November 16, 2013
በየቦታው ተበትናችሁ ለአገር የሚበጅ ስራ እየሰራን ነው ለምትሉ የፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሙሉ። እንዴት ከርማችሁልኛል? እንደ አገር ልጅ ብናፍቃችሁም እንኳ የናንተ እንጀራና የኔ ኑሮ አልገጥም ብሎ ካጠገባችሁ ከራቅሁ አመታት አልፈዋል። ብዙ ሰዎች የሰው ልብ ያላችሁ፣ አዛኝ አንጀት ያላችሁ መሆናችሁን ይጠራጠሩ ይሆናል። እኔ ግን እንደሱ አላስብም ብዙዎቻችሁ ድህነት በግዱ ገፍትሮ እዚህ ውስጥ እንደ ጨመራችሁ አውቃለሁ። ምክንያቱም ብዙ ጓደኞቼ የሚላስ የሚቀመስ ሲያጡ፣ እንደኔ ለመሰደድ መድፈር ሲያቅታችውና ቢፈልጉም እንኳን ሱዳንና ኬንያ የምታደርስ ገንዘብ በማጣታቸው እንጀራ ብለው የገቡ ብዙ እንዳሉ አውቃለሁ። እነዚህ በሙሉ የድሀ ልጆች ቤት ተቀምጦ በረሀብ ከመሞት የምችለውን አድርጌ እኖራለሁ ብለው እንደሚኖሩ አውቃለሁና በተለይ እናንተ ከዚህ የመከራ ማጥ እንድትወጡልኝ አምላኬን መለመን አልተውኩም። ግምገማ ፈርታችሁ የራሳችሁን ወገን በዱላ መጨፍጨፍ እንዴት እንደሚሰማ አውቀዋለሁ። ባዶ እጁን ያለን ሰውማ በጥይት መግደል የባሰ ነው። በተለይ ያልበላን ሆድ ተርቦ የሚያውቅ ሆድ እንዲህ ያለውን ግፍ በደንብ ያውቃል። ዞሮ ዞር የሚመታውም ሆነ የሚገደለው የናንተ ዘመድ እንኳን ባይሆን አንዱ ቦታ ተመድቦ የሚሰራ የባልደረባችሁ ዘመድ መሆኑ መች ይቀራል።
ጫካ የነበራችሁና ለነፃነት ሲባል የተቀላቀላችሁ ወገኖቼም ብትሆኑ ብዙዎቻችሁ የድሀ ገበሬ ልጆች ናችሁ ወይም ነበራችሁ። ድህነት ጣዕሟን ታውቃላችሁ። ወገናችሁ በሰው አገር እንደ ውሻ ሲቀጠቀጥ ወንጀለኛ ነው ወይም ሕገ ወጦች ናቸው ተብሎ ይበሏቸው የሚል አንጀት ይኖራችሃል ብዬ አላስብም። ከተወለደበት ቀዬ ወደማያውቀው አገር ብን ብሎ የሚሄደው የቸገረው ብቻ ነው። እጅና እግር እያለኝ እናትና አባቴ በረሀብ አይሞቱም ያለ ብቻ ነው። የምታጠባው ጡት ደርቆባት ልጆቿን የምታቀምሰው አጥታ ባሏ እጅና እግር እያለው ስራ አጥቶ ሲንከራተት ያየች ነች ጉዱን እያወቀች አረብ አገር የምትሄደው። አንዳንዶቻችሁ ሲከፋችሁ ምናባቱ ብላችሁ ጫካ እንደገባችሁት ባወጣ ያውጣው ብለው ያሉት የተሰደዱት የናንተው ቢጤ ምስኪኖች፣ ሀገራቸውንና ወገናቸውን የሚወዱ ድሆቹ ናቸው። ለነዚህ መከረኞች አለሁ ማለት ካቃታችሁ የትኛውን አገር ነው የምትጠብቁት? የትኛውን ነፃነት ለማምጣት ነው ጫካስ የገባችሁት? ምነው ታውቁት የለም የሱማሌ ስደተኞችን ተቀብለን አላኖርንም? ከ ኤርትራ የመጡ ስደተኞች ኢትዮጵያ ይኖሩ የለም? አረ ምን ስደተኞች ባለስልጣኖቹስ ቢሆኑ እነማን ሆነው ነው? ደግሞስ ከሀገራችን ይውጡ ካሉ አሳፍሮ መላክ ነው እንጂ እንደ አይጥ መንጋ መጨፍጨፉንስ ምን አመጣው? ምናልባት ጥፋት ስለሰሩ ነው ብለው ነግረዋችሁ ከሆነ ውሸት ነው። ሲብስባቸው የሚደርስላቸው ሲያጡ ባንዲራ ለብሶ መታረድ ቢሰለቻቸው ነው መቆጣት የጀመሩት። እውነት ቢኖራቸው ኖሮ መረጃውን ሁሉ አይከለክሏችሁም ነበር። አይናችሁን ሸፍነው ጆሮአችሁን ደፍነው ከሰውነት ወደ አውሬነት ለመቀየር ስለሚፈልጉ ነው። አረቦቹ ኢትዮጵያውያኑን በስፋት መግደል የጀመሩት የሀገራችሁ መንግስት ውሰዱልን ብንል እምቢ ስላሉ ነው እያሉ ነው።
ወገኖቼ ያለባችሁን ችግር አውቃለሁ ብዙ ብጽፍ ለማንበብም እድል አታገኙ ይሆናል። ግን ትንሽም ቢሆን የተሰማኝን ስሜት ላካፍላችሁ ብዬ ነው። አይምሰላችሁ የናንተን ችግር ሕዝቡም ያውቀዋል። እናንተ የእንጀራ ጉዳይ ሆኖባችሁ እንጂ አንጀታችሁ እርር እንደሚል አውቃለሁ። ከዚያም በላይ ደግሞ ብዙዎቻችሁ እህቶቻችሁ የወንድም የእህቶቻችሁ ልጆች ሁሉ አረብ አገር እንዳሉ አውቃለሁ። አንዳንዶቻችሁ እጮዎቻችሁ ጭምር ትንሽ ገንዘብ ሰርተው ኑሮ ለማሳመር ሲሉ አረብ አገር እንደሄዱባችሁ ሁሉ አውቃለሁ። ያው ነና የኔም ዘመዶች እኔኑ እያስቸገሩ እዚህ ተቀምጠን የማይሆን ነገር ውስጥ ከመግባት ሲሉ ስቅቅ እያልኩ ገንዘብ እልክላቸው ነበር። ካልሆነልን በዝሙት መተዳደር ነው እድላችን ያሉኝም አሉ። እቤት ተቀምጨ ረሀብ በሶስት ቀን ከሚገድለኝ ትንሽ ፋታ የሚሰጠው ኤድስ ይሻላል የሚሉ ሁሉ እንዳሉ አውቃለሁ፣ እናንተም ይህን በደንብ ታውቃላችሁ። ይህን እየሰማ አልጨክን የሚል ሆድ ያለው ግማሹ ገንዘቡን ልኮ ሌላውም ጥሪቱን ሽጦ ወይም ተበድሮ ነወ የላከው። ይህ ወገኑን የአረብ መጫወቻ ሲሆን እንባ አይደለም ለምን ደም አያስለቅስም። እናንተ ከዚህ የባሰ ሀዘን ውስጥ እንደምትሆኑ አውቃለሁ። ለመነጋገር ቀርቶ ለማሰብም እንደምትፈሩ ይገባኛል። ጥርነፋው የሚያወላዳ አይደለም። ግን ከእሳት የሚያወጣ ሀይል ያለው አምላክ አለላችሁ። የወገን ግፍ በቃ በሉ። ስለወገናችሁ መዋረድ ተቆርቆሩ። ይህን ሰርቶ እንጀራ ከመብላት ታግሎ መውደቅ ይመረጣል በእውነት ክፉ እንዲነካችሁ አልፈልግም ነገር ግን በዚህ ከቀጠልን ለናንተም እየፈራሁ ነው።
እናንተ እኮ የሀገር መከላከያ እንጂ የባለስልጣን ዘበኛ አይደላችሁም። ሀገር ስትዋረድ የአስራ አምስትና አስራ ስድስት አመት ልጆች በስድስትና ሰባት ወንድ እየተደፈሩ ደም በደም ሆነው በየሜዳው ሲጣሉ ምን አንጀት ያስጨክናችሁ ይሆን? ወገኖቼ አገራችን ብዙ አምባገነን መንግስታትን አስተናግዳለች። ሰራዊቱና ፖሊስም ለዚህ መሳርያ ሆኖ ያገለገለበት ወቅት ነበር። ነገር ግን የሀገር መከላከያ ሙሉ በሙሉ በጠላት እጅ ወድቆ ለጠላት አድሮ ኢትዮጵያን በዚህ ደረጃ ያዋረደበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም። የዚህ የጠላት ጦር አጋር መሆን ወንጀል ነው። ልጆቻችንን አትንኩብን ወንድም እህቶቻችንን አትግደሉብን ብለው ሰልፍ የወጡ ሰዎችን አረቦች ፊት፣ ኤምባሲያቸው ፊት ለፊት በናንተ ዱላ መጨፍጨፍ ወንጀል ነው። ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ከጣልያን ጎን በመሰለፍ የሀገራቸውን ሕዝብ ያስጨፈጨፉ ጥቂት ባንዳዎች ነበሩ። የአንድ ሀገር ጦር እንዳለ የባንዳ ሰራዊት ሲሆንና ለእለት እንጀራ ሲባል የዚህ ጦር አባል መሆን ጭካኔ ነው አውሬነትም ነው። አውሬም እንኳ የራሱን ዘር መልሶ አይበላም። ለመሆኑ እናንተ ከማን ተፈጠራችሁ?
