ጥቅምት ፳(ሃያ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሪፖርተር ዛሬ ባወጣው ዘገባ በአገሪቱ የሚገኙ ሶስቱ ታላላቅ ስሚንቶ ፋብሪካዎች በአመት 12 ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ቢኖራቸውም በገበያ ውስጥ የሚገኘው ስሚንቶ ድምር ከ5 ሚሊዮን አይበልጥም።
አብዛኛውን ስሚንቶ የሚገዛው መንግስት ሲሆን፣ የግሉ ዘርፍ ድርሻ ቀዝቃዛ መሆኑ ተዘግቧል።
የሼክ ሙሀመድ አላሙዲን ንብረት የሆነው ደርባን ኩባንያ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ በኩንታል 209 ብር እየሸጠ፣ ለደንበኞቹ ቤታቸው ድረስ እያደረሰ ነው። ሙገር ስሚንቶም በተመሳሳይ ለልዩ ደንበኞቹ ምርቶቹን ቤታቸው ድረስ እያደረሰ ነው።
ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የገለጹ ባለሙያዎች ” ብዙም ግልጽ ባልሆነ ምክንያት የሲሚንቶ ገበያ እየተቀዛቀዘ መጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በ2006 ዓ.ም 21 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን፣ በ2007 ዓ.ም. 27 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ አገሪቱ እንደምትፈልግ ከአራት ዓመት በፊት የወጣው ጥናት ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡
‹‹ለሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ ከፍተኛ የካፒታል ኢንቨስትመንት ፈሷል፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን የሚሰጡት ባለሙያዎች፣ ጉዳዩን መንግሥት ከሥሩ ሊያጤነው እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዚህ ሁሉ መሀል መሰቦ ስሚንቶ ፋብሪካ 70 በመቶ የሚሆነውን ምርቱን ለአባይ ግድብ እና ለግልገል ጊቤ 3 የሀይል ማመንጫ ግድቦች በማቅረብ ላይ ነው። መሰቦ ሲሚንቶ በምን መስፈረት ለአባይ ግድብ ግንባታ አቅራቢ ሆኖ እንደተመረጠ አልታወቀም። ሙገር ስሚንቶ የመንግስት ወይም የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ሆኖ ሳለ፣ እንዲሁም ለአባይ ግድብ ማሰሪያ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በውድም በግድም ገንዘብ እንዲያዋጣ እየተደረገ ፣ ለድርጅቱ ስሚንቶ የሚያቀርበው ሙገር መሆን ሲገባው የህዝባዊ ወያን ሀርነት ትግራይ ኩባንያ የሆነው መሰቦ ስሚንቶ ፋብሪካ እንዲሆን መደረጉ ” የኢትዮጵያ ህዝብ ያዋጣል፣ ገቢው ወደ ህወሀት ኪስ ይገባል” ሲል አስተያየቱን የተጠየቀው የኢሳት የአዲስ አበባ ዘጋቢ ገልጿል።
ህዝቡ ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ገንዘብ እንዲያዋጣ ቢገደድም፣ ገንዘቡ በተዘዋዋሪ መንገድ ወደ ህወሀት ካዝና ነው የሚገባው የሚለው ዘጋቢያችን፣ መስፍን ኢንጂነሪንግና የወ/ሮ አዜብ መስፍን የእህት ልጅ ንብረት የሆነው ወርኪድ የተለያዩ የግንባታ እቃዎችንና የብረታ ብረት ውጤቶችን በማቅረብ ከግድቡ ከፍተኛ ገቢ እያገኙ ነው ብሎአል።
ሼክ ሙሀመድ አላሙዲን ለአባይ ግድብ ለማዋጣት 500 ሚሊዮን ብር ቃል ቢገቡም በተለያዩ ሰበቦች እስካሁን አጠናቀው አልከፈሉም። ዘጋቢያችን ምናልባትም ኩባንያቸው ደርባን ለግድቡ ስሚንቶ እንዳያቀርብ በመከልከሉ ተበሳጭተው ሊሆን ይችላል ብሎአል።
No comments:
Post a Comment