Wednesday, August 23, 2017

ወያኔ እስካልተወገደ ድረስ ህዝባችን እረፍት አይኖረውም!!!

ባለፉት 26 ዓመታት በወያኔ ዘረኛ፣ ከፋፋይ፣ አፋኝና ገዳይ ፖሊሲ ስቃይ ያልደረሰበት ዜጋ አለ ከተባለ ያ ግለሰብ የአገዛዙ አባል መሆን አለበት። በወያኔ ፖሊሲ ህዝባችን ተገድሏል፤ አካለ ጎደሎ ሆኗል፣ ታስሯል፤ ተገርፏል፤ ተሰዷል። ህዝባችን በምድር ላይ ያለውን ስቃይና መከራ ሁሉ ተቀብሏል። ከዛሬ ነገ ይሻሻል ብሎ ተስፋ ሲያደርግ፣ ስቃዩ እየጨመረ፣ የህዝቡ የመኖር ህልውና አደጋ ውስጥ እየወደቀ፣ እንደ ህዝብ በጅምላ የሚጠፋበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ጥቂቶች የህወሃት ሽፍቶችና ግብረአበሮቹ፣ የማይጠረቃውን ቋታቸውን ለመሙላት ሲሉ ህዝቡን በአጥንቱ አስቀርተው አገሩን ሁሉ ለመውረስ ላይ እና ታች እያሉ ነው።

የመንግስት ሰራተኛው በአንድ ለአምስት ተጠርንፎ በኑሮ ውድነት ሲጠበስ ቆይቶ አሁን ግን የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ትግል ማድረግ ጀምሯል። አርሶአደሩ ሞፈሩንና ቀንበሩን እየሰቀለ፣ ጎተራውን አራቁቶ፣ ጥሪቱን አሟጦ ረሱን ለመከላከል እየተጋደለ ነው። “በብልጽግና ላይ ብልጽግናን አጎናጸፍነው” እየተባለ በእየለቱ የሚዘመርለት አብዛኛው ነጋዴ ደግሞ፣ ጥቂቶች ለበሉት እሱ እዳ እንዲከፍል በመታዘዙ ፣ “ በቃኝ” ብሎ ትግሉን ለኩሷል። ወያኔ አስፈራርቶ ለመግዛት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወደ ጎን በመተው፣ ህዝባችን ከአቅጣጫው ትግሉን ማቀጣጠሉ ለወያኔ ያለውን ንቀት ብቻ ሳይሆን፣ ከእንግዲህ ወያኔንና ሰንኮፉን በአገራችን ምድር ለማየት እንደማይፈልግ ማሳያ ሆኖአል። ኩሩውና ጀግናው ህዝባችን ለወያኔ ያለውን ንቀት፣ የወያኔን የተጣመመ ህግ አልቀበልም ብሎ በማደም ብቻ ሳይሆን፣ የወያኔን የጥይት ጥቃት በመመከት ጭምር እያሳየ ነው። ጥይትና አፈና የማያንበረክከው ህዝባችን፣ ወያኔን ስልታዊ በሆነ ትግሉ ወደ ማይመለስበት መቃብር እየከተተው ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝባችን እየተገበራቸው ያለው የትግል ስልቶች፣ ነጻነት ወዳዱን ህዝብ ሁሉ የሚያኮራ፣ ገዳዮችን የወያኔ ጀሌዎች ደግሞ የሚያስበረግግ ነው።

ወያኔ በአምሳሉ የፈጠረው የአየር ሃይል ሲፈተሽ

አየር ሃይል ለአንዲት አገር መከላከያ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ የላቀ ነው። በዚህም አገራችን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ የራሷን የአቪየሽን ተቋም በመመስረት ግንባር ቀደምት ነች።ወይንም ነበረች ሳይሻል አይቀርም።ያኔ የአፍሪካ አገራት በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ወድቀው በሚማቅቁበት ዘመን ኢትዮጵያ የራሷ ጠንካራ የአየር ሃይል ተቋም ነበራት።በኢትዮጵያ የአቪየሽን ታሪክ የሚጀምረው በ1921 ዓ/ም እንደጀመረ ታሪክ ይነግረናል።የኢትዮጲያን አየር ሃይል በዘመናዊ መልኩ ማደራጀት የተጀመረው ደግሞ በ1936 ዓ/ም ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ በኋላ ነው። አየር ሃይሉ ከሌሎች የሃገሪቱ መከላከያ ተቋማት ጋር በመጣመር የሃገሪቱን ዳር ድንበርና ሉአላዊነትን ለማስከበር በተደረጉ ተጋድሎዎች  እስከደርግ ወድቀት ድረስ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በተለይም የኢትዮጵያን የአየር ክልል በማስከበር ረገድ የማይተካ ሚና ነበረው።

