ጥላቻው እያደገ ሔዷል ፣ ሳውዲ አሰሪዎች ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞቻቸውን ድሮ ድሮ በአረቦች ዘንድ የተከበርን ፣ የታፈርን የእኛን የሃበሻ ልጆች “ጨካኞች ፣ የማይታመኑ !” እያሉ ጥላቻቸውን መገልጽ ጀምረዋል። November 14,2013 የወጣው አረብ ኑውስ Recent clashes make Saudis wary of Ethiopian maids በሚል ርዕስ ስር ሳውዲ አሰሪዎች ኢትዮጵያን ሰራተኞችን ለማባረር እየዛቱ ነው ! ይህ የአረብ ኒውስ ዘገባ በሹክሹክታ የምንሰማው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
የሪያድ መንፉሃን ግጭት ተከትሎ ደም እድገብሮም ለኢትዮጵያን ተሰጠው ወደ ሃገር ቤት የመግባትን እድል ለመጠቀም ከሃያ ሽህ በላይ ኢትዮጵያውያን የሪያድ መጠለያወችን አጨናንቀዋል። እንዳውም በሪያድ የኢትዮጵያ አንባሳደር ቁጥሩን ወደ ሃያ ሶስት ሽህ እንደሆነ ረቡዕ November 14,2013 ለወጣው አረብ ኒውስ አስታውቀዋል። አሁንም በሽዎች የሚቆጠሩ ወደ መጠለያ ለመግባት እየጎረፉ ነው ። በመጠለያው የምግብና የሚጠጣ ውሃ እጥረቱ ደግሞ ኢትዮጰያውያኑ አጥር ሰብረው እንዲወጡ እያስገደደ ነው ተብሏል።
በጅዳ እና በተለያዩ የሳውዲ ከተሞች ያሉ ህጋዊ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያንም የሚይዙት የሚጨብጡት አጥተው በቋፍ ላይ ናቸው ። በሪያድ እና በተለያዩ ከተሞቸ ባሳለፍነው ቅዳሜ በመንፉሃው ሁከት ጭካኔ የተቀላቀለበት በሃገሩ ነዋሪዎች ተወሰደ በተባለው እርምጃ ገና በመሰራጨት ላይ ያለው መረጃ ምስል ህጋዊ ሆነ ህገ ወጥ የሆነውን ሁሉንም እያስጨነቀ ነው ። እኔም እዚያው መንፉሃ ሆነውን የአይን እማኝ ከሰማሁ ወዲህ ከ16 አመታት በላይ የማውቃቸው ሳውዲዎች ይህን ፈጸሙ ለማለት ብቻ ሳይሆን በዚህች ሃገር ይህ መሰል ግፍ በሰው ልጅ ይፈጸማል ለማለት ተቸግሬያለሁ። እውነት መሆኑን ደጋግሜ ሳሰላስለው ደግሞ የሳውዲ ኑሮ እየጎረበጠኝና ተስፋየን እየሟጠጠው ሄዷል። ብዙዎች በዚህና በመሳሰለው የማሳደድ ችግር ምክንያት ወደ ሃገር መግባት ይፈልጋሉ ፣ በሪያድ ከመንፉሃ በተጨማሪ በኮንትራት ስራ የመጡና ለበርካታ አመታት በሳውዲ ነዋሪ የሆኑት ሳይቀሩ እንደ መንፉሃ ግፉአን በውድ የገዙትን እቃ በርካሽ እየሸጡና መኖሪያ ፍቃዳቸውን አሽቀንጥረው በመጣል ወደ መጠለያው እየገቡ ነው ።
