ኤርትራ ራሷን እያወደመች ነው የኢትዮጵያ ትምህርት ችግሮች ቋንቋና ያለ እቅደ መስፋፋት ናቸው
ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ በስዊድን አገር በኡፕስላ ዩኒቨርሲቲ የዘመናዊ ታሪክ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ በኢትዮጵያ ትምህርት ላይ ከፍተኛ ምርምሮችን ያደረጉ፣ በመስኩም የታወቁ ምሁር ሲሆኑ ከከዓምናው ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ተጋባዥ ፕሮፌሰር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ1947 በአስመራ ከተማ ተወልደው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአስመራ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጅማ ተከታትለዋል፡፡ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ከአስመራ ዩኒቨርሲቲ በህግ አግኝተዋል፡፡ ከ1972 እስከ 1974 በአስመራ ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩት ፕሮፌሰር ተከስተ፤ በለንደን ዩኒቨርሰቲ ከ“ስኩል ኦፍ ኦሪየንታል ኤንድ አፍሪካ ስተዲስ” ማስተርስ ድግሪ ያላቸውን ያገኙ ሲሆን ዶክትሬታቸውን ከስዊድን አገር ኡፕስላ ዩኒቨርስቲ በታሪክ ትምህርት ሰርተዋል፡፡ የኤርትራን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ይገልፁታል? እኔ የኤርትራን ጉዳይ መከታተል ካቆምኩ አስራ ሶስት አመት ሊሆነኝ ነው፡፡ ምክንያቱም ልለው የምችለውን ሁሉ ብያለሁ፡፡
“Brothers at war” በሚል ከአንድ የኖርዌይ ተወላጅ ጋር በመሆን በፃፍነው መጽሐፍ፤ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርትነት የወንድማማችነት ጦርነት ነው፤ ችግሩን ለመፍታት ሁለቱ አገሮች ወንድማማችነታቸውን ማመን አለባቸው ብለን ደምድመናል፡፡ ከዛ በኋላ ምንም ሠላም አልተገኘም፤ በኔ አስተያየት የሚገኝም አይመስለኝም፡፡ እስከአሁን በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ወንድማማችነቱን ማመን ላይ አልተደረሰም፡፡ የሁለቱ አገራት የወደፊት ግንኙነት ምን የሚሆን ይመስልዎታል? የኤርትራን ጉዳይ ማጥናት የተውኩት ተገድጄ አይደለም፡፡ በአንድ በኩል በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ ነገሮች በጣም በጎ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ለውጥ እየተካሄደ ነው የሚል አቋም ስላለኝ ሲሆን በሌላ በኩል የኤርትራ ጉዳይ አልቆለታል ብዬ ስላመንኩ ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ኤርትራ ራሷን በራሷ እያወደመች ነው፡፡ ኤርትራ ምንም ተስፋ የላትም ብዬ አምናለሁ፡፡
ወደ ጥያቄሽ ስመለስ… የኤርትራና የኢትዮጵያ ሁኔታ እንዴት ይቀጥላል ለሚለው በኔ አስተያየት ከዚህ በኋላ ጦርነት አይካሄድም። ኤርትራ ግን የሶማሊያን አይነት የምትሆንበት፣ በአንድ ልትመራ ወደማትችልበት ደረጃ ልትደርስ ትችላለች ብዬ አምናለሁ፡፡ ከኢሳያስ አፈወርቂ በኋላ ኤርትራ ሶማሊያን ትሆናለች በሚል የሚሰጡ አስተያየቶችን ይቀበላሉ ማለት ነው? አዎ፡፡ ኢሳያስ እስካለ እሱ የፈጠረው ስርዓት ይቀጥላል፡፡
የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አቋም እና የኢትዮጵያ መንግስት የያዙት አቋምም ለዚህ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ከኢሳያስ በኋላ ግን የኢኮኖሚ ችግር ብቻ ሳይሆን የብሔር ግጭቶች አሉ፡፡ ቆላማው የኤርትራ ክፍል የራሱ አጀንዳ አለው፤ ደገኞቹ ደግሞ እርስበርሳቸው በጣም የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ ይህን መያዝ የሚችለው ኢሳያስ ብቻ ነው፡፡ ከሱ በኋላ አገሪቱን አንድ አድርጐ ወደፊት ሊያራምድ የሚቻል ይመጣል ብዬ አላምንም፡፡ የኤርትራ ጥያቄ ለምርጫ በቀረበበት ወቅት ከነበሩ አማራጮች ዋነኞቹ፤ መገንጠል፣ በፌዴሬሽን መቆየት እና አንድነት የሚሉ ነበሩ፡፡ በውድም ይሁን በግድ ሁሉም አማራጮች ተግባራዊ ሆነዋል፡፡ ኤርትራ ከተገነጠለች 23 አመት ሊሆናት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አንድነት የሚለው አቋም ቅሪት አለ ወይስ ሙሉ በሙሉ ተሸርሽሯል? የደጋው ኤርትራ ባህል በመሠረቱ ኢትዮጵያዊነቱን እንደያዘ ነው፡፡ ኢሳያስ ስልጣን እንደያዘ በሶስተኛ አመቱ ሆላንድ መጥቶ ባደረገው ውይይት፤ እኔም እድሉን አግኝቼ ሰምቼዋለሁ፡፡ እኛ ሠላሳ አመት ሙሉ ታግለን ብዙ ሰው ሞቶብን፣ ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ የኤርትራ ህዝብ የከፈልነውን መስዋዕትነት ረስቶ ከኢትዮጵያ ጋር ወዲያ ወዲህ ይላል ብሎ ተናገረ፡፡ ኤርትራ ነፃ ከወጣች ጊዜ ጀምሮ እስከ ጦርነቱ ድረስ የኤርትራ ህዝብ ከኢትዮጵያ ተለይተናል የሚል ብዙ ስሜት አልነበረውም፡፡ ደርግ መሸነፉ ላይ ነበር እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር የመለየቱ ብዙ ግንዛቤ አልነበረውም፡፡ ጦርነቱ ሲጀመር ስሜቱ መቀዛቀዙን መናገር ይችላል፡፡
ሌላው በደጋው ኤርትራ ያለው ትግርኛ ተናጋሪ ከጣሊያን ጊዜ የጀመረ የገዢና የተገዢ ግንኙነት ነበረው፡፡ እኛን ጣልያን ነው የገዛን በሚል፣ ትግራይ ያሉትን ትግሪኛ ተናጋሪዎች “እናንተ ከአዲግራት፣ ከመቀሌ፣ ከአድዋ የምትመጡ…” የሚል ነገር ነበር፡፡ ከጦርነቱ በኋላ የትግራይ ህዝብ የራሱን ማንነት ኢኮኖሚ በማሻሻል ላይ ስለሚገኝ በነዚህ ሁለት ትግሪኛ ተናጋሪዎች መካከል ያለው ፉክክር ማን ትግሬን ይወክላል የሚል ነው፡፡ ይህ ለጊዜው ችግር ሊፈጥር ይችላል፤ ግን እኔ እስከምረዳው ድረስ ኢትዮጵያዊነት ስሜት፣ ባህል፣ አስተሳሰብ አለ የምንል ከሆነ በደጋማው ኤርትራ አሁንም አለ። ከዛ ደግሞ ከአፋር ጋር ያለውን ትስስር ማየት ይቻላል፡፡ በኤርትራ ያሉ ቢለኖች አገዎች እንደሆኑ አይጠራጠሩም፤ አሁን ባለው ሁኔታ ምንም ማድረግ አይችሉም፡፡ ኩናማዎችንም ካየሽ ተመሳሳይ ነው፡፡ ወቅታዊውን የአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ እንዴት ይገልፁታል? በአፍሪካ ቀንድ የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያን ካየን፣ ለሁለቱም የሚጠቅማቸው የሶማሊያ አንድ መሆን ነው፡፡ አሁን ያለው ሁለት ሶማሊያ በኔ አስተያየት ረጅም የሚጓዝ አይደለም፡፡ ከጥቅም አንፃር ካየነውም፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሶማሊያ አይጠቅምም፡፡ በኤርትራና በኢትዮጵያ በኩል ስናየው፣ ኤርትራ የምትፈልገው ድንበር ሊኖር አይችልም፡፡ ይህን ደግሞ ሁለቱም አገሮች ያውቁታል፡፡
የኤርትራ ሁኔታ ከኢሳያስ በኋላ አዲስ መልክ ይይዛል፡፡ በአዲሱ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሚና ምን ሊሆን እንደሚችል በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ የኢትዮጵያን ጥቅም ለመጪው ሁለት መቶ ሶስት መቶ አመት ሊያራምድ የሚችል ሆኖ መቀረፅ ይገባዋል፡፡ የኢትዮጵያን የፌደራል አወቃቀር እንዴት ያዩታል? አወቃቀሩ በፌደራል መሆኑ ጥሩ ነው፡፡ በብሔር መሆኑ ግን መጥፎ ነው፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ያደረገው ትልቁ ስህተት ነው፡፡ ፌደራል ስርአት በፊትም የነበረ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የኋላ ታሪክ ካየሽ የፌደራል አወቃቀር አዲስ አይደለም፡፡ ንጉሠ ነገስት ስንል እኮ ንጉሶች አሉ፡፡ ከበላያቸው ንጉሠነገስት አለ ማለት ነው፡፡ አካባቢያዊ ፌደራሊዝም ነበር፡፡ የኤርትራ ህዝብ አሁን ያሉበትን የነፃነት ሁኔታ ከቀድሞው ጋር ሲያስተያዩት ምን ትርጉም ይሰጥዎታል? እኔ እኮ በመጀመሪያም ኤርትራውያኖች ከማን ነው የሚገነጠሉት የሚል አቋም ነው ያለኝ። ማነው ከማን የሚገነጠለው? የደቡብ ወይም የኦሮሞ ህዝቦች እንገነጠላለን ቢሉ ኖሮ ምክንያት ነበራቸው፡፡ የኤርትራ የነፃነት ጥያቄ በተነሳበት ወቅት ኤርትራውያኑና ከላይ የጠቀስኳቸው ህዝቦች በኢትዮጵያ ውስጥ ያገኙትን እድል (Comparative advantage) ስናይ፣ ኤርትራውያኑ በጣም ተጠቃሚ ነበሩ፡፡ (በጣሊያን፣ በእንግሊዝ፣ በፌዴሬሽኑ ዘመን) በ1960ዎቹ የአዲስ አበባ ሀብታሞቹ እነሱ ነበሩ። በትምህርት መስክ ሃያ አምስት በመቶ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች ኤርትራውያን ነበሩ። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችንም ካየሽ 25 በመቶ የሚሆኑት ኤርትራውያን ነበሩ፡፡ ከተማረው ሰላሳ አምስት በመቶው ክፍል ኤርትራውያን ነበሩ፡፡
ይህን እድል ያገኙ ሰዎች ከኢትዮጵያ እንገነጠላለን ሲሉ ምክንያቱን ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ምንም ምክንያት አልነበራቸው፡፡ ለነፃነት የተደረገው እንቅስቃሴ 30 አመት ቢፈጅም ስልሳ ሺህ ሰው ቢሞትም በቂ ምክንያት አልነበረውም። የኔ ጥናት የጣልያን ቅኝ አገዛዝ በኤርትራ የሚል ነው። እንዲገባኝ ሞክሬያለሁ፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል እንዳለበት የሚያሳይ ምንም ነጥብ አላገኘሁም፡፡ ነፃ ወጣን አሉ፡፡ ሁለት አመት ሳይቆዩ እኛ የታገልነው ለነፃነት ብቻ አይደለም፤ የኛ ዕድል ከኢትዮጵያ ጋር ነው ማለት ጀመሩ፡፡ ይህን የሚሉት ተገደው ነው፤ ምክንያቱም የኤርትራ ኢኮኖሚ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ በራሱ ሊቆም የሚችል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ልዩ አገር ነች፤ ነፃነቷን ጠብቃ የቆየች አገር ናት፡፡ የኤርትራ ቴሌቪዥን በቅርቡ “Ancient Eritreans” (የጥንት ኤርትራውያን) የሚል ዶክመንተሪ አቅርቦ ነበር፡፡ አይተውታል? (ረጅም ሳቅ) አላየሁትም፡፡ ግን ምንም አዲስ ነገር አይፈጥርም፡፡ ወጣቶቹ ኢትዮጵያን አያውቋትም፤ ነገር ግን መንግስት የሚያደርገው አንድ ነገር ነው፣ ህዝቡ የሚያስበው ሌላ ነገር ነው፡፡
መንግስት በቴሌቪዥን የሚየሳየውና ህዝቡ የሚመኘውና የሚያስበው ሌላ ነው፡፡ እስከቅርብ ጊዜ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ ብትለያይም በድብቅ ወጣቶቻቸውን ለትምህርት ወደ ቤጌምድር (ጐንደር) ይልኩ ነበር፡፡ የኢሳያስን መረጃ በማየት ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ ኤርትራዊውን ማን አገኘው፡፡ የተለየን ነን የሚል አቋም የት ነው ያለው? በኤርትራ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ምን ያህል አለ ለሚለው መልስ ለማግኘት ድንበሩ መፍረስ አለበት፡፡ ለሁለቱ ህዝቦች መፍትሔ የሚሆነው በኤርትራ በኩል እየተጠየቀ ያለው ድንበር ሲሰመር ሳይሆን ከደርግ ሽንፈት በኋላ የተሰመረው መስመር ሲፈርስ ነው፡፡ ትናንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቋንቋ፣ እውቀት እና የጋራ ህልውና በሚል የውይይት መነሻ ጥናት አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ትምህርት ላይ ጥናቶችን አድርገዋል፡፡ ዕይታዋ ምንድን ነው? ዋና ጥናቴ እሱ ነው፡፡ ትምህርት በጣም ተዳክሟል፡፡ የተዳከመው በሁለት ምክንያት ነው ብዬ አስቀምጣለሁ፡፡ አንዱ ያለዕቅድ መስፋፋቱ ነው። የሚፈለጉ ህንፃዎች፣ አስተማሪዎች፣ መፃሕፍቶች ሳይሟሉ እንዲሁ ሠፍቷል፡፡ ሌላው ዋነኛ ምክንያት የቋንቋ ጉዳይ ነው፡፡ እንግሊዝኛ ቋንቋ አያዋጣንም፡፡ በራስ ቋንቋ መማር የህልውናና የመበት ጥያቄ ነው፡፡ ዜግነትዎ ከየትኛው ነው? ስዊድናዊ ነኝ፡፡
No comments:
Post a Comment