ “ያልተሔደበትን መንገድ” መጽሃፍን የቃኘ መድረክ

(በዘሪሁን ሙሉጌታ) ባለፈው እሁድ በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት ውስጥ አንድ የመፅሐፍ ምረቃ ፕሮግራም ተካሂዶ ነበር። መፅሐፉ “ያልተሄደበት መንገድ” በሚል ርዕስ በቅርቡ ለሕትመት የበቃ መፅሐፍ ነው። መፅሐፉን ያሳተመው በአሁኑ ወቅት በሽብርተኝነት ክስ ጥፋተኛ ተብሎ የዕድሜ ልክ ፍርደኛ በሆነው የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል የነበረው አንዱአለም አራጌ ነው።

መፅሐፉ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሁሉ አቀፍ ህፀፅ የሚዳስስ ታሪክ-ቀመስ የፖለቲካ መፅሐፍ ነው። ከመድረኩ ሲገለፅ እንደሰማነው 10ሺህ ቅጂ ታትሟል። በዕለቱ መፅሐፉን ቀደም ብለው አንብበው አስተያየት እንዲሰጡ የተፈቀደላቸው ሁለት ሰዎች ነበሩ።
አንደኛው የቀድሞው የአረና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ አስራት አብርሃም ሲሆኑ፤ ሁለተኛው ደግሞ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ነበር። ሁለቱም አስተያየት ሰጪዎች የመፅሐፉን አንኳር ጉዳይ ነቅሰው በማውጣት የየራሳቸውን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዕለቱ የሁለቱም አስተያየት ሰጪዎችን ትኩረት የሳቡት በዋናነት ሦስት ወይም አራት ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው። የመጀመሪያው ጠቅለል ባለ ዕይታ የሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ሲሆን፤ ይህንኑ ደካማ የፖለቲካ ባህልን ተከትለው የሚታዩ ጎጂ ልማዳዊ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን ነው። በተለይም የጉልበት ፖለቲካ ባህል፣ የትግራይ ሕዝብና ህወሓትን አለመለያየት፣ የሰላማዊ ትግል የአተገባበር ችግርና የብሔራዊ መግባባት አስፈላጊነት ዙሪያ ላይ ያጠነጠኑ ነበሩ። በአቶ አስራት አብርሃም እምነት መፅሐፉ የተፃፈው ከማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ ህሊና በመሆኑ በሚዛናዊ አስተሳሰቦች የታጀበ መሆኑን አስምረውበታል። በአብዛኛዎቹ የመፅሐፉ ገዢ ሃሳቦች እንደሚስማሙበት ገልፀዋል።

የሀገሪቱ ምስቅልቅል የፖለቲካ ጉዞ መነሻ የሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል አለመዳበር መሆኑን፤ በተለይም ከሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ባህልን ለማስረፅ የኦሮሞ ብሔር ባህላዊ አስተዳደር ዘይቤ የሆነውን የገዳ ስርዓት በሀገሪቱ ውስጥ ቢኖርም እንደ ሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል አለመወሰዱ፤ በአንፃሩ የሰሜኑ የጉልበት ፖለቲካ፣ በሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ሚዛን ደፍቶ መታየቱ ለሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል አለመዳበር በማሳያነት ቀርቧል።

የኦሮሞ የገዳ ስርዓት ከስልጣን ሽግግር አንፃር ዴሞክራሲያዊ መልኮች ቢኖሩትም የሴቶችን ተሳትፎ ላይ ካለው ውስንነት አንፃር ጠቃሚ የሥልጣን ሽግግር ባህል ተደርጎ በአንዱአለም መፅሐፍ መገለፁ አግባብ መሆኑን አቶ አስራት አስምረውበታል።




የሰሜን የጉልበት ፖለቲካ እንደ ሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ተደርጎ የተወሰደበትን አግባብ ሲያሳዩም ከመፅሐፉ አንድ ምሳሌ ጠቅሰዋል። ነገሩ የሆነው በ1983 ኢህአዴግ የደርግን ሥርዓት ጥሎ ስልጣን ከያዘ በኋላ ወሎ ውስጥ የኢህአዴግ ካድሬዎች ሕዝቡን ይሰበስቡና “አሁን ነፃ ወጥታችኋል። ደርግም የለም። እስቲ የመሰላችሁን ተናገሩ። አሁን ዴሞክራሲ አለ” ይላሉ። ይሄንን የሰሙ አያ ሙሄ የሚባሉ ሰው እጅ አውጥተው “ለምሳሌ እናንተ [ካድሬዎቹን] ልክ ልካችሁን ብንነግራችሁ ምንም አትሉኝም?” ይሏቸዋል። “ይናገሩ ችግር የለውም” ተባሉ። በዚህ ወቅት አያ ሙሄ “እናንተ ሀገር አስገንጣይ…. ናችሁ” ብለው ቁጭ አሉ። በአያ ሙሄ ንግግር የተበረታቱት አቶ ይመር የሚባሉ ሌላ ሰው፤ “አያ ሙሄ እንዳለው” ብለው ወደ እሳቸው ዞረው ሲያዩ፤ አያ ሙሄ በቦታቸው አልነበሩም። አቶ ይመርም ለመናገር ከተነሱ አይቀር “ዴሞክራሲ አያ ሙሄ እንዳለው ዴሞክራሲ ነው” ብለው ተቀመጡ። ይህ ምሳሌ የሰሜን የጉልበት ፖለቲካና የኢህአዴግ ዴሞክራሲ የይስሙላ ዴሞክራሲ መሆኑ አመላካች እንደሆነም ገልፀዋል። ኢህአዴግ በንድፈ-ሃሳብ ከደርግ ቢለይም በተግባር ግን ብዙ የሚያመሳስለው መገለጫዎች እንዳሉት ነው የገለፁት።
ለጉልበት ፖለቲካ ባህል መዳበር ሀገሪቱ የክርስትና ሃይማኖትን ተቀብላ ተግባራዊ ያደረገችበት ሁኔታ እንደሆነም በመፅሐፉ ውስጥ ትሁት በሆነ አቀራረብ መጠቀሱን ያደነቁት አቶ አስራት፤ በሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ውስጥ “ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ” የሚለው ብሂል የገዢዎችን የተጠያቂነት የፖለቲካ ስርዓት ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር እንደሆነም ገልፀዋል።

በገጠሪቱ ኢትዮጵያም፤ “ኢህአዴግን ያመጣው እግዚአብሔር ነው” የሚል ኀሳብ መኖሩን ያስታወሱት አቶ አስራት፤ ይህን አመለካከት ተከትሎም “እግዜር ያመጣውን እግዜር ያውርደው” የሚል አረዳድ መኖሩን አስረድተዋል። እንደዚህ ብሎ በሚያስብ ማህበረሰብ ውስጥ ለዴሞክራሲ የሚደረግ ትግልም በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል። እግዜር መቼ እንደሚያወርደው አይታወቅም። “ምክንያቱም አንዳንድ የቤተ-ክህነት ሰዎች እንደሚሉት ለእግዜር አንድ ሺህ ዓመትም አንድ ቀን ሊሆን ስለሚችል እግዜር እስኪያወርደው መጠበቅ አይገባም” ብለዋል። ፖለቲካ የምድራዊ ጉዳይ በመሆኑ ሰማያዊ ገፅታን ማላበሱ ተገቢ አለመሆኑንም አስምረውበታል።

የሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል የጉልበት በመሆኑም በመፅሐፉ ውስጥ ሦስት አይነት የፖለቲካ አማራጮች ብቻ መኖራቸውን አቶ አስራት ገልፀዋል። እነሱም አርፎ መቀመጥ፣ መሰደድ ወይም መታሰር መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። በዚህ ወቅት መታሰር ደግሞ ጀግንነት መሆኑን በማውሳት “የጀግና ቤቱ እስር ቤት ነው” የሚለውን የአቶ አንዱአለምን ኀሳብ ይበልጥ አጠናክረውታል።

ህወሓትና የትግራይ ሕዝብ የተለያዩ መሆናቸው በመፅሐፉም መጠቀሱን እንዲሁም እሳቸውም እንደሚያምኑበት ገልፀዋል። “የትግራይ ሕዝብና ህወሓት አንድ ቢሆኑ፤ እኔም ዛሬ በዚህ መድረክ ላይ ባልተገኘሁ” ያሉት አቶ አስራት “የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል” እንዲሉ ሕወሓትንና የትግራይን ሕዝብ ደባልቆ መመልከት ተገቢ አይደለም ብለዋል። አንድ ሥርዓትና ሕዝብ አንድ የሚሆኑበት አጋጣሚ እንደሌለ በመግለፅ በዚህ በኩል ያለው መደናገር ሊስተካከል እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሌላው በመፅሐፉ የተገለፀው የሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባህሪና መገለጫ ነው። በሀገሪቱ ሦስት አይነት አደናጋሪ የፓርቲ አይነቶች መኖራቸውም እነሱም በኢህአዴግ የሚመሰረቱና ለኢህአዴግ ዓላማ የቆሙ፣ በንፁህ ህሊና ተቋቁመው እየበረቱ ሲሄዱ ኢህአዴግ ሰርጎ ገብ አስገብቶ ፓርቲዎቹ እንዲከፋፈሉ የሚደረጉና እንዲሁም ሕዝብን መቀስቀስና ማደራጀት ያልቻሉ የሌሎችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተፅዕኖ መቋቋም ያልቻሉ፣ እንዲሁም ኢህአዴግ ከሚሰነዝርባቸው ዱላ የተነሳ ለኢህአዴግ የሚያገለግሉ ፓርቲዎች መኖራቸውን መጠቀሱ ተገቢነት ያለው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዲያስፖራ ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ በመፅሐፉ ላይ በእውቀትና ድፍረት ላይ የተመሠረተ ኀሳብና ትችት መቅረቡን ያወሱት አቶ አስራት በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በገንዘብ የሚረዱ በመሆኑ የእነሱን ደካማ ጎን መግለፅ አስቸጋሪ ነው፤ እነሱም ቶሎ የሚገነፍሉ ናቸው ብለዋል። አንዱአለም ግን በህሊናው በመመራት እነሱን መተቸቱ ተገቢ እንደሆነም ገልፀዋል። በዳያስፖራ ዴሞክራሲ ያለገደብ ቢኖርም አጠቃቀሙን ካላወቅንበት በኋላ ለእኛም አስቸጋሪ እንደሆነም አስገንዝበዋል። በዲያስፖራ በዘር፣ በሃይማኖትና በጎጥ ያለው መከፋፈል አስፈሪ ከመሆን አልፎ ተስፋም የሚጣልበት ከመሆን እየራቀ ነው ብለዋል።

ብሔራዊ መግባባት አስፈላጊነት በተመለከተም በመፅሐፉ መገለፁ ተገቢ እንደሆነ ያስረዱት አቶ አስራት የሀገሪቱ ፖለቲካ የጉልበት ፖለቲካ ባህል መሆኑን ተከትሎ ደም መፋሰስ በመፈፀሙ ብሔራዊ የመግባባት ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ መሆኑን አውስተዋል። በዚህ ረገድ አንዱአለም ይሄንን የእርቅ ጥያቄ ማንሳቱ በአዎንታዊ ጎኑ የሚታይ እንደሆነና እንደዚህ አይነቱ አመለካከት በእነማንዴላና በእነ ማሕተመ ጋንዲ ይቀነቀን የነበረ አጀንዳ እንደነበረም አስረድተዋል።

በመቀጠል በመፅሐፉ ላይ አስተያየት የሰጠው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ነው። የተመስገን አስተያየቶች አቶ አስራት ከሰጡት አስተያየት ጋር ተቀራራቢነት ያላቸው ነበሩ። መፅሐፉ የተፃፈበት ሁኔታ አስቸጋሪና ውስብስብ በመሆኑ ደካማ ጎኑን ለማንሳት አስቸጋሪ እንደሆነም አመልክቷል። መፅሐፉ በብርድ ልብስ ተከልሎ የተፃፈ ከመሆኑ አንፃር የመፅሐፉን ደካማ ጎን ከማጉላት ይልቅ መፅሐፉ ተፅፎ ለንባብ መብቃቱን በአዎንታዊ ጎኑ መመልከቱ ተገቢ እንደሆነም አስምሮበታል።

መፅሐፉ ምስጢራዊ በሆነ መልኩ በመፃፉና በማረሚያ ቤቱም “መለስ ከልጅነት እስከ እውቀት” ከሚል መፅሐፍ በተለየ ሌሎች ማጣቀሻ መፅሐፎችን ማግኘት ስለማይቻል በማጣቀሻ መፅሐፎች ባይዳብር ላይገርም እንደሚችል ገልጿል።

በመፅሐፉ የሀገሪቱን የፖለቲካ ውጣ ውረድ የተገለፀ ቢሆንም ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ግን ብዙዎች ተስፋ አድርገው እንደነበር፤ ከእነዚህም መካከል አንዱአለምም አንዱ እንደነበር የጠቀሰው ጋዜጠኛ ተመስገን ኢህአዴግ ጫካ በነበረበት ጊዜ የሚያቀርበው ፕሮፓጋንዳ ደርግን አባሮ አራት ኪሎ ቤተ-መንግስት ለመግባት ሳይሆን፤ እየሱስ ክርስቶስን ማርኮ ገነትን ለመቆጣጠር ይመስል ስለነበር በወቅቱ በኢህአዴግ ላይ ተስፋ ማድረጉ ላይገርም ይችላል ብሏል። ነገር ግን ኢህአዴግ ከመጣ በኋላ ከገሃነብ ያልተሻለ ሀገር ነው ያለን ሲል ገልጿል።

በመፅሐፉ ከቤተ-እምነቶች ጋር ተያይዞ የተነሳው ኀሳብ ትኩረት የሚስብ መሆኑን የጠቀሰው ተመስገን የቤተ-እምነቶች ልዕልና ማጣትን ተከትሎ የአፋሸ አጎንባሽ ልማድ በመስፋፋቱ ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለቄሳር መገዛት መጠቀሱ ተገቢ መሆኑን አስምሮበታል። ይህ ልማድ አሁን ላለው የሴራ ፖለቲካ መስፋፋት አስተዋፅኦ እንዳለውም አመልክቷል።

ህወሓትና የትግራይ ሕዝብን በአንድ ላይ ጨፍልቆ የመግለፅ አዝማሚያ ተገቢ አለመሆኑን የጠቀሰው ተመስገን፤ ኢህአዴግ አድዋ ላይ ማር አላዘነበም። አድዋ ላይ ህወሓትን የደገፈ ይጠቀማል። ጎንደር ላይ ብአዴንን የደገፈ ይጠቀማል። ወለጋም ላይ አባዱላንና ኦህዴድን የተወዳጀ ይጠቀማል እንጂ የአንድ ብሔር የበላይነት አይደለም ብሏል። ነገር ግን በዚህ አመለካከት “የሚጀነጅኑ” መኖራቸውን የጠቀሰው ተመስገን በተለይ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ህወሓትንና የትግራይን ሕዝብ የመቀላቀል ሁኔታ መኖሩንም አውስቷል።

