ህዳር ፲፫(አስራ ሦስት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሳዑዲ ዓረቢያ ኢትዮጵያዊያን በአስከፊ ሁኔታ እንዲባረሩ ከተደረገ በኃላ መንግስት በሳዑዲ ስፖንሰርነት
ያጓጓዛቸውን ከ10ሺ በላይ ተመላሾች በካድሬዎች ማሰልጠኛ በሆነው የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በማሳረፍ ባለሃብቶች እንዲረዱዋቸው በመማጸን ላይ ነው።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለተመላሾቹ ማቋቋሚያ መንግስት 50 ሚሊየን ብር መመደቡን፣ ገንዘቡ ሊያድግ እንደሚችልና በማቋቋም ረገድ ችግር እንደሌለ ከገለጹ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ባለሃብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ ከዚህ ቀደም ቃል የገቡትም ቃላቸውን እንዲፈጽሙ ትላንት በዩኒቨርሲቲው በተካሄደ የምሳ መርሃግብር ላይ ጠይቀዋል፡፡
አንዳንድ ባለሃብቶቹ በራሳቸው ተነሳሽነት ኮሚቴ በማቋቋም ለተመላሾቹ ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ያስታወሱት ዶክተሩ ሌሎችም ይህንን አርአያነት እንዲከተሉ በመምከር መንግሰት ከነዚህ ባለሃብቶች ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ተመላሾቹ ከህብረተሰቡ ጋር እንዳይገናኙ ተደርጎ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በከፍተኛ ጥበቃ ስር ሲሆኑ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው በቀላሉ ተመላሾችን መጎብኘት ባለመቻላቸው አንዳንድ ቤተሰቦች ቅሬታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡
አንድ በሳዑዲዓረቢያ እህት እንዳላት የጠቀሰች አስተያየት ሰጪ እህቴ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች ማወቅ
አልቻልኩም፡፡ መጥታ እንደሆነ ውጪ ጉዳይ መ/ቤትን ብጠይቅም መልስ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ገብቶ ለመፈለግም የሚፈቀድ ባለመሆኑ ግራ ተጋብቻለሁ ስትል ጭንቀትዋን ለአዲስአበባው ዘጋቢያችን ተናግራለች፡፡
ወደ አገር ቤት ለመመለስ በፈቃዳቸው ተመዝግበዋል የተባሉት ኢትዮጽያዊያን ቁጥር ከ23ሺ በላይ ሲሆን ይህ ቁጥር በሕገወጥነት ከተፈረጁት ከ100ሺ በላይ ኢትዮጽያዊያን ቁጥር አንጻር አነስተኛ ነው፡፡ እስከትላንትና በስቲያ ማምሻውን ድረስ 10ሺ707 ሰዎች መመለሳቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
በሳውዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አሁንም ችግሮች እየደረሱባቸው እንደሆነ ለኢሳት ገልጸዋል። የኢትዮጵያን ኢምባሲ አሰራር ክፉኛ የሚተቹት ኢትዮጵያውያኑ፣ ሁሉም ዜጋ ከችግራቸው እንዲታደጋቸው እየተማጹ ነው።
በተመሳሳይ ዜናም በሳውድ አረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚቃወሙ ሰልፎች ቀጥለዋል። ረቡእ እለት በኦክላንድ ኒውዚላንድ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ መደረጉን ከአስተባባሪዎች መካከል አንዱ የሆነው አቶ አንዱአለም ሀይለማርያም ገልጿል
በተመሳሳይም በፈረንሳይ ፓሪስ ደማቅ የተቃውሞ ሰልፍ መደረጉን አስተባባሪዋ የገለጸች ሲሆን፣ የሳውዲ ኢምባሲ ሰራተኞች ጥያቄያቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። ኖቨምበር 29 ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ በሳውዲ ኢምባሲ ፊት ለፊት እንደሚካሄድ የገለጸችው ወ/ት ማክዳ፣ የፈረንሳይ የመገናኛ ብዙሀን ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በእለቱ ለመገኘት እንደሚፈልጉ መግለጻቸውንም ተናግራለች።
No comments:
Post a Comment