በ1969 ዓ/ም የሱማሊያው መሪ ጀነራል ዚያድ ባሬ የኦጋዴንን መሬት በመጠቅለል ታላቋን ሶማሊያ ለመመስረት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት የኢትዮጵያ የአየር ሃይል የዚያድባሬን ህልም ወደቅዠት በመቀየር አኩሪ ታራክ በመስራት ረገድ የፊታውራሪውን ድርሻ ወስዷል።እናም በታጠቀው ዘመናዊ መሳሪያ እጅግ የሚልቀውን የሱማሊያውን የአየር ሃይል ተቋም ለምን ጉድ ባሰኘ መልኩ ድባቅ መትቶቷል።በወቅቱ ኢትዮጵያ ለጦርነቱ በዋናነት ያሰለፈቻቸው F 5E የተባሉ የአየር ላየር ተዋጊ ጀቶች  በቁጥር ከ8 የማይበልጡ ሲሆኑ እንዲሁም ቁጥራቸው ከ—– የማይበልጡ F 5A ቦምብ ጣይ ጀቶች ብቻ ነበሯት።የዚያድ ባሬው የሱማሊያ አየር ሃይል በበኩሉ በመቶዎች በሚቆጠሩ በጊዜው እጅግ ዘመናዊ በሆኑ ሶቪያት ሰራሽ MIG 19 እና MG-21 በተባሉ ተዋጊና ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች እስከ አፍንጫው የታጠቀ ነበር።ኢትዮጲያ ለጦርነቱ ካሰለፈቻቸው የጦር ጀቶች አንጻር ሲመዘን የሶማሊያው አየር ሃይል በዘመናዊነቱም ሆነ በቴክኖሎጂ ጥራቱ የነበረው ብልጫ እጅግ የላቀና ለውድድርም የማይቀርብ ነበረ። ታዲያ በወቅቱ እንዴት የኢትዮጵያው የአየር ሃይል እጅግ የሚልቀውን የሱማሌውን የአየር ሃይል ተቋም  በልጦ ተገኘ? ጥያቄው ይሄ ነው።

ትልቁ ሰውዬና የጅጅጋ ሕዝብ ሰቆቃ

ከሙክታር ኦማር የእንግሊዝኛ መጣጥፍ በግርድፉ የተተረጎመ

በድህረ ቅኝ ግዛት ዘመኗ አፍሪካ የገባችበትን የአስተዳደር ብልሹነትና የፖለቲካ ቀውስ አስመልክቶ  እንደ ካሜሩናዊው የማህበረሰብ ጥናት ተመራማሪ አቺሌ ሜምቤ  በትክክል የተረዳና የጻፈ ምሁር  ጥቂት ነው። ” የብልግና ውበት” በተባለው ድንቅ ጥናታዊ ጽሁፉ የነጮቹን ጌቶቻቸውን ቦታ ተረክበው አፍሪካን እየተጫወቱባት ያሉት “ጌቶቹ አምባገነን መሪዎቻችንና ባለስልጣናቱ” የፈጠሩት ስርዓት ጥቂቶቹን ጨቋኞችና ብዙሃኑን ተጨቋኝ ህዝብ በአንድ ላይ ጠፍንጎና አቆላልፎ አስከፊ ወደሆነ የስብዓና ዝቅጠትና ሕይወት አልባ ወደሆነ የደመ ነፍስ ጉዞ እንደሚጎትታቸው በሚያስደንቅ ብዕሩ ገልጾታል።

ገደብ አልባ በሆነ የስልጣን ኮርቻ ላይ ለዕድሜ ልክ የተፈናጠጡት ትላልቆቹ አምባገነኖች በመንፈሳቸው የበሰበሱና ፍቅርና ሰላም አልባ ውስጣዊ ማንነታቸው ከውጭ በሚታየው አካላዊ ቅርጻቸው ላይ ይነበባል ይላል አቺሌ ሜምቤ። እነኚህ የቁም ሙታኖች፣ ቦርጫቸው አለቅጥ ተንዘርጥጦ፣ ፊታቸው ጤናማ ባልሆነ ውፍረት ተነፍቶና ላባቸው አለማቋረጥ ሲወርድ፣ ቅርጽ የለሽ ደረታቸውና ሆዳቸው በጸጉር ተወርሮ ለሚያያቸው ለዓይን የሚቀፉ ሰው መሰል አውሬዎች ያስመስላቸዋል። ይህ ጸያፍ የሆነውን አካላዊ ቅርጻቸውን እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሰው ደግሞ ስርዓትና ገደብ የሌለው የአመጋገብ ባህላቸው ነው። ከሆዳቸው ፍቅር በተጨማሪም ለዚህ እንስሳዊ ማንነት የዳረጋቸው ስልጣናቸውን ተገን አድርገው የሚፈጽሙት የዜጎች ላይ ጥቃትና ግድያ፣ ለከት የሌለው የወሲብ ፍላጎትና ነውረኛ እርካታ፣ የእርስ በርስ የመጠላለፍ ሴራ፣ አጠቃላይ የምግባረ ብልሹነትና ነፍስን ለስጋ ፍጹም አሳልፎ የመሸጥ ክፉ ውጤት ነው ይላል አቺሌ ሜምቤ።