“ነፍጠኛ አማራን አይወክልም ብለን፤ ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ይወክላል የሚል ፖለቲካ መኖር የለበትም” ሲል የገለፀው ተመስገን፤ ፓርቲዎችም ይህንኑ ግልፅ በማድረግ ጉልበተኛውን ስርዓት ከሕዝቡ መለየት አለባቸው ብሏል። ፓርቲዎቹ በ1967 ዓ.ም ህወሓት እንጂ የትግራይ ሕዝብ አልተመሰረተም ብለው አፅንኦት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብሏል።

በትግራይ ሕዝብ ስም የተቋቋሙ ድርጅቶችም የስርዓቱን ተዋንያኖች ከመጥቀም ባለፈ የትግራይን ሕዝብ ተጠቃሚ አለማድረጋቸውንም ጋዜጠኛ ተመስገን ገልጿል።

የአደናጋሪ ፓርቲዎች ውልደትና ሚና ከእነመኢሶን ጊዜ ጀምሮ ያለ ችግር መሆኑን የጠቀሰው ጋዜጠኛ ተመስገን በታጠረ መንገድ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችን በተመለከተም በመፅሐፉ የተጠቀሱ ጉዳዮች መካከል ውህደትን የመፍራትና ተያያዥ ችግሮችን መገለፁን አስረድቷል።

አንዱአለም የራሱን ፓርቲ አንድነት ጭምር መተቸቱ ተገቢ እንደነበረም አመልክቷል። በተቃዋሚ ፓርቲዎች ያደፈጠ ሽኩቻ መኖሩም ለፓርቲዎች መዳከም ጉልህ ሚና መጫወቱንም አስረድቷል።

በውጪ ሀገር ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አንዱአለም በመፅሐፉ በሁለት መክፈሉን ያወሳው ተመስገን፤ የመጀመሪያዎቹ ሞክረው፣ ሞክረው ያልተሳካላቸው ኦነግን ጨምሮ መኢሶን፣ ኢህአፓ ሲሆኑ፤ ሁለተኛዎቹ ስሪታቸው እዛው ሰሜን አሜሪካና አውሮፓ የሆኑ ግንቦት ሰባትን የመሰሉ ናቸው ብሏል። በተለይ “ግንቦት ሰባትን” በተመለከተ አንዱአለም በመፅሐፉ ውስጥ መረር ያለ ነገር መግለፁ ዋጋ ያስከፈለው ጉዳይ በመሆኑ ነው ያለው ተመስገን፤ አንዱአለም “ኢህአዴግ ግንቦት ሰባት ያልዘራውን እንዲያጭድ አድርጎታል” የማለቱ ውጤት ትክክል መሆኑንና በርካቶችንም ለእስር እንዲዳረጉና ለሰላማዊ ትግሉ መዳከምም አስተዋፅኦ ማድረጉን አስረድቷል።

አንዱአለም የሰላማዊ ትግል አቀንቃኝ መሆኑ የሚደገፍ እንደሆነ የጠቀሰው ጋዜጠኛ ተመስገን የሥርዓት ለውጥ በጠመንጃ አፈሙዝ ከመጣ ለውጥ አይመጣም ብሏል። በሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታም በአፈሙዝ የመጣው ለውጥም የሥርዓቱን ቁንጮዎች ቱጃር ከማድረግ ባለፈ አስተማማኝ የዴሞክራሲ ስርዓት አለመገንባቱንም አስረድቷል። ይሁን እንጂ የሰላማዊ ትግሉን በአግባቡ በመጠቀም ላይ ችግር መኖሩንም አስረድቷል።

“ዛሬም አስፈቅደን ነው የተቃውሞ ሰልፍ የምናደርገው። ጋዳፊም ሆኑ ሙባረክ በፍቃድ ሰልፍ አይደለም ከስልጣን የተወገዱት። እኛን የሚያስቆጣ በቂ ምክንያት ስላለን የሥርዓት ለውጥ ለማድረግ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ሰልፍ መውጣት አለብን” ሲል ተመስገን ተናግሯል።

ጋዜጠኛ ተመስገን በዲያስፖራው በኩልም ኢትዮጵያውያን ከተሰደዱ በኋላ በሃይማኖትና በብሔር የሚከፋፈሉበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን አንዱአለም በመፅሐፉም መገለፁ እሱም የሚጋራው ስጋት እንደሆነ ገልጿል።

ክፍፍሉ “የጎንደሬ ገብሬል፣ የትግራይ ማርያም” እስከመባል መድረሱ ዞሮ ዞሮ እየጠቀመ ያለው 22 ዓመት ስልጣን ላይ ለቆየውና ለሌላ 22 ዓመት እየተዘጋጀ ላለው ሥርዓት ነው ብሏል። ስለሆነም በመፅሐፉ ላይ ለዲያስፖራው የተላለፈው መልዕክት ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብሏል።

በመጨረሻም በመፅሐፉ ውስጥ ያልተሄደበት መንገድ ሲባል ሰላማዊ ትግል መሆኑን ነገር ግን ሰላማዊ ትግሉ በሚገባ ያልተተገበረ መሆኑን ለመግለፅ ነው ያለው ተመስገን፤ ለነገዋ ኢትዮጵያ የተቀመጠው የብሔራዊ መግባባት የመውጫ መንገድ (exit strategy) ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተናግሯል።

ከኢትዮጵያ እሳት ወደ ሳውዲ አረቢያ እረመጥ፤ከድጡ ወደ ማጡ (ከፕ/ር አለማየሁ ገ/ማርያም)

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም ከነጻነት ለሀገሬ

ባለፉት አስርት ዓመታት በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች በአገራቸው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አህጉር በተለየ መልኩ ተንሰራፍቶ እየተፈጸመ ካለው ጭካኔና ርህራሄ የጎደለው አምባገነናዊ ስርዓት ለማምለጥ ሲሉ እግራቸው ወዳመራቸው አገር በመሰደድ ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ “ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር” እንደዘገበው ከሆነ እ.ኤ.አ በ2012 በግምት 200,000 ኢትዮጵያውያት ሴቶች በውጭ አገር በአብዛኛውም በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የውጭ የስራ ዕድል ለመፈለግ ተገደዋል፡፡ ከእነዚህ ኢትዮጵያውያት ሰራተኞች አብዛኞቹ በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ከሚገኘው አምባገነናዊ የእሳት ነበልባል አመለጥኩ የሚል እምነት ነበራቸው፣ ሆኖም ግን ወደ ሳውዲ አረቢያው የእሳት እረመጥ ተወርውረው እራሳቸውን አገኙት፡፡

የግንቦት7 እና አክራሪ የእስልምና ሀይሎች በኢህአዴግ አባላት ስም ፓርላማውን በመቆጣጠር ኢህአዴግን ሊጎዱት ይችላል ሲሉ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ተናገሩ

ህዳር ፲፯(አስራ ሰባት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም ይህን የተናገሩት ” በክርስትና እና በእስልምና ሃይማኖት ሽፋን የሚካሄደው የፖለቲካ እንቅስቃሴ የመንግስት ቀጣዩ የምርጫ ፈተና” በሚል ርእስ ለኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ባቀረቡት ጽሁፍ ነው።
ኢሳት የሚኒስትሩን  ሙሉ ንግግር የያዘ ሰነድ የደረሰው ሲሆን፣ በሰነዱ ግርጌ ላይ ” ለመደበኛ አባላት የማይነገር፣ ለከፍተኛ አመራሮች ብቻ” የሚል ተጽፎበት ይታያል።  በዚህ ርእስ ስር ደግሞ ” ቀጣዩ የምክር ቤት አባላት ምርጫ የግንቦት ሰባት እና አክራሪ እስልምና ሀይሎችን የሚያስቀጥሉ አባላት ወንበሩ በኢህአዴግ አባላት ስም ሊነጠቅ ይችላል። ” ብሎአል። ሚኒስትሩ ለዚህ አስተሳሰባቸው የምርጫ 97ትን ሁኔታ እንደማጠቃሻ ተጠቅመዋል። ” የ97 የቅንጅት አሸናፊት አካሄድ ስልት ማለትም የተቃዋሚ አባላት ሁነው በህቡእ ተደራጅተው በኢህአዴግ የአባላትን ካርድ ሙሉ በሙሉ ፓርቲውን ሊጎዱት ይችላሉ” ሲሉ ሚኒስትሩ ጽፈዋል።

Tuesday, November 26, 2013

ተዋርደን አንቀርም!! ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)

November 26, 2013
ሳውዲ አረቢያ በዜጎቻችን ላይ እያደረሰች ያለውን ግፍና በደል በሰላማዊ ሰልፍ ለመቃወም ፓርቲያችን በወሰነው መሰረት ለሚመለከተው ክፍል አሳውቀን ነበር፡፡መቸም ህዝባችን በጭቆና ውስጥ ስለኖረ በመብቱና በግዴታው መሀል ያለውን ድንበር በውል ካለመረዳቱ የተነሳ ሰልፉ እንዲደረግ ስለመፈቀዱ በተደጋጋሚ ስንጠየቅ ነበር፡፡ህጉ የሚለው ግን ማስፈቀድ ሳይሆን ማሳወቅ ብቻ ነው፡፡በተቃራኒው መንግስት በተለያዩ ጉዳዮች ሳቢያ በእለቱ ለሰላማዊ ሰልፉ የደህንነት ከለላ መስጠት የማይችልበት ሁኔታ ከገጠመው ሰልፉን ለጠራው አካል ችግሩን ገልጾ ቀኑ እንዲተላለፍለት ይጠይቃል፡፡በመሆኑም ይህን መሰል ጥያቄ ከሚመለከተው መስሪያ ቤት ለፓርቲያችን ባለመቅረቡ በሙሉ ልብ ቅድመ-ዝግጅት ማድረጉን ተያያዝ

ሁሌም ቢሆን መንግስት ሰበብ ፈልጎ ሊወነጅለንና ከመስመር ሊያስወጣን እንደሚፈልግ በሚገባ እናውቃለንና በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ጥንቃቄ እናደርጋለን፡፡ለሚመለከተው መስሪያ ቤት ባሳወቅን በአስራ ሁለት ሰአታት ውስጥ ምላሽ ስላልመጣ ሙሉ በሙሉ ህጋዊነታችንን አረጋግጠናል ማለት ነው፣እነሱ ደግሞ ጠብ-መንጃ በእጃቸው አለና የፈለጉትን ሁሉ ማድረግ ይችላል፡፡

አቶ ሽመልስ ከማል ለሚዲያወች የሰጡትን ፍጹም ከእውነት የራቀ ውንጀላና ሰበብ አዳምጨዋለው፡፡ “ሰላማዊ ሰልፉን ያገድንበት ምክንያት ጸረ-አረብ መፈክሮች ስለነበሩ ነው“ብለዋል፡፡መጀመሪያ ደረጃ ሰልፉ ገና ከግቢው ፈቅ ሳይል ነው ያፈኑት፣ሆኖም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም አንድ በአንድ እየሆንን ወደ ሰላማዊ ሰልፉ መዳረሻ ለመሄድ ስንሞክር የተወሰኑ አመራሮችን አራት ኪሎ አካባቢ ያዙን፣እነሱ ቀድሞውኑ ሰልፉ እንዳይካሄድ ስለወሰኑ ነው እንጅ ትንሽ እንኳ ተንቀሳቅሶ የሰልፉን ባህሪ ለመገምገም ምንም እድል አልሰጡንም፡፡

ለምሳሌ ሰልፉን እንደምናደርግ ይፋ ባደረግን ማግስት ከራዲዮ ፋና ተደውሎ አንዳንድ ጥያቄዎች ተጠይቄ ነበር፡፡በቃለ-መጠይቁ ሰላማው ሰልፉ በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም እንደምናደርግ ተናግረናል፡፡ጋዜጠኛው ለሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች መልዕክት ካለ ብሎ በጠየቀኝ ወቅት የሳውዲ አረቢያ ሰንደቅ አላማ ላይ ያለው ምልክትና ጽሁፍ ሀይማኖትን የሚመለከት በመሆኑ ዜጎች በስሜታዊነት ባንዲራ እንዳያቃጥሉ፣እነሱ ቢያዋርዱንም እኛ ግን ክብር ያለን ዜጎች ስለሆንን ተቃውሟችንን ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ማካሄድ እንዳለብን ተናግሬ ነበር፡፡ከሰላማዊ ሰልፉ በፊት በዚህና በተለያየ መንገድ በማያሻማ ሁኔታ መልዕክት ባስተላልፍም እነሱ ግን ይህን በመቁረጥ አላስተላለፉትም፡፡እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ሲደመሩ የአቶ ሽመልስ ከማል ንግግር ነጭ ውሸት መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

ሁለተኛ የአንድ ሀገር መንግስት ዜጎቹ እየተደፈሩ፣በማጎሪያ ካምፕ በረሀብና በውሃ ጥም፣ሌላው ቢቀር መጸዳጃ ቤት እንኳ ተከልክለው ፍጹም ከሰውነት ክብራቸው ወርደው እየተበደሉ፣እየተገደሉ ባለበት ወቅት ገና ለገና ተቃዋሚ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ ላይ በሚንጸባረቅ ጥላቻና ተቃውሞ የዲፕሎማሲ ግንኙነቴ ይበላሽብኛል ብለን መናገር እንችላለን?ሌላው ይቅር አንድ ክፉና ደጉን የለየ ሰው የሚያስበው ጤነኛ ሃሳብ ነው ማለትስ ይቻላል?

