Tuesday, November 26, 2013

በሽብርተንነት ስም የህዝብ መብቶችን ማፈን ይቁም!

November 26, 2013
ከቅዱስ ዬሃንስ

ፀረ -ሽብርተኝነት ለአምባገነኖች ሁለት ጥቅም ያስገኝላቸዋል፡፡ አንደኛ በፀረ- ሽብርተኝነት ስም ከምዕራባውያን ኃያላን ጎን በአጋርነት በመቆማቸው በጥሬ ገንዘብም ሆነ በዓይነት (ለምሳሌ በመሣሪያ፣ በፖለቲካ ድጋፍ) ዳጎስ ያለ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ ሁለተኛ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስም የሚያወጡት ሕግ የውስጥ የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውን ለማጥቃት የሚያስችላቸውን ሕጋዊ ሽፋን ይሰጣቸዋል፡፡ ስለዚህ ነው ፀረ -ሽብርተኝነት ለአምባገነኖች ከሰማይ የወረደ የተቀናቃኝ ማጥቂያ መሣሪያ ነው የሚባለው፡፡ ይህንን ያልኩበት አብይ ጉዳይ ዛሬ ሃገራችንንና ህዝቧን እያስጨነቀ ያለው የወያኔ አገዛዝ የፀረ ሽብርተኝነት ህግን ከለላ በማድረግ በሰላማዊ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው የመብት ረገጣ፤ እጅግ የከፋ ደረጃ በመድረሱ ነው።


በሰላማዊ ትግል ዴሞክራሲያዊ የመንግስት ለዉጥ ለማምጣት የሚታገሉ ሰላማዊ ዜጎችን አግባብ ባልሆነና ባልተጨበጠ ክስና ዉንጀላ ማሰር፣ አፍኖ መሰወር፣ ንብረትን ማዉደምና መዉረስ እንዲሁም የአደባባይ ግድያ ባለፉት 22 የወያኔ  የአገዛዝ ዘመናት የተለመዱ ተግባሮች ሆነዉ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ ይህ አምባገነናዊና ኢፍትሀዊ ተግባር በህግ ሽፋን ተጠናክሮ ቀጥሏል። ለገዥዉ ስርአት የአፈናና የጥርነፋ መዋቅር ተባባሪ ያልሆኑና ለመብታቸዉ መከበር የሚታገሉ ዜጎች በአሸባሪነት ስም በጅምላ እየታፈሱና እየታሰሩ ይገኛሉ። ታፍነዉ የተወሰዱና ያሉበት ቦታ የማይታወቀዉም ጥቂቶች አይደሉም። ባለፉት ጥቂት አመታት ብቻ በሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በሽብርተኝነት ተወንጅለዉ ታስረዋል። ሰብአዊ መብታቸዉም በማንአለብኝነት እየተረገጠ ይገኛል። ከነዚህ ንፁሀን ዜጎች ዉስጥ ብዙዎቹ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላቶች፤ የእምነት መሪዎችና ለሞያቸዉ ታማኝ የሆኑ ጋዜጠኞች መሆናቸዉን ስናይ ደግሞ ዘመቻዉ በሀገራችን ተጠናክሮ የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚደረገዉን ሰላማዊ ትግል ለመጨፍለቅና ህዝብን ከትክክለኛ መረጃ አርቆና አፍኖ ለመግዛት ታስቦበትና ሆነ ተብሎ የተያዘ ስልት መሆኑን ግልፅ ነው።