“በመንፉሃ ቁጥራቸው የማይታወቅ ኢትዮጵያውያን ሞተዋል … ” በሚል ነዋሪው በሚሞግተውና መንግስት ” ሶስት ብቻ ነው የሞተው! ” ያላቸው ኢትዮጵያውያን ደም ፈስሶ በድርድርም ቢሆን ሳውዲዎች የጣሉትን ቅጣት አንስተው ህገ ወጥ ነዋሪዎች በፍላጎት እንዲገቡ ተፈቅዷል። ይህ ለሪያድ ነዋሪዎች የተሰጠው እድል በሁሉም ከተማ ላሉት ዜጎች ስለመስራቱ ማወቅ ባለመቻሉ ነዋሪው ተጨናንቋል። በመካ ያለው ከበድ እያለ መጥቷል። በጅዳ ከንደራ የሚፈራውን ያህልም ባይሆን በእለተ ሃሙስ November 14,2013 እኩለ ቀን ለግማሽ ሰአት የዘለቀ ፍጥጫ እንደ ነበር እለታዊው አረብ ኒውስ ጋዜጣ ከቀትር በኋላ ዘግቦታል። በጣይፍ ፣ በጀዛንና በአቅራቢያ የተለያዩ አካባቢዎችም ጉዳይ አሳሳቢ ነው ። ቢያንስ የመንግስት ሀላፊዎች መረጀ በመስጠት ሰውን ማረጋጋት ካልቻሉ ያየን የሰማነው የመንፉሃ አደጋ በከፋ መልኩ እንዳይጫር ስጋት አለኝ።
በጅዳ ቆንስል ምን እየተሰራ እንዳለ የሚታወቅ ነገር የለም ። እርግጥ ነው ስራ እየተሰራ ነው ። ፖስፖርት ይታደሳል ፣አዲስ ይሰጣል፣ ከአስር ሽህ በላይ ይሆናሉ ለሚባሉ በእስር ቤት ላሉት ሊሴ ፖሴ ይሰጣል፣ ሌላም ሌላ ስራ ይሰራል። ከዚህ አልፎ ከግቢው በመታመስ ላይ ላሉ ወደ አስር የሚጠጉ ያበዱትን ፣ ከሰላሳ በላይ የነሆለሉና የታመሙትን ጨምሮ ሁለት መቶ የሚጠጉ ዜጎች ጉዳይ መቋጫ አልተገኘለትም። ለወራት ሲንከባለል የቆየ ወደ ሃገር የማሳፈር ክትትል ምን ምን ላይ እንደ ደረሰ የሚታወቅ ነገር የለም። የቻለው ምግብ እና ውሃ ብሎም አንዳንድ አስፈላጊ ቁሳቁስ እያቀረበላቸው ይገኛል ። ከዚህ ባለፈ ሁኔታውን አይቶ እንባውን እየረጨ ከመሄድ ባለፈ ምንም መስራት አልቻለም ፣ አቅሙም የለውም! በርካታ ወገኖች እየሆነ ያለውን ለማወቅ ጉጉት አላቸው ። ያም ሆኖ የጅዳ ቆንስል የበላይ መረጃ መስጠትም ሆነ መቀበል አልፈለጉም። ወጌን በማስረጃ በአንዲት ማስረጃ ብቻ ላስረግጥ … !
ኢትዮጵያውያን እንደጨው ተበትነናል። ከቀናት በፊት ባሳለፍነው እሁድ ሰባት ኢትዮጵያውያን ታሳሪዎች ይዞ ከጀዛን ክልል ወደ ሽሜሲ አዲሱ እስር ቤት ሲጓዝ የነበረ አንድ የፖሊስ መኪና እኩለቀን ሊዝ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሰበት አደጋ አራት ኢትዮጵያውያን መሞታቸውና ሶስት ያህሉ መቁሰላቸውን በሰማሁ ማግስት መረጃውን በትኩሱ ለማድረስ ተወካዮቻችን በስልክ ደውየ ሳጣቸው ከጭንቀቱ ጋር ውስጤ የተሰማውን ለመግለጽ እቸገራለሁ ። ነገሩ እንዲህ ነው …እሁድ ለሰኞ አጥቢያ በጅዳ መኮሮና አካባቢ እኩለ ሌሊት ላይ አንድ መረጃ ደረሰኝ “ኢትዮጵያውያንና እዚህ አገር ተወልደው ባደጉ የውጭ ዜጎች መካከል ሁከት ተቀስቅሷል! “የሚል ነበር። መረጃ ለማቀበል ለብቸኛ ተጠሪዎቻችን ስልክ ደወልኩ ። አይመልሱም። መረጃ አቀባዮቸን መልሸ ስደውል አካባቢው በጩኸትና ረብሻ ሲታመስ ሰማሁ። ደግሜ ወደ ለሃላፊዎች ደወልኩ ። ዋና ሃላፊው አቶ ዘነበ ከበደም ሆነ ምክትላቸው አቶ ሸሪፍ ኸይሩ ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን አያነሱም ። ፖሊስ ደርሶ ረብሻው ተበተነ። አካባቢው መረጋጋት ያዘ ። መንፉሃን እያስታወስኩ በደረቁ ሌሊት በአይኔ እንቅልፍ ሳይዞር ነጋ … !