ከእገዳው ባሻገር የሚደንቀው ነገር ደግሞ በፓርቲያችን አመራሮችና አባላት ላይ የተደረገው ድብደባ ነው፣የሆነ ማስተላለፍ የፈለጉት ነገር ያለ ይመስላል፡፡የጭካኔያቸውን መጠን እንድናውቅ የሚደበድቡት አቅመ-ደካሞችን፣ሽማግሌወችንና ሴቶችን እየመረጡ በፍጹም አረመኔነት ነበር፡፡ይህን ተግባራቸውን ስመለከት የደረሱበትን የዝቅጠት ደረጃ መታዘብ ችያለው፡፡ከፖለቲካ ልዩነትም፣ከአምባገነንነትም በላይ ሰወቹ እንደታመሙ ነው ለመረዳት የቻልኩት፣ስር የሰደደ የቁስ ሰቀቀንና የስልጣን ጥም የተጣባቸው፣ለዚያ ሲሉም የትኛውንም አይነት ውርደት ለመቀበል የቆረጡና የሞራል ልዕልናቸውን ሙሉ በሙሉ ያጡ ሰዎች ናቸው፡፡ስነ-ልቦናቸው ክፉኛ ተቃውሷል እንጂ ሀገር እመራለው የሚል ቡድን እንዲህ ያለ ተግባር ይፈጽማል ለማለት እቸገራለው፡፡በአባላቶቻችን ላይ ክፍኛ ድብደባ ተፈጽሟል፣እስከዛሬም እግሮቻቸው መራመድ የማያስችላቸው፣የሚያነክሱ ሰዎች አሉ፡፡እውነት ለመናገር ይሄ እብደት ነው፡፡አንዲት እራሷን መከላከል የማትችል ሴትን ለሶስት መደብደብን ከዚህ በተሸለ ልገልጸው አልችልም፡፡

አንድ ማስገንዘብ የምፈልገው ነገር ለኛ ዋነው ጉዳይ የዜጎቹ ህጋዊነት ወይም ህጋዊ ያለመሆን ጉዳይ አይደለም፡፡በምንም አይነት መንገድ ሴቶች እየተደፈሩ፣ወንዶች በየስርቻው እንደ ውሻ ተቀጥቅጠው እየተገደሉ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች ታጉረው ይህን ሁሉ መከራ መቀበላቸውን ልንታገሰው፣ወይም ከህጋዊነት አንጻር እየተራቀቅን ልንመለከተው አንችልም፣ስለ ህግም ከተወራ የሳውዲ አረቢያ መንግስት ጭፍጨፋው ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ባላቸው ላይ ጭምር ሲፈጸም እንደነበር አምኗል፡፡

ባለንበት የግሎባላይዜሽን ዘመን የአንዱ ሀገር ዜጋ ካለ ሀገሩ መገኘት አገር ይያዝ የሚያስብል አይደለም፡፡መውጣት ካለባቸው ጊዜ በመስጠት፣ከመንግስታቸው ጋር በመነጋገር በዘዴ ነገሩን መከዎን እየተቻለ አንድ ሀገርና መንግስት በሰዎች ላይ እንዲህ የጭካኔ ጥግ የሆነን አቋም ይዘው መንቀሳቀሳቸው ፍጹም ኢ-ሰብአዊነት ነው፡፡
ለኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለ አስከፊ ጊዜ የለም፣እውነቱን ለመናገር ለአገዛዙ ሰዎች የነበረኝ ጭላንጭል ተስፋም አፈር ተደፍቶባታል፣እንዲህ ግልጽ የሆነ ጭፍጨፋ እየደረሰብን እንኳ በድፍረት ለመናገር አልፈለጉም፡፡ስለ ኢትዮጵያውያን መገደል ለማውራት ሲፈልጉ ሌላ ሀገር ይጠቅሱና እነሱም እኮ እየተገደሉ ነው ይላሉ፣ወገን ከምንለው የማህበረሰባችን አካል ይሄን መስማቱ ከጥቃቱ ይበልጥ ያማል፡፡

ለምሳሌ ኢቲቪ ስጉዳዩ ሲያወራ ህገ ውጥ ሊባል የሚችል ድርጊት ተፈጽሟል በማለት ነው፡፡ተመልከቱ! እንዴት ያለ ባዕድነት ነው?ኢትዮጵያውያን በድህነትም ውስጥ እንኳ ለክብራችን የመሞት ባህሪ አለን፣ይሄ ከቀደሙት አንጡራ ኢትዮጵያውያን የወረስነውና ዛሬም ያለን ሀብታችን ነው፡፡

ትናንት ፍየል ጠባቂ የነበረ በረኸኛ ይህን ክብራችንን ገፍፎ እንደውሻ ቀጥቅጦ ስርቻ ሲጥለን ያልተቆጣ መንግስት ኢትዮጵያዊ ነው?ከዜጎቹ የወጣና ለህዝቡ የቆመ እውነተኛ መንግስት ከዚህ የበለጠ የሚቆጣበት ጉዳይ ከወዴት ይመጣል? እውነተኛ መንግስት ቢሆን ኖሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሳውዲ ካምፓኒዎችን በሰአታት ውስጥ ማባረር፣ኢምባሲውን ዘግቶ አምባሳደሩን ማሰናበትን የመሳሰሉ ውሳኔዎችን ያሳልፉ ነበር፡፡የሆነው ግን በተቃራኒው ነው፣የድፕሎማሲ ግንኙነቴ ሊበላሽ ይችላል ብሎ እኛ ድምጻችን እንዳናሰማ ደበደበን፣አፈነን፡፡በግልጽ እንደሚታየው የጥቅም ትስስሩ ነው አፋቸውን ያዘጋቸው፣ይህች ጥቅማቸው እንዳትቋረጥ በዜጎች ህይዎት መደራደርን መርጠዋል፡፡

ስነ ልቦናቸው የተቃወሰ በመሆኑና ተራ ስስታሞች በመሆናቸው እንጂ ኢንቨስትመንትም ሆነ ዲፕሎማሲ ግብአትነታቸው ለሰው ልጅ ነው፣እንደ አህያ ሲያፈጋ ከርሞ ሬሳቸውን ለላከ መንግስት እንዴት ተመጣጣኝ ምላሽ ለመመለስ ይገዳል?እንዴት እንደ ኢትዮጵያ ያለች ታሪካዊትና ለአፍሪካ የነጻነትና የኩራት ተምሳሌት የሆነች ሀገርን እየመሩ እንዴት ትናንት የነዳጅ ዘይት ባቆማቸው እረኞች ስትዋረድ ዝም ይላሉ?!::

እንዴት!በዜጎች ህይወት የተደራደረው አገዛዝ ማለፉ አይቀርም፣ለዚህ ጥርጥር የለኝም፡፡ታሪክ ለመጥቀስ ብዙ ርቀት መሄድ አያስፈልግኝም፡፡የቅርብ የሰሜን አፍሪካ አምባገነኖች የከፋ ፍጻሜ አለና፡፡ኢትዮጵያውያን ፍቅርም ጸብም እናውቃለን፣ሳውዲወችም የፈጸሙትን ግፍ ማወራረዳቸው አይቀርም፡፡በዚህ ክፉ ጊዜ ስለስብአዊ መብት ቆመናል የሚሉ አለም አቀፍ ተቋማት ዝምታን መምረጣቸው እውነተኝነታቸውን ለመመርመር ጥሩ እድል ይሰጠናል፡፡

መንግስት ቢኖረን ኖሮ ይሄ ሁሉ ውርደት ይፈጸምብን ነበር ብየ አላስብም፡፡በዚህ ሰአት ርዕሰ-መንግስት ብሆን ኖሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ድርጅት እንደመሆኑ፣ወደየትኛውም ሀገር የሚደረገውን ጉዞ አቋርጨ ዜጎቸን ማስወጣትን አስቀድም ነበር፡፡ያሄ ጥቂት ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ሊያመጣብን ቢችልም ከከፋው የዜጎች ስቃይ ጋር ግን በአንድ ሚዛን ላይ አይቀመጥም፡፡የአደጋ መከላከያና ዝግጁነት ኮሚሽን የሚባል ድርጅት አለ፡፡በዜጎቻችን ላይ ጎርፍና ድርቅ ሲመጣ ብቻ ነው የሚንቀሳቀሰው? ይሄም ሰው ሰራሽ አደጋ ነው ሙሉ ሀይሉን ወደዚህ አዙሮ ሊንቀሳቀስ ይገባው ነበር፡፡

እርግጥ ነው ባቀድነው መሰረት ሰላማዊ ሰልፉ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ እንዳይሆን አድርገውታል፡፡ጩኸቱ ግን ይቀጥላል……ባለን አቅም ሁሉ አፈናውንም፣ወከባውንም ተቋቁመን ለዜጎቻችንና ለኢትዮጵያዊነት እንታገላለን፡፡

አገዛዙ ይሄን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያፍን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንድ መልእክት አስተላልፏል፣ይህን መልእክት እንዲያስትላልፍ ማስገደዳችንም ለኛ ትልቅ ስኬት ነው፡፡የሳውዲ መንግስት ያሻውን ያደርግ ዘንድ የፈቀድኩት እኔ ነኝ፣በመሆኑም እሱን በመቃወም ግንኙነቴን አታበላሹ ብሎ እርምጃ በመውሰዱ ህዝቡ የነገሩ ቁልፍ የት እንዳለ፣የአጥቂወቹ በራስ መተማመን ምን ላይ እንደቆመ በጠራ ሁኔታ ለመመልከት እንዲችል ሆኗል፡፡

ይሄ ሁሉ ነገር እየተፈጸመ የተስተዋለ አንድ ነገር አለ፡፡የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝምታ እውነተኛ ማንነታቸው፣እውነተኛ በአገዛዙ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ያሳየን ክስተት ነው፡፡እንደሚታወቀው እሳቸው በኢህአዲግ እንጂ በኢትዮጵያ ህዝብ የተመረጡ አይደሉም፡፡ኢህአዲግ የሚናገረው ከሌለ እርሳቸው የሚሉት አይኖርም፡፡እንደ አንድ ሀገርና ህዝብ መሪ ግን የመኮነንም ሆነ የማጽናናት ቃል ይጠበቅባቸው ነበር፡፡

ባሉበት ቦታ ያስቀመጣቸው ህወሀት ነው፤ድርጅቱ ደግሞ ይሄን አቋም አልወሰደም፡፡ስለዚህ እንደሚቆጣቸው ስለሚያውቁ ዝምታን መረጡ፣ቸልታንም አስበለጡ፡፡በሀገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ከዚህ በላይ ሽንፈት ያለ አይመስለኝም፡፡

(ይህ ጽሁፍ በፋክት መጽሄት ተስተናግዷል፣ነገር ግን መጽሄቱ ላልደረሳቸው ሰዎች ይደርስ ዘንድ እዚህ ለማስተናገድ ወደድኩ፡፡)

በሽብርተንነት ስም የህዝብ መብቶችን ማፈን ይቁም!

November 26, 2013
ከቅዱስ ዬሃንስ

ፀረ -ሽብርተኝነት ለአምባገነኖች ሁለት ጥቅም ያስገኝላቸዋል፡፡ አንደኛ በፀረ- ሽብርተኝነት ስም ከምዕራባውያን ኃያላን ጎን በአጋርነት በመቆማቸው በጥሬ ገንዘብም ሆነ በዓይነት (ለምሳሌ በመሣሪያ፣ በፖለቲካ ድጋፍ) ዳጎስ ያለ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ ሁለተኛ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስም የሚያወጡት ሕግ የውስጥ የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውን ለማጥቃት የሚያስችላቸውን ሕጋዊ ሽፋን ይሰጣቸዋል፡፡ ስለዚህ ነው ፀረ -ሽብርተኝነት ለአምባገነኖች ከሰማይ የወረደ የተቀናቃኝ ማጥቂያ መሣሪያ ነው የሚባለው፡፡ ይህንን ያልኩበት አብይ ጉዳይ ዛሬ ሃገራችንንና ህዝቧን እያስጨነቀ ያለው የወያኔ አገዛዝ የፀረ ሽብርተኝነት ህግን ከለላ በማድረግ በሰላማዊ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው የመብት ረገጣ፤ እጅግ የከፋ ደረጃ በመድረሱ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ ሰራዊት በጋራ ወታደራዊ ጥቃት ፈፀሙ

November 26, 2013
የጋራ ትግል አስፈላጊ መሆኑን በፅኑ የሚያምኑት የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር /ኢሕአግ/



የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ /ጋሕነን/ በሕዳር 13/2006 ዓ.ም በሁመራ ሉግዲ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1፡00 ለሶስት ሰዓት ያህል በወሰደው ውጊያ የወያኔው 24ኛ ክፍለ ጦር ድባቅ ተመቷል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት በ24ኛው ክፈለ/ ጦር ላይ በተመሳሳይ ሥፍራ  ከፍተኛ ድል መቀዳጀቱ ይታወሳል።

በሕዳር 13/2006 ዓ.ም የኢሕአግና የጋህነን ሰራዊት በወሰዱት ድንገተኛ ወታደራዊ ጥቃት 66 /ስልሳ ስድስት/ ገድለው 113 /አንድ መቶ አስራ ሶስት/ በማቁሰል እንዲሁም ቁጥራቸው የበዛ የጦር መሳሪያዎችን ከነ ሙሉ ትጥቃቸው ማርከዋል።

ሁለቱ ድርጅቶች በጋራ በተለያየ የትግል መስክ ሲተጋገዙና ሲተባበሩ ቆይተዋል የግንኙነታቸውን እድገትና ለውጥ የሚያሳይ ወታደራዊ ጥቃትም ፈፅመዋል።

ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመኘውና የሚፈልገው የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ስምምነትና አንድነት መገለጫ ሊሆን የሚችል አኩሪ ጥቃት መሆኑ ይታመንበታል ። በጥቃቱ የተካፈሉ የሁለቱ ድርጅቶች ታጋዮች እንዳብራሩት ዛሬ በጋራ የጀመርነው ወታደራዊ ጥቃት በዚሁ የሚያበቃ ሳይሆን የጋራ ዓላማና ራዕይ እስካለን ድረስ ወደኋላ የማይቀለበስ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህም አክለው የዚህ ወታደራዊ ዘመቻ ዓላማ አገር እንደሌለው ሁሉ በሰው አገር ፍዳውን እያየና እየተሰቃየ እንዲሁም ለሞት እየተዳረገ የሚገኙውን በሳውዲ አርቢያ ለተፈፀመው በደል ለመበቀልና ሕዝባዊ ወገንተኝነታችንን ለማሳየት ታስቦ የተወሰደ ወገናዊ እርምጃ ነው በማለት አብራርተዋል።

በውጊያው ከሞት ተርፎ ለከባድ ቁስልና የአካል ጉዳት የተዳረገው የወያኔው ቅጥረኛ የ24ኛ ክፈለ ጦር አባላትን ከሁመራ አንስቶ እስከ ትግራይ የሕክምና ማዕከሎች ማጋጋዝ ዋነኛ ተግባሩ ሆኗል።

ይህንን የጀግና ጥቃትና ድል የተመለከቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ሰራዊቱን እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎ በመቀበልና ስንቅና ትጥቅ በማቅረብ አጋርነቱን ያስመሰከረ ሲሆን የተጀመረው ወታደራዊ ጥቃት በተለያዩ አካባቢዎች ላይ እንዲደገም ያላቸውን ልባዊ ምኞት ገልፀው በንፁሃን ላይ ያለ አግባብ ሲወሰድ የነበረው የቅጥረኞች እርምጃ አንጀቱ ላረረው ሕዝብ እምባ ያበሰ እንደሆነም ተናግረዋል።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር/ ኢሕአግ/ እና የጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ /ጋህነን/ ወያኔ ለ22 ዓመት ያህል አገሪቷን ሲበዘብዝና ሕዝቡ የዲሞክራሲያዊ መብቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን በሃይል የመግዛቱ ሂደት እንዲያከትም የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ቆርጠው መነሳታቸውን አስታውቀዋል።

