ህዳር ፳(ሃያ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባል እና የኢትዮጵያን የ1997 ምርጫ የታዘቡት ወ/ሮ አና ጎሜዝ ይህን የተናገሩት አዲስ ስታንዳርድ ለተባለ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ነው።
በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለው የአውሮፓ፣ አፍሪካና ካረቢያን አገሮች የፓርላማ ጉባኤ ላይ የተገኙት ወ/ሮ አና የአምባገነን ምንጭ የሆነው መለስ ዜናዊ ቢሞትም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካዊ ለውጥ አለመምጣቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ተለውጣለች በማለት በአደባባይ የሚናገሩት ባለስልጣናት በግል ሳነጋግራቸው በኢትዮጵያ ፈጣን ለውጥ መደረግ አለበት ብለው ይላሉ ያሉት ወ/ሮ አና፣ አቶ ሀይለማርያም ከሙስና ጋር በተያያዘ አንዳንድ መጠነኛ እርምጃዎችን ቢወስዱም፣ የትግራይ ተወላጅ ባለመሆናቸው ስልጣናቸውን ለማቆየት እየተቸገሩ መሆኑን ገልጸዋል። ቀደም ብለው እስክንድር ነጋንና ርእዮት አለሙን ለመጎብኘት በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ትእዛዝ ወደ ቃሊቲ የተጓዙት የአውሮፓ ህብረት ልኡካን፣ በእስር ቤቱ ሀላፊዎች መከልከላቸው በአገሪቱ ውስጥ ያለውን እውነታ የሚያሳይ ነው ያሉት ወ/ሮ አና በኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ የስልጣን ሽኩቻ እንዳለ እንደሚያውቁም ተናግረዋል።
የመለስ ዜናዊ መንግስት ስልጣኑን ለማቆየት ሲል ሙስሊምና ክርስቲያኑን ለማጋጨት ጥረት ሲያደርግ እንደነበርም የፓርላማ አባሉዋ ተናግረዋል። የኢትዮጵያን ወጣቶች አፍኖ መያዝ አይቻልም ያሉት ወ/ሮ አና የፖለቲካ ሜዳውን ለዲሞክራሲ መክፈት ኢትዮጵያን ከውድቀት እንደሚታደጋት ገልጸዋል።
No comments:
Post a Comment