በሳውዲ አረቢያ በሚገኙ ዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ያለው በደል እና ስቃይ መጠኑ ከመጨመር አልፎ ሕይወትን እስከማሳጣት መድረሱ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህን በደል እና ስቃይ ለመቃወም እና ሀዘናችንን ለመግለፅ በዛሬው ዕለት ማለትም ህድር 6 ቀን 2006 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው በሳውዲ አረቢያ ኢምባሲ ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ የተጠራ ቢሆንም በመንግሥት ታጣቂዎች በተወሰደ በአሰቃቂ እርምጃ ሰልፉ ሊካሄድ አልቻለም፡፡
እኛ ኢትዮጵያን በውጭ በሚገኙ ዜጐቻችን ላይ የሚደርሰው በደልና ግፍ እንዲቆም፣ ይህንንም ድርጊት የፈፀሙት ለሕግ እንዲቀርቡና የተጐዱ ዜጐች ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም በዜጐቹ ላይ ያሳየውን ቸልተኝነት በአስቸኳይ በማቆም ተገቢ የሆነውን የመንግሥት ኃላፊነት እንዲወጣ ቢጠየቅም፤ ሰልፉ በተቃራኒው በመንግሥት ታጣቂዎች በተወሰደ አሰቃቂ እርምጃ ተጠናቋል፡፡
በሳውዲ እየተፈፀመ ያለውን በደል በመቃወም በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያዊያን ድምፃቸውን በማሰማት ላይ ቢሆኑም እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን በገዛ ሀገራችን ድምፃችንን እንኳን እንዳናሰማ ታፍነናል፡፡ በዚህም እንቅስቃሴ ላይ የተሳተፉ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ድብደባ፣ እንግልትና እስር ተፈፅሞባቸዋል፡፡
የመንግሥት ፖሊሶች የራሳቸውን ዜጋ በመደብደብና በማሰቃየት ብሎም በማሰር በሳውዲ በሚገኙ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን ላይ የተፈፀመውን በደል ሀገር ውስጥ በሚገኙ ንፁሐን ወገኖቻቸው ላይ ደግመውታል፡፡
ይህ በውሸት ዲሞክራሲ ስም የተደበቀው አምባገነን መንግሥት ሕዝብን ለማሸማቀቅ የወሰደውን እርምጃ ወደ ጐን በመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅድም አያቶቹን በማስታወስ ያስረከቡትን ክብር ከማስመለስ ወደ ኋላ እንደማይል እርግጠኛ መሆናችንን እንገልፃለን፡፡
ፓርቲያችን እንዲህ አይነቱን የለየለት የመንግሥት ሕገ ወጥ ተግባር ትኩረት ሰጥቶ የሚመለከተው መሆኑን እየገለፅን፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጐናችን እንዲቆም በአፅንኦት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
No comments:
Post a Comment