Monday, November 25, 2013

ኢትዮጵያዊ ዋጋው ስንት ነው? (ተመስገን ደሳለኝ)

ኢትዮጵያዊ ዋጋው ስንት ነው?
ተመስገን ደሳለኝ
November 25, 2013


የዚህ ፅሁፍ ማጠንጠኛ የፖለቲካ አመለካከትን መተቸት አይደለም፤ ከዋና ዋና ሀገራዊ አጀንዳዎች ወረድ ያሉ የጉልበታሙን ስርዓት የሥራ አፈፃፀሞችን ማብጠልጠልም አይደለም፤ የተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ስንክሳር መንቀስም… አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ (አል-ሀበሽ) መሆን ለፈተና፣ ለመከራ፣ ለሰቆቃ… መዳረጉ የወለደው ብሶት እንጂ፤ መመረር-ማምረር ነው፡፡ …ይህ የእኛ ዕጣ ፈንታ የሆነበትን ምስጢር መመርመር ነው፡፡

ሰሞኑን የሳውዲ አረቢያ መንግስት ታጣቂዎች እና በድጎማ የሚያድሩ የሀገሬው ተወላጆች በመሰረቱት የጥፋት ግንባር ጉልበታቸውን ገብረው፣ በላብ በወዛቸው በሚያድሩ ስደተኛ ወገኖቻችን ላይ የተፈፀመው አረመኔያዊ ወንጀል፣ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ልብ በከባድ ሀዘን የሰበረ፣ በቁጭት ያንገበገበ አሳዛኝ ፍፃሜ ሆኗል፡፡
ጭፍጨፋው ሃይማኖታዊው ጀሀድ ያወጀው አይደለም፤ ኢትዮጵያዊነት ባመጣው ዕዳ በድሃ ወንድም-እህቶቻችን ጀርባ ላይ ያረፈ ምህረት የለሽ ብትር እንጂ፡፡ …ይህ ግን ለምን ሆነ? ጥያቄ ነው፡፡

ርግጥ ነው፣ እንዲህ አይነቱ የእልቂት ነጋሪት መጎሰም ከጀመረ ዓመታት ነጉደዋል፤ መነሻ ሀገሩ ግን ሳውዲ አረቢያ ወይም ሊቢያ አይደለም፤ እዚሁ ኢትዮጵያችን ምድር ላይ እንጂ…

ዘ-ፍጥረት…
የየካቲቱ አብዮት ድንብዥታ (ሀንግኦቭር) ዛሬም ድረስ ዘመን ተጋሪዎቼን እያሳደደና እያሰደደ ይገኛል፡፡ ያኔ ያ ትውልድ ‹ኑ እንነሳ፣ ከተማውን እንውረር፤ አሮጌውንም ቅፅር በጩኸት አፍርሰን፣ አዲሱን እንፍጠር!› የሚል መለከት መንፋቱ ሙሉ ለሙሉ ስህተት ባይሆንም ‹የተጠሩ ብዙዎች፣ የተመረጡ ጥቂቶች› እንዲል መፅሀፉ፣ እፍኝ ለማይሞሉ ‹ምርጥ ወታደራዊ መኮንኖች› የተናጠል አሸናፊነት፣ የወል ተጠያቂ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ስለምን ቢሉ? ስለተከሰተው ታሪክ ይሆናል መልሱ፡፡ በርግጥም ‹ፓርቲ› የሚባል የ‹ጦስ ዶሮ› ባነበረው ልዩነት በጥይት ደብድበው ሲያበቁ፣ አፈር ፈጭቶ፣ ውሃ ተራጭቶ ባደገበት መንደር እንደ መናኛ በየመንገዱ አስጥቶ ማዋል፣ ለግብዓተ መሬቱ የጥይት ዋጋ ማስከፈል፣ ወላጆችን እርም መከልከል… ከዚህ የከፋ ምን ሊያመጣ ኖሯል? …ከተኛበት አልጋ
እያነቁ መስቀል፣ ከገሀነም በከፋው ቅጣት ‹ወፌ-ላላ› ገልብጦ ማሰቃየት፣ በአንድ ጉድጓድ ስልሳውን አነባብሮ መቅበር… ከዚህ ሌላ ምን ሊያስገኝ ኖሯል? …የሆነውም ይህ ነበር፡፡ እነሆም ያ ትውልድ የፀነሰው የተገነባውን መናድ፣ የተሰራውን ማፍረስ፣ በራስ ወገን ላይ መከራ ማዝነብን የሚመክረው የዘ-ፍጥረት መፅሀፍ ምዕራፍ እዚህ ጋ ነበረ የጀመረው፡፡

አዲስ ታሪክ አልተሰራም!

‹አዲስ ንጉስ እንጂ፣ ለውጥ መቼ መጣ!› እንዳለው ከያኒው፣ ታጋዮቹ በወታደሮቹ ቦታ ከተቀመጡ በኋላ የነበረው-እንደነበረው ነው የቀጠለው፤ ‹ባለሙያ› ገራፊዎች በአሸናፊዎቹ ከመተካታቸው በቀር፣ ማሰቃያ ጎሮኖቹ ዛሬም ወደ ሙዚየምነት አልተቀየሩም፣ መገረፊያው፣ መገልበጫው፣ መግደያው፣ መጋዣው… አሁንም የቀድሞውን ግልጋሎታቸውን እየሰጡ ነው፡፡ ማን ያውቃል? ነገም በዚሁ ይቀጥሉ ይሆናል፤ ለአጎራባች መንደሮች መቀጣጫ በሚል የጭካኔ ፈሊጥ፣የአማፅያን ኮሽታ የተሰማበትን መንደር ሁሉ ዶግ አመድ ማድረግም፣ የጄነራሎቻችን የጦር ‹ጠበብ›ነት መገለጫ ሆኖ ቀጥሏል፤ በሀውዜን፣ አርባ ጉጉ፣ አርሲ፣ ሐረር፣ ጋምቤላ፣ አዋሳ፣ ኦጋዴን፣ ቀብሪ-ደሀር፣ ደገ-ሀቡር… የፈሰሰው የግፉአን ደም፣ የተከሰከሰው የንፁሀን አጥንት ታሪክ ነጋሪ ጥቁር ሀውልት መሆኑን ማን ይክዳል? ይህንን ሁሉ ምድራዊ ፍዳ፣ ዓለም እንደ ማንኛውም አሳዛኝ ዜና ሰማው እንጂ፣ ሰለባዎቹን ለመታደግ ያደረገው እዚህ ግባ የሚባል እንቅስቃሴ
አልነበረም፤ በራስ መንግስት፣ በራስ ወገን መናቅ፣ ክብር መነፈግ፣ ለ‹ምርኮኛ ሕግ› ማደር… ክፋቱ እዚህ ላይ ነው፡፡ የዛሬዎቹ አረቦቹም በወገኖቻችን ላይ የጭካኔ እጃቸውን እንዲያነሱ የልብ ልብ የሰጣቸው፣ ይኸው የእኛው የእርስ በእርስ አለመደጋገፍና አለመከባበር ነው፡፡ ትላንትና በጉራ ፈርዳና ቤንች ማጂ ዞን ጎሳ መመዘኛ ሆኖ ‹ውጡ የክልሉ ተወላጅ አይደላችሁም› በሚል በገዛ ወገኖቻቸው እንደጠላት ሀገር ሰው በጦር መሳሪያ ተከበው፣ ንብረታቸውን ሜዳ በትነው ስለተባረሩ ኢትዮጵውያኖች፣ የሰሙ አረቦች ‹ሳወዲያ አረቢያን ልቀቁና ውጡ› ብለው ይህ አይነቱን መዓት ቢያወርዱ ምን ይደንቃል? የባዕድ ሀገር ሰው የትንኝ ነፍስ ያህል እንኳ ሳይጨነቅ እንደዘበት ህይወታችንን ቢነጥቀን በእርሱ ላይ መፍረድ እንዴት ይቻለናል? አሳልፈው የሰጡን እነማን ሊሆኑ ነው?

እመነኝ፣ በሳውዲ አረቢያ ጎዳናዎች የሰው ራስ ቅል እንደ በግ በመጥረቢያ ሲከሰከስ፣ እንደ ጦስ ዶሮ ተጋድሞ ሲታረድ፣ በቁሙ እሳት ሲለቀቅበት፣ ህፃናት የወታደር መለዮ በለበሱ አረመኔዎች ሲረገጡ… ልብህ እያለቀሰ፣ ፊትህ በእንባ እየታጠበ ያየኸው አይነት ጭካኔ ምንጩ ይህ ነው፤ ይህም ነው የኢትዮጵያን ሰው በአልባሌ ምክንያት መግደል፣ እያፏጩ ጉዞን የመቀጠል ያህል ያቀለለው፤ ለዚህም ነው በሙስሊሞች ቅድስቲቷ መዲና ላይ በድንጋጤ የጨው አምድ የሆነ አካለ-ቁመና፣ በሽብር ተውጣ አቅሏን የሳተች እህት፣ ስጋት ያናጠበው ወንድም ተመልክተህ በሀዘን የተቆራመድከው፤ ‹‹ወይኔ ወገኔ!›› ብለህ ደም እንባ የተራጨኸው፡፡ …እናስ! ለዚህ ሁሉ ጥፋት ተመጣጣኝ ዋጋ መክፈል ያለበት ማን ነው? ንጉሥ አብደላና ዕኩይ ተከታዮቹ ብቻ? ወይስ እንዲህ የፊጥኝ አስሮ ለአረብ ሀገራት መቀለጃ የዳረገህ መንግስትህም ጭምር?

ከችጋርና ጭቆና ያልተፋታ ሕዝብ ዳቦና ነፃነት ፍለጋ እግሩ ወዳደረሰው ሀገር ተሰዶ መኖሩ በእኛ የተጀመረ አይደለም፤ እንዲያውም ስደተኞችን ካስተናገዱ ከመጀመሪያዎቹ ጥቂት የዓለም ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምነት የምትጠቀሰው የእኛዋ የአቢሲኒያ ምድር ኢትዮጵያ ነች፡፡ የሩቁን ትተን እስከ የኃ/ስላሴ ስርዓት ፍፃሜ ድረስ የነበረውን ተጨባጭ ሁነት ብንመለከት እንኳ፣ ‹አረብ ቤት› በሚል ተቀፅላ የሚታወቁት ብዙዎቹ ሱቆችና የንግድ መደብሮች፣ በስደት መጥተው እኩል እንደ ዜጋ ሀገራችን መኖር በቻሉ አረቦች የተያዙ ነበሩ፡፡ የዛሬን አያድርገውና ይህች ገናና ሀገር ለሌሎች ሀገራት ሕዝቦች የነፃነትና የክብር ተምሳሌትም ነበረች፡፡ በመፅሀፍ ቅዱስም ሆነ በቅዱስ ቁርአን ውስጥ በፈሪሐ እግዚአብሔርነቷ፣ በፍትሐዊነቷና በርትዓዊነቷ ስሟ ተደጋግሞ የተወሳና የተመሰከረላት፣ የታላቅ ሕዝብ ታላቅ ሀገር ነበረች፡፡ ዛሬ በተፈጥሮ ማዕድን በልፅጋ የሀበሻ ስደተኞች መናኸሪያ ለመሆን በበቃችው ሳውዲ አረቢያ የተወለዱት ነብዩ መሀመድ የዛሬ 1400 ዓመታት ገደማ በስደት መጠለያነት የመረጧት፣ ሀገሪቷም ተከታዮቻቸውን እጇን ዘርግታ በመቀበል ከራሷ ዜጋ እኩል ተንከባክባ ያኖረቻቸው ስልጡን ሀገር ነበረች፡፡ ማን ነበረ ‹ወርቅ ላበደረ…› ያለው? እነሆም ዘመኑ ተቀያየረና ‹‹የኋላኞቹ ፊተኞች፣ የፊተኞቹ ኋለኞች›› ይሆኑ ዘንድ ግድ በማለቱ ዛሬ አብዛኞቹ የአረብ ሀገራ ኢኮኖሚያዊ ልዕልና እየተጎነፀፉ ሲመጡ፣ እኛ የኋሊት ተንሸራተን ቁልቁል ለመውረድ በቃን፡፡

ምንም እንኳ እነዛ ሁሉ መልካም መገለጫዎቻችን ዛሬም ድረስ ባናጣቸውም፣ በብሔር ክፍፍልና በእርስ በእርስ ሹኩቻ የተነሳ ግን በደህነት ማጥ ውስጥ ተዘፍቀን፣ እኛም በተራችን መሰደድ ዕጣ ክፍላችን ሆኖ ቀረ፡፡ ዛሬ አብዛኛው ወጣት በሀገሩ የመኖር ተስፋው በመሟጠጡ፣ በስደት ወጀብ የሚንገላታ፣ ማረፊያ እንዳጣች ወፍ ሲናወዝ መሽቶ የሚነጋለት ብኩን ሆኗል፡፡ በሀገሩ እጅግ ከመመረሩም የተነሳ ራሱን ለሻርክ ጥርስ፣ ለእንግልት፣ ለግርፊያና ለበልዓ-ሰቦች አሳልፎ እስከ መስጠት በሚያደርሰው የስደት ጉዞ ለማለፍ የማያመነታ ትውልድ ለመሆን ተገዷል፡፡ ይህ ከድህነት ወለል ስር ያሳደረን የዘመን ግርሻ፣ ይህ ከመንግስት ጋር አይንና ናጫ ያደረገን አምባገነናዊ አገዛዝ፣ ለዚህ ሁሉ አሳረ-መከራ ዳርጎን፣ ከሀፍረት ጋር አንገታችንን እስደፋን… ውለታን ከማስረሳቱም በላይ ለከፋ በደል አጋልጦ ቁጭት አስታቀፈን፡፡

ሰሞኑን ‹‹የበላችበትን ወጪት…›› ከሰበረችው ሳውዲ አረቢያ የተሰማው አሰቃቂ ዜናም የእዚህ የኢትዮጵያን ስደተኞች ተከታታይ ፍዳ ጉትያ ነው፡፡ እርግጥ አብዛኛው የአረብ ሀገራት መሬቱ ሰለጠነ እንጂ ሕዝቡ ገና ጨለማ ዘመን ውስጥ ነው፤ ሌላ ሌላውን ወደጎን ብለን የሰሞኑን አውሬአዊ ባህሪያቸው እንኳን እንደ አይነተኛ ማሳያ ልንወስደው እንችላለን፤ ይህ ድርጊትም እንሰሳዊ ባህሪያቸው የስነ-ዝግመት ለውጥን ገና አለማገባደዱን ያመለከተ ነው፡፡ ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒሊክ አድዋ ላይ፣ ያውም ሀገራቸውንና ዙፋናቸውን በጦር ኃይል ለመንጠቅ የጎመዠችው ሮም ያዘመተቻቸው ወታደሮች፣ እልፍ አእላፍ ሠራዊታቸውን ፈጅተው፣ የቅርብ ወዳጆቻቸው የሆኑ የጦር አበጋዞቻቸውን ገድለው የማታ ማታ የሽንፈትን ፅዋ አስጎንጭተው ከማረኳቸው በኋላ በርህራሄ ተንከባክበው እንደያዟቸው የዓለም ታሪክ ያውቀዋል፡፡

በሀገሩ ኑሮ አልቃና ብሎት፣ በሰው ምድር የሰው አደፋ አፅድቶ፣ ቆሻሻ ለቅሞ… ፋታ የማይሰጠውን የእህል ውሃ ጥያቄ ለመሙላት በማሰነ፣ ሆድቃን በሳንጃ መዘርገፍና የዱር አውሬ እንኳ የማይፈፅመው የጋርዮሽ ሴት ደፈራ መፈፀም… ምን አይነት ‹ኢብሊሳዊ› (ሠይጣናዊ) ተግባር ነው? የተቸነፈን መልሶ ማቸነፍ፣ የወደቀን መርገጥስ ‹ከመክፈር› (ፈጣሪን ከመካድ) በምን ይለያል?

