Thursday, November 7, 2013

የኢትዮ ምህዳር ጋዜጠኞች ያለምንም ክስ በገንዘብ ዋስ ተለቀቁ

በለገጣፉ ፖሊስ ከቢሮው ቅዳሜ ዕለት የተወሰደው ጋዜጠኛ ሚልዮን ደግነውና ሰኞ ማለዳ የስራ አጋሩን የተቀላቀለው ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ በእስር ከቆዮ በኋላ ትናንት አመሻሽ እያንዳንዳቸው 600 ብር ዋስ በማስያዝ መለቀቃቸው ታውቋል፡፡

ጋዜጠኞቹ ለእስር የተዳረጉት በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ በለገጣፉ የተፈጸመን የመሬት ሙስና የሚያትት ዜና እና ዘገባ በመስራታቸው መሆኑም ታውቋል፡፡ፖሊስ ቅዳሜ የያዘውን ሚልዮንን በማረፊያ ቤት በማቆየት ቃሉን የተቀበለው ሰኞ ምሽት ነው፡፡ሰኞ ባልደረባውን በዋስ ለማስፈታት ወደ ለገጣፉ ያመራው ጌታቸው የታጠቀውን ቀበቶ በማውለቅ ሚልዮንን በማረፊያ ቤት እንዲቀላቀለው ተደርጓል፡፡ፖሊስ የጌታቸውን ቃል የተቀበለው ከአንድ ቀን እስር በኋላ ማክሰኞ ምሽት ነበር፡፡


ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በፖሊስ ጣብያው ውስጥ በሚገኝ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ የተነገራቸው ጋዜጠኞቹ ፍትህ በማግኘት ከህገ ወጡ እስር እንደሚለቀቁ በማሰብ በአንድ አነስተኛ ክፍል ዳኛውን መጠባበቅ ይጀምራሉ፡፡አንድ ሰው ወደ ክፍሏ በመግባት ለሁለቱ ጋዜጠኞች ዳኛ መሆኑን ይነግራቸውና በቀጥታ ወደ ጉዳዮ ይገባል ‹‹የተከሰሳችሁት በጋዜጣ ላይ ባወጣችሁት ዘገባ ምክንያት ነው፡፡ፖሊስ ምርመራዬን ስላላጠናቀቅኩ የ14 ቀን ጊዜ ይሰጠኝ ብሏል፡፡እኛ ግን የ4 ቀን ግዜ ሰጥተነዋል፡፡ስለዚህ እስከ አርብ እዚሁ እንድትቆዮ ወስነናል››ይላቸዋል፡፡ከሳሽ አቃቤ ህግ ባልቀረበበትና ሌሎች የፍርድ ቤት ስነ ስርዓቶች ባልተከበሩበት ሁኔታ በቀጥታ ያለ ምንም የግራ ቀኝ ክርክር ውሳኔ የተነገራቸው መሆኑን በመቃወም ጌታቸው ወርቁ ቅሬታውን አቅርቧል፡፡‹‹አትቸኩል እኛ እናንተን ለመርዳት ነው እዚህ ያለነው፡፡ይህ ችኮላህ ለብዙ ነገር ይዳርግሃል፣ለማንኛውም ጌዜ ቀጠሮው ወደ ሐሙስ እንዲያጥር ይደረግልሃል››መባሉን ለፍኖተ ነጻነት ተናግሯል፡፡

ከፖሊስ ጣብያው ጊዜያዊ ፍርድ ቤት ከወጡ በኋላ ወደ ክፍላቸው እንደገቡ ጉዳያቸውን የያዘው መርማሪ ሁለቱን ጋዜጠኞች በመያዝ ሰንዳፋ አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት ያቀርባቸዋል፡፡ፍርድ ቤቱ የተከሰሱበትን ጉዳይ በመመልከት መዝገቡን መዝጋቱን በመግለጽ ለማንኛውም ከላይ የተጠቀሰውን ገንዘብ በማስያዝ ወደ ቤታቸው እንዲያመሩ ፈቅዷል፡፡

ከእስር ከተፈታ በኋላ ለፍኖተ ነጻነት በስልክ አስተያየቱን የተጠየቀው የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ‹‹ከመነሻው የታሰርነው የሚዲያ አዋጁን ጨምሮ ህገ መንግስቱን በተጣረሰ መንገድ ነው፡፡ጋዜጠኛን ከዚያም ከፍ ሲል ዜጋን እያሰሩ ሂደቱን ህጋዊ ለማስመሰል እንዲህ አይነት ድራማ መሰራቱ ያስገርማል፡፡››በማለት ትዝብቱን አኑሯል፡፡
sourse abugida

No comments:

Post a Comment