አይነጋ የለም ነግቶ ፣ ኢትዮጵያውያኑ የተያዙት ተይዘው የቀሩት ቤታቸው ተዘርፎ ድልድይ ስር ማደራቸውን በቦታው ሔጀ ተመልክቻለሁ። በግጭቱ የቅርብ ርቀት ተሸብረው ያገኘኋቸው የግጭቱ ተጎጅዎች ህክምና ያገኙ እንደሁ እና ጉዳዩንም ስልክ የማያነሱት የቆንሰሉ ሃላፊዎች ጉዳታቸውን እንዲያውቁላቸው አሁንም ወደ ሃላፊዎች ደወልኩ። አያነሱም ። ተጎጅዎችም ሌሊት ለእኔ እንደ ደወሉ ወደ ቆንስሉ ከሃያ ጊዜ በላይ ደውለው ስልኩን የሚያነሳ ስላጡ ወደ እኔ መደወላቸውን አጫወቱኝ ። ግራ ብጋባም ቢያንስ የሆነውን ሁሉ ለማስረዳት ተጎጅዎችን ወደ ቆንስሉ ለመውሰድ ወስኘ ሳማክራቸው ” አድርገህው ነው! ” አሉኝ ከነፍሰ ጡሯ እህት ተጎጅና ሁለት በግጭቱ የቆሰሉ የተደበደቡትን እና ወደ ስምንት የሚደርሱ እማኞችን ይዠ ወደ ጅዳ ቆንስል መስሪያ ቤት አመራሁ። በሙግት ወደ ግቢው ብንገባም ሃላፊውን እኔን ለማነጋገር እንደማይችሉ እና ስብሰባ ላይ መሆናቸው እንደ ምክንያት ተሰጠኝ። ሰውነቴ ተቆጣ ፣ “የእነሱን ስራ ስሰራ ለምን አይተባበሩኝም!” ራሴን ጠየቅኩ ፣ መልስ ግን የለኝም! ከማይጋነን መጉላላቱ በኋላ ዋና ሃላፊው አቶ ዘነበ ከበደ አማካኝነት በወረደ ትዕዛዝ የዲያስፖራዋ ሃላፊ ቆንስል ሙንትሃ እንዲያነጋግሩኝ ተደርጎ ቆንስሏን አግኝቸ አነጋገርኳቸው ። ለመኮረና ግጭት መረጃ አዲስ እንደሆኑ ገልጸው ለመረጃው አመስግናውኝ ቁስለኛና ተጎጅዎችን አስተዋውቄያቸው ወደ ስራየ ከመውጣቴ በፊት ማለት የፈለግኩትን በስጨት እንዳለኩ ተናገርኳቸው ! ቆንስል ሙንትሃ ባዩትና በሰሙት ተደናግጠው እዚያው እያለሁ በውስጥ መስመር ደውለው ለአቶ ዘነበ የጉዳዩን አሳሳቢነት አሰረዷቸው። ወደ ቆንስሉና ወደ ሃላፊዎች ስልክ ስደውል የማይነሳበትን እንቆቅልሽ ከማስረዳት ባለፈ በዚህ ሰአት በአንድ የስልክ ጥሪ በሚታጣ መረጃ ብዙ ጥሩም መጥፎም ሁኔታ ስለሚያስከትል የዜጎችን መብት ለማስከበር የተቀመጠ የመንግስት አካል ለመረጃ የራቀ መሆኑን አደገኛ አካሔድ ገለጽኩላቸው ። ብዙም ሳልቆይ ባለጉዳዮችን እዚያው ትቸ ወደ ስራየ አቀናሁ …
ከቀትር በኋላ የቆንስሉ ሃላፊ አቶ ዘነበን ጨምሮ ሶስቱም ዲፕሎማቶች የመኮረናው ግጭት ወደ ሚመለከታቸው የሽማልያ ፖሊስ ጣቢያ ማቅናታቸውን ሰምቻለሁ። በመኮረና ሆነ ተብሎ በወሰድኳቸው ተጎጅወች የሰማነውን በዜጎች ላይ የመቁሰልና የሞት አደጋ መከሰቱን ጠይቀው ከጀኔራል አዛዡ መልስ እንደተሰጣቸው ቆንስል ሙንትሃ ስልክ ደውለው ገልጸውልኛል። የፖሊስ አዛዡም ረብሻው በኢትዮጵያውያንና በቻድ ዜጎች መካከል ከሶስት ቀብ በፊት በተጀመረ መጠነኛ ጸብ ምክንያት እንደነበር መረጃ እንደነበራቸው ፣እሁድ ለሰኞ አጥቢያ ደግሞ ሁከቱ መከሰቱን እና ፖሊስ እንዳበረደው ማስረዳታቸውን ፣ በእለቱ ግጭት