አሁንም እደግመዋለሁ፡- ይህ ፖለቲካ አይደለም፤ እየፈሰሰ ስላለ የንፁሀን ደም፣ የወላድ መሀን ስለሆኑ እናቶች፣ ጧሪ ቀባሪ ስላጡ የተራቡ አባቶች፣ አሳዳጊ አልባ ስለሆኑ ህፃናት፣ ያለሚስት ስለቀሩ አባወራዎች፣ ባላቸውን ስለተነጠቁ የቤት እመቤቶች … የሰቆቃ እሪታ ነው፡፡ በወጡበት ሰው ሀገር ላይ ወድቀው ስለሚቀሩ ወገኖቻችን ዋጋ ስለመጠየቅ ነው፤ ለነጋዴው መንግስታችን ኢትዮጵያዊው ዜጋ ዋጋው ስንት እንደሆነ የመሞገት ጉዳይ ነው፡፡

ሀገር ምን ማለት ነው? ‹ሀገር› የሚለውን ቃል የኢህአዴግ መራሹ-መንግስት መዝገበ ቃላት ምን ፍቺ ሰጥቶት ይሆን? ሉዓላዊነትስ በ‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ› ቀዩ መፅሀፍ አንደምታው ምን ይሆን? …ቀለብ ሰፍረን የምናሳድረውን ሠራዊት ሞቋዶሾ ድረስ ልኮ፣ የባራክ ኦባማን ስጋት ማቃለል? በ‹ተባበሩት መንግስታት› ስም የሲ.አይ.ኤ ቅጥረኛ ሆኖ በሱዳናዊያን የውስጥ ችግር ላይ-ታች እንዲማስን ማድረግ? የሕዝብ ደህንነት መ/ቤትስ ኃላፊነቱ የእናንተንና የቅምጦቻችሁን ደህንነትና ምቾት መጠበቅ ነውን? የአምባሳደሮቻችን የሥራ ድርሻ ፓስፖርት ማደስና የመግቢያ ፍቃድ መስጠት ብቻ ነው? በስደተኛ ወገኖቻችን ላይ ‹ጊንጥ ሰላይ› መሆን? ቦንድ መሸጥ? ‹ኢህአዴግ ጌታ ነው› እያሉ መስበክ? …ወይስ የዜጎችንም ደህንነት መከታተልና መጠበቅንም ጭምር? …ይህ ነው የወቅቱ ዓብይ ጥያቄ፡፡

የዲፕሎማሲ ግንኙነትስ ምን ማለት ነው? አገዛዙ በአንድ ወቅት ተቀማጭነቱ ኳታር-ዶሀ የሆነው ‹አልጄዚራ› ቴሌቪዥን ‹ስሜን አጠፋ› በሚል የኳታርን ኢምባሲ እንደ ዘጋው አይነት ስራን ብቻ የሚመለከት ይሆን? ከዋነኞቹ ለጋሽ ሀገራት በግንባር ቀደምነት የምትመደበው ኖርዌይስ ኢምባሲዋ የተዘጋው ለማን ትርፍ ነበር? ለብሔራዊ ጥቅም መቆርቆርስ ‹ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አልተከበረም› ብለው ዘገባ ባወጡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ላይ ያንን ሁሉ አቧራ ማስነሳት ይሆን?

ሌላው ቢቀር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለምን እንደ ተመሰረተ ይዘነጋል? አባቶቻችን ኮሪያና ኮንጎ ድረስ የዘመቱት ለዓለም ዜጎች ሰላም መሆኑስ እንዴት ይረሳል? የድርጅቱ አባል ሀገራት የፈረሙት ስምምነትስ የሳውዲ አረቢያን ሽፍትነት እንኳ ለመከላከል አቅም አይኖረውም? በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት እልፍ አእላፍ ወታደሮቻችን ካለቁብን በኋላ ከባረንቱ የተመለስነው፣ ባድሜ ላይ የቆምነው፣ በዛላንበሳ የታገድነው… የማንን ሕግ አክብረን ነበር? ያውም ‹በስለላ ስራ ሊሰማሩ ይችላሉ› ተብለው የተጠረጠሩ ኤርትራውያን እንዲያ በክብርና በእንክብካቤ ወደ ትውልድ ሀገራቸው የተሸኙት፣ በጦር ሜዳ የተሸነፈው ሻዕቢያ ተፈርቶ ነበር እንዴ? …ይህ ነው እንቆቅልሹ፡፡

ዛሬስ መንግስታችን የስደተኛ ዜጎችን ደህንነት በምልዓት የማይከታተለውና የድረሱልኝ ጩኸታቸውን ሰምቶ ፈጥኖ እጁን የማይዘረጋላቸው ለምን ይሆን? ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ ሆኖበት? ወይስ በለመደው የንቀት መነፅር አይቶ እንዳላየ በቸልተኛነት አልፎት ነውን? በርግጥ ይህንን የበደል ማማ ካለፈው ታሪኩ አንፃር ከገመገምነው ምክንያቱ ሀገራዊ ስሜቱ ደካማና ከሥልጣኑ ሌላ ምንም የሚያሳስበው ነገር ባለመኖሩ ብቻ እንደሆነ ይገባናል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሠማያዊ ፓርቲ የአረቦቹን ወደር የለሽ ጭካኔ ለማውገዝ በሳውዲ አረቢያ ኢምባሲ በር አጠገብ የጠራውን የተቃውሞ ሰልፍ ያገደው ‹ይህ አይነቱ ሀገራዊ መቆርቆር ነገ ደግሞ መስቀል አደባባይን በሕዝብ ሱናሚ ለማጥለቅለቅ መነቃቃት የሚፈጥር ገፊ ምክንያት ሊሆን ይችላል› ብሎ በስጋት ስለተጠፈነገ ይመስለኛል፡፡

የሆነው ሆኖ የመንግስት ህልውናም ሆነ አቅም በእንዲህ አይነቱ ወቅት ነውና የሚፈተነው ኢህአዴግም በዚህ ተግባሩ ዜጎቹን የመታደግ ገት እንዳሌለው አስመስክሯል፡፡ መቼም በሲ.አይ.ኤ ተላላኪነቱ በ‹ዋይት ሀውስ› ማህደረ-መዝገብ ውስጥ ከጊዜ ጊዜ እየዳጎሰ የመጣው የ‹ውለታ›ው ዶሴ ለእንዲህ አይነቱ ፈታኝ ወቅት መሆን ይሳነዋል ማለት ይከብዳል፡፡ ሼክ መሀመድ አላሙዲንን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ የሳውዲ ነጋዴዎች፣ ሀገራችን ውስጥ በበርካታ የንግድ ዘርፎች ተሰማርተው አትርፈው ማደራቸው፣ በሰፋፊ እርሻዎች ዘርተው ማጨዳቸውስ እንደምን ተዘነጋ? ይህ ቢያንስ በነፍስ-ውጪ ነፍስ-ግቢ ለተያዙ ወገኖቻችን እንዴት የመደራደሪያ ጉልበት መፍጠር ሳይችል ቀረ? …በርግጥ መለስ ዜናዊ በ2004 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ከጎራ ፈርዳ ስላፈናቀላቸው አማርኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን በተጠየቀበት ጊዜ ‹‹ደን ጨፍጫፊዎች ናቸው›› ሲል የስላቅ መልስ እንደሰጠው ሁሉ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኀኖምም የሳውዲውን እልቂት
በተመለከተ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርቦ ‹‹የማባረር ሥራው በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዳልነበረ ተረድተናል›› በማለት መቀለዱ፣ ስርዓቱ ‹አስተዳድረዋለሁ› ከሚለው ሕዝብ ይልቅ ሥልጣኑንና ተያይዘው የሚመጡ ጥቅሞቹን በዜጎች ሕይወት ጭምር ተደራድሮ ከማስከበር እንደማይመለስ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ እንደ መንግስት በሀገር ሀብት እንደአሻው እየተምነሸነሸ፣ ‹ግዴታዬ የባቡር መንገድና ኮንዶሚንየም ቤት መስራት ብቻ ነው› ማለቱ ይህንኑ ይመሰክራል፡፡ አሊያማ ፋሺስቱ ጣሊያን እንዲያ በርካታ ድልድዮች፣ መንገዶች፣ ቤቶች… ገንብቶ ሲያበቃ፣ ‹ሀገር› ማለት ሕዝብ የሰፈረበት ሉዓላዊ ግዛት ማለት ነው ተብሎ ያ ሁሉ መስዕዋትነት ተከፍሎ በኃይል እንዲባረር ባልተደረገ ነበር፡፡

‹ሕዝቤን ልቀቅ!›

በዘመነ-ኦሪት በግብፅ ዙፋን ላይ በተፈራረቁ ፈርኦኖች፣ ለባርነት የተዳረጉ ዕብራዊያንን ነፃ ያወጣ ዘንድ በፈጣሪ ተመርጦ የተላከው ሙሴ ‹‹እግዚአብሄር ‹ያመልከኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ!› ብሎሀል›› ማለቱ በቅዱሳት መፃህፍት መገለፁ እውነት ነው፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ ራሱን ‹ኢህአዴግ› ሲል በሚጠራው ‹አምሳለ-ፈርኦን› ለመከራና ለሀፍረት የተዳረጉ ሕዝቦች አርነት ይጎናፀፉ ዘንድ ‹የሙሴ ያለህ!› የሚለው ጩኸታቸው ከተራራ ተራራ እያስተጋባ መሆኑ ሌላ እውነታ ነው፡፡ በሳውዲ አረቢያ የግፍ ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵውያን ደምም ዋይታ እየተበራከተ ነው፤ ስርዓቱ እንዲህ አይነቱ ሰቆቃን ለፖለቲካ ትርፍ እየተጠቀመበት መሆኑንም ሰሞኑን የመንግስት እና ደጋፊዎቹ ሚዲያዎች የሚያሰራጩትን ዘገባ መመልከት በቂ ነው፡፡ መቼም መሬት ልሰው፣ አፈር ቅመው ያፈሩትን ንብረት ተነጥቀው፣ ባዶአቸውን እየተመለሱ ያሉ ስደተኞችን ‹በሀገራችን መስራት ይሻለን ነበር› እንዲሉ ማስገደድ ለርካሽ ፖለቲካዊ ትርፍ ካልሆነ በቀር ሌላ ትርጉም  የለውም፡፡ አስከፊው ድህነታችን ጉርሻ እስከ መግዛት፣ ከቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ቅልጥም እስከ መምጠጥ፣ የወደቀ ምግብ ከውሻ ጋር ተጋፍቶ እስከ መመገብ… በደረሰበት በዚህ የችጋር ዘመናችን ላይ በምን አመክንዮ፣ ከየትኛው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ተመዝኖ ሊታመን ይችላል ተብሎ ነው ‹ሀገር ውስጥ ሰርቶ በሰላም መኖር ይቻላል› የሚለው ተራ ፕሮፓጋንዳ ነጋ-ጠባ የሚደሰኮረው? ምንድር ነውስ የሚሰራው? እዚህ እኛ ሀገር የማንን መፀዳጃ ቤት ንጽህና መጠበቅ ይሆን የአረቦቹን ያህል ዳጎስ ያለ ክፍያ ማስገኘት ቀርቶ፣ በቀን ሁለቴ ለመብላት የሚያግደረድረው? ቅጥ አንባሩን ያጣው የግብር ፖሊሲያችን፣ እንጀራ ቸርቻሪዎችን ሳይቀር አሳድዶ የእለት ጉርሻቸውን እየነጠቀና በተንሰራፈው ድህነት ላይ ተጨማሪ እልቂት አውጆ ድሆችን ለማጥፋት ሰይፉን በሚያወናጭፍበት በዚህ ወቅት፣ ወጣቱ እንዴት ብሎ ነው በሀገሩ ሰርቶ መኖር ይችላል የሚባለው? ገና ጀንበር ከማዘቅዘቋ ጎዳናውን የሚያጥለቀልቁት ህፃናት ሴተኛ አዳሪዎችንስ ምን እንበላቸው? የትኛው ተቀጣሪስ ነው በደሞዙ የወር ቀለቡን ሳይሳቀቅ መሸመት የቻለው? …ሁላችንም የመዳፋችንን ያህል አብጠርጥረን የምናውቀው በመሬት ያለው ተጨባጭ እውነታ ይህ ነው፡፡

እነሆም በመጨረሻ እንዲህ ማለት ወደድኩ፡- ስርዓቱ ሰባኪው እንዳለው ‹የከንቱ ከንቱ፣ ከንቱ› ቢሆንም፣ አቶ መለስ ዜናዊ በኤርትራ የመጀመሪያው የነፃነት ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ተገኝቶ በአስመራ ሳባ ስታዲዮም ለተሰበሰበው ህዝብ በደርግ የደረሰባቸውን በደል በማስታወስ ‹‹በእናንተ ጀርባ ላይ ያለው ጠባሳ በእኛም ላይ አለ›› ሲል ሀዘኑንና መቆርቆሩን እንደገፀላቸው ሁሉ፣ በሳውዲ አረቢያ የግፍ ሰለባ የሆናችሁ ወንድም-እህቶቼ ሆይ! የእናንተ ሰቆቃና በደል፣ በእኛም ግንባር ላይ ተቸክችኮ ሀፍረታችችንና ውድቀታችንን የጋራ እንዳደረገው የታሪክ ፍርድን መጠበቁ አይቀሬ ነው፡፡ እመኑኝ ያች ዕለትም አብረን የምንነሳበት፣ ከፍ ብለን የምንበርበት ትሆናለች፡፡›

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

የታላቁ ሩጫ ተሳታፊዎች ተቃዉሟቸዉን አሰሙ!!!