በሽብርትኝነት ያለመከሰስ መብቱን በጠመንጃ ያስከበረው ወያኔ ግን ሰላማዊውን ህዝቡ በተለያዩ መንገዶች  እያሸበረ የስልጣን ቆይታውን ለማርዘም ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል። ዜጐችን በማፈናቀል፤ በእምነት ውስጥ ጣልቃ በመግባትና የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት በመከፋፈል እያፋጀ የሽብር ሴራውን እየፈፀመ ይገኛል። ሰላማዊ ዜጋውን ፣አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩን በልማት ስም ተወልዶ ባደገበት እትብቱ ከተቀበረበት ሃገር እያፈናቀለ ለስደት እየዳረገው ይገኛል፡፡ ለዚህም የሽብር ሴራው ሰለባ የሆኑት፤ የሚበሉት፤ የሚጠጡት እና በመጠለያ እጦት በየአደባባዩ ሰፍረው የድረሱልኝ ጥሪ እያሰሙ የሚገኙት የአማራ ብሔረሰብ ወገኖቻችን ናቸው፤ እነዚህ ወገኖቻችን በሃገሪቱ አራቱም ማዕዘናት እየተፈናቀሉና እየተዋከቡ ይገኛሉ። ማፈናቀለ አልበቃ ያለው የወያኔ የሽብር መረብ ወደ እምነት ቦታዎችም በመዛመት ዋልድባን እና የተለያዩ የሃይማኖት ቦታዎችን በማፈራረስ በአለም ደረጃ እውቅና እና አድናቆት የተሰጣቸውን የሃገሪቱን የሃይማኖት፤ የታሪክ ቅርሶች በማውደም፤ ኢትዮጵያውያን በቀደምትነት በምንታወቅበት እምነታችን ላይ አደጋ በመፍጠር፤ አዋራጅ ድርጊቶችን በንቀት እና በጥላቻ እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡ ከእምነት ቦታዎች ባሻገር በአለም ደረጃ እውቅናን ካገኙት ታሪካዊ ቦታዎች ውስጥ ተጠቃሹ የታችኛው አዋሽ እና ኦሞ ሸለቆዎች አንዱ ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ ቦታ ያራዊቶች እና የተለያዩ የደኖች ስብስብ ያለበት ሰፊ የሃገራችን ቅርስ የነበረው ሲሆን ዛሬ ላይ ግን ወያኔዎች በልማት ስም ለውጭ ባለሃብቶች አስረክበውት ድብዛው እየጠፋ ነው፡፡ አምባገነኑ ወያኔ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ያነሱትን የመብት ጥያቄ ወደ ጎን በመተው በእኔ አውቅላችኋለሁ እብሪት የተሞላ አስተሳሰብ በማፈን ንፁሃኑን ሙስሊም እየገደሉ ብሎም በሽብርተኝነት በመወንጀል እያሰቃዩት ይገኛሉ። ሙስሊሙ ህብረተሰብ የተቃውሞ ድምፁን ያሰማበትን አላማ ምንድነው? ችግሩስ ከምን የመነጨ ነው? ብሎ እልባት ከመስጠት ይልቅ ጥያቄአቸውን በማንቋሸሽ እና በማጥላላት በጠመንጃ አፈ ሙዝ የሚመልሱት ይመስል ህዝበሙስሊሙን ለከፋ መከራና ስቃይ ዳርገውታል። ለዚህ ድርጊታቸው ደግሞ ሚስጥሩ ንፁሃኑ ህዝበ ሙስሊም ላይ የሃሰት ታርጋ በመለጠፍ አሸባሪነትንና አክራሪነትን እየተዋጋው ነው በሚል የማስመሰልና የማታለል ስራው የምዕራባውያን ሃገራትንና የአሜሪካ ቀልብ ለመሳብና እርዳታ ለማጋበስ ነው። ቢያውቁት ግን ይህ ድርጊታቸው አውሬ እንጅ ሰው አለመሆናቸውን ቁልጭ አድርጐ ያሳያል። ለገንዘብ ሲባል ሰውን ያክል ፍጡር መግደል፤ ማሰርና ማሰቃየት ከአንድ ሰው የሆነ ሰብአዊ ፍጡር አይጠበቅምና።

ሌላው ወያኔዎች 22 ዓመታት በጠመንጃ ስልጣን ላይ ከወጡበት ጊዜ አንስቶ ሲጠነስሱት የነበረው ሽብር የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት በመከፋፈልና በማፋጀት የኢትዮጵያን ህልውና አንድነትን፣ ማንነትን በማናወጥ፤ የስልጣን እድሜያቸውን ማርዘም ነው። ይህ ስራቸው ከምን ጊዜውም በላይ በአሁኑ ሰአት እያፋፋሙትና፤ ሰላማዊውን ህዝብ በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት በማጋጨት የሽብር ሴራቸውን እያስፋፉ ይገኛሉ። ዳሩ ግን ለወያኔዎች ህዝብን መከፋፈል የሚበጅ ቢመስላቸውም የዚህ የሽብር ድራማቸው ተጠቂዎች ግን በፍፁም ልንሆን አልቻልንም፤ ወደፊትም ልንሆን አንችልምም። ምክንያቱም መቻቻል እና በፍቅር አብሮ መኖር መለዬ ባህላችንን በፍፁም ይህ ሰይጣናዊ ድርጊታቸው ሊያመክነው ስለማይችል ነው። ይህንን አንድነታችንን፤ ፍቅራችንን የመቻቻል ባህላችንን የበለጠ በማጎልበት፤ ባህላችንን፣ አንድነታችንን፣ ሃይማኖታችንን እየተፈታተነ ያለው የወያኔን የሽብር ስልት በማክሸፍ፤ ለበለጠ ድል እስክንበቃ ትግላችንን ማጠናከር ይኖርብናል።

በመጨረሻም የወያኔ ባለስልጣናት በፈረጠመ አምባገነናዊ ክንድ ህዝብን በማሸበርና በማፈን የስልጣን ዘመንን ለማራዘም መሞከር አወዳደቅን ማክፋት መሆኑን ካለፉት አምባገነናዊ ስርአቶች ሊማሩ ይገባል! አሁንም በድጋሚ ወያኔዎች ጠንቅቀው ሊያውቁት የሚገባ እውነት የኢትዮጵያ ህዝብ ሽብኝነትን በጽናትና በቁርጠኝነት ይቃወማል፤ ያወግዛልም፡፡ በፀረ -ሽብርተኝነት ሽፋን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እየጣሰ ያለውን የወያኔ አገዛዝንም በተመሳሳይ ጽናትና ቁርጠኝነት ይቃወማል፤ ይታገላልም!!!

ድል ለጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ!

ያለዎትን አስተያየት በፀሃፊው አድራሻ: kiduszethiopia@gmail.com ይላኩ።

No comments:

Post a Comment