ታህሳስ ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፓርቲው ” የምንናገርበትን የመገናኛ ብዙሃን ማንም እንዲመርጥልን ወይም እንዲወስንልን አንፈቅድም” በሚል ርእስ ባወጣው የአቋም መግለጫ፣ ” ሰማያዊ ፓርቲ መልዕክቱን የሚያስተላልፍበትን መገናኛ ብዙሃን ማንም አካል እንዲመርጥለት ወይም እንዲወስንለት የማይፈልግ መሆኑን ግልፅ ” አድርጓል።
“በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠውን ማንም ሰው በመረጠው መንገድ ሃሳቡን የማስተላለፍ መብቱን በመጠቀም በኢሳትም ሆነ እድሉን ካገኘ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አቋሙንና እምነቱን ማስተላለፍ የሚቀጥል መሆኑን ማረጋገጥ ይወዳል” በማለት ፓርቲው በኢሳት ላይ ቀርቦ አቋሙን ከመግለጽ እንደማይገታ ግልጽ አድርጓል።
ሰማያዊ ፓርቲ ታህሳስ 25 ቀን 2006 ዓም በኢቲቪ የተላላፈውን ዶክመንታሪ ፊልም “የእብሪት መልዕክት” ያዘለና እና “ከተራ ርካሽ ፕሮፓጋንዳነት የማያልፍ የሕግና የዲሞክራሲያዊ መብት ገደብን ካለማወቅ የሚመነጭ አስተሳሰብ ነው” ሲል አጣጥሎታል።
“የብሔራዊ ደህንነት መረጃ እና የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል በተደጋጋሚ ጊዜ በሽብር ወንጀል ጠርጥሬአቸዋለሁ የሚላቸውን ሁሉ በመክሰስ ወደ እስር ቤት እንዲወርዱ እያደረገ ጉዳያቸው የፍርድ ቤት ውሳኔ ሳያገኝ እንደፈለገ በሚቆጣጠረው ወይም በሚያዘው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት አማካኝነት የፈለገውን ዓይነት ፍረጃና ሥም ማጥፋት ሲያካሒድባቸው” መቆየቱን ያስታወሰው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ይህ ራሱን ከሕግ በላይ የሰቀለ አካል ያለምንም ገደብ ከሚሰራቸው ተግባራት እንዲታቀብ በሕግ የሚያስቆመው በመጥፋቱ እስካሁን የፈፀማቸውን የማንአለብኝነት ተግባራት እንደጥፋት ሳይሆን እንደ መልካም ሥራ ቆጥሯቸው በተመሳሳይ የሥም ማጥፋትና የፍረጃ ተግባሩ እንዲገፋበት አድርጎታል” ብሎአል።
“ኢሳት” የተባለ የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ መንግስት በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገለትና በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በተለይም ሰማያዊ ፓርቲ በዚህ የመገናኛ ብዙሃን እንዳይጠቀም የማስጠንቀቂያ ዛቻ ተላልፎለታል” ሲል ያስታወሰው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ይህ አስፈራሪ አካል ራሱን ሕግ አውጭና ሕግ ተርጓሚ በማድረግ የዚህች ሐገር ዜጎች ሃሳባቸውን የሚገልጹበትንና የማይገልጹበትን የመገናኛ ብዙሃን እየወሰነላቸውና እየመረጠላቸው ይገኛል፣ ብሎአል ።
የገዥው ቡድን ሰዎች ሀሳብን በሃሳብ ማሸነፍ እንደማይችሉ ስለሚያውቁት የቀራቸው አማራጭ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ሃሳባቸውን የሚያሰራጩባቸውን መንገዶች መዝጋት ብቻ መሆኑን ፓርቲያችን ይገነዘባል ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ማንም አካል በሕግም ሆነ በሞራል ተጠያቂ የሚሆነው የሚያስተላልፈው መልዕክት ይዘት የሌሎችን ዲሞክራሲያዊና ሞራላዊ መብት የሚጋፋ መሆን አለመሆኑ እንጂ ገዥው ቡድን በጠላው ወይም በወደደው የመገናኛ ብዙሃን መልዕክቱን ማስተላለፉ አይደለም” ሲል አቋሙን ግልጽ አድርጓል፡፡ መልዕክትን የገዥው ቡድን ሰዎች በጠሉት የመገናኛ ብዙሃን ማስተላለፍ በራሱ ወንጀለኛ ወይም ሽብርተኛ ለማድረግ የሚያበቃ ምንም ዓይነት የሕግ መሰረት እንደሌለውም ገልጿል፡፡
ፓርቲው በመጨረሻም ” ሰማያዊ ፓርቲ መልዕክቱን የሚያስተላልፍበትን መገናኛ ብዙሃን ማንም አካል እንዲመርጥለት ወይም በዚሁ አጋጣሚም የፓርቲያችንን መልካም ስም በሃሰት ለማጉደፍ የተሰነዘሩ ቃላትን በቀላሉ የማንመለከታቸው መሆኑን ሕግ ባለበት ሐገር ራስን ከሕግ በላይ በማስቀመጥ ማንንም አካል መፈረጅና ስም ማጉደፍ በሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑን የዘጋቢ ፊልሙ ባለቤቶች እንዲያውቁትና ወደፊትም ተመሳሳይ ድርጊት ከመፈፀም እንዲቆጠቡ እናሳስባለን፡፡” ብሎአል።
በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ሰማያዊ ፓርቲ እና አንድነት ፓርቲ በኢሳት ላይ ቀርበው አቋማቸውን እንዳይገልጹ መንግስት ሰሞኑን ምክር አዘል ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ በኢቲቪ አማካኝነት መስጠቱ ይታወሳል።
ከመጪው ምርጫ ጋር ተያይዞ ኢሳት ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ፕሮግራሞቻቸውንና መልእክቶቻቸውን በነጻ እና ያለገደብ የሚያስተላልፉበትን አሰራር በመቀየስ ላይ ነው።
No comments:
Post a Comment