ቁጥራቸዉ ቀላል የማይባል ወገኖች ዛሬ በተካሄደዉ የ ታላቁ ሩጫ ላይ በሳዑዲ ስለሚሞቱና ስለሚንገላቱ ኢትዮጵያዊያን ድምፃቸዉን ሲያሰሙና በመንግስትም ላይ ወቀሳቸዉን በመፈክር እዲዲሁም በዜማ አሰምተዋል፡፡ መንግሰት በዚህ ሩጫ ላይ ህብረተሰቡ የሰማያዊ ፓርቲን ጥሪ እዳይቀበል በአዘጋጀቹ በኩል ቢያሳስብም(ጥቁር ሪቫን እንዳይደረግ) የሀገር ፍቅር ያቃጠላቸዉና የወገኖቻቸዉ ጥቃት ያተሰማቸዉተሳታፊዎች ከፍተኛ የፖሊስና የደህንነት ቁጥጥር ከቁብ ሳይቆጥሩ “በሳዑዲ ነገር እንነጋገር የሳዑዲን ነገር ” ሲሉ አርፍደዋል፡፡ ገና ከመግቢያዉ ጀምሮ ከፍተኛ ፍተሻ ሲደረግ የነበረ ቢሆንም አብዛኞቹ ተሳታፊዎች ሪቫኑን ትተዉ በጥቁር ኮፍያና ሱሪዎች ሩጫዉን መካፈል ችለዋል(በተቃዉሞዉ የተሳተፉቱ)፡፡

በሳዑዲ ላይ ተቃዉሟቸዉን ሲያሰሙ በነበረበት ወቅትም ዳር ዳር ላይ ቆመዉ ሁኔታዉን ሲከታተሉ የነበሩ ሰዎችና በእድሜ የገፉ ሰዎች በእልልታ እና በጭብጨባ ያበረታቱዋቸዉ ነበር፡፡ በዚህ አኳኋን የተካሄደዉ ሩጫ(እርምጃ) ወደ መጠናቀቁ ላይ ግን በደህንነቶች የሚነዳዉ(የሚታዘዘዉ) የፖሊስ ሀይል አንድ ቡድን ላይ በማተኮር ከበባ የሚመስል ነገር በማድረግ እየቆራረጡ ወደ ጃንሜዳ ግቢ እዲገቡ በማድረግ በሩ አካባቢ ላይ ሶስት የሚሆኑ ወጣቶችን(በከፍተኛ ሁኔታ መፈክር ሲያሰሙ የነበሩ) አስረዋል፡፡ በዚህ የተደናገጡት ተሳታፊዎችም ጩኸት በማሰማት ወደ ዉስጥ እየተሯሯጡ በመግባት ሩጫዉም ተቃዉሞዉም ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

ጎንደር ዩኒቨርስቲ አንድ ተማሪ ተገደለ

(ኢ.ኤም.ኤፍ) በጎንደር ዩኒቨርስቲ የ3ኛ አመት ማርኬቲንግ ተማሪ የነበረው አንተነህ አስፋው መገደሉን የደረሰን ዘገባ አመልክቷል። ትላንት ምሽት ወደ ዩኒቨርስቲው ከሴት ጓደኛው ጋር ወደዩኒቨርስቲ እየሄደ የነበረው ወጣት፤ ከግቢው ውጭ የዩኒቨርስቲው ጠባቂ ያስቆመዋል። ተማሪውም “ከዩኒቨርስቲ ውጪ ልታስቆመኝ አትችልም” የሚል ክርክር ይገጥማል። በዚህ መሃል ሴት ጓደኛው ተመትታ ራሷን ስታ ትወድቃለች። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተነሳ ግርግር ጥበቃው ተኩስ ይከፍትና ተማሪዎች ይበታተናሉ። በንጋታው ጠዋት ግን ያልተጠበቀ ነገር ገጠማቸው።

ምሽቱን ተማሪዎችን ለመበተን ይሁን ወይም ሆን ተብሎ በተተኮሰው ጥይት አንድ ተማሪ ቆስሎ ኖሮ፤ ጠዋት ወደ ዩኒቨርስቲ ሲመለሱ፤ አንድ ተማሪ ሞቶ ተገኝቷል። ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ነው። በጎንደር ዩኒቨርስቲና በከተማው አካባቢ ይህ ጉዳይ ህዝቡን እያነጋገረ ይገኛል። ይበልጥ ነገሩን ያካረረው ደግሞ፤ የጥበቃውን ተግባር ለመሸፈን ሲባል ፖሊስ “እርስ በርስ በጩቤ ተወጋግተው ነው የተገደለው” ማለቱ ነው። ተማሪዎቹ ግን “የለም። ገዳዩ ምሽት ላይ የተኮሰው የጥበቃ ሰራተኛ ነው” በማለት ላይ ናቸው። እንግዲህ የአስከሬን ምርመራ የሚደረግ ቢሆን፤ የአሟሟቱን ምክንያት ለማወቅ ይቻላል። እስከዚያው ግን ነገሩ እንዳወዛገበ ይቆያል – ማለት ነው።

የሟችን ፎቶ እና ተጨማሪ መረጃዎች ካገኘን ቆየት ብለን እናቀርባለን።

ኢትዮጵያዊው ቢንያም አሰፋ ከነቤተሰቡ ተገድሎ ተገኘ

(EMF) ከከተማው ራቅ ያለ ቦታ ነው የሚኖሩት – የ40 አመቱ ኢትዮጵያዊው ቢንያም አሰፋ፣ ጣልያናዊቷ ሚስቱ እና ልጆቹ። ድንገት በደረሰባቸው ጥቃት ባል እና ሚስቱ ከሶስት ወር ልጃቸው ጋር ሲገደሉ የአምስት አመት ልጃቸው ግን ተደብቃ ለማምለጥ ችላለች። ግድያው ከተፈጸመ በኋላ፤ የ5 አመቷ ልጅ ከተደበቀችበት ወጥታ ወደ ጎረቤት በመሄድ፤ “ቤተሰቦቼ ተጎድተዋል” ብላ ነገረቻቸው። ከዚያ በኋላ ነው ለፖሊስ የተደወለውና አሳዛኙ ድርጊት ይፋ የሆነው።
ቤን አሰፋ
በመጀመሪያ የሜሪላንድ ነዋሪ የሆኑት የቤን አሰፋ ቤተሰቦች የደረሰው አደጋ፤ የርስ በርስ ግጭት ሊሆን ይችላል፤ በሚል ብዙዎችን ሲያነጋግር ቆይቶ ነበር። ሆኖም ፖሊስ ዛሬ እንደገለጸው ከሆነ፤ ግድያው በሌላ ወገን የተፈጸመ ነው ተብሏል።

ፖሊስ የደረሰበትን የምርመራ ውጤት ይፋ አላደረገም። ይልቁንም የሟች (የቤን አሰፋ ሚስት) ቤተሰቦች ከጣልያን አገር ይገባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው። እነሱ ወደ አሜሪካ ከገቡ በኋላ ፖሊስ የደረሰበትን የምርመራ ውጤት ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።

ሁለቱም ባል እና ሚስቶች የባዮ ሜዲካል ህክምና ሳይንቲስቶች ነበሩ።

አዜብ ህወሀትን ለመልቀቅ ማመከቻ ማስገበቷ ተሰማ

የቀድሞዉ ጠ/ሚኒስቴር ባለቤት የሆነችዉና የሙስናዋ እመቤት በመባል የምትታወቀዉ አዜብ መስፍን ከወጣትነት እድሜዋ ጀምሮ የገለገለችዉን ህወሀት ፓርቲ በቃኝ ብላ ለመተዉ ለፓርቲዉ ማ/ኮሚቴ የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባቷን ዉስጥ አዋቂ ምንጮች አስታወቁ። ከባለቤቷ ከመለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ በፓርቲው የነበራት ተሰሚነትና የበላይነት እየተሸረሸረ በመምጣቱ፤ ከኤፈርት ሃላፊነቷ ሳትወድ በግድ በመነሳቷና እንዲሁም ጓግታለት የነበረው የአዲስ አበባ ከንቲባነት ስልጣን በማጣቷ፣ የተበሳጨችዉ አዜብ ተስፋ መቁረጥ መጀመሯ ፓርቲውን ለመልቀቋ ዋና ምክንያት እንደሆነ ምንጮቹ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ አዜብ የምትተማመንባቸዉ አብዛኞቹ የህወሀት ባለስልጣኖች ከስልጣን ተባርረዉ መታሰራቸዉና እንዲሁም በስብሃት ነጋ ቡድን እየተወሰደባት ያለው ፖለቲካዊ የበላይነት መቋቋም ስለተሳናት ከፓርቲው በግዜ መሰናበቷ ሌላ አማራጭ የሌለዉ መሆኑን በቅርብ የሚያዉቋት ሰዎች በመናገር ላይ ናቸዉ። የህወሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ በቅርብ ቀን ዉስጥ ተሰብስቦ የአዜብ መስፍንን ጥያቄ እልባት እንደሚሰጠዉ የጠቆሙት ምንጮች ከዚሁ ጋር አያይዘው ጥያቄው ተቀባይነት ካገኘ አዜብ በሲውዲን ወይም አሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ዉስጥ በገዛቸዉ መኖሪያ ቤት ለመኖር ጓዟን እንደምትጠቀልል አመልክተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ዘረኛዉና ለብዙ ሰላማዊ ዜጎች ሞት ተጠያቂ የሆነዉ ጄ/ል ሳሞራ የኑስ ከኢታማጆር ሹምነቱ ቦታ ተነስቶ በምትኩ በቅርቡ የሌፍቴናነት ጄኔራልነት ሹመት የተሰጠዉ ጄ/ል ዮሃንስ ገ/መስቀልን ሊተካ እንደሚችል አዲስ አበባ ዉስጥ የሚገኙ ወታደራዊ ቃል አቀባዮቻችን ገለጹ።

Friday, November 22, 2013

በኢትዮጵያ 38 ሚሊዮን ህዝብ የሚጸዳዳው ሜዳ ላይ ነው ተባለ

ህዳር ፲፫(አስ ሦስት )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ዩኒሴፍ ባወጣው ሪፖርት እንደማለከተው ይህን ችግር ለመቅረፍ የኮሚኒቲ አስተባባሪዎች ከፍተኛ  ሚና መጫወት አለባቸው።
ኤርትራ ውጭ ላይ መጸዳዳትን በማስቀረት ከፍተኛ ድል ማስመዝገቡዋን ዩኒሴፍ ጠቅሷል። በመላው ኤርትራ ውጤታማ ስራ በመሰራቱ አገሪቱ ውጭ ላይ መጸዳዳትን ያስቆመች አገር የሚል ሰርተፊኬት እንደሚሰጣት ድርጅቱ ገልጿል።
በአለም ላይ 34 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች ንጹህ የመጸዳጃ ቦታ የላቸውም።

መንግስት ከሳዑዲ ዓረቢያ የተመለሱ ኢትዮጵያዊያንን ባለሃብቶች እንዲረዱዋቸው በመማጸን ላይ ነው።

ህዳር ፲፫(አስራ ሦስት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሳዑዲ ዓረቢያ ኢትዮጵያዊያን በአስከፊ ሁኔታ እንዲባረሩ ከተደረገ በኃላ  መንግስት በሳዑዲ ስፖንሰርነት
ያጓጓዛቸውን ከ10ሺ በላይ ተመላሾች በካድሬዎች ማሰልጠኛ በሆነው የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በማሳረፍ ባለሃብቶች እንዲረዱዋቸው በመማጸን ላይ ነው።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለተመላሾቹ ማቋቋሚያ መንግስት 50 ሚሊየን ብር  መመደቡን፣ ገንዘቡ ሊያድግ እንደሚችልና በማቋቋም ረገድ ችግር እንደሌለ ከገለጹ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ባለሃብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ ከዚህ ቀደም ቃል የገቡትም ቃላቸውን እንዲፈጽሙ ትላንት በዩኒቨርሲቲው በተካሄደ የምሳ መርሃግብር ላይ ጠይቀዋል፡፡
አንዳንድ ባለሃብቶቹ በራሳቸው ተነሳሽነት ኮሚቴ በማቋቋም ለተመላሾቹ ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ያስታወሱት ዶክተሩ ሌሎችም ይህንን አርአያነት እንዲከተሉ በመምከር መንግሰት ከነዚህ ባለሃብቶች ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ተመላሾቹ ከህብረተሰቡ ጋር እንዳይገናኙ ተደርጎ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በከፍተኛ ጥበቃ ስር ሲሆኑ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው በቀላሉ ተመላሾችን መጎብኘት ባለመቻላቸው አንዳንድ ቤተሰቦች ቅሬታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡
አንድ በሳዑዲዓረቢያ እህት እንዳላት የጠቀሰች አስተያየት ሰጪ እህቴ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች ማወቅ
አልቻልኩም፡፡ መጥታ እንደሆነ ውጪ ጉዳይ መ/ቤትን ብጠይቅም መልስ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ገብቶ ለመፈለግም የሚፈቀድ ባለመሆኑ ግራ ተጋብቻለሁ ስትል ጭንቀትዋን ለአዲስአበባው ዘጋቢያችን ተናግራለች፡፡
ወደ አገር ቤት ለመመለስ በፈቃዳቸው ተመዝግበዋል የተባሉት ኢትዮጽያዊያን ቁጥር ከ23ሺ በላይ ሲሆን ይህ ቁጥር በሕገወጥነት ከተፈረጁት ከ100ሺ በላይ ኢትዮጽያዊያን ቁጥር አንጻር አነስተኛ ነው፡፡ እስከትላንትና በስቲያ ማምሻውን ድረስ 10ሺ707 ሰዎች መመለሳቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
በሳውዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አሁንም ችግሮች እየደረሱባቸው እንደሆነ ለኢሳት ገልጸዋል። የኢትዮጵያን ኢምባሲ አሰራር ክፉኛ የሚተቹት ኢትዮጵያውያኑ፣ ሁሉም ዜጋ ከችግራቸው እንዲታደጋቸው እየተማጹ ነው።
በተመሳሳይ ዜናም በሳውድ አረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚቃወሙ ሰልፎች ቀጥለዋል። ረቡእ እለት በኦክላንድ ኒውዚላንድ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ መደረጉን ከአስተባባሪዎች መካከል አንዱ የሆነው አቶ አንዱአለም ሀይለማርያም ገልጿል
በተመሳሳይም በፈረንሳይ ፓሪስ ደማቅ የተቃውሞ ሰልፍ መደረጉን አስተባባሪዋ     የገለጸች ሲሆን፣ የሳውዲ ኢምባሲ ሰራተኞች ጥያቄያቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። ኖቨምበር 29 ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ በሳውዲ ኢምባሲ ፊት ለፊት እንደሚካሄድ የገለጸችው ወ/ት ማክዳ፣ የፈረንሳይ የመገናኛ ብዙሀን ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በእለቱ ለመገኘት እንደሚፈልጉ መግለጻቸውንም ተናግራለች።

