ህዳር ፭(አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአውሮፓና አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮያውያን በሰልፍ ተቃውሟቸውን ሲገልፁ ውለዋል።
በሳዑዲ ዐረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍ ተባብሶ መቀጠሉን ተጠቂዎቹ ለኢሳት ገለፁ።
በሪያድ ወደማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የተወሰዱ ኢትዮጵያውያን ካሉበት ስፍራ ሆነው ለ ኢሳት በስልክ እንደገለፁት፤ በትናንትናው ዕለት ብቻ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በከባድ መኪናዎች እየተጫኑ ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል።
ስደተኞቹ-ለሳዑዲ ፖሊሶች፦” ወደ ሦስተኛ አገር የማታሻግሩን ከሆነ ወደ አገራችን መልሱን” የሚል ጥያቄ ቢያነሱም፤ “ከብዛታችሁ የተነሳ ማንም አገር አይቀበላችሁም፤እንኳን ሌላ አገር ሊቀበላችሁ የራሳችሁ መንግስትም ሊቀበላችሁ ፈቃደኛ አይደለም” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ተናግረዋል።
የ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በትናትን ምሽቱ የዜና እወጃው መንግስት ዜጎቹን ከሳዑዲ ዐረቢያ ማመጣት እንደጀመረ በመጥቀስ፤ በመጀመሪያው ዙር 54 ስደተኞችን እንዳመጣ መግለፁ ይታወሳል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች ችግር ላይ ወድቀው በምንገኙበት ሰዓት 54 ሰዎችን ወስዶ ‘ዜጎቼን እየመለስኩ ነው”ማለቱ አሳዝኖናል ያሉት በሪያድ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፤ የኢቲቪን ዜና ሢሰሙ ይበልጥ መበሳጨታቸውን ለኢሳት እያለቀሱ ተናግረዋል።
“በማናውቀው ቦታ በጅምላ አንድ ላይ አጉረውናል፤ በቂ ምግብና ውሃ አይሰጠንም…እህቶቻችንን አናስደፍርም ብለን ስንነሳ ይደበድቡናል..ይገሉናል…ከሞት የተረፍነውን ደግሞ በረት ወስጥ አጉረው በራብ ይቀጡናል”ብሏል-ከድር የተባለ ኢትዮጵያዊ ለ ኢሳት ያለውን ሁኔታ ሲያብራራ።
ይህ በ እንዲህ እንዳለ በተለያዩ የ አውሮፓና የአሜሪካ ከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ዐረቢያ በሚገኙ ዜጎቻቸው ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልት በሰልፍ ሲቃወሙ ውለዋል።
በጀርመን፡ፍራንክፈርት ኟ፡በስዊድን-ስቶኮልም በሚገኙ የ ሳኡዲ ኤምባሲዎች ፊትለፊት በተደረጉ ሰልፎች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በመገኘት በሳዑዲ መንግስት ላይ ቁጣቸውን ገልጸዋል።
የሳኡዲ ዐረቢያን ንጉስ ፎቶ በቁጣ ያቃጠሉት ሰልፈኞቹ- በወገኖቻቸው ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ ባስቸኻይ እንዲቆም ጠይቀዋል።
በፍራንክፈርትና በስዊድን በተደረጉት የዛሬዎቹ ሰልፎች ብዙ ኢትዮጵያዊ ከየሚኖርበት ከተማ በመንቀልና የ ኤምባሲዎቹን ፅህፈት ቤቶች በመማጨናነቅ ድምፁን ሲያሰማ ውሏል።
በስዊድን የሰልፈኞቹ ሁኔታ ያሰጋቸው የሳዑዲ ኤምባሲ ሀላፊዎች የ አገሪቱን ፖሊስ በመጥራት ጥበቃ እንዲደረግላቸው አድርገዋል።
በ ሆላንድ-ደን ሀግ የፊታችን ሰኞ፣ በእንግሊዝ -ለንደን የፊታችን ማክሰኞ፣በስዊዘርላንድ -በርን በማግስቱ ረቡዕ፣ እንዲሁም በኖርዌይና-ኦስሎ እና በሌሎችም የአውሮፓ ከተሞች በተከታታይ ሰልፎች እንደሚደረጉ የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዋሽንግተን ሲቲ እና በተለያዩ የ አሜሪካ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ዛሬ በተመሣሳይ የተቃውሞ ሰልፎችን አድርገዋል።
በወገኖቻቸው ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ እንዲቆም፣መንግስትም ዜጎችን የመጠበቅና የመታደግ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።
በአሜሪካ-በሲያትል እና በሐውስተን እንዲሁም በፊንላንድ ሄልሲንኪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ነገ አርብ በተመሣሳይ መንግድ በየከተሞቹ በሚገኙ የሳኡዲ ዐረቢያ ፅህፈት ቤቶች ፊት ለፊት ሰልፍ የሚያደርጉ ሲሆን፤ የፊታችን እሁድ ደግሞ በደቡብ-ኮሪያ-ሴዑል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ ሰልፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
No comments:
Post a Comment