ይህ ጭካኔያችሁን የተመለከተ ኢትዮጵያዊ የያዛችሁትን ቆመጥ ተቀብለው ሊያደርጓችሁ የሚችለውንስ ታውቁ ይሆን? ወገናችሁን በመጨፍጨፍስ የደም እንጀራ ስትበሉ እንቅልፍስ እንደምን ትተኛላችሁ? ድህነት ክፉ ነው ሆድ ብዙ ያደርጋል ግን አሁን በቃ ልትሉ ይገባል። ልታምጹ እምቢ ለትሉ ይገባል። ጥያቄው የስልጣን አይደለም፣ የሀይማኖት አይደለም፣ የዘር አይደለም የነጻነት ጥያቄ ነው! የክብር ጥያቄ ነው! የ ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ነው።
ከጠላቶቻችን ጋር ተባብራችሁ የሀገራችሁን ሕዝብ ለመጨፍጨፍ ቁርጠኛ ሆናችሁ ከቀጠላችሁ ይሄ ሕዝብ ሊያደርጋችሁ የሚችለውን አስባችሁ ይሆን? ወገኖቼ ይህ ቀን ሳይጨልም እምቢ በሉ። ዘረኞች፣ የአረብ አሽከር ሆነው ሀገራችሁን መሬታችሁን እየሸጡ፣ ሚስት ልጆቻችሁን ለግርድና እየላኩ ሀብት ሲያጠራቅሙ የነሱ ዘበኛ መሆንና የእንደዚህ አይነት ከሀዲዎች አጋር መሆን ጨካኝነት ብቻ ሳይሆን የሀገር ጠላትነት ነው። በታሪክ የሚያስጠይቅ በክህደትም የሚያስጠይቅ ነው። እምቢ የምትሉበት ጊዜ አሁን ነው። በየሜዳው ላይ እየተደፈሩና እየተገደሉ ያሉ ኢትጵያውያን ደም ይፋረዳችኋል። ይህ መረጃ ለሁሉም ሊደርስ የሚገባው ነው ላልሰማው አሰሙ። ይህ የፍረሀት አጥር ይፈርሳል ያኔ የታጠቃችሁት መሳርያ ዋጋም አይኖረውም። ብዙዎች ወገኖቻቸውን ለመቀላቀል መነሳሳትን አሳይተዋልና እናንተም ተነሱ፣ ቁጣችሁን አሳዩ ወገናዊነታችሁን አስመስክሩ! አገራችሁን ኢትዮጵያንና ሕዝባችሁን ታደጉ። የመገናኛ ብዙሃን በድምጽም ቢሆን መልዕክቴን ያደርሱላችሁ ይሆናል አመጽ በልብ ይጠነሰሳል ሁኔታ ሲፈቅድ ደግሞ ይፈነዳልና ልባችሁ ይሸፍት እምቢታችሁን መግለጫ መንገድ አስቡ። ኢትዮጵያ ከዚህ መዐት ተውጣለችና የመፍትሄው አካል ሁኑ። አምላካችሁ የእውነቱን መንገድ ያሳያችሁ።
ወንድማችሁ ዳኛቸው ቢያድግልኝ
No comments:
Post a Comment