በሳዉዲ የኢትዮጵያውን ስቃይ ያስነሳዉ ተቃዉሞ

ሕጋዊ ፈቃድ በሌላቸው ኢትዮጵያውን ላይ የሚደርሰውን ችግር እና ጥቃት በመቃወም በተለያዩ ሀገራት ሰሞኑን የተቃውሞ ሰልፍ ሲካሄዱ ሰንብተዋል። ዛሬም በበርሊን እና በፓሪስ የሚገኙ ዜጎች አደባባይ ወጥተዋል።
Titel: Äthiopien - Demonstration in Paris 
Thema: Äthiopien - Protest gegen Saudi Arabiens Aktion gegen Einwanderer aus Äthiopien 
Autor/Copyright: Haimanot Tiruneh Torode (Paris Korri.) 21.11.2013 
Schlagworte:Äthiopien, Demonstration, Addis Abeba, Saudi Arabien, Einwanderer, Paris
ሳዉድ አረቢያ በሚገኙ ዜጎች ላይ የሚፈፀመዉን ጥቃት በመቃወም ከመላ ጀርመን የተሰባሰቡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ዛሬ በበርሊን ከተማ ሰልፍ አካሄዱሰልፈኞቹ የሳውዲ መንግሥት የወሰደውን ርምጃ የሚያወግዙ መፈክሮች በማሰማት ርምጃው እንዲያበቃ ጠይቀዋል። ከሰልፉ አዘጋጂዎች መካከል አንዱ የሆኑትን አቶ በላይነህ ተሾመን ስለሰልፉ በስልክ አነጋግሬያቸዋለሁ። የፓሪሱንም ሰልፍ ወኪላችን ሀይማኖት ጥሩነህ ተከታትላዋለች።
ሃይማኖት ጥሩነህ
አርያም ተክሌ

ተገን ጠያቂዎች እና የጀርመን የስለላ መስሪያ ቤት

ጀርመን እንድትቀበላቸው ያመለከቱ ተገን ጠያቂዎች ማመልከቻቸው ተቀባይነት እስኪያገኝ ረዥም ጊዜ በሚወስድ ሂደት ውስጥ ማለፍ አለባቸው ። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌደራል ጀርመን የውጭ ዜጎችና የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤት ባልደረቦች አመልካቾቹን ስለ ሃገራቸው ሁኔታ ና የፖለቲካ ክትትል ይደረግባቸው እንደሆነ ይጠይቋቸዋል ።
Dolmetscher Ahmed Yasser spricht am 10.10.2013 in einem Büro in der Außenstelle des Bundesamts für Migration und Flüchtlinge in Berlin-Spandau mit Asylbewerbern aus Syrien . Foto: Bernd von Jutrczenka/dpa
Beratung für Asylbewerber
በምን ዓይነት መንገድ ወደ ጀርመን ሊመጡ እንደቻሉም ያጣራሉ ። ይህ የተለመደና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚታወቅ አሠራር ነው ። ይሁንና በዚህ ሂደት የጀርመን ህዝብ እንኳን የማያውቃቸው ሌሎች ባለሥልጣናት በዚህ ሂደት ውስጥ እንደሚሳተፉ የዶቼቬለው የቮልፍጋንግ ዲክ ዘገባ ያስረዳል ።

መቀመጫውን በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ያደረገው የውጭ ዜጎችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የሚቆጣጠረው የፊደራል ጀርመን መሥሪያ ቤት በይፋ በመራሄ መንግሥት ጽህፈት ቤት ስር የሚገኝ ተቋም ነው ። ተቋሙ እጎአ ከ 1958 ዓም አንስቶ ለጀርመናውያን ደህንነት አስፈላጊ የሆኑ ለጀርመን የስለላ መስሪያ ቤት የሚጠቅሙ መረጃዎችን ይሰበስባል ። ዙድ ዶይቸ ሳይቱንግ የተባለው ጋዜጣና NDR የተባለው የጀርመን ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች በጋራ እንደዘገቡት የዚህ ተቋም የሥራ ባልደረቦች ተገን ጠያቂዎች በሃገራቸው የአሸባሪ ድርጅቶች አባላትን ያውቁ እንደሆነ ወይም ደግሞ የጦር መሣሪያ
Rechtsanwalt Pfaff.
Er ist spezialisiert auf alle Rechtsfragen, die Unionsbürger und Ausländer betreffen, unter anderem: 
EU-Migrations- und Ausländerrecht 
Staatsangehörigkeitsrecht 
Asyl- und Flüchtlingsrecht 
Arbeitsgenehmigungsrecht 
Berufszulassungsrecht 
Strafverteidigung mit ausländerrechtlichem Bezug
Rechte geklärt
ፋፍ
ስለሚደበቁባቸው ቦታዎች የሚያውቁት እንዳለ ይጠይቁዋቸዋል ። በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ እነዚህ መረጃዎች ለጀርመን የስለላ መስሪያ ቤት ተላልፈው አሸባሪዎችን በሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ለመግደል ሊውሉ ይችላል ። ጀርመን ውስጥ ለተገን ጠያቂዎች ጥብቅና የሚቆሙ በርካታ ጠበቆች እነዚህን ባለሥልጣናት ያውቃሉ ። ቪክቶር ፋፍ ፍራንክፈርት ውስጥ ከ40 ዓመታት በላይ የተገን ጠያቂዎች ጠበቃ በመሆን ሰርተዋል ። ከበርሊኖቹ ባለሥልጣናት ጋርም በግል ተነጋግረዋል ። ፋፍ እንደሚሉት ሠራተኞቹ ትሁትና ግልፅ ናቸው ። ከፌደራል ጀርመን የስለላ መስሪያ ቤት ጋር ግንኙነት እንደሌላቸውም ነው የሚናገሩት ።

«ከፌደራል የስለላ መስሪያ ቤት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ነው የሰማሁት ። ለመራሄ መንግሥት ጽህፈት ቤት ዘገባ እንደሚያቀርቡ ና እዚያ የሚገኙትም ለጽህፈት ቤቱ ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው የሚያስቧቸውን አንዳንድ መረጃዎች ለማግኘት መሆኑን ነው በቀጥታ የተነገረኝ ። »
የጀርመን የስለላ መስሪያ ቤትም በመራሄ መንግሥቱት ቢሮ ስር ነው ። ፋፍ እንደሚሉት በ40 ዓመት የአገልግሎት ዘመናቸው ቃለ መጠይቅ በመደረጌ ችግር ገጥሞኛል ያላቸው ተገን ጠያቂ አላጋጠማቸውም ። በተቃራኒው ፋፍ አንዳንዴ የተገን
Asylsuchende vor dem Gebäude der zentralen Aufnahmestelle für Asylbewerber in Berlin.ተገን ጠያቂዎች በበርሊን
ጠያቂዎች ማመልከቻዎች አፋጣኝ መልስ እንዲያገኙ የመስሪያ ቤቱን ባልደረቦች ያነጋግራሉ ። ደንበኞች ለዚህ መሥሪያ ለስለላው መሥሪያ ቤት ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን መስጠት ከቻሉ በጥቂት ቀናት ውስጥ የመኖሪያ ፈቃድ ያገኛሉ ። እንደዚህ ዓይነት ስምምነቶች ላይ የሚደረሰው ግን ሁሌም አይደለም ። መረጃዎችን ሳያሳውቁ መሰብሰብም ሊኖር ይችላል ። በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ አደገኛ ሊሆንም ይችላል ይላሉ ።
« አደገኛ ሊሆን የሚችለው የውጭ የስለላ ድርጅቶች ተገን ጠያቂዎቹ የሚሰጡትን መረጃ ማወቅ ከፈለጉ ነው ። ይህ ግን ሁሌም የሚሆን አይደለም ። »
ፋፍ እንደሚሉት ይህ የሚደረግ ከሆነ ተገን ጠያቂዎች መጠቀሚያ እንደሆኑ ሊሰማቸው ይችላል ። እነዚህን ስለመሳሰሉ ጉዳዮች መስማታቸውን የሚናገሩት ፋፍ በርሳቸው እምነት ይህን መሰሉ አሰራር አደገኛ ነው ። ምክንያቱም በርሳቸው አስተያየት አሸባሪዎች በክህደት የሚጠረጥሩዋቸውን በዚያው ተገን በጠየቁባቸው ቦታዎች ሊበቀሉዋቸው እና ሊገድሏቸውም ይችላሉ ።
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ

የተቃውሞ ሰልፍ በእሥራኤል

ሳዉድ አረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያን ላይ የሚፈፀመዉን ጥቃት በመቃወም ሰሞኑን በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያካሂዱ ሰንብተዋል።
Foreign workers wait for a taxi as they leave the Manfuhah neighbourhood of the Saudi capital Riyadh on November 10, 2013, after two people have been killed in clashes between Saudi and other foreign residents the previous day, according to the Saudi police. On November 4, the authorities began rounding up thousands of illegal foreign workers following the expiry of a final amnesty for them to formalise their status. AFP PHOTO/FAYEZ NURELDINE (Photo credit should read FAYEZ NURELDINE/AFP/Getty Images)
ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከመላው እሥራኤል የተሰበሰቡ በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን መገኘታቸውን ሰልፉን የተከታተለው የኃይፋ ዘጋቢያችን ግርማው አሻግሬ ገልጾልናል። የዛሬውን ሰልፍ አስመልክቶ ያካሄድነውን ቃለ ምልልስ ከታች ያገኙታል።
ግርማው አሻግሬ
ልደት አበበ