ተኩስ እንደ ነበር ነገር ግን በተኩሱ የቆሰለ እንደ ሌለ እንዳሰረዷቸው ፣ አምስት ያህል በድብድቡ የቆሰሉ እንጅ የሞተ ሰው እንደ ሌለ አስረግጠው ሲነግሯቸው በግርግሩ የታሰሩትን ኢትዮጵያውያን እንዳስጎበኟቸው ቆንስል ሙንትሃ ገልጸውልኛል። ሳውዲ ጋዜት በቀጣዩ ቀን Tuesday 12 November 2013 የመኮሮናውን ግጭት እንዲህ ብሎ አሽሞንሙኖ አቀረበው 57 held after Chadian-Ethiopian clash http://www.arabnews.com/news/475786 . እንግዲህ ከላይ ለማሳየት የሞከርኳቸው የመረጃ ግብአቶች በዲፕሎማቶች ዙሪያና በጭንቀት ላይ ስላለው ነዋሪ መጠነኛ መረጃ በመስጠት እየሆነ እና እየተሰራ ያለውን በትክክል ካሳየ መልካም ነው ።
መሬት ላይ በአይናችን የምናየውን እንዲህ ሆኖ እያለ እውነት የሚጣረስ ፕሮፖጋንዳ መሰል መረጃ ደግሞ ከመንግስት ቴሌቪዥንና ራዲዮ ሲነገር እየሰማን ነው። መንፉሃ ላይ ፍጅቱ ሊጀመር ሲዳዳው ፍጥጫውን ማርገብ ያልቻሉት ዲፕሎማቶች መንፉሃ በደም ከተበከለች በኋላ ዜጎች ያለ መቀጮና እስራት ወደ ሃገራቸው እንዲገቡ ስምምነት ማድረጋቸው እውነት ነው። ያም ሆኖ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደሚነግሩን ስራውን በቅንጅትና በማቀላጠፍ እየሰሩ አይደለም የሚል መረጃ ከተጨባጭ ምንጮች ይደርሰኛል።
ከቀናት በፊት አንድ ጽነፈኛ የምለው የፊስ ቡክ አፍቃሬ ኢህአዲግ ወዳጀ Ramatohara Dertogada ችግሩ ሲከሰት የሰጣቸው ለወገን ተቆርቋሪነት የታየበት አስተያየት ተቀይሮ ተመለከትኩት ። “… ሳውዲን ጨምሮ በሁሉም ዓረብ ሀገራት በዜጎቻችን የሚያደርሱት በደልና ግድያ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ የጥላቻ ሴራ ነው። … መንግስት በዜጎቹ የሚደርሰው በደል እንዲቆም ህጋዊ የሆነ አቋም ለዓለም ማህበረሰብ ያቀርባል። በአሁኑ ስዓት ለዜጎቹ ግዝያዊ የሆኑ የነብስ አድን ስራዎችና የዲፕሎማሲ ማግባባቶች እየሰራ ነው። ” ይላል! ይህን ሃሳብ ወዳጀ አለመጻፉን ብረዳም በሃሳቡ መስማማት መደገፉን ጠረጠርኩና የተዛባ መረጃ እየሰጠ ያየሁትን የኢትዮጵያ ቲቪን ረገምኩ! እንደተባለው ስራው እየተሰራ መሆኑ እውነት ቢሆን ምንኛ ደስ ይል ነበር! ግን በመንግስተ መገናኛ ብዙሃን ” በሳውዲ የሚገኙ ዲፕሎማቶች 24 ሰአት እየሰሩ ነው! ” የተባለው መረጃን ተሰራ ከተባለው ስራ ጋር ስናነጻጽረው እውነት አይደለም! ባሳለፍናቸው ቀናት መረጃን ለማግኘት በየቀኑ ወደ ሪያድ እደውላለሁ። በርካታ መረጃዎችን ለመስብሰብ ሞክሬያለሁ ፣ በመጠለያ ያሉት በርሃብና በውሃ ጥም እየተቸገሩ ነው። ማረጋገጥ አልተቻለም እንጅ አዲስ የሞት ዜናም አለ!
