ጥቅምት ፳፯(ሃያ ሰባት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከወጣት እስከ አዋቂ ያለው ከግማሽ በላይ የሚሆነው ኢትዮጵያ በልጅነቱ በቂ ምግብ ሳያገኝ ተጎድቶ እንደሚያድግ የተመለከተው በኢትዮጵያ ይፋ በሆነው the cost of hunger in Ethiopia ጥናት ውስጥ ነው።
67 ከመቶ የሚሆነውና ከ15 አስከ 64 የእድሜ ክልል ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊ ጠንካራ ሰራተኛ ቢመስልም በልጅነቱ ያጣው የተመጣጠነ ምግብ አቀንጭሮትና አቀጭጮት አቅም አሳጥቶት በስራው ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል።
እነዚህ ሰዎች በልጅነታቸው የተፈለገውን ምግብ አግኝተው ቢሆን ኖሮ በያመቱ 53.6 ቢሊዎን ብር ማዳን ይችሉ ነበር ተብሏል።
ልጆቹ ሲያድጉ አንድም በጤና ምክንያት ከስራ ይቀራሉ ሌላም ለህክምና ገንዘብ ያወጣሉ። በዚህም ምክንያት 4.8 ቢሊዎን የስራ ስዓት ሲያባክኑ፣ አገሪቱ 40 ቢሊዎን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ታጣለች።
በትምህርት በኩልም ቢሆን አእምሮአቸው ብዙም ያልዳበረ በመሆኑ የተመጣጠነ ምግብ አግኝተው ካደጉት አገሮች በበለጠ ትምህርታቸውን ይደግማሉ።
በ2001 የትምህርት ዘመን ብቻ በዚሁ ችግር ውስጥ ያለፉ ከ152 ሺህ በላይ ታዳጊዎች ወደ ቀጣይ ክፍል ሳያልፉ ቀርተዋል። ትምህርት መከታተል ተስኗቸው ያቋረጡም ብዙ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ተምረው ቢሆን ኖሮ እውቀታቸውን አዳብረው በያመቱ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው 625 ሚሊዎን ብር ተጨማሪ ገቢ ያስገኙ ነበር ይላል the cost of hunger in Ethiopia ጥናት ። ጥናት በኡጋንዳ ግብፅና ሲዋዚላንድ ተመሳሳይ ምርምር አድርጎ የኢትዮጵያ ችግር የከፋው መሆኑን ገልጿል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2006 አስከ 2015 ኢትዮጵያ ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ 144 ቢልየን ብር ታጣለች ፡፡ ችግሩ ቀጣይ ና አሳሳቢ ነው የሚሉት ባለሙያዎች ፣ የምግብ እጥረት የቀጣዩ ትውልድ ፈተናዎች ይሆናሉ ይላሉ፡፡
በመላ ሀገሪቱ ከ5 ሚልዮን በላይ ዜጎች ነገ ሰለሚበሉት ዋስትና እንደሌላቸው የፌድራል አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሺን መረጃ ያሣያል፡፡
No comments:
Post a Comment