የኢትዮ-ኤርትራ ችግር መፍትሄ፣ ድንበር ማስመር ሳይሆን ድንበር ማፍረስ ነው

ኤርትራ ራሷን እያወደመች ነው የኢትዮጵያ ትምህርት ችግሮች ቋንቋና ያለ እቅደ መስፋፋት ናቸው
ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ በስዊድን አገር በኡፕስላ ዩኒቨርሲቲ የዘመናዊ ታሪክ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ በኢትዮጵያ ትምህርት ላይ ከፍተኛ ምርምሮችን ያደረጉ፣ በመስኩም የታወቁ ምሁር ሲሆኑ ከከዓምናው ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ተጋባዥ ፕሮፌሰር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ1947 በአስመራ ከተማ ተወልደው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአስመራ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጅማ ተከታትለዋል፡፡ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከአስመራ ዩኒቨርሲቲ በህግ አግኝተዋል፡፡ ከ1972 እስከ 1974 በአስመራ ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩት ፕሮፌሰር ተከስተ፤ በለንደን ዩኒቨርሰቲ ከ“ስኩል ኦፍ ኦሪየንታል ኤንድ አፍሪካ ስተዲስ” ማስተርስ ድግሪ ያላቸውን ያገኙ ሲሆን ዶክትሬታቸውን ከስዊድን አገር ኡፕስላ ዩኒቨርስቲ በታሪክ ትምህርት ሰርተዋል፡፡ የኤርትራን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ይገልፁታል? እኔ የኤርትራን ጉዳይ መከታተል ካቆምኩ አስራ ሶስት አመት ሊሆነኝ ነው፡፡ ምክንያቱም ልለው የምችለውን ሁሉ ብያለሁ፡፡
“Brothers at war” በሚል ከአንድ የኖርዌይ ተወላጅ ጋር በመሆን በፃፍነው መጽሐፍ፤ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርትነት የወንድማማችነት ጦርነት ነው፤ ችግሩን ለመፍታት ሁለቱ አገሮች ወንድማማችነታቸውን ማመን አለባቸው ብለን ደምድመናል፡፡ ከዛ በኋላ ምንም ሠላም አልተገኘም፤ በኔ አስተያየት የሚገኝም አይመስለኝም፡፡ እስከአሁን በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ወንድማማችነቱን ማመን ላይ አልተደረሰም፡፡ የሁለቱ አገራት የወደፊት ግንኙነት ምን የሚሆን ይመስልዎታል? የኤርትራን ጉዳይ ማጥናት የተውኩት ተገድጄ አይደለም፡፡ በአንድ በኩል በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ ነገሮች በጣም በጎ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ለውጥ እየተካሄደ ነው የሚል አቋም ስላለኝ ሲሆን በሌላ በኩል የኤርትራ ጉዳይ አልቆለታል ብዬ ስላመንኩ ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ኤርትራ ራሷን በራሷ እያወደመች ነው፡፡ ኤርትራ ምንም ተስፋ የላትም ብዬ አምናለሁ፡፡
ወደ ጥያቄሽ ስመለስ… የኤርትራና የኢትዮጵያ ሁኔታ እንዴት ይቀጥላል ለሚለው በኔ አስተያየት ከዚህ በኋላ ጦርነት አይካሄድም። ኤርትራ ግን የሶማሊያን አይነት የምትሆንበት፣ በአንድ ልትመራ ወደማትችልበት ደረጃ ልትደርስ ትችላለች ብዬ አምናለሁ፡፡ ከኢሳያስ አፈወርቂ በኋላ ኤርትራ ሶማሊያን ትሆናለች በሚል የሚሰጡ አስተያየቶችን ይቀበላሉ ማለት ነው? አዎ፡፡ ኢሳያስ እስካለ እሱ የፈጠረው ስርዓት ይቀጥላል፡፡
የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አቋም እና የኢትዮጵያ መንግስት የያዙት አቋምም ለዚህ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ከኢሳያስ በኋላ ግን የኢኮኖሚ ችግር ብቻ ሳይሆን የብሔር ግጭቶች አሉ፡፡ ቆላማው የኤርትራ ክፍል የራሱ አጀንዳ አለው፤ ደገኞቹ ደግሞ እርስበርሳቸው በጣም የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ ይህን መያዝ የሚችለው ኢሳያስ ብቻ ነው፡፡ ከሱ በኋላ አገሪቱን አንድ አድርጐ ወደፊት ሊያራምድ የሚቻል ይመጣል ብዬ አላምንም፡፡ የኤርትራ ጥያቄ ለምርጫ በቀረበበት ወቅት ከነበሩ አማራጮች ዋነኞቹ፤ መገንጠል፣ በፌዴሬሽን መቆየት እና አንድነት የሚሉ ነበሩ፡፡ በውድም ይሁን በግድ ሁሉም አማራጮች ተግባራዊ ሆነዋል፡፡ ኤርትራ ከተገነጠለች 23 አመት ሊሆናት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አንድነት የሚለው አቋም ቅሪት አለ ወይስ ሙሉ በሙሉ ተሸርሽሯል? የደጋው ኤርትራ ባህል በመሠረቱ ኢትዮጵያዊነቱን እንደያዘ ነው፡፡ ኢሳያስ ስልጣን እንደያዘ በሶስተኛ አመቱ ሆላንድ መጥቶ ባደረገው ውይይት፤ እኔም እድሉን አግኝቼ ሰምቼዋለሁ፡፡ እኛ ሠላሳ አመት ሙሉ ታግለን ብዙ ሰው ሞቶብን፣ ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ የኤርትራ ህዝብ የከፈልነውን መስዋዕትነት ረስቶ ከኢትዮጵያ ጋር ወዲያ ወዲህ ይላል ብሎ ተናገረ፡፡ ኤርትራ ነፃ ከወጣች ጊዜ ጀምሮ እስከ ጦርነቱ ድረስ የኤርትራ ህዝብ ከኢትዮጵያ ተለይተናል የሚል ብዙ ስሜት አልነበረውም፡፡ ደርግ መሸነፉ ላይ ነበር እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር የመለየቱ ብዙ ግንዛቤ አልነበረውም፡፡ ጦርነቱ ሲጀመር ስሜቱ መቀዛቀዙን መናገር ይችላል፡፡
ሌላው በደጋው ኤርትራ ያለው ትግርኛ ተናጋሪ ከጣሊያን ጊዜ የጀመረ የገዢና የተገዢ ግንኙነት ነበረው፡፡ እኛን ጣልያን ነው የገዛን በሚል፣ ትግራይ ያሉትን ትግሪኛ ተናጋሪዎች “እናንተ ከአዲግራት፣ ከመቀሌ፣ ከአድዋ የምትመጡ…” የሚል ነገር ነበር፡፡ ከጦርነቱ በኋላ የትግራይ ህዝብ የራሱን ማንነት ኢኮኖሚ በማሻሻል ላይ ስለሚገኝ በነዚህ ሁለት ትግሪኛ ተናጋሪዎች መካከል ያለው ፉክክር ማን ትግሬን ይወክላል የሚል ነው፡፡ ይህ ለጊዜው ችግር ሊፈጥር ይችላል፤ ግን እኔ እስከምረዳው ድረስ ኢትዮጵያዊነት ስሜት፣ ባህል፣ አስተሳሰብ አለ የምንል ከሆነ በደጋማው ኤርትራ አሁንም አለ። ከዛ ደግሞ ከአፋር ጋር ያለውን ትስስር ማየት ይቻላል፡፡ በኤርትራ ያሉ ቢለኖች አገዎች እንደሆኑ አይጠራጠሩም፤ አሁን ባለው ሁኔታ ምንም ማድረግ አይችሉም፡፡ ኩናማዎችንም ካየሽ ተመሳሳይ ነው፡፡ ወቅታዊውን የአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ እንዴት ይገልፁታል? በአፍሪካ ቀንድ የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያን ካየን፣ ለሁለቱም የሚጠቅማቸው የሶማሊያ አንድ መሆን ነው፡፡ አሁን ያለው ሁለት ሶማሊያ በኔ አስተያየት ረጅም የሚጓዝ አይደለም፡፡ ከጥቅም አንፃር ካየነውም፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሶማሊያ አይጠቅምም፡፡ በኤርትራና በኢትዮጵያ በኩል ስናየው፣ ኤርትራ የምትፈልገው ድንበር ሊኖር አይችልም፡፡ ይህን ደግሞ ሁለቱም አገሮች ያውቁታል፡፡
የኤርትራ ሁኔታ ከኢሳያስ በኋላ አዲስ መልክ ይይዛል፡፡ በአዲሱ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሚና ምን ሊሆን እንደሚችል በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ የኢትዮጵያን ጥቅም ለመጪው ሁለት መቶ ሶስት መቶ አመት ሊያራምድ የሚችል ሆኖ መቀረፅ ይገባዋል፡፡ የኢትዮጵያን የፌደራል አወቃቀር እንዴት ያዩታል? አወቃቀሩ በፌደራል መሆኑ ጥሩ ነው፡፡ በብሔር መሆኑ ግን መጥፎ ነው፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ያደረገው ትልቁ ስህተት ነው፡፡ ፌደራል ስርአት በፊትም የነበረ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የኋላ ታሪክ ካየሽ የፌደራል አወቃቀር አዲስ አይደለም፡፡ ንጉሠ ነገስት ስንል እኮ ንጉሶች አሉ፡፡ ከበላያቸው ንጉሠነገስት አለ ማለት ነው፡፡ አካባቢያዊ ፌደራሊዝም ነበር፡፡ የኤርትራ ህዝብ አሁን ያሉበትን የነፃነት ሁኔታ ከቀድሞው ጋር ሲያስተያዩት ምን ትርጉም ይሰጥዎታል? እኔ እኮ በመጀመሪያም ኤርትራውያኖች ከማን ነው የሚገነጠሉት የሚል አቋም ነው ያለኝ። ማነው ከማን የሚገነጠለው? የደቡብ ወይም የኦሮሞ ህዝቦች እንገነጠላለን ቢሉ ኖሮ ምክንያት ነበራቸው፡፡ የኤርትራ የነፃነት ጥያቄ በተነሳበት ወቅት ኤርትራውያኑና ከላይ የጠቀስኳቸው ህዝቦች በኢትዮጵያ ውስጥ ያገኙትን እድል (Comparative advantage) ስናይ፣ ኤርትራውያኑ በጣም ተጠቃሚ ነበሩ፡፡ (በጣሊያን፣ በእንግሊዝ፣ በፌዴሬሽኑ ዘመን) በ1960ዎቹ የአዲስ አበባ ሀብታሞቹ እነሱ ነበሩ። በትምህርት መስክ ሃያ አምስት በመቶ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች ኤርትራውያን ነበሩ። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችንም ካየሽ 25 በመቶ የሚሆኑት ኤርትራውያን ነበሩ፡፡ ከተማረው ሰላሳ አምስት በመቶው ክፍል ኤርትራውያን ነበሩ፡፡
ይህን እድል ያገኙ ሰዎች ከኢትዮጵያ እንገነጠላለን ሲሉ ምክንያቱን ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ምንም ምክንያት አልነበራቸው፡፡ ለነፃነት የተደረገው እንቅስቃሴ 30 አመት ቢፈጅም ስልሳ ሺህ ሰው ቢሞትም በቂ ምክንያት አልነበረውም። የኔ ጥናት የጣልያን ቅኝ አገዛዝ በኤርትራ የሚል ነው። እንዲገባኝ ሞክሬያለሁ፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል እንዳለበት የሚያሳይ ምንም ነጥብ አላገኘሁም፡፡ ነፃ ወጣን አሉ፡፡ ሁለት አመት ሳይቆዩ እኛ የታገልነው ለነፃነት ብቻ አይደለም፤ የኛ ዕድል ከኢትዮጵያ ጋር ነው ማለት ጀመሩ፡፡ ይህን የሚሉት ተገደው ነው፤ ምክንያቱም የኤርትራ ኢኮኖሚ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ በራሱ ሊቆም የሚችል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ልዩ አገር ነች፤ ነፃነቷን ጠብቃ የቆየች አገር ናት፡፡ የኤርትራ ቴሌቪዥን በቅርቡ “Ancient Eritreans” (የጥንት ኤርትራውያን) የሚል ዶክመንተሪ አቅርቦ ነበር፡፡ አይተውታል? (ረጅም ሳቅ) አላየሁትም፡፡ ግን ምንም አዲስ ነገር አይፈጥርም፡፡ ወጣቶቹ ኢትዮጵያን አያውቋትም፤ ነገር ግን መንግስት የሚያደርገው አንድ ነገር ነው፣ ህዝቡ የሚያስበው ሌላ ነገር ነው፡፡
መንግስት በቴሌቪዥን የሚየሳየውና ህዝቡ የሚመኘውና የሚያስበው ሌላ ነው፡፡ እስከቅርብ ጊዜ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ ብትለያይም በድብቅ ወጣቶቻቸውን ለትምህርት ወደ ቤጌምድር (ጐንደር) ይልኩ ነበር፡፡ የኢሳያስን መረጃ በማየት ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ ኤርትራዊውን ማን አገኘው፡፡ የተለየን ነን የሚል አቋም የት ነው ያለው? በኤርትራ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ምን ያህል አለ ለሚለው መልስ ለማግኘት ድንበሩ መፍረስ አለበት፡፡ ለሁለቱ ህዝቦች መፍትሔ የሚሆነው በኤርትራ በኩል እየተጠየቀ ያለው ድንበር ሲሰመር ሳይሆን ከደርግ ሽንፈት በኋላ የተሰመረው መስመር ሲፈርስ ነው፡፡ ትናንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቋንቋ፣ እውቀት እና የጋራ ህልውና በሚል የውይይት መነሻ ጥናት አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ትምህርት ላይ ጥናቶችን አድርገዋል፡፡ ዕይታዋ ምንድን ነው? ዋና ጥናቴ እሱ ነው፡፡ ትምህርት በጣም ተዳክሟል፡፡ የተዳከመው በሁለት ምክንያት ነው ብዬ አስቀምጣለሁ፡፡ አንዱ ያለዕቅድ መስፋፋቱ ነው። የሚፈለጉ ህንፃዎች፣ አስተማሪዎች፣ መፃሕፍቶች ሳይሟሉ እንዲሁ ሠፍቷል፡፡ ሌላው ዋነኛ ምክንያት የቋንቋ ጉዳይ ነው፡፡ እንግሊዝኛ ቋንቋ አያዋጣንም፡፡ በራስ ቋንቋ መማር የህልውናና የመበት ጥያቄ ነው፡፡ ዜግነትዎ ከየትኛው ነው? ስዊድናዊ ነኝ፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ፣ የዜጎችን ሰቆቃ እና በደል ችላ ማለት ከግፈኞች ጋር እንደመተባበበር ይቆጠራል!!

November 22, 2013
ሰማያዊ ፓርቲ በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎቻችን ላይ የሳውዲ መንግስት እያደረሰ ያለውን እስራት፣ ስቃይ እና ግድያ በመቃወም እና ህይወታቸው ላለፈ፣ ለተደበደቡ እንዲሁም የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ህዝቡ ሃዘኑን እንዲገልጽ በመጪው እሁድ በሚደረገው ታላቁ ሩጫ ላይ የሚሮጡ ተሳታፊዎች ጥቁር ሪቫን አድርገው እንዲሮጡ ጥሪ ማስተላለፉ የሚታወቅ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የታላቁ ሩጫ አስተባባሪዎች ይህንን ጥሪ እንደሚቃወሙት እና በፕሮግራሙም ላይ ጥቁር ሪቫን ያሰረ ተሳታፊን እንደተሳታፊ እንደማይቆጥሩ መናገራቸው ፓርቲያችንን እጅግ አሳዝኖታል፡፡ ፓርቲያችን ይህንን ጥሪ ሲያስተላልፍ አላማው ፍጹም ፖለቲካዊ አንድምታ የሌለው ሲሆን ጥያቄውም በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እና ግድያ እንዲቆም እና ፍትሃዊ እርምጃም እንዲወሰድ ለመጠየቅ ብቻ እና ብቻ እንጂ ሌላ አላማ እንደሌለው እየታወቀ የታላቁ ሩጫ አስተባባሪዎች ግን ጉዳዩ ከፖለቲካ ጋር ለማያያዝ መሞከራቸው የሚያስተዛዝብ እና ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፡፡

ስፖርት ሰላማዊ ነገር የሚሰበክበት እንዲሁም እኩይ ተግባራት የሚወገዙበት መድረክ ነው፡፡ በአለማችን ላይ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ አሰቃቂ ሰው ሰራሽ አደጋዎች በተለያዩ ስፖርታዊ ዝግጅቶች ላይ ሲወገዙ እንዲሁም ለሰለባዎች ሃዘን የመግለጽ ስነ ስርዓትና የህሊና ጸሎት ሲደረግ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ታዲያ በጠራራ ፀሀይ በአደባባይ እናት ልጆችዋ ፊት እንዲሁም ሴት ልጅ ቤተሰቦችዋ ፊት ስትደፈር ከማየት የዘለለ ምን እኩይ ተግባርስ ሊኖር ነው? ታዲያ ስፖርት ይህንን ካላወገዘ ምንን ሊያወግዝ ነው?
በመጨረሻም የታላቁ ሩጫ አስተባባሪዎች የፓርቲውን ጥሪ መቃወማቸው ፓርቲያችንን ያሳዘነ እና ያስቆጣ መሆኑን እየገለጽን አሁንም ፓርቲያችን በድጋሜ በዝግጅቱ ላይ ተሳታፊዎች ጥቁር ሪቫን አድርገው እንዲሮጡ እየጠየቀ ጥቁር ሪቫኖችን ማግኘት ለማትችሉ በሰማያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ተገኝታችሁ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እናስታውቃለን፡፡

ክብር ለዜጎቻችን ይሁን!!

Thursday, November 21, 2013

የስዊድን የጦር ፍርድ-ቤት አቃቢ-ህግ በኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ወሰነ፡

ህዳር ፲፩(አስ አንድ )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-የጦር ፍርድ ቤቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በቅርቡ በኦጋዴን የተፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በተመለከተ፣ የክልሉ የወጣቶች ሊቀመንበርና የፕሬዚዳንቱ የግል ዌብሳት ማኔጀር እና አማካሪ የነበረው ወጣት አብዱላሂ ሁሴን በኦጋዴን የጦር ወንጀልና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መፈጸሙን የሚያሳይ ማስረጃ ለፍርድ ቤቱ አቃቢ ህግ ማቅረቡን ተከትሎ ነው።
የጦር ፍርድ ቤቱ ዋና አቃቢ ህግ ክሪስተር ፒተርሰን በ10 የኦጋዴን ክልል ባለስልጣናትና የመከላከያ አዛዦች ላይ የቅድመ መርምራ እንዲካሄድ የወሰኑ ሲሆን ከተመርማሪዎች መካከል የክልሉ ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሀመድ ኡመርና ምክትሉ አብዱላሂ ዌረር እንደሚገኙበት ወጣት አብዱላሂ ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ገልጿል።
ውሳኔው ለኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ድል ነው ያለው አብዱላሂ፣ ምርመራ መጀመሩንም ገልጿል።
ምርመራው እንደተጠናቀቀ ሁለት አማራጮች ሊኖሩ እንደሚችል ተናግሯል። አንደኛው አማራጭ ጉዳዩን በስዊድን የጦር ፍርድ ቤት ማየት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ወደ አለማቀፉ የወንጀል ፍርድቤት መላክ ነው።
በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መረጃዎችን በመላክ እንዲሁም የምስክርነት ቃላቸውን በመስጠት እንዲተባበሩ ወጣት አብዲ ገልጿል።
በሌላ በኩል በተለያዩ የአለም ክፍሎች  የሚገኙና በኢትዮጵያ መንግስት በደል  የደረሰባቸው ሰዎች መረጃዎቻቸውን እንዲሁም የምስክርነት ቃል ለመስጠት የሚፈልጉ የስልክ ቁጥራቸውን በ0031 68 71 54 530 ወይም በ editor@ethsat.com ቢልኩ  ኢሳት ጉዳዩን በቅርብ ከሚከታተሉ ወገኖች ጋር የሚያገናኛቸው መሆኑን ለመግልጽ ይወዳል።