አሁን አሁን በመላ ሃገሪቱ በተለይም በሪያድ የሚሰማው ደስ አይልም። ረቡዕ ከቀትር በኋላ ሪያድ መንፉሃ የከፋ ችግር ተከስቶ ነበር ። ለጊዜው በረድ ቢልም የተጎዳ ሰው አለ ….መካ ውስጥ ወደ ሃገራችን ስደዱን ባሉ ዜጎቻችን መካከል ሁከት ሊቀሰቀስ እንደ ነበር ተጨባጭ መረጃዎች ደርሰውኛል። የሳውዲ ጋዜጦችም ይህንን አረጋግጠዋል። የሪያድ ዲፕሎማቶች ነዋሪውን በማቀናጀት ማስተባበሩ ላይ ዳተኛ መሆናቸው ሲያስተዛዝብ ፣ በጅዳ ዲፕሎማቶች ሌላው ቢቀር ነዋሪውን ሰብሰበው መረጃ ሊሰጡት አልፈቀዱም። በቆንስሉ መጠለያው እየተርመሰመሱ አንጀት ስለሚበሉት ተፈናቃይ ሰራተኞችም ሆነ “ከሃገር ይውጣ !” በተባለው ህጋዊነመኖሪያ ፈቃዱን ማስተካከል ባልቻለው ዜጋ ዙሪያ እንዲመክር እንዲዘክር የሚሰሩት ስራ የለም! ይህን ለማጣራት ከቀናት በፊት ወደ ጅዳ ቆንስል ጎራ ብየ ነበር ። ጠባቂው ወንደሜ የቀድሞው የህዝባዊ ሃርነት ግንባር መድፍ አገላባጭ ታጋይ “ገሬ! ” አትገባም አለኝ ። ምክንያቱን ስጠይቀው ” አቶ ዘነበ እኔ ሳልፈቅድ አታስገባው ብለውኛል !” ሲል መለሰልኝ ። ከብዙ ሙግት በኋለ በአማላጅ ገባሁ ። በጅዳና አካባቢው ያለ ነዋሪ መረጃ ተጠምቷል ፣ ሃላፊዎች መረጃ መስጠት ቀርቶ መረጃ ለነዋሪው ለመስጠት የምንሞክረውን ክብራችን እየነኩ እያሳዘኑን ነው! እውነቱ ይህ ነው! ብዙ አልልም ! ብቻ በሳውዲ አረቢያ ሪያድና ጅዳ የሚገኙት የኢትዮጵያ መንግስት ኢንባሲና ቆንስል መስሪያ ቤቶች እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ መረጃ በመስጠት እንኳ ለህዝብ ማስረዳት ፣ማረጋጋት እንዳይቻል በራቸው በብረት ሰረገላ ተከርችሟል። በሩን ለማስከፈት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም አልተቻለም!
የሳውዲ በርካታ ክልሎች የተለያዩ መረጃዎችን አገኛለሁ። መረጃዎችን በተገቢ መንገድ ለመጠቀም እሞክራለሁ። ከሪያድ መንፉሃ ከተሰደው እርምጃ ውጭ በቀሩት የሃገሪቱ ክፍሎች በኢትዮጵያውያን ላይ ማንኛውም ህገ ወጥ እንደሚያዘው ይያዛሉ እንጅ የተለየ ተጽዕኖ ወይም ማሳደድ ተፈጠረ ሲባል አልሰማሁም። ከምህረት አዋጁ ማለቂያ ከፍተሻው የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ በሪያድ መንፉሃ እየሆነ ስላለው የአይን እማኞችን በአካል ከማግኘት ጀምሮ በስልክ እና በተንቀሳቃሽ ምስል ሳይቀር መረጃዎች ይደርሱኛል። አሁን አሁን ቁጥራቸው ወደ ሃምሳ ሽህ ይዘልቃሉ የሚባሉት ዜጎች ኢትዮጵያውያን በመላ ሳውዲ ይገኛሉ ተብሎ እየተገመተ ነው ። ይህ ቁጥር ቀላል አይደለም ። ጉዳዩ የሃገር የህዝብ ጉዳይ በመሆኑ ዜጎችና የመንግስት ተወካዮች ዘር ፣ ሃይማኖት እና ፖለቲካ ሳይለያየን በጋራ መረጃን ከመለዋወጥ ባለፈ ብዙ መንገድ ሂደን በአደጋ፣ በስጋትና በጭንቀት ላይ ያሉ ወገኖቻችን ብንታደጋቸው መልካም ነበር ። ባሳለፍነው ሳምንት በዘር በሃይማኖትና በፖለቲካ ለየቅል የሚያነጉደው በመላ ሳውዲ አረቢያ ብቻ ሳይሆን በመላ አለም በሚገኙ ወገኖች መሆናቸውን እንደኔ የታዘበ ካለ አላውቅም። ያም ሆኖ መንግስት በአዋጁ ማብቂያ የመጨረሻ ቀን በሰጠው መግለጫ “የቤት ለቤት ሰበራ አይኖርም!” ብሎ ነበር ። ይህ የወጣው መመሪያ ግን በእኛ ላይ አልሰራም። መመሪያው በመንግስት ፈታሾች ለመጣሱ እና በመንፉሃ ለተወሰደው እርምጃ በመንፉሃ በዜጎቻችን ከዚህ ቀደም የተሰሩ ወንጀሎች እንደ ምክንያት ቢቀርቡም ተንቀን ለተወሰደብን ከሰብዕና የወጣ ነውረኛ ወንጀል ግን ብዙዎች አብረን በህብረት ደወርጊቱን በማውገዝ የተሳካ ድምጽ መሰማቱን ተመልክቻለሁ !
በመንፉሃ ዳግም ሁከት ተቀስቅሶ ከበረደ ወዲህ በሪያድ መጠለያ አና በአካባቢው የመረጃ ክፍተት የፈጠረው ከባድ ጭንቀት ነግሷል። ይህ ጭንቀት በሪያድ ከሴቶች እና ከወንዶች ጊዜያዊ መጠለያ ቤት ጀምሮ ከውስጥም ከውጭም አገር ቤትን ባካለለ መልኩ እየተስፋፋ መሆኑን ከሚደርሱኝ መረጃዎች ለመረዳትና ለማወቅ ችያለሁ። በተለይም ከመጠለያ ፣ ከእስር ቤት እና ከነዋሪው ከሚበተኑትና ከሚደርሱት መረጃዎች አንጻር ነዋሪው ችግሩን እየለጠጠው ፣ ችግሮች በራሳቸው እያደጉ የሚያዝ የሚጨበጥ እንዳይጠፋ ስጋቴ ከብዷል ! የከበደውን አደጋ በመረጃ ልውውጥ የተደፋብንን የጭንቀት ደመና ለመግፈፍ መጠቀም ከቻልን እድሉ አላለቀም! በአሁኑ ሰአትም የመረጃው ክፍተት የሚታይበት የመንግስት ዲፕሎማቶችና የነዋሪው ግንኙነት መጠገን የማይቻል አይደለም ። ይቻላል! እናም የመፍትሄ ሃሳብ ልጠቁም …
እኔም እንደ መፍትሔ ሃሳብ በጅዳና ሪያድ የምትገኙ መንግስት ተወካዮች እንደ ከዚህ ቀደሙ በድርጅታዊ አወቃቀር ሳይሆን ሁሉም አትዮጵያዊ እንደ ዜጋ የሚሳተፍና የሚመክርበት ስብሰባ በአስቸኳይ መጥራት ! ሌላው በዙሪያው የምንገኝ ወገኖች በማህበራዊ ገጾች አምድ ላይ የመጻፍ መብታችን የተጠበቀ ቢሆንም በየስርቻው እየተነዛ የስነ ልቦና ጭንቀት እየለቀቀ ያለው ያልተጨበጠና ያልተረጋገጠ መረጃ ከማሰራጨት መቆጠብ ይኖርብናል ! ጠቃሚ መረጃዎች ካሉ ከላይ ይቋቋም ዘንድ ሃሳብ ላቀረብኩት ኮሚቴ በመላክ የመረጃ ክምችት ከመፍጠር ባለፈ ትክክለኛውን መረጃ ለህዝብ አንዲደርስና በጥንቃቄ እና በተረጋጋ ሁኔታ እንድንመራ ይረዳናል።
ሌላውና ዋንኛው ስራ መሰራት አለበት ብየ የማምነው ወደ ሃገር ለማሳፈር የሚደረገው መንገድ እስኪስተካከል ድረስ ማንኛውም ስደተኛ ሰልፍ ማድረግና ወደ ንብረት ሰበራ አመጽ እንዳይሸጋገር ነዋሪውን የማረጋጋት ስራ መስራቱ ግድ ይላል !
መላ ካልተባለ አጠቃላይ ሁኔታው ጥሩ አይደለም ፣ ልዩንትን አስወግደን በህብረት የማንሔድ ከሆነና አሁንም በተቃራኒ ጥላቻ የምንሔደው አካሔድ ፍጹም አዋጣም! ይህ አደጋም ከዜጎች አልፎ በሳውዲና በኢትዮጵያ የቆየ ግንኙነት ታሪክ ትልቁን ስህተት ወደ መስራቱ እንዳያስኬደን ስጋት አለኝ ! ችግሩ ሳያንሰን በግፉአን ዜጎችና በዲፕሎማቶች የሰመረ ግንኙንት እጦት ከሚኮላሸው የነፍስ አድን ህብረት ክፍተት ጣጣ አንድየ ይሰውረን !
የግርጌ ማስታዎሻ :
በመላ አሜሪካና አውሮፖ ብሎም በተለያዩ አለማት የምትገኙ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ ላለው ወገን ድጋፍ ስታደርጉ ማየት ለወገን ያላችሁን ፍቅር ያሳያልና ደስታየ ወሰን አጥቷል። የሳውዲ አረቢያን ባንዴራ ነገር ግን አደራ ! ይህ በአረንጓዴ መደብ ላይ በነጭ ቀለም የቁርአን ቃል የሰፈረበት ባንዴራ በመሆኑ በክብር ልንይዘው ይገባል! በስህተት አለያም በጥላቻ ስሜት ተገፋፍተን ለማቃጠልና ለመቅደድ ብንሞክር መላ የአለምን ሙስሊም አስከፍቶ ወገኖቻችን ወደ ሃገራቸው እንዳይሄዱ ከሚፈጥረው ጫና በተጨማሪ በዜጎቻችን መብት ይከበርልን ጥያቄ ዙሪያ ልናጣ የምንቸለው ድጋፍ ማስተዋል ግድ ይለናል! ይህን አልፈን ከሔድን ተጠቃሚ ካለመሆናችን በተጨማሪ ጸብ ቅያሞታችን ከሳውዲ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመላ የሙሰሊም እምነት ተከታዮች ጋር ስለሚሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል! በፍጹም ጨዋነት የሚካሔደው ሰላማዊ ሰልፍ ለማየት ጓጉቻለሁ!
ከምንም በላይ ደግሞ ከመጣብንን መከራ አንድ አምላክ ይጠብቀን!
No